1/ የምንሰበስበው እና ቆጥበን የምናስቀምጠው እጃችን ላይ የገባውን ሳንቲም በሙሉ አይደለም! ይልቁንም ለኑሯችን አስገዳጅ የሆነውን ያክል ብቻ በመጠቀም ቀሪውን ማስቀመጥን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ በመሆኑም እጃችን ላይ ከሚገቡት ሳንቲሞች የግድ አስፈላጊ የሆነውን ያክል ብቻ በመጠቀም ቀሪውን በማስቀመጥ ብቻ እንወሰናለን፡፡
2/ ሳንቲም ቆጥቦ የመሰብሰብ ተቃውሞው የሚካሄደው በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች እና ከተሞች ነው፡፡
3/ ሳንቲም ቆጥቦ የመሰብሰብ ተቃውሞው የሚጀምረው የፊታችን አርብ መጋቢት 18/2007 ጀምሮ ሲሆን በዚሁ ገጻችን ማብቃቱ እስኪገለጽ ድረስም ላልተወሰነ ጊዜ ይቀጥላል፤ በአላህ ፈቃድ!
አዎን! እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በሃይማኖታችን ምክንያት በመንግስት ከፍተኛ በደል እየደረሰብን ያለን ሰላማዊ ዜጎች ብንሆንም መንግስት ከበደሉ ሊቆጠብ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ለዓመታት ሰላማዊ ትግል ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ሰላማዊነታችንን ለመግለጽ ነጭ ጨርቅ እያውለበለብን በአደባባይ በተገኘን ቁጥር መንግስት አስፈራርቶናል፤ ዘልፎናል፤ ደብድቦናል፤ ዘርፎናል፤ አስሮናል፤ ገድሎናል፡፡ እኛ ነጭ ሶፍት ይዘን ሰላማዊነታችንን በአደባባይ ስንዘምር መንግስት ደግሞ ዝናሩን ታጥቆ በጥይት እሩምታ ተቀብሎናል፡፡ የማይጠፋ ጠባሳ የጣለ ጥቁር ሽብር ፈጽሞብናል፤ ፈርመን የላክናቸውን ወኪሎቻችንን በግፍ እስር እና በከፍተኛ ቶርቸር አሰቃይቶብናል፡፡ እስካሁንም ነጻነታቸውን ነፍጎ የምርጫ ቅስቀሳ መጠቀሚያ እያደረጋቸው ነው። እንግዲህ አሁን ላይ መንግስት ጥይት ሊተኩስበት በማይችለው ሜዳ ሰላማዊ ተቃውሟችንን ከመቀጠል ውጭ ሌላ ምርጫ ያለን አይመስልም፡፡ ዛሬ ይፋ ያደረግነው የትብብር መንፈግ ተቃውሞ ዋነኛ ዓላማም መንግስት ጥይት የሚተኩስበት ዒላማ የማያገኝበትን የትግል ድባብ በመፍጠር መብታችንን የማጎናጸፍ ግዴታውን እንዲወጣ የተቃውሞ መልእክት ማስተላለፍ ነው፡፡ ወደፊትም አንድ ብርና ከዛም በላይ ያሉ የብር ኖቶችንም ከመሰብሰብ ጀምሮ ሌሎች በአተገባበራቸውም ሆነ በእንድምታቸው ጠንክረው እያደጉ የሚሄዱ የትብብር መንፈግ እና የቦይኮት ስልቶችን ቀስ በቀስ በመለማመድ ሰላማዊ ትግላችንን እስከድል ደጃፎች እንቀጥላለን፡፡ ከአላህ ፈቃድ ጋር ይሳካልናል፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
The post ድምጻችን ይሰማ:- ሳንቲም ሰብስቦ የመቆጠቡ ተቃውሞ አተገባበር - appeared first on Zehabesha Amharic.