የህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እምቢተኝነት የተናጠል መስዋእትነትን የሚቀንስ አሳታፊ የትግል ስልት ነው!
ረቡዕ መጋቢት 9/2007
የኢትዮጵያ ሙስሊም በእምነቱ ላይ የተቃጣውን የአስተሳሰብና የጥቃት ዘመቻ ለመመከት፣ አስተሳሰቡን በኢስላማዊ አስተሳሰብ ለማረቅ፣ በሽፋን የሚደረገውን ጥቃት በህግ እልባት ያገኝ ዘንድ ባደረገው የትግል ሂደት ከላይ ወደታች የሆነ የተመሪነት ስርዓት ብቻ ሳይሆን ከታች ወደላይ ፍሰት ያለው መሪዎችን የመምራት ሥርዐት መፍጠር ችሏል፡፡ ይህም ህዝበ ሙስሊሙን የትግሉ ባለቤትና የመሪዎቹም መሪ አድርጎታል፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ አደባባይ የወጣው ‹‹በጊዜ ሂደት ይፈታሉ፣ አልያም ከሀገሪቷ ሁለንተናዊ ዕድገት ጋር አብረው ይቀረፋሉ›› በሚል በሆደ ሰፊነት የተሸከማቸውን ስር የሰደዱ መንፈሳዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ተቋማዊና መሰል ችግሮች ለመጠየቅ ሳይሆን ተገድበው የተሰጡትን መሰረታዊ መብቶች መልሶ የመንጠቁን እኩይ ዘመቻ ለመግታት ነው፡፡ የእነዚህ እኩይ ተግባራት ድምር ውጤት ዘመን ተሻጋሪና በእምነታችን ላይም ሆነ በማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ማንነታችን ላይ የሚያደርሰውን ከፍተኛ አደጋ መረዳቱ ለህዝበ ሙስሊሙ የመንቃት ምንጭ፣ ለትግሉም ገፊ ሀይል ከመሆን ባሻገር ህዝቡን ፅናት ያላበሰና ለመስዋእትነት ያዘጋጀ ነበር፡፡
ከሰው ልጅን የታሪክ ምዕራፍ ሰፊውን ቦታ የሚሸፍነው ትግል ነው፡፡ በተለያዩ ወቅቶች የሰው ልጆች በግልም ይሁን በህብረት ለተለያየ ዓላማና ግብ የተለያዩ ስልትና መርሆዎችን የተከተሉ ትግሎችን አካሂደዋል፡፡ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እምቢተኝነት የትግል ስልት ደግሞ የህዝብን ንቃተ ህሊና መጎልበት የሚያመላክት የሰለጠነ የሰላማዊ የመብት ትግል መገለጫ ነው፤ ምክንያቱም መንግስት የህዝብን ጥያቄ ጆሮ ሰጥቶ ከማድመጥ ይልቅ የህዝብን ድምፅ በኃይል ለማፈን የሚያደረገው ጥረት ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ በመጣ ቁጥር ህዝብ የመንግስትን ደጅ ከማንኳኳት ይልቅ መንግስት ላይ ዘርፈ ብዙ ጫና በመፍጠር መንግስት ወደህዝቡ ደጅ እንዲመጣ የሚያስገድዱ ለእምቢተኝነት የተሰጡ የእምቢተኝነት ምላሾችን አማራጭ አድርጎ ይወስዳልና! በተጨማሪም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እምቢተኝነት የተለየ መዋቅር የማይጠይቅ፣ ሁሉም ህብረተሰብ በየአካባቢውና በየዘርፉ የሚታገልበትና የተናጠል መስዋእትነትን የሚቀንስ የትግል ስልት ሲሆን ተጽእኖ ፈጣሪነቱም ዓይነተኛ መሆኑ አሌ የሚባል እንዳልሆነ ታሪክ ይመሰክራል፡፡
ይህ ህዝባዊ የለውጥ ፍላጎት ምክኒያታዊ የለውጥ እርከኖችን ተሻግሮ የመጣ እንደመሆኑ ተግባራዊነቱ ዋስትና ያለው፣ ከጠባቂነት የሚያላቅቅ፣ እስከ ድል ደጃፎች ድረስ የተዘረጋው የመብት ትግል በሰላማዊነት እና ቁርጠኝነት ድልድይ ላይ ተሻግሮ የችግርን ወንዝ እንዲሻገር ያስችላል፡፡ ይህን ህዝባዊ የለውጥ ፍላጎት ማዳመጥ ደግሞ ተገቢ ብቻ ሳይሆን ህዝብ የመሪዎቹ መሪ መሆኑን ማሳያም ጭምር ነው፡፡ በመሆኑም በመጪዎቹ ሳምንታት በቦይኮት እና ህዝባዊ ትብብር መንፈግ (እምቢተኝነት) ላይ ያተኮሩ የተቃውሞ መንገዶችን በመጠቀም የምናካሂዳቸው መርሃ ግብሮች ይኖሩናል፤ በአላህ ፈቃድ! ሁላችንም በዚህ መሰሉ ትግል ላይ ግንዛቤያችንን የሚያዳብሩ ጽሁፎችን በማንበብ እና መንፈሳዊም ሆነ ስነ ልቦናዊ ዝግጅት በማድረግ ሰላማዊ ትግላችንን እስከድል ደጃፎች ለማድረስ የገባነውን ቃል እናድስ፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
The post “በመጪዎቹ ሳምንታት በቦይኮት እና ህዝባዊ እምቢተኝነት ላይ ያተኮሩ መርሃ ግብሮች ይኖሩናል” – ድምጻችን ይሰማ appeared first on Zehabesha Amharic.