Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

“ኢንተርኔትና ሚድያውን አጨናንቀዋለሁ ”ጥበቡ ወርቅዬ የቀድሞ ድምፃዊ፣ የአሁኑ ዘማሪና ሰባኪ

$
0
0

አቤንኤዘር ጀምበሩ

ጥበቡ ወርቅዬ አገልግሎት ለመታደም ወደ ቤዛ ቤተ/ክ በ06/07/07 ዓም ተገኝቼ ነበር። ምንም እንኳ ዝግጅቱ 8:00 ይጀመራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ጥበቡ ቦታው የደረሰው ከዘጠኝ ሰዐት በኃላ ነበር። ጥቤ የቀድሞ አስታይለኛ አለባበሷ አና ፍሪዟ እንዳለች ነው፣ ፊቱ ላይም ላቅ ያለ የደስ ደስ ስሜት እና መመቸት ይታይበታል። ለአድምተኛው ምንም አይነት ቀረፃ ማድረግ አንደማይፈቀድ ከተላለፈ በኋላ ፣ ጥሪ ተደርጎለት ወደ መድረክ ሲወጣ የነበረው ህዝብ ቆሞ እያጨበጨበ እና እየጮኸ ሲቀበለው “አለማዊ” መድረክ ስራዎቹን ሳያስታውሱት የቀሩ አይመስለኝም።

በኋላ ላይ እራሱ እንደገለፀው “እዛ በታለንትና በድፍረት፣ እዚህ ግን በቅባት” ብሏል። ዝማሬን በሚያቀርብበት ወቅት በሙዚቃ ህይወቱ የሚታወቅበት መልካም ቃና ያለውን ድምፁን ወደ መዝሙር ቀይሮታል፣ ምንም እንኳን አልፎ አልፎ ያሉ መሸጋገሪያዎች ላይ የለመዳቸው የሙዚቃ መግቢያዎች ሲጐትቱት ታዝቤያለሁ። ለምሳሌ አንድ ጊዜ “ነይ ነይ” ብሎ ወዲያው “ሃሌሉያ” አድርግዋታል። የመዝሙር አገልግሎቱን ጨርሶ ወደ ቃል ማካፈል ሲያልፍ፣ የትምህርቱን መነሻ ያደረገው ሐዋሪያት ስራ ምእራፍ 2 ላይ ስላለው የበአለ ሀምሳ ክብረ በአል ላይ ነበር። ጥበቡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀቱ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን መገንዘብ አያዳግትም፣ እንዲሁም ለእምነቱ ከፍተኛ ቅንአት እንዳለውም ጭምር። ይህም የሚያመለክተው ከፍተኛ ጊዜውም በመፅሐፍ ንባብ ላይ እንደሚያሳልፍ ነው። እራሱም እንደገለፀው ለሶስት አመት ተኩል በር ዘግቼ ጨለማ ቤት ጭምር በንባብና በመፅሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ አሳልፌያለሁ ብሏል ።
tibebu workiye

“አንዳንዶች ይመለሳል ይሉኛል፣ ግን ወዴት ነው የምመለሰው” ሲልም አፅእኖት ሰጥቷል። ምንም እንኳን ጥቤ ጥሩ አንዳነበበ አና መረዳት አንዳለው መገንዘብ ቢቻልም፣ በማስተማሩ ረገድ ግን የአቅም ውስንነትና ድፍረት እንደሚስተዋልበት ደፍሮ መናገር ይቻላል። በተለይ ባሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እይታን ፣ ከተጨባጭ ገሃዳዊ ሁኔታዎች እና ከስነ ልቦናዊ ዝግጅት ጋር አያያዙ የሚስቡ ትምህርቶችን ማዘጋጀት በአለም ሁሉ ላይ ባሉ የፕሮቴስታንት ቤተ/ኖች የሚንፀባረቅ ነገር ነው። እንዳየሁት የቃሉ መረዳት ቢኖረውም ከላይ የተጠቀሱት ክህሎቶች ጐድለውት ተመልክቻለሁ። ትምህርቱ ባብዛኛው ረድፍ ያልጠበቀ እና መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ ነገሮችን መልሶ የመናገር፣ ወይም ትንታኔያዊ አስተምሮ ያለማቅረብ ሁኔታዎች ታዝቤያለሁ። ዘማሪው በትምህርቱ ወቅት የተለያዩ ነገሮችን አንስቷል፣ በአለማዊ ህይወቱ በተለይ በጫት ሱስ እጅጉን እስረኛ አንደነበረ ፣ቄማ ላይ እያሉ ከአርቲስቶች ጋር አብዝቶ ይጋጭ እንደነበር “አይወደኝም፣ ሌላ ሰው ባጠፋው ጭምር እኔ ነበርኩ የምሰደበው፣ ሰይጣን የሱ አንዳልሆንኩ ያውቅ ስለነበር ነው። ” ብሏል።

አርቲስቱ ድሮ በመቃብር አካባቢ እንኳን ሲያልፍ እጅጉን ይሸበር እንደነበርና አሁን ግን በራሱ አገላለፅ “በኮንፊደንስ ነው” ሲል ተደምጧል። ለሱ ከአለም ለመውጣት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደነበርና ብዙ የሚይዙ ነገሮች እንደነበሩ ጠቅሰዋል። “የሙዚቃ ዝና፣ ሙዚቃቤት፣ ቁጥሩ የበዛ የሙዚቃ መሳሪያና ሌሎችም ነበሩ” ብሏል። ወደ ጌታ ከመጣ በኋላ መንፈሳዊ ክንውኖቹን ሲናገር፣ 1900 በላይ ሰዎችን ወደ ጌታ አንደመለሰ (የመገናኛ ብዙሃን የተጠቀሙትን ሳይጨምር) ፣ ትልልቅ አርቲስቶችን ሰብስቦ አንደመሰከረ፣ ወደ ጌታ አንደመለሰ እንዲሁም ብዙዎች በመንገድ ላይ እንደሆኑ ገልፅዋል። ሌላው አሁን አሁን በአንዳንድ ድህረ ገፆች ላይም እንደሚታየው ተአምራዊ አገልግሎቱ ነው።

ከንግግሩ መረዳት የሚቻለው እነዚህ እነዚህ አገልግሎቶች ሁሉም ቤት እንዲገቡ ይፈልጋል ፣ በቃሉም “ካሁን በኃላ ኢንተርኔትንና ሚድያውን አጨናንቀዋለሁ” ብሏል። በቅዳሜው አገልግሎት በስራ ማጣት የተፀለየላት ወጣት ፣ ስራ ማጣቷ መንፈሳዊ ተግዳሮት እንደነበር እና በፀሎት ወቅት ጮሆ ሲወጣ በዛው ቅፅበት አቤቷ ስልክ ተደውሎ ለስራ መጠራትዋን እሱ ሲናገር አሷ እጇን በማውለብለብ በእሁዱ ፕሮግራም አረጋግጣለች። እንዲሁም እሱ ፀሎት ያደረገላቸው ሰዎች በእንቅልፍ ወደ መንግሥት ሰማያት ደርሰው እንደተመለሱ ጠቅሷል፣ በስልክ ልውውጥ አጋነንትን እንዳስወጣም ጭምር። ትላልቅ አርቲስቶች ላይ ያለ መሪ መንፈስ ሲመታ መንጋው ይበተናል የሚለው አርቲስቱ፣አሁን ላይ ብዙ አርቲስቶች አንደሚደውሉለት እርሱም አንደሚፀልይላቸው መስክሯል። ሌላው የገረመኝ ነገር በትልልቅ ዘፋኞች ስም የተሰየሙ አርኩሳን መናፍስቶች መኖራቸውን መግለፁ ነው፣ ምድራዊ ህግ ስለማይፈቅድ እንጂ ቢጠራቸው እየጮሁ ወደ አርሱ እንደሚመጡ ገልፅዋል። ድምፃውያኑ አንደ ኮካ በስማቸው የተሰየሙ መናፍስት መኖራቸው አያስገረመኝ፣ ይህችን አረፍተ ነገር በሚናገርበት አፍታ ሁለት አርቲስቶች ወደ አእምሮዬ መጡ።ታደለ አና ሰማኸኝ። በእነዚህ ሙዚቀኞች የተሰየሙ መናፍስት ይኑሩ አይኑሩ ባላውቅም፣ ኖረው ቢጠራቸው ብዬ አሰብኩት። የታደለ “አጋቡዮ” እያለ የሰሜ “አላበድኩም ፣ ጤነኛ ነኝ፣ ያዥኝ” እያሉ ወደ ፊት ሲሮጡ በምናቤ ታየኝ።

ጥቤ ጌታ ይባርክህ። ቸር!

The post “ኢንተርኔትና ሚድያውን አጨናንቀዋለሁ ” ጥበቡ ወርቅዬ የቀድሞ ድምፃዊ፣ የአሁኑ ዘማሪና ሰባኪ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>