ለ 3 አመታት በተለያዩ የሰላማዊ ትግል ዘዴዎች መብቴን አክብሩ ሲል የቆየው ህዝበ ሙስሊም የህዝብን ድምፅ ለመስማት ፈቃደኛ ያልሆነው የሃገራችን መንግስት በቀጣይ የህዝብን ድምፅ ይሰማ ዘንድ ወደሚያስገድዱ ህዝባዊ እንቢተኝነት ትግሉ መሸጋገሩን ድምፃችን ይሰማ አስታውቋል፡፡
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል፡-
ሕዝብ የአንድ አገር መሠረት ነው፡፡ የአገር ምሰሶዎች የሚተከሉትም በህዝብ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ሕዝብ ለአንድ አገር ሕልውና ዋነኛው ምንጭ ነው›› ብንል በእርግጥም አንሳሳትም፡፡ የመንግስት ተቋማትም ሆነ መንግስት ራሱ የመቋቋሚያ ዓላማው ህዝብን ማገልገል፣ የህዝብን ፍላጎት ማስፈጸም ነው፡፡ ይህ ሳይሆንለት ሲቀር ህዝብ ይቀየማል፤ ይቆጣልም፡፡ መብቱን በተለያዩ መንገዶች መጠየቅ ይጀምራል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሙስሊምም ላለፉት ሶስት ዓመታት ሲያደርግ የቆየው ይህንኑ ነው
ትግል የራሱ ደረጃዎች ያሉት ሂደት ነው፡፡ በለዘብተኛ አቤቱታ ይጀምራል፡፡ ድርድሮችን ያልፋል፡፡ ጠንከር ያሉ የመብት ጥየቃ ሂደቶችን ያሳልፋል፡፡ ጥያቄውም ወደትግል ይቀየራል፡፡ መስዋእትነቶች ይከፈሉበታል፡፡ እያዳንዷ መስዋእትነት በራሷ ለትግሉ የሚኖረውን ቁርጠኝነት እና ወኔ እየጨመረች ትሄዳለች፡፡ አሁንም ችግሩ ካልተፈታ ህዝብ ያገለግለው ዘንድ ራሱ በሾመው አካል ላይ ተስፋ መቁረጥ ይጀምራል፡፡ የአገሪቱ ተቋማት ዋነኛ ባህሪያቸውን ለውጠው በደልን የማገልገል ሚና መወጣት በቀጠሉ ቁጥር የህዝቡም ቁርጠኝነት በዚያው ልክ እያደገ ይመጣል፡፡
የአንድ መንግስት ህልውና በእሺተኛ ህዝብ ፍቃደኝነት ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ሕዝብ ሲመረውም ‹‹መብቴ ይከበርልኝ›› ከሚል ጩኸት ‹‹መብቴን ካላከበርክ እኔም….. !›› ወደሚል ዛቻ መሄዱ አይቀሬ ነው፡፡ ይህን ጊዜ ሕዝቡ ‹‹ትብብር የመንፈግ ትግል ውስጥ ገባ›› ይባላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ትግል ውጤታማ መሆኑ አይቀሬ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን አጽንኦት ሰጥተው ያስተምራሉ፡፡
አዎን! በጨዋ ደንብ እና በአንጸባራቂ ሰላማዊ ስነ ምግባር ለሶስት ዓመታት መብቱን ሲጠይቅ እና ሲታገል የቆየው ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ‹‹መብቴ ይከበርልኝ›› ከሚል ያልተሰማ ጥያቄው ‹‹መብቴን ካላከበርክ እኔም….. !›› ወደሚልበት የትግል ምዕራፍ ላይ እነሆ ደርሰናል! ሰሞኑን ይህንኑ አስመልክቶ የምንለው ይኖራልና ሁላችንም ቃል የገባንበትን ትግል እስከድል ደጃፎች ለማድረስ ወገባችንን እናጥብቅ፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
The post የሕዝበ ሙስሊሙ ትግል ወደ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ማደጉን ድምጻችን ይሰማ አስታወቀ appeared first on Zehabesha Amharic.