የግንቦት 7 ወቅታዊ ጽሑፍ
የኢትዮጵያ ሕዝብ በአለፉት 23 ዓመታት በህወሓት ዘረኛ አገዛዝ የደረሰበት ስቃይ እንዲቀንስ፤ ገዢዎቹ ከጫንቃው እንዲወዱ፤ ህወሓትን አውርዶ የሚፈልጋቸው መሪዎችን በነፃነት እንዲመርጥ ሲጠይቅና አቤቱታ ሲያሰማ ቆይቷል። በ1997 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝብ ምኞት የሚሳካ መስሎ የታየ የነበረ ቢሆንም በአገዛዙ አረመኔዓዊ እርምጃ ተሰናክሏል። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ “ድምፃችን ይሰማ” የሚሉ አቤታዎች ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መምጣት ጀምሯል – “ድምፃችን ይሰማ ሙስሊሞች”፣ “ድምፃችን ይሰማ ኦርቶዶክሶች”፣ “ድምፃችን ይሰማ መምህራን”፣ “ድምፃችን ይሰማ ተማሪዎች”፣ … ወዘተ። በተለይ ሙስሊም ወገኖቻችን በተደራጀ መንገድ “ድምፃችን ይሰማ” እያሉ ሲወተውቱ ሦስት ተከታታይ ዓመታት አልፈዋል። ወገኖቻችን “ድምፃችን ይሰማ” በማለታቸው ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፣ ተገድለዋል።
አቤቱታ የሚሰማ ጆሮ የሌለው አገዛዝ ሲገጥም ምን ይደረጋል? ለአቤቱታ አቅራቢው ያለው ምርጫ ከሁለት አንድ ነው። ወይ አቤቱታን እርግፍ አድርጎ ጥሎ በደልን ተቀብሎ “እህህ !” እያሉ መኖር፤ አሊያም “በቃኝ፣ እንቢ አልገዛም” ማለት፤ ሦስተኛ ምርጫ የለም።
አቤቱታ ሰሚ ሲያጣ እና ሕዝብ መሮት “እንቢኝ፣ አልገዛም” ሲል ነው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ተቀሰቀሰ የሚባለው። ሕዝባዊ እምቢተኝነት ብዙ መልኮችና ቅርጾች ቢኖሩትም ዋነኛዎቹ መገለጫዎች ሁለት ናቸው። አገዛዙ ሕዝብ እንዲያደርግ የሚፈልገውን አለማድረግ እና/ወይም አገዛዙ ሕዝብ እንዲያደርግ የማይፈልገውን ማድረግ።
ለምሳሌ፣ አገዛዙ ሹማምንቱ እንዲከበሩ፣ ሕዝብ እንዲታዘዝላቸው ይፈልጋል፤ እንቢ ያለ ሕዝብ ግን የአገዛዙን ሹማምንት ይንቃል፣ በየደረሱት ያዋርዳቸዋል፣ “አልታዘዛችሁም” ይላቸዋል። ማንኛውም መንግስት የዳኝነት ሥርዓቱ እንዲከበርለት ይፈልጋል፤ በደል የመረረው ሕዝብ ግን የአምባገነኖች ችሎት ውሳኔ አይቀበልም፤ ዳኞችንም ዳኝነትንም አያከብርም። ሕዝብ የመንግሥትን ግብር በወቅቱ እንዲከፍል የማንኛውም መንግሥት ፍላጎት ነው። በመንግሥት ያመረረ ሕዝብ ግን ግብር አይከፍልም፤ መክፈል ግድ ከሆነበትም አዘግይቶ፣ አስለፍቶ ነው። የመረረው ሕዝብ ምሬቱን መፃፍ በሌለበት ቦታ ይጽፋል። በደል የበዛበት ሕዝብ “ዝም በል” ሲሉት ይናገራል፤ “ተናገር” ሲሉት ዝም ይላል።
አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝባዊ እምቢተኝተኝነት እርምጃዎች ጅምሮች እየታዩ ነው። በአማራ ክልል፣ ሕዝብ በሹማምንት ላይ የራሱን እርምጃ መውሰድ ጀምሯል። ሕዝብ ራሱ የፓሊስንም የፍርድ ቤትንም ሥራ ተክቶ እየሠራ ነው። ይህ መበረታታት ያለበት ትልቅ እርምጃ ነው። እንደዚሁም ሁሉ በተለይ ወጣቶች ብሶቶቻቸውን በብር ኖቶች ላይ ጽፈው ገበያው እንዲያዘዋውራቸው እያደረጉ ነው። ይህም “የወረቀት ገንዘብን ለተሠራበት ዓላማ ብቻ ተጠቀሙ” የሚለውን ህግ በመጣስ ለቅስቀሳ ሥራ መጠቀም በመሆኑ የሕዝባዊ እምቢተኝነት አካል ነው። በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ በርካታ የወረቀት ገንዘቦች በምሬት መግለጫነት ይውላሉ ተብሎ ይገመታል።
በተጓዳኝ በርካታ አማራጭ ስልቶች ሥራ ላይ መዋል ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ፣ ተቀማጭ ገንዘብን ከህወሓት ባንኮች ማውጣት በቀላሉ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ስልት ነው። በውጋጋን ባንክ ተጀምሮ ወደ አንበሳ ኢንተርናሽናል ከዚያም ወደ ንግድ ባንክ ማሸጋገር ይቻላል።
በወገኖቻችን ላይ የግፍ ፍርድ የሚያስፈርዱ አቃቢያነ ህግ እና የግፍ ብይኖችን የሚሰጡ ዳኞች በቸልታ ሊታለፉ አይገባም። በእስር ቤቶችም በወገኖቻችን ላይ ሰቆቃ እየፈፀሙ ያሉ ጨካኞች ከሰላማዊ ሕዝብ ጋር ተደባልቀው ሰላማዊ ሕይወት እንዲመሩ ሊፈቀድላቸው አይገባም። እነዚህ ሁሉ ሊወገዙ፣ ሊገለሉ፣ በየደረሱበት ሊዋረዱ ይገባል።
በአገዛዙ መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችን በሥራቸው ላይ መለገም ተቀባይነት ያለው በጎ ተግባር እንደሆነ ሰፊ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል። ከአምባገነን ሥርዓት ጋር መተባበር እኩይ ተግባር ሲሆን አምባገነን ሥርዓትን ከውስጥ መቦርቦር ደግሞ የሚበረታታ ሰናይ ሥራ ነው።
ለወያኔ አገዛዝ ግብር መክፈል የምናቆምበት ሰዓትም ተቃርቧል። በራሳችን ገንዘብ ገዳዮቻችን እንዲሰለጥኑብን መፍቀድ የለብንም። ስለሆነም “ግብር አንከፍልም”፤ “መዋጮዎቻችሁ አይመለከቱንም” የምንልበት ቀን ቀርቧል።
በፋይዳ የለሽ ምርጫ የሀገር ሀብት ሲመዘበር ማየት አንሻም። በአግባቡ ለማይቆጠር ድምፃችን አንድም ደቂቃ የምናባክንበት ምክንያት የለምና ሁላችንም የምርጫ ካርዶቻችንን ቀዳደን ቁርጭራጮቹን በየመንገዱ ልንበትናቸው ይገባል።
እነዚህን እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው የሕዝባዊ እምቢተኝነት የመጀመሪያ ደረጃዎች። እነዚህን እያደረግን በምስጢር መደራጀታችንን እንቀጥል። ከጥቂት በኋላ አምባገነኑን ሥርዓት የሚያንበረክክ ኃይል እንፈጥራለን። ጥቃት ቢደርስ የሚመክት ኃይል የተደራጀ በመሆኑም ሕዝባዊ እምቢተኝነትና ሕዝባዊ አመጽ ተቀናጅተው እንዲሄዱ ይደረጋል።
አርበኞች ግንቦት 7:የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ሕዝባዊ እምቢተኝነትንና ሕዝባዊ አመጽን አቀናጅቶ ለመምራት የተዘጋጀ፤ ለዚህ የሚያበቃው ድርጅታዊ አቅም እየገነባ ያለ ድርጅት ነው። አርበኞች ግንቦት 7 “እንሰባሰብ በወያኔ ላይ የምናቀርባቸው ተቃውሞዎች በሙሉ ወደ እምቢተኝነት ከፍ እናድርጋቸው” ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
The post “ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ ይቀጥል… ገንዘባችሁን ከሕወሓት ባንኮች ከወጋገንና አንበሳ ባንኮች አውጡ” – አርበኞች ግንቦት 7 appeared first on Zehabesha Amharic.