ሰሞኑን አቶ ኤርሚያስ ለገሰ “ግልጽ ደብዳቤ ለዲያቆን ዳንኤል ክብረት” ብሎ የጻፈውን፤ ከዚያም ዲያቆን ዳንኤል ለዚህ ደብዳቤ የሰጠውን ምላሽ (ታላቅነቱን በሚያሳይ ትህትና)፤ እንዲሁም አቶ ኤርሚያስ “የመጨረሻ ደብዳቤ” (በሃሳብ መሸነፍ የወለደው የስድብና አሉባልታ ጥርቅም) ብሎ የሰጠውን መልስ ብዙዎቻችን አንብበነዋል፡፡
“አወቅሽ አወቅሽ ቢሏት የባሏን መጽሃፍ አጠበች” እንደተባለው አቶ ኤርሚያስ ራሱም ተዋናይ ሆኖ ሲተውነው የኖረውን ስለተረከ ብቻ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚለው የተሳሳተ ብሂል ጆሮ ሲሰጠው ጊዜ ራሱን ሊያስገምት በሚችል ሁኔታ ያኛውን ትረካ ሲጨርስ ወደዚህም መጣ፡፡ በነገራችን ላይ “የመለስ ትሩፋቶች ደራሲ” የምትለዋ ሁልጊዜ የእሱ ስም ሲነሳ ከፊት ትቀድማለች፡፡ ይቺ ነገር ከፊት ካልቀደመች እሱ አይታወቅም ማለት ነው? ወይስ “እንዴ! እንዲህ ያደረገ ሰው እኮ ነው!” ለማለት ነው? (በጣም ገርሞኝ ነው)
በኢትዮጵያ ፖለቲካ አንድ አስቂኝ ጨዋታ አለ፤ በገዢው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ዘንድ አንድ የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና (ግንዛቤ) ያለው ሰው የእነሱ ፓርቲ አባል ወይም ደጋፊ ካልሆነ “እንዴ! እሱማ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ወይም ደጋፊ ነው” የሚል ጭፍን ፍረጃ ይሰጡታል፡፡ ተቃዋሚዎቹ ደግሞ ያ ሰው ጨዋታውን እነሱ በሚፈልጉት መንገድ የሚጫወት ሰው ካልሆነ “እሱማ ወያኔ ነው፣ ካድሬ ነው፣ ከእነ እንትና ጋር ግንኙነት አለው” (የልደቱ አያሌውን መጽሃፍ ማንበብ ትችላላችሁ) ብለው ሃላፊነት በጎደለው አኳኋን ይፈርጁታል፡፡ ነገር ግን የሁለቱም ጨዋታ ያልተመቸውና ከአስተሳሰቡም ጋር ያልሄደለት ሰው መሃል ላይ ራሱን ሆኖ እንደሚኖር አይረዱትም፡፡ በተግባርም ብዙዎቹ ገዢውም ሆነ ተቃዋሚዎቹ ፓርቲዎች የሚያራምዱት አልጥማቸው እያለ በንጽህናና በነፃ ህሊና ራሳቸውን ሆነው የራሳቸውን አስተሳሰብ እየተከተሉ ይኖራሉ፡፡ ይህን ደግሞ ሃጢያት አድርገውት ቁጭ ይላሉ፡፡ ምን እንሁን ታዲያ? “እኛ ጋር ካለሆናችሁ እነሱ ጋር ናችሁ” ብለው በጭፍን ይፈርጃሉ፡፡ ታዲያ ይሄን የሚሉት “ዜጎች የፈለጉትን ሃሳብ በነፃነት ማራመድ እንዲችሉ እንዲሁም የሀሳብ ብዝህነትና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በኢትዮጵያ እንዲመጣ ጠንክረን እየሰራን ነው ወዘተ . . . ” እያሉ የሚምሉትና የሚገዘቱት ሲሆኑ ነገሩ ያስገርማልም፣ ያሳፍራልም፡፡
ዲያቆን ዳንኤልን በተመለከተ ልክ እንደ ኤርሚያስ ሁሉ ብዙዎች ብዙ ብለዋል፤ እሱ ግን የሚወራበትን ሳይሆን በተግባር እሱ የሆነውን (የታላቁን አባት የብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ ካልዕን መርህ በመከተል (“ሥራህን ሥራ፤ አንበሳው ሲያጓራ ፍንክች አትበል፤ የሰይጣንን ውሾች ለመውገር አትቁም . . . ”)) በሚለው መሰረት ከእነዚህ ከሚያወሩት ሰዎች በላይ ትርጉም ያለው ስራ ለሀገሩ እየሰራና ትውልድን በተሻለ አስተሳሰብ ለመቅረጽ፣ የሀገር ታሪክ፣ ባህልና ትዉፊት በዚህ ትውልድም ታውቆና ተጠብቆ እንዲኖር እየሰራ ያለ ሰው ነው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ሄዳችሁ ከምታገኟቸው አምስት ሰዎች ውስጥ ቢያንስ አንዱ ስለ ዳንኤል በሚገባ ብዙ ነገሮችን ሊነግራችሁ ይችላል፡፡ ይሄ በቅንነትና በትጋት ከመስራት የመጣ መሆኑ በነፃ ህሊና ለሚያስብ ሰው ግልጽ ነው፡፡ ታዲያ እነ ኤርሚያስ ይህን ሰው ፈልገውት ኖሮ “እናንተ ጋርም አልሄድም፣ እነዚያ ጋርም እየሄድኩ አይደለም፣ እንደ እስካሁኑ ሁሉ አሁንም በራሴ መንገድ ነው መሄድ የምፈልገው ሲላቸው” “አይ አንተማ እነሱ ጋር ነህ” ብለው ፈረጁት፡፡
ዳንኤልን በአካል አንድ ቀን ብቻ አግኝቼው ለተወሰኑ ደቂቃዎች አውርተናል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን በተለያዩ መድረኮች አስተምሮኛል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሁኑ ብዙ ሰዎች የራሳቸው ብሎግ ሳይኖራቸው (በኢትዮጵያ እየኖረ የራሱ ብሎግ የነበረው የመጀመሪያው ወይም ከመጀመሪያዎቹ አንዱ የሆነ ሰው ነው) በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩና ከህይወታችን፣ ከባህላችንና ከሀገራችን ታሪክ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን እጅግ መሳጭና ነገሮችን በተለየ መንገድ እንዲናይ የሚያደርጉ ጽሑፎቹን በማንበብ፤ እንዲሁም በሚያሳትማቸው መጽሃፍቶቹ በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ ጽሑፎቹን በተመስጦ ሳነብ ኖሬያለሁ፤ ብዙ እውቀቶችንም አግኝቻለሁ፤ ወደፊትም እንደ አምላክ ፈቃድ እንዲሁ ይቀጥላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ስለ አንድ ሰው ይህን ያህል ራሱን ሊገልጹ የሚችሉ የአዕምሮው ውጤቶች የሚነግሩንን ትተን ወደ ተራ አሉባልታ የምንወርድበት ሁኔታ ግን ከምቀኝነትና እርሱም በአንድ ወቅት ከአንድ እንግሊዛዊ ጋር አፄ ኃ/ስላሴን በተመለከተ ሲወያዩ ሰውየው ያለውን “አይከንን መግደል” (ሃሳቡን እንጂ ርዕሱ በትክክል ይሄ መሆኑን ርግጠኛ አይደለሁም) በሚል ጽሑፉ እንዳሰፈረው ኢትዮጵያን ሁልጊዜም ልጅ እያላት የልጅ ደሃ የሆነች ሀገር ያደርጋታል፡፡ ይሄ ሰው ለብዙ ወጣቶች አርዓያ መሆን የሚችልና እውነት ለመናገር ከብዙዎቻችን በላይ ለሀገርም ትልቅ ዋጋ ያለው ሥራ እየሰራ ያለ ወደፊትም ትልቅ ነገር ማድረግ የሚችል በመሆኑ በተራ አሉባልታ ስም ማጥፋቱ ጉዳቱ ለሀገር ነው፡፡ እንደ ሀገር ያሉንን እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ቁጥራቸውን ማብዛት እንጂ ያሉትን ሁልጊዜ ማጥፋቱና መግደሉ አይጠቅመንም፡፡
በ“ግልጽ ደብዳቤው” “የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል” እንደሚባለው አቶ ኤርሚያስ ብዙ ስህተቶችን ጭምር ተሳስቷል፡፡ ዳንኤል ጥናታዊ ጽሑፉን ሲያቀርብ የነበረውን እውነታ ወደ ጎን ትቶ ሃሳቡ አሁን ካለው ሁኔታ ጋር አገናኝቶ ብቻ ከስሶ ለከሳሽ ለመስጠትም ሞከረ፡፡ በነገራችን ላይ “እንዲህ ነው” “እንዲያ ነው” የሚለውን አሉባልታውን ትተን በጥናታዊ ጽሑፉ ከተነሱት ጉዳዮች ውስጥ እነዚህ እውነት አይደሉም ብሎ ማስረጃ በማቅረብ ብንወያይ ጥሩ ነበር፡፡ ዳንኤል በወቅቱ የሆነውንና እየሆነ የነበረውን በማስረጃ አቅርቧል፤ በጊዜው የሆነውን ነገር መግለፁ ጥፋት ከሆነ ጥያቄው ለምን ተናገረ የሚለው ይሆናል ማለት ነው፡፡ አየህ ወንድም ኤርሚያስ! እውነትን መናገርና ዝም አለማለት የተለያዩ ናቸው፡፡
አቶ ኤርሚያስ “የመጨረሻ…” ባለው ጽሑፉ ውስጥ ደግሞ “እኔን ከአማራዎች ጋር ልታጋጨኝ ነው” ብሎ ሲናደድ አስገርሞኛል፡፡ እሱ ዳንኤልን ከሙስሊሞች ጋር ለማጋጨት መሞከሩ ትክክል ነው፤ ነገር ግን አማራን በተመለከተ ኤርሚያስ ሲያደርግ የኖረውን ሲነግረው ጮቤ ረገጠ፡፡ አይ ኢትዮጵያ! እንዲህ ዓይነቱ ሰው ነው እንግዲህ ሲገዛን የኖረው እንዲሁም ወደ ፊት ሊገዛን የሚቋምጠው፡፡
ብዙ ጊዜ እንደምናየው ሰዎች በሀሳብ ሲሸነፉ ሃሳቡን በሌላ አሸናፊ ሃሳብ ከመሞገት ይልቅ ወደ ስድብና ተራ ነገር እያነሱ ስም ወደ ማጥፋት ይሄዳሉ፡፡ አቶ ኤርሚያስም ይህንኑ ሲያደርግ እናየዋለን፡፡
“ሰዎች ፊት ቆመህ የምትሰብከው እንደዚህ ዓይነት የከረፋ አመለካከትና ውሸት ተሸክመህ…” ይሄን ማለት ያለባቸው በተመስጦ ቁጭ ብለው ትምህርቱን የሚያዳምጡትና የሚከታተሉት ምዕመናን ናቸው እንጂ አንተ አይደለህም ወንድም ኤርሚያስ፤ አንተ ያነሳኸውን ጉዳይ በተሻለ ሀሳብ (ካለህ) ብትሞግት ይሻላል፡፡ ሲያስተምር አንተ መቼ አይተኸው ታውቅና ስለዚያ ታወራለህ? ብታየውማ ለዚህ ስህተት አትዳረግም ነበር፡፡
“እኔን በፀረ-አማራ ፈርጀህ (የኦርቶዶክሱን እንዴት አለፍከው ወይስ ተቀብለኸዋል ማለት ነው?) ብትጽፍ ሚዛን እንደሚደፋልህ የተቀመረች…” እሱ ካየውና ከታዘበው በመነሳት የሆንከውን ነገረህ፤ ላለመሆንህና ላለማድረግህ የራስህን ሃሳብ ማቅረብ ትችላለህ፡፡ እዚህ ላይ ግን አንተም በተለመደው ፖለቲካዊ ቀመር የሆነች ትርፍ ለማግኘት ብለህ ነው ይህን ጽሑፍ ለመፃፍ የተነሳኸው እንጂ ያነሳኸው ጉዳይ የምር አሳስቦህ አይደለም ማለት ነው፡፡
“አቦይ የላከው… እንድልህም…” ዝም ብሎ የመጣልህን ከማለት ለእኛም ሊያሳምነን የሚችል ማስረጃህን ብታቀርብ እንዴት ጥሩ ነበር መሰለህ፤ እስካሁን ሲያስነብበን የኖረው የአዕምሮው ውጤቶች ከብዙሃኑ የተሻለ የአስተሳሰብ ልዕልና ላይ ያለ ሰው መሆኑን ነው የሚመሰክሩት፡፡ (እባክህ ሌላውን ተወውና ሰሞኑን በብሎጉም ሆነ በፌስቡክ ገፁ የፃፋቸውን አንብባቸው)
ሌላው ደግሞ መገንዘብ ያለብህ አስተማሪ ማስተማር እንጂ መሳደብ የለበትም፤ ስላልተሳደበ ደግሞ ወዳጃቸው ነው ማለቱ ከንቱ ፍረጃ ነው፡፡ ክርስቲያን በ“ቢላዋው” ስርም ሆኖ ያስተምራል፣ ይፀልያል እንጂ አይሳደብም፡፡
በጣም ያስገረመኝ የአንተ “ማተማቲክስ” “ሙስሊሞች ሁሉ ቅዱሳን ናቸው እንደማልለው ሁሉ ክርስቲያኖች ሁሉ አክራሪዎች ናቸው ብዬ አላውቅም በል” ትለዋለህ፤ እንዲህ የምትለው ዲያቆን ዳንኤል እኮ የክርስትና ሃይማኖት መምህር እንጂ የስነ-ዜጋ መምህር አይደለም፡፡ አንተ እንዲታከብረው ከእምነቱ ውጪ የሆነን ነገር ይንገርህ? ይሄን ማለትስ ለምን አስፈለገ?
እንደው እነዚህን ነጥቦች አነሳሁ እንጂ ብዙ ያስገረሙኝና ያሳዘኑኝ ሃሳቦችም ነበሩ፤ “የመጨረሻ ደብዳቤ” ብለህ ቋጨሃት፤ ዓላማህን አሳካህ ማለት ነው? ለኩሶ ዘወር . . . ለነገሩ ከዚህ በላይ መሄዱ እንደማያዋጣህ አስልተሃታል (ቀመረኛው)፡፡
ንትርክና ክስ ህዝቡ እንዴት እንደሰለቸው ባወቅክ፤ በእንደዚህ ያለው አስተሳሰብ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከማስቀጠል ባለፈ ምንም የተሻለ ነገር አናመጣም፡፡ ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲካሄድ ኖረ፤ ምን አተረፍን? የት አደረሰን? ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም “የፓርቲ ፖለቲካ በቃኝ” ብለው ሲሰናበቱ “ሁላችንም የኢትዮጵያን ህዝብ አልቅሰን ይቅርታ መጠየቅ አለብን” ብለው ነበር፡፡ ወደምንመኘው መድረስ ከፈለግን ንስሃው የግድ ለሁላችንም አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ አዲስና ከእስካሁኑ የተሻለ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡
እስካድማስ አየነው ፣ አዲስ አበባ
The post በዲ/ን ዳንኤል ክብረትና በኤርሚያስ ለገሰ ዙሪያ እኔም የምለው አለኝ:- “እኛ ጋር ካልሆናችሁ እነሱ ጋር ናችሁ” appeared first on Zehabesha Amharic.