Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Sport: ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተመራጩ ሰውነት ቢሻው ወይስ ማሪያኖ ባሬቶ?

$
0
0

ታምራት አበራ

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1982ዓ.ም በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለ2013ቱ አፍሪካ ዋንጫ ስታልፍ መላው ኢትዮጵያዊ ደስታውን በየአደባባዩ ሲገልጽ ላስተዋለ «ከበስተጀርባ ማን አለ?» ሲባል ሰውነት ቢሻውን የሚዘነጋ የለም፡፡የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለኚህ ባለውለታ ለሰሩት ሥራ ምስጋና በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል አዘጋጅቶ ልዩ ሽልማት ማበርከቱም ይህንኑ ያጠናክራል፡፡
sewenet
እ.ኤ.አ ጥቅምት 2011 ከቀድሞው ቤልጂየማዊው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቶም ሴንትፊልት ተረክበው ብሄራዊ ቡድኑን ለሁለት ዓመት ያህል ያሰለጠኑት የ62 ዓመቱ ሰውነት ቢሻው በሁለት ዓመት የብሄራዊ ቡድን ቆይታቸው 32 ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን አድርገዋል።ከዚህም በ11 ሲያሸንፉ፣ በ12 ተሸንፈው እንዲሁም በ9 ጨዋታ አቻ ወጥተው ዋልያዎቹን ለ2013ቱ የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ በማሰለፍ የሰሩት ውለታ መቼም አይዘነጋም፡፡በአብዛኛው የኢትዮጵያ እግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ ዋልያዎቹ ከ31 ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፉ፣ በ1962 የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን የሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሌላ ታሪክ ተተኪ ትውልድ አገኘ ብሎ ያልጓጓ አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን ያልተጠበቀው ሆነና ተስፋ የተጣለባቸው ዋልያዎቹ ሁሉንም የምድብ ጨዋታዎች ተሸንፈው ከመጀመሪያው ዙር ተባረሩ፡፡

እጅግ አጓጊ በሆነና ምርጥ ሁለተኛ በሚል ናይጄሪያን ተከትለው ወደ 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድናቸውን ይዘው የከተሙት የ62 ዓመቱ ሰውነት ቢሻው፣ በመጀመሪያው ዙር ከምድቡ ማለፍ ተስኗቸው ቢባረሩም በየጨዋታው ላይ ያሳዩት የጨዋታ ፍሰት ከየሀገራቱ ተውጣጥተው ደቡብ አፍሪካ የከተሙ የስፖርት አፍቃሪያንን በማስገረም ‹‹አዲሱ ብራዚል›› የሚል ስያሜ እስከ ማግኘት መድረሳቸው አይዘነጋም፡፡በምድብ ድልድሉ ከቡርኪናፋሶና ናይጄሪያ ጋር የተደለደለችው ኢትዮጵያ በሁሉም ጨዋታ ብትሸነፍም በፍጻሜው ጨዋታ ቡርኪናፋሶና ናይጄሪያ መገናኘታቸውን ያየ ሁሉ ምድቡ የሞት ምድብ መሆኑን ለመረዳት ቀላል ነበር፡፡

አሰልጣኝ ሰውነት በተለይ ደግሞ ዋልያዎቹ በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት ለተካሄደው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፉ በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ከዘወትር ተቀናቃኛችን ሱዳን ጋር በደርሶ መልስ ጨዋታ 5ለ5 በመውጣት ከሜዳ ውጪ ባገባ በሚለው ህግ ታግዘው ወደ ምድብ ድልድሉ መግባታቸው ይታወሳል፡፡ የዋልያዎቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለስ ለረጅም ዓመታት ተቀዛቅዞ ለነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ የማነቃቂያ ደወል የሆኑት ሰውነት ቢሻው መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት 31 ዓመታት የበይ ተመልካች ከሆነበት የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ እንዲሆን ያበቁ አሰልጣኝ ናቸው፡፡

mariano bareto ethiopia coachበሌላ መልኩ ሰውነት ከሰሯቸው ጥሩ ሥራዎች በተጨማሪ ደካማ ጎናቸውን ስንመለከት ምንም እንኳን ከሌሎች አሰልጣኞች በተሻለ መልካም የሚባል ጨዋታን የማሸነፍ ሪከርድ ቢኖራቸውም ከሜዳቸው ውጪ ባደረጓቸው አስራ ስድስት ጨዋታዎች 1 ብቻ ሲያሸንፉ 6 አቻ እንዲሁም በ9 ጨዋታ ሽንፈትን መቅመሳቸው ከሜዳቸው ውጪ ያላቸውን ክፍተት ጠቋሚ ሆኗል።በብሄራዊ ቡድን ውስጥ የሚጠቅሟቸው ተጫዋቾች በእድሜ የገፉ መሆን እና በውጭ ሀገር ክለብ ውስጥ የሚጫወቱ ኢትዮጵያዊ ተጫዋቾች ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ እድል አለመስጠታቸው ሌላው እንደ ክፍተት የሚታይ ነው፡፡

ከሰውነት ቢሻው ሥራ መልቀቅ በኋላ በተደረገው ውድድር ከሰርቢያዊው ጎራን ስቴቫኖቪች ተሽለው ዋልያዎቹን የተቀበሉት በትውልድ ህንዳዊ በዜግነት ፖርቹጋላዊው የ57 ዓመቱ ማሪያኖ ባሬቶ ከሚያዝያ 2014 ጀምሮ ለሁለት ዓመት የሚቆይ ኮንትራት በወር 18ሺ ዶላር እየተከፈላቸው ብሄራዊ ቡድኑን እያሰለጠኑ ይገኛሉ፡፡ባሬቶ ሚያዝያ ወር ላይ ሥራቸውን ሲረከቡ ከገቡት ቃል ውስጥ ዋልያዎቹን ለ2015ቱ ሞሮኮ ዋንጫ ማሰለፍና እድሜያቸው የገፉ ተጫዋቾችን በወጣት መተካት ዋነኛ ዓላማቸው እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ፖርቹጋላዊው ማሪያኖ ባሬቶ የአሰልጣኝነት ታሪካቸው እ.አ.አ ከ2003 የሚጀምር ሲሆን ዳይናሞ ሞስኮን ጨምሮ ስድስት ክለቦችን እንዲሁም ለ9 ወር ያህል የጋናን ብሄራዊ ቡድንምም አሰልጥነዋል። ይህም ይበልጥ ተመራጭ አድርጓቸዋል፡፡በወር 378 ሺ ብር ወደ ካዝናቸው የሚያስገቡት ባሬቶ ዋልያዎቹን ከተቀበሉ ሚያዝያ 2014 ጀምሮ አስር ጨዋታዎችን አድርገዋል።በዚህም 1 ጨዋታ አሸንፈው በ8ቱ ተሸንፈው እንዲሁም በአንድ ጨዋታ አቻ ወጥተው በንጽጽር 80በመቶውን ተሸንፈው ቃል ከገቡትም የአፍሪካ ዋንጫ ውጪ መሆናቸው አሰልጣኙ ይህ ነው የሚባል ሥራ አለመስራታቸውን ይጠቁማል፡፡ ባሬቶ ዋልያዎቹ ለረጅም ጊዜ ያላስደፈሩትን የሱዳን ተፎካካሪነት በቅርቡ በድሬዳዋ ስታድየም 2ለ1 እንዲሁም ባለፈው ዓርብ ለመልስ ጨዋታ ወደ ሱዳን አቅንተው 2ለ0 መሸነፋቸው በሱዳን ብልጫ እንዲወሰድብን ምክንያት ሆነዋል፡፡

በተቃራኒው ከባሬቶ ጥሩ ጎኖች ውስጥ በውጭ ሀገር ክለብ የሚጫወቱ ኢትዮጵያዊ ተጫዋቾችን ለብሄራዊ ቡድን በመጥራት ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ማድረጋቸውና ለወጣት ተጫዋቾች ዕድል መስጠታቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ባሬቶ በትውልድ ስዊድናዊ በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆኑትን ዋሊድ አታንና የሱፍ ሳላን እንዲሁም አሚን ኦስካርን ከኖርዌይ ለብሄራዊ ቡድኑ መጥራታቸው ተጫዋቾቹ በአውሮፓ ያካበቱትን ልምድ እንዲያካፍሉ ዕድሉን ቢያመቻቹም ይህ ነው የሚባል ውጤት ማስመዝገብ አልቻሉም፡፡

ሌላው ማሪያኖ ባሬቶ በተተኪ ትውልድ ላይ የሰሩት ሥራ ይበል የሚያስብል ነው፡፡ ባሬቶ ብሄራዊ ቡድኑን ሲረከቡ ቃል ከገቡት ውስጥ አዳዲስ ወጣት ተጫዋቾችን በቡድኑ ውስጥ ታያላችሁ ያሉት ይገኝበታል፡፡ እውነትም ባሪያቶ እንደተናገሩት ለወጣት ተጫዋቾች ዕድል በመስጠት ናትናኤል ዘለቀን የመሰለ የማይታክት ተጫዋች ማፍራት መቻላቸው እንደ ጥሩ ጎን ይወሰዳል፡፡

በአጠቃላይ «ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተመራጩ በዝቅተኛ ደመወዝ ብሄራዊ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ያበቁት ሰውነት ቢሻው ወይስ በወር 378ሺ ብር የሚከፈላቸው ማሪያኖ ባሬቶ?» የሚለው የሁሉንም እግር ኳስ ወዳድ ህዝብ ምላሽ የሚጠብቅ ጥያቄ ነው፡፡እስከ ዛው ግን ባሬቶ በሽንፈት የሚቀጥሉ ይሆን? ወይስ ተጨማሪ ጊዜ ቢሰጣቸው(የሰውነት ቢሻውን ያህል ቆይታ ቢኖራቸው) የተሻለ ውጤት ያስመዘግቡ ይሆን? ጊዜ የሚፈታው እንቆቅልሽ፡፡

The post Sport: ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተመራጩ ሰውነት ቢሻው ወይስ ማሪያኖ ባሬቶ? appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>