Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

“የምኖረው ለልጆቼ ነው”–አርቲስት ገነት ንጋቱ

$
0
0

የዛሬዋ እንግዳ በሀገራችን አሉ ከሚባሉ ሁለገብ አርቲስቶች መካከል አንዷ የሆነችው አርቲስትና ጋዜጠኛ ገነት ንጋቱ ነች፡ ፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪዋን ካገኘች በኋላ በጋዜጠኝነት ፣ በትወናና ዝግጅት በርካታ ስራዎችን ሰርታለች፡፡ በይበልጥ ግን በብዙዎች ልብ ውስጥ ለመግባት ያስቻላት ‹ውሳኔ› የተሰኘው ፊልም ሲሆን በ ‹ሰው ለሰው› ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማም ድንቅ ብቃቷን አሳይታለች፡፡ ጋዜጠኛና አርቲስት ገነት ንጋቱ ‹ገነት የኪነጥበብ ፕሮሞሽን› የተሠኘ የማስታወቂያ ድርጅት ያላት ሲሆን በFM 96.3 ሬድዮ ጣቢያ ይተላለፍ የነበረ ‹አሸወይና› የተሠኘ ፕሮግራም ታቀርብ ነበር፡፡ ከቁምነገር መጽሄት ጋር ተጨዋውታለች::
Genet
ቁም ነገር፡- ከተጫወትሻቸው ገጸ-ባህሪያት ውስጥ ውስጥሽ የቀረ ንግግር የቱ ነው?
ገነት፡- ውሳኔ ፊልም ላይ ልጆቼን (የፊልሙን ልጆች ) ለተለያዩ አሳዳጊዎች ለመስጠት የወሰንኩበት ምሽት ላይ የነበረውን ንግግርን ከትወናው በጣም አስታውሰዋለሁ፡፡ ልጆቹ በጋራ ምግብ እየበሉ ሁለቱ ወንዶች ልጆች በአጥንት ሥጋ ይጣላሉ ፤ ያንን ያየችው እናት ‹እኔ በህይወት እያለሁ እንደዚህ የሆናችሁ ሳልኖር ምን ልትሆኑ ነው? › ስትል የት ልትሄድ እነንደሆነ ከልጆቿ ለቀረበላት ጥያቄ ስትመልስ ‹‹ እሩቅ ሀገር ፤ ሁላችሁም አንድ ቤት ትሄዳላችሁ ፤ በጣም የሚወዷችሁ እናትና አባት ፡፡ ጥሩ ቤት ፣ጥሩ ልብስ፣ ጥሩ ተውምህርት…….›› እያለች በእንባ ስርቅርቅ የሚቋረጥበት ቦታ ሁሌም በውስጤ አለ፡፡

ቁም ነገር፡- ወላጆች ለልጆቻቸው ማውረስ አለባቸው የምትይው ትልቁ ነገር ምንድነው?
ገነት፡- በራስ መተማመን ፤ፍቅርና ትምህርት ፡፡ ልጆች ሦስቱን ነገር በሚገባ ከያዙ የራሳቸው ጌቶች ይሆናሉ፡፡ ፍቅር ቤተሰባዊና ማህበራዊ ህይወታቸው ውስጥ ቀስ በቀስ የሚገነባ ነው፡፡ ወንድምና እህቶች እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱና እንዲተሳሰቡ ከተደረገ ከማህበረሰቡ ጋርም ሲቀላቀሉ ፍቅር እንጂ ሌላ ተቀጽላ ባህሪ አያሸንፋቸውም ፡፡ ምክንያቱም ፍቅር ከቤት ከጓዳ ይጀምራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ትርፉ ብዙ ይሆናል ፡፡ይህ በየትኛውም ቦታና ጊዜ ቢቀርብ ለድርድር የማይቀርብ ነገር ነው፡፡ ብርሃን ፈንጣቂ አማራጭ የሌለው በራስ የመተማመን መሰረት ነው፡፡ ትምህርትና ፍቅር በለጋ ዕድሜያቸው ላይ ከመገብናቸው በስተእርጅናቸውም አይቸገሩም፡፡ ከእግዚያብሔር ጋር ሁሌም አሸናፊ ይሆናሉ፡፡ ቀና ብለው መሄድም ይችላሉ፡፡

ቁም ነገር፡- የሴት ልጅ ዕድሜና የወንድ ልጅ ደሞዝ አይጠየቅም የሚባለው ለምንድን ነው?
ገነት፡- እም…. ምናልባት ስለምንፈራ ይሆን? አንዳንዴ ከእግዜር ጋር ሁላ የሚያጣላ ይመስለኛል፡፡ ‹ይሄን ያህል ዕድሜ ስለሰጠኸኝ አመሠግናለሁ› ማለትን የምንፈራ ሁላ ይመስለኛል፡፡ ዕድሜ ሰጭና ነሺም እሱ እያለ ፣እኛ የሱን ሀብትና ስጦታ ለመናገር አለመፈለግ ሁሌም ነው እንቆቅልሽ የሚሆንብኝ! እንደሚታወቀው በእያንዳንዱ ዓመት አንድ አንድ ዓመት እድሜአችን ላይ መደመራችን እንደሆነ የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡ የወንድ ልጅ ደመወዝ አይጠየቅም ላልሽኝ እኔም “ለምን አይጠየቅም ?” የሚል ጥያቄ ነው የማነሳው፡፡ በነገራችን ላይ ይህን አባባል ማን እንዳለው ባውቅ ኖሮ መልሼ
እሱን /እሷን እጠይቅ ነበር፡፡

ቁም ነገር፡- መጀመሪያ የትወና ሥራ የጀመርሽው የት ነበር?
ገነት፡- በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪዬን በምሰራበት ጊዜ ነው የሰራሁት፡፡

ቁም ነገር፡- ቆጮ እንዴት ይዘጋጃል
ገነት፡- በነገርሽ ላይ የቆጮ አፍቃሪ ናቸው ከሚባሉት ሰዎች መሃል አንዷ ነኝ፡፡ በልጅነቴ አሰላ እያለሁ በግቢያችን ውስጥ ይዘጋጅ ነበር፡፡ እድሜ ጠገብ የሆነ የኮባ ተክል መረጣ ጀምሮ ፣ አቆራረጡን፣ እግር ሰቅሎ በመክተፊያ ላይ የሚደረገውን የአፋፋቅ ሁኔታ ፣ የጉድጓድ አዘገጃጀት እና አቀባበር ፣ የተብላሎት እድሜውን፣ ለመጋገር ሲፈለግ ከጉድጓድ ወጥቶ እንዴት ተከፍቶ እና ቃጫው ወጥቶ ንፁህ ሊጥ የሚገኝበትን ጊዜ በሂደት ልነግርሽ እችል ነበር፡፡ ጊዜ ስለሌለን እንለፈው እንጂ፡፡ ሊጡ ከወጣ በኋላ በሚገባ ውሃ ጠብ እየተደረገ ከታሸ በኋላ በኮባ ወይም በገጠር አካባቢ በራሱ የቆጮ መጋገሪያ ስጋጃ ላይ ተጠፍጥፎ ወይ በኤሌክትሪክ ምጣድ አልያም በብረት ምጣድ የሚጋገርበት ሂደትን በሚገባ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- ገነትን ምን ያዝናናታል?
ገነት፡- ከልጆቼ ጋር የማሳልፈው ጊዜ ለእኔ ዓለምን የጨበጥኩ እስኪመስለኝ ድረስ በደስታ፣ በእርካታ የምቦርቅበት ጥዑም ጊዜዬ ነው፡፡ ከወላጆቼ፣ ከወንድምና ከእህቶቼ ጋር የማሳልፈውንም ጊዜ እደሰትበታለሁ፡፡ አረንጓዴ የበዛበት ተፈጥሮአዊ ቦታ መኪና ነድቼ በመሄድ ብቻዬን በተመስጦ በሃሳብ የማሳልፈውን ጊዜ ማን ይቀማኛል? . . . . በጣም እወደዋለሁ፡፡ በወረቀት መሀል ተከብቤ መቀመጥም እንዲሁም መዝናኛዬ ነው፡፡ ትወናም እግዜር ለመዝናኛዬ አስቦ የሰጠኝ ሌላው መክሊቴ መሆኑ እግዜርን የማመሰግንበት አጋጣሚ ይፈጥርልኛል፡፡

ቁም ነገር፡- ልጆቼ ባይጠይቁኝ እመርጣለሁ የምትይው ጥያቄ አለ?
ገነት፡- ልጆቼ የፈለጉትን የመጠየቅ መብት እንዳላቸው የማምንና በወቅቱም በደስታ መልስ የምሰጥ እናት ነኝ፡፡ ነገር ግን ከጥያቄ ከምትይኝ እርስ በእርሳቸው እየተጣሉና እየተደባበደቡ ለስሞታ ወደ እኔ የሚመላለሱበት የድግግሞሽ ሰዓት አጥብቄ እጠላዋለሁ፡፡ ልጅ ሆኜ ከወንድሞቼ ጋር እየተደባደብኩኝ እናትና አባቴን ምን ያህል እንዳታከትኳቸው እንዳስብና ለትዕግስታቸውም ክብርና አድናቆትን እንድሰጣቸው ያስገድደኛል፡፡ በተለይ ሐሳቤን በሰበሰብኩበትና በንባብ ወይም በድርሰት ፅሁፍ ላይ እያለሁ ሲሆን፤ ንዴቴ በእጥፍ ይጨምራል፡፡ ግን በቃ እናት አይደለሁ! የመቻል ሞራላዊና ፍቅራዊ ግዴታ ስላለብኝ ለማቻቻል እሞክራለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- ስምንተኛው ሺህ ሲገባ ዓለም ትጠፋለች በሚለው ታምኛለሽ?
ገነት፡- እሱ ነገር ልጅ ሆኜ ጀምሮ ስሰማው ነው ያደግኩት! እስካሁን አላለፈም እንዴ? መቼም ያለፈ ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ ስምንተኛው ሺህ ማለት የዓለም መጨረሻ ነው፡፡ ለእኔ እንደገባኝ የዓለም መጨረሻ ማለት ደግሞ የምድራዊው ዓለም መጨረሻ ነው፡፡ ከዛ ሰማያዊው ዓለም ይቀጥላል፡፡ እንደሚመስለኝ ሰዎች ስምንተኛው ሺህ የሚሉት የምድራዊ ዓለም መጨረሻን ጊዜ ነው፡፡ የክርስቶስ መምጣትን፡፡ ክርስቶስ ደግሞ ድንገት እንደ ሌባ ነው የምመጣው ስላለ ስምንተኛው ሺህ መቼ እንደሆነ ማወቅም መገመትም አይቻልም፡፡ ያኔ ግን ዓለም ትጠፋለች ማለት ሳይሆን አሁን የምንንኖረው ምድራዊ ህይወት አይኖርም ማለት ነው፡፡ ይሄ የዓለም መጥፋት ከሆነ ትርጉሙን አንቺ እንደዛ በይው፡፡

ቁም ነገር፡- ደስታ እንዴት ይገኛል?
ገነት፡- አንቺ አዕምሮ ውስጥ፡፡ ለኔም አዕምሮዬ ውስጥ ነው፡፡ ለነ እርሱም አዕምሮአቸው ውስጥ ነው ያለው፡ ፡ ደስታን ከገበያ ገዝተሽ አትደሰችበትም፡፡ ሁላችንም ባለን ነገር መደሰት ከቻልን ፣የምንደሰትበትን ቦታና ጊዜ ከመረጥን ደስታ የኛ ነው፡፡ ሁላችንም በመዳፋችን ጨብጠን የምንዞረው የቀና አስተሳሰባችን ውጤት ነው፡፡ ለእንካ ሰላምትያው፣ ለትርኪሚርኪውና፣ ለመንደርተኛው አስተሳሰብ ቦታ ካልሰጠን የደስታችንን አጥር አጥብቀን ከያዝነው ደስታ ከዚያ ነው፡፡

ቁምነገር፡- ምን ያህል ዓመት መኖር ትፈልጊያለሽ?
ገነት፡- የእግዜሩን ለእግዜር ትቼ፤ እኔ መኖር የምሻው ልጆቼን አስተምሬና ለቁም ነገር አብቅቼ ኃላፊነቴን ከትከሻዬ እስከማወርድበት ጊዜ ነው፡፡ እስከዚያ እግዜር ጨክኖ ባይወስደኝ ደስ ይለኛል፡፡ እኔ ለልጆቼ ነው የምኖረው፡ ፡ ከዚያ ለእናትና አባቴ፤ ለምን ብትይኝ እነሱ ቀደም ሲል ለእኔና ለወንድም እህቶቼ ሲሉ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፤ ዕድሜም ለምነዋል፡፡ የእኔ መኖር በእነሱ ዕድሜ ላይ በጎ ተጽእኖ አለው፡፡ አየሽ ልጅ ከመጣ በኋላ መኖር ያጓጓል ፡፡ እነሱ መርጠውኝ ሳይሆን በእኔ ፈቃድ ምድር ላይ ለመጡ ልጆቼ ከእግዜር ቀጥሎ የማኖር ፣የማድረግ ፣ለቁም ነገር የማብቃት የእነዚህ ሁሉ ነገሮች ዋስትና በእኔ እጅ ስላለ ይዤባቸው ቶሎ አልሙትባቸው፡፡

ቁም ነገር፡- በሃገራት ስም የሚጠሩ የሰው ስሞችን የትኞቹን ታውቂያለሽ?
ገነት፡- እ . . . እየሩሳሌም፣ ኢትዮጵያ፣ ኤደን፣ ቻይና፣ አፍሪካ(ይሄ ከአህጉር መሆኑ ነው) አስመራ ወዘተ. . . ይሄ የተናገርኩት አይበቃም? ክፍል ውስጥ ለፈተና የተቀመጥኩኝ አስመሰላችሁኝ እኮ ሆ!
Mogachoch

ቁም ነገር፡- የኔ ድክመቴ ነው የምትይው ነገር ምንድነው ጥንካሬሽስ
ገነት፡- ድክመቴ ለልጆቼ ስል የማላምንበትን ነገር ሁሉ ላደርግ እችላለሁ፡፡ ከወንጀል በስተቀር ማለቴ ነው፡፡ እነሱን የሚያስደስታቸው ነገር ከሆነ እንደሻማም ቀልጬ ባልቅ ህመሙ የሚሰማኝ አይመስለኝም፡፡ ልጆቼ እንደ ልባቸው የሚያዙኝ እናት ነኝ፤ አንዳንዴ ትዕዛዛቸው የግል እምነቴንና አቋሜን ሁሉ ቀስ በቀስ ሲሸረሽርብኝ ይታወቀኛል ፡፡ በራሴ ላይ በግርምት እስቃለሁ፡፡ በቃ ምን አደርጋለሁ እኔ ደግሞ አንዲት ኢትዮጵያዊ እሩህሩህ እናት ነኝ፡፡ ጠንካራ ጎኔ ነገሮችን እንደ አመጣጣቸው በተለያዩ በጎ በጎ ትርጉሞች በመለወጥ የመመለስ ፍጥነቴን እንደ
አንድ ጥንካሬ አየዋለሁ፡፡ ብዙ ሰዎችን የጎዳ፣ ያቆሰለ፣ ያሳዘነ ነገር ገነት ጋር ሲደርስ ተራና ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ቀለል የማድረግ ብቃቴ ከአባቴ የወረስኩት ባህሪ ይመስለኛል፡፡ አባቴ ጠንካራና ብልሃተኛ ነው፡ ፡ ሁሌም ቢሆን ለነገሮች ትኩረትና ጊዜ በሰጠሽ ልክ ነው የምትናደጅውም የምትደሰችውም፡፡ ከአባቴ ይህንን ተምሬያለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- የፊልም ስራ አትራፊ ነው አትራፊ አይደለም?
ገነት፡- አትራፊም ነው፡፡ አትራፊም አይደለም፡፡ አገሩን እንደሚወድ ፕሮፌሽናል ባለሙያ ካሰብነው ፊልም የአገር ገጽታን፣ ባህልን፣ ቋንቋና አጠቃላይ የአኗኗር ስርዓትን አሳማኝና አስደማሚ በሆነ መንገድ ደግሞም በቦታና በጊዜ በማይገደብ ደረጃ ለትውልዶች ሁሉ የሚሸጋገር እሴት እንዲኖረው ተደርጎ መሰራት አለበት፡፡ ከዚያ በኋላ ለገበያ ሲቀርብ የአትራፊነቱ ጥያቄ የሚወድቀው ለፕሮሞሽን እንደሚከፈለው ዋጋ ወይም እንደሚሰጠው ጊዜ ይለያይ ይሆናል፡፡ ፕሮሞሽን ላይ የበረታ ፕሮዲውሰር ያተርፋል እንጂ አይከስርም፡፡

ቁም ነገር፡- ባላደርገው ኖሮ ይቆጨኝ ነበር፤ የምትይው ነገር ምንድን ነው?
ገነት፡- ባልወልድ ኖሮ በደንብ ይቆጨኝ ነበር፡፡ በእርግጥ ልጅ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ለእኔ ደግሞ የልቤን መሻት ሰጥቶኛል፡፡ ዩኒቨርስቲ ባልገባ ኖሮ በጊዜ ነበር የምወልደው፤ የሚገርምሽ ልጆቼ አድገው ለእናት አባታቸው ሲያስቡ፣ ሲጨነቁና እኛን ለማስደሰት ጥረት ሲያደርጉ ሳይ ደጋግሜ “ባልወልዳችሁ ነበር የሚቆጨኝ” ብዬ የልቤን እውነት በቀልድ እያዋዛው እነግራቸዋለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- ሐውልትሽ ላይ እንዲጻፍ የምትፈልጊው ነገር ምንድን ነው?
ገነት፡- እንዴ! ሐውልትሽ ስትሉኝ እኮ ሞቴን እያስታወሳችሁኝ ነው፤ ምናለ ትንሽ ብትታገሱኝ?
ቁም ነገር፡- ለማለት የፈለግኩት አልገባሽም ?
ገነት፡- አ….አ… ተይው ገብቶኛል፡፡ ለቀልድ ያህል ነው /ሳቅ…../፡፡ ምን ተብሎ ቢጻፍ እ. . ./እንደማሰብ/ “ለልጆቿ ኖራ፤ ለልጆቿ የሞተች ምርጥ እናት!” ቢባልልኝ አይከፋኝም፡ ፡ ምክንያቱም አሁን ላይ የምኖረው ህይወት በተለይ በእነሱ ፍላጎትና ትዕዛዝ ላይ ያተኮረ በመሆኑ የውስጤን እውነት የሚገልጽልኝ ይመስለኛል፡፡
Mogachoch

ቁም ነገር፡- በአሁኑ ጊዜ የጋብቻውን ያህል ፍቺው በዝቷል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ በአንቺ አመለካከት ምን ይመስልሻል?
ገነት፡- በአደባባይና በጓዳ ውስጥ ያለው ማንነታችን እንደ ሳንቲም ግልባጭ
መለያየቱ ብልሽስ ? በፍቅረኝነት ዘመን ብዙ ነገር ግልጽ አይሆንም፤ ፍቅር ፍቅር እንጂ ገበና ለገበና ተገላልጦ መተዋወቅ አይታሰብም፡፡ ፍቅር ደግሞ በአደባባይ ይጣፍጣል፡፡ ያንን ይበልጥ ለማጠናከር በመጓጓት ለመኖር ይወሰናል፤ መኖርም ይጀመራል፡ ፡ ያኔ ታዲያ እርቃን ማንነታችን፣ ድብቅ ባህሪያችን ቀስ በቀስ ሲወጣ አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ በመሰረቱ ሁለት በተለያዩ ማህበረሰብ ውስጥ ያደጉ ሰዎች በአንድ ቤት ውስጥ ሲገናኙ መጋጨታቸው አይገርምም ፡፡ የትዳር ምስጢር ያለው እዚህ ጋር ነው፡፡ ፍጹምነት ከጓደኛችን መጠበቃችን ነው ለፍቺ የሚያበቃን እንጂ የትዳር ሚስጢሩ ረቂቅ ነው፡፡ ትዳርን እርስ በእርስ በግልጽነት ላይ ከገነባነው የትዳርን ምስጢር ለሶስተኛ ሰው አሳልፈን ካልሰጠን፣ ቤታችንን ትተን የሌላ ባለትዳሮች አድናቂ ካልሆንንና ሁሌም ማደስ ከቻልን ፍቺ የት ያገኘናል?

ቁም ነገር፡- በህይወትሽ ደግሞ እንዳይመጣ የምትፈልጊው ቀን አለ?
ገነት፡- የመጀመሪያ ልጄን ስወልድ ስቃይ ብቻ ሳይሆን ወደ ሞት አምርቼ ዳግም ነፍስ የዘራሁበት ጊዜ ስለነበር ደግሞ አይምጣብኝ፡ ፡ ደግሞ ቢመጣብኝ ደስ የሚለኝ ቀን ደግሞ፤ በስቃይ የወለድኳት ቆንጅዬዋን ልጄን፤ ከህመምና ስቃይ ጋር ግብ ግብ ፈጥሬ ቀና ብዬ አይቼ ሳም አድርጌ “ስታምር!” ያልኩበትን የእርካታ ጊዜ አቤት ደስታዬ !

ቁም ነገር፡- ሁለገብ አርቲስት መሆን ጥቅሙ ምንድነው? ጉዳቱስ ?
ገነት፡- ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ ሁለገብነት የተለያዩ አማራጭ የስራ መስኮች የመፍጠር አቅምን ያመለክታል፡፡ ለምሳሌ ወደ እኔ ብትመጪ በድርሰቱ ባይሳካልኝ ዝግጅት አለልኝ፡፡ በዝግጅት ውጤታማ ባልሆን፤ ትወናው ይጠብቀኛል፡ ፡ ትወናው ይቅርብኝ ብል ደግሞ ጋዜጠኝነቱ የኔ ነው፡፡ ታዲያ ምን ጉዳት ይኖረዋል ትያለሽ? ከጥቅሙ በቀር ጉዳትስ የለውም፡፡

ቁም ነገር፡- አንድ ሰው ስንት ጊዜ ያፈቅራል? አንቺስ ስንት ጊዜ ፍቅር ያዘሽ?
ገነት፡- ነፍሱ እስከፈቀደችለት ድረስ ቢያፈቅር ምን አለበት? አመንዝራነት እንለዋለን እንጂ ፍቅርን አንገድበውም፡፡ ይህ እኮ የነፍስ ምስጢር ነው፡፡ ካልኩሌሽን የለውም፡፡ ወደ እኔ ከመጣሽ ከልጆቼ አባት ጋር አንድ ሶስት ጊዜ አላፈቀርኩም ብለሽ ነው ፡፡ ፍቅር ስቃዩ ጣፋጭ ነው፤ የኔው ፍቅር ደግሞ ሂደትም ውጤትም አለው፡፡

ቁም ነገር፡- ህይወትሽን የምትመሪበት የራስሽ የሆነ ፍልስፍና አለ?
ገነት፡- የኔ ፍልስፍና በዋናነት ‹‹ሁሉም ነገር ለበጎ ነው ነው›› የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹አንኳኩ ይከፈትላችኋል ፤እሹ ታገኛላችሁ›› ነው፡ ፡ በእያንዳንዱ ቀን ውሎዬና አዳሬ ህይወትን በነዚህ ፍልስፍናዎች መነፅር ውስጥ ማየት ችያለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- አመሠግናለሁ፡፡

The post “የምኖረው ለልጆቼ ነው” – አርቲስት ገነት ንጋቱ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles