በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በዘላለም ወርቃገኘው ክስ መዝገብ የተከሰሱት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በማረሚያ ቤት አስተዳደር ላይ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 25/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጠ፡፡ በዛሬው ችሎት የተከሳሾቹ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ‹‹ህዳር 12 ለ 13/2007 ዓ.ም አጥቢያ ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎ የተጠርጣሪዎቹ ንብረት ተወስዶባቸዋል፣ የሰብአዊ ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል፣ ድንገተኛ ፍተሻው ህገ ወጥ ነው›› በሚል በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ላይ ላቀረቡት አቤቱታዎች ማረሚያ ቤቱ የሰጠውን መልስ ሰምቷል፡፡
የማረሚያ ቤቱ መልስ በጽሁፍ ከቀረበ በኋላ በቃልም እንዲቀርብ በታዘዘው መሰረት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የቀጠሮ ማረፊያ አስተዳደር አስተዳዳሪ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አምባዬ ክቡር ፍተሻው መካሄዱን አምነው ነገር ግን፤ ‹‹ፍተሻው የተከናወነው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከጠዋቱ 12 ሰዓት በኋላ ነው፡፡ ፍተሸውም በአቤቱታው ላይ እንደቀረበው ባልታወቁ ሰዎች ሳይሆን በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጥበቃዎች ነው የተከናወነው›› ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡ የፍተሻውን አላማም ‹‹የታራሚዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የተከለከሉ ነገሮችን ፈትሾ ለማስወገድ ነው፡፡ በፍተሸውም ሚስማር፣ ስለት ነገሮች፣ እንዲሁም ብጥብጥ የሚቀሰቅሱ ጽሁፎች ተገኝተዋል፡፡›› ብለዋል፡፡
ባለፈው የአብዛኛዎቹ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ውድቅ ሲደረግ የ7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን፣ እንዲሁም 8ኛ ተከሳሽ ሰለሞን ግርማ የተወሰኑ የክስ ማሻሻያዎች እንዲያደርግ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰረት በዛሬው ዕለት በሁለቱ ተከሳሾች ላይ አሻሽየዋለሁ ያለውን ክስ አቃቤ ህግ ይዞ ቀርቦ በንባብ አሰምቷል፡፡
በመጨረሻም በፍተሻው ወቅት ተፈጽሟል በሚል በተከሳሾቹ ጠበቃ የቀረበውን አቤቱታና ማረሚያ ቤቱ የሰጠውን መልስ አገናዝቦ ውሳኔ ለመስጠት እንዲሁም፤ በሁለቱ ተከሳሾች ላይ የቀረበው ማሻሻያ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ‹‹ተሸሽለዋል ወይንም አልተሸሻሉም›› የሚለውን ለመወሰን ለየካቲት 25/2007 ዓ.ም ጠዋት 3 ሰዓት ላይ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
The post ፍርድ ቤቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አቤቱታ ላይ ቀጠሮ ሰጠ appeared first on Zehabesha Amharic.