Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ምን እየጠበቅን ነው? «የትግራይ ሪፑብሊክ ድንበር አል-ወሃ ድረስ ነው» –ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት

$
0
0

ማክሰኞ የካቲት ፲፩ ቀን ፪ሺህ፯ ዓ.ም. ቅፅ ፫ ፣ ቁጥር ፲፩

የትግሬ ወያኔ በኃሣብ፣ በዕቅድ እና በተግባር ፀረ-ዐማራ፣ ፀረ-ኢትዮጵያ እና ፀረ-ኢትዮጵያዊ የሆነ ድርጅት መሆኑን ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ያረጋገጠው ሃቅ ነው። ሠሞኑንም ከመገናኛ ብዙሃን የሚደመጠው «የትግራይ ድንበር አል-ውሃ ድረስ ነው» የሚለው ወሬ የዚሁ የሚጠበቀው የትግሬ-ወያኔ ተከታይ እርምጃ እንደሆነ አያጠያይቅም።
R_of_Tigrai
ኢትዮጵያን የማፈራረሱ የንድፈ-ኃሣብ መሠረት የተጣለው በተለያዩ የውጭ ኃይሎች እንደሆነ ይታወቃል። ከእነዚህ መካከል ሮማን ፕሮቻዝካ የተባለው የኦስትርያ-ሐንጋሪ መሥፍን (Baron Roman Prochazka) ወጥነት ባለው መንገድ አዘጋጅቶ ያሠራጨው መጽሐፍ ዋና ተጠቃሽ ነው። የሮማን ፕሮቻዝካ መጽሐፍ ኢትዮጵያ በፋሽስት ጣሊያን በተወረረችበት በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. (1935 G.C.) በጀርመንኛ ቋንቋ «Abessinien: die schwarze Gefahr» በሚል ርዕስ፣ በኋላም በ1935 G.C. ወደ እንግሊዘኛ ተተርጉሞ «Abyssinia: The Powder Barrel» ተብሎ ወጥቷል። መጽሐፉ፣ በተለይም ዐማራውን፣ «የነጮችን የበላይነት የማይቀበል፣ ሌሎችን ነገዶች እና ጎሣዎች ጨቁኖ እና ረግጦ የሚገዛ» እና አልፎ ተርፎም «ኢትዮጵያን በአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ሥር እንዳትውል የሚያደርግ ቀንደኛ ጠላታቸው» እንደሆነ ያትታል። ሮማን ፕሮቻዝካ ባቀረበው የመፍትሔ ኃሣብ በግልጽ እንዳሠፈረው፣ ኢትዮጵያን ለማዳከም እና ለማፈራረስ በቅድሚያ የሥልጣን ምንጭ እና የአንድነት ምልክት የሆነውን ዘውዳዊ ሥርዓት መገርሰስ፤ የሕዝቡ መንፈሣዊ ሕይዎት የበላይ እና የዘውዳዊ ሥርዓቱ ርዕዮተ ዓለማዊ ክንድ የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ማዳከም እና ማጥፋት፣ እንዲሁም ራሱን በቋንቋ ክልል ያላደራጀ፣ በሠፊዋ ኢትዮጵያ ተሰራጭቶ የሚኖር የኢትዮጵያዊነት ብሔርተኝነት አቀንቃኝ የሆነውን የዐማራው ነገድ መጥፋት እንዳለባቸው ለፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ምክር ይለግሣል። የፋሽስት ጣሊያን መሪ የነበረው ሞሶሎኒም ሆነ የትግሬ-ወያኔ ያስፈጸሙት እና የሚያስፈጽሙት ይህንኑ ነው።

ፋሽስት ሞሶሎኒ ለ፭(አምስት) ዓመታት ከኢትዮጵያ አርበኞች የሚደርስበትን ጥቃት እየተከላከለ፣ በኢትዮጵያ ከተሞች ዙሪያ በቆየበት ወቅት ያከናወናቸው ተግባሮች የሮማን ፕሮቻዝካን ምክር ተከትሎ ነበር። በቅድሚያ ለ፫(ሦሥት) ሺህ ዘመናት የዘለቀውን ዘውዳዊ ሥርዓት አፍርሶ ኢትዮጵያን በይፋ የኢጣሊያው ንጉሥ ኢምቤርቶ ግዛት ተቀጥላ አደረጋት። የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኃይማኖትን በልዩ ልዩ መንገዶች አዳከመ። የአገሪቱን አስተዳደራዊ ክልል ቋንቋን መሠረት ባደረገ በ፮(ስድስት) ከፋፍሎ አደራጀ። «ዐማራ» ብሎ ከከለለው ግዛቱ ውጭ የሚኖሩ ዐማሮችን ዛሬ የትግሬ-ወያኔ እንደሚያደርገው አባረረ። «ጋላ ሲዳማ» ብሎ ዋና ከተማውን ጅማ ላይ አድርጎት በነበረው ግዛት ከ80,000 (ሰማኒያ ሺ) በላይ ዐማሮችን አባሯል። ልክ ዛሬ የትግሬ-ወያኔ በሚያደርገው መልኩ የአማርኛ ቋንቋ ከዐማራ ክልል ውጭ እንዳይነገር አድርጎ ነበር፣ ወዘተርፈ። በተመሣሣይ ሁኔታም የትግሬ-ወያኔ በቁጥር ከ፭(አምሥት) ሚሊዮን የማያንሱ ዐማሮች ገድሏል። «የዐማራ ክልል» ብሎ ከከለለው ግዛት ሣይቀር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዐማሮችን «አገራችሁ አይደለም» ብሎ አባሯል። የዐማርኛ ቋንቋን ለማጥፋት ሠፊ ዘመቻ ከፍቷል።

የትግሬ-ወያኔ ኢትዮጵያን የማፈራረሱ ዓላማው የሠከነ እንዲሆን ከሠራቸው መሠሪ ዋና ዋናዎቹ ሥራዎች መካከል «ሕገ መንግሥት» ብሎ ባዘጋጀው ሕገ-አራዊት በአንቀፅ 1፣ 2፣ 39 እና 50-52 ያሠፈራቸው ናቸው።

አንቀጽ 1፦ «እኛ የኢትዮጵያ ብሔር/ብሔረሰቦች ሕዝቦች ….» ሲል ነው የሚጀምረው። ይህም አንድ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ዜጋ ወይም ሕዝብ እንዳይኖር፣ ሁሉም በነገዱ ዙሪያ ብቻ ተሰባስቦ ኢትዮጵያዊነትን አውልቆ እንዲጥል ከታለመ የሩቅ ግብ አኳያ የተቀመረ ለመሆኑ ማንም አይስተውም። ቀመሩም የኢትዮጵያ ማፍረሻ መሆኑን አንድ በሉ። በዓለም ላይ የሚገኙት ነገዶች እና ጎሣዎች ሁሉ ተቀላቅለው በሚኖሩባት አሜሪካ፣ በርካታ ጎሣዎችን ባቀፉት ቻይና እና ሕንድ፣ ወዘተርፈ በሕገ-መንግሥታቸው «ሕዝብ» እንጂ «ሕዝቦች» አይሉም። በአንድ ሕገ-መንግሥት ሥር የሚተዳደር ሕዝብ፣ «ሕዝብ» እንጂ «ሕዝቦች» ተብሎ አይጠራም።

አንቀጽ 2፦ «የኢትዮጵያ ወሰን የብሔር /ብሔረሰቦቿ ወሰን ነው» ይላል። የኢትዮጵያ ዳር ድንበር በታወቁትና ዓለም በተቀበላቸው ቋሚ የድንበር መለያዎች የተቀመጠ አይደለም። የትግሬ-ወያኔ «ኢትዮጵያዊ መንግሥት» ሆኖ ለመዝለቅ ቢያስብና ፍላጎቱ ቢኖረው ኖሮ ይህን አንቀጽ በዚህ መልክ አያስቀምጠውም ነበር። በምትኩ በአንቀጹ ሊቀመጥ የሚገባው፦ «የኢትዮጵያ ወሰን በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት ዕውቅና ባገኘውና በካርታ ላይም ከምድር ወገብ በስተሰሜን ከ-እስከ ዲግሪ፣ ከግሪንዊች ሜሪዲያን ወደ ምሥራቅ ከ-እስከ ዲግሪ» ተብሎ መሆን ነበረበት። ይህን ግን እንዲሆን አልተፈለገም። ምክንያቱም እነዚህ ቋሚ መስፈርቶች ከተቀመጡ ሕዝቡ የአገሩን ወርድና ቁመት ሊያውቅ ነው። ወያኔ እየሸራረፈ ለፈለገው አካል የሚሰጠው መሬት «ለምን?» ሊባል ነው።

አንቀፅ 39 (1)፦ «ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው።» ይላል። ይህ ምን ማለት ነው? ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊ፣ ጋምቤላ፣ ወዘተርፈ ተብለው የተፈጠሩት አዳዲስ የባንቱስታን ግዛቶች በሕገ አራዊቱ አንቀጽ 39 በተሰጣቸው መብት መሠረት «በኢትዮጵያ ሥር አንቀጥልም፣ አብሮነት አንሻም፣ እንገነጠላለን» ካሉ የእነዚህ ክልሎች «ዜጋ» ከሚባለው ውጪ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በጉዳዩ ላይ ድምፅ የማሰማት መብት የለውም ማለት ነው። በእርግጥ የዚህ አንቀጽ በሕገ-አራዊቱ መካተት ተጠቃሚ ማንም ሣይሆን የትግሬ-ወያኔ ብቻ ነው። ምክንያቱም የመገንጠል ጥያቄ የሚያነሱ ሌሎች ኃይሎች ለግንጠላው ማሟላት የሚገባቸውን ጉዳዮች በቀላሉ ማሟላት አይችሉም። እያንዳንዱ ክልልም ለይስሙላ በራሱ ክልል ተወላጅ የሚገዛ ቢሆንም፣ እኒህ አሻንጉሊት ገዢዎች ከትግሬ-ወያኔ ፍላጎት ውጭ ምንም ነገር ማድረግ አይችሉም። ስለዚህ የዚህ አንቀጽ ዋና ዓላማ ወደፊት የምትመሠረተዋን የትግራይ-ትግሪኝ ሪፑብሊክን ለመመሥረት «ሕጋዊ መሠረት» ለመስጠት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

ከአንቀጽ 50-52፦ የሥልጣን መዋቅሩን የሚያመለክቱ አንቀጾች ናቸው። በእኒህ አንቀጾች እንደተጠቀሰው ከፍተኛ የሆነው እና በአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ የመወሰን ሥልጣን ባለቤት ያለው «ፓርላማ» ተብዬው ነው። ሆኖም በተግባር የሚታየው ሃቅ ግን በኢትዮጵያ ከፍተኛውን ሥልጣን የያዘው «ፓርላማው» ሣይሆን፣ በሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች በአምባገነንነት ተጨምድዶ የተያዘ መሆኑን ነው። ስለሆነም፥ ፓርላማ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና ኢሕአዴግ የሚባሉት መዋቅሮች የተሞሉት የትግሬ-ወያኔ ፖሊት ቢሮ አባላት ወስነው የሰጡዋቸውን «ለምን? እንዴት?» ሣይሉ በሚያስፈጽሙ ታዛዥ አሽከሮች ነው።

በሌላ በኩል የትግራይ ግንጠላ የማይቀር እና የትግራይ-ትግሪኝ ሪፑብሊክ ምሥረታ ሁኔታ እየተመቻቸ እና የማይቀር መሆኑን በቅርቡ ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን መድኃኔ የተባሉ « ይኸውና! ኤርትራ ሞተች። ትግል ለሀገር ትንሣዔ!» በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ አያሌ ማስረጃዎችን በመዘርዘር ግልጽ ኣድርገውታል። ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን የትግሬ-ወያኔ የትግራይ-ትግሪኝ ምሥረታ ዕውን ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ የሚከተሉትን ማስረጃዎች ይጠቅሳሉ።

ሜንሆት ወልደማርያምን በመጥቀስ «ሕወሓት የትግራይ ነፃ ሀገር ኅልውና ለማመቻቸት ሲል የብሔር ብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚል መሠረት ድንጋይ አስቀምጧል። ይህም በሀገሪቱ የጸደቀውን (ኤትኒክ ፌዴራሊዝም) መሠረት ባደረገው ሕገመንግሥት የተደገፈና የታቀፈ እንዲሆን ተደርጓል። ትልቁ ዓላማም ሀገረ ትግራይን ለማቋቋም አንዳንድ የኤርትራ ቦታዎችን ቆርሶ ወደ ትግራይ ማካለል ነው።»( ገጽ 12)

«አቶ ስብሐት የባድመ ቀውስ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ፣ ኢሣያስ ሰላማዊ መፍትሔ አልቀበልም ብሎ አፈንግጦ በነበረበት ጊዜ፣ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ የኃይል ርምጃ እንዳትወስድ የሚቻለውን ያህል አድርጎ ነበር። አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር መዋጋት አልነበረባትም ባይ ነው። የአቶ ስብሐት ነጋ አቋም መነሻው የኤርትራና የትግራይ ዝምድና ሕያው ነው የሚል አመለካከት ነው። አቶ ስብሐት «ትግራይ እኮ ካለ ኤርትራ አትኖርም፣ ኤርትራም እንደዚሁ» (ገጽ 13) የሚለው አክራሪ እምነቱ የትግራይ መገንጠል አይቀሬነት የሚያመልክት አቋም እንደሆነ ጸሐፊው ያምናሉ። ይህ የስብሐት አቋም ወይም አባባል ደግሞ ዝም ብሎ ለማለት ያህል የተባለ ሳይሆን፣ ከመለስ ሞት በኋላ በወያኔ መሪዎች አካባቢ የትግራይ መገንጠል እና ከኤርትራ ጋር ሊኖራት የሚችል ዝምድናን በሚመለከት ውስጥ ለውስጥ እየተካሄደ ያለው መመሣጠር መገለጫ መሆኑን ያስረዳል።

«ወያኔ ወይም አመዛኙ የአመራር ክፍል በኢትዮጵያ ሥልጣን ለመቆጣጠር ካልተሳካለት ለብቻው ተገንጥሎ ነጻ ሪፑብሊክ ለመመሥረት ዕቅድ ያለው ነው።» (ገጽ 20)
«ሪፈረንደም በሚል ስም የተካሄደው የይስሙላ ሂደት ትግራይ ከኢትዮጵያ መገንጠል ለሚችል የረጅም ጊዜ ዕቅድ መንገድ የሚያመቻችና የሚጠርግ እንጂ፣ የኤርትራን ሕዝብ መብትና ጥቅም ለማስከበር ተብሎ በቅንነት የተቀናጀና የተደራጀ አልነበረም።» (ገጽ 27)
ተስፋጽዮን እንደጠቆሙት የትግሬ-ወያኔዎች «ሥልጣን ላይ ከሌሉ የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚፈቅደውን ሕገ መንግሥታቸውን ተጠቅመው ትግራይ ከኢትዮጵያ በኃይል ለመገንጠል ሊሞክሩ ነው። ይህንን ዕውን ለማድረግ ደግሞ አስቀድመው የቀረችውን ኢትዮጵያ በረቀቀ መንገድ መበታተን፣ አለያም የሕዝቧን እና የግዛቷን አንድነት የሚያዳክምና የሚያላላ ተግባር ከመፈጸም ወደኋላ አይሉም።» በማለት የትግራይ ሪፑብሊክን የመመሥረቱ ሁኔታ በከፍተኛ ሚስጢር ተይዞ እየተሠራበት መሆኑን ሰሚ ካለ ነግረውናል።
የትግሬ-ወያኔዎች ቀደም ብለው ከ፲፱፻፹፫ ዓም ጀምሮ፣ ከሰሜን ጎንደር እና ሰሜን ወሎ አውራጃዎች የዐማራ ተወላጆችን ገድለው፣ አፈናቅለው እና ማንነታቸውን በግድ አስቀይረው ሠፊ የትግራይ ግዛት መስርተዋል። ሠሞኑን ደግሞ ከተለያዩ የብዙሃን መገናኛ ተቋሞች የተሠራጩ ይፋ መግለጫዎች እንደሚያመለክቱት የትግራይ ግዛት እስከ አል-ውሃ (ወሎ) የሚዘልቅ እንደሆነ ተገልጿል። ወደፊት ደግሞ አሰብን ያካተተ ግዛት ያለው የትግራይ-ትግሪኝ ሪፑብሊክ ለመመሥረት በሠከነ ሁኔታ እየሠሩ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። የትግሬ-ወያኔ አገር ለማፍረስ ይህን ያህል ርቀት ሲጓዝ፣ «ኢትዮጵያዊ ነኝ» የሚለው ኃይል ግን ይህንን እንቅስቃሴ የሚገታ አንዳችም ተጨባጭ ሥራ ካለመሠራቱም በላይ፤ የአገሪቱን የአፈራረስ ሂደት በቅጡ የተረዳም ሆነ ሊረዳ የሚሻ ወገን ያለ አይመስልም። እነዚህ ሁሉ በአንድነት ተጠቃለው ሲመዘኑ ኢትዮጵያ እንደ አገር መኖሯን የሚያመለክቱ አይደሉም። ዕውነታው አገሪቱ በ፳፬(ሃያ አራት) ዓመታት አዝጋሚ የመፈራረስ ሂደት፣ በሰመመን መልክ እየተበታተነች መሆኑን ነው። ይህ ደግሞ በዕቅድ እና በሰከነ መልኩ በኢትዮጵያ ጠላቶች የተቀነባበረ ረጅም ጊዜ የወሰደ ሂደትን የተከተለ መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለበትም።

ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን የሚወዱና የሚያፈቅሩ ዕውነተኛ ዜጎች፣ «ምኗን ሰዳ ምኗን ጨበጠች» እንዳይሆን ነገሩ፣ ከአሁኑ ተቻችሎ እና ልብ ለልብ ተዋውጦ ይህ ዘረኛ ቡድን የፈለውን ሣያደርግ፣ ኢትዮጵያን የምንታደግበትን መንገድ በጋራ መላ እንድንል ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት የተለመደ ጥሪውን ያቀርባል። ከሁሉም በላይ የጥፋት ዘመቻ የተከፈተበት የዐማራው ነገድ ተወላጆች ለዚህ ጥሪ የሚያቀርቡት አሉታዊ ምክንያት ሊኖር አይገባም። ጥሪው የሞት፣ የሽረት ነውና ኅልውናችን በማስጠበቅ የኢትዮጵያን ትንሣዔ ዕውን የማድረግ ትውልዳዊ ኃላፊነታችን ልንወጣ ይገባል።

ዐማራውን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደግ!

ፈለገ አሥራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው!

ኢትዮጵያ በጀግና እና ቆራጥ ልጆቿ መስዋዕትነት አንድነቷ እና ነፃነቷ ተከብሮ ለዘለዓለም ትኖራለች!

The post ምን እየጠበቅን ነው? «የትግራይ ሪፑብሊክ ድንበር አል-ወሃ ድረስ ነው» – ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>