መነሻ
በቅርቡ ማክቤዝ ሚዲያ ኮሚኒኬሽን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ኤች አይ ቪ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ወሲባዊ ንግድ የሚፈጸምባቸው ማሳጅ(መታሻ) ቤቶች መስፋፋት በወጣቶችና በሴቶች ላይ የሚያስከትሏቸው አሉታዊ ተፅዕኖዎች በሚል ርዕስ አንድ ጥናት አሰርቶ ነበር፡፡ ወሲብና ወሲባዊ ተግባራት የሚፈፀምባቸውን ማሳጅ ቤቶች በተመለከተ bማህበራዊ ስነልቦና ባለሙያዎቹ አቶ በላይነህ ዘለለውና አቶ ዮሴፍ አህመድ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው በአዲስ አበባ ከተማ በተለይም ቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኙ መታሻ (ማሳጅ) ቤቶች ውስጥ ህገ ወጥ የሆኑ ማሳጅ ቤቶች በአሳሳቢ ደረጃ ተስፋፍተዋል፡፡ ማሳጅ ቤቶች ለወሲብ ቱሪዝም መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
እንደሚታወቀው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተለያዩ ሃገራት ዲፕሎማቶችና የውጭ ሃገር ድርጅት ሰራተኞች በብዛት ይኖራሉ፡፡ ትላልቅ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና ጉባኤዎች በተደጋጋሚ ይደረጋሉ፡፡ በነዚህ ጉባኤዎች ላይ ለመሳተፍ የሚመጡ የባህር ማዶ ሰዎች በአብዛኛው ጊዜ አዳራቸውን የሚያደርጉት በህገወጥ ማሳጅ ቤቶችና በትላልቅ ሆቴሎች ውሰጥ በግዥ ከሚቀርቡላቸው ሴተኛ አዳሪዎች ጋር አንዳንዴም በደላሎች አማካኝነት ከሚቀርቡላቸው የቤት ልጆች ጋር እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህ ሂደት በገንዘብ ተጠቃሚ የሚሆኑ በርካታ ሰዎች አሉ፡ ፡ በወጣት ሴቶች ስነልቦና እና ስነተዋልዶ ጤና እንዲሁም በማህበረሰቡ ግብረገባዊ አስተሳሰብ ላይ የሚነግዱ፣ ኢ – ሞራላዊና ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ገንዘብ የሚሰበስቡ ማሳጅ ቤቶች ድርጊት በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ይላል ጥናቱ፡፡ ይሁንና ችግሩን ለመፍታት የተደረጉ እንቅስቃሴዎች የሉም ወይም አነስተኛ ናቸው፡ ፡ የዚህ ጽሁፍ አላማ ጥናቱን ጨምቆ በማቅረብ የጉዳዩን አሳሳቢነት በማሳየት የሚመለከታቸው አካላት በፍጥነት ወደተግባራዊ እርምጃ እንዲገቡ ግፊት ማድረግም ነው፡፡
16ኛው “ዓለም አቀፍ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እና የአባላዘር በሽታዎች ጉባኤ በአፍሪካ” (16th International Conference on AIDS and STLs in Africa – ICASA) ከሦስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ እንደተስተናገደ ይታወሳል፡፡ከዚያ ቀደም ብሎ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ያስደነገጠና ያወዛገበ አንድ ስብሰባ ሊደረግ ታስቦ ነበር፡፡ “የአፍሪካ ግብረ ሰዶማውያን የቅድመ ኮንፈረንስ ማነቃቂያ ስብሰባ” የተባለው ይህ ስብሰባ በተለይ በሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ውግዘት ገጥሞት ነበር፡፡ በማህበራዊ ድረ ገጾችና በተለያዩ የሃገር ውስጥ ጋዜጦችና መጽሔቶች (ቁም ነገር መጽሔትን ጨምሮ) ብዙ ፅሁፎች በጉዳዩ ዙሪያ ወጥተው ነበር፡ ፡ ለግብረ ሰዶማውያን መስፋፋትና የወሲብ ቱሪዝም እየጨመረ እንዲመጣ ከሚያደርጉ አባባሽ ነገሮች አንዱ የህገ ወጥ ማሳጅ ቤቶች መኖር ነው፡፡ እንደ ታይላንድ ያሉ ሃገራት ለዚህ ምሳሌ መሆን ይችላሉ፡፡
የወሲብ ቱሪዝም ‹ማግኔት›
በቅርቡ በወጣ አንድ ዓለም አቀፍ ሪፖርት ላይ ኢትዮጵያ የወሲብ ቱሪዝም እየተስፋፋባቸው ከመጡ ሃገራት አንዷ መሆኗን ‹‹Ethiopia has become a magnet for sex tourism›› (ኢትዮጵያ የወሲብ ቱሪዝም ማግኔት እየሆነች ነው) በማለት ይገልጻታል፡፡ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ጉባኤዎችንና ስብሰባዎችን ማስተናገዷ እያስገኘላት ከሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ገቢ በተጻራሪ ለማህበራዊ ችግሮች እየዳረጋት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ወደ ሃገሪቱ የሚገቡ የውጭ ሃገር ጎብኝዎችና የጉባኤ ተሳታፊዎች ለመጤ ባህሎች እያጋለጧት ነው፡፡ በመጠጥ ቤቶችና በተለያዩ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች የሚዘወተረው ወሲባዊ ንግድ ወደ መኖሪያ ቤቶችም ገብቷል፡፡ በተለይ የእንግዳ ማረፊያ ተብለው የተዘጋጁ አንዳንድ ቤቶች ለህገ ወጥ ማሳጅ ቤቶችና ለወሲብ ንግድ መፈጸሚያነት እየዋሉ ነው፡፡
እንደ ተባበሩት መንግስታት የዓለም የቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) ‹‹ የቱሪዝምን ቅርጽ እና መረብ በመጠቀም በማንኛውም የወሲብ ነክ እንቅስቃሴ ላይ ለመሳተፍ የሚደረግ ጉዞ ›› የወሲብ ቱሪዝም ወይም ዘመናዊ የወሲብ ንግድ ነው ሲል ይገልጻል፡፡
በዓለማችን ከቅርብ አሥርት ዓመታት ወዲህ የወሲብ ቱሪዝምን ህጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖረው በማድረግ ለሃገሪቱ እንዲሁም ለዘርፉ ተዋንያን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሊያመጣ በሚችል መልኩ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡
ከእነዚህ ሃገራት ውስጥ ጀርመን፣ ብራዚል ፣ሞሮኮ፣ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ እንዲሁም በምርጥ የእግር ኳሰኞቿ የምናውቃት ኔዘርላንድስ ከአጠቃላይ የሃገራቸው ኢኮኖሚ ከ ሁለት እስከ አምስት በመቶ የሚሆነውን ከዚሁ ዘርፍ ይሸፍኑበታል፡፡
ይህ ዘርፍ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በርከት ያሉ አገልግሎት ሰጪዎችን የሚያቅፍ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አየር መንገዶች፣ሆቴሎች የየብስ ትራንስፖርት ተቋማት የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡ ፡
ከዚህ በተጨማሪ እነዚሁ ሃገራት በድርጊቱ ለሚሳተፉት ሴት ዜጎቻቸው የማህበራዊ ዋስትናን እስከ ጡረታ ድረስ በመስጠታቸው ድርጊቱ የሚያስከትለው ማህበራዊ ቀውስ ዝቅተኛ ቢሆንም ሞራላዊ ተጠያቂነቱ ግን ከፍ ያለ ነው፡፡
በሃገራችን በተለይም በመዲናችን እና በተለያዩ የቱሪስት መናኸሪያ በሆኑ አካባቢዎች ከራቁት ጭፈራ ቤቶች የጀመረው ይህ የዘመናዊ የወሲብ ንግድ (የወሲብ ቱሪዝም) በአሁኑ ሠዓት በርከት ያሉ የወሲብ ንግድ ተቋማትን፣ ሰፊ የድርጊቱ መረብ፣ እሳት የላሱ ደላሎችን እንዲሁም ሰፋ ያለ ካፒታል የሚያንቀሳቅስ እና ወደ ኢንዱስትሪ ደረጃ ሊሸጋገር የደረሰ ተግባር ሆኗል፡፡ በተለይም የሃገራችን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ እየተጠናከረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት እየጨመረ ያለውን የወጭ ሃገራት ዜጎችን ፍሰት ተከትሎ ዘርፉ ጠንከር ወደማለት እና የአደባባይ ሚስጥር በሚባለው ደረጃ ላይ ለመድረስ ችሏል፡፡
እነዚህ የወሲብ ንግድ ማዕከላት በዘርፉ ተዋንያን እና ቅርበት ባላቸው ወገኖች ዘንድ ‹‹ፍርድ ቤት ›› በመባል የሚታወቁ ሲሆን የድርጊቱ ተሳታፊ ሴቶች ደግሞ ከፈረንሳይኛ ቃል በተወረሰ ነገር ግን ከድርጊቱ ጋር ምንም ተዛምዶ በሌለው ‹‹ትራባዪ›› በሚል ስያሜ ይታወቃሉ፡፡
እነዚህን ‹‹ፍርድ ቤቶች›› እና ‹‹ትራባዪዎች›› ከውጭ ሃገራት ዜጎች ጋር በማገናኘት ረገድ የአንበሳውን ሚና የሚጫወቱት ደላሎች በተለምዶ ‹‹ጋይድ››የሚባሉ ሲሆን የትራባዪዎች (የወሲብ ንግድ ተሳታፊ ሴቶች) ማደሪያ እና መዋያ ቦታ የወሲብ ንግድ ማዕከላቱ ‹‹ፍርድ ቤቶቹ›› ናቸው፡፡
አንድ ፍርድ ቤት በውስጡ ከ 15-20 ለሚሆኑ ‹‹ትራባዪዎች›› ደንበኞቻቸው እስኪመጡ የሚገለገሉበት የማደሪያ አልጋ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን የሚያሟሉ ሲሆን ለሚጎበኟቸው የውጭ ሃገራት ዜጎችም በውድ ዋጋ የሚሸጡ መጠጦችን ለሽያጭ ያቀርባል፡፡
አንድ የውጭ ሃገር የወሲብ ደምበኛ የመረጣትን ‹‹ትራባዪ›› ከፍርድ ቤቱ ለአንድ አዳር ወይም ውሎ ይዞ ለመውጣት ከአንድ ሺህ እስከ አምስት ሺህ ብር የሚከፍል ሲሆን እንደየ ፍርድቤቱ ህግ ደግሞ ተጨማሪ የመውጫ የኮቴ የመሳሰሉትን ክፍያ መክፈል ይጠበቅበታል ፡፡
ለአንድ አዳር ወይም ውሎ የተስማማች አንድ ‹‹ትራባዪ›› ሊከፈላት ከተስማማችው የብር መጠን ውስጥ ከ50-70 በመቶ የሚሆነው በወሲብ ተቋሙ ባለቤት እና በደላሎች የሚወሰድ ነው፡፡
እነዚህ የወሲብ ንግድ ተቋማት በአብዛኛው በትላልቅ ቪላ ቤቶች የሚገኙ ሲሆን በተለይም ከቦሌ ድልድይ እስከ ደምበል፣ በሃያ ሁለት ፣ሲኤምሲ፣ መስቀል ፍላወር እንዲሁም የቱሪስት እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ተበራክተው ይገኛሉ፡፡
ይህ የወሲብ ቱሪዝም ወይም የወሲብ ንግድ ከወሲብ ንግድ ተቋማቱ ባለፈ መሸታ ቤቶችን፣የጫት ማስቃሚያ ቤቶችን ፣ የእንግዳ ማረፊያዎችን እንዲሁም ሌሎች መሰል ተቋማትን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንደማስተሳሰሩ መጠን የሚያዘዋውረው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ ቢሆንም ከዚህ ዘርፍ መንግሥትም ሆነ የድርጊቱ ተሳታፊ ሴት እህቶቻችን የሚያገኙት ጥቅም ዘላቂነት ያለው እና ቀጥተኛ ባለመሆኑ በህብረተሰቡ ላይ የሚፈጥረው ማህበራዊ ቀውስ ከፍተኛ ነው፡፡
ምንም እኳን ይህ ተግባር በኢትዮጵያ ህጎች የተከለከለ ቢሆንም ድርጊቱን ከመቆጣጠር አኳያ የመንግሥት ጥረት ዝቅተኛ የሚባል ነው፡፡ለዚህም በከተማችን በርክተው የሚገኙት እነዚህ የወሲብ ንግድ ተቋማት ምስክሮች ናቸው፡፡
በዚሁ በወሲብ ንግድ ላይ በሁለት ጎራ የተከፈሉ አስተያየት ሰጪዎች የሚደመጡ ሲሆን በአንደኛው ወገን ድርጊቱ የሃገሪቱን መልካም ስም እና የማህበረሰቡን ሞራል የሚነካ በመሆኑ የቱንም ያህል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ቢያመጣ ሊወገዝ እና ቁጥጥር ሊደረግበት የሚገባ ተግባር ነው ሲሉ የሚሞግቱ አሉ፡፡ በሌላኛው ጎራ ይህን ተግባር ማስቆም ለሚጠይቀው ቁርጠኝነት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት አሊያም ድርጊቱ ይፋዊ በሆነ መንገድ ተፈቅዶ ከድርጊቱ ተዋንያን ከግብር እና ከሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎችን በመሰብሰብ የሚገኘውን ገቢ በመጠቀም ድርጊቱ የሚፈጥረውን ማህበራዊ ቀውስ መቀነስ ተገቢ ነው ባዮች ናቸው፡፡
የማሳጅ ታሪካዊ
ዳራ
የማሳጅ ታሪካዊ አመጣጥ በብዙ ሀገሮች የብዙ ሺህ ታሪክ ያስቆጠረ ነው፡፡ በጥንታዊ ጽሑፎች ላይ ተጽፎ እንደሚታየው በምስራቃዊያንና በምዕራባዊያን ስልጣኔ ሰዎችን ለመፈወስና ለማሻል ሰዎችን በመንካት/በማሸት/ እንደሚያደርጉ ታሪካዊ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ አብዛኛውን በአሁኑ ሠዓት የምንጠቀመው የማሳጅ ዘዴዎችና አቀራረቦች አጀማመራቸው ከጥንቱ የማሳጅ ዘዴዎች ነው፡፡በጥንት ጊዜም ቢሆን ማሳጅን የሰዎችን ህመም ለማሻል፣አደጋን ለማሻል(ጉዳቱን ለመቀነስ)፣ሰዎችን ሰውነታችውንና አዕምሮአቸውን ዘና ለማድረግ(ለማዝናናት) እንዲሁም ህመምን ለመከላከልና ለማዳን ሲጠቀሙበት ነበረ፡፡
በምስራቁ ዓለም የማሳጅ ታሪክ እንደሚያሳየው ማሳጅ እንደ መለኮታዊ ተዓምር/ Divinely- created system/ ተደርጎ የሚታይበት ሁኔታ ነበር፡፡በህንድ ሀገር ማሳጅን አይሩቨዳ / Ayurveda/ ብለው ይጠሩት የነበረ ሲሆን፣ይህም ህዝብ ይተገብርበት/ይገለገልበት የነበረው ከ3000 ዓ.ዓ ቀደም ብሎ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎችና ቦታዎች እንዲሁም በደቡብ ምስራቅ ኢሲያ ሀገራትም ተስፋፋተው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉው፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ የማሳጅ ህክምና በጥንታዊት ቻይና የረዥም ዓመት ታሪክ ያለው ነው፡፡ይህም የህክምና አይነት ከ2700 ዓ.ዓ አካባቢ ተግባራዊ ይደረግ እንደነበረ የታሪክ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ጥንታዊ ቻይናዊያን ማሳጅን ለህክምና አገልግሎትና ራስን ለማዝናናት ይጠቀሙበት ነበር፡፡
ወደ አህጉራችን አፍሪካ ስንመጣም ይህ የማሳጅ ህክምና አይነት በተለያዩ ሀገሮች ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በሺ የሚቆጠሩ ዓመታት አስቆጥሯል፡ ፡ለምሳሌ በጥንታዊ ግብጽ የእራሳቸው የሆነ የማሳጅ አይነት ይጠቀሙ እንደነበር በፖፒረስ ላይ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡የተለያዩ ተመራማሪዎች እንደሚገምቱት ሪፈሎኤሶሎጂክ/Reflexology/ የሚባለው ማሳጅ አይነት በግብጽ በ2500 ዓ.ዓ አካባቢ እንደተጀመረ ይገመታል፡፡ይህን የማሳጅ አይነት የተወሰነ የሰውነት ክፍልን ብቻ የማሻል ስራ ላይ ያተኩራል፡፡(በሀገራችን ወጌሻ ጋር እንደምንሄደው)
በተለያዩ ጊዜያት እንደሚታየው ማሳጅ የተለያዩ ጠቀሜታዎች እንዳለው ቢታወቅም ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወደቀ እየተነሳ የቆየበት ሁኔታ ስለነበረ አንዳንድ ባለሙያዎች በተለይም ከጥቂት መቶ ዓመታቶች በፊት ጠቀሜታው ወሳኝ እንደሆነ በመረዳት በ1600 ዓ.ም አከባቢ በምዕራባዊያን የህክምና ባለሙያዎች ድጋሚ ጠቀሜታውን በመገንዘብ ለአገልግሎት እንደ ገና ማዋል ተጀመረ፡ ፡ሆኖም ግን እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ማሳጅ ከፍተኛ እውቅና በማግኘት በብዛት ጥቅም ላይ መዋል ጀመረ፡፡
አዲሱ ጥናት
በቅርቡ ማክቤዝ ሚዲያ ኮሚኒኬሽን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ኤች አይ ቪ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ወሲባዊ ንግድ የሚፈጸምባቸው ማሳጅ ቤቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የተሰራው ጥናት ዋና ዓላማ ‹በሀገራችን መዲና በሆነችው አዲስ አበባ መጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች በተለይም የተለየ ወሲባዊ ንግድ የሚፈጸምባቸው መታሻ/Massage parlor/ ማረፊያ ማሳጅ ቤቶች መስፋፋት እያስከተለ ያለውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፤የስነተዋልዶ ጤና እና ስነልቦናዊ ተፅዕኖዎች እና ቀውሶች በሚመለከት ለችግሩ መነሻ ፣ አባባሽ ምክንያቶች እና የምክረ ሀሳብ/ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማቅረብ እንደሆነ› ይገልፃል፡፡
መጤ ባህልና ልማዳዊ ድርጊቶች በወጣቶችና ሴቶች ላይ የሚያደርሷቸው ተጽዕኖዎች በርካታ
መሆናቸውን የሚጠቅሰው ጥናቱ በአፍሪካ ሀገራትም መጤ ባህል በአምራች ትውልዱ ላይ አሉታዊ ተጽኖ እያሳደረው እንደሆነ እንደ አብነትም ለምሳሌ፡ -በግብጽ ፤በሊቢያ(ከጎረቤት ሀገር)፤በሞሮኮ(ወንደኛ አዳሪነት..)፤በኬፕ ቬርዴ(የወሲብ ቱርዝም)እንዲሁም በናይጄሪያ(በፍተኛ ወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ሴቶችን ወደ ሌሎች ሀገሮች በመላክ የቀዳሚውን ድርሻ ከያዙት ሀገራት ውስጥ እንደሆኑ ያብራራል፡፡
ጥናቱ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ፤ ማለትም ከማሳጅ ማሰልጠኛ ተቋማት፣፤ ከማሳጅ ቤት ተጠቃሚዎች ፤ ከማሳጅ ቤት ሰራተኞች ጋር በርእሱ ዙሪያ ቃለ መጠይቅ በማድረግ የተሰራ ሲሆን ከዚህ `በተጨማሪም በአሳታፊ የአካል ምልከታ ማሳጅ ቤቶችን በመቃኘት መረጃዎች ተሰብስበዋል ይላል ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አስር ክፍለ ከተማዎች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ ክፍለ ከተማዎች ማሳጅ የሚከናወንባቸው ቦሌ187 ፣ጉለሌ 5 ፣የካ 20፣ አዲስ ከተማ 9 ፣አቃቂ ቃሊቲ 0 ፣ቂርቆስ 77 ፣አራዳ 10 ፣ንፋስ ስልክ 30 ፣ልደታ 3፣ ኮልፌ 8 ሲሆኑ በጠቅላላው 349 (ሶስት መቶ አርባ ዘጠኝ ) ማሳጅ ቤቶች ከአዲስ አበባ ከንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ፈቃድ አግኝተው በመስራት ላይ እንደሆኑ ጥናቱ ያመለክታል ፡፡ አብዛኛዎቹ የሚገኙትም ቦሌ አካካቢ በመሆኑ ቦሌ ክ/ከተማ ውስጥ ከሚገኙ 187 ማሳጅ ቤቶች ውስጥ 35 የሚሆኑ ማሳጅ ቤቶችን በመምረጥ ጥናቱ ተካሂዷል፡፡ የማሳጅ አገልግሎቱ የሚሰጥባቸውም ትላልቅ ህንፃዎች፣ ሰፋ ያለ ግቢ ያላቸው ቤቶች፣ አፓርታማዎችና በከተማዋ ዋና ዋና አካባቢዎች በሚገኙ ፎቆች ላይ የሚገኙ ቤቶች መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ከእነዚህ ማሳጅ ቤቶች መካከል አብዛኞቹ ወደ ህገወጥ ተግባራት እየገቡ ሲሆን ጥናቱ እንደሚለው ለህገወጥ ማሳጅ ቤቶቹ መስፋፋት ተከታዮቹ ምክንያቶች በዋናነት ይነሳሉ፡-
– ወሲባዊ ንግድ የሚፈጸምባቸው ማሳጅ ቤቶች ለባለቤቱና ወሲባዊ ንግድ ለሚትፈጽሙ ሴቶች ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚያስገኝላቸው፣
– ተገልጋዮቹ የተሻለ ነጻነት እንዲሰማቸው ስለሚያደርግ፣
– ወሲባዊ ንግድ የሚፈጽሙ ሴቶች በሆቴልና በጎዳና ላይ ከሚያደርጉት ወሲባዊ ንግድ የማሳጅ ቤቱ በተሻለ ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ስለሚያደርግላቸው፣
– ደላሎች ከዚህ ስራ የተሻለ ገንዘብ እያገኙበት ስለሆነ ስራውን እንዲስፋፋ አድርጎታል፣
– ወሲባዊ ማሳጅ ቤቶች ተጠቃሚ የማህበረሰብ ክፍል እየጨመረ መምጣቱና ሌሎችም ምክንያቶች እንዳሉት ጥናቱ ደርሶበታል፡፡
ከገቢ አንፃርም በእነዚህ ማሳጅ ቤቶች ውስጥ መስራት ስለሚያስገኘው ገቢ በጥናቱ ውስጥ የተካተተ አንድ ሰራተኛ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቶ እናገኛለን፡፡ ‹በአሁኑ ሰዓት በመዲናችን ስትዟዟር በተለይም ደግሞ ቦሌ ክ/ከተማ ዞር ዞር እያልክ ብታይ ልክ እንደ ካፌ በየአካባቢው ወሲባዊ ንግድ የሚፈጸምባቸው ማሳጅ ቤቶች ተከፍተው ታገኛለህ፡፡ለዚህ ስራ በዋናነት ምክንያት የሚሆነው ደግሞ ለተጠቃሚው የሚሰጠው ተጨማሪ አገልግሎት (ወሲብ) ነው፡፡ለምሳሌ እኔ እሰራበት የነበረው ቤት ወደ ስድስት ማሳጅ የሚደረግባቸው ክፍሎች ነበሩት፡፡ከእነዚህ ክፍሎች ውስጥ ከምንሰራው ስድስት ወጣቶች ውስጥ እኔ ብቻ ነኝ ወንድ አምስቱ ሴቶች ናቸው፡፡እኛ ሁሌም ቀን ቀን ነው የምንሰራው፡፡ ማታ ፈረቃ የሚሰሩር በሙሉ ሴቶች ናቸው፡፡ እያንዳንዳችን በቀን ወደ 25 የሚጠጉ ደንበኞችን እናስተናግዳለን፡፡የማታ ፈረቃ ሰራተኞች ደግሞ ከ25 በላይ የሚሆን ሰው ያስተናግዳሉ፡፡በቀላሉ 50 ሰዎች ቢያስተናግዱ ለአንድ ሰው ዝቅተኛው ከ500 ብር እስከ 1200 ብር ያስከፍላሉ፡፡ በትንሹ 500 ብር ቢያስከፍሉ በአንድ ቀን 25,000 ብር ያገኛሉ ማለት ነው፤በወር ደግሞ 750,000 ብር ያገኛሉ፡፡ለሰራተኞችና ለአንዳንድ ወጪዎች 250,000 ብር ቢያወጡ ወደ 500,000 ብር ያገኛሉ፡፡በዚህም ምክንያት ማሳጅ ቤቶች እጅግ በፈጣን ሁኔታ እየተስፋፋ ይገኛሉ ፡፡›
እንደዚህ ያለው ስራ በአብዛኛው ሀገር እጅግ በጣም የሚያዋጣ የስራ ዘርፍ ነው፡፡ እንደ ታይላንድ ያሉ ሀገሮች በወሲብ ንግድ በዓመት ውስጥ ወደ 4.3 ቢሊየን ዶላር ያገኛሉ ከወሲብ ንግድ ብቻ፡ ፡ ይህም ብዙ ሰዎች በእንደዚህ አይነት ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ እንደሆነ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡ በተመሳሳይ መልኩም በአሜሪካ በተደረገ አንድ ጥናት መሰረት ወሲባዊ ንግድ ወደሚፈጸምባቸው ማሳጅ ቤቶች ስራ እንዲሰማሩ ምክንያት ከሆናቸው አንዱ ህጋዊ ማሳጅ ሲሰሩ የሚያገኙት ገንዘብ ዝቅተኛና ስራው አድካሚ ስለሆነ ወሲባዊ ንግድ ላይ ቢሰማሩ ግን በቀላሉ በዛ ያለ ገንዘብ ስለሚያገኙ ወደዚህ ስራ ይገባሉ ይላል ጥናቱ፡፡
የችግሩ ስፋት
በማህበራዊ ስነልቦና ባለሙያዎቹ አቶ በላይነህ ዘለለውና አቶ ዮሴፍ አህመድ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ወሲባዊ ንግድ የሚፈጸምባቸው ማሳጅ ቤቶች በሴቶችና በወጣቶች ላይ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ስነ-ልቦናዊ እና የስነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮችን እንደሚያስከትሉ ያሳያል፡፡ በአንድ ማሳጅ ቤት ትሰራ የነበረች ወጣት ከስራው ጋር በተያያዘ ስለሚያጋጥማት ችግር ምንም አይነት ዋስትና እንደሌላት እንዲህ ስትል ታስረዳለች‹አገልግሎት ፈልጎ የሚመጣው ሰው በጣም የተለያየ ባህሪ ያለው ሰው ነው፡፡በዚህ ምክንያት ሁሉም የተለያየ ፍላጎት ስላለው፤አንዳንዱ ሰው ኮንዶም መጠቀም አይፈልግም፣ሌላው ደግሞ በፊንጢጣ የሚደረግ የግብረ ስጋ ግንኙነት ፈልጎ የሚመጣ አለ፡፡ ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ ግጭት የሚፈጠረው፡ ፡ በተለይም ማታ የሚመጡት ወንዶች አብዛኛዎቹ መጠጥ ጠጥተው ስለሚመጡ የጠየቁትን ወሲብ አይነት እንቢ ካልኳቸው በጉልበት ሊፈጽሙብኝ ይሞክራሉ፤ አንዳንድ ከውጭ የመጡ ኢትዮጵያውያን (ዲያስፖራ) ወሲባዊ ፍላጎታቸው የሚረካው እኔን በማሰቃየት፣በመምታት፣በመንከስ ስለሆነ የተለያየ ጊዜ አደጋ ደርሶብኝ ያውቃል፡፡ ግን ይህንን ችግር ለማን ትናገረዋለህ ለባለቤቱ ብትነግረው ቢዝነሱ እንዳይበላሽበት ስለሚፈልግ ለፖሊስ እንድንናገር አይፈልግም እንዲሁም ደንበኞችን ላለማጣት ሲል ምንም እርምጃ አይወስድም፡፡እኔ ተጎድቼ ብቻ ነው የምቀረው ብናገር ሊያባረኝ ስለምችል ዝም ነው የምለው፡፡ ›
እነዚህ ሴቶች ምንም አይነት ጥቃት ቢደርስባቸው ለህግ አስከባሪ አካላት ሄደው አይናገሩም፤ ምክንያቱም የሚሰሩት ስራ በማህበረሰብ የተወገዘና እራሳቸው እራሱ የማያምኑበት ስለሆነ ጉዳት ደረሰብኝ ብለው ለፖሊስ ሪፖርት አያደርጉም፡ ፡ይህ ደግሞ በእነሱ ላይ የሚደርሰውን የሀይል ጥቃት መጠን ለማወቅ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡የመፍትሄ እርምጃ እንዳይወሰድ ደብቆ ያስቀረዋል ከዚህም አልፎ በሴ ቶ ቹ ላይ የሚደርሰውን አካላዊና ስነ- ልቦናዊ ጉዳት ተገንዝቦ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ያስተጓጉለዋል› ይላል፡፡
ይህ የስነ-ልቦና ችግር በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀይማኖታዊና ወግ አጥባቂ ማህበረሰብ ባለበት እነዚህ ወጣቶችና ሴቶች ከፍተኛ ለሆነ ለስነ-ልቦና ችግር ይጋለጣሉ፡፡በዚህም ምክንያት ወደ ጫትና ሺሻ ቤቶች በመሄድ ሱስ አስያዥ ዕፅና አልኮል በመጠቀም ችግራቸውን ለመርሳት ይሞክራሉ፡፡
የመፍትሔ
እርምጃዎች
ጥናቱ የተለያዩ የመፍትሔ ርምጃዎችን በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ለማህበረሰቡ በቂ ግንዛቤ መፍጠር፣ ባለድርሻ አካላት በጋራ ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው፣ የተለያዩ የሀይማኖት ተቋማት ለተከታዮቻቸው ግንዛቤ መፍጠር እንዳለባቸው፣ ባለሀብቱ ኢንቨስትመንቱን ሀገር በሚጠቅም ነገር ላይ እንዲያውለው ተከታታይነት ያለው ትምህርት መሰጠት እንዳለበት፣ህጋዊ ማሳጅ ቤቶችን ማበረታታና ሌሎችም የመፍትሄ ሀሳቦች ተጨምረዋል፡፡ ባለድርሻ አካላት ተቀራርበው በመስራት እየተፈጠሩ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የጋራ እቅድ በማውጣት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ፤ ስነ-ልቦናዊ የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ከወሲባዊ ንግድ ከሚካሄድባቸው ማሳጅ ቤቶች ጋር ያላቸው ትስስር ጠንካራና ቀጥተኛ መሆኑንና እነዚህ ችግሮች አምራች የሆኑትን ትውልዶች ለሀገራቸው ማበርከት የሚጠበቅባቸውን እንዳያበረክቱ እያደረጋቸው እንደሆነ ጥናቱ አሳይቶል፡፡ በስተመጨረሻም በመጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች አሉታዊ ተፅዕኖ ምክንያት ላልተገቡ ባህሪያት እየተጋለጡ ያለውን ትውልድ ለመታደግ የተለያዩ እርምጃዎችን መወሰድ እንዳለበት ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
የተለያዩ የሀይማኖት ተቋማት ሰለወሲባዊ ንግድ አስነዋሪነትና መጥፎ ገጽታዎች ለተከታዮቻቸው በማስተማር ወጣቶችና ሴቶች ከእንዲዚህ አይነት ተግባር እንዲቆጠብ ትምህርት ቢሰጡ፣ ባለሀብቱ ማህበረሰብን የሚጎዱ ተግባራት ላይ ኢንቨስት እንዳያደርግና ሴቶችንና ወጣቶችን ዘለቀታዊ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ግንዛቤ መፍጠር ስራዎችን ማከናወን ይኖርበታል:: ለማሳጅ ቤት ባለቤትቶች ህጋዊ ሆነው ለህብረተሰብ ተገቢውን ማሳጅ አገልግሎት እንዲሰጡ በየጊዜ ትምህራታዊ ስልጠና መስጠት ያስፈልጋል :: በህጋዊነት እና የማሰጅን ስነምግባር ጠብቀው የሚሰሩ ማሳጅ ቤቶችን የተለየ ደጋፍ እና እረዳታ በደረግላቸው በቀላሉ ከገበያው የማይወጡ ይሆናሉ፡፡ ትምህርት ቤቶች አካባቢ የተከፈቱ እንዲሁም መኖሪያ አካባቢ የተከፈቱ የወሲብ ንግድ የሚፈጸምባቸው ማሳጅ ቤቶች በቶሎ ካካባቢው ቢነሱ እና በቦታው ለሌሎች የማህበረሰብን የእለት ተእለት እንቅስቃሴ የማያውክ ተግባረት የሚፈፀምባቸው በሆኑ ሀገርም ህብረተሰብንም የሚጠቅም ይሆናል :: ቤተሰብና ትምህርት ቤት በጋራበመጣመርየልጆቻቸውንናየተማሪዎቻቸውን ውሎ በቅርብ ሆነው መከታተል አለባቸው፡፡ በተለያዩ ጊዜ የልጆቹን ሁኔታ ለመገምገም ወላጅና ትምህርት ቤት በጋራ በመዋያየት የሚታዩ ችግሮችን
በእንጭጩ ለመቅጨት ይረዳቸዋል፡:
ይህ ዘገባ ቁምነገር መጽሄት ላይ ታትሞ የወጣ ነው::
The post የአዲስ አበባ ጉዶች: በማሳጅ ስም የወሲብ ገበያ ደርቷል * ኢትዮጵያ የወሲብ ቱሪዝም ‹ማግኔት› በሚል በውጭ ሚድያዎች መጠራት ጀምራለች (ልዩ ዘገባ) appeared first on Zehabesha Amharic.