ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
nigatuasteraye@gmail.com
ጥር ፲፩ ፳፻፯ ዓ.ም.
ታህሳስ 19 ቀን በቅዱስ ገብርኤል ስም የሚታሰበው በዓል፤ እግዚአብሔር ሥነ ባህርይን
(ሞራልን) እንዲያከብር ቅዱስ ገብርኤልን የላከበት ቀን ነው።
ማሳሰቢያ፦ በቅዱስ ገብርኤል ስም በየስርቻው ቤተ ክርስቲያን ከፍተው ህዝብን በመዝረፍ ላይ የሚገኙት ብዙዎቹ “ቅዱስ ገብርኤል ተከበረ እንጅ አከበረ” የሚለውን ሰምተውት ስለማያውቁ፤ “ቅዱስ ገብርኤል አይከበር አለ” እያሉ፤ አንብበው ከእውነቱ መድረስ የማይችሉትን አንዳንድ የዋሆችን ውዥንብር ውስጥ መክተታቸው አይቀርም። እኔ ኢትዮጵያን በመምራት ያሉ ፖለቲከኞችና በየስርቻው ቤተ ክርስቲያን የሚከፍቱትን የአስመሳይ ነጋዴዎች ባህርይ፤ አባቶች ስለበዓሉ አላማና ምክንያት ካስተማሩኝ ጋራ ሳንጻጽረው፤ ቅዱስ ገብርኤል ካከበረበት ምክንያትና ዓላማ ጋራ ምንም ግንኙነት እንደሌለው ገለጽኩ እንጅ ቅዱስ ገብርኤልማ ክብር ይገባዋል ።
መግቢያ:
ታሕሳስ 19 አስርቱ ቃላት የተጻበት ጽላት ከመንበሩ የሚንቀሳቀሰው ቅዱስ ገብርኤል ያከበረውን ሥነ ባህርይ (ሞራል) በቅርብና በሩቅ ላለ ሁሉ ለማንጸባረቅ ነው። ይሁን እንጅ ይህን ማስተጋባት የሚጠበቅባቸው መንፈሳውያን መሪዎችም ሆኑ ዓለማውያን መሪዎች በዚያ ወቅት በአገርና በወገን የፈጸሙት በደልና ግፍ፤ ለተከበረው በዓል ተቃራኒ ነበር።
1. የባህርዳርነዋሪህዝብለታቦትማንገሻየምንገለገልበትንአውደምህረትወደሌላአገልግሎት ልታውሉብን አይገባም አሉ። ወያኔ ግን ደበደባቸው፣ አሰራቸው ገደላቸው። ተብሎ በይፋ ተነገረ።
2. ህዝቡ ለጥምቀት ሰማያዊ ቀለም ያለው ቲሸርት መልበስ ፈለገ። ወያኔ እንዳይለብሱ ከለከላቸው ተብሎ በይፋ ተነገረ።
3. ወያኔም በሕዝብ ላይ የፈጸመውን በደል አስተባብሎ አቀረበ። ”ያካባቢው ብዙዎች ካህናት ወያኔ ከደበደበው፣ ካሰረውና ከገደለው ህዝብ ጎን መቆም ሲገባቸው፤ ከወያኔ ጋራ ተስማምተው በመቆም የወያኔን ሸፍጥ አስተጋቡ“ ተብሎ በይፋ ተነገረ።
እነዚህ ነገሮች የተፈጸሙበት ወቅት፤ ቅዱስ ገብርኤል ሥነ ባህርይ (ሞራል) ያከበረበት ወቅት ነበር። በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለምሳሌ: በደብረ ማርቆስ፤ በወልቃይት ጠገዴ፤ በቤኒሻንጉል፤ በአርማጮ፤ በዑጋዴን ወገን በከንቱ ተገደለ የሚል ድምጽና ዋይታም ተሰማ። በዚሁ ወቅት “ሥነ ባህርይ (ሞራል) ክብር የምናስታውስብተን አውደ ምህረት ለሌላ ጉዳይ ልታውሉብን አይገባም” ብሎ የተሰለፈውን ህዝብ መምራትና መደገፍ የሚገባቸው ያካባቢው ጳጳስና ከካህናት ብዙዎች ወያኔ የፈጸመውን ግፍ ደግፈው ህዝቡን ጥፋተኛ አድርገው ካቀረቡ በኋላ፤ በዓሉን አከበርን ማለታቸው፤ ከመስመራቸው ውጭ አደረጋቸው። ከዚህ በታች በዘረዘርኳቸው አንቀጾች ከተሰለፉበት ተልእኮ ጋራ መጋጨታቸውን ለመግለጽ እሞክራለሁ።
❖ ፩ኛ. የበዓሉ ምክንያትና ዓላማ በጉባዔው ትምህርት
❖ ፪ኛ. ቅዱስ ገብርኤል ያከበረው ሥነ ባህርይ ከማለም ባሻገር፤ የተሰወረ ሕልም ፈች ብልጥ ያደርጋል።
❖ ፫ኛ. ወያኔ ሊደመስሳቸው የሞከራቸው፤ ያባቶች ህልም የተመሰረተባቸው፤ ኢትዮጵያውያን
የተወሀድንባቸው 4 መንገዶች
❖ ፬ኛ. ለጥምቀት ሰማያዊ ቀለም ያለው ቲሸርት ባለመልበስ የሚጎድል ነገር የለም።
፩ኛ. የበዓሉ ምክንያትና ዓላማ በጉባዔው ትምህርት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት መጻሕፍትን የሚተረጉሙበት ስልት አንድምታ ይባላል። አንድምታ ማለትም፤ “ይህም አለ። ያም አለ። እንዲህም ይባላል። እንዲያም ይባላል” ለማለት ንጽጽር (comparative) ነው። የበዓሉን ታሪክ በተሸከመው በዳንኤል መጽሐፍ፦
➔ 1ኛ “ብረቱን፤ ናሱን፤ ሸክላውን ብሩንና ወርቁን የሰው እጅ ሳይነካው ከተራራ ወርዶ አደቀቃቸው” (2 ፡ 45) ተብሎ የተገልጸውን ድንጋይ
➔ 2ኛ “ግዛቱ የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው። መንግሥቱም የማይጠፋ ነው”(7፡14)የተባለውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ለክርስቶስ ብቻ ከመስጠት በቅር፤ ቅዱስ ገብርኤል ባከበረው ሥነ ባህርይ ዙሪያ ያለውን ታሪክ፤ እንደ ሌሎች መተርጉማን በሮም፣ በባቢሎን፣ በፋርስና በግሪክ መንግሥታት ብቻ አይወስኑትም። አሁንም በየዘመናት የሚነሱትን የመንግስታትንና በነሱ ዙሪያ ተኮልኩለው በታላላቅ ወንበር ለይ የተቀመጡትን የሥነ ባህርይ ጉድለትና ብርታት ይለኩበታል።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “ትእቢተኞችን በትኗል። ገዥዎችን ከዙፋናቸውም አዋርዷል። ትሁታንንም ከፍ አድርጓል። የተራቡትን ከበረከቱ አጥግቧል። ባለጠጎችን ባዷቸውን ሰዷቸዋል”(ሉቃ 1፡5153) ብላ የተናገረችውንም፤ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት “ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል። መንግስታትን ያፈልሳል። ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ላስተዋዮች ይሰጣል” (2፡21) ከሚለው ጋራ ተፈጻጻሚ እንደሆነ ይናገራሉ። የዳንዔልን ንግግር ከእመቤታችን ንግግር ጋራ በማዛመድ፤ የክርስቶስ መንግሥት ሁሉንም እንዳልነበሩ እስኪያደርጋቸው ድረስ ይቀጥላል ብለው ስለሚያምኑ፤ ያፋችን መፍቻ በማድረግ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በቃላችን እንድንይዘው አደረጉ። በግልም፣ በማህበርም በየእለቱ እንዲደገም ስርዓት ሰሩ።
ታሪኩ ከዘመነ ሥጋዌ አምስት ምዕት ዓመታት በፊት በባቢሎን አገር የተፈጸመ ነው። በዚያ ዘመን የባቢሎን መንግሥት እንደ አሜሪካ ጥገኝነት ቢቅፈድና ሁሉም በችሎታው በእውቀቱ ለመኖር ሰፊ እድል ቢሰጥም፤ ሁሉም የፈለገውን እያመለከ ባህሉን እየጠበቀ እንዲኖር አሜሪካ የሰጠውን ዓይነት ነጻነት የናቡከደነጾር መንግሥት አልፈቀደም።
ድርጊቱ በተፈጸመበት አገር በምርኮ ይኖሩ የነበሩት ዳንዔልና ሶስት ወጣቶች፤ ከሆዳምነት ከፍርሀት ከጥርጥር የራቁ፤ ከመንግሥት አካባቢ በሚዘጋጁት በጥቅማ ጥቅም ንክኪ ላለመርከስ የወሰኑ የእምነትና የሥነ ባህርይ (ሞራል) ሰዎች ነበሩ (ዳን 1፡8)። እምነታቸውን ባህላቸውን ለቀው፤ የሚኖሩበትን ሃይማኖትና ባህል እንዲከተሉ በናቡከደነጾር ተገደዱ። እነሱ ግን “አምላካችን ያድነናል። ባያድነንም አንተ ላቆምከው ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ” ብለው መለሱ። በሥነ ባህርይ (ሞራል) ጽናታቸው “በጥበብና በማስተዋል በአገሪቱ ዙሪያ አሉ ከሚባሉት ምሁራን
ሊቃውንት አሥር እጅ የላቁ ሆነው ተገኙ”። (20)። የራሱ ህልም የጠፋበት ናቡከደነጾር በአካባቢያው አሉ ለሚባሉት ምሁራን ሊቃውንት ነን ለሚሉ ለሆዳሞችና ላስመሳዮች ህልሜን ከነትርጉሙ ካላመጣችሁ ትገደላላችሁ ብሎ ቀጭን ትእዛዘ ሰጠ (ዳን 2: 5) ። በዚህ ቀውጢ ሰአት እነዚህ የሥነ ባህርይ (ሞራል) ሰዎች ተገኙ።
እምነታችሁን ሞራላችሁን ልቀቁ ባትለቁ ወደሚንበለበለው እሳት ትጣላላችሁ የሚያድናችሁ የለም። (ዳን 3፡15)ተባሉ። እነሱ ግን “አምላካችን ያድነናል። ባያድነንም አንተ ላቆምከው ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ” የሚል ያሰፈሪውን የናቡከደነጾርን ትእዛዝ በትእዛዛቸው ሻሩት”(3፡18 19)። ባያድነንም”የምትለው ሁለተኛዋ ቃላቸው፤ ዋሽተው መስለው ረክሰው በዚህ ዓለም ከመኖር ይልቅ፤ ለሞራላቸው ሞትን በመምረጥ ገናናውን ናቡከደነጾር አስገረሙት። ለአምላካቸውም አምበረከኩት። የበዓሉ ምክንያትና ዓለማ ይህን ማንፀባረቅ ነው ። አዕምሯቸውን ባብነቱ ቅኔ አበልጽገው፤ ባንድምታው ትርጔሜ የሚዋኙ፤ አካባባያቸውን የታዘቡ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት “ልቡ ለጻድቅ ወኩሉ ከመ አንበሳ”(ተግሳጽ 4፡1)ብሎ ሰሎሞን የተናገረውን መንደርደሪያ በማድረግ፤ “በሶስቱ ወጣቶች የተንጸባረቀውን እምነትና ሥነ ባህርይ (ሞራል) እንዲያከብር እግዚአብሔር ቅዱስ ገብርኤልን ላከ” ይላሉ።
፪ኛ. ቅዱስ ገብርኤል ያከበረው ሥነ ባህርይ ከማለም ባሻገር፤ የተሰወረ ሕልም ፈች ብልጥ ያደርጋል።
ናቡከደነጾር ያለመው ህልም ጠፋበት፤ በዙሪያው የነበሩትም ሥነ ባህርይ የሌላቸው የሲኖዶስ አባል ነን እንደሚሉ እንደ እነ አባፋኑኤልና፤ አባ ፋኑኤል ያቆሞሷቸውን ፈቶችን የመሳሰሉ ነበሩ። የነ አባ ፋኑኤልን ሁኔታ መረዳት ከፈለጉ አባ ፋኑኤል ያቆሞሷቸውን ፈቶችን የመሳሰሉ ነበሩ የሚለውን ይጫኑ። ህልሙ ከተሰወረበት ከናቡከደነጾር በታች የወደቁ ነበሩ። የሥነ ባህርይ ሰዎች የተሰወረውን ህልምና ትርጉም ይዘው ብቅ አሉ። ከመካከላቸው አንዱን ዳንኤልን ናቡከደነጾር “ብልጣሶር” ብሎ ሰየመው። ጎዳና ለሚባለው የቅኔ ዓይነት ሊቅ፤ የደብረ ሊባኖሱ የኔታ አምዴ፤ ሰምን ግሥ በሚያደርገው ጎዳና ቅኔያቸው፤ ብልጣሶር የሚለውን ቃል፤ “አዋቂ ሆነ” ወደ ሚል ግሥ በመለወጥ የዘረፉትን ቅኔ አስታውሳለሁ። የዘረፉትን ቅኔ ሲያመሠጥሩም “ብልጥ” የምትለው አማረኛ ቅጽል የብልጣሶር ከፊል እንደሆነች የተናገሩትም ትዝ ይለኛል።
የኔታ አምዴ ከሳቸው በፊት ከነበሩ ከጥንታውያን ሊቃውንት አበው ስለበዓሉ ከገለጹባቸው ቅኔዎች ለምሳሌ ያህል አንዱን እጠቅሳለሁ። ይህ ቅኔ የሥነ ባህርይ (ሞራል) ልዕልና የሚያተርፈውን ክብር። የሥነ ባህርይ (ሞራል) ውድቀት የሚስከትለውን ውርደት ያንጸባርቃል። ቅዱስ ገብርኤል ይህንን ለማክበር እንደተላከ ይገልጻል። ቅኔው ከዚህ በታች ያለው ነው።
“በባቢሎን አመ ተሠርዐ፤ መስዋዕተ ገሞራ ነደ እሳት፤ እሳታውያን ደቂቅ ለኪፎቶ ዝንቱ ኢክህሉ። እሳት አማጣነ በላኢ ወመፍርህ ለኩሉ።
ላእካነ ባቢሎን ህዝብ ባህቱ አመ በእከይ ወዐሉ።
መቅሰፍቶሙ በልኡ ወተካፈሉ።
ላእከ ቤተ መቅደስ ገብርኤል ጊዜ በአሉ። እስመ ሠርዐ እሳተ ለኩሉ።”
ወደ ድርብርብ ጽንሰ ምሥጢሩ ሳንገባ፤ ቅኔው በቁሙ ሲተረጎም፦ ሥነ ባህርይን ለማክበር፤ የሥነ ባህርይን ጉድለት ለመደምሰስ በባቢሎን እሳታዊ ሚዛን በተዘረጋ ጊዜ፤ እሳታውያን ወጣቶችን የእሳቱ ነበልባል ሊበላቸው ይቅርና በእሳቱ ላይ የበለጠ እሳት ሆኑ። በነሱ ላይ የነደደው እሳት ሥነ ባህርይ የሌላቸውን በላቸው። ገብርኤል ይህን ድንቅ ሥነ ባህርይ (ሞራል) ለማክበር ተላከ። ማለት ነው።
የሊቁ ቅኔ የሚያንጸባርቀው “አምላካችን ከሞት ባያድነንም፤ ለእምነታችን፤ ለህሊናችን፤ ለቃላችን፤ ለባህላችንና ለታሪካችን እንሞታለን ብለው የወሰዱትን ቆራጥ ውሳኔ ነበር። ሶስቱ ወጣቶች በተማረኩበት አገር የማረካቸውን የናቡከደንጾርን አዋጅ ገሰሱ። “ባያድነንም እሳቱ ይብላን” ብለው እሳቱ ውስጥ ገቡ። እሳቱ በሰውነታቸው ላይ የሚፈስስ ወደ ወርቅ ጎርፍነት ተለወጠ። በወርቅ በብርና በዓልማዝ ፈርጥ የተንቆጠቆጠ የክብር ጌጥ ሆነላቸው። ከሰውነታቸው ሙቀት ጋራ ተስማማ፣ ተመቻቸው፣ ሞቃቸው። የራስ ወርቅ፤ የውርቅ ጫማ ሆነላቸው። እነሱን ወደ እሳቱ የወረወሯቸውን ሞራለ ቢሶችን እንደ ማግኔት እየጎተተ በመሳብ በላቸው። ሶስቱ ወጣቶች የናቡከደነጾርን ጭንቅላት ተቆጣጠሩት። የራሱን አምልኮ አስለቅቀው ለአምላካቻው አምበረከኩት (ዳን 3 2830)። የቅኔ መምህራን የነ ሲድራቅን ሥነ ባህርይ (ሞራል) ሰም፤ የበላይ ዘለቀን ሥነ ባህርይ (ሞራል) ወርቅ፤ በማድረግ የዘረፉትን ቅኔ ተቀብያለሁ። እራሴም ቆጥሬ ነግሬበታለሁ።
“አምላካችን ያድነናል። ባያድነንም አንተ ላቆምከው ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ” ብለው ናቡከደነጾርን ሳይፈሩ ለእምነታቸውና ለሞራላቸው የበለጠ ክብር እንደሰጡ፤ በላይ ዘለቀም በመከራ በፈታኝ ጊዜ ለሞራሉ ክብር ለወሰደው ቆራጥ ርማጃ ሲቀኙለት የኖሩት የቅኔ መምህራን ብቻ አይደሉም። ክብረት በላይን የመሳሰሉ የዘመናችን አዘማሪዎችም፦
“ጀግንነት ወንድነት ለትውልድ አውርሶ
አለፈ ያ ጀግና የልቡን አድርሶ” እያሉ ለበላይ ዘለቀ ክብርና ልዕልና በመዘመር ላይ ናቸው።
ሳይፈሩ ሳያፍሩ “አምላካችን ያድነናል። ባያድነንም አንተ ላቆምከው ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ” በማለት ናቡከደነጾርን ሰለሰቱ ደቂቅ እንደተፋለሙት፤ በላይ ዘለቀም ሞሶለኒን ሳይፈራ ተፋለም። ክብረት በላይ
“የበረሀው ዳኛ የጫካው ንጉሥ፤
በላይ ሰው አይፈራም ያለ ክርስቶስ” እያለ በማዘመር ለበላይ ዘለቀ አንጸባረቀው። ሙሉውን ለማየት የሚቀጥለውን ሰንሰለት ይጫኑ። [ ክብረት በላይ ለበላይ ዘለቀ ሥነ ባሕርይ ልዕልና የዘመረለት ውዳሴ ]
አባቶቻችን በሰሩልን፤ በያመቱ በሚታወሰው ቅዱስ ገብርኤል ባከበረው ሥነ ባህርይ ሚዛን፤ ኢትዮጵያን በመምራት ላይ ያሉትን ብዙዎችን መንፈሳውያን መሪዎችን እና ወያኔዎችን ባንድ ረድፍ፤ በኢትዮጵያ ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጭ በማፈለም ላያ ያሉትን የኢትዮጵያ ልጆች ደግሞ በሌላ ረድፍ ስንመዝናቸው፦ ወያኔ በወገን ላይ የሚፈጽመው በደልና ግፍ ፤ ናበከደነጾር ከፈጸመው ግፍና በደል እጅግ የከፋ ነው። በወያኔ ላይ የሚደርሰው ቅጣትም፤ በናቡከደነጾር ላይ ከደረሰው እጽፍ ድርብ የከበደ ቅጣት የሚጠብቀው ይመስላል። ”ናቡከደነጾር በህዝብ ላይ የሚፈጽመውን በደል ትቶ ትክክለኛ የሆነውን ባለማድረጉ ክፋትን ትቶ ለተበደሉት ለተጨቆኑት ቸርነት ባለማድረጉ (4፡27)“እንደከብት ሳረ በላ ሆነ። የራሱ ጸጉር እንደንስር ላባ፤ ጥፍሮቹ እንደ ወፍ ጥፍር ሆኑ። በራሱ በደልና ኃጢአት ረግረግ ውስጥ ሰመጠ”(4፡33)እንደዚሁ ሁሉ፤ወያኔም በህዝብ ላይ በሚፈጽመው ደባ ወደ እመቀእመቃት በመስመጥ ላይ እንዳለ በሰፊው እየተነገረ ነው።
የወያኔ መንግሥት ሊቃውንት ብሎ በታላላቅ ማእረግ ላይ የሰየማቸው በናቡከደነጾር ዙሪያ እንደነበሩት ህልም መፍታት ማስታወቅ ያቃታቸው የሚቆረጡ ምቱርራን ሆኑ። (ዳን 2፡5)በዙሪያው ያሉት ምሁራን ጸሀፊዎች ጋዜጠኞች ነን የሚሉ ሁሉ በአገሪቱ ካሉት ሁሉ አዋቂዎች በሥነ ባህርይ (ሞራል) በጥበብ በማስተዋል አሥር እጅ በልጠው መገኘት (1፡20) ሲገባቸው፤ የህልም ምሥጢር ሊተረጉሙ ቀርቶ፤ በሞተው ባቶ መለሰ ህልም ተደናባሪና ህዝብ አደናባሪዎች ሆኑ።
ያየውን ህልም ረስቶ ህልሜን ከነትርጉም ንገሩኝ ካለው ከናቡከደነጾር ወያኔ እጅግ በጣም ተንኮታኩቶ ወደቀ። ናቡከደነጾር የሰጠው ትእዛዝ ፤ ከሱ በፊትና ከሱ በኋ ያሉ መሪዎች ያላደረጉትን እስካሁን ተሰምቶና ተደረጎ የማይታወቅ የጠፋብኝን ህልሜን ከነትርጉሙ ውለዷት የሚል የእብድ ትእዛዝ ነበር። የራሱን ህልም ከረሳው ከናቡከደነጾር ወያኔን የባሰ የሚያደርገው፤ ህልሜን ከነትርጉም ንገሩኝ አለማለቱ ብቻ አይደለም። ያቦቶቻችን ህልም የተመሰረተበትን የ ኢትዮጵያውነትን ህልም ሆን ብሎ እየደመሰሰ መምጣቱ ነው።
፫ኛ. ወያኔ ሊደመስሳቸው የሞከራቸው፤ ያባቶች ህልም የተመሰረተባቸው፤ ኢትዮጵያውያን የተወሀድንባቸው 4 መንገዶች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አባቶች እንደሚገልጹት የኢትዮጵያዊነት ህልም የተመሰረተባቸው ወያኔ የደመሰሳቸው አራት መንገዶች ናቸው።
● 1ኛ “ከ8ኛው ክፍለ ዘመን በፊት አክሱም የሰው ዘር መናሀሪያ ነበረች። ከጎረቤት አገሮች ከየመን ከግብጽ ከእስራኤል ከመካከለኛውና ከሩቅ ምስራቅ አገሮች ወደ አኩስም ከተማ ለንግድና፤ ከተማዋ ያፈራችውን ስልጣኔን ለመካፈል፤ በተለያዩ ምክንያያቶች ብዙ የተለያዩ የሰው ዘሮች ይጣለፉባት ነበር። በዚያ ወቅት በዚህ ሁኔታ ከየአቅጣጫዎች የተሰበሰቡ ሁሉ ተዋልደዋል። ተቀላቅለዋል።ተቀይጠዋል። አንድ ሆነዋል።
● 2ኛ: የተቀየጠው ህዝብ የሚኖርባትን የአኩስምን ከተማ በስምንተኛው ክፍለ ዘመን ዮዲት ስታፈርሳት፤ ከሞት የተረፈው ህዝብ ወደ መሀል ኢትዮጵያና ወደ ጠረፍ ወደ ባሌ፣ አሩሲ፣ ሀረር ድረስ ተበትኖ ካካባቢው ህዝብ ጋራ ተቀላቀለ። ተዋለደ በደም ባጥንት አንድ ሆነ።
● 3ኛ፦ በ12ኛ ክፍለ ዘመን ከምሥራቅ ኢትዮጵያ የተነሳው ግራኝ መሀመድ በዮዲት ወረራ ምክንያት በመላ ኢትዮጵያ ተበትኖ በየደረሰበት ትዳር እየያዘ ንብረት እያፈራ ኑሮ የጀመረውን ህዝብ ሠራዊት አድርጎ፤ ወደ መሀል ኢትዮጵያ እና ወደ ሰሜኑ ጠረፍ በማዝመት እንደገና መለሰው። ይህም ማለት ወደ ቅድመ አያቱ ቦታ በዘመቻ መልክ ተመለሰ ማለት ነው።
● 4ኛ፦እርሱ በርሱ እየተዋደደ እየተስማማ በመጋባት ተዋልዷል። ሆኖም በፍጥነት ከሚገናኙባቸው ቦታወች ራቅ ብለው ለብዙ ዘመን የቆዩት ወገኖች ያካባቢውን ቋንቌ በመናገርና በወንዝና በሸንተረር ቢወሰኑም።በሶስቱ መንገዶች ሳይቀላቀሉ ያመለጡ ምንም የደም ንክኪ የሌላቸው አይደሉም።
ጌታችን በወንጌሉ “ከኔ ጋራ ያልሆነ ጠላት ይበትነኛል” እንዳለው። ከህዝብ ጋራ ዝምድና የሌለው ጠላት፤ ህዝብ ይበትናል እንጅ አይሰበስብም። ህዝብ መበተን የሥነ ባህርይ ጉድለት ነው። የህዝብ አንድነት የኃይል ነው። የሥነ ልቡና ጉድለት ያለው ቅኝ ገዥ ነው። ቅኝ ግዛትን የሚወድ ደግሞ የአዕምሮ በሽታ ያጠቃው ነው። በዚህ ዓይነት በሽታ የተጠቃው ወያኔ ያቦቶች ስነ ልቡና የተመሰረተበትን ህዝቡ በደምና በአጥንት የተሳሰረበትን ህብረት እያፈረሰ መጣ።
በናቡከደነጾር ላይ የደረሰው መከራ “እንደከብት ሳረ በላ ” በመሆን በራሱ ላይ የቆመ አልነበረም። “የራሱ ጸጉር እንደንስር ላባ፤ ጥፍሮቹ እንደ ወፍ ጥፍር ሆነ”(4፡33። እንደተባለ፤ ወያኔ ኢትዮጵያን የሰነጠቀበት፤ የህዝቡን ገላ የሚቧጥጥባቸው ኃያላን መስለው የሚታዩ ኢትዮጵያውያንን በመደብደብ ላይ ያሉ ወታደሮች ጥፍሮቹ ናቸው። እነዚህ እንድንስር ላባ በነው ያልቃሉ። በዓሉ የሚነግረን ይህንን ነው።
የአባቶች ስነ ልቡና የተመሰረተበትን ህብረት እያፈረሰ የመጣውን፤ ባካባቢው ያሉት “ዘመናት ይለወጣሉ መንግስትም ያልፋል። ጥበብን ለጠቢባን እውቀትን ላስተዋዮች ይሰጣል”(2 ፡21)እያሉ መገሰጽ ሲኖርባቸው፤ በህልም አልባነቱ ተጨንቆ ህዝቡን በማስጨነቅ ላይ፤ መንፈሱም ታውኮ ህዝቡን በማወክ መኖሪያውን በማፍረስ ላይ ካለው ከወያን ጋራ ተባበሩ ። በናቡከደነጾር ዙሪያ የነበሩት “ህልሙን ከነፍቹ ባታሳውቁ ትቆረጣላችሁ። ቤቶቻችሁም የጉድፍ መጥያ ይሆናሉ” (2፡5)። እንደተባሉ፤ ህዝቡ ለስለት የሰጠውን ገንዘብ እየዘረፉ ንብረት ቤት የገነቡ በወያኔ ዙሪያ ያሉ ሆዳሞች ስግብግብ አስመሳይ ጳጳሳት ቆሞሳት ቀሳውስትና የሰንበት መምህራን የከፋ ፍርድ ይጠብቃቸዋል። ከበዓሉ እንደምንረዳው ከዚህ አይነት መከራ ተርፈው ሌላውን ማትረፍ የሚችሉት “ምህረትን ከሰማይ አምላክ የሚለምኑ”(ዳን 2፡18)የሥነ ባህርይ (ሞራል) ሰዎች ብቻ ናቸው። “ለጥምቀት ሰማያዊ ቀለም ያለው ቲሸርት እንዳንለበስ ወያኔ ከለከለን” የሚሉ ወገኖችም ያባቶቻቸውን ሥነ ባህርይ (ሞራል) እያንጸባርቀ ለረዥም ዘመን የኖረውን ቅዱስ ገብርኤል ያከበረውን ሥነ ባህርይ ማስተጋባት አያቁሙ እንጅ፤ ሰማያዊ ቀለም ያለው ቲሸርት ባለመልበሳቸው የሚጎድልባቸው ነገር እንደሌለ በዚህ አጋጣሚ ሊገነዘቡ ይገባቸዋል።
፬ኛ. ለጥምቀት ሰማያዊ ቀለም ያለው ቲሸርት ባለመልበስ የሚጎድል ነገር የለም።
የዚህ መንግሥት ተሳታፊዎች አንድነትን እያፈረሱ ባንዲራ እያቃጠሉ በኢትዮጵያ ላይ የመጡባት ጠላቶች ናቸው። መሪዎቻቸው ወደ አገራችን ሰርገው በገቡ፤ Only Jesus (ኢየሱስ ብቻ) በመሳሰሉ ሰባኪዎች ኢትዮጵያዊነታቸውን ከጭንቅላታቸው የታጠበባቸው ናቸው። እነዚህ ሰዎች ለጥምቀት ሰማያዊ ቀለም ያለው ቲሸርት መልበስ ቢከለክሉ የሚያስገርም አይደለም። ይልቁንስ ቅዱስ ገብርኤል ያከበረውንም ሆነ በጥምቀት በዓል የሚከበረውን በዓል ወደ መከልከሉ ደረጃ እንዳይደርሱ ጠንክሮ ለመታገል መዘጋጀት ነው። ጥምቀት ክርስቶስ ጽድቅን የፈጸመበት፤ ነፍሰ ገዳዮችን አረመኔዎችን “ከህገ አራዊት ተላቀቁ!ከህገ አረሚ ውጡ!እያልን የምናውጅበት፤ ስነባህርይ የጎደላቸውን የምንዋጋበት መሳሪያችን ነው።

ታላላቅ መንፈሳውያን በዓሎቻችን ”አምላካችን ያድነናል። ባያድነንም ለሆዳችን በመገዛት ከረከሰው መንግሥት ጋራ በመርከስ በዚህ ዓለም ከመኖር ይልቅ፤ ለስነ ባህርያችን መሞት ይሻለናል” እያሉ አባቶቻችን ኢትዮጵያውያን፤ ከገረቤቶቿና ከቀረው ዓለማት ልዩ አድርገው ነጻነቷንና ክብሯን የጠበቁባቸው ሥነ ባህርይ፤ በትውልዱ ልቡና መቀረጽ ያለባቸው ናቸው። Only Jesus (ኢየሱስ ብቻ) የመሳሰሉ ሰባኪዎች፤ ከኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የበለጠ የነገረ መለኮት እውቀት እንዳላቸው በመምሰል፤ “ከክርስትና ጋራ ምን አገናኛቸው“ እያሉ የሰበኴቸው ወገኖች” “እኛ ምን አገባን” እያሉ እየነቀፉ እየተቹ እየናቁ እያጥላሉ ያልተገነዘባቸውን ወገን በመስበክ ላይ ናቸው። ይህን ስርአት የዘረጉት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ወራሪዎች የሚሉትን ሳያውቁ ቀርተው አይደለም። ከወያኔ መንግሥት ጋራ በመተባበር፤ ተንቀሳቃሽ ያልሆኑትን ንብረቶች በማቃጠል፤ በመቅበርና በመናድ፤ ተነቀሳቃሽ የሆኑትን ቅርሶች በመሸጥ ላይ ናቸው። የዋሀን ጥቂት ወገኖቻችንን ከቋንቋቸው ከቀለማቸውና ከስማቸው በቀር ልባቸውንና ጭንቅላታቸውን አጥበው ባዶ ቀፎ በማድረግ እዚህ ውዥንብር ውስጥ ኢትዮጵያን ከተዋታል።
ይህን የተባበረ አፍራሽ ኃይል መቋቋምና ማሸነፍ የሚቻለው፤ ለጥምቀት እለት ሰማያዊ ቀለም ያለው ቲሸርት በመልበስ አይመስለኝም። “የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውን ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም”(ሮሜ 10፡3)። እንዳለው፤ ጠላት በቀላሉ የሚመታቸውን ሰማያዊ ቀለም ያለው ቲሸርት የመሳሰሉትን በህዝቡ ደም ያልገቡትን ነገሮች ከመፍጠር ይልቅ፤ አባቶቻችን በእግዚአብሔር ጽድቅ በመሰረቱት ሥነ ባህርይ (ሞራል) ኢትዮጵያዊነትን ጠብቀው ያቆዩበትን ስርአት ወደ መሰረታዊ ትርጉሙ መልሰን በትውልዱ ጭንቅላት ሰርጾ እንዲገባ በማድረግ ብቻ ነው። ኢትዮጵያን ጠብቀው ያስረከቡን ዳዊት ደጋሜ የነበሩ አባቶች፤ ራሱን ዳዊትን እንደ ምሳሌ ይጠቅሱታል። ዳዊት ሳኦልን ታግሎ ያሸነፈው ከስነ ባህርዩ ጋራ በተዛመደለት በእጁ በነበረው ወንጭፍ ነበር (1 ሳሙ 17፡50)። እንደዚሁ ሁሉ፤ አገርን ወገንን እምነትን ለማዳን የሚያስፈልገው ሰማያዊ ቀለም ያለው ቲሸርት በመልበስ ሳይሆን፤ ከላይ እንደገለጽኩት ተጠብቀው በቀዩት ዓበይት በዓላት በሚንጸባርቁት ሥነ ባህርይ (ሞራል) ነው።
እንደ ሰለስቱ ደቂቂ ከሆዳምነት ከግል ጥቅምና ሥነ ምግባሩ ከረከሰበት መንግስት ንኪክ ከመርከስ ህሊና ማራቅ ነው። “ላቆምከው ምስል እንደማንሰግድ እወቅ”(3 ፡18 )ብለው ሶስቱ ወጣቶች ናቡከደነጾርን እንዳበረከኩት፤ እግዚአብሔር ይመስገን!ዛሬም የቀደሙ ኢትዮጵያውያን አባቶቻቸውን ምሳሌ በመከተል፤ ለጥምቀት ሰማያዊ ቀለም ያለው ቲሸርት እንዳይለብሱ የተከለከሉ ወጣቶች፤ ከወያኔ ንክኪ ላለመርከስ እራሳቸውን ጠብቀው በያሉበት እየታገሉ ናቸው። ወያኔ ባነደደው እሳት(እስር ቤቶች)የገቡ፤ የሚደበደቡ የሚገረፉ ሁሉ እግዚአብሔር ስነ ልቡና አክባሪ የሆነውን ቅዱስ ገብርኤል በመላክ ሰውነታቸው ከሚችለው በላይ እንደማያደርግባቸው እናምናለን።
በኢትዮጵያ፡ በኢሮፕ፡ ባሜሪካ፡ በከናዳ በዓለም ዙሪያ ተበትናችሁ ወያኔን በመታገል ላይ ያላችሁ ሁሉ የኢትዮጵያ ልጆች ሆይ!ለጥምቀት ሰማያዊ ቀለም ያለው ቲሸርት እንዳይለብሱ ወያኔ በመከልከሉ ወያኔን ይታዘቡት ይናቁት እንጅ የሚጎድልባቸው ነገር እንደሌለ ለተከለከሉት ወገኖች ንገሩ!ይልቁንስ፤ በህገ አራዊትና፤ በህገ አረሚ ኢትዮጵያን በማመስ ላይ ያሉትን ሁሉ፤ ጽድቅን ለመፈጸም የክርስትና እምነት ባይኖራችሁም፤ “ከህገ አራዊት ተላቀቁ!ከህገ አረሚ ውጡ!“አትግደል አትዝረፍ“ ከምትለው ከኦሪት ለመድረስ ሞክሩ እያላችሁ በተባበረ ድምጽ መንገራችhሁን አትሰልቹ! በተረፈ፤ ጌታችን አምላካችን ጽድቅ የፈጸመበትን የጥምቀትን በዓል ለማክበር እንኳን አደረሳችሁ በማለት፤ ቅዱስ ገብርኤል ስላከበረው ሥነ ባህርይ መግለጽ የጀመርኩትን ከዚህ ላይ በመግታት እሰናበታችኋለሁ።
ማሳሰቢያ፦ ስለ ሕገ አራዊት፣ሕገ ኦሪትና ሕገ ክርስቶስ የበለጠ ለመረዳት ከፈለጉየሚቀጥለውን ሰንሰለት ይጫኑ : የጥምቀት በዓል
ለሌሎች ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ጦማሮች የሚከተለዉን ድረገጽ ይመልከቱ:: http://medhanialemeotcks.org/

The post ቅዱስ ገብርኤል ሥነ ባህርይን (ሞራልን) አከበረ! – ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ appeared first on Zehabesha Amharic.