የማለዳ ወግ… አርቲስት ሜሮንና አስቴር ተናገሩ ፣ እኛስ !
* በስደት የግፉአኑን መከራ ለመቅረፍ ምን እየሰራን ነው ?
* የውዴታ ግዴታ የለብንምን?
ነቢዩ ሲራክ
ሜሮንና አስቴር …
ያን ሰሞን አርቲስት ሜሮን ጌትነት ” አትሂድ ” ባለችው የተዋጣለት ግጥሟ ታሸበሽብ ታረግድለት የነበረውን የኢህአዴግ አመራርና ስርአቱን በሰላ ብዕሯ መሸነቋቆጧ ከጫፍ እስከ ጫፍ የሃበሻ መነጋገሪያ ሆኖ ከርሟል ። የሜሮን ፋና ወጊ ፣ በጥበብ የተከሸነ ፣ ነፍስ አሽር ግጥም በድምጽ ብቻ ሲሰራጭ ገዥውን ፖርቲ የመከላከያ ሰራዊት መለዮ ከነኮፊያው ሳይቀር እየደነቀረች የተለያዩ ወቅታዊ ደጋፊ ዝግጅቶችን ስታቀርብ የምናውቃት አርቲስት ሜርን ጌትነት ድምጽ መሆኑን ለማመን ቸግሮንም ነበር ። ብዙም ሳይቆይ ግን ዛሬ በእሳት ዶግ አመድ በሆነው የጣይቱ ሆቴል ጥበብ ይዘንብበት በነበረው የጃዝ አንባ ዳራሽ መድረክ ላይ ግጥሙን ስታነብ የተቀረጸችው ፍንትው ያለ መረጃ ቀረበ ።
“ጉድ ” አልን … ” እውነት ሜሮን ናትን ” ስንል አይሆን መስሎን የተጠራጠርነው ገሃድ ሆኖ እውነቱ ተገለጠ ፣ ጥበቧን የወደዱላት ” ጥበብ የህዝብ ስሜት ጉዳት ሲገልጥበት እንዲህ ነው ፣ አበጀሽ ሜሮናችን ” በሚል የቆየ ብሽቀታቸውን ትተው የአድናቆት ፍቅር ስሜት ቀየሩት ፣ በቅኔ በውዳሴም በክብር ” ሜሮን ሜሮን ” እያሉ ከፍ ከፍ አደረጓት ! ሜሮን ጨክና ትደግፈው ይደግፉት የነበረውን የኢህአዴግ መንግስት ቅኔ ዘርፋ መሸንቆጧን ያልወደዱላት ምላሽ ቅኔ ሳይቀር ተቀኘን ብለው ትንታጓን ሜሮንን የስድብ ውርጅብኝ አወረዱባት ! ” ይህች ደግሞ ምን ጎደለብኝ ብላ ነው? ” ሲሉ የህዝብ ህመም ፣ የህዝብ ሮሮና ዋይታን የህዝብ ልጆች ጥበበኞች የመግለጽ ሃላፊነት እንዳለባቸው እያወቁት እንዳላቀቁ ሆነው ዘለፏት ፣ ተሳለቁባት !
የጥበብ ሰዎች እንደ ሃገሬው በከፋው የእኛ ፖለቲካ ዘባተሎ እየተገፉ ” ሃብታችን የህዝብ ፍቅር ነው! ” እንዳላሉ መሸነጋገላቸው አስተዛዛቢ ሆኖ መንጎድ ያዘ ፣ ህዝብና ጥበብ በፖለቲካ ቅኝት ተለያዩ ! አርቲስቱ ትዝብት ላይ ወደቁ … ይለይለት ያላ የሚመስለው መንግስት ያን ሰሞን ህወሃት ኢህአዴግ ያለፈበትን የትግል ጉዞውን ያዩለት ዘንድ አርቲስት የጥበብ ሰዎችን ወደ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የትጥቅ ትግል መጠንሰሻ ወደ ደደቢት ሲወስዳቸው ነገሩ ሁሉ ግልጥልጥ ማለት ያዘ !
በጉዞው ጉብኝቱ ስለሆነው ሁሉ አናወጋም …በዚያው በጉብኝቱ በተደረገው ውይይት የተነሱ በርካታ ውይይቶች አንዱ ግን እናነሳለን ! ቀልብ ሳቢ ከነበሩት ውይይቶች መካከል የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣኖች በተካፈሉበት አንድ ውይይት የሰላ ጥያቄ ለመከላከያ የበላይ ለጀኔራል ሳሞራ የኑስ የሰላ ጥያቄ ያቀረበችውን የአስቴር በዳኔ ጥያቄ ይጠቀሳል ፣ በእርግጥም የአስቴር በደኔ ጥያቄ ፍጹም ይሆንል ያልተናል ፣ ያልተጠበቀና ያልታሰበ ነበር ፣ የአስቴር ይህን ሁሉ አመት አውራ ሁናችሁ መግፋታችሁ ያዋጣ ይሆን የሚል አንድምታ ያለው ምክር የተቀላቀለበት ጥያቄ ለጀኔራል ሳሞራ ቀርቦ ምላሽ የተባለው ምልሽ ተሰጠው …
እናም የአስቴር ጉዳይ ፣ የአስቴርን እያንሾካሾከ ከራሱ ጋር የሚፋተገው የእኔ ቢጤ ፈሪ ጥያቄው የእሱ ጭምር ሆኖ እያለ የህዝብ ልጇ የብርቱዋ አርቱስት አስቴር በዳኔ ጥያቄ እያለ እንደ ሜሮን ሾተላይ ግጥም እየተቀባበለ መመልከቱ እውነት ነው ፣ በእርግጥም ጥያቄው የብዙሃን ጥያቄ ነበርና የአርቲስት አስቴር በዳኔ ጥያቄና መልስ የያዘው ተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፈ መረጃ እንደ ሜሮን ግጥም ከጫፍ እስከ ጫፍ በሰፊው ተናኘ !
እኛስ እንደ ዜጋ !
ከሜሮን ሰሞነኛ መነጋገሪያ ግጥም ለጥቆ አርቲስት አስቴር በዳኔ ለኢህአዴግ መንግስት ቁንጮ ባለስ ልጣናት ያቀረበችው ጥያቄ እንደ ሜሮን ሁሉ በድጋፍና በጥላ ቻ የታጀበ ነበር ። እኔ የምለው እኛስ የት ነው ያለነው ነው? ይህን ብየ የማጠይቀው ! መልስም አለኝ !
አዎ አርቲስት አስቴርና አርቲስት ሜሮን ያሻቸው የፈቀዱትን ተናግረዋል ፣ በቃ ! ሁለቱም እህቶች ስሜታቸውና ማስተላፍ ያለባቸው መልዕክት ያመኑበትን ሲሆን በአደባባይ ነው የተናገሩት ! እኛ ግን እነሱ ያመኑበትን ለመቀበል ምክንያቱ ግልጽ ሆኖ እያለ አግድመን እየተራኮትን ያለነው ! አርቲስቶች ባነሱት በብዙሃን የሃገሬ ሰው ውስጥ የሚንቀለቀል መሰረታዊ እውነትና ጥያቄ ውስጥ ራሳችን ማየት ተስኖናል ። እንደ ዜጋ በከባቢያችን ከእኛ የሚገባውን ጥቂቱን ሃላፊነት ሳንወጣ ማግለል ፣ ማንቋሸሽ ፣ ማጥላላትና መኮፈስን ለምደነዋል ! ግን ለምን ? አልልም ! እስከ መቸ እንዲህ ሁነን እንቀጥላለን ? ግን እላለሁ !
የሃገር ቤቱ ፖለቲካ እሳት ሆኖ ይፋጃል ቢባል ፣ በአረቡ አለም በስደት የሚገኙ እህቶቻችን መከራ እንዲያቆም በስደት ያለን የተሻለ ኑሮ የምንገፋው እንደ ዜጋ ለግፉአኑ የቻልነውን ማድረግ የሞራል ግዴታ እያለብን ለማድረግ ፈቃደኞች አይደለንም ! መከራና ሰቆቃው ከቀን ወደ ቀን እየከፋ መጥቷል ፣ የመንግስት ሹማምንት ከሞቀው ወንበራቸው ተነስተው ለተጎጅ ወገኖቻቸው እንዲተጎ እንኳ የሰላ ሂስ ሰንዝረን ቀርቶ ተሽቆጥቁጠን በየበአላቱ ስናጅባቸው ለተገፊው ወገን እንዲደርሱለት አንመክራቸውም ! በስደት የግፉአኑን መከራ ለመቅረፍ ምን እየሰራን ነው ? የውዴታ ግዴታ የለብንምን ?
አንዳንዶቹም ሹሞቻቸን ከማስተማር ከምመከር ወጥተን ጥሩ ነገር እንደሰሩ እናሞካሻቸዋለን ፣ የሰላ ሂስ የምናቀር በውን ” የግንቦት 7 ፣ የኦነግ ፣ የአረናና የማንቴስ ተቃዋሚ አባላት ” እያልን ለጥቅም ማግበስበሱ እኩይ ምግባር መትጋት ይቀናናል ፣ አድርባይ አጎብዳጅነቱን ትተንና ላንመለስበት ንስሃ ገብተን ፣ መቸ ይሆን ወደ ትክክለኛው መንገድ የምንጓዘው? መቸ ነው ለፖለቲካ ወገንተኛነትን ፈንግለን ለወገናችን መከራ መቆም ፣ ለሰብዕና ብለን እውነትን የምንከተለው ?
ከሰብአዊ ሰው በወጣ የአድርባይነት ካባ ደርበን የሚ ገፋውን ህይዎታችሁን መታዘብ ዘልቆ ያማል ! እንደ አርቲስት ሜሮን እውነትን ሸፋፍነን ብንከርምም ቀኑ ሲደርስ ፣ ውስጥ አልቀበል ሲል ለእውነት መስዋዕት ለመሆን የምንተጋበት ውበትን እውነት ብለን የምንገልጥበት ቀን ናፍቆኛል ። እንደ አርቲስት አስቴር ደፍረን የህዝብ የወገናችን “የህሊና ድምጽ ” መሆኑ ቢሳነን ፣ የሚፈሩትን ሹሞች ሳንፈራ በግምባር የምናጠይቅበት ስለ እውነት የምናፈጥበት ሞራል ባይኖረን … እንደ አቅማችን ፣ እንደ ራሳችን ፣ እንደ ቤታችም ፣ እንደ ጉዳታችን ሆነን የግፉአን ስደተኛ እህቶ ቻችን መከራ እንዲያቆም የምተጋበት ቀን ናፍቆኛል ! እውነቱን በገሃድ መገላለጥ ፣ ለየቸገረው ስደተኛ እርዳታን ድጋፍ የማድረጉ ሃላፊነት ከማናችንም የሚጠበቅ የውዴታ ግዴታ መሆኑን ልብ ልንለው ይገባል ! ያ ሲሆን ማየት ደግሞ በጣሙን ናፍቆኛል !
እስኪ ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
ጥር 12 ቀን 2007 ዓም
The post የማለዳ ወግ… አርቲስት ሜሮንና አስቴር ተናገሩ ፣ እኛስ ! * በስደት የግፉአኑን መከራ ለመቅረፍ ምን እየሰራን ነው ? * የውዴታ ግዴታ የለብንምን? appeared first on Zehabesha Amharic.