ይህ ፅሑፍ የኢሳት ባልደረባ ተ/ሚካኤል አበበ “የኢሳት 3ኛ ዓመት ክብረ በአል የሙስሊሞች ብቻ ነው እንዴ?( http://www.zehabesha.com/amharic/archives/1923) ’’ በሚል ርዕስ ላቀረበው ፅሑፍ አቶ ቶፊቅ ጀማል ከቼክ ሪፖብሊክ(ፕሪግ) መልስ እንዲሆን ብለው “ልጅ ያቦካው (http://www.zehabesha.com/amharic/archives/2039) ” በሚል ርዕስ “ ለሰጡት ባለ 12 ነጥብ (የቃላት ጨወታ) የተሰጠ ምላሽ ነው፡፡
- ውድ አቶ ቶፊቅ ጀማል “የአብዬን ወደ እምዬ ልክክ” እንዲሉ በኢሳት 3ኛ ዓመት ክብረ በአል ዝግጅት ላይ በሙስሊም ( እዚህ ላይ አወልያን መሰረት አድርጎ የተነሳውን የሙስሊም እንቅስቃሴ የማትደግፉ ወይም አካሄዱን የማትቀበሉ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች እንድትረዱኝ አደራ የምለው በዚህ ፅሑፍ “የሙስሊም ተወካዮች” እያልኩ የምጠቅሰው አወልያን መሰረት አድርጎ የተነሳውን የሙስሊም እንቅስቃሴ ደግፋው “በዲያስፖራ” የሚንቀሳቀሰውን ቡድን መሆኑን እንድትረዱኝ አደራ እላለሁ ) ተወካዮች ብቻና ብቻ እንዲሞላ መደረጉ ተገቢ አይደለም ከዚህ ይልቅ የሁሉም ሃይማኖት ተወካዮች ጥሪ ሊደረግላቸው ይገባል የሚል ግልፅ የሆነ የእርምት መልዕክት ያለውን ፅሑፍ የኢሳት ባልደረባ የሆነው ተ/ሚካኤል አበበን ቁምነገር አዘል ምክር “ልጅ ያቦካው” ነው ብለህ ለመተቸት በመድፈረህ “ልጅ” ማን እንደሆነ ምላሽ እንድሰጥህ ግድ ሆኖብኛል፡፡
አንተ ግን ያደረገውንና የተናገረውን ፈጥኖ እንደሚረሳ ሕፃን በዚህ ፅሑፍ አልተበሳጨሁም ወይም አያበሳጭም ብለህ ከፃፍክ ከጥቂት መስመሮች በኋላ ቀለሙ እንኳን ሳይደርቅ ወዲያው “ኧረ በጣም ያበሳጫል” ብለህ መፃፍህንና ተ/ ሚካኤል አበበ የጻፈዉን ጽሑፍ አንብበህ ሳትጨርስ ለትችት መንደርደርህን የተመለከትን ማለትም የኢሳት ባልደረባ ተ/ሚካኤል አበበ የፃፈውን ባለ 15 (አስራ አምስት) ነጥብ ፅሑፍ ባለ 12 (አስራ ሁለት) ነጥብ የአቋም መግለጫ ብለህ ከጅምሩ ስትቀባጥር የታዘብን አንባብያን የአንተን ፅሑፍ “ልጅ ያቦካው” ነው ወይስ “ሕፃን ያቦካው” ነው የምንለው?
ተ/ሚካኤል አበበ የተጠቀመበት የአነጋገር ስልት ገና ከጅምሩ ሊገባህ እንዳልቻለ ስለ ማበሳጨት እና ስለ ማስጨብጨብ የሰጠኸው ትንታኔ ያሳብቅብሃል እንዲያው በከንቱ ያለአቅምህ ተወጣጠርክ እንጂ:: አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን በሚተቸው ፥ በሚገስፀውና ስህተቱን በሚያርመው የማይደሰት ከሆነ መስተካከልና መታረም ባለመፍቀዱ “ያበሳጨዋል”። እንዲሁም ምክር አዘል መልዕክቶችን አንብበው ከስህተታቸው ለመታረም : ለችግራቸው መፍትሄ ሰጪ ይሆናል ብለው ለሚያምኑና ለሚያነቡ ደግሞ “አስጨብጫቢ” ይሆናል ማለት እንጂ “ማበሳጨት” ማለት ፊትህ እስኪቀላ መኮሳተርን ወይም “ማስጨብጨብ” ማለት ደግሞ እጅህ እስኪቃጠል በመዳፍህ አጋና መምታትን የሚመለከት አለመሆኑን ለመረዳት ከፈለክ ለማቡካት የሚጣደፉትን የህፃን እጆችህን ሰብሰብ ብታደርጋችው መልካም ነው’።
- የኢሳት ባልደረባ ተ/ሚካኤል አበበ ከዜና አንባቢነት ጀምሮ በኢሳት በሚተላለፉ የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ግዜውን ፥ እውቀቱንና ጉልበቱን ያፈሰሰ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከመሆኑም በላይ በተለያዩ የኢሳት የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ላይ በበርካታ የሰሜን አሜሪካ ክፍለ ሃገራት ( states) በመገኘት የታወቀ ሆኖ ሳለ መሰረታዊውን የፅሑፉን መልዕክት በተ/ሚካኤል መጋበዝና ባለመጋበዝ ዙሪያ ለማቡካት መከጀልህ አንተን የመሳሰሉ ህፃናቶችን ልትቀልድባቸው አልመህ ካልሆነ በስተቀር ኢሳት የኢትዮጵያውያን ሁሉ እንደ መሆኑ መጠን የሃይማኖት ተወካዮች መጋበዛቸው አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የሁሉንም ኃይማኖት ተወካዮች ማካተት አለበት የሚለውን ጭብጥ ሊያጠፋው አይችልም።
አቶ ቶፊቅ ጀማል ስታቦካ የረሳኸውን ነገር ላስታውስህ የኢሳት ባልደረባ ተ/ሚካኤል አበበ ጳጳስ ነኝ ፥ ቄስ ወይም ፓስተር ነኝ ወይም የሃይማኖት ተወካይ ነኝ አላለም ነገር ግን የሃይማኖት ተወካዮችን መጋበዝ ካስፈለገ ኢሳት የኢትዮጵያዊያን ሁሉ እንደመሆኑ መጠን ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ የሚያካትት መሆን ስለሚገባው የሁሉንም ሃይማኖት ተወካዮች መጋበዝ ነበረባቸው በማለት ምክር አዘል እርምት መስጠቱ በየትኛውም የአፈታት ወይም የአተረጓጎም ስልት(ተፍሲር) ተ/ሚካኤል አበበ እኔ ጳጳስ በመሆኔ የሃይማኖት ተወካይ ነኝና ጋብዙኝ ማለትህ ነው ሊያስብለው የሚያስችል ጭብጥ የለውም።
- በ3ኛው ነጥብህ ላይ ኢሳት ለዲያስፖራ የሙስሊም ተወካዮች ሽፋን የሰጣቸው የኢትዮጵያዊያን የመብት ትግል ሲያቀጣጥሉት በመገኘታችው ነው ብለሃል ነገር ግን የሙስሊም ተወካዮች ትግሉን ለማቀጣጠል መነሳታችው የሚለካው ከሃይማኖት ጎራ ወጣ ብሎ ለዜግነት ክብር በመቆም በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ ለሚደርሰው የመብት ጥሰትና ጭቆና በጋራ መቆም ሲችሉ እንጂ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ዜጎች ለምሳሌ ለጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ፥ አንዷለም አራጌ ፥ ጋዜጠኛና መምህር ወ/ት ርዮት አለሙ ፥ አቶ በቀለ ጎረባና ለሌሎችም የህሊና እስረኞች መቆምና መታገል ካልቻሉና ልባቸው ካልተነካ እንዲሁም በየሄዱበት ቦታ በዋነኛነት የሚያነሱት የሙስሊም እስረኞችን ጉዳይ ብቻ ከሆነ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መብትና ነፃነት የሚታገለው ኢሳት ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ይልቅስ ኢሳት የአንድ ሃይማኖት ተወካዮችን ብቻና ብቻ በዓመታዊ ክብር ባዓሉ ላይ ለመጋበዝ መወሰኑ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ ኢሳት የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ሳይሆን አወልያን መሰረት አድርጎ ለሚንቀሳቀሰው የሙስሊም ተወካዮች ብቻ የሚሰራ የፕሮፖጋንዳ ማሽን ያስመስለዋል እንጂ።
- አቶ ቶፊቅ ጀማል በአራተኛው ነጥብ ላይ ምጡቅ ሃሳብ ልታመነጭ የምትንደረደር በሚመስል መልኩ “ያልተረዳኸው ወይም ልትረዳው ያልፈለከው ወይም ያልሞከርከው ጉዳይ ያለ የመስለኛል” ብለህ ከጀመርክ በኋላ የሙስሊሙ ችግር የሃይማኖት እንጂ የፖለቲካ አይደለም የሚንቀሳቀሰውም ይህንኑ የሀይማኖት ችግር ለመፍታት ብቻ ነው” ብለሃል።አስተሳሰብህ የሕፃን ቡኮ ሆኖብህ ነው እንጂ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ በጥራት የሚገባህ ሰው ብትሆን ኖሮ በዚህ ነጥብ ላይ ያነሳኸው የተ/ሚካኤልን ስጋት የሚያጠናክር ነው።
ሙስሊሙ የሚመለከተው የሙስሊሙን ሃይማኖታዊ ጉዳይ ብቻ እንጂ የመላው ኢትዮጵያውያ ህዝብ ያለበት የኢኮኖሚ ፥ የፖለቲካና ማህበራዊ ቀውስ አይመለከተውም የምትል ከሆነ አንተና አንተን መሰል አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በዜግነት አጀንዳ ዙሪያ ወደ ላይ ከፍ ለማድረግ በተቋቋመው በኢሳት ዙሪያ ሳይሆን መሰብሰብ የሚገባቸው በሃይማኖት ጣራ ስር ወይም በመስጊድና በመስጊድ ብቻ ነው።
አንተ ሊገባህ ያልቻለው ኢሳት የኢትዮጵያውያን ሁሉ የዜግነት አጀንዳ የሚስተናገድበት ሚድያ እንጂ ከሙስሊሙ ጥያቄ ውጪ የሌላው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ችግር አይመለከተንም ለሚሉና እንዲሁም በኢሳት ዓመታዊ ክብር በዓል ላይ መጋበዝ ያለባቸው የሙስሊሙ ተወካዮች ብቻ ናቸው ብለው ለሚያስቡ ወገንተኛ አስተሳሰብ ላላቸው የጠባቦች ንብረት አይደለም።
- እዚህ ላይስ እኔም መልስ መስጠት የለብኝም ብዬ አሰብኩና “ለዚህ መልስ መስጠት ያለብኝ አይመስለኝም” ካልክ በኋላ ወዲያው ከቼክ ሪፖብሊክ የአማርኛ ሰዋሰው እርማት ለማድረግ መከጀልህን አይቼ “መልስ በመስጠትና ባለ በመስጠት” መካከል ያለው ልዩነት የማይገባህ ህፃን መሆንህ ትዝ ስላለኝ አንድ ሁለት ነገር ልጠቁምህ ወሰንኩ።
ኢሳት በዜግነት ክብር እንጂ እንዳንተ በሃይማኖት ብቻ የማያስቡ ውድ ኢትዮጵያዊያን የተሰባሰቡበት በመሆኑ ዓመታዊ ክብረ በዓሉ ላይ የሚጋበዙ እንግዶችም ይህንኑ የሚያንፀባርቁ ሊሆን ይገባል ስለዚህም የሃይማኖት ተወካዮችን መጋበዝ ካስፈለገ ሁሉም ቤተ እምነቶች በመወከል በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እየተፈጠረ ያለውን ስጋት እና ጥርጣሬ ያገናዘበ ቢሆን እንደዜጋ በኢትዮጵያዊነታቸው
: ዜግነትን መሰረት አድርጎ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ መብት ለመታገል ለቆመው እንደ ኢሳት ዓይነት ተቋም ጠንቅ መሆኑን መቀበል ፥ መረዳትና መገንዘብ አቅቶህ ብትዘባርቅ ሃይማኖታዊ ብቻ እንጂ ብሔራዊ አጀንዳ የለንም ከምትለው ከአንተ እና ከመሰሎችህ ሌላ ምን ይጠበቃል።
- በ6ተኛ ነጥብ ላይ ያነሳኸውን ሃሳብ “የራስዋ አሮባት የሰው ታማስላለች” የሚለውን ቁም ነገር አዘል ምሳሌ እንዴት እንዳስታወስከኝ እንደሚከተለው ላመላክትህ:: በዚህ ነጥብ ጅማሬ ላይ “መንግስትና ሃይማኖት አይለያዩ ማለታችን ነው..” የሚለውን አረፍተ ነገር ጠቅሰህ የአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም ላይ ትችት ለመስጠት በማሰብ ያልገባህ በመምሰል የህፃን ነገር ሆኖብህ ነውረኛና ነገረኛ ለመሆን ሞክረሃል ነገር ግን በዚሁ አረፍተ ነገር ላይ በዚህ ነጥብ አንተው ራስህ “በእርግጥም ምን ለማለት እንዳወብህ አልገባኝም” ስትል ምን ማለት ፈልገህ ነበር? “እንዳወብህ” የሚል አዲስ የአማርኛ ቃል አንተ ፈጥረህ ነው? ወይስ ከመኖሪያ ሃገርህ ከቼክ ሪፖብሊክ ቃላት ተውሰህ ነው? አየኸው የራስዋ አሮባት የሰው ታማስላለች ይሉሃል እንዲህ ነው።
እንዲያው ለነገሩ ነው እንጂ ከአረፍተ ነገሩ አሰካክና ከአውደ ንባቡ አንፃር ለማለት የፈለከውን ለመረዳት በጣም ቀላል ነው የሚጠይቀው ቅንነት ብቻ ነው አንተ ለማለት የፈለኩት ሌላ ነው ካላልከኝ በስተቀር መጠቀም የፈለግከው ቃል በታይፕ ግድፈት “ሰ” በ “ወ” ቢቀየርብህም “እንዳሰብህ” ለማለት ፈልገህ እንደሆነ ይታየኛል ከዚህ የምረዳው የተ/ሚካኤልን ጽሑፍ በቅንነት ለማንበብ አለመሞከርህንና በዚህም ምክንያት ለአላስፈላጊ ትችትና ጥላቻ መዳረግህን ብቻ ነው።
ተ/ሚካኤል በ7ተኛው ነጥብ ላይ የገለፀውን ሃሳብ አንተ ለጥላቻ መልዕክትህ እንደቆረጥከው ወይም ለመጠምዘዝ እንደሞከረከው ሳይሆን አውደ ንባቡ በግልፅ እንደሚያስረዳው መንግስትና ሀይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን ነው:: በተ/ሚካኤል ፅሑፍ በ6ተኛው ነጥብ መጀመሪያ ላይ “… ሀይማኖትና መንግስት የተለያዩ ናቸው፤ መንግስት Secular ይሁን፤ የሚለውን መሰረታዊ የፖለቲካ መርህ አምነንበት…” ነው ይላል:: በተጨማሪም በ 7ኛው ነጥቡ ላይ “ አሁንም መንግስትና ሀይማኖት ይለያዩ፤ መንግስት በሙስሊሞች ጉዳይ ጣልቃ አይግባ ስንል ያ ብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን የሞቱለት መርህ ይከበር ማለታችን ነው ”ይላል:: እነዚህን አረፍተ ነገሮች ያነበበ ቅን ሰው
ከላይ “አይለያዩ ” የሚለው ቃል “አ” በታይፕ ግድፈት የገባች እንጂ በግንዛቤ ችግር የገባች አለመሆንዋ እየታወቀ ይህን ያህል በጥላቻ የተሞላህና በእድሜ ብቻ የገፋህ በአስተሳሰብህ ጨቅላ ህፃን ያስመሰለህን ጉዳይ ቆም ብለህ እንድታስብበት እጠይቅሃለሁ።
- ለነገር ከመቸኮልህ ብዛት ናላህ ስለዞረ የተ/ሚካኤል 6ተኛ እና 7ተኛ ነጥብ ከአንተ 6ተኛ እና 7ተኛ ነጥብ ጋር የተለያዩ ቢሆኑም “ህፃን ያቦካው” እንዲሉ አገለባብጠከኸዋል ስለዚህም ነጥቦቹን እየተከታተሉ ለሚያነቡ አንባቢያን አደናጋሪ እንዳይሆን በበኩረ ፅሑፉ ቅደም ተከተል ሳይሆን መልስ የምሰጠው ላንተ በመሆኑ አንተ የፃፍክበትን ቅደም ተከተል መርጫለሁ። የኢሳት ባልደረባ ተ/ሚካኤል አበበ የኢሳት ዓመታዊ ክብረ በዓል የሁሉም ኢትዮጵያውያን በመሆኑ የሁሉም ሀይማኖት ተወካዮች ሊጋበዙ ይገባል የሚል ምክር በማቅረቡ “የልጅ ራዕይ ነው” ብለህ ከተሳለቅክበትና ለማጣጣል ከሞከርክ ፣ በበዓሉ ላይ መጋበዝ ያለባቸው የሙስሊም ሀይማኖት ተወካዮች ብቻና ብቻ መሆን አለበት ብለህ ሽንጥህን ገትረህ የምትሟገተውን ያንተን ህልም “የሕፃን ቅዥት ነው” ከማለት የተሻለ ምን ማለት ይቻላል?
- በዚህ ነጥብ ላይ የሚገርመው ይሄን ሁሉ ትችት ስትደረድር ከቆየህ በኋላ በእርግጠኝነት ባልገባህ ጉዳይ ስትፅፍ መቆየትህን “…በእርግጥ አልገባኝም …“በማለት ማመንህ ነው። በእርግጠኝነት ባልገባህ ጉዳይ ላይ ስትቸከችክ መቆየትህ ዘባራቂ መሆንህን አረጋገጠልኝ። በእርግጥም ሊገባህ ያልቻለውን ነገር እኔ ልንገርህ አንተ ያልገባህ ኢሳት የኢትይጵያዊያን ሁሉ መሆኑና በዓመታዊ ክብረ በዓሉ ላይ መጋበዝ ያለባቸው የአንድ እንቅስቃሴ ተወካዮች ብቻ መሆን እንደማይችል ነው። በዓመታዊ ክብረ በዓሉ ላይ የሃይማኖት ተወካዮችን መጋበዝ ካስፈለገ ሁሉም የሃይማኖት ተወካዮች ቢጋበዙ ኢትዮጵያዊነትን ከማንፀባረቅ በስተቀር ሌላ ምን ችግር ይኖረዋል?
አንተ ግን አንዳንድ የአክራሪ ኢስላም አቀንቃኞች እንደሚናገሩት ኢትዮጵያዊነትን በሚያንፀባርቁ ጉዳዮች ላይ ቀስ በቀስ መታየትና መገኝት ያለባቸው የሙስሊም ተወካዮች ብቻና ብቻ መሆን አለባቸው በሚል በሸሪያ ፍልስፍና የተጠመቁ ሰዎችን አስተሳሰብ ለማራመድ የምትከጅል ሕፃን በመሆንህ ነው።
ተ/ሚካኤል በተደጋጋሚ ለማስረዳት የሞከረው ኢሳት ኢትዮጵያዊ ዜጎችን ሁሉ በሚያካትት መልኩ ሊሆን ስለሚገባ የሃይማኖት ተወካዮችን መጋበዝ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የሁሉም ሃይማኖት ተወካዮች ቢገኙም ባይገኙም መጋበዝ ተገቢ ሆኖ ሳለ የአንድ ሃይማኖት ተወካዮችን ብቻ ነጥሎ መጋበዝ አደጋ ከመፍጠር በስተቀር ጠቃሚ ሊሆን አይችልም:: በተለይ ደግሞ የሙስሊሙን እንቅስቃሴ በጥርጣሬ የሚመለከቱ ኢትዮጵያዉያን እንዳሉ በተረዳንበት ግዜና ወቅት::
9. በዚህ ነጥብ ላይ ያነሳኸው ነጥብ በአጭሩ “የእርጎ ዝምብ” መሆንህን ከማሳየት በስተቀር ሌላ ምንም ቁም ነገር የለውም በ5ተኛው ነጥብህ ላይ የአማርኛ ሰዋሰው ሊቅ ለሞሆን ሲቃጣህ አንብቤ ሲገርመኝ አሁን ደግሞ የታማኝ በየነ በኢትዮጵያዊነቱ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የቆመበትን አላማ በመጠምዘዝ አሳፋሪ አፈቀላጤ ለመሆን ሞከርህ ከዚህም በላይ ኢሳት የኢትዮጵያውያን ሁሉ ዓይን ፥ ጆሮና አንደበት እንጂ እንደ አንተና እንደ መሰሎችህ በኢሳት ክብረ በዓል ላይ መጋበዝ ያለባቸው የአወልያ እንቅስቃሴ ተወካዮች ብቻና ብቻ ናቸው ብለው ሽንጣቸውን ገትረው ለሚሟገቱ ሕፃናቶች መፈንጫ አይደለም።
የሃይማኖት ተወካዮችን መጋበዝ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የሙስሊሙን ተወካዮች ብቻ ነጥሎ መጋበዝ ታላቅ አደጋ አለው በተለይ ደግሞ አወልያን መሰረት አድርጎ የተነሳውን የሙስሊም እንቅስቃሴ በጥርጣሬ የሚመለከቱ እና የማይደግፉ ሙስሊሞችንም ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ በሚታወቅበት በዚህ ወቅት ጥንቃቄ ማድረጉ ተገቢ መሆኑን መጠቆሙ ሊገባህ ያልቻለበት ምክንያት አንድም ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ እንደ ዜጋ ለመቀበል ችግር ያለብህ ከመሆኑም በላይ ሙስሊም ላልሆነው ኢትዮጵያዊ ክብር የሌለህ መሆኑን ነው።
10. የኢሳት ባልደረባ ተ/ሚካኤል በፅሑፉ 11ኛ ነጥብ ላይ “የሀይማኖት መሪዎች ከጋበዝን ደግሞ ቢመጡም ባይመጡም የኦርቶዶክሱንም የፕሮቴስታንቱንም፤የይሁዲውንም፤ የካቶሊኩንም ነው እንጂ፤ በምን መስፈርት ነው የሙስሊሞቹን ብቻ የምንጋብዘው? ይሄአደገኛና መታረም ያለበት አካሄድ ነው። “ እንዲሁም በ12ተኛ ነጥብ ላይ ኢትዮጵያ “ የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች ያሉባት ሃገር “ መሆኗን በግልፅ ጠቅሷል። ይህም ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች የሚኖሩባት አገር መሆኗን የሚያስረዳ ሆኖ ሳለ ነገር ግን አንተ ከአውደ ንባቡ ውጪ የሆነ መደምደምያ ይዘህ ለዚህ ትችት መነሳትህ ቀደም ሲል ደጋግመህ እንዳረጋገጥክልኝ የኢትዮጵያዊነት ፅንሰ ሃሳብ ያልገባህ መሆንህን ነው።
ለነገሩ “የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል” እንዲሉ አንተ እስከ 12ተኛው ነጥብ ብቻ በማየት የፅሑፉን መዳረሻ ሳትረዳ በመዘባረቅህ ይቅርታ መጠየቅ ይገባሃል። ምክንያቱም የተ/ሚካኤል ፅሑፉ ሙሉው አንተ እንዳልከው ባለ 12 (ኣስራ ሁለት) ነጥብ ብቻ ሳይሆን 15 (ኣስራምስት) ናቸውና :: ለምሳሌ ስለ ብሔር ብሔረሰቦች ስብጥር ለመግለጽ ቢያስፈልገን ከ80 በላይ የሆኑትን የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች በንግግሩም ሆነ በፅሑፉ ላይ ሁሉንም ካልጠቀሰ በስተቀር በአንተ የ “ህፃን” አስተሳሰብ መሰረታዊ የጠባብነት ማስረጃ ሆኖ ከተወሰደ እስከ ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የብሔር ብሔረሰቦችን የሚመለከት ንግግር ሲያደርጉ ወይም ሲፅፉ ለናሙና ያህል የተወሰኑትን ጠቅሰው በማለፋቸው በአንተ የጠባብነት መስፈርት መሰረት ሁሉንም ባለ መዘርዘራቸውና የተወሰኑትን ጠቅሰው ሌሎቹን ግን “የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች” በማለታችው በአንተ የ”ሕፃን” መስፈርት መሰረት በጠባብነት ጎራ ተፈርጀው ላልበሰለ ትችትህ ተጋልጠዋል ማለት ነው።
አንተ በመግቢያህ ላይ ማንንም አልወክልም ብትልም የተፅዎ ስምህ አልያም የብዕር ስምህ “ቶፊቅ ጀማል” እንደሚያሳብቅብህ ሙስሊም ልትሆን ትችላለህ ነገር ግን ኢትዮጵያ የጀግና ሙስሊሞችም አገር ናት ብለን ለምናምን እንደኔ ላሉ እንደዜጋ በኢትዮጵያዊያነት ለምናምን ወገኖች አንተና አንተ ያለህበት ማህበረሰብ ምናልባትም እንዳንተ የሚያስቡ ከሆነ የኢትዮጵያ ግማሽ አካል ተበላሽቷል ፥ ታሟል፡ በድን ሆኗል ፥ አልያም ከርፍቷልና የወገን ያለህ ብዬ ጩኸቴን አሰማለሁ።
11. በ11ኛው ነጥብ “ኢሳት በህዝብ ድጋፍ የሚተዳደር ነፃ ሚድያ ይመስለኛል” ብለሃል እዚህ ላይ “ይመስለኛል” ስትል መቼ ይሆን “ነው” ብለህ የምታምነው? በዜግነት የሚያምኑ ኢትዮጵያዊያን የሚሰባሰቡበት መሆኑ ቀርቶ ኢሳት ሙሉ በሙሉ በሙስሊሙ ተወካዮች ብቻና ብቻ ሲሞላ ነው? ሌላው ደግሞ ኢሳት “በህዝብ ድጋፍ የሚተዳደር ነው” ብለሃል እንግዲያውስ ኢሳት በህዝብ ድጋፍ የሚተዳደር ከሆነ በኢሳት ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ የሚገኘው ሁሉም ህዝብ ማለትም በሙስሊሙ እንቅስቃሴ ላይ ጥርጣሬ ያለውም ጭምር ማለት እንጂ ኢትዮጵያዊ ህዝብ ማለት የሙስሊም ተወካዮች ማለት ብቻ ሊሆን አይችልም።
ወይስ አንዳንድ ቅዠታሞች እንደሚደሰኩሩት ከአቡጃ አዋጅ (Abuja declaration of 1989 http://en.wikipedia.org/wiki/Abuja_Declaration) ወዲህ ኢትዮጵያ ኢስላማዊ አገር ሆናለችና መወከል ያለባት በሙስሊም ብቻ ነው ብለው ከሚያስቡት ቡድን በመሆንህ ምክንያት እንጂ በኢትዮጵያዊያን ስብሰባ ላይ መጋበዝ ያለባቸው የሁሉም ሃይማኖት ተወካዮች ናቸው የሚለው የተ/ሚካኤል አበበ ጥሪ ባልጎረበጠህ ነበር።
ስለዚህም ኢሳት ሕዝባዊነቱን ጠብቆ ረጅሙን ጉዞ መጓዝ እንዲችል የሃይማኖት ተወካዮችን መጋበዝ ሲያስፈልግ የሁሉንም የሃይማኖት ተወካዮችን መጋበዝ አለበት እንጂ የሙስሊም ተወካዮችን ብቻ መጋበዙ የአወልያን እንቅስቃሴ በጥርጣሬ ለሚመለከቱ ኢትዮጵያዊያን ተጨማሪ ስጋትና አደጋ መፍጠር ስለሆነ የሁሉንም ሃይማኖት ተወካዮች መጋበዙ እውነታና ጥበብ መሆኑን የሕፃን አይምሮህ ከልክሎህ ካልሆነ በቀር በቀላሉ ሊገባህ የሚገባ ገዢ ሃሳብ ነበር።
12. በአስራሁለተኛው ነጥብህ ላይ ከላይ ከፃፍካቸው 11 ነጥቦች በባሰ ሁኔታ የተሳከረ ሃሳብ አንፀባርቀሃል። በአጠቃላይ እርግጠኛ ባልሆንክባቸው ጉዳዮች ሁሉ እንደ እርጎ ዝንብ ዘለህ እየገባህ የምታስቸግር ዘባራቂ መሆንህን ዳግም ያሳየህበት ነጥብ ነው።
በ12ተኛው ነጥብህ ላይ “እንዳልሆኑ ቢናገሩስ?” “ከማሳወቃቸው በፊት ቢሆንስ?” “ተነሳሽነት አሳይተው ቢሆንስ?” በሚሉ ኀረጎች የተሞላ በመሆኑ ስለምትጽፍበት ጉዳይ በቂ ግንዛቤ የሌለህ ለዜግነት ክብር ያላቸውን ሰዎች ለኢትዮጵያዊነት መጎልበት የሚሰጡትን ሃሳብና እርማት የማጣጣልና የማብጠልጠል አባዜ ይዞህ በጽንፈኝነት ለአንድ ቡድን ከመቆም የመነጨ ደካማና መጥፎ ባህሪ በመሆኑ ለወደፊቱ ቆም ብለህ ራስህን እንድትገመግም አደራ እላለው።
ፅሁፌን ለማጠቃለል ሳስብ በጣም የሚገርሙ ከላይ ከፃፍካቸው በበለጠ ማንነትህን ያጋለጥክበት ሃሳብ በማጠቃለያ ፅሑፍህ ውስጥ በማግኘቴ ለማጠቃለያህም ማጠቃለያ መፃፍ አስፈላጊ ሆነ:: ነገር ግን የአማርኛ ሰዋሰው ሊቅ በመሆንህ በሮማኖች ቁጥር (Roman number) መጠቀም ትቼ ትንሽ ደስ ይልህ እንደሆን ብዬ የነጥቦቹን ተራ ቁጥር በአማርኛ ፊደላት እንደሚከተለው ገልጫቼዋለው:-
ሀ. ተ/ሚካኤል በግልፅና በተደጋጋሚ ኢትዮጵያዊነትን አጉልቶ በማሳየት የፃፈውን ፅሑፍ አንኳር ሃሳቡን አውርደህ አውርደህ የቃላት ጨዋታ ለማድረግ ስትሞክር “የአማርኛ ክፍተት ይታይብሃል” ብለሃል ጉዳዩ ግን የአማርኛ ክፍተት ጉዳይ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያን በዜግነታቸው ተሰብሰበው በሃገራቸው ላይ ለሚከሰቱ ችግሮች የጋራ መፍትሔ እንዲፈልጉ የማድረግ ጉዳይ ሆኖ ሳለ አንተ ግን ጭብጡ ላይ ከማተኮር ይልቅ የአማርኛ ቋንቋ ውድድር ልታስመስለው መሞከርህ እጅግ በጣም ያሳዝናል :: ነገር ግን እግረ መንገድህን “የኢሳት ባልደረቦችን የአማርኛ ክፍተት ለመሙላት” የአማርኛን ቋንቋ ለማስተማር ሃሳቡ ካለህ ለኢሳት አስተዳደር ማመልከቻ ብታስገባ የተሻለ ነው።
ለ. አቶ ቶፊቅ ጀማል በኢሳት ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያንን በሚያካትት መልኩ መዘጋጀት አለበት ብሎ ተ/ሚካኤል አበበ መፃፉ ኢሳትን ማጠልሸት ነው ብለሃል:: ለመሆኑ በኢሳት ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ የሃይማኖት ተወካዮችን መጋበዝ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የሁሉም ሃይማኖት ተወካዮችን መጋበዙ ጣቃሚ ነው መባሉ በየትኛው አተረጓጎም (ተፍሲር) ነው ኢሳትን ማጠልሸት የሚሆነው?
የማጠልሸት ጉዳይ ከተነሳ ግን በግልፅ እንዲገባህ የሚያስፈልገው ነገሩ “የእምዬን ወደ አብዬ ልክክ”መሆኑን ነው ። አንተንና አንተን የሚመስል ሃሳብ ያላቸው አንዳንድ በሙስሊሙ ስም የሚነግዱ ቅዠታሞች ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ኢስላማዊ በመሆንዋ ልትወከል የሚገባው በሙስሊሞች ብቻ ና ብቻ መሆን አለበት እያሉ በተለያዩ ሚዲያዎች እንደሚደሰኩሩት ( http://www.selamta.net/Downloads/Letter_to_International.pdf ) አንተም የነዚህን የቀን ህልመኞች ፈለግ ተከትለህ በቂ ግንዛቤ ሳይኖርህ ይህንን ተራ ቱልቱላ ተሸክመህ ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ በዜግነት የሚያሰባስበንን ኢሳትን ለማጠልሸት የተነሳኸው አንተ ሆነህ ሳለ የኢሳትን ገፅታ እንዳይበላሽ ምክርና እርምት የለገሰንን ሰው ጥፋተኛ ለማድረግ በመሞከርህ “የእምዬን ወደ አብዬ” ብዬ ከማለት በቀር ሌላ አማራጭ የለም። ነገር ግን በዚህ “የህፃን” አስተሳሰብህ በአንተም ፥ አንተን በሚመስሉህም በተጨማሪም እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖርህ ተፅኖ ባደረገብህም የማህበረሰብ ክፍል እጅግ በጣም አዝኛለሁ።
ሐ. በመጨረሻም በአንተና የአንተን አስተሳሰብ ተከትለው በሚነጉዱ ሰዎች እኔንና እንደ እኔው ለኢትዮጵያዊ ዜግነት ክብር ላለን ሰዎች ተስፋ አስቆራጭ የሆነውን ማጠቅለያ ስትፅፍ እንዲህ ነበር ያልከው “ ሌላው ልትረዳው እምፈልገው ጉዳይ ቢኖር እንደው ግላዊንት ካልሆነ በስተቀር ምንን ምክንያት አድርገው ነው የሌላው የሃይማኖት አባቶች ሊሳተፉ የሚችሉት በብዙ ሺህ የታሰሩት ሙሰሊሞች፣ ከአመት በላይ ደምፃቸውን ያለማቋረጥ በሰላማዊ መልኩ እያሰሙ ያሉት ሙሰሊሞች፣ ከትምህርት ገበታቸው በጅምላም በችርቻሮም እየታፈኑ ያሉት ሙሰሊሞች፣ በምሽት እየተዋከቡ የሚገኙት ሙሰሊሞች ወንድሜ ቆም ብለህ ማሰብ ያሻሃል፡፡”
በዚህ አስተሳሰብህ አንተን ኢትዮጽያዊ ዜጋ ነህ ብሎ ለመቀበል አይቻልም ወይም ለኢትዮጽያዊያን በችግራቸው ወቅት ከጎናቸው ልትቆምላቸውና ልትደግፋቸው የሚገባህ በሀይማኖታቸው አይነት ሳይሆን በዜግነታቸው ብቻ መሆኑን የማታምን የዜግነት ክብር የሌለህ “ጨቅላ ህጻን” መሆንክን ክማረጋገጡም በላይ ለሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ችግሮች; በሃይማኖታቸው ሳይሆን በዜግነታችሀው ብቻ ለሙስሊሙ መብት ቀንና ሌሊት ሲጮሁ የከረሙትን የሃይማኖት መሪዎች : የፖለቲካ መሪዎች: የሲቪክ ማህበራት : ታዋቂ ግለሰቦች: የሰባዊ መብት ተሟጋቾች: የሚዲያ ተቋማት : ጋዜጠኞችና እንደ ኢሳት አይነቱን የቴሌቪዥን ጣቢያ በግልጽ ያቃለልክበትን: ያላገጥክበትና ለኢትዮጵያዊያን ያለህን ንቀት ያረጋገጥክበት የማንነትህ መገለጫ ነው::
v አቶ(ሼክ) ቶፊቅ ጀማል ለሙስሊሞች ችግር ሙስሊሙ ብቻ ከሆነ መቆም ያለበት ለመሆኑ እነዚህ ሁሉ “ምንን ምክንያት አድርገው ” ነበር ለሙስሊሙ ጥያቄዎች ክሙስሊሙ ጋር አብረው በየ አደባባዩ ሲጮሁ የከረሙት?
v በዚህ ጽሁፍ ላይ በስም የጠቀስከው “አርቲስትና አክቲቪስት” ታማኝ በየነ ምንን ምክንያት አድርጎ ነበር በየ አደባባዩና በየ ሚድያው ድምጹን ሲያሰማ የነበረው?
v በኢትዮጵያዊነት ብቻ አንዳችን ለአንዳችን በመቆም የማታምን ከሆነ ታድያ እንደ አንተ አይነቱን “እጅ ነካሽ” አምነን ለዜግነት ክብር ያለውንና ኢሳትም ይህንኑ መስመር ይዞ እንዲቀጥል ሃሳቡን ያካፈለንን የወንድማችንን የተ/ሚካኤል አበበን ምክር አዘልና የተቀደሰ ሃሳብ አጣመህና አወላግደህ በማቅረብ ልታወናብደነን የሞከርከው?
v አንተንና ስምህ እንደሚያመለክተው ምናልባት ሙስሊም ከሆንክ የአንተ አይነት አስተሳሰብ ያላቸውን ሙስሊሞች ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆናችሁን እንዴት ለማመን ይቻላል?
v አንተንና አንተን የመሰሉ ሰዎች በሚኖሩባት ኢትዮጵያ አወሊያን መሰረት አድርጎ የተነሳውን የሙስሊሙን እንቅስቃሴ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን አጥፍተው በኢስላማዊ ዜግነት ለመተካት ነው የሚፈልጉት ብለው የሚጠራጠሩና ስጋት ያለባቸው ኢትዮጵያዊያን ቢኖሩ ጥፋታቸው ምንድነው?
v በኢትዮጵያ ውስጥ በሃይማኖታቸው ዙሪያ ችግር የገጠማቸው ሙስሊሞቸ ብቻ መሆናቸውን በዝርዝር አስቀምጠሃል ነገር ግን የኢትዮጵያ ኦርተዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ከሃገር ተሰደው የሚኖሩት በሃይማኖታቸው ሙስሊም ስለሆኑ ነው?
v አቶ(ሼክ) ቶፊቅ ጀማል እነ እስክንድር ነጋ ፥ አንዷለም አራጌ ፥ ርዮት አለሙ ፥ አቶ በቀለ ጎረባና በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በየ እስር ቤቱ የሚሰቃዪት በሙሉ በሃይማኖታቸው ምስሊሞች ናቸውን?
መካሪ ህሊና ወይም ለመካሪነት የደረሱ ሰዎች በዙሪያህ ካሉ በዚህ ሃላፊነት በጎደለው አባባልህ በሀይማኖት ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት ከሙስሊሙ ጋር አብረው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሲያሰሙ የነበሩትን ወገኖች ሁሉ የሚያሳዝን አፀያፊ ስራ ሰርተሁልና በአደባባይ ይቅርታ ልትጠይቅ ይገባሃል::
ኢትዮጵያዊያን በገጠማቸው ማናቸውንም ችግሮችና የሰብዓዊ መብት ረገጣ ላይ አፋጣኝ መፍትሄ ሊያመጡ የሚችሉት በሃይማኖት ፥ በጎሳና በፖለቲካ ሪዮተ ዓለም ሳይሆን ከምንም በላይ በኢትዮጵያዊ ዜግነት ላይ መሰረት ሲያደረጉ ብቻ ነው።አንተ ግን ይሄ እውነታ እንዲገባህ ያልፈቀድህ በኢትዮጵያዊንት ላይ የምትቀልድ “ህፃን” ብቻ መስለኸኝ ነበር በዜግነት ክብር ላይ ያልህን ንቀት ካረጋገጥክልኝ በኋላ ግን “ሕፃን” ብቻ ሳትሆን “ከሕፃንም ሕፃን” እንጂ።
ኢሳት ለዜግነት ክብር ላላቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ የጋራ ሃብት በመሆኑ በኢሳት ክብረ በዓል ላይ የሙስሊም ተወካዮች ብቻ እና ብቻ የሚጋበዙበት መስጊድ አይደለም!!!
አስተዋይ: ታዛቢ