ዘ-ሐበሻ ዛሬ በቀዳሚ ዜናዋ ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ በታላቁ እና በጥንታዊው የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም አካባቢ ተነስቶ ስለነበረው ድንገተኛ የእሳት አደጋ መዘግቧ ይታወሳል:: አሁን በደረሰን መረጃ መሠረት ይህ እሳት ወደ ገዳሙ ሳይዛመትና ብዙ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ከቀኑ 11 ሰዓት አካባቢ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በገዳሙ ጫካ ውስጥ የተነሳው የዚህ እሳት መንስኤ በይፋ ባይረጋገጥም፣ መሬቱን ለጌሾ ልማት ዝግጁ ለማድረግ በአንድ የገዳሙ መነኰስ የተለኰሰው እሳት በአቅራቢያው በብዛት በሚገኙት የሐረግ ተክሎችና ሸምበቆዎች መቀጣጠሉ እንደኾነ ማኅበረ መነኰሳቱን ያነጋገሩ የዐይን እማኞች ገልጸዋል ሲል ሃራ ተዋህዶ ዘግቧል::
እሳቱ ወደ ሰማይ 100 ሜትር ከፍታ መያዙና ጭሱ በቅርብና በርቀት ላይ በሚገኙ ደሴቶች ውስጥ በሚኖሩ ነዋሪዎች በመታየቱ በተለይ በደቅ ደሴት ላይ የሚኖሩ ነዋሪዎች በጀልባ ወዲያው በመድረስ ከገዳሙ አባቶች ጋር በመሆን እሳቱ እንዳይዛመት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በስፍራው ከሚታየው ጢስና የተዳፈነ እሳት ጨርሶ መጥፋቱን ለማረጋገጥ ከሚደረግ እንቅስቃሴ በቀር የእሳት ቃጠሎው ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል::
እሳቱ ባይጠፋና ተዛምቶ ወደ ገዳሙ ቢዘልቅ ኑሮ በርከት ያሉ የኢትዮጵያ ታሪክና ቅርሶች ሊወድሙ ይችሉ ነበርና ወደፊትም እንዲህ ያለው አደጋ እንዳይከሰት አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ ዘ-ሐበሻ ሃሳቧን ታካፍላለች::