Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የአንድነትን ፓርቲና የምርጫ ቦርድ –ግርማ ሠይፉ ማሩ

$
0
0

ደብዳቤ ልውውጦች ዝርዝር ሁኔታ በማሰረጃ የተመሰረተ

ታህሳስ 19-20፡
*********

(ግርማ ሰይፉ)

ግርማ ሠይፉ ማሩ

አንድነት ፓርቲ ታህሳስ 19-20/2006 ዓ.ም ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ አካሄድ፡፡ ይህ ጠቅላላ ጉባዔ ልዩ የተባለበት ምክንያት የአንድነት አምስት ዓመት ስትራቴክ ዕቅድ ላይ በተቀመጠው መሰረት ፓርቲ ከ2007 ዓ.ም ምርጫ ቀደም ብሎ የአመራር ሽግሽግ በማድረግ ፓርቲውን በአዲሰ አመራር ወደ ምርጫ ይዞ ለመግባት በተቀመጠ ግብ መሰረት ነው፡፡ በዚህ ጠቅላላ ጉባዔ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው የፓርቲው ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጠዋል፡፡ ይህ ጠቅላላ ጉበዔውም የተለያዩ ውሳኔዎች አሳልፎዋል ከዚህ ውስጥ መሰረታዊ ሊባል የሚችለው ጉባዔው በሌለበት ወቅት ፕሬዝዳንቱን ማንሳት የሚያስችል ስልጣን ለብሔራዊ ምክር ቤቱ መስጠቱ ሲሆን ሌሎችም ለምሳሌ የወጣቶች፣ የሴቶች ጉዳይ ኃላፊዎች በስራ አስፈፃሚ ውስጥ እንዲካተቱ ያደረገ ሲሆን የተቀደሚ ፕሬዝዳንት ቦታም እንዲኖረው አድርጎዋል፡፡
አንድነት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔውን ባካሄደ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ አመራሩ በሚጠበቅበት ፍጥነት አልሄደም በሚል አለመስማማት የተፈጠረ ሲሆን በአጋጣሚ አንድነት ከመኢህአድ ጋር የሚያደርገው ውህደት ጉዳይ ውይይት በመጀመሩና ለመጠናቀቅ አፋፍ ላይ የደረሰ ሲሆን ይህንንም አጋጣሚ በመጠቀም የውህዱን ፓርቲ የሚመራ የአንድነት ተወካይ ዕጩ ፕሬዝዳንት በብሔራዊ ምክር ቤት ተሰይሞ ውሕደት ይጠናቀቃል ሲባል ውህደቱ እንደማይቻል በምርጫ ቦርድ በኩል ይፋ ተደረገ፡፡ ኢ/ር ግዛቸው ሸፈራው በዚህ አጋጣሚ ተጠቅመው ለወጣት አመራር ቦታ ይለቃሉ ሲባል ይህን ከማድረግ ይልቅ ለውህደት በሚጠራው ጉባዔ በዕጩነት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ይፋ አደረጉ፡፡
ሐምሌ 14-30፡
*********
በኢንጅነር ግዛቸው የሚመራው ስራ አስፈፃሚ በታህሳስ 19-20 የተካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ ሪፖርት ገቢ ያደረገው 7 ወር ዘግይቶ ሐምሌ 14 ቀን 2006 ዓ.ም ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች ይህ ሪፖርት እንዲዘገይ የተደረገው በአዲሱ አመራር ስለሚመስላቸው ነው ይህን ነጥብ መግለፅ የፈለኩት፡፡ ይህን ሪፖርት መሰረት አድርጎ ምርጫ ቦርድ ሐምሌ 25 ቀን ዘጠኝ ነጥቦችን አንስቶ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቆዋል እነዚህም፤

በጉባኤው ዕለት በቀረበው ሪፖርት የገቡት አላሰፈላጊ ቃላት እንዲወጡ፤
የፓርቲው ባንዲራ እንዲቀርብ፤
ፓርቲው አሻሽሎ ባቀረበው አንቀፅ 8 ንዑስ አንቀፅ 2 ሰር የተዘረዘረው ሃሳብ ግልፅ አለመሆኑ፤
የጉባዔተኛው ቁጥር አለመገለፁ፤
የፕሬዝዳንቱን በብሔራዊ ምክር ቤት መመረጥ ከህግ አንፃር ያለው ጉዳይ በሚመለከት፤
የፓርቲው የገቢ ምንጭ በአዋጅ ቁጥር 573/2000 መሰረት ያለመቀመጡ፤
የፓርቲ መፍረስ በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 573/2000 መሰረት ያለመቀመጡ
የፓርቲው አባልነት በውርስ እንደማይተላለፍ አለመገለፁ፤ እና
ፓርቲው ያቀረባቸው የፓርቲ አካላት ውስጥ የሚሳተፉ አባላት አድራሻና በኃላፊነት ለመስራ የተሰማሙበት ሰነድ ያለመቅረቡ፤

የሚሉት ናቸው፡፡ ለእነዚህ ለቀረቡት ጥያቄዎች ሐምሌ 30 ቀን 18 ገፅ ያለው ማብራሪያ ተሰጧዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የመኢህአድና የአንድነት ውህደት አሰመልክቶ ከምርጫ ቦርድ ጋር በሚደረግ ውይይት በአንድነት በኩል ምንም ችግር እንደሌለ ነገር ግን ቦርዱ ሲሰበሰብ ውሰኔ እንደሚሰጥ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቶ የመኢህአድ ጠቅላላ ጉባዔ ኮረም ሳይሞላ የተካሄደ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም በሚል ሰበብ ውህደቱ እንደማይሳካ በምርጫ ቦርድ ተገለጠ፡፡ ይህንንም ተከትሎ የአንድነት ስራ አሰፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የነበሩ አምሰት ከፍተኛ አመራሮች በሰራ አሰረፃሚነት ላለማገልገል መወሰናቸውን ገልፀው መልቀቂያ ደብደቤ አሰገቡ፡፡ ኢንጂነር ግዛቸውም በምትካቸው ሌሎች አመራሮቸን በመሰየም ስራቸውን ለመቀጠል ሞከሩ፡፡
ጥቅምት 3፤
********
ኢንጂነር ግዛቸው ሸፈራው የብሔራዊ ምክር ቤቱን ጠርተው በጥቅምት ሁለት ካቢኔያቸውን ማሰናበታቸውን በመግለፅ ከውስጥና ከውጭ በደረሰባቸው ጫና ለፓርቲው እልውና ሲሉ ጠቅላላ ጉባዔ የሰጣቸውን ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ እንደወሰኑ ለምክር ቤት አቀረቡ፡፡ ምክር ቤቱም ኃላፊነት ለመልቀቅ መወሰናቸው ተቀብሎ ፓርቲው አመራር በቀጣይ እንዴት መሆን አለበት በሚል ባደረገው ከፍተኛ ውይይት ፓርቲው ለአንድ ቀንም ያለ አመራር ማድር እንደማያስፈልግ ታምኖበት ከዚህ በፊት የመኢህአድና አንድነት ውሕደት አስመልክቶ ለዕጩነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን ጨምሮ ሌሎች ተጨማሪ ዕጩዎች በፈቃደኝነት ቀርበው ውድድር ተደርጎ በሚስጥር ደምፅ አስጣጥ በተደረገ ምርጫ አቶ በላይ ፍቃዱን በፕሬዝዳንትነት ሰየመ፡፡ በሳምንቱ ጥቅምት 10 ደግሞ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴውን ሰይሞ ስራውን በይፋ ጀመረ፡፡
ጥቅምት 19-21፤ የምርጫ ቦርድ ፅ/ቤት ምክትል ኃለፊ ጥቅምት 19 በተፃፈ ደብዳቤ አንድነት ፓርቲ ያደረገው የፕሬዝዳንት ምርጫ በታሕሳስ 19-20 በተደረገው ጉባዔ የተሻሻላው ደንብ በቦርዱ ባለፀደቀበት ሁኔታ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም የሚል ስሜት ያለው ደብዳቤ ሲፃፍልን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ጥቅምት 20 የቦርዱ ፅ/ቤት ኃላፊ ጋር ለመነጋገር የፓርቲ ወኪሎች ስንሄድ የቦርዱን ጥቅምት 19 ያደረገውን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ውሳኔ ደረሰን፡፡ ፓርቲያችን ሁለቱን ደብዳቤዎች መሰረት አድርገን ከቦርዱ ፅ/ቤት ኃላፊ ጋር ባደረግነው ውይይት ቦርዱ በጥቅምት 20 ላቀረባቸው ጥያቄዎች መልስ ስጡ ዋናውም የቦርዱ ጥያቄ ነው ተብለን በመግባባት መንፈስ ተለያየን፡፡ ቦርዱ ጥቅምት 19 ተሰብስቦ ለፓርቲያችን ያቀረበልን ጥያቄዎች፤
1. ሪፖርቱ ለምን 7 ወር ዘገየ፤
2. የጠቅላላ ጉበዔ አባላት ቁጥር በደንቡ ውስጥ የለም እና
3. የፕሬዝዳንት መረጣ ለማድረግ ጠቅላላ ጉባዔ ለብሔራዊ ምክር ቤት ውክልና የሰጠበት አግባብ ከዲሞክራሲያዊነት እና ከአባላት ተሳትፎ አንፃር ማብራሪያ ይፈልጋል፤
የሚሉት ናቸው፡፡
ለእነዚህ የቦርዱ ጥየቄዎች እና ጥቅምት 19 በቦርዱ ምክትል ኃላፊ ለቀረቡት ህገወጥ ጥያቄዎች መልስ አዘጋጅተን ጥቅምት 21 2007 ዓ.ም ለቦርዱ ፅ/ቤት ገቢ አደረገን፡፡
ህዳር 10 -19/2007፤
*************
የምርጫ ቦርድ በጥቅምት 20 ላቀረባቸው ጥያቄዎች በጥቅምት 21 ለሰጠነው መልስ ገምግሞ የሚከተሉትን ውሳኔዎች የያዘ ደብዳቤ ህዳር 10 2007 ዓ. ም ለፓርቲያችን እንዲደርስ አደረገ፡፡ እነርሱም
1. ሪፖርት መዘግየቱ አግባብ ያለመሆኑን ጠቅሶ ለወደፊት ሪፖርቶች በወቅቱ ገቢ እንዲደረግ፤
2. የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ቁጥር ተወስኖ በደንብ ውስጥ መግባት እንደሚያስፈልግ እና
3. የፕሬዝዳንቱን ምርጫ አስመልክቶ ጠቅላላ ጉባዔው ለብሔራዊ ምክር ቤት ውክልና የሰጠበትን አግባብ በቅንንት እንደሚያየው ገልፆ፤
በተራ ቁጥር 2 ለተጠየቀው ጥያቄ መልስ ሲቀርብ ውሳኔ እንደሚሰጥ የሚጠቅስ ነበር፡፡
ህዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ቁጥር 320 እንደሆነ እና ከዚህ ውስጥ 161 ሲገኝ (ሃምሳ ከመቶ በላይ)ምልዓተ ጉባዔ እንደሆነ ገልፀን ለቦርዱ አስገባን፡፡ በዚሁ መሰረት መልስ ይሰጡናል ብለን ስንጠብቅ፣ በቦርዱ በኩል ደግሞ ዝምተው ስበረታብን የቦርዱን ፅ/ቤት ኃላፊ እንዲሁም የቦርዱን ሰብሳቢ ሰናነጋግር ደንብ የሚሻሻላው በደብዳቤ ሳይሆን ይህን ማድረግ በሚችለው በጠቅላላ ጉባዔው መሆኑን በተዘዋዋሪ ገለፁልን፡፡ በዚህ ውይይት ዘወትር የሚሰጠን ምክር አርፋችሁ ለምርጫ ዝግጅት አድርጉ እኛ በቅንንት ነው የምናየው የሚሉ የማግባቢያ ንግግሮች ነበሩት፡፡ ይህንን ግን በፅሁፍ እንዲያደርጉት ባደረግነው ጉትጎታ ህዳር 19 ቀን ቦረዱ ያለውን የመጨረሻ ጥያቄ በፅሁፍ ሰጠን፡፡ ይኽውም የጠቅላላ ጉባዔ አባላትን ቁጥር በደንብ ውስጥ አካቱና አምጡ የሚል ነው፡፡ ቦርዱ ከዚህ በኋላ ባደረገው የደብደቤ ልውውጥ የህዳር 10 እና ህዳር 19 ደብዳቤ ሆን ተብሎ አይጠቅስም፡፡ የቦርዱን ቅንነትና ሆደ ሰፊነት የሚለውን አባባል ያልተመቻቸው አባላት ጠቅላላ ጉባዔ አባላት ተጠርተው ለጉዳዩ መቋጫ ለመስጠት በመወሰን ጉባዔ እንዲጠራ ተወሰነ፡፡
ታህሳስ 3-4፤
*********
የአንድነት ፓርቲ በቦርዱ በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የጠቅላላ ጉባዔ ኮረም በደንብ ውስጥ ለማስገባት ብቻ መጥራት ተገቢ አይደለም በሚል እምነት ከጉባዔ አባላት ቁጥር ከማካተት በተጨማሪ ያሉ የዞን አመራሮችን ጨምሮ በምርጫ ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት የሚያደርግበት በፓርቲያችን ላይ በምርጫ ቦርድ በኩል በሚዲያ እየተፈጠረ ያለውን ብዥታ ለማጥራት የሚያሰችል ደማቅ ጉባዔ ተካሄደ፡፡ መፈክራችንም “ምርጫ 2007 ለለውጥ” የሚል ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የተቃዋሚዎች ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሸበረቀ ጉበዔ አካሄደን የሚከተሉትን ውሳኔዎች ጉባዔ አሳለፈ፤
1. የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ቁጥር 320 እንዲሆን እና ኮረም 50 ከመቶ ሲደመር አንድ እንዲሆን፤
2. የብሔራዊ ምክር ቤቱ የፓርቲውን ፕሬዝዳንት ለመምረጥ የሄደበት መንገድ ህገ ደንባዊ መሆኑን፤
3. በቀጣይ ምርጫ ቦርድ በጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔ ላይ ጥያቄ የሚያነሳ ቢሆን ብሔራዊ ምክር ቤቱ የጠቅላላ ገባዔውን ወክሎ ምላሽ እንዲሰጥ የሚሉት፤
ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ታህሳስ 10፤
**********
የጠቅላላ ጉበዔውን ሪፖርት ታህሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም ለቦርዱ ፅ/ቤት ገቢ የተደረገ ሲሆን ቦርዱ ይህንን ችላ በማለት ፍፁም ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ በዕለቱ ምሽት የቦርዱ ኃላፊዎች በሚዲያ ቀርበው በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ችግር እንዳለ የሚገልፅ መግለጫ ይሰጣሉ፡፡ በማግስቱ ቅዳሜ ደውለው ደብዳቤ እንድንወስድ ይነግሩናል፡፡ በታህሳስ 10 ቦርዱ ተሰብስቦ በወሰነው መሰረት የጠቅላላ ጉባዔ ሪፖርት በ7 ቀን ውስጥ እንድታስገቡ የሚል ነበር፡፡ ይህን ደብዳቤ አስመልክቶ እና በሚዲያ የሰጡትን መግለጫ አስመልክቶ ከቦርዱ ስብሳቢ ጋር ባደረግነው ውይይት ያቀረብነውን ሪፖርቱን በአጭር ጊዜ ተሰብሰበው ውሳኔ እንደሚሰጡት መግለጫ በክፋት ሳይሆን በቅንንት እንደሆነ ይገልፁልናል፡፡ ይህ እንደማይሆን ግን ምልክቶች እያየን ነበር፡፡ የቦርዱ ፅ/ቤት ኃላፊና ምክትላቸው በተለያየ መልኩ ከፓርቲያችን ውስጥ ቅሬታ ተሰምቶናል የሚሉ ህገወጦች ጋር በቢሮዋቸው እንደሚዶልቱ እየሰማን ነበር፡፡ በግንባርም በኃላፊው ቢሮ ከግለሰቦቹ ጋር ሲመክሩ አግኝተናቸዋል፡፡
ታህሳስ 27 -30፡
***********
ቦርዱ ተሰብሰቦ ያቀረብነውን ሪፖርት መርምሮ መልስ ይሰጣል ብለን በቅንንት ስንጠብቅ ታህሳስ 26 እሁድ በስልክ ተደውሎ የቦርዱ ኃላፊዎች ለውይይት እንደሚፈልጉን ይነገረናል፡፡ የዚያኑ እለት እሁድ በፓርቲያችን ለሆዳቸው ያደሩ ባንዳዎች አራት ኪሎ በሚገኝ ካፍቴሪያ ተሰብሰበው ፊርማ ተፈራርመው ለቦርዱ ገቢ አድርገዋል፡፡ በእሁድ ቀን ማለት ነው፡፡ ታታሪው ምርጫ ቦርድ አንድነትን ለማናጋት እሁድን ጨምሮ ሌት ከቀን ይሰራል፡፡ ታህሳስ 27 ቀን 2007 ዓ.ም ቦርዱ ፅ/ቤት ስንገኝ ካሜራ ደቅነው ከአቶ የማነአብ አሰፋ እና ከአቶ አየለ ሰሜነህ ጋር “ውይይት” እንድናደርግ ግብዣ ያደርጉልናል፡፡ ዓላማው በምሽት ቦርዱ ሊሰጠው ላሰበው ውዥንብር መፍጠሪያ መግለጫ የቪዲዮ ግብዓት ለማግኘት የነበረ ሲሆን መኢህአዶች በየዋህነት በቪዲዮ ተቀርፀው ሲቀርቡ እኛ ከእነዚህ ሰዎች ጋር በምርጫ ቦርድ መድረክ የምናደርገው ውይይት እንደሌለ፤ ቦርዱ ያሰገባነውን ሪፖርትና ግለሰቦች ያቀረቡትን ሪፖርት መርምሮ ውሳኔውን እንዲያሳውቅ ብቻ መሆኑን ገልፀን ተመለስን፡፡ በምሽቱ የቦርዱ ምክትል ሰብሰቢ የውስጥ ችግራቸውን እንዲፈቱ ልናስማማቸው ሞክረን አልተሳካም፤ የታህሳስ 19-20 ሪፖርት 7 ወር አዘግይተው አስገብተዋል፤ የፕሬዝዳንቱ ምርጫ ህገወጥ ነው፤ የሚሉ መግለጫዎችን በመስጠት ህዝቡን ብዥታ ውስጥ ለመክተት ሞከሩ፡፡ ይህን ሲያደርጉ ቦርዱ ስብሰባ የተጠራው ለታህሳስ 28 ሲሆን ቦርዱ ከመሰብሰቡ በፊት በቅድሚያ በማን አለብኝነት የቦርዱ ምክትል ሰብሰቢ የግል ውሳኔያቸውን አስታውቀው ለቀሪዎቹ የቦርድ አባላት ዋጋ ቢስነት በህዝብ ፊት አረጋገጡ፡፡
በታህሳስ 28 በምሳ ሰዓት ተደውሎ የቦረዱን ውሳኔ ለመስማት በ9፡00 ሰዓት እንድንገኝ ጥሪ ተደርጎልን ስንሄድ ገዛኽኝ አዱኛ የሚባል የወረዳ ስድሰት አባል እና እራሱን የወረዳ ሰድስት ዕጩ አድርጎ ያቀረበ 10+1 ያጠናቀቀ እና ሰፊው የሚባል የወረዳ 7 አባልና አራሱን ለ2007 ምርጫ የወረዳ 7 ዕጩ አድርጎ አቅርቦ ያልተሳካለት አኩራፊ አኩራፊ የአንድነት አባላትን ወክለው እንዲገኙ በአኩራፊዎች ተወክለው ነበር፡፡ ይህ ቡድን ምርጫ ቦርድ ከመምጣቱ በፊት በአምባሳደር መናፈሻ ድራፍት ቢራ እየተጎነጩ በአቶ ትዕግሰቱ አውሎም መመሪያ ሲሰጣቸው ነበር፡፡
ቦርዱ ፅ/ቤት ያለውን ሁኔታ ስንረዳው አሁንም ለኢቲቪ የቪዲዮ ግብዓት ለማግኝት ካልሆነ ትርጉም እንደሌለው በመረዳታችን የቦርዱ ውሳኔ በፅሁፍ እንዲሰጠን ጠይቀን ወደ ቢሮዋችን ተመለስን፡፡ በምሽት ዜና እና በቅርቡ በከፍተኛ ወኔ ገዢውን ፓርቲ ለመከላከል የቆመው የኢህአዴግ ሚዲያ የሆነው ሬዲዮ ፋና የቦርዱ ውሳኔ ነው ያሉትን ነገር ግን ቦርዱ ከመሰብሰቡ በፊት በቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ በሚዲያ የተነገረውን ውሳኔ በትንተና አቀረቡት፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጊያም ከንፈራች እስኪደርቅ ድረስ አንድነት ላይ አለ የሚሉትን ክስ ሁሉ አዘነቡት፡፡ ታህሳስ 29 የገና በዓል በመሆኑ ታህሳስ 30/ 2007 ዓ.ም ጠዋት ማልደን ምርጫ ቦርድ ተገኘተን በሚዲያ የነዙትን ክስ በፅሁፍ እንዲሰጡን ስንጠይቅ ደብዳቤ እየተዘጋጀ እንደሆነ ገልፀውልን በ5፡00 ሠዓት ደብዳቤ ሰጡን፡፡ አባላቶቻችን ቁጭ ብሎ ተረቆ የተፃፈ ደብዳቤ አስገራሚው በሆነ ሁኔታ በታህሳስ 28 ተደርጎ ወጭ እንዲሆን ተደርጎ ቀን ተፃፈበት፡፡ እዚህ ጋ የቦርድ ኃላፊዎች የበታች ሰራተኞችን ምን ያህል ከህግ ውጭ እንደሚያሰሩ ነው፡፡ የቦርዱ ፅ/ቤት ምን ያህል ለመዋረድ እንደተዘጋጀ የሚያሳይ ነው፡፡ ለማነኛውም ታህሳስ 30 የደረሰን ደብዳቤ አራት ነጥቦች ያሉት ለማስመስል ቢሞክርም ሁለት ጥያቄዎች ናቸው ያሉት፡፡ እነርሱም
1. የታህሳስ 19-20 ሪፖርት ለምን ዘገየ የሚል እና
2. የፕሬዝዳንቱ ምርጫ የፓርቲውን ህገ ደንብ የተከተለ አይደለም የሚል ነው፡፡
የሚያሳዝነው ነገር ቦርዱ የታህሳስ 3 ቀን 2007 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባዔ ሪፖርት ለመመርመር ተሰብሰቦ የታህሳስ 19-20/2006 ዓ.ም ሪፖርት ለምን ዘገየ ማለቱ ብቻ ሳይሆን በቅንንት ተቀብዬዋለሁ ያለውን የፕሬዝደንት ምርጫ በድጋሚ ማንሳቱ ነው፡፡ በግልፅም ቦርዱ የአንድነትን ሪፖርት በጥልቀት ገመገምኩ ይበል እንጂ እንዳልገመገመው ማሳያ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቦርዱ ወሰነ የተባለው እና የቦርዱ ምክትል ሰብሰቢ ከቦርዱ ስብሰባ በፊት በሚዲያ የሰጡት መግለጫ መመሳሰል ብቻ ሳይሆን ቦርዱ ሊመረምረው ከተቀመጠው ሪፖርት ይዘት የወጣ ውሳኔ አሳለፈ መባሉ ነው፡፡
ስለዚህ የታህሳስ 19-20/2006 ዓ.ም ሪፖርት ለምን ዘገየ ከአሁን በፊት በቂ መልስ ተሰጥቶታ ቦርዱ እንደተቀበለው ማስታወስ እና አንድነትም በተከታይ ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ በሰባት ቀን ሪፖርት ማስገባቱ ነው፡፡
ጥር 1-3፤
********
አንድነት ፓርቲ ለመጨረሻ የደረሰው ደብደቤ ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ 11፡45 (ከሰራ ሰዓት ውጭ) የደረስን ህገወጥ ደብዳቤ በጥር 3/2007 ዓ.ም ለሚደረገው ጠቅላላ ጉባዔ የምርጫ ቦርድ ታዛቢ መላክ እንደማይችሉ ገልፀው ለዚህም የሰጡት ሰበብ በእነ አየለ ሰሜነህ የሚመሩ አባላት ሌላ ጠቅላላ ጉባዔ በሳሬም ሆቴል በመጠራቱ ሁለት ቦታ ጉባዔ ታዛቢ መላክ አልችልም የሚል ነው፡፡ በመሰረቱ የምርጫ ቦርድ በእጁ በሚገኝው የፓርቲያችን ደንብ አባላት ጠቅላላ ጉባዔ ሊጠሩበት የሚችሉበት ስርዓት በግልፅ ተቀምጦ እያለ ከዚህ ውጭ የፓርቲውን ጉባዔ ለማደናቀፍ ምን ያህል እየተሰራ እንደሆነ ግልፅ ማሳያ ነው፡፡ አንድነት በማግስቱ መገኘት ባይፈልጉም ጉባዔው በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት እንደሚቀጥል ጥር 2/2007 ዓ.ም እንዲያውቁት ተደርጎዋል፡፡ በዚሁ መስረት አድነት ጥር 3/2007 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ይህን መስመር የፃፍኩት ጉባዔዬው አመስራጭ ኮሚቴ ሰይሞ ሲያጠናቅቅ ነው፡፡ ትግሉ ይቀጥላል……….. የደብዳቤው ልውውጥም ይቀጥላል፡፡ ይህ ታሪካዊ ዘገባ ይሆናል፡፡

ግርማ ሠይፉ ማሩ (ጥር 3/ 2007)

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>