Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የአርቲስቶቻችን ክፍያ እና ግነቱ –እውን የአርቲስቶቻችን ክፍያ እንደሚባለው ነው? ነው ወይስ ያጋንኑታል?

$
0
0

የቁምነገር መጽሄት ትንታኔ

መነሻ

በሀገራችን የኪነ ጥበብ ሙያ ውስጥ በሙያው አንቱ የተባለ አንድ አርቲስት ከዓመታት በፊት በአንድ ፊልም ላይ እንዲተውን ጥያቄ ይቀርብለታል፡፡ ጥያቄውን ተቀብሎ በክፍያውም ተስማምቶ ፊልም ይሰራል፡ ፡ የፊልሙ ምረቃ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ከፊልሙ ፕሮውዲውሰሮች መሀከል አንዱ ወደ እዚህ አንጋፋ አርቲስት መጥቶ ስለፊልሙ ምረቃ ሥነሥርዓት ዝግጅት ያጫውተዋል፡፡

ስለ ፊልሙ ምረቃ ዝግጅት ካብራራለት በኋላ ከፊልሙ የምረቃ ቀን ቀደም ብሎ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ስለሚደረገው የማስታወቂያና ገበያ መጥሪያ እቅድ በመንገር የእሱም ትብብር በዚህ ረገድ እንደሚያስፈልግ ይነግረዋል፡ ፡ አንጋፋው አርቲስት ስለ እቅዱ ሁኔታ በጥሞና ሲያዳምጥ ከቆየ በኋላ ‹ታዲያ እኔ በዚህ በኩል ምን አስተዋፅኦ ላደርግ እችላለሁ?› የሚል ጥያቄ ያቀርብለታል፡፡

ፕሮውዲውሰሩ ፊልሙ የተሰራው በአነስተኛ በጀት ቢሆንም ከፍተኛ ወጪ እንደወጣበትና የፊልሙ ተዋንያንም ከፍተኛ ተከፋይ እንደሆኑ የሚገልፅ ማስታወቂያ በየሬዲዮና ጋዜጣ ላይ ለማስነገር አስበናል› ይለዋል፡፡ ‹እናስ?› የአንጋፋው አርቲስት ጥያቄ ነበር፡፡ ‹እናማ አንተም የፊልማችን ዋና መሪ ተዋናይ በመሆንህ የእስከ ዛሬውን የፊልም ክፍያ ሪከርድ እንደሰበርክና ከፍተኛ ክፍያ እንደተከፈለህ አስመስለን ለማስነገር ስላሰብን በዚህ በኩል እንድትተባበረን ነው› አንጋፋው አርቲስት ሁኔታው አልገባውም፡፡ ‹ስለሁኔታው ምናልባት ጋዜጠኞች ደውለው ቢጠይቁህ ግር እንዳይልህ ብዬ ነው› በማለት ሁኔታውን ቀለል አድርጎ ነግሮት ይለየዋል፡፡ ከቀናት በኋላ እሱም ባልሰማው ሁኔታ ‹የሀገራችን የፊልም ክፍያ ሪከርድ ተሰበረ› በሚል ርዕስ በአንድ የኤፍ ኤም ጣቢያ ላይ ስሙ ተጠቅሶ ፊልሙን ከሰራበት ክፍያ በሶስት እጥፍ ከፍ ያለ ገንዘብ እንደተከፈለው ተጠቅሶ ለህዝብ ይተላለፋል፡፡ ይህንን የሬዲዮ ወሬ የሰማችው የአርቲስቱ ባለቤት በማግስቱ ባለቤቷን ታኮርፈዋለች፡፡ ‹ምነው?› ሲላት ‹ለምንድነው በየፊልሞቹ ላይ ስትሰራ የሚከፈልህን ክፍያ ዋጋ የምትደብቀኝ?› ትለዋለች፡፡ አርቲስቱ ውሸት ያደገበት ነገር ባለመሆኑ ‹እንዴት ነው አንቺን የምዋሽሽ?› በማለት ጥያቄውን በጥያቄ ይመልሳል፡፡

በሬዲዮ የሰማችውን የሪከርድ ክፍያ ዜና ዋቢ አድርጋ ስትነግረው የሰራው ስህተት ቁልጭ ብሎ ታየው ፡፡ ለማስታወቂያና ለገበያ መሳቢያ በሚል በቃል ቀለል ተደርጎ የተነገረው ነገር ውሎ ሳያድር ትዳር ለማፍረስ የሚበቃ ወሬ መሆኑ ታወቀው፡፡‹እኔስ ለባለቤቴ እውነቱን በመናገርና በማስረዳት ችግሩን ተወጣሁት፤ በሬዲዮ አማካይነት የተዋሸው የኢትዮጵያ ህዝብንስ እንዴት ብዬ ነው የማሳውቀው?› የአንጋፋው አርቲስት አቤቱታ ነበር፡፡

የአርቲስቶች ክፍያ እንደተባለው ነውን?

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአንድ የጥበብ ስራን ጥበባዊ ዋጋ ከክፍያ ጋር የተያያዘ መሆኑን ለማሳየት በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ አንደ አንድ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው ለሥራው የወጣውን ወጪ ከፍ አድርጎ በማቅረብ እየሆነ ነው፡፡ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ሥራ ከፍተኛ ተመልካች አልያም አድማጭ ያገኛል በሚል ስሌት የሚቀርበው የክፍያ አሃዝ ግነት ጥበቡን ከመጥቀም ይልቅ እየጎዳው እንደውም ‹ይሄ ነው እንዴ ይህንን ያህል ወጪ ወጣለበት የተባለው ፊልም/ሙዚቃ?› እስከመባልና ለኪሳራ በር ሲከፍት ይታያል፡፡ ከፍተኛ በጀት ተመድቦላቸው የሚሰሩ ፊልሞችና የሙዚቃ ሥራዎች በሰለጠኑት ሀገራት ከፍተኛ ተቀባይነትና ገቢ ሲያገኙ ይስተዋላል፡፡ የወጣው ከፍተኛ ወጪም የስራውን ደረጃ ለመጠበቅ ስለመዋሉ ሌላ ተናጋሪ ሳይሆን ፊልሙ ወይም የሙዚቃ ሥራው አፍ አውጥቶ ሲናገር ይታያል፡፡ በኛ ሀገር ያለው እውነታ ግን ከዚህ በተገላቢጦሽ ያለ ይመስላል፡፡ ከፍተኛ ወጪ ወጣባቸው የሚባሉትና የሚነገርላቸው ፊልሞች እና ሙዚቃዎች ተገቢ የሆነ የተመልካችና የአድማጭ አትኩሮት ሲነፈጋቸው በአነስተኛ በጀት ብቻ ሳይሆን በጀማሪና ወጣት ተዋንያን የሚሰሩት ሥራዎች ገበያውን ሲቆጣጠሩት ይታያል፡፡

የማስታወቂያ ሥራ አንድን የጥበብ ስራ በሚፈለገው ደረጃ ወደ አድማጭና ተመልካች እንዲደርስ ለማድረግ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ ያለው ቢሆንም ሥራን በአግባቡ ሳይሰሩ በማስታወቂያ ሥራ ላይ ብቻ የማተኮሩ ሁኔታ ከፈረሱ ጋሪው እንዲቀድመው ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ የተጋነኑ አልፎ አልፎም ሀሰተኛ የክፍያ ዜናዎች በይፋ በመገናኛ ብዙሃን ማስነገር ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ጠቀሜታ እንደነበረው የሚናገሩ የፊልምና የሙዚቃ ፕሮውዲውሰሮች አሉ፡፡ በዚህ መንገድም ገና እያቆጠቆጠ ከነበረው የሀገራችን ፊልም ኢንዱስትሪ ላይ ጠቀም ያለ ገቢ የሰበሰቡ ፕሮውዲውሰሮች ስለመኖራቸው ይነገራል፡፡ ቁም ነገሩ ግን በዚህ መንገድ አንዱ ተጉዞ ተጠቃሚ ስለሆነ ብቻ ሁሉም ይህንን ጎዳና መከተል አለባቸው ወይ ? የሚለው ነው፡፡ ከዓመታት በፊት ከመቶ አስከ አምስት መቶ ሺህ ብር ወጪ እንደወጣበት ይገለፅ የነበረው የፊልም ስራ በአጭር ጊዜ ከአንድ ሚሊዮን እስከ ሃያ ሚሊዮን ብር ‹ወጣበት› ሲባል በየመገናኛ ብዙሃኑ ለህዝብ ሲተላለፍ እያደመጥን ነው፡፡ በሙዚቃው ዘርፍም እስከ አራት ሚሊዮን ብር ‹ተከፈለ› የሚሉ ዜናዎች ይነገራሉ፡፡ እውነታውስ?

ጉዳዩ በፊልምና ሙዚቃ ሙያዎች ውስጥ ጎልቶ ይታይ እንጂ በስፖርቱ ዘርፍም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ‹እከሌ የተባለው ተጫዋች በዚህ ያህል ክፍያ ወደ እዚህ ክለብ ተዛወረ › የሚሉ ዜናዎችን በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ ማድመጥ የተለመደ ሆኗል፡፡ ከተጫዋቾች ዝውውር ጋር ተያይዞ ያለውን ጉዳይ አሳሳቢነት መነሻ በማድረግም መፅሔታችን የሽፋን ርዕሰ ጉዳይ አድርጋው ነበር፡፡ በቁም ነገር መፅሔት 13ኛ ዓመት ቅፅ 13 ቁጥር 185 ላይ እንደገለፅነው እስካሁን ይፋ በተደረጉት መረጃዎች መሠረት በዚህ ዓመት ክለቦቹ በአጠቃላይ ለተጫዋቾቹ ወጭ ያደረጉት የገንዘብ መጠን 28 ሚሊዮን ብር ገደማ ነው፡፡ ይህ ቁጥር ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡናና ደደቢት ይፋ ያላደረጉትን የዝውውር ወጭ ያላካተተ ነው፡፡ የነዚህ ክለቦች ወጭ ሲደመር ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ ይሁንና ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ሀገሪቱ የምታገኘው ምንም ጥቅም የለም፡፡፡ የዝውውር (የፊርማ) ወጭ በከፍተኛ ሁኔታ (ካላቸው አቅም አንጻር) የሚያወጡት ክለቦችም ሆኑ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን የሚያጡት ክለቦች ከጥቅማቸው የባሰ ኪሳራን ያስተናግዳሉ፡፡
መንግስት በተጫዋቾቹ ላይ የሚቆርጠው ግብር እንደማንኛውም የመንግስት ሠራተኛ በደሞዛቸው ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በአሳዛኝ ሁኔታ በኛ ሀገር ለአንድ ተጫዋች የሚከፈለው ደሞዝ ከፍተኛው በወር 3ሺ 500 ብር ነው፡፡ በ2 ዓመታት ውል ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ከንግድ ባንክ እግር ኳስ ክለብ የተከፈለው ፊሊፕ ዳውዝ የወር ደሞዙ ተብሎ ፔሮል ላይ የተቀመጠው ብር 2800 ብቻ ነው፡፡ መንግስት ግብር የሚቆርጠውም ከ1 ሚሊዮን ብር ላይ ሳይሆን ከወርሃዊ ደሞዙ ላይ ነው፡፡ የሌሎቹም ተጫዋቾች ተመሳሳይ ነው፡፡ ደመወዛቸውና ለፊርማ ተብሎ የሚሰጣቸው ክፍያ የማይገናኝ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ሀገሪቱ ከእግር ኳስ ተጫዋቾች ዝውውር ማግኘት የሚገባትን ገንዘብ እያገኘች አይደለም፡፡ ለውጭ ሃገር ተጫዋቾች የሚከፈለው ገንዘብ ደግሞ ወደ ዶላር ተመንዝሮ ከሀገር የሚወጣ ብር መሆኑ ሲታሰብ ነገሩን የባሰ ያደርገዋል፡፡

የተሻለ ገቢን ለማግኘት ሲባል በማስታወቂያ ሰበብ የተሳሳተና ሀሰተኛ መረጃን ለህዝብ ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን የግለሰቦችን ዝና አላግባብ መገንባትም ከሙያ ስነ ምግባር አንፃር እንዴት እንደሚታይ ግልፅ አይደለም፡፡ በተለይም ግለሰቦች ባገኙት ልክ ግብር መክፈላቸው ተዘንግቶ ያላገኙትን ገቢ እንዳገኙ አስመስሎ ማስነገር ከህግ አንፃር እንዴት እንደሚታይ ያነጋግራል/ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የስራ ኃላፊ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ በገፅ 8 ላይ ይመልከቱ /፡፡
የቁም ነገር መፅሔት የጋዜጠኞች ቡድን ባለፉት ዓመታት በመገናኛ ብዙሃን ስም ተጠቅሰው የተላለፉ የአርቲስቶች ክፍያ ዋጋዎችን ለመመርመርና እውነተኛነቱን ለማረጋገጥ ሙከራ አድርጓል፡፡ ሙከራው ራሳቸው አርቲስቶቹ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ቀርበው የተናገሩትና በይፋ ያረጋገጡትን ይጨምራል፡፡
bedlu
አርቲስት ሔለን በድሉ
ይህቺ ወጣት ተዋናይት በተለያዩ ፊልሞች ላይ ስትሰራ ትታወቃለች፤ በቅርቡም በተጠናቀቀው ሰው ለሰው ድራማ ላይ ስትተውን የነበረችው ሔለን በቅርቡ ይወጣል ያለችው አዲስ ፊልም ላይ እንድትተውን 80ሺህ ብር እንደተከፈላት መፈራረሟን በጥር ወር 2006 ከታተመው ላይፍ መፅሔት ጋር ያደረገችው ቃለ ምልልስ ላይ ተናግራለች፡፡

አርቲስት መሐመድ ሚፍታ

መሐመድ ቀደም ሲል በሞዴሊንግ ሙያ ላይ የተሰማራና በተለያዩ መድረኮች ላይ የሚታይ ወጣት ነው፡፡ የዛሬ ሶስት ዓመት የተጠናቀቀው ገመና የቲቪ ድራማ ላይ በመተወን ወደ ፊልሙ ዓለም የተቀላለቀለው መሐመድ ወደ እውቅና ማማ ላይ የወጣው ወዲያውኑ ነው፡፡ መሐመድ ከፊልም ስራው በተጨማሪም የተለያዩ ድርጅቶችን ምርት ለማስተዋወቅ የማስታወቂያ ሞዴል ሆኖ የሚሰራ ሲሆን የዛሬ ዓመት ገደማ ‹ስማድል› ለተባለው ሞባይል ለሁለት ዓመት የማስታወቂያ ሞዴል ለመሆን 400 ሺህ ብር እንደተከፈለው በመጋቢት ወር በተላለፈ የታዲያስ አዲስ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ቀርቦ ተናግሯል፡፡

ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ደግሞ ተቀማጭነቱ ሳውዲ አረቢያ የሆነ አንድ የንግድ ተቋም መሀመድን በ30 ሺህ ዶላር /600ሺህ ብር/ የማስታወቂያ ሞዴል ሆኖ እንዲሰራ መፈራረሙ በኢትዮፒካ ሊንክ ፕሮግራም ላይ ለህዝብ ተላልፏል፡፡
daniel
አርቲስት ሚኪያስ መሐመድ

ባለ ታክሲው በተሰኘው የመጀመሪያ ፊልሙ ተቀባይነትን ያገኘው ወጣቱ ተዋናይ ሚኪያስ መሐመድ በቅርቡ ተመርቆ ለእይታ በበቃው የመቅደስ በቀለ ማክዳ ‹ሊነጋ ሲል› ፊልም ላይ በመሪ ተዋናይነት ይሰራል፡፡ ከዚሁ ፊልም ምረቃ ጋር ተያይዞ በታዲያስ አዲስ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ የተላለፈው ዘገባ እንደሚያመለክተው ከሆነ ሚኪያስ መሐመድ በዚህ ፊልም ላይ ለመስራት ብር 400 ሺህ ተከፍሎታል፡፡ ይህንን ክፍያ ስለማግኘቱም ሚኪያስ በፕሮግራሙ ላይ ቀርቦ አረጋግጧል፡፡
helen berehe
ድምፃዊት ሔለን በርሄ
ወጣቷ አቀንቃኝ ሔለን በርሄ የመጀመሪያ አልበሟን ተከትሎ የተለያዩ ፊልሞችን የማጀቢያ ሙዚቃ እንድትሰራ ጥያቄ የቀረበላት አርቲስት ነች፡፡ በ2003 ዓ.ም ተመርቆ ለእይታ የበቃውን ‹ፔንዱለም› ፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ የሰራችው ሔለን ለዚህ ነጠላ ዜማዋ ብር 100 ሺህ ከፕሮዲውሰሩ ቶም ፊልም ፕሮዳክሽን እንደተከፈላት በኢትዮፒካ ሊንክ ፕሮግራም ላይ ተናግራለች፡፡
የአርቲስቶቻችን ክፍያ እና ግነቱ – እውን የአርቲስቶቻችን ክፍያ እንደሚባለው ነው? ነው ወይስ ያጋንኑታል?
ዝናህ ብዙ ፀጋዬ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በልዩ ልዩ ፊልሞች እና የቴሌቪዥን ድራማ ላይ በመስራት የሚታወቀው አርቲስት ዝናህብዙ በሙያው የፊልም ባለሙያ ባይሆንም በየተሳተፈባቸው ፊልሞች ላይ ብቃቱን እያሳየ ያለ አርቲስት ነው፡፡ ዝናህብዙ በፊልም ሥራ ላይ ብቻ ሳይሆን በማስታወቂያ ሥራዎች ላይም ከፍተኛ ተከፋይ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ በቅርቡም
መስከረም 10 ቀን 2007 ዓ.ም በኢትዮፒካ ሊንክ ፕሮግራም ላይ በቀጥታ ስልክ ላይ ቀርቦ ዘሚሊ ለተባለው ፋብሪካ ለአንድ ዓመት ማስታወቂያ ለመስራት አንድ መቶ ሺህ ብር፤ ለካንጋሮ ጫማ ፋብሪካ ማስታወቂያ ደግሞ ለሁለት ዓመት ኮንትራት 200 ሺህ ብር እንደተከፈለው ተናግሯል፡፡
jossy gebre
ድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ/ ጆሲ/

ዮሴፍ ገብሬ ጆሲ ኢን ዘ ሀውስ/ዮሴፍ በቤት ውስጥ/ የተሰኘ ፕሮግራም በኢቢኤስ ቲቪ ላይ የሚያቀርብ አርቲስት ሲሆን በቅርቡ ‹መቼ ነው› የተሰኘውን ሁለተኛ አልበሙን ለአድማጭ አቅርቧል፡ ፡ ጆሲ ይህንን አልበሙን ሰርቶ ለአድማጭ ለማቅረብ ከፍተኛ ወጪ ማውጣቱንና ከአልበሙ ሽያጭ ላይም 193ኛ ዕትም የተወሰነ ገቢውን የበጎ አድራጎት ስራ ለሚሰራ ድርጅት ለመስጠት መወሰኑን በገዛ ፕሮግራሙ ላይ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ ተናግሯል፡፡ መስከረም 24 ቀን 2007 ዓ.ም በተላለፈው በታዲያስ አዲስ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ እንግዳ ሆኖ ቀርቦም ‹ዳሽን ቢራ› አልበሙን ሁለት ሚሊዮን ብር ስፖንሰር እንዳደረገውና እንደከፈለው ተናግሯል፡፡

አርቲስት /ሞዴል ሳያት ደምሴ

Sayat-Demissie-press-conferenceሳያት ደምሴ ወደ ኪነጥበቡ ዓለም ከመግባቷ በፊት የምትታወቀው በቁንጅና ውድድር
ላይ ተሳትፋ ‹ሚስ ኢትዮጵያ› የተሰኘውን ውድድር በማሸነፏ ነው፡፡ ሳያት ከቁንጅና ውድድሩ በኋላ መጀመሪያ ፊልም ከዚያም ወደ ሙዚቃው ዓለም ገብታ የመጀመሪያ አልበሟን ከሶስት ዓመት በፊት ለአድማጭ አቅርባለች፡፡ ህዳር 13 ቀን 2007 ዓ.ም የወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ በፊት ለፊት ገፁ ላይ የሳያት ደምሴን ፎቶግራፍ በማድረግ ከአንድ የጀርመን ኩባንያ ጋር እጅግ ከፍተኛ በሆነ ክፍያ ፊልም ልትሰራ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ሳያት (የጋዜጣው ዘገባ እውነት ከሆነ) በዚህ ፊልም ላይ በመስራቷ በሀገራችን ታሪክ ከፍተኛዋ የፊልም ተከፋይ ትሆናለች ይላል ጋዜጣው፡፡ ነገር ግን ሳያት በፊልሙ ላይ በመስራቷ ከፍተኛ ክፍያ ታገኛለች ተባለ እንጂ ምን ያህል ክፍያ እንደምታገኘ ጋዜጣው አልጠቀሰም፡፡ ክፍያውን የተመለከተ ህጋዊ የውል ስምምነት ከፊልሙ ፕሮውዲውሰሮች ጋር ስለማድረጓም የተባለ ነገር የለም፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ አርቲስት ሳያት ደምሴን አግኝተን የተባለው ነገር እውነት ስለመሆኑና ስለ ውል ስምምነቷ ለመጠየቅ ያደረግነው ሙከራ/ ስልኳ ከአገልግሎት ውጪ ነው ስለሚል/ ለጊዜው አልተሳካልንም፡፡ ሳያት በማንኛውም ጊዜ የዜናውን ትክክለኛነት ሊያረጋግጥ የሚችል ህጋዊ መረጃ ካላት ለአንባቢያን ለማቅረብ የምንችል መሆኑን እንገልፃለን፡፡

የአርቲስቶቹ ምላሽ ምንድነው?

በጉዳዩ ዙሪያ ስማቸው የተጠቀሱ አርቲስቶችን በተመለከተ አግኝተን ለማነጋገር ሙከራ ያደረግን ሲሆን የአንዳንዶቹ ስልክ ዝግ ሲሆን የሌሎቹ ስልክ ምላሽ አይሰጥም ወይም አያነሱትም፡ ፡ ካገኘናቸው አርቲስቶች መሀከል የአንዳንዶቹ ምላሽ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

አርቲስት ዝናህብዙህ ፀጋዬ ከሁለቱ ድርጅቶች ጋር የተደረገው ስምምነት ትክክል እንደሆነና የውሎቹ ማለቂያ ቀን ጊዜ በቅርቡ የሚጠናቀቅ በመሆኑ በስራውም ለውጥ እየታየበት በመሆኑ ከዚህ የተሻለ ክፍያ ለማድረግ እየተነጋገረ እንደሆነ ለቁም ነገር መፅሔት ተናግሯል፡፡ ያልተከፈለን ክፍያ አጋኖ ማቅረብ ህዝብን መዋሸት እንደሆነ የገለፀው ዝናህብዙ ከድርጅቶቹ ጋር የተደረገውን የውል ስምምነት ለማሳየት እንደሚችልና ከአንድ ሳምንት በኋላ ለመገናኘት ቀጠሮ ጠይቋል፡፡

አርቲስት መሀመድ ሚፍታ ከሁለቱ ድርጅቶች ማለትም ከስማድልና ከሳውዲው ኩባንያ ጋር የማስታወቂያ ስራ እንደሚሰራ አረጋግጦ ዝርዝር ምላሽ ለመስጠት ግን የፊልም ቀረፃ ላይ በመሆኑ መልሶ እንደሚደውል ገልፆ ስልኩ ተዘግቷል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊነት

መገናኛ ብዙኃን በእውነት ላይ የተመሰረተ መረጃ ለህዝብ ማቅረብ ዋና ስራቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር በጋዜጠኞች አማካይነት ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ ዘገባዎች በመረጃ ላይ የተመሰረተና ተአማኒነት ያለው መሆን እንዳለበት መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆነው፡፡ በጓደኝነትም ሆነ በትውውቅ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚቀርቡ ተመሳሳይ መረጃዎች እውነት ሆነው ካልተገኙ የተአማኒነት ችግር እንደሚፈጥሩ ግልፅ ነው፡፡ በመሆኑም ትክክለኛና ህጋዊ አሰራሮች በተግባር መመልከት የማንኛውም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑ ሳይዘነጋ ገንዘብንም ሆነ ሌሎች የግል ዝናን የሚያገዝፉ ዘገባዎች ለህዝብ ሲተላለፉ በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ሊሆኑ ይገባል፡፡
ህብረተሰቡ በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርብለትን ዘገባ አምኖ የሚቀበለው ጋዜጠኞች ሁኔታውን ‹አረጋግጠው ነው› በሚል እምነት በመሆኑ ከክፍያ ጋር የተያያዙ ዘገባዎች በውሎች የታሰሩ መሆኑን ማረጋገጥ የጋዜጠኞች ሃላፊነት ነው፡፡ አለበለዚያ ለማስታወቂያና ለግል ዝና መገንቢያ በሚል ‹እከሌ ይህን ያልህ ተከፈለው› የሚለው ዜና የተአማኒነት ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርምና ጋዜጠኞች ለሙያቸው ክብር ሊሰጡ ይገባል፡፡

በነገራችን ላይ እስከ ዛሬ ድረስ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ከክፍያ ጋር ተያይዞ ስማቸው የተጠቀሱ አርቲስቶች የተባለው ነገር እውነት መሆኑን በማስረጃ ለማቅረብ ፍላጎቱ ካላቸው ዝግጅት ክፍላችን አሁንም በሩ ክፍት እንደሆነ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>