Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ነባር ተመዝጋቢዎች በቅርቡ ይተላለፋሉ በተባሉ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ተደናግጠዋል

$
0
0

‹‹በተከታታይ ስድስት ወራት ያልቆጠቡና ቆጥበው ያቆሙ አይካተቱም›› የቤቶችና ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ

መንግሥት በ2007 ዓ.ም. በመጋቢት ወር 75,000 ቤቶችን ለነባር ተመዝጋቢዎች እንደሚያስተላልፍ የገለጸ ቢሆንም፣ ተመዝጋቢዎች ግን ከቁጠባ ጋር በተያያዘ ዕጣ ውስጥ አይገቡም በመባሉ ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን እየተናገሩ ነው፡፡

ነባር ተመዝጋቢዎች ሥጋት ውስጥ የወደቁት በኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ሰሞኑን ባስተላለፈው ማስታወቂያ ምክንያት መሆኑን ሪፖርተር ከተመዝጋቢዎቹ ለመረዳት ችሏል፡፡ ኤጀንሲው በቅርቡ ግንባታቸው ሙሉ ለሙሉና 80 በመቶ የተጠናቀቁ 75,000 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን (ኮንዶሚኒየም) በዕጣ ለባለድለኞች እንደሚያስተላልፍ ገልጿል፡፡ የዕጣው ተጋሪ ወይም ባለዕድል የሚሆኑት፣ ከዳግም ምዝገባው ጊዜ ጀምሮ በተከታታዩ ስድስት ወራት ለቆጠቡ መሆኑን አክሏል፡፡

2e499ffff526548702f96c6f5ce36153_L

እንደ ኤጀንሲው ገለጻ፣ በተከታታይ ለስድስት ወራትና ከዚህም ቀጥሎ እንደየሁኔታው ጨምሮም ይሁን አጠቃሎ የሚከፍል ያለምንም ችግር የዕጣው ተጋሪ ሲሆን፣ ለተከታታይ ስድስት ወራት ያልቆጠበና ለስድስት ወራት ቆጥቦ ያቆመ ተመዝጋቢ፣ ሁለቱም ከዕጣው ውጪ እንደሚሆኑ አስታውቋል፡፡ ተመዝጋቢው የከተማ ቤቶች፣ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ባወጣው መመርያና በገባው ውል መሠረት መቆጠቡን ከባንክ ደብተሩ ማረጋገጥ እንደሚቻል የጠቆመው ኤጀንሲው፣ ተመዝጋቢው ስለመቆጠቡ የባንክ ሥራ በመሆኑ ምንም እንደማይል አስታውቋል፡፡

አንዳንድ ነባር ተመዝጋቢዎች ግን በተከታታይ ለስድስት ወራት መቆጠብ ያለባቸው አዲስ የተመዘገቡት ስለመሰላቸው፣ በሁለት ወራትና በሦስት ወራት እየቆጠቡ መሆናቸውን በመግለጽ፣ በድንገት ‹‹በተከታታይ ያልቆጠበ ከዕጣ ውጪ ይሆናል›› መባሉን ተቃውመዋል፡፡

ኤጀንሲው ቤቶቹን ለማስተላለፍ ወራት ሲቀሩት በተከታታይ መቆጠብ አስገዳጅ መሆኑን መናገሩ አግባብ አለመሆኑን የገለጹት ተመዝጋዎቹ፣ ሁሉም ተመዝጋቢ በደንብ ገብቶትና እየተቸገረም ቢሆን ሳያቆራርጥ እንዲቆጥብ ተደጋጋሚ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሥራት ይገባው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ትዕግሥት ሰለሞን የተባሉ ነዋሪ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የጋራ መኖሪያ ቤት ለማግኘት የተመዘገቡት በመጀመሪያው ዙር ነው፡፡ በሁለተኛ ምዝገባ ሲመዘገቡ ልብ ያሉት ነገር የመጀመርያዎቹ ተመዝጋቢዎች አግኝተው ሳይጠናቀቁ አዲስ ተመዝጋቢዎች ዕጣ ውስጥ አይገቡም የሚለውን ነው፡፡ በመሆኑም ከሚያገኙት ትንሽ ገቢ የተወሰነችውን አልፎ አልፎ የሚቆጥቡ ቢሆንም፣ ኤጀንሲው እንደሚለው በተከታታይ ለስድስት ወራትና ከዚያም ቀጥሎ ባሉት ጊዜያት እየቆጠቡ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከነገ ዛሬ ዕጣ ይወጣና ከኪራይ እላቀቃለሁ የሚል ጉጉት እንዳላቸው የሚናገሩት ወ/ሮ ትዕግሥት፣ ኤጀንሲው ያወጣውን ማስታወቂያ ሲሰሙ ከመደንገጥም አልፈው ተስፋ እስከ መቁረጥ መድረሳቸውን አስረድተዋል፡፡ በቀጥታ ካልቆጠባችሁ በማለት ተስፋቸውን ከማሳጣት ይልቅ፣ ያላቸውን ቤት የማግኘት ጉጉትና አልፎ አልፎም ቢሆን እየቆጠቡ ያሉበትን ሁኔታ ተመልክቶ በዜግነታቸው ማግኘት የሚገባቸውን የመኖሪያ ቤት እንዲያገኙ የሚመለከተው አካልና የመንግሥት ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ ትዕግሥት ሁሉ፣ በርካታ ተመዝጋቢዎች የመጀመርያዎቹን ሁለትና ሦስት ወራት በተከታታይ ከቆጠቡ በኋላ አልፎ አልፎ ከሁለትና ከሦስት ወራትበኋላም ቢሆን እየቆጠቡ መሆኑን ተናግረው፣ በድንገተኛ ማስታወቂያ በተከታታይ ያልቆጠበ ከዕጣ እንደሚወጣ ማወጅ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ዜጎቹን የማኖር፣ የመንከባከብና መጠለያ እንዲያገኙ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት የተናገሩት ተመዝጋቢዎቹ ከዕጣ እንደሚወገዱ ተናግሮ ዜጎችን ከማሳቀቅ ይልቅ፣ የዕጣው ተሳታፊ ሆነው ቅድሚያ ክፍያ መፈጸም ካቃታቸው ወይም ቤቱን ተረክበው በተከታታይ መክፈል ካልቻሉ፣ ዕርምጃውን ቢወስድ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጇ ወ/ሮ ሐሊማ ባድገባ አማካይነት በቅርቡ በዕጣ ለነባር ተመዝጋቢዎች ይተላለፋሉ ስለተባሉት 75,000 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተሰጥቷል ስለተባለው ማስጠንቀቂያና ማስታወቂያ፣ ማብራሪያ ለማግኘት፣ ሪፖርተር በተደጋጋሚ እሳቸውን ለማግኘት ባደረገው ጥረት ‹‹ስብሰባ ላይ ነኝ›› በማለታቸው አልተሳካም፡፡ ኮንዶሚኒየም ቤቶቹ የተገነቡትና በመገንባት ላይ ያሉት አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት፣ የካ ጨፌ፣ ቦሌ አራብሳ፣ ቂሊንጦ፣ ቱሉ ዲምቱና የካ አባዶ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

Source:: Ethiopian Reporter


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>