ከሊሊ ሞገስ
(ዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ወጥቷል)
የደስታ መንገድህን ለመጥረግ ደስታህ በተሸረሸረበት፣ በጠፋበት፣ በተጨነክ ጊዜ ብታደርጋቸው ፍቱን ናቸው ስለሚባሉ መፍትሄዎች ዛሬ ብንጨዋወትስ?
እስቲ እንደው! ከደስተኛነት ስሜት የሚገቱህን ነገሮች የምትወረወርበት ማጠራቀሚያ እና ማስወገጃ አለ ብለን እናስብና፤ በአሁኑ ሰዓት ‹‹ኧረ በቃ፣ ወደዚያ…!›› ብለህ ወደ ማጠራቀሚያው መወርወር የምትፈልጋቸውን ነገሮች ለጥቂት ጊዜ ንባብህን ገታ አድርግና ለማጤን ሞክር… ሸጋ!
በተለያዩ የሕይወት ፍሰቶቻችን ውስጥ አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ከመጨመር፣ ሁሉን አጥብቆ ከመያዝና ብዙ ትርኪ ምርኪ ነገሮችን ከማወቅ ይልቅ መቀነስ፣ ነገሮችና ሁኔታዎች እንዲያልፉ መፍቀድ፣ ያለንበትን ሁኔታ መለስ ብሎ ለማየት መሞከር እጅግ ከሚጠቅሙንና ደስተኛ ከሚያደርጉን ዋና ዋና ምክንያቶች ወይም መፍትሄዎች ውስጥ ጎልተው የሚወጡና የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
አሁን ካሉህ ነገሮችም ሆነ ማንነት ውስጥ ሸክም የሆኑብህና ደስታህን የነጠቁህ ነገሮች (ሁነቶች) አሉ ብለህ ታስባለህ? ከብደውኛል የምትላቸውን አስር ነገሮች ወደ ማጠራቀሚያው ለመወርወር ተዘጋጅ ብትባል ምን ይሰማሃል? ምን ምን ይሆናሉ…? ትንሽ የአስተውሎት/የማሰቢያ ጊዜ ሰጥተህ ማለፍህን አትርሳ፡፡
በሕይወትህ ውስጥ ደስታን እንዳታጣጥም እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች በዝተውብህ ከሆነ፣ ምናልባትም የህይወት ሹረት አብዝቶ ምቾት ከነሳህ፣ ከዚህ የአሽከርካሪት ጫና ብሎም ሸክማቸው የከበደ የሃሳብ ክምሮች፣ ሲቀጥልም እርስ በእርስ ተተብትበው እየጠለፉ የሚጥሉህን የአስተሳሰብ ሂደቶች ለመቀነስ እጅግ ይረዳሉ ያልኳቸውን አስር ሸጋ የለውጥ መንገዶች አጠር አድርጌ ከዚህ በመቀጠል አብራራለሁ፡፡
በሚገባ ከተተገበሩ ደግሞ ተጭኖ የሸፈነንን ከንቱ አስተሳሰብ ገሸሽ አድርገን፣ የምንሞቃት የደስታ ፀሐይ በእውነት ሁሌም ከጎን እንዳለች፣ ብርሃኗንም ፈንጥቃ ከእቅፏ እንዳስገባችን እናስተውልባቸዋለን፡፡
1. ‹‹አበጀህ! አንተ ባትኖር እኮ…›› መባልን የመፈለግ ፍላጎት በውስጥህ ካለ፤ ይህ ፍላጎት ተንሰራፍቶ የያዘውን ቦታ የመቀነስ ስራ መስራት እንዳለብህ ሁሌም ለማስተዋል ሞክር፡፡
2. ‹‹እኔ ያልኩትን አልተረዱኝም፣… ሊረዱኝ ይገባቸዋል!›› የሚል ሐሳብ በአዕምሮህ የያዘውን ቦታ እንዲያስረክብህ (እንዲለቅ) አድርግ፡፡
3. ዙሪያህ ላሉ ነገሮች ሁሉ ምላሽ የመስጠት ፍላጎትን ብሎም ስሜትህን ቀንስ፡፡ ባለንበት የመረጃ ዘመን በየአቅጣጫው የሚነጉዱትንና፣ የአንተንም ምላሽ ለማግኘት የሚያንኳኩ ጥሪዎችንና መረጃዎችን ሁሉ ለማስተናገድ አለመሞከር፣ አንተን ከማጨናነቃቸው በዘለለ ምላሽ ሰጥተህ ለማትጨርሳቸው ነገሮች፣ ሳታጣጥማቸው የሚያልፉ ብዙ የህይወት እንቅስቃሴዎች እንደሚኖሩ ልብ በል፡፡
4. በሁኔታዎች ወይም በተለያዩ ቦታዎች ላይ ካለፍላጎትህ በሰዎች ወይም በሌላ ተፅዕኖዎች ግፊት ወይም ጫና መገኘትን ወይም ያለመገኘትን ከመወሰን ይልቅ ምርጫውን ወይም ፍቃድህን በፍላጎትህ ለራስህ ስጥ፡፡ አንዳንዴ ጓደኞችህ ሰብሰብ ብለው እንድትቀላቀላቸው ጥሪ ሊያደርጉልህ ይችላሉ፤ አይቀሬ የተባለ ድግስ (ግብዣ) ላይ እንድትገኝ ጥሪ ሊደርስህ ይችላል፤ እዚህ ጥሪ ላይ መገኘት ካልፈለግክ እና የሚያሳጣህ ነገር እንደሌለ ከተገነዘብክ ‹‹ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፤ ግን አልችልም›› ማለት ከባድ ነገር እንዳልሆነ ስትረዳ፣ የደስታህ ቁልፍ በአንተ እጅ እንዳለ አዕምሮህን የምታስገነዝብበትና የምታጠነክርበት ክስተቶች ናቸው፡፡
5. ‹‹እገሌ/እገሊት ወይም ያ ነገር ለስኬቴ/ ለደስታዬ ወሳኝ ነው/ነች/ናቸው!›› ከሚል የሀሳብ እስር ቤት ራስህን ነፃ ማድረግ እጅግ አትኩሮትህን ሊያገኝ የሚገባ ነጥብ ነው፡፡ ስለምን የደስተኛነቴን ቁልፍ አሳልፌ እሰጣለሁ? ‹‹የደስታዬ ቁልፍ›› በእጄ መሆኑን ሳስተውል ከራሴ አልፌ ለሌሎች ‹‹የደስታ ምንጭ›› መሆን መቻሌ ቀላል መሆኑን ለማለት አልቸገርም፡፡
6. ራስን አጉልቶ የማሳየት ጠንካራ ፍላጎትና ስሜት ከአንተ ውስጥ ማረፊያ እንዳይኖረው ማለፊያ አበጅላቸው፡፡ ያለህ የአንተ ማንነት በራሱ በቂ እንደሆነ ደግመህ ደጋግመህ ለራስህ ማረጋገጫ ስጠው፡፡ ያለህበት ማንነትህ ካንተ ማብራሪያም ሆነ ማረጋገጫ ሳይፈልግ ሳያስፈልገው የሚያዩህና የሚቀበሉህ ሰዎች እንዳሉም አስተውል፡፡
7. በሁሉም ሰው ተቀባይነትን የማግኘትን ሙከራ ራቅ አድርጎ መወርወር፡፡ ሁሉም ሰው ሁሌም በሁሉም ሁኔታ ሊቀበልህ አይችልም፤ ይህ ደግሞ ምንም ማለት አይደለም፤ አንዱ የህይወት ክህሎት ይህን በደስታ መቀበል መቻል ነውና!!
8. እያንዳንዱን የህይወትህን እንቅስቃሴና ክስተት ማወቅ እንደማይጠበቅህ ተገንዘብ! ሁሌም ህይወት የምትፈስበት ቦይና የራሷ የሆነ ምስጢር አሏትና፡፡ ስለዚህ ካለማወቅ ጋር ተመቻችቶ ማለፍ ሌላው ክህሎት እንደሀነም አስተውል፡፡
9. ሁሌም ትክክል ወይም ፍፁም ነኝ ብሎ የማሰብ አባዜና የመሆን ፍላጎት በአስቸኳይ ልታስወግደው የሚገባ ጠባይ ነው፡፡ ይህን ካደረግህ የደስታ መንገድህን በሰፊው ለመቀየስ ያለህን ዝግጁነት ያሳያል፡፡ መሳሳት ያለ፣ የነበረ እና የሚኖር ከመሆኑ ባሻገር የዕድገት መሰላል እንደሆነም መዘንጋት አያስፈልግም፡፡ አንዳንዴ ግራ ተጋብተህ መታየት ራሱ ተአምራዊ ነገር አይደለም፡፡ ይልቅስ ሁላችንም የሚያጋጥመን ክስተት እንጂ!
10. በአካባቢህ ላሉ ሰዎች ሁሉ ኃላፊነት አለብኝ በሚል ስሜት የሚመጣ ጭንቀት ወይም የሐሳብ ሸክም እንዲጫንህ አትፍቀድ፡፡ በእርግጥ ሌሎችን ማገዝና መርዳት በጎ ነገር ነው፤ ሆኖም ግን የሐሳብ ጫና በሚኖርበት ጊዜ ነገሮች እንዲያልፉ ፍቃድ መስጠት እንዳለብህ ተረዳ፡፡ ሁሌም አንተን የሚረዳህና የሚያግዝህ የህይወት ኃይል እነርሱንም እንደማይጥላቸው እመን፡፡
የተሸከምካቸውንና የከበዱህን የሐሳብ ጫናዎች ለማራገፍ ቀላሉ ነገር ‹‹ራስን ነጻ›› ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ነፃነት ውስጥም አዲስ ጥንካሬ፣ አዲስ ተነሳሽነትና አዲስ አቅም በህይወት እንቅስቃሴህ ውስጥ አዳዲስ ተጋባዦች መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ውስጥም በግል ህይወትና በስራ ወደላቀ ደረጃ ማለፍ በጣሙን እየቀለለህ መሄዱን ካንተ አልፎ አንተን የሚያዩህ ሰዎች የሚያስተውሉት ይሆናል፡፡ በዙሪያህ ላሉ ሰዎችም የሚኖርህ የእገዛ መጠን በብዛትም ሆነ በአይነት ያድጋል፡፡
ደስተኛው ማንነትህ በአንተ፣ በቤተሰብህ፣ በአካባቢህና በዓለም ላይ የተሻሉ ተፅዕኖዎችን የመፍጠር አቅሙ ታላቅ ነው፡፡ እናም የሆነች ያክል ጊዜ ወስደህ ከ5-10 የሚሆኑ ደስተኛነቴን ሸፍነዋል፤ ልወረውራቸው ይገባኛል፤ ለዚህም ዝግጁ ነኝ የምትላቸውን ነገሮች ለመዘርዘር ለራስህ ቃል ግባ፡፡ የዘረዘርካቸውንም አንድ በአንድ ከማንነት እንዲለዩ ቆራጥነትህና ፍቃድህ በአንተው እጅ እንደሆኑ ሁሌም አስታውስ፡፡
እውነትም ዘይደሃል!! ደስተኛነት?!… ይገባሃል! ደስታ ለሁላችንም ይገባናል! ሸጋ እንሰንብት በደስታ፡፡