አንጀሊና ጆሊ የዛሬ የኪነጥበብ አምድ እንግዳችን ናት፡፡ ይህቺ እንስት ተዋናይት ከትወና ባሻገር በርካታ መልካም ስራዎችን በመሥራት ትታወቃለች፡፡ በኢትዮጵያም ዘሀራ የተባለች ልጅ በጉድፈቻነት እያሳደገች ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት በሀገራችን በመምጣት በጎ ስራዎችን አከናውናለች፡፡
አንጀሊና ጆሊ ትውልድና እድገቷ እ.ኤ.አ. 1975 በሎሳንጀለስ ሲሆን የትወና ፍቅር የጀመራት ገና በህፃንነቷ እንደነበር ይነገራል፡፡ ወላጆቿም በትወና ሙያ ያለፉ በመሆናቸው አሁን ለደረሰችበት ከፍተኛ ደረጃ የበኩላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ይነገራል፡፡
በ199ዐዎቹ በወጣትነት እድሜዋ ትወናን ጀምራለች በሊስትራስበርግ ትያትር የተማረች ሲሆን በኋላም ኒውዮርክ ዩንቨርስቲ በመግባት ትምህርቷን ተከታትላለች፡፡ በዚያው ዓመትም ጥሩ ፐርፎርማስ በማሳየቷ ከዝና ማማ ላይ ለመቀመጥ ችላለች፡፡ በዚህም በ1998 በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ እንድትሰራ እድሉን እንድታገኝ ረድቷታል፡፡ በዚሁ ዓመትም የምርጥ የጎልደን ግሎቭ አዋርድን አግኝታለች፡፡ በ1999 እ.ኤ.አ. የመጀመሪያዋን የአካዳሚክ አዋርድን በምርጥ ሴት ረዳት ተዋናይነት ልታሸንፍ ችላለች፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ ተዋናይት አንጀሊና ጆሊ የሚያግዳት አልተገኘም፡፡ የተለያዩ ይዘት ያላቸው ፊልሞችን መስራትና ብቃቷን ማሳየት ጀመረች፡፡ በዚህ ዓመትም / Lara craf, Taking lives /2004/ እንዲሁም Mrs smith የተሰኘውን ፊልም በ2ዐዐ5 ሰርታ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝታለች፡፡ 2ዐዐ7 አንጂሊና ጆሊ በጣም ምርጥ ብቃት ያሳየችበትን Mariane, pear, pregnant Widow,Mighty Heart. የተሰኙት ፊልሞችን በመስራት ለዕይታ አብቅታለች፡፡ በዚህም በሆሊውድ ምርጥ ተፅእኖ ፈጣሪ ከሚባሉት ሴት ተዋንያን ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች፡፡
አንጂሊና ጆሊ ከተዋናይነትና ከዳይሬክተርነት ባሻገር በበጎ ስራዎቿ ትታወቃለች፡፡ በ2ዐዐ2 የበጎ ፈቃድ ስራዎችን የጀመረችበት ዓመት ነበር፡፡
በዚህም ከካምቦዲያ የጉድፈቻ ልጅ በመውሰድ እንደ ራሷ ልጅ ማሳደግ ጀመረች፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ጎራ በማለት ዘሀራ የምትባል ልጅ በጉድፈቻነት ለማሳደግ ወስና ወስዳለች፡፡ በ2ዐዐ5 ባሏ ብራድ ፒት ህጋዊ በሆነ የወረቀት ሰነድ በመፈረም ሁለቱን ልጆች ተቀብሎ አብረው ማሳደግ ጀመሩ፡፡
2ዐዐ6 ለአንጀሊና ጆሊና ለብራድ ፒት ጥሩ ዓመት ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የራሳቸውን ልጅ ናሚቢያ ውስጥ አግኝተዋልና ነው፡፡ 2ዐዐ7 ላይ ደግሞ አዲስ የ3 ዓመት ህፃን ከቬትናም በማምጣት የቤተሰባቸው ቁጥር አራት የደረሰበት ወቅት ነበር፡፡ 2ዐዐ8 ላይ ደግሞ የራሷን መንታ ልጆች ወለደች፡፡ በዚህ ወቅት የመንትያ ልጆቿን ፎቶ ግራፍ ለፒፕልና ለሄሎ መጽሔት 14 ሚሊየን ብር ሸጣለች፡፡ በዚህም እስከ አሁን በፎቶግራፍ ሽያጭ ክብረወሰን ለመሆንና ለመቆየት ችሏል፡፡ ነገር ግን አንጀሊና ጁሊ በ2ዐዐ7 በርካታ ስኬቶችንና ልጆችን ያገኘች ቢሆነም በህይወቷ ያዘነችበት ዓመትም ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወላጅ እናቷ በማህፀን ካንሰር በሽታ ለበርካታ ዓመታት ከታመመች በኋላ በ56 ዓመቷ ያለፈችበት ዓመት በመሆኑ ነበር፡፡ አንጀሊና ጁሊ በማህፀንና በጡት ካንሰር ህመም ምክንያት ለበረካታ ጊዜያት በሆስፒታል ቆይታለች፡ ፡ በዚህም ሰርጀሪ ተሰርቶላታል ከህመሟ እንደተፈወሰች በተደጋጋሚ በምትሰጠው ቃለ መጠይቅ ገልፃለች፡፡
ተዋናይቷ ለበርካታ ዓመታት በፍቅረኛነት ከቆየው ብራድ ፒት ጋር በ2ዐ12 ቀለበት አስረዋል፡፡ እንደገና ነሐሴ ወር 2ዐ14 በፈረንሳይ ወዳጅ ዘመድ በተሰበሰቡበት የጋብቻ ሥነ- ሥርዓታቸውን አከናውነዋል፡፡
አጂሊና ጆሊ ከትወና ባሻገር በመልካምና በበጎ ሥራዎቿ የዩናይትድ ኔሽን የበጎ ፈቃድ አምባሳደርነት ማዕረግን አግኝታለች፡ ፡ በዚህም በተፈናቃዮች ካምፖች ውስጥ በካምቦዲያ፣ዳርፉርና ጆርዳን በመዘዋወር በጎ ስራዎችን ሰርታለች፡፡ በዚህ ሥራዋም በ2ዐዐ5 የግሎባል ሂውማን ተሪያል አክሽን አዋርድ ከአሜሪካን ማህበር ለበጎ ስራዎቿ ተበርክቶላታል፡፡
በኢትዮጵያም በርካታ በጎ ሥራዎችን ሰርታለች፤ በተደጋጋሚም ከባለቤቷ ብራድ ፒት ጋር በመሆን ሀገራችንን ጎብኝታለች፡፡
በቅርብም ድፍረት የተሰኘውን በስደት ላይ የሚያጠነጥነውን ፊልም እንዲሰራ ከፍተኛ ድጋፍ ከማድረጓ ባሻገር ፕሮዲውስ በማድረግም ተሳትፋለች፡፡