Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ከዓመታት በፊት ነው፡፡ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባት ሴት አስገድዶ ከደፈራት ታረግዛለች፡፡ የልጇን አባት በውል የማታውቀው ይህችው እናት ከወለደች በኋላ በርካታ ችግሮች ከፊቷ ተጋረጡ፡፡ ገቢ አልነበራትም፡፡

$
0
0

ረፖርተር

ከዓመታት በፊት ነው፡፡ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባት ሴት አስገድዶ ከደፈራት ታረግዛለች፡፡ የልጇን አባት በውል የማታውቀው ይህችው እናት ከወለደች በኋላ በርካታ ችግሮች ከፊቷ ተጋረጡ፡፡ ገቢ አልነበራትም፡፡

በመሆኑም በቂ ገቢ ከሌላቸው ዘመዶቿ ጋር ከጅላ መኖር ግድ ሆነ፡፡ በቂ ምግብና እንክብካቤ የሕፃኗ ችግር ሲሆኑ ገና ድክ ድክ ስትል የገጠማት የሚጥል በሽታ ደግሞ ብዙ መዘዞችን ማስከተሉ አልቀረም፡፡

bcba2c7d61a07f13286612c710db37fe_Lችግሩ በይበልጥ መባባስ የጀመረው ሕፃኗ ዕድሜዋ ለትምህርት ደርሶ መዋዕለ ሕፃናት ከገባች በኋላ ነበር፡፡ ይኸውም ከቤት ወደ ትምህርት ቤት ስትሄድ ወይም ወደ ቤት በምትመለስበት ሰዓት አንዳንዴ ደግሞ እንጨት ለመግዛት በምትወጣበት ጊዜ ድንገት ከሚጥላት በሽታ ጋር ተያይዞ ይገጥማት የነበረው መደፈር ነው፡፡

የሚጥላት በሽታ አልፎላት ከወደቀችበት ስትነሳ ደምና ፈሳሽ ነገር በአካሏ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ማየቷን ሆኖም ትኩረት እንዳልሰጠችውና ለማንም እንዳልተናገረች ታስታውሳለች፡፡ ዕድሜዋ ከፍ እያለ ሲመጣ ለመምህሮቿ ‹‹የደም ፍንጣቂና ነጣ ያለ ፈሳሽ በአካል ላይ ማየት የምን ምልክት ነው፡፡ በጓደኛዬ ላይ ተከስቷል?›› ስትል በተደጋጋሚ ጊዜ ብትጠይቅም ‹‹ይህ ነው›› ከማለት ይልቅ ‹‹ልጅቷን አገናኝንና እናነጋግራት›› ስለሚሏት ነገሩን በዝምታ ታልፈዋለች፡፡

ዕድሜዋ ከፍ እያለ ሲመጣ አካሏ ላይ የምታገኘው ፈሳሽ በመደፈሯ ምክንያት የመጣ እንደሆነ ገባት፡፡ ይሁን እንጂ ማን እንደደፈራት የማወቁ ዕድል አልነበራትም፡፡ ‹‹ራሴን ስቼ ስወድቅ ነው የሚደፍሩኝ፤›› የምትለው ተጠቂዋ ሰብዓዊ ክብሯን የሚጋፉ ወንዶችን ለይታ ማወቅ እንዳልቻለች ትገልጻለች፡፡

የ13 ዓመት ልጅና ዘጠነኛ ክፍል ስትደርስ በጤናዋ ላይ ካለው ችግርና ከሚገጥማት የአስገድዶ መድፈር ጥቃት በተጨማሪ እሷንና እናቷን የሚያስተዳድሩት ዘመዶቿ ኑሮ ከበዳቸው፡፡ ‹‹አንዳንዴ ከቤት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ ይጠፋል›› የምትለው ታዳጊዋ፣ ነገሮችን በውል ማገናዘብ የማትችለውን እናቷን ነፍስ ለመታደግ ‹‹አንዴ ከአንዱ ሱቅ የሚበላ ተበድሬ አመጣለሁ፡፡ አንዴ ደግሞ ከሌላኛው ሱቅ ተበድሬ እያመጣሁ 49 ብር ዕዳ ደረሰብኝ፡፡ ከዚያ ‹ክፈይን› እያሉ ሲጨቀጭቁኝ መደበቅ ጀመርኩ፤›› በማለት ይህ አጋጣሚ ሌላ ችግር ፊት ለፊት እንድትጋፈጥ ምክንያት እንደሆነ ተናግራለች፡፡

እንደ እሷ ገለጻ፣ በቤት ውስጥ ያለው የኑሮ ችግርና ታዳጊዋ የገባችበትን ዕዳ በቅርበት ያስተዋለው በአያት በኩል የምትዛመደው ግለሰብ፣ ገንዘቡን እንደሚሰጣት ሲነግራት ደስታዋ ወደር አልነበረውም፡፡ የተባለውንም ገንዘብ ለመቀበል ከምትኖርበት ቤት ብዙ ወደ ማይርቀው የግለሰቡ መኖሪያ ቤት አመራች፡፡ የጠበቃት ነገር ግን ፍፁም የተለየ ነበር፡፡

ታዳጊዋ እንደ ከዚህ ቀደሙ ራሷን ስታ አልወደቀችም፡፡ ገንዘብ ሊሰጣት ቃል የገባላት ዘመዷ ሲደፍራት እያንዳንዱን ሁኔታ ታስታውሳለች፡፡ ‹‹ለመጀመርያ ጊዜ የደፈረኝን ሰው አየሁ፡፡ ሁሌም ይደፍረኝ የነበረው እሱ መሰለኝ፡፡ ዕድሌን እያማረርኩ አለቀስኩኝ፤›› በማለት በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ታስታውሳለች፡፡

ስለደረሰባት ጥቃት ግን ለማንም ከመናገር ተቆጥባ ነበር፡፡ ተፈጥሮ ግን ጊዜውን ጠብቆ ከማሳበቅ አልተቆጠበም፡፡ እንደሌላው ጊዜ ተደፍራ ብቻ አልቀረችም፡፡ እርግዝናም ተከተለ፡፡ የሆዷን መግፋት በጥርጣሬ የተመለከቱት ዘመዶቿ በጥያቄ አጣደፏት፡፡ ዱላ ዘለፋና ከትምህርት ገበታ መቅረት፣ ተደፍራ የማርገዟን ዕውነታ ስትናገር አሳዳሪ ዘመዶቿ የወሰዱባት ዕርምጃዎች ነበሩ፡፡

ነገር ግን በድርጊታቸው ብዙም ሳይገፉ ሐሳባቸውን ቀይረው ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ ወስደዋት ስለ ሁኔታው ለፖሊስ አስረዱ፡፡ ፖሊሶችም ታዳጊዋ ለተጨማሪ ምርመራ ቀጥታ ወደ ጋንዲ ሆስፒታል እንድትሄድ አዘዙ፡፡ ቀጥሎም ጥቃት ፈጻሚው ለምርመራ ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ተደረገ፡፡

ከዚህ በኋላ ግን ከቤተሰቦቿ ጋር የነበራት ቆይታ ከሳምንት ሊበልጥ አልቻለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ብዙ መግፋት ስላልቻለች ችግሯን ለፖሊስ አስረዳች፡፡ እሷን የመሰሉ ጥቃት የደረሰባቸው በሚኖሩበት የተጠቂ ሴቶች መጠለያ ማኅበር እንድትቀላቀልም ተደረገ፡፡

ወደ መጠለያው ከመጣች አሥር ወር አልፏታል፡፡ ልጇንም በሰላም ተገላግላለች፡፡ ይሁን እንጂ ስለተፈጸመባት ወንጀል የማጣራት እንቅስቃሴው ምን ያህል እንደተጓዘ አታውቅም፡፡ ‹‹አብረውኝ የሚኖሩ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በየጊዜው ለምስክርነት ፍርድ ቤትና ፖሊስ ጣቢያ ሲጠሩ አያለሁ፡፡ እኔ ግን አንድም ቀን ተጠርቼ ሄጄ አላውቅም፤›› በማለት የእሷ የፍትሕ ጥያቄ እልባት ሳያገኝ የቀረ እንደሆነ ትገምታለች፡፡

‹‹የመጨረሻ ፍርድ ካልተሰጠ ካለሁበት መጠለያ መውጣት አልችልም›› የምትለው ታዳጊዋ ክሱ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ብታውቅና ያቋረጠችውን ትምህርቷን በመቀጠል ልጇንና እናቷን የምታስተዳድርበት ሁኔታ ቢፋጠንላት ምርጫዋ እንደሆነ ትናገራለች፡፡

እሷ በምትኖርበት መጠለያ ውስጥ 83 የሚሆኑ እናቶች ሲኖሩ ከነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ተደፍረው ወደ ማዕከሉ የመጡ ናቸው፡፡ 42 የሚሆኑ በማዕከሉ የሚኖሩ ሕፃናትም ተገደው የተደፈሩ እናቶች የወለዷቸው ናቸው፡፡ መኖሪያቸው በሚስጥር የተያዘ በመሆኑ ወደ ውስጥ ለመዝለቅ ብዙ ቅድመ ሁኔታች አሉት፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በመጠለያው የሚኖሩ ሴቶች የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ሲሆኑ ከተከሳሽ በኩል የሚደርስባቸውን የማስፈራራትና ተጨማሪ ጥቃት ለመከላከል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

መጠለያው ለዓመታት በርካታ የጥቃት ሰለባ የሆኑ እንስቶች ማረፊያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በየጊዜውም የሚደፈሩ ሴቶች ቁጥር እያየለ በመምጣቱ ምንም እንኳ የጀመሩት የሕግ ክትትል ፍጻሜ አግኝቶ ወደ የመጡበት የሚመለሱ ሴቶች ቢኖሩም በየቀኑ የሚመጡ የጥቃት ሰለባዎች ሞልተዋል፡፡ እስከ ሦስት ዓመት ድረስ የቆዩ ሴቶችም ይገኙበታል፡፡

ከዓመታት በፊት በኦሮሚያ ክልል አርሲ አካባቢ የምትኖረው ታዳጊ እንደወትሮዋ የገብስ ማሳውን እያቆራረጠች ወደ ትምህርት ቤት መጓዝ ጀምራለች፡፡ ነገሮች ግን እንደቀድሞው ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ድንገት መልካቸውን ቀየሩ፡፡ እንደ እሷ ገለጻ፣ ማሳውን አቋርጦ የሚያልፈው ግለሰብ ባለ በሌለ ኃይሉ ግጥም አድርጎ ያዛት፡፡ ለማምለጥ ያደረገችው መወራጨት ከምንም አላዳናትም፡፡ አስገድዶም ደፈራት፡፡ ግለሰቡ ግን በዚህ ብቻ ሊለቃት ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ‹‹ለሰው እንዳትናገር›› በሚል ሰበብ በስለት አንገቷን አርዷት ተሰወረ፡፡ የታዳጊዋ ሕይወት ግን በቀላሉ አላለፈም፡፡ ይልቅኑ የአካባቢው ሰዎችና ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች መጠለያ ማኅበር ባደረጉት ርብርብ ሕይወቷ ተረፈ፡፡ የምትተነፍሰው በተገጠመላት አርቴፊሻል መሣሪያ ሲሆን፣ ሦስት ዓመት ያህል በመለጠያው ቆይታለች፡፡

ግለሰቡም ከተሰወረበት ተገኝቶ የሕግ ፍርደኛ ሊሆን በቅቷል፡፡ ይሁን እንጂ የተሰጠው ፍርድ በእሷ ላይ ከደረሰው ጉዳት አንፃር ዝቅተኛ ነው በሚል እንደተከፋች በማዕከሉ የሚገኙ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ባደረሰባት ከፍተኛ ጉዳትም እንደማንኛውም ሰው ተንቀሳቅሳ መሥራት አትችልም፡፡ ለእሷ ከደረሰባት ጉዳት አንፃር በበደላት ላይ የተፈረደው እሥራት ምንም ማለት አይደለም፡፡

ሌላዋ በማዕከሉ የምትገኘው የ18 ዓመት ታዳጊ ስትሆን በአክስቷ የልጅ ልጅ አማካይነት በደረሰባት የአስገድዶ መደፈር ጥቃት ክስ በማቅረቧ ከአክስቷ ጋር መቆየት አልቻለችም፡፡ ስለዚህም ወደ ማዕከሉ መምጣት ብቸኛ አማራጯ ነበር፡፡ ወደ ማዕከሉ የመጣችው በ2005 ዓ.ም. ሲሆን፣ በወቅቱ ከሁለት ቀናት በኋላ እንደምትወጣ ተነግሯት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በፍርድ ቤት ተገኝታ የምስክርነት ቃሏን ብትሰጥም ጉዳዩ እስካሁን ድረስ መቋጫ ስላልተገኘለት ከትምህርቷም ሆነ ከሌሎች ማኅበራዊ ሕይወቷ ታቅባ በማዕከሉ መቀመጥ ግድ ሆኖባታል፡፡

ወጣት ባዩሽ ጋዲሳ በመጠለያ ማዕከሉ ለሚመጡ ሴቶች የሕግ አገልግሎት ክትትል ኦፊሰር ናት፡፡ እንደ እሷ ገለጻ፣ ጥቂት የማይባሉ ክሶች ውሳኔ ሳያገኙ ለዓመታት ይንጓተታሉ፡፡ በሌላ በኩልም በወንጀለኛው ላይ የሚተላለፉት ፍርዶች አነስተኛ ይሆናሉ፡፡ ሁኔታው ብዙ ጊዜ የሚስተዋል በመሆኑ ተጠቂዎቹን ፍትሕ የማግኘት ተስፋ እያጨለመው እንደሚገኝ ትገልጻለች፡፡

‹‹እኛ አደራ ተቀባዮች ነን›› የምትለው ባዩሽ፣ ተጠቂዎቹ ከማዕከሉ ዕውቅና ውጪ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ትናገራለች፡፡ ‹‹መውጣት ቢፈልጉ እንኳን እኛ ከጎናቸው መሆን ይጠበቅብናል›› ትላለች፡፡ ይህንንም ተከትሎ የመጨረሻ ፍርድ ሳያገኙ ለዓመታት በሚቆዩበት ሁኔታ የውጪው ዓለም ስለሚናፍቃቸው ያለመረጋጋትና የመረበሽ ስሜት ይፈጥርባቸዋል፣ በዚህም ምክንያት ማዕከሉን የሚረብሹበት አጋጣሚዎች መኖራቸውን ትናገራለች፡፡

በሴቶች ዙሪያ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ላይ የሚሰጡት ፍርዶች አነስተኛና ኢፍትሐዊ ናቸው፣ በመሆኑም የወንጀል ሕጉ እንደገና እንዲከለስና የሚጣለው ቅጣትም ከባድ እንዲሆን የሚጠይቅ ደብዳቤ በቅርቡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት መላኩ የሚታወስ ነው፡፡

ይህንንም ተከትሎ በርካታ ሐሳቦች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል፡፡ በጉዳዩ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር የሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ወ/ሮ ዜናዬ ታደሰ፣ በፍርድ ቤት በሚሰጡ ፍርዶች ፍትሐዊነት ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በወንጀል ሕጉ የተቀመጡት ቅጣቶች ይህን ያህል የሚያስከፋ አይደሉም፡፡ ይሁን እንጂ የሚሰጡ ፍርዶች ብዙ ጊዜ ፍትሐዊነት የጎደላቸው ሆነው ይታያሉ፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ዳኝነት ላይ የሚቀመጡት ግለሰቦች ስለ አስገድዶ መድፈር የሚኖራቸው አመለካከት፣ ማስረጃ ላይ የሚኖራቸው ዕይታ፣ ድርጊቱን እንዴት ይመለከቱታል? ውጤቱንስ እንዴት ያዩታል? የሚለው መሠረታዊ ነገር የዳኞችን ግላዊ አመለካከት የያዘ ፍርድ እንዲሰጡ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በቂ መረጃ እያለ መረጃ የለም በሚል ኢፍትሐዊ ውሳዎኔች ይሰጣሉ፡፡ ተጠርጣሪውን በአነስተኛ ዋስ መልቀቅና እንዲያመልጥ መንገድ መክፈት፣ አንዳንድ ቅጣቶች ላይ እላግባብ ማቅለያ በማድረግ፣ ኢፍትሐዊ ፍርድ ሲሰጥ ይታያል ይላሉ፡፡

ይህንን በተመለከተም በአንድ ወቅት በፍርድ ሒደት ያስተዋሉትን እንዲህ ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ወንጀሉ ስለመፈጸሙ ሙሉ መረጃ ነበረ፡፡ ነገር ግን ዳኛው ፍርዱን ሲያስተላልፉ ‹ሴቶች በጉያቸው እሳት ይዘው የሚዞሩ ፀብ አጫሪዎች ናቸው› የሚል ጽሑፍ አስፍሮ ወንጀለኛውን በነፃ ለቀቀው›› ይላሉ፡፡

ስለዚህም በፍርድ ቤት የሚሰጡ ፍርዶች ፍትሐዊ እንዲሆኑ ሕጉ ሳይሆን፣ በቅድሚያ መስተካከል ያለበት በፍርድ ላይ የሚስተዋሉ የግላዊ አመለካከቶች መቅረት እንደሆነ ወ/ሮ ዜናዬ በአጽንኦት ይገልጻሉ፡፡

በመረጃ እጥረት ምክንያት ወደ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የሚቀሩ ኬዞችን በሚመለከት ማኅበረሰቡ ያየውን ሁሉ በመመስከር ለመረጃ መጠናቀር የበኩሉን ቢያበረክት፣ ችግሩ እልባት እንደሚያገኝ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በወንጀለኞች ላይ የሚተላለፉ ፍርዶች በማኅበረሰቡ ላይ አስተማሪና መቀጣጫ ሆነው ማለፍ አለባቸው›› ሲሉም ያክላሉ፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>