የጠ/ሚ/ር ስልጣን ወደ ሕወሐት ለመመለስ የፓርቲው ቁልፍ አመራሮች በምስጢር ሲመክሩ መስንበታቸውን የቅርብ ምንጮች አስታወቁ። በአቶ ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል፣ አባይ ፀሐዬ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ጄ/ል ሳሞራ የኑስ፣ ፀጋይ በርሔ፣ አርከበ እቁባይና ስብሃት ነጋ የሚመራው የሕወሐት ከፍተኛ አመራሮች ከዚህ ቀደም ሲካሂዱት በነበረውና ህወሀት የጠ/ሚ/ ርነት ስልጣን መልሶ መያዝ ይኖርበታል፣ የሚለውን ምክክር ከዳር ለማድረስ አቋም መያዘያቸውን ያስታወቁት ምንጮቹ በተለይ በቅርቡ የተካሄደው የአራቱ ፓርቲዎች ጉባኤ ላይ በብአዴንና ኦህዴድ በኩል ቅሬታና ተቃውሞ እየበረታ በመምጣቱ የሕወሐት አመራሮች ስልጣኑን በእጃቸው ለማስገባት ቆርጠው መነሳታቸውን አስረድተዋል። በብአዴን በኩል የአቶ በረከት ስሞን ከስልጣን መገፋት በደጋፊዎችቻቸውና አመራሩ በኩል ቅሬታ መፍጠሩን የጠቆሙት ምንጮቹ በረከት ስሞን የጠ/ሚ/ር ሃ/ማርያም አማካሪ ተብለው ቢሾሙም ነገር ግን በጠ/ሚ/ር ፅ/ቤት ቢሮ እንዳልተሰጣቸውና የተሰጣቸው ካዛንቺስ አካባቢ የሚገኘው የቀድሞ የደህንነት ቢሮ መሆኑን ምንጮቹ ገልፀው በዚህ ቢሮ ኩማ ደመቅሳ እንደሚገኙና በጠ/ሚ/ር ፅ/ቤት አዲስ ቢሮ ተገንብቶ ይሰጣችኋል የተባለው ተግባራዊ እንዳልሆነ አያይዘው አስረድተዋል። በጠ/ሚ/ር ፅ/ቤት ቢሮ የተሰጣቸውና ከአቶ ሃ/ማርያም እያንዳንዷ እንቅስቃሴ ያልተለዩት አርከበ እቁባይ፣ አባይ ፀሐዬና ፀጋይ በርሄ ሲጠቀሱ በም/ጠ/ሚ/ር ቦታ ደብረፂዮን መኖራቸውን ምንጮቹ አመልክተዋል። ለሕወሐት አመራሮች ሌላው ራስ ምታት የሆነባቸው የኦህዴድ ፓርቲ ከሕወሐት እኩል መገዳደር እያሳየ መምጣቱ ነው ያሉት ምንጮቹ በተለይ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ኦህዴድ የተለያዩ የስልጣን ጥያቄዎች በማንሳት ድፍረት እያሳየ መጥቷል ብለዋል። ሕወሐት የጠ/ሚ/ርነት ስልጣኑን መቆጣጠር የፈለገበት አንዱ ምክንያት ይህ መሆኑን ምንጮቹ አልሸሸጉም። በኦህዴድ በኩል የጠ/ሚ/ር ስልጣን ለኦሮሞ ይገባል በሚል ከዚህ ቀደም የነበረው የሕወሀት ስልጣንን አንሰራፍቶ የመያዝ አካሄድ መገታት አለበት የሚል አቋም እንደተያዘ ያስረዱት ምንጮቹ በተለይ የህወሀት አመራር የኦህዴድ አካሄድ እንዳልተዋጠለትና ከዚህ ቀደም ማን ጠ/ሚ/ር ስልጣን ይያዝ የሚለው የህወሀት ምክክር በእንጥልጥል ቆይቶ በቅርቡ ግን ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ስልጣኑን መያዝ አለበት የሚል ውሳኔ ላይ መድረሱን ምንጮቹ አስገንዝበዋል። የደብረፂዮን ወደ ጠ/ሚ/ር ስልጣን የማምጣት እቅድ በተመለከተ አርከበ እቁባይ ተቃውሞ አሰምተው መከራከራቸውንና በመጨረሻ ግን ኦህዴድና ብአዴን ለመጨፍለቅ ሲባል አርከበ መቀበላቸውን ምንጮቹ አመልክተዋል። የህወሀት አመራሮች ከስምምነት የደረሱበትን ጉዳይ ከቀጣዩ ምርጫ በኋላ ጠ/ሚ/ር አቶ ሃ/ማርያም ደሳለኝን ከብቃት ማነስ ጋር በማያያዝ ከስልጣን ለማውረድና በምትካቸው የጠ/ሚ/ርነቱን ቦታ ለደብረፂዮን ለመስጠት መወሰናቸውን ምንጮቹ አጋልጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አዜብ መስፍን ከባለቤታቸው ህልፈት በኋላ የፓርቲው ሊቀመንበርና የጠ/ሚ/ር ስልጣን ለመረከብ አቅደው እንደነበረ ታማኝ ምንጮች አጋለጡ። የደህንነት ዋና ሹም የነበረው ወ.ስላሴ ወ/ሚካኤልን ከፊት በማስቀደም ወ/ሮ አዜብ የሞከሩትና በፓርቲው አንዳንድ አመራሮች “መፈንቅለ ድርጅት ሙከራ” ሲሉ ፈረጀውታል። ከምንጮቹ የተገኘው ዝርዝር መረጃ ተከታዩን ይመስላል። አቶ መለስ ዜናዊ መሞታቸውን ተከትሎ በሕወሐት ውስጥ ሁለት አይነት ቡድኖች ብቅ አሉ። ወ/ሮ አዜብ የድርጅቱ ሊቀመንበር በመሆን የጠ/ሚ/ር ስልጣኑን ለመረከብ ካልሆነም ምክትል ጠ/ሚ/ርነትን ለመቆናጠጥ ከፍተኛ ፍላጐት አሳደሩ። ከአዜብ ጐን የቆሙት በረከት ስሞኦን “የመለስን ራዕይ የማስፈፅመው እኔ ነኝ” ሲሉ ለካድሬዎቻቸው ቀሰቀሱ። በአንፃሩ እነስብሃት ነጋ ከጀርባ የሚመሩትና ፀጋይ በርሄ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ አርከበና ደብረፂዮን ያሉበት ቡድን በተቃራኒው ቆሞ በውስጥ አድፍጦ የፖለቲካ መስመሩን እያስተካከለ ነው። አዜብ ከጐናቸው ያሰለፏቸው የደህንነት ሹም ወ/ስላሴ፣ ገ/ዋህድን እንዲሁም ሚሊየነሩ ነጋ ገ/እግዚያብሄር መቀሌ ድረስ ኔትዎርክ ዘረጉ። አዜብን የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጐ ለማስመረጥ አዜብ የመደቡት በ10ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በአቶ ነጋ በኩል ወጪ እየተደረገ በነወ/ስላሴ አማካይነት ለበርካታ ካድሬዎች ይታደል ጀመር። አዜብ ያንን ሁሉ ገንዘብ ያለምንም ጠያቂ ፈሰስ ማድረጋቸውና ያለመጠየቃቸው አስገራሚ ነበር። ለካድሬዎች በነፍስ ወከፍ ከ3 እስከ 8 ሚሊዮን ብር ተከፋፈለ። ካድሬው ድምፅ ለአዜብ በመስጠት የሕወሐት ሊ/መንበር ማድረግ እንዲሁም ወ/ስላሴን በፓርቲው ማ/ኮሚቴ አባልነት ለማስመረጥ በተጨማሪ ጌታቸው አሰፋን እንዳይመረጥ ማድረግ የሚሉ መመሪያዎች ገንዘቡን ለሚቀበሉ ካድሬዎች ጥብቅ መመሪያ ከነወ/ስላሴ ተላለፈ። ካድሬው እነወ/ስላሴ የሰጡትን ገንዘብ በመቀበል ትእዛዙን ተፈፃሚ እንደሚያደርግ ነገራቸው። ጉዳዩን ሰምተው እንዳልሰሙ የሆኑት እነጌታቸው አሰፋ በጐን ካድሬውን እያስጠሩ « የሚሰጧችሁን ገንዘብ ተቀበሉ። የሚሏችሁን እሺ በሉ። በጉባኤው ላይ ግን ከእኛ ጐን ትቆማላችሁ» ሲሉ በማስጠንቀቂያ መልክ ነገሩ። ካድሬው ከነጌታቸው ጐን እንደሚቆም ቃል ገባላቸው። እነወ/ስላሴ፣ አባይ ወልዱ፣ ገ/ዋህድ..እንዲሁም በባለሃብት ሽፋን የአዜብን ተልእኮ ለማስፈፀም ሲሯሯጡ የከረሙት ነጋ ገ/እግዚያብሄር ጉባኤው ሳምንት እየቀረው በመቀሌ “ቡቡ ሂልስና አክሱም” በመሳሰሉ ሆቴሎች ካድሬውን በግብዣ ሲያንበሸብሹ ሰነበቱ።
የጉባኤው እለት ደረሰ። ለሕወሐት ሊቀመንበርነት እጩዎች ሲጠቆሙ ወ/ስላሴ እጅ በማውጣት “አዜብ መስፍን” ሲል ጠቆመ። ተሰብሳቢው ድጋፍና ተቃውሞ ሲጠየቅ 12 ጣቶች (ድምፆች) ብቻ ሲደግፉ የተቀረው አዜብን በመቃወም ውድቅ አደረገው። አባይ ወልዱ፣ ወ/ስላሴ፣ ቴዎድሮስ ሃጐስ፣ ትርፉ፣ በየነ፣ ገ/ዋህድ…ለአዜብ ድጋፍ ከሰጡ 13 ድምፆች ይጠቀሳሉ። አዜብ « የመለስ ራዕይ ሳይበረዝ ሳይከለስ ለማስቀጠል..» አልጨረሱም የመድረኩ መሪ ጣልቃ ገብተው « ስነ ስርዓት ..አሁን የእጩዎች ምርጫ እያካሄድን ነው» ሲል አርከበ ቀበል አድርግው « የመለስ ራዕይ የሚባል የለም። የፓርቲው ራዕይ ነው ያለው» ሲሉ አዜብ በግልምጫ እያዩ ተናገሩ። ካድሬው እንደካዳቸው ያወቁት አዜብ ንዴት በገፅታቸው ላይ ይነበብ ነበር። ብሽቀት የገባው ወ/ስላሴ እቅዳቸውን ጌታቸው እንዳኮላሸው የተረዳ ይመስላል። እጁን በማውጣት « ጌታቸው አሰፋ ለማ/ኮሚቴ አባልነት አይመጥንም። ሰካራም ነው፣ ሴሰኛ (ሴት በማማገጥ) ነው። ውሎና አዳሩ ሸራተን ነው። እንዳውም አቶ መለስ ዜናዊ በጌታቸው ዙሪያ ማጣራት እንዲካሄድ ያስጀመረው ምርመራ ነበር። ውሳኔ ሊሰጥበት ጫፍ ሲደርስ እንዳጋጣሚ ሞት ቀደመው። ስለዚህ ጌታቸው ለፓርቲው ማ/ኮሚቴ አባልነት አይመጥንም» በማለት በእልህ ስሜት ይናገራል። አስመላሽ ወ/ስላሴ (በቅፅል ስማቸው አባይ ነብሶ- በፓርላማ ከመለስ ዘናዊ ኋላ አዘውትረው የሚቀመጡና ጥቁር መነፅር የሚያጠልቁ አይነስውር) እጃቸውን በማንሳት በዚህ ዙሪያ መናገር እንደሚፈልጉ ይጠይቃሉ። ሲፈቀድላቸው እንዲህ አሉ፥ « አሁን ወ/ስላሴ እንዳለው በጌታቸው ዙሪያ ማጣራት ስናካሂድ ከነበርነው ሶስት ሰዎች አንዱ እኔ ነኝ። እንድናጣራ ያዘዘን መለስ ነው። የቀረበልን ጥቆማ “ጌታቸው ቪላ ቤት ገንብቷል፣ ሙስና ውስጥ ገብቷል” የሚሉ ነበሩ። ረጅም ጊዜ ስናጣራ ቆየን። ነገር ግን የተባለውን ቤትም ሆነ በሙስና ያፈራው አንዳች ነገር ልናገኝ አልቻልንም። ከዚያ በጌታቸው ላይ ጥቆማውን ያቀረበው ወይም ያመጣው ማነው?.ብለን ስንጠይቅ ወ/ስላሴ መሆኑን አወቅን። በወ/ስላሴ ዙሪያ ለምን ማጣራት አናካሂድም ብለን ጀመርን። በስሙ፣ በወንድምና እህቱ እንዲሁም በቤተሰቡና በሌሎች ግለሰቦች በሙስና መበልፀጉን አረጋገጥን» በማለት የሙስናውን ማስረጃ በዝርዝር አባይ ነብሶ ለጉባኤው አቀረቡ። ለማ/ኰሚቴ የተጠቆመው ወ/ስላሴ 2 ድምፅ ብቻ በማግኘቱና ከጨዋታ ውጭ በመሆኑ ኩም አለ። ጉባኤው በነጌታቸው አሰፋ ድል አድራጊነት ተጠናቀቀ። የሙስናዋን ፋይል የያዙት ጌታቸው አሰፋ በቅድሚያ ያደረጉት ወ/ስላሴን ከስልጣን ማባረር ነበር። ከዛም እነገ/ዋህድን ጨምሮ ለአዜብ ገንዘብ ሲረጩ የነበሩትን እነነጋ ገ/እግዚያብሄርን በሙስናው ፋይል እስር ቤት መክተት የሚለውን እቅድ ተግባራዊ አደረጉ። የደህንነቱን ቢሮ እንዳሻው ይፈነጭበት የነበረውና የአቶ መለስና አዜብ ቀኝ በመሆን አገሪቱን በአፈና መዋቅር ሲያሰቃያት የከረመው ወ/ስላሴ ወ/ሚካኤል በበርካታ የደህንነት አባላት ጥርስ የተነከሰበት ጭምር ነበር። ይህን የሚያውቁት ጌታቸው አሰፋ በደህንነቶች ለተከታታይ ቀናት ወ/ስላሴ እንዲደበደብ ማድረጋቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።