Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የሐበሻ ሬስቶራንት ሥራ አስኪያጅ ድምፃዊት ኢየሩሳሌም አስፋው (ጄሪን) ለምን ውስጥ እግሯን እና ታፋዋን በቢለዋ ወጋቻት? (ያንብቡ)

$
0
0

ድምፃዊት ኢየሩሳሌም አስፋው (ጄሪ) በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ‹ሀሎ አዲስ አበባ› በተሠኘ ተወዳጅ ዘፈኗ ትታወቃለች፡፡ እስካሁን ድረስ ሁለት የሙዚቃ አልበሞች የሠራች ሲሆን ስድስት ያህል ነጠላ ዜማዎችም አሏት፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ ባደረባት የሙዚቃ ፍቅር የተለያዩ ድምፃዊያንን ዘፈኖች ትጫወት የነበረ ሲሆን ታዋቂው ኮሜዲያን አለባቸው ተካ በችሎታዋ ተደንቆ በተወዳጁ ‹‹አለቤ ሾው›› የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ላይ እንግዳ አድርጓት ነበር፡፡ የተለያዩ ነጠላ ዜማዎች ከማውጣቷ ጎን ለጎን ሶስተኛ የሙዚቃ አልበሟን እየሠራች ባለበት በዚህ ወቅት ከሠዎች በተሠነዘረባት ጥቃት ያልተጠበቀ ጉዳት ደርሶባት ህክምና እየተከታተለች ትገኛለች፡፡ የቁምነገር መጽሔት ድምፃዊቷን ያለችበትን ሁኔታ አነጋግሯል፤ መልካም ንባብ
1425440_1379530885635493_1774138377_o
ቁም ነገር፡- ሙዚቃ መጫወት የጀመርሽው መቼ ነበር?
ኢየሩሳሌም፡- ወደ ሙዚቃ ህይወት የገባሁት በልጅነቴ ነው፡፡ ወላጅ አባቴ ከመሞቱ በፊት ‹‹ልጄ ዘፍና ትጦረኛለች›› ይል ነበር፡፡ አያቴ ግን አይፈቅድልኝም ነበር፡፡ ቀበሌ እሠለጥን በነበረበት ጊዜ ከሠባ አምስት ተወዳዳሪዎች መካከል አንደኛ ወጥቼያለሁ፡፡ በውድድሩ ላይ እኔ የምዘፍነው የንዋይን ነው ስላቸው ሳቁብኝ፡፡ ከዚያም የማርታ አሻጋሪን፣ የበዛወርቅ አስፋውንና የአስቴር ከበደን ዘፈኖች ዘፍኜ አሸነፍኩና እዚያ ጀመርኩ፡፡
ቁም ነገር፡-ከዚያ በኋላስ የት የት ሠርተሻል?
ኢየሩሳሌም፡- ሴሌክት የምሽት ክለብ ለሠባትና ስምንት ዓመት ያህል የሠራሁ ሲሆን ‹ሀሎ አዲስ አበባ›› የሚለው የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበሜ ከወጣ በኋላ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ የራሴን ምሽት ክለብ ከፍቼ መስራት ጀምሬ ነበር፡፡ ግን አላዋጣኝም፡፡ ከዚያ ደግሞ ‹‹ከሚሚ መጋሎ››፣ ሐሊማ አብዱረህማን እና ከዝናሽ (ሀቢቢ) ጋር በጋራ የምሽት ክለብ ከፍተን ለመስራት ሞክረን ነበር፡፡ በመሀል ልጅ ወለድኩና አቋረጥኩኝ፡፡
ቁም ነገር፡- ወደ ሐበሻ ሬስቶራንት ገብተሽ መዝፈን የጀመርሽው መቼ ነበር?
ኢየሩሳሌም፡- ከአምስት ከስድስት ዓመት ምናምን በፊት ነው፡፡ በ2005 ዓ.ም ሮዛ ግዛው በተባለች ማናጀሬ በኩል ወደ ዱባይ ሄጄ ከታንዛንያ፣ ከናይጄሪያና ከኮንጎ የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር እየሠራሁ ሙሉውን ዓመት አሣልፌያለሁ፡፡ ገራጅ የሚባል የምሽት ክበብ ነበር የምንሠራው፡፡ እንዲያውም ሌሎቹ ባለሙያዎች በየሶስት ወሩ ሲቀያየሩ እኔ ምንም ቪዛ ሳልቀይር እዚያው መቆየት ችያአለሁ፡፡ ክለቡ ከሠባት መቶ እስከ ስምንት መቶ የሚደርሡ ሰዎች ይይዛል፡፡
የጊኒ፣ የታንዛኒያ፣ የናይጄሪያ፣ የኬንያ ዜጎች እንዲሁም አረቦችና ህንዶች የሚዝናኑበት ሲሆን አንዳንድ አበሾችም አልፎ አልፎ ይመጡ ነበር፡፡ ሽልማታቸው፣ ፍቅራቸው ሁሉ ልዩ ነው፡፡ የእነሡን ሙዚቃ የምሠራላቸው ያህል በተለያየ ሁኔታ ነው የሚያዩኝ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ዘፋኝ አይተን አናውቅም ብለው ነበር ገንዘብ የሚሸልሙኝ፡፡
ቁም ነገር፡- ሐብታም ሆነሽ ነበራ ከውጪ የመጣሽው? (ሣቅ)
ኢየሩሳሌም፡- ብዙ ቤተሠብ ነው ያለኝ፡፡ ቤት ተከራይቼ ነው የምኖረው፡፡ ዱባይና አቡዳቢ እየተመላለስኩ ቤተሠቦቼን ነበር የምረዳው፡፡ ያስተማርኳቸው፣ የዳርኳቸው አሉ፡፡ ለእኔ ብዬ ያደረኩት ነገር የለም፡፡
ቁም ነገር፡ እስካሁን ድረስ ምን ያህል የሙዚቃ አልበሞች ሠርተሻል?
ኢየሩሳሌም፡- የመጀመሪያ አልበሜ ‹ሀሎ አዲስ አበባ› የሚለው ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም በህዳር ወር ነበር የወጣው፡፡ ‹ይጠራኛል› የሚል ሌላ አልበምም አሣትሜ ነበር፡፡ በአጋጣሚ የክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ህይወት ያለፈበት ቀን ላይ ነበር ሣይታሠብ የወጣው፡፡ በዚህ ምክንያት ሣይደመጥ ቀረ፡፡ በ2006 ዓ.ም ከዱባይ የመጣሁት ለአልበም ሥራ ነው፡፡ የአልበም ሥራ መስራት ጀምሬያለሁ፡፡ የሁለት ዓመት ቪዛ እያለኝ ነው የአልበም ሥራዬን ለመጨረስ የመጣሁት፡፡ ጥሩ ጥሩ ግጥምና ዜማዎች ሠብስቤያለሁ፡፡ ከአለማየሁ ይለፍ ጋር ነው የምሠራው፡፡
ቁም ነገር፡- የተለያዩ ነጠላ ዜማዎችም አሉሽ አይደል?
ኢየሩሳሌም፡- አዎ! ከ‹ሀሎ አዲስ አበባ› አልበሜ በኋላ ያወጣሁት ‹ጀነናው› የሚል ነጠላ ዜማ አለ፡፡ የሄለን በርሄ ‹‹ኦዛዛ አሌና›› የተሠኘው ዘፈን ያለበትና የሌሎች ዘፋኞችንም ሥራዎች የያዘ ፣‹ድሪም ኮሌክሽን› የሚል አልበም ላይ የተካተተ ነበር፡፡ ‹አግባ አግቢ› የሚል ነጠላ ዜማም ሠርቼያለሁ፡፡ ‹ደቅ ላይ› የሚል የባህል ዘፈን፣ ‹ዞማ ዞማ› የሚል በኮንሶ ስልት (ሪትም) የተሠራ ነጠላ ዜማም አለኝ፡፡ የተለያዩ ቪዲዮ ክሊፖችንም እሠራለሁ፡፡ አላረፍኩም፡፡ እለፋለሁ፡፡ በጣም እለፋለሁ፡፡ የተቀመጥኩበት ጊዜ የለም፡፡ እንደኔ የሚለፋ ሠው ያለ አይመስለኝም፡፡ ለምን እግዚአብሔር ይህን እንዳደረገ አላውቅም፡፡
ቁም ነገር፡- ቅድም ልጅ እንዳለሽ ነግረሽኛል፡፡ የትዳር ሁኔታ ግን አላነሣንም?
ኢየሩሳሌም፡- ልጅ ወልጄያለሁ፡፡ አባቱ ከእኔ ጋር አይኖርም፡፡ ተለያይተናል፡፡
ቁም ነገር፡- ስንት ዓመቱ ነው?
ኢየሩሳሌም፡- እግዚአብሔር የተመሠገነ ይሁን ስምንተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ልደቱን ለማክበር ሶስት ቀን ሲቀረው ነው የታረድኩት፡፡

ድምፃዊት እየሩሳሌም እግሯን እና ታፋዋን ከተሰፋች በኋላ

ድምፃዊት እየሩሳሌም እግሯን እና ታፋዋን ከተሰፋች በኋላ

ቁም ነገር፡- በቅርቡ አንድ አደጋ ደርሶብሽ እንደነበር ሠምተናል፡፡ ምን ነበር ምክንያቱ? ሁኔታው እንዴት ተፈጠረ?
ኢየሩሳሌም፡- ‹እስማማለሁ አልስማማም› በተሠኘው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ እንግዳ ሆኜ ቀርቤ ነበር፡፡ እና ፕሮግራሙ በሚለቀቅበት ምሽት ቀድሜ ነው ወደ ሐበሻ ሬስቶራንት የገባሁት፡፡ ለምሽት ስራዬ ዝግጁ ሆኜ ሚኒስከርት ለብሼና ሂል ጫማ አድርጌ ነው ወደ ሬስቶራንቱ የገባሁት፡፡ ሰው ገብቷል ሙዚቃ ግን አልተጀመረም፡፡ ለባለቤቱ ደውዬ የሙዚቃ ስራ እስከሚጀመር ቴሌቪዥን እንዲያስከፍትልኝ ስነግረው እርሡ ለማናጀሯ ደውሎ ‹‹ሙዚቃ አልተጀመረም›› ሲላት ከእኔ ጋር መነጋገር ትጀምራለች፡፡ ከእሷ ጋር ስንነጋገር ሁለቱ የሬስቶራንቱ አስተናጋጆችሙዚቃ እንዳልጀመረ ለምን ነገርሽው በማለት መጥተው አንዷ ገፍታ ጥላኝ ላዬ ላይ ወጣች፤ ሌላኛዋ ደግሞ ፀጉሬን ያዘችኝ፡፡ በዚህ መሀል ማናጀሯ ቢላ ይዛ መጥታ የግራ እግሬ መሀል ታፋዬ ላይ፣ ቀኝ እግሬ መቀመጫዬ ላይ እና የቀኝ ውስጥ እግሬን ትወጋኛለች፡፡ የሠውነቴ መጋጋጥ የሚነገር አይደለም፡፡ በወቅቱ ራሴን ስቼ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ፍርድ ይስጠኝ፡፡ የደረሠብኝን ጉዳት እንደዚያ ተቀድጄ ሠውነቴ እየደማ ለሆቴሉ ባለቤት ሄጄ አሣየሁት፡፡ እሡ ሀሌሉያ ክሊኒክ ወስዶ ህክምና እንዳገኝ አደረገ፡፡ ከዚያም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ አስመዝግቤ ሁለቱ ሴቶች በቁጥጥር ስር ሲውሉ የሬስቶራንቱ ማናጀር ትጠፋለች፡፡ በቢላ የወጋችኝ የሬስቶራንቱ ማናጀር ለአሥራ ሁለት ቀናት ጠፍታ የእነርሡን መታሠር ስትመለከት ለፖሊስ እጇን ሰጠች፡፡ አሁን ሶስቱም በሦስት ሺህ ብር ዋስ ተፈትተው የፍርድ ቤት ቀጠሮ እየተጠባበቅን ነው፡፡
ቁም ነገር፡- አድናቂዎችሽስ የደረሠብሽን ነገር ሲመለከቱ ምን ተሠማቸው?
ኢየሩሳሌም፡- ማመን ከምችለው በላይ ነው የሠው ምላሽ፡፡ ‹ስንት ዓመት ጠፍተሽብን የመጣሽ ልጅ ምን ብታደርጊያቸው ነው ይህን ያደረሡብሽ› ብለውኛል፡፡ ያላዘነ፤ የማያለቅስ የለም፡፡ ከሱዳንና ከዱባይ እየደወሉ ሲያለቅሱ እኔንም ያስለቅሡኛል፡፡ ብዙ ቦታዎች ላይ መወጋቴ ነው ትልቁ አደጋ፡፡ ደም በብዛት ነበር የፈሠሠኝ፡፡
ቁም ነገር፡- አደጋውን ካደረሱብሽ ሠዎች ጋር የቆየ ቂም ነበራችሁ?
ኢየሩሳሌም፡- ማናጀርዋ ወደ ሬስቶራንቱ ከመጣች ዘጠኝ ወሯ ነው፡ ፡ ሁለቱ ደግሞ ከአስር ዓመት በላይ የቆዩ አስተናጋጆች ናቸው፡፡ መሀል ላይ ማናጀሯ ደሞዝ ስትቆርጥ፣ ሠራተኛ ስታባርር ለምንድነው ይህን የምታደርጊው እያልኩ እናገር ነበር፡፡ ያ ነገር ነው እዚህ ደረጃ ያደረሰን፡፡ ለሠሚም፣ ለተመልካችም፣ ለራሴም ነው (የደረሠብኝ ጉዳት) ትንግርት የሆነብኝ፡፡ እንደተገረዘ ህፃንነበር ቆሜ የምሸናው፡፡ ለሥራ ወጥቼ ያልሆነ ነገር ሆንኩኝ፡፡ ወይ እንደ ጓደኞቼ እንደሚካያ እና እንደ ኢዮብ መኮንን ታምሜ ሰው ሠምቶ ብሞት የተሻለ ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- አሁን ያለሽበት ሁኔታ እንዴት ነው? ጤንነትሽ?
ኢየሩሳሌም፡- ከሠባት ቀን ህክምና በኋላ የቤቱ ባለቤት እኔን ማሣከም አቁሟል፡፡ የጭንቅላቴን ውጤት መስማት አልተቻለም፡፡ ህክምና ላይ ያለው ነገር በሙሉ ቆሟል፡፡ የሁለት ወር ደመወዝም አልተሠጠኝም፡፡ ቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼና እኔ ራሴ ነኝ እየተሯሯጥን ያለነው፡፡ አሁን ቤት ውስጥ ነው ያለሁት፡፡ መጥቶም፣ ጠይቆኝም አያውቅም፡፡ የውስጥ እግሬና ጭንቅላቴ አሁንም ያመኛል፡፡ አንደኛው ስካን ማድረጊያ መሣሪያ በሀገር ውስጥ የለም ተብሎ እየፈለግኩኝ ነው፡፡ እግሬ በጣም ነው የተጎዳው፡፡ ውስጥ እግሬ ድረስ ነ በር የተወጋሁት፡፡ ሌላውን የልጄ አምላክ አትርፎኛል፡፡
ቁም ነገር፡- ከዚህ በኋላ አበሻ ሬስቶራንት ተመልሠሽ የምትሠሪ ይመስልሻል?
ኢየሩሳሌም፡- በፍፁም፡ ፡ አሁን ለሦስተኛ ስራዬ ‹‹ውብ አዲስ አበባ›› የሚል ትልቅ ፖስተር (አበሻ ሬስቶራንት) ለጥፌያለሁ፡፡ ሰው እኔን ብሎ ነው የሚመጣው፡፡ ማናጀሯ ግን አርቲስትነቴን እንኳን አላየችውም፡፡
ቁም ነገር፡- ከዚህ ቀደም ‹‹ሐሎ አዲስ አበባ›› የሚል የሙዚቃ አልበም አሣትመሻል፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹ውብ አዲስ አበባ›› የሚል አልበም ነው እየሠራሽ ያለሽው፡፡ አዲስ አበባ ላይ የተለየ ትኩረት የሰጠሽበት ምክንያት ምንድን ነው?
ኢየሩሳሌም፡- ጨርቆስ ነው ተወልጄ ያደግኩት፡፡ ከወላጅ አባቴ ቤተሰቦች ጋር ነው ያደግኩት፡፡ አዲስ አበባ አገርህ ናት፤ መለያህ ናት፡፡ ውጪ ሀገር በምሔድበት ወቅት ይከፋኛል፡፡ እዚህ ደግሞ አየሩ ያምራል፡፡ ባህል አለኝ፡፡ ያለው ለሌለው ያበድራል፡፡ እዚያ ናፍቆት አለ … ብዙ ነገር አለው፡፡
አሁን የምሠራው ‹‹ውብ አዲስ አበባ›› የሚል አልበም ደግሞ የአሁኗ አዲስ አበባ መጀመርያ ከነበረችው የተለየች መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡

Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>