* የእህት ሰሚራ እንግልት
* የጠፉት ኮንትራት ሰራተኞች ያለ እስር ወደ ሀገር እንዲገቡ የሚያስችለው መመሪያ
* የእህት ሰሚራ እንግልት
===============
ትናንት ምሽት ከምስራቃዊው የሳውዲ ግዛት በአርአር ከተማ የኢንተርኔየት ስልክ መልዕክት ደረሰኝ …እህት ሰሚራ ነበረች ፣ ሰሚራ ( ስሙ የተቀየረ) ከሁለት አመት ከመንፈቅ በፊት ሳውዲ በኮንትራት ስራ የገባች እህት ናት ፣ የፊስ ቡክ ጓደኛየ የሆነችው የኢንባሲ ጉዳይ ፈጻሚ መስያት እንደነበር አስታውሳለሁ። በመረጃ መረቡ ተገናኝተን ስንጫወት ግን የኢንባሲም ሆነ የቆንስል መስሪያ ቤቱ ሰራተኛ አለመሆኔን ገልጨላት ያም ሆኖ ከሴት ወንድ ይሻላልና እንመካከለራለን ብያት ጥሩ ጓደኛየ ከሆኑት አንዷ ብርቱ ጓደኛየ እህቴ ናት ።
እህት ሰሚራ ለተከታታይ አንድ አመት እየደወለች ያለባትን ችግር የምታጫውተኝ የምታማክረኝ እህትም ናት ። በእለታት በአንዱ ቀን ግን ሰሚራ እንደተለመደው ከአሰሪዋ ጋር ከፍ ያለ ጸብ ላይ እንደደረሱ በነገረችኝና እንድትረጋጋ ባማከርኳት ማግስት መልሳ ሳትደውልልኝ ቀረችና እንደተለያየን ይህው አመት ነጎደ … ሰሚራ ባላሰብኩት በዚህ አጋጣሚ ጠፋችብኝ ፣ የጸብ ድብደባውን ክብደት ታጫውተኝ ነበርና ለማንም ባልናገረውም የእሷ እጣ ፈንታ ውስጤን ሁሌም ያውከዋል ፣ አሳስቦኛል … የሰሚራ ህይወት በወንጀል አልፎ ሌላ መከራ እሰማለሁ ብየ እሰጋለሁና ” ሀበሻ ገደለ! ” የሚለውም ዜና ስሰማና ሳነበው ሁሌም ሰሚራ ትታየኛለች … ምስኪኗ ሰሚራ ለቤተሰቦችዋ መትረፍ ስላለባት ለመግደል ቀርቶ ለመደባደብ ፍላጎት እንደሌላት አጫውታኝ ነበርና “…ተበድላ ፣ ተገፍታ ማንም ሳይደርስላት የትም ወድቃ ይሆናል!” የሚለው ከአዕምሮየ የማይጠፋው ስጋቴ ሆኖ ከርሟልና አሁን መኖሯን በማወቄ ደስ አለኝ …ተመስገን ያሰጋኝ ሁሉ ግን በሰሚራ ላይ አልሆነም …
አመሻሹ ላይ ከሰሞነኛው በኮሚኒቲ የከሸፈ ስብሰባና ነዋሪው በምርጫው ላይ ባሳየው ሽሽት ዙሪያ ረብ የለሽ ውጥንቅጥ ሙግት ላይ እያለሁ ነበር የእህት ሰሚራ ጥሪ ያስናገድኩትና ሰላም መሆኗን የተረዳሁት ፣ የሆነውን ማመን አቃተኝ … መጫወት ያዝን !
* የተገኘችው ሰሚራ …
============
ሰሚራ የነበረችበን ምስራቃዊ የሳውዲ ግዛት አርአርን ከአሰሪዎቿ ጠፍታ ለቃዋለች ፣ ዛሬም እንደወትሮዋ እያለቀሰች ያለችበትን ሁኔታ በዝርዝር አጫወተችኝ ፣ አደዋወሏ እንደ ቀድሞው ምሬቷን ልታወራኝ ሳይሆን በመረጃ በኩል የምችለውን እንድረዳት ለመማጸን ነበር …
ሰሚራ ከስደቱ እንግልት ተላቃ ወደ ናፈቋት ቤተሰቦቿዋ ወደ ሀገር ቤት መግባት ፈልጋ አንድ ደላላ ማነጋገሯንና ከፍተኛ ገንዘብ ጠይቋት ለመክፈል ፈቃደኛ ብትሆንም ከገንዘብ አልፎ የአንሶ መጋፈፍ ጥያቄ ስላቀረበላት ያንን ለሟሟላት ፈቃደኛ አለመሆኗን አጫወተችኝ ። እናም ” እባክህ ወደ ሃገር ቤት የምገባበትን መንገድ ጠቁመኝ !” አለችኝ ከቀናት በፊት ” ከአሰሪዎቻቸው የጠፉ ወደ ሀገራቸው መግባት ይችላሉ!” የሚለው መረጃ በእጀ ገብቷልና ለሰሚራ የምስራች ስለያዝኩ ደስ ብሎኛል ፣ ለተጨነቀችው ሰሚራ መንገዱ በእርግጠኝነት እንዳለ ካጫወትኳት በኋላ ከአሰሪዎቿ ስትጠፋ ወንጀል አለመፈጸሟን ለማረጋገጥ የመኖሪያ ፈቀዷን ቁጥር ተቀበልኳትና መልሸ በዚህው የፊስ ቡክ ኢንተርኔት ስልክ እንደምደውልላት ቃል ገብቸ ተለያየን !
… እህት ሰሚራ አሰሪዎቿ “ጠፋችብን ” ብለው ሪፖርት ከማድረግ ባለፈ በወንጀል እንደማትፈለግ መረጃ አሰባሰብኩና መልሸ ደወልኩላት ፣ ያም ቢሆን ሰሚራ ከወንጀል ነጻ መሆኗ የሚረጋገጠው አሻራ ስትሰጥ መሆኑን አሳወቅኳት ፣ ሰሚራ ስልኩን ስታነሳ ” ወይ ፈጣሪየ ነቢዩ ምን ልታሰማኝ ይሆን? ” ስትለኝ ከወጣው አዲስ መመሪያ ጋር ማሟላት ያለባትንና የሆነውን አጫወትኳት ፣ የተጎዳችው እህት ሰሚራ ደስታዋን የገለጸችው በእንባ ተንሰቅስቃ እያቀሰች ነበርና ውስጥ ስሜቷ ተረድቸዋለሁ …የእኔም ነፍስ የምትወደውን አገኝታለችና በሃሴት ደመቀች :)
* ሰሚራ ከአሰሪዎቿ ለምን ጠፋች ?
=====================
ከሰሚራ ጋር ስለተለያየንበት አጋጣሚና ከአሰሪዋ እንዴት እንደ ጠፋች ስታጫውተኝ ያስታወስኩት ብዙ ሰሚራዎችን ነበር ። …በኮንትራት ስራ መጥተው በበርሃው ከተሞችና ገጠሮች አበሳቸው በዝቶ ደራሽ አጥተው፣ ለከፋ የወስጥ ደዌ በሸወታ ፣ ለአዕምሮ መታወክ ፣ለወንጀልና ለተለያየ አደጋ መጋለጣቸውን አስራወሰኝናም ቆዘምኩ! የሰሚራ አጠፋፍ ከማሳዘን ማስገረም አልፎ ለቀሪዎች ካስተማረን በሰሚራ አንደበት የተነገረኝን እነሆ … ” …አሰሪየ ልትገድለኝ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጋ አልተሳካላትም ፣ ሁሌም በሌለሁበትና በማላውቀው ነገር ትመታኛለች ፣ ትሰድበኛለች …በባሏ እየቀናች ታንገላታኛለች … ለመከላከል በማደርገው ግብግብ ናላየ ዙሮ ነፍስ ከማጠፋ ብየ ጠፍቸ ወጣሁ .. አምልጨ የተጠጋሁት ካልሆነ ቦታ ነበር … ይጨንቃል ፣ ግን ሁሉም አልፏል ! ” ነበር ያለችኝ ምክንታቷን ጨምቄ ሳቀርበው … ይህንን ዘርዝራ ስታጫውተኝ የእንባ ሳግ ይቀድማትም ነበር…
ሰሚራ ብልጥና ትጉህ ሴት በመሆኗ ለዛሬ ደርሳለች ፣ ዛሬ ደግሞ ለሷ ከቤተሰብ የምትገናኝበት ወደ ሃገሯ የምትገባበት ቀን የደረሰበት መልካም ቀን ነው ! …ሰሚራን የመሰሉ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩት እህቶች በሃገራት መካከል የረባ የሁለትዮሽ ውል ባልተደረገበት ሁኔታ በኮንትራት ስራ ሳውዲና ወደ ተለያዩ አረብ ሃገራት መጥተው መግቢያ መውጫው የጨነቃቸው እህቶች ብዙ ናቸው ፣ በጭንቀት በስሜት ተነሳስተው ራሳቸውን ከፎቅ የጣሉ ፣ ራሳቸውን አንቀው የገደሉ ፣ እስከ ድብደባና ነፍስ እስከ ማጥፋት ወንጀል ህይወታቸው መቀመቅ የወረደባቸውን ቤት ይቁጠረው …
እዚህ ላይ መከራው የከበደባቸውን ድምጽ ደጋግሜ ባቀርበውም በሁሉም የአረብ ቤት ችግር አለ ማለት አይቻልም ። ቀንቷቸው ከደጎች ቤት የገቡ ከራሳቸው አልፎ ወገኖቻቸውን የጠቀሙ በርካታ እህቶች አሉ። አልፎ አልፎ እዚሁ ነዋሪ በሆኑ ጓደኞቻቸው ፣ ዘመድ አዝማድና ደላላ “ደመወዝሽ ትንሽ ነው! ” በሚል እየተታለሉ ከስራ ይጠፋሉ ፣ ይፈናቀላሉ። አልፎ አልፎን በተለያየ ምክንያት የተሻለ ኑሮ ፍለጋ “ጠግበውም” በሉት ” ተጨንቀው ” ከአሰሪዎቻቸው ይጠፋሉ ። ጠፍተው ከሰሩ በኋላ ወደ ሃገር ቤት ለመግባት ግን የእስከ ዛሬው መንገድ የወት አልነበረም ፣ ዛሬ ግን ለጊዜውም ቢሆን ያ ሁሉ ተለውጧል ፣ “የጠፉ የኮንትራት ሰራረኞች ያለ እስርና እንግልት ወደ ሀገራቸው ይገባሉ!” ተብሎ ተፈቅዷል ፣ የእህት ሰሚራ እንግልት አክትሟል ፣ እንደ እህት ሰሚራ ሩቅ አስቦ ፣ ስሜትን ተቆጣጥሮ መከራ ሰቆቃውን ላለፈው ደግሞ እንዲህ ይነጋል ….
እዚህ ላይ ማሰሪያ ትሆን ዘንድ ለሰሚራ ደላላ የምለውን ልበል …በነጻ ወደ ሀገር የመግባት ህጉ ወጥቶ እያለ ” ጉዳይሽን ልጨርስልሽ ከ5000 የሳውዲ ሪያል ክፈይኝ ፣ አንሶላም እንጋፈፍ! ” ባዩ የሀገር ልጅ ያዘንኩብህ መሆኑን ልብ በል ! …ያም ሆኖ ስታየኝ እንድትሸማቀቅ አልሻም ፣ ከስህተት መታረም ብትችል ደጋግመህ ላደረስከው ጉዳትና ክብረ ነክ ስራህ ልጆች ካሉት አባት የማይጠበቅ ጥፋት ነውና በእኔ የቀረበልህ ይህ ማስታወሻ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ከሆነህ መልካም ነው ፣ ያለበለዚያ ተበዳዮች በስም ጠርተው የሚያቀርቡትን ስሞታ አሰማ ዘንድ እገደዳለሁ ! …ዛሬ ብዙ አልልም !
እንደ እህት ሰሚራ የተንገላታችሁ በራሳችሁ ወንድም ደላላ የተጎሳቆለችሁና የተጎዳችሁ ፣ መንገዱ እንዳይጠልፋችሁ ፣ መንገዱ እንዳያደናቅፋችሁ በሳውዲ መንግስት የወጣውን መመሪያ ከዚህ በታች በዝርዝር አቅርቤዋለሁና ተመልከቱት !
*የወጣው አዲስ መሪያው ዝርዝር …
======================
በኮንትራት ስራ ወደ ሳውዲ አረቢያ መጥተው በተለያየ ምክንያት ከአሰሪዎቻቸው ጠፍተው በግል ይሰሩ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንና የተለያዩ ሀገር ዜጎች ወደ ሀገር የሚገቡበት መንገድ የጠበበ በመሆኑ በርካታዎች ለችግር ተጋልጠው ነበር ። ከሁለት ቀናት በፊት በሳውዲ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኩል ለተለያዩ ሀገሮች የቆንስልና የኢንባሲ መስሪያ ቤቶች በተላለፈ መመሪያ ከኮንትራት የጠፉ የማናቸውም ዜጎች ያለምንም አይነት እስር ወደ ሀገራቸው ሊገቡ እንደሚችሉ ይፋ ሆኗል። መረጃውን ከዚህ ጋር ባያያዝኩት የአረብ ኒውስ ዘገባ ተብራርቷል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሽሜሲ ጊዜያዊ መጠለያ እስር ቤት ተወካይ የሆኑት መሃመድ አብዱልወሃብ ኑጋሊ በኩል የተሰራጨው ይህ መመሪያ የያዘው የጋዜጣው መረጃ ያለ እስር መግባት የተፈቀደላቸው የኮንትራት ሰራተኞች በወንጀል ነጻ የሆኑትንና ከአሰሪዎቻቸው ጋር ክስ ያለባቸውን እንደማይጨምር ያስረዳል።
መመሪያው ከዚሁ ጋር በማያያዝ ሰራተኞች ጉዟቸውን ለማሳካት ማሟላት ያለባቸውን ሶስት ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጧል። ቅድመ ሁኔታዎችም የሚከተሉት ናቸው
1ኛ/ በመንግስት በኩል ያለባቸው ውዝፍ ቅጣት መክፈል
2ኛ/ በኢንባሲና ቆንስሎች በኩል አስፈላጊውን የጉዞ ሰነድ(ሊሴ ፖሴ አለያም ፖስፖርት ) ማቅረብ
3ኛ/ የአውሮፕላን ቲኬት ማቅረብ ቅድመ ሁኔታዎች እንደሆኑ መመሪያው ጠቁሟል ።
ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን መስፈርት የሚያሟሉ የጠፉ የኮንትራት ሰራተኞች በኢንባሲና ቆንስል መ/ቤቶች በኩል ሰነዶች አሟልቶ ማቅረብ እንዳለባቸው መመሪያው ያሳስባል። አስፈላጊ መስፈርቶች እንደተጠናቀቁም አሁንም በመንግስታቸው ተወካዮች አማካኝነት ጅዳ አካባቢ ላሉት መካ አጠገብ በሚገኘው የሺሜሲ ጊዜያዊ መጠለያ በመቅረብና የጣት አሸራ በመስጠት ጠቅልሎ መውጫ ቪዛ እንደሚሰጣቸው ታውቋል። ያም ሆኖ የመውጫ ቪዛው እንፈተመታላቸው በ72 ሰዓታት ውስጥ ሳውዲን ለቀው ወደ ሀገር ቤት መግባት እንዳለባቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር የተላለፈው ይህው መመሪያ ያስረዳል።
በኮንትራት ስራ መጥተው የሚጠፉ ሰራተኞች ” አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው ወደ መጡበት ሃገር ያለ እስርና እንግልት ይገባሉ “የሚለው ይህ መመሪያ በአይነቱ የመጀመሪያ ነው። ከዚህ በፊት በተሰጡት የምህረት አዋጆች እንኳ የጠፉ ሰራተኞችን አካትቶ አያውቅም። ነገር ግን ኢንባሲና ቆንስሎች የህመም ፣ በስራ ላይ ጉዳትና በደል የደረሰባቸውን የጠፉ የኮንትታት ሰራተኞችን አጥጋቢ ምክንያቶችን በመያዝ ከሳውዲ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የፖስፖርት ፖሊስ ከፍተኛ ሃላፊዎች በልዩ ሁኔታ እያስፈቀዱ ወደ ሃገር ይልኩ እንደነበር ይጠቀሳል።
ይህም በርካታ በችግር ይዋልሉ ለነበሩ ወገኖች መልካም የምስራች ነው !
ነቢዩ ሲራከ
ህዳር 20 ቀን 2007 ዓም