የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ህዳር 7/2007 ዓ.ም ጠርቶት ለነበረው የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ አርብ ህዳር 5/2007 ዓ.ም በቅስቀሳ ላይ እንደነበሩ የታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ 7 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጠባቸው፡፡የአዲስ አበባ ከተማ ም/ሰብሳቢና የምርጫ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል ወጣት ማቲያስ መኩሪያ እና የምርጫ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል ወጣት ሳምሶን ግዛቸው በቅስቀሳ ወቅት ተይዘው አራዳ ፖሊስ መምሪያ የታሰሩ ሲሆን ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ችሎት ቀርበው የ7 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ወጣቶቹ ‹‹ሽብር በማነሳሳት›› የሚል ‹ክስ› የተመሰረተባቸው ሲሆን ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ በተለይ ሌሊት ደህንነቶች በተደጋጋሚ በኃይልና በዛቻ እንደሚመረምሯቸው መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡ባለፈው የፍርድ ውሎ ታሳሪዎቹ ህጋዊ እውቅና ለተሰጠው ስብሰባ የቀሰቀሱ መሆኑን ጠቅሰው መታሰራቸው ህገ ወጥ በመሆኑ እንዲፈለቀቁ ቢከራከሩም፤ ፖሊስ ‹‹ሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ስላልተያዙ መያዝ አለብን፡፡ እነሱም ከተለቀቁ መረጃ ያጠፉብናል›› በሚል የ7 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተቀባይት አግኝቷል ለዛሬ በቀጠሯቸው መሰረት ፍርድ ቤት ቢቀርቡም ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ አንድ ሳምንት ጊዜ ለፖሊስ ፈቅዶለታል፡፡ በአንጻሩ ታሳዎቹ የቀረቧቸው ቅሬታዎችና መከራከሪያዎች ተቀባይነት ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡