ነገረ ኢትዮጵያ
በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች ለእሁዱ የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የታሰቱትን የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የሄዱት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ታሰሩ፡፡
በቅስቀሳ ወቅት የነበሩት የሰማያዊ አባላትና አመራሮች መያዛቸውን ተከትሎ የእሁዱን የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ ለስበስባና ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ያሳወቁበትን ህጋዊ ደብዳቤ በመያዝ የአባላቱና አመራሩ እስራት ህገ ወጥ መሆኑን ለማስረዳትና አባላቱን ለመጠየቅ ወደ አራዳ መምሪያ ፖሊስ ጣቢያ ያቀኑት የሰማያዊ ፓርቲ የፋይንስ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ወሮታው ዋሴ እና የአደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊው አቶ ብርሃኑ ተ/ያሬድ በፖሊስ ተይዘው ታስረዋል፡፡
በቅስቀሳ ላይ የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና አመራሮች እየታሰሩ ነው
የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር እሁድ ህዳር 7/2007 ዓ.ም ለሚያደርገው የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ ቅስቀሳ ላይ የነበሩ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ታሰሩ፡፡
የብሄራዊ ምክር ቤት አባል የሆነው አቶ ዮሴፍ ተሻገር እንዲሁም የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የሆነው ሲሳይ በዳኔ መገናኛ አካባቢ ቅስቀሳ ላይ በነበሩበት ወቅት ታስረዋል፡፡
በተመሳሳይ የምርጫ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሳምሶን ግዛቸው እንዲሁም የአዲስ አበባ ዞን ምክትል ሰብሳቢና ህዝብ ግንኙነት አቶ ማቲያስ መኩሪያ በአራዳ ክፍለ ከተማ ቅስቀሳ ላይ በነበሩበት ወቅት በፖሊስ ተይዘው አራዳ ፖሊስ መምሪያ ታስረዋል፡፡
በሌሎች የአዲስ አበባ ክፍሎች ቅስቀሳ ላይ የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና አመራሮች በፖሊስ ወከባ እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ህዳር 7/2007 ዓ.ም ቤልየር ሜዳ ላይ የሚደረገው የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ ሰማያዊ ፓርቲ የሚያስተብብረው ሲሆን በአንድ ወር የሚደረጉትን ሌሎቹን መርሃ ግብሮች 9ኙ ፓርቲዎች በየተራ እንደሚያሰተብብሩ መስማማታቸው ይታወቃል፡፡