ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር አህመድ ረጃ እንደፃፉት ስለ ስንፈተ ወሲብ መፃፍም ሆነ መነጋገር አስቸጋሪ ጉዳይ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ይህም የሚሆነው ባህላችንና ሃይማኖታችን በሚያሳድርብን ተፅዕኖ ነው፡፡ ነገር ግን ችግሩ አሳሳቢና የትዳር ሁኔታንም የሚፈታተን በመሆኑ ለስኳር ህሙማንም የሚፈታተን በመሆኑ ለስኳር ህሙማንም ሆነ የትዳር ጓደኞቻቸው ግልፅ እንዲሆኑ ይህን ፅሑፍ አቅርበናል፡፡ በዚህ በስንፈተ ወሲብ ችግር በፍርሃት ዝሙትን መርጠው ውስጥ ውስጡን ለአካላዊና ስነ-አዕምሯዊ ችግር የሚዳረጉት ስኳር ህሙማን ስለ ችግሩ ከህክምናቸውና ከትዳር ጓደኞቻቸው በግልፅ ለመወያየት ይህ ፅሑፍ ይጠቅማቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ አንባቢያን እንዲረዱልኝ የምፈልገውን አንድ ነገር በቅድሚያ ላስቀምጥ፡፡ ስለ ስንፈተ ወሲብ በምንፅፍበት ጊዜ ከባህላችንና ከልምዳችን ውጭ አንዳንድ ቃላቶች ብንጠቀም ስለ ጉዳዩ በግልፅ ለማስረዳት ሲባል ብቻ ታስቦ መሆኑን ከይቅርታ ጋር እንድትረዱልን እንጠይቃለን፡፡
ስንፈተ ወሲብ ማለት ምን ማለት ነው?
ስንፈ ወሲብ ስንል አንድ ወንድ ወሲባዊ ግንኙነት ለማድረግ ብልቱ መነሳት ሲያቅተው ወይም ተነስቶ ግንኙነት ሳይፈፅም ሲተኛበት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ለወሲብ ግንኙነት ፍላጎት ከማጣት ጋር ወይም አስቀድሞ የዘር ፍሬ ፈሳሽን ከማውጣት ጋር ለይተን ማየት ይኖርብናል፡፡
በጣም አብዛኛዎቹ ስኳር ህሙማን የሚያጋጥማቸው ችግር ለወሲባዊ ግንኙነት ከፍተኛ የሆነ ውስጣዊ ፍላጎት እያላቸው ነገር ግን ግንኙነት ለማድረግ ሲያስቡ ብልቱ አልሰራ ሲላቸው ነው፡፡
የስንፈተ ወሲብ ስርጭት ምን ይመስላል?
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት 35 ከመቶ እስከ 50 ከመቶ የሚሆኑት ስኳር ህሙማን ስንፈተ ወሲብ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ይጠቁማሉ፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ስለ ችግሩ የሚያወሩት ግን በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ በፍርሃትና በመሸማቀቅ ውስጥ ውስጡን በመቃጠል ለብዙ ችግር ይዳረጋሉ፡፡ ብዙዎቹ ወንዶች ለትዳር ጓደኞቻቸው በግልፅ ስለማይናገሩ ትዳራቸው የሚፈርስባቸው ብዙ ናቸው፡፡ ችግሩ ስር ሳይሰድ ከባለሙያ ጋር ቢመካከሩበት ደግሞ መፍትሄ ሊገኝለት ስለሚችል፣ ስኳር ህሙማን ከዝሙት ወጥተው ሐኪሞቻቸውን መጠየቅና መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ወንዶች ጊዜያዊ በሆነ መልኩ ስንፈተ ወሲብ ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ይህም የሚሆነው ለምሳሌ ያህል ከመጠን ያለፈ አልኮል ሲጠጡ ወይም በስራ ብዛት ከልክ ያለፈ ድካም ሲያጋጥማቸው ነው፡፡ ይህ ቋሚ ስላልሆነ መደናገጥ ወይም መረበሽ አያስፈልግም፡፡ ነገር ግን በተከታታይ ስንፈተ ወሲብ ካጋጠመ ባለሙያን ማማከሩ አስፈላጊ ነው፡፡
ለመሆኑ ስንፈተ ወሲብ በምን ምክንያት ይከሰታል?
ወሲባዊ ግንኙነት ለማድረግ የወንድ ብልት መነሳትና መጠንከር ይኖርበታል፡፡ ብልቱ እንዲጠነክርና እንዲነሳ ሶስት ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው፡፡
- ወደ ብልቱ የሚሄድና የሚያንቀሳቅሱት ነርቮች ስራቸውን በአግባቡ መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
- ወደ ብልቱ የሚሄዱት የደም ቧንቧዎች ጤናማ መሆንና የደም ዑደቱ በቂ መሆን አለበት፡፡
- ከአንጎል የመነሳሳት ስሜት መኖር አለበት፡፡
ከነዚህ ሶስት ሁኔታዎች አንዱ ላይ እንኳን ችግር ቢገጥም ስንፈተ ወሲብ ይከሰታል፡፡ ለረጅም ጊዜ በቁጥጥር ስር ያልዋለ የስኳር ህመምና በስኳሩ መብዛት የተነሳ ወደ ብልት የሚሄዱት ነርቮች የደም ቧንቧዎች ስለሚጎዱ ስኳር ህሙማን ወንዶች ስንፈተ ወሲብ ያጋጥማቸዋል፡፡ ከስኳር ህመም በተጨማሪ የደም ግፊትና ደም ውስጥ የስብ መጠን መጨመር በሚታይባቸውና ሲጋራ የሚያጨሱ ህሙማን ችግሩ እጥፍ ድርብ ይሆንባቸዋል፡፡
ስንፈተ ወሲብን የሚያባብሱ ሁኔታዎች
- ከመጠን ያለፈ ክብደትና ውፋሬ
- ሲጋራ ማጨስ
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ
- ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት
- ጫት መቃም
- አደንዛዥ እፆችን መጠቀም
- ለሌላ በሽታ የሚዋጡ አንዳንድ መድኃኒቶች
- የመንፈስ ጭንቀትና ውጥረት (Anxiety, Stress)
- ድብርት (Depression)
የስንፈተ ወሲብ ፈርጀ ብዙ ችግር
ወንዶች ስኳር ህሙማን ስንፈተ ወሲብ ችግር ሲያጋጥማቸው የተለያዩ አካላዊና ስነ-አዕምሯዊ ችግሮች ያጋጥማቸዋል፡፡ ከነዚህም በጥቂቱ፡-
- የመንፈስ ጭንቀት፣ ድብርት፡፡
- ገና ለገና እምቢ ይሉኝ ይሆናል በማለት የወሲብ ፍርሃት፡፡
- የትዳር ጓደኛ ጋር በየጊዜው መጨቃጨቅና መጣላት፡፡ ብሎም የትዳር መፍረስ፡፡
- ቁጭትና ፀፀት፡- የትዳር ጓደኛን ባለማርካት የሚፈጠር ስሜት፡፡
- ለራስ ያለን ስሜት ማሳነስ፡፡ ቀደም ሲል ስንፈተ ወሲብ ካጋጠመ የሚፈጠር ስሜት ነው፡፡
- የስንፈተ ወሲብ ያለባቸው ሰዎች የልብ ችግርም ሊኖርባቸው ይችላል ተብሎ ስለሚታምን ህሙማን ልባቸውን በሚገባ መመርመር ይኖርባቸዋል፡፡
የወንድ ብልት ለወሲባዊ ግንኙነት ዝግጁ የሚሆነውና የሚጠነክረው እንዴት ነው?
የብልት መነሳት የሚጀምረው ከአንጎል ነው፡፡ አካላዊ ሆነ አዕምሯዊ መነቃቃት ሲኖር በአንጎል ውስጥ ያሉ ነርቮች በተለያዩ ኬሚካሎች አማካይነት ወደ ብልት ለሚሄዱ ነርቮች መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡
በዚህም የተነሳ ወደ ብልት የሚሔዱት የደም ቧንቧዎች መስፋት ይጀምሩና ብልቱ በደም በተሞሉ ቧንቧዎች አማካይነት ይወጠርና ይጠነክራል፡፡ ወደ ብልት የሚሄደው የደም ዝውውር ሲቀንስና የገባው ደም ተመልሶ ወደ ሌላ አካላት በሚሄድበት ጊዜ ብልቱ መጠኑ ቀንሶ ለስላሳ ይሆናል፡፡
አንድ የስኳር ህመምተኛ የስንፈተ ወሲብ ችግር ሲያጋጥመው መደረግ ያለበት ነገር ይህ ችግር ሲያጋጥም መጀመሪያ ከስኳሩ ውጭ ሌላ ህመም መኖር አለመኖሩ መረጋገጥ አለበት፡፡ ሌላው መረጋገጥ ያለበት ነገር ስንፈተ ወሲብ ሊያስከትሉ የሚችሉ መድኃኒቶች ይወስድ እንደሆነ መለየት አለበት፡፡ ቀደም ሲል የተገለፁት ስንፈተ ወሲብን የሚያባብሱ ነገሮች ይኑሩ አይኑሩ መታወቅ አለበት፡፡
ከዚህ ተጨማሪ የሆርሞኖች መዛባት መኖር በመመርመር ተለይቶ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ተጠንተው ስንፈተ ወሲብ ከስኳር ህመም ጋር በቀጥታ ተያያዥነት አለው ተብሎ ከታመነ የሚከተሉት የሕክምና ዘዴዎችን መጠቀም ያሻል፡፡
የስንፈተ ወሲብ የህክምና ዘዴዎች
- ስለ ችግሩ በግልጽ መወያየት፡፡ ከህክምና ባለሙያ ጋርና ከትዳር ጓደኛ ጋር
- ስኳሩን በቁጥጥር ስር ማዋል
- የደም ግፊትና የኮሌስትሮል መጠንን መቆጣጠር
- ሲጋራ የሚያጨሱ ከሆነ ማቆም አልኮልም፣ ጫትና አደንዛዥ ዕጾችን አለመጠቀም
- ውፋሬን ማስወገድና አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ
- ጭንቀትና ውጥረትን ለማስወገድ የምክር አገልግሎት ከባለሙያ ማግኘት
- በአፍ የሚዋጡና በህክምና ትዕዛዝ የሚሰጡ እንክብሎች፡- ከነዚህም መድኃኒቶች በሀገራችን በአሁኑ ሰዓት አንድ አይነት በስራ ላይ ውሏል፡፡ ሲልዲናፈል ይባላል፡፡
- በብልት ቀዳዳ ውስጥ የሚጨመሩ መድኃኒቶች
- በብልት ላይ የሚወጉ በመርፌ የሚሰጡ መድኃኒቶች ያሉ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን አይገኙም፡፡