Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በ‹‹ዴሞክራሲ›› ያጌጡት አምባገነኖች

$
0
0

ጌታቸው ሺፈራው

የማይገባውን ማንነት ለመላበስ የሚደረግ ጥረት ከሰዎች ተፈጥሯዊ የመታወቅ አሊያም የመከበር ተፈጥሮ የመነጨ ይመስላል፡፡ ከጸባያቸው በተቃራኒ ደግ፣ ሩህሩህ፣ ለስው አሳቢ መስለው ለመታየት የሚጥሩ አሊያም የእንደዚህ አይነት ሰዎችን ማንነት የሚገለጽበት ስም ሳይገባቸው የሚይዙ አሊያም የሚሰጣቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ከፍ ሲል ደግሞ በወታደራዊ፣ ፖለቱካ፣ ኃይማኖራዊ፣ አካዳሚያዊ ጉዳዮች ከሚገባቸው በላይ ማዕረግ የሚያገኙትም የትየለሌ ናቸው፡፡ መንግስትም የእነዚህ ግለሰቦች ስብስብ ነውና የማይገባው ማዕረግ ወይንም ማንነት ይሰጠዋል ወይንም ይላበሳል፡፡
eprdf_meeting
እነዚህ ከማንነታቸው ውጭ አጓጊዎቹን ማንነቶች በአጋጣሚ የስልጣን ባለቤት ሲሆኑ አሊያም ተጽዕኖ ሲኖራቸው ደግሞ አገራት፣ መንግስት፣ ፓርቲ፣ መሪዎች የሚኖራቸው ስብዕና የተጋነነና ከነባራዊ ሁኔታው ጋር የማይመሳሰል ይሆናል፡፡ መንግስት ወይንም አገር ከሚጠሩበት የተገናነ ማንነት መካከል ሪፖብሊክ፣ ጭራሹን ሲጋነን ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ አንዱ ነው፡፡ ከእነዚህ አገራት መካከል ደግሞ የኢህአዴጓ ‹‹ኢትዮጵያ›› አንዷ ነች፡፡ ይች የኢህአዴግ ‹‹ኢትዮጵያ›› ከሪፖብሊክም በላይ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ተብላ ትጠራለች፡፡

የዓለም ‹‹ሪፖብሊኮች››

በዓለም ከሚገኙት 206 እውቅና ያላቸው አገራትና እንዲሁም ግዛቶች መካከል 154 በሪፖብሊክ ነው የሚጠሩት፡፡ አፍሪካ ውስጥ ካሉት ጥቂት ግዛቶችና 55 አገራት መካከል አራት ያህል እውቅና ያላገኙ ግዛችና ከ44 አራት በላይ አገራት ራሳቸውን የሚጠሩበት በሪፖብሊክነት ነው፡፡ ከእነዚህ ራሳቸውን በሪፖብሊክነት የሚጠሩ መንግስታት የየራሳቸው መግለጫዎች አሏቸው፡፡ አንዳንዶቹ እስላማዊ፣ ሌሎቹ ፌደራላዊ፣ ቀሪዎቹ ህዝባዊ፣ ሌላኛዎቹ ደግሞ ሶሻሊስት፣ አረባዊ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ መሆናቸውን በመግለጽ የመንግስታቸውን ማንነት ለመግለጽ ይጥራሉ፡፡ እንደ አሜሪካ፣ ካናዳና ቦትስዋና ያሉ አገራትና ግዛቶችን ጨምሮ 15 ያህሉ ብቻ ምንም መግለጫ ሳያስፈልጋቸው መንግስታቸውን በአገራቸው ስም ይጠራሉ፡፡ እንደ እስራኤል፣ ሊቢያና ኤርትራ ያሉ አገራት ደግሞ ዴሞክራሲያዊ፣ ሪፖብሊካዊ……የተባሉ መግለጫዎችን ሳይጨምሩ ‹‹የእስራኤል መንግስት፣ የኤርትራ መንግስት …›› ብለው ራሳቸውን በእንቅጩ ይገልጻሉ፡፡

በዓለም ከሚገኙት አገራት መካከል አብዛኛዎቹ ሪፖብሊክነትን ሲጠቅሱ ‹‹ሪፖብሊክ›› የሚለው አንዳች ተወዳጅ ነገር መያዙን ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ሪፖብሊክ እንደ መንግስት ስም እንደ ፈረንሳይና ጀርመን ከመሳሰሉት ዴሞክራሲያዊ አገራት እንደ ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ጅቡቲ የመሳሰሉ አገራት መጠቀሚያ ሲሆን ደግሞ እነዚህ በምንም አይነት መንግስት ስርዓታቸው የማይመሳሰሉ አገራት ቃሉን አወላግደው እየተጠቀሙበት ስለመሆኑ ያስጠረጥራል፡፡ አፍሪካ ውስጥ ካሉት ጥቂት ግዛቶችና 55 አገራት መካከል አራት ያህል እውቅና ያላገኙ ግዛችና ከ44 በላይ አገራት ራሳቸውን የሚጠሩበት በሪፖብሊክነት ነው፡፡

ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ፣ ፌደራል ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ የሚባሉት ደግሞ ጭራሹን የመንግስታትን ማንነት ለማጋነን የሚደረጉ ስሞች ስለመሆናቸው እንደ በአገራችን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ መውሰድ ይቻላል፡፡ በዓለም ከሚገኙት 154 ሪፖብሊኮች መካከል 10ሩ ብቻ ራሳቸውን ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ይጠራሉ፡፡ ከአስሩ መካከል ደግሞ 5ቱ (አልጀሪያ፣ ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ፣ የሳኦ ቶሚና ፕሪንሲፒ፣ ምዕራብ ሰሃራ (ሳሃራዊ ሪፖብሊክ) አፍሪካ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ቀሪዎቹ 5ቱ (ሰሜን ኮሪያ፣ ላኦስ፣ ሲሪላንካ፣ ምስራቅ ቲሞርና ኔፓል) ከአፍሪካ ቀጥሎ አምባገነኖች በሚገኝበት ኤስያ ውስጥ የሚገኙ አገራት ናቸው፡፡

‹‹ሪፖብሊክ›› ለምን?

ሪፖብሊክ በእነ አርስቶትል ጀምሮ ረዘም ያለ ታሪክ ያለው የመንግስት አይነት ነው፡፡ አንድ መንግስት ሪፖብሊክ ለመባል ለፖለቲከኞች አሊያም ለተወሰኑ ቡድኖች ሳይሆን ለህዝብ መስራት አለበት፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች የህዝብ መንግስት የሚሉት ይህን አይነስ ስርዓት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ‹‹ሪፖብሊክ›› ሲባል የመንግስት የስልጣን ምንጭ ህዝብ ሲሆንና ይህ መንግስትም የሚሰራው ለህዝብ ነው ሲባል ነው፡፡

በድሮ ዘመን ልዓላዊ ስልጣን ያለው ንጉስ ወይንም ሌላ አካል ነበር፡፡ የመንግስት ስርዓትም ቢሆን ከአሁኑ ይለያል፡፡ በአሁኑ ዘመን ህዝብ የራሱን መንግስት ሊመሰርት የሚችለው ተወካዮቹን በነጻነት በመምረጥ ነው፡፡ ሆኖም በዚህ ምርጫ ላይ የራሳቸውን ተመራጭ በመምረጥ ሂደት ልኡላዊ ሰልጣን ሊኖራቸው የግድ ነው፡፡ ስለሆነም ‹‹ሪፖብሊክ›› ምርጫ በግድ፣ በንጉሳዊ ቤተሰብ አሊያም ፓርቲ ወይንም ሌላ ባስቀመጠው ሳይሆን በህዝብ፣ ለህዝብና የህዝብ ስርዓት መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡

በእርግጥ ድሮም ቢሆን እንደ ሮማ ያሉት በርካታ ህዝቦችን በግድ እየወረሩ፣ እያፈናቀሉ፣ ባሪያ እየፈገሉ፣ ቅኝ እየገዙም ስሙን ተጠቅመውበታል፡፡ በአንድ አገር ሳይቀር አንዱ ‹‹ሪፖብሊክ›› ብሎ የሰየመውን መንግስት አይነት ሌላኛው ‹‹የህዝብ መንግስት አይደለም›› ብሎ አፍርሶ የራሱን ‹‹ሪፖብሊክ›› ለመምስረት ስለመጣሩ ታሪክ ያትታል፡፡ ለዚህ በምሳሌነት የምትጠቀሰው ፈረንሳይ ናት፡፡ ከታዋቂ እ.ኤ.አ ከ1792 የፈረንሳይ አብዮት ጀምሮ እስከ 1958 ድረስ ፈረንሳይ አምስት የተለያዩ ‹‹ሪፖብሊኮች›› ስም ተጠርታባቸዋለች፡፡

የዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊኮች እንቆቅልሽ

ሪፖብሊክ የመንግስት የህዝብ መንግስት ቢሆንም በብዙሃን ወይንም በሌላ ምክንያት የሚያጣ ህዝብ የለም፡፡ ዴሞክራሲ (የብዙሃን ዴሞክራሲ) የሚባለው ግን ብዙሃን ጥቂቶች በምርጫና በመሳሰሉት ድምጽ በተሻለ የሚገዛበት ነው፡፡ በሪፖብሊካን መንግስት ውስጥ ሁሉም የአገር ንብረት የህዝብ ንብረት ነው፡፡ በዘመናዊው ትርጉም ተቋማትና መንግስት ከፓርቲ የተለዩና ለህዝብ የቆሙ ናቸው፡፡

ዴሞክራሲም ሆነ ሪፖብሊክ ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› ስርዓቶች መገለጫ ቢሆኑም በአንጻራዊነት ‹‹ሪፖብሊክ›› የህዝብ መንግስት መገለጫ ነው፡፡ ሪፖብሊካ ከህዝቦች ልዓላዊ ስልጣን (Sovereign power›› ጋር የተገናኘ በመሆኑ በምርጫና በሌሎች ዴሞክራሲያዊ እሴቶች ጋር በቀላሉ የማይነጻጸር ‹‹በህዝብ፣ ለህዝብ፣ የህዝብ›› የመንግስት አይነት ነው፡፡ በአንጻሩ ከሪፖብሊክነት ጋር ሲነጻጸር ዴሞክራሲ የብዙሃን ጨቋኝነት ይታይበታል ተብሎ ይተቻል፡፡ በሪፖብሊክነት ተጨቋኝም ጨቋኝም የለም፡፡ ለአብነት ያህል የአሜሪካ ሁለት ፓርቲዎች ከሚለያዩበት መካከል ነጻነት ላይ ያላቸው አመለካከት ነው፡፡ ዴሞክራቶቹ ህዝብን በሀብትና በመሳሰሉት ለማመጣጠን ክትትል፣ መጠነኛ የመንግስት ጣልቃ ገብነት (እርዳታ) ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ፡፡ ይህ መርሃቸው ከሪፖብሊካኞቹ በአንጻራዊነት ሲታይ አምባገነኖች ያስብላቸዋል፡፡

በተቃራኒው ሪፖብሊካኖቹ ህዝብ ብቁ የሚሆነው ነጻ ሲሆን በመሆኑ በነጻነት ሲንቀሳቀስ ነው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሊደርስ የሚችለው ብለው ያምናሉ፡፡ በመሆኑም መንግስትም፣ አገርም፣ ግለሰቦችም ሊለወጡ የሚችሉት በህዝብ ነጻነት ጣልቃ ካልተገባበት ነው ብለው ያምናሉ፡፡ የእያንዳንዱን ግለሰብ በነጻነት የተገኘ ውጤት ለአገሪቱም ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል፡፡ ግለሰቦች በነጻነት የሚመርጡት ማንኛውም ነገር በአገሪቱ ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል ባይ ናቸው፡፡

የአሜሪካ ሪፖብሊካኖቹ ለመንግስት መሰረቱ የዜጎች ነጻነት ነው ሲሉ ዴሞክራቶቹ መንግስት ለዜጎች ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለው ያምናል፡፡ ሶሻሊዝም ደግሞ ከመንግስትም ወደ ፓርቲ ይመጣል፡፡ ከአሜሪካዎቹ ፓርቲዎች መካከል የትኛው ወደ ሶሻሊዝም ይቀርባል ብንል የምናገኘው ዴሞክራቶቹን ነው፡፡ ሆኖም ከዚህ የራቁት እነ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ይሉታል፡፡ ኢትዮጵያ የምትገኝበትና የሶሻሊዝም አንድ ውላጅ የሆነው አምባገነንነትና ጠቅላይነት ፓርቲዎች ስልጣንን ዴሞክራሲም ሆነ ሪፖብሊክ ከሚከተለው የህዝብ ስልጣን ይልቅ ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥቂት ሰዎች ከዛም ወደ አንድ ግለሰብ ያወርደዋል፡፡

የአምባገነኖቹ ተቃርኖ

በዓለም ከዴሞክራሲም ጥቂት የዴሞክራሲያዊ እሴቶችን የማይተገብሩት ራሳቸውን በዴሞክራሲያውነት ከዚህም አልፈው በሪፖብሊክነት ይጠራሉ፡፡ ይህ አልበቃቸው ሲል ደግሞ ከዴሞክራሲም እንደሚበልጥ የሚነገርለትን ‹‹ሪፖብሊክ›› ስርዓት በዴሞክራሲ ለማሳመር ይጥራሉ፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ 10 የአለማችን ሪፖብሊኮች ከዚህ ፍጹም ነጻነት ጋር ከሚያያዘው የመንግስት ስርዓት ስያሜ ላይ ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› የሚል ቅጥያ የጨመሩበት ‹‹ይበልጥ ዴሞክራሲያዊ›› መሆናቸውን ለመግለጽ ነው፡፡ እንደ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና፣ ያሉ አገራት የሪፖብሊክነትን በቅጥያ ቢወስዱም ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› የሚል አልወሰዱም፡፡ እንደ ቻይና ያሉት አምባገነን መንግስታትም ቢሆን ልክ እንደ ጀርመንና ሌሎች ዴሞክራቶች ጋር በእኩል ‹‹ ሪፖብሊክ››ን ብቻ ነው የወሰዱት፡፡ ቢያንስ ዴሞክራሲና ሪፖብሊክ ምን ማለት እንደሆነ የገባቸው ይመስላል፡፡

አብዛኛዎቹ ስርዓቶች በእውነተኛ ማንነት መገለጽ ከነበረባቸው በዴሞክራሲያውም ሆነ በሪፖብሊክነት መጠራት አልነበረባቸውም፡፡ እንዲያው ይጋነን ከተባለ እንኳ የብዙሃን አምባገነንነት እንደ ህጸጽ የሚጠቀስበትን ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› ስርዓት መጠሪያ ማድረግ አንድ ነገር ነበር፡፡ ከዚህ በላይ እናጋንን ቢሉም ልክ እንደ ቻይና የህዝብ መንግስት የመሰረትን ‹‹ሪፖብሊኮች›› ነን ማለት ይችሉ ነበር፡፡ እነ ኢትዮጵያና ሰሜን ኮሪያ ግን ፍጹም ነጻነት አለው የሚባለውን ‹‹ሪፖብሊክ›› ከዚህ የመንግስት ስርዓት ባነሰው ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› ለማጋነን ሲሉ ነው የተሳሳቱት፡፡ ነጭን ነገር ይበልጡን ለማንጻት ከሌላ ቀለም ጋር እንደመለወስ ማለት ነው፡፡

ከምንም በላይ እነዚህ ሪፖብሊካንን ከዴሞክራሲ ጋር የሚያጣርሱ አገራት በዓለም ካሉት አምባገነኖች መካከል ቀዳሚ መሆናቸው ነው፡፡ ከ10 አገራት መካከል የተሻሉ የሚባሉት ብቸኛዋ ሳኦቶሚና ፕሪንሲፒ ተባለችው ሁለተኛዋ የአፍሪካ ትንሽ አገር ነች፡፡ በእርግጥ ይች ሀገር ከአፍሪካ አገራት መካከል አስከ 10 ካሉት ዴሞክራቶች የምትመደብ ነች፡፡ ከዚች አገር ቀጥሎ አልጀሪያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ተስፋ ያላት ብትሆንም አሁንም ቢሆን በምርጫ ማጭበርበር፣ በሙስና፣ ሰብአዊ መብት ጥሰትና በሌሎች ኢ-ዴሞክራሲያዊነት እንደታጀበ ነው፡፡ ግራ የተጋባው የዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክና ሪፖብሊክ ቀርቶ ዴሞክራሲያዊ የሚለው ይበዛባታል፡፡

ላኦስ ከአምባገነኗ ቻይና ጥግ የምትገኝ አገር ናት፡፤ ከኩባ፣ ቻይና እና ቬትናም ቀጥሎ አራተኛዋ የሶሻሊስት ቅሬት የምትከተል አገር ናት፡ ገዥ ፓርቲዋም የላኦስ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ ይባላል፡፡ ምንም እንኳ ከ1983 ጀምሮ ዴሞክራሲያዊ የተባለ ህገ መንግስት ቢጸድቅም የራሳቸውን ህዝቦች ከሚያሳቃዩ መንግስታት መካከል በቀዳሚነት እየተወቀሰ ነው፡፡ ደቡብ ምስራቅ ኤሲያዋ ትንሽና ድሃዋ ምስራቅ ቲሞርም ‹‹ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክን›› የምትጠቀም የኢህአዴግ ኢትዮጵያ አይነት አገር ነች፡፡
ሌላኛዋ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ነኝ የሚለው አምባገነኑ የሰሜን ኮሪያ መንግስት ነው፡፡ በሰሜን ኮሪያ ለስሙ ብዙሃ ፓርቲ ስርዓት እንዳለ ተደርጎ ነው የሚቆጠረው፡፡ ሆኖም ግን በአንድ ቤተሰብ በመጣ አንድ ፓርቲ የምትደዳደር አገር ከሆነች ከርማለች፡፡ ሪፖብሊክ ትርጉሙ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በውርስ፣ በቤተሰብ መሆን እንደሌለበት የሚያስረዳ ቢሆንም የሰሜን ኮሪያ አምባገነን መንግስት ግን ፊውዳሊዝምና ሶሻሊዝምን ያጣረሰ አዲስ ስርዓት ነው፡፡ ምን አልባትም በዓለም ላይ ለሪፖብሊክ እንደሱ የሚርቅ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ከኢህአዴግ ከሰሜን ኮሪያው የሚለየው የሰሜን ኮሪያው ቀጥታ የቤተሰብ ስርዓት በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክን›› ከሚጠቀሙት ሌሎች ግራ የተጋቡ መንግስታት መካከል ኮንጎ በእርስ በእርስ ጦርነት እየተናጠች ነው፡፡ እ.ኤ.አ በንጉሳዊ ስርዓት ስትመራ የነበረችው ኔፓል በአሁኑ ወቅትም ቢሆን በማኦኢስት ፓርቲ ነው የምትታመሰው፡፡ ስሪላንካ በሶሻሊስት ፓርቲ የምትመራ አገር ነች፡፡

የ‹‹ብሄር›› ቁርሾና ከፋፍለህ ግዛም የእነዚህ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊኮች›› ዋነኛ መገለጫዎች ናቸው፡፡ በሁሉም አገራት ለስም መድብለ ፓርቲ፣ ህገ መንገግስት፣ ፍርድ ቤት……. የሚባሉ የዴሞክራሲያዊ እሴቶች የመንግስታቱን ስም ጣራ ለማድረስ ተብሎ እንደተጨመረው ‹‹ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክነት›› በስም የይስሙላህ ብቻ ነው፡፡ ሰብአዊ መብት ረገጣም፣ የምርጫ ማጭበርበር፣ አፈና እና ሌሎች የአምባገነን እሴቶች ዋነኛዎቹ መገለጫዎቻቸው ቢሆኑም ዴሞክራሲንም ሆነ ሪፖብሊክን ግን ሳይገባቸው ለሌላቸው ማንነት ማስጌጫነት ይጠቀሙበታል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>