Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ቀንዲሎቿን የረሳች ሀገር

$
0
0

ይህ ቁም ነገር መፅሔት 13ኛ ዓመት ቁጥር 190 የሽፋን ርዕስ ነው፡፡
መነሻ
አራት ኪሎ ከዳግማዊ አፄ ምንሊክ ቤተ መንግስት ከፍ ብሎ የተገነባው የቅድስት ስላሴ ካቴድራል በስነ ህንፃ ውበቱም ሆነ በግዙፍነቱ ለአይን ማራኪ የሆነ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ከዚሁ ካቴድራል ጋር ተጎራብቶና ታኮ የሚገኘው የበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያንም ምንም እንኳ እንደ ካቴድራሉ የገዘፈ ስነ ህንፃዊ ውበት አይኑረው እንጂ የሚያመሳስላቸው ታሪክ አላቸው፡፡ ሁለቱም በጉያቸው የቀደምት ታዋቂ ኢትዮጵያውያን አፅም ይዘዋል፡፡
yofetahe nigussie
በዓለ ወልድ ቤተክርስቲያን ማንም የእምነቱ ተከታይ ከዚህ ዓለም ሲለይ በቤተክርስቲያኗ ቀኖና መሰረት የሚያርፍበት የቀብር ቦታ እስከ 2001 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ነበረው፡፡ በዚህም ሳቢያ ብዙ ታዋቂ የሆኑና ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን በዚሁ ስፍራ ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈፅሟል፡፡ በ2001 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ግን በመሀል አራት ኪሎ የሚገኘው የበዓለ ወልድ ቤተክርስቲያን እንደማንኛዎቹም ከተማ መሀል እንዳሉት አብያተ ክርስቲያናት አንድ ጥናት አሰርቶ ‹‹የቀብር ቦታውን ለልማት እፈልገዋለሁ›› አለ፡፡ ይህንኑ ተከትሎም አንድ ማስታወቂያ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ተነገረ፡፡ ቤተሰቦቻችሁን በበዓለ ወልድ ቤተክርስቲያን የቀበራችሁ ምዕመናን ‹አፅሙን በአስቸኳይ እንድታነሱ› የሚል፡፡

ከዓመታት በፊት ወዳጅ ዘመዶቻቸውን አልቅሰው የቀበሩ ቤተሰቦች ዳግመኛ እያለቀሱ የወዳጅ ዘመዶቻቸውን አፅም ቀላል የማይባል ክፍያ በመክፈል ማስወጣት ጀመሩ፡፡ የቻሉ ዳግመኛ ቦታ እየገዙ የቤተሰቦቻቸውን አፅም ሲያሳርፉ አቅም የለንም ያሉ ቤተሰቦች አፅሙ በአንድ ማጠራቀሚያ ውስጥ ከየሐውልት ማስታወሻቸው ጋር እንዲገባ አስደረጉ፡፡ ሁሉም የየራሱንና የሚያውቀውን ግለሰብ አፅም ሲያስነሳና አግባብ ነው ባለው መልኩ እንዲቀመጥ ሲያደርግ ወዳጅ ዘመዶች ያጡ /ወይም የሌላቸው ጥቂት ሐውልቶች አፅማቸውን በሆዳቸው ይዘው ቆመው ይታዩ ነበር፡፡ እነዚህ ወዳጅ ዘመድ አጥተው የተተውትን አፅሞች ቤተክርስቲያኗ በራሷ ግብረ ሀይል አስነስታ ወደ ማጠራቀሚያ የምትከታቸው ሲሆን ‹እዚህ ነው ያረፉት› ወይም እነእከሌ ናቸው› የሚል ማስታወሻ የማግኘት ዕድላቸው ይጠባል፤ ምክንያቱም ጠያቂ ወገን ለሌለው ሰው ቤተክርስቲያኗ የምታደርገው ነገር ስለሌለ፡፡

ከነዚህ ወገን ጠፍቶ አፅማቸውን የሚያወጣላቸው አጥተው ከቆሙ ሐውልቶች መካከል አንዱ የአንድ እውቅ ኢትዮጵያዊ የጥበብ ሰው መቃብር ነበር፡፡ ይህ መቃብር ለምን ሰው አጣ? ለምን አስታወሽ አላገኘም? እኝህ ሰው በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ውስጥ አሻራቸውን ያኖሩ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ቴአትር አባትና ፋና ወጊ ናቸው – ቀኝ ጌታ ዩፍታሔ ንጉሴ፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር ታሪክ ፈር ቀዳጅ የሆኑት ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ህዝብ መዝሙር ደራሲ ሲሆኑ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩና ለዛሬዋ ኢትዮጵያ መሰረት የሆኑ ተግባራትን ያከናወኑ ሰው ናቸው፡፡

የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ አፅም የሚያሰነሳው ጠፍቶ ባለበት ሰዓት ታሪክና ስምን ጠንቅቀው በሚያውቁና ኢትዮጵያዊ ወኔና ደም ባልተለያቸው ሶስት ሰዎች አስተባባሪነት አፅማቸው ተቆፍሮ ሲወጣ ይህ ነው የሚባል ተቋም ወይም የኪነ ጥብብ ሰው አብሯቸው አልነበረም፡፡ የዮፍታሔ አፅም እንዲወጣና የተራውን ኢትዮጵዊ ወግ እንዳያጡ ያደረጉት ሶስት ሰዎች አቶ ጀማነህ ወርቁ፤አቶ ጌታቸው ግዛውና ዶ/ር ፍስሃ ገ/አብ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከዮፍታሔ ጋር የስጋ ዝምድናም ሆነ ቤተሰባዊ ግንኙነት የላቸውም፡፡ ‹ማንም ሰው ከሞት አያመልጥም፤እኝህን ስንት ታሪክ የሰሩ ሰው መዘንጋት ከህሊና ወቀሳ አያድንም፡፡ የዛን ጊዜ ከሞቱ 62 ዓመታቸው ቢሆንም በአዲሱ ትውልድ ትልቅ አርአያ የሆኑ ሰው መሆናቸው ሊረሳ አይገባም›› ይላል ጎልማሳው አቶ ጀማነህ በወቅቱ ሀውልቱን ለማስነሳት ከሀገር ፍቅር እስከ ቤተ ክህነት የተመላለሰበትን ሁኔታ በማስታወስ፡፡ ግለሰቡ በወቅቱ የነበረውን አፅም የማስወጣት ሂደት ለታሪክ እንዲቆይ በፎቶግራፍ ጭምር ቀርፆ ይዟል፡፡ ይህንኑም ለዝግጅት ክፍላችን አቅርቧል፡፡

ዮፍታሔ ንጉሴ ማነው?

በሀገራችን የቴአትር ታሪክ በቀዳሚነት ስሙ የሚነሳው ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ የተወለደው በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በደብረ ኤልያስ ሙዛ በተባለ ቀበሌ ሲሆን ጊዜው ሚያዚያ 23 ቀን 1887 ዓ.ም ነበር፡፡ በዘመኑ እንደነበሩ ሊቃውንት ሁሉ ዮፍታሔም ፊደልን የቆጠረው በቤተክህነት ትምህርት ነው፡፡ በዚያ ጊዜ በጣም ጎበዝ ተማሪና አስተዋይ እንደነበር ባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ በፃፈው የዮፍታሔ ግለ ታሪክ ላይ ሰፍሯል፡፡
‹‹ከህፃንነቱ ጀምሮ ልበ ብሩህ እንደነበረ፣ እንኳን የተነገረው የሰማው ቀለም ቀርቶ፣ አልፎ ሄያጅ ቀለም እንኳ ሳይሻው ሳይፈቅደው ይጠልፈው እንደነበር በተለይ ኤልያስ በነበረበት ጊዜ የሚያውቁት ሁሉ ይናገራሉ፡፡›› በማለት ዮሐንስ ስለ ዮፍታሔ ይነግረናል፡፡

በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ቤተሰቦች የተገኘው ዮፍታሔ የልጅነት ህይወቱን ያሳለፈው በተቀማጠለ ኑሮ ነው፡፡ የቅኔ ተማሪዎች የሚያጋጥማቸው ችግርና መንገላታት በሱ ላይ አልደረሰም ማለት ይቻላል፡፡ የቤተሰቦቹ የኑሮ ደረጃ ጥሩ መሆንና በዚያው በደብረ ኤልያስ በዘመኑ የታወቁት የቅኔ ሊቅ መምህር ገ/ሥላሴ ዘኤልያስ መኖራቸው ከአካባቢው ስላላራቀው ከችግሩ ለማምለጡ ዋና ምክንያቶች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡
በፅሑፍ የተቀመጡ መረጃዎችን መሠረት አድርገን ዮፍታሔ ቅኔ መዝረፍ የጀመረበት እድሜውን ስንፈልግ 12 ወይም 13 ዓመቱ ላይ ሊሆን እንደሚችል እንገምታለን፡፡ ዮሐንስ አድማሱ እንደፃፈው ዮፍታሔ የቅኔ ትምህርቱን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ቢበዛ ሦስት ዓመት ብቻ ነው፡፡

በአጠቃላይ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣቱ በፊት ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ቅኔና ዜማ ተምሮ አጠናቆ ተምሯል፡፡ በዮፍታሔ ታሪክ ውስጥ እጅግ የሚያስደንቀው እነዚህን ሁሉ ትምህርቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ መማሩና ማጠናቀቁ ብቻ አይደለም፡፡ ዮሐንስ እንደሚለው አስደናቂው ነገር ገና 20 ዓመት እንኳን ሳይሞላው ‹ቀኝ ጌታ› የሚለው ማዕረግ ማግኘቱ ነው፡፡ ቀኝ ጌትነት የሽማግሌዎች ሹመት ነው ይባላል፡፡ በዕድሜያቸው የገፉና በዕውቀታቸው አንቱታን ያተረፉ ሰዎች የሚያገኙትን ሹመት ገና በለጋ ዕድሜው ማግኘቱ በዘመኑ የነበሩትን ሁሉ ያስደነቀ ነበር፡፡
ዮፍታሔ ደብረ ኤልያስን ለመጨረሻ ጊዜ ተሰናብቶ ወደ አዲስ አበባ የገባው በ1909 ዓ.ም እንደሆነ ይነገራል፡፡ የአባቱን መሞት ተከትሎ እናቱ ወ/ሮ ማዘንጊያ ቁርባናቸውን አፍርሰው ሌላ ባል በማግባታቸው ምክንያት ዮፍታሔ ተቀይሞ የትውልድ ቀየውን እንደሸሸ ተፅፏል፡፡

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ አሻራውን ማኖር የጀመረው ከ1920ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ እንደሆነ ይገመታል፡፡ በተለይ በዘመኑ የነበረውን ፖለቲካዊ ሽኩቻ ገፀ ባህሪያት በመቀያየር ለማሳየት ጥሯል፡፡ በተምሳሌትና ስም ለበስ ቅኔ ስልት የፃፈው ‹ምስክር›› የሚለው ቴአትሩ ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡ ቴአትሩ የተፃፈበት ጊዜ 1923 ዓ.ም መሆኑ ይነገራል፡፡ በኢትዮጵያ ቴአትር ውስጥ የነገሰው ዮፍታሔ ንጉሴ ዕርበት ፀሐይ፣ አፋጀሽኝ፣ ዳዲ ቱራ፣ እመት አታላይ ባላቸውን አቶ መታለያን እንዳስታመሙ፣ የሕዝብ ፀፀት የእመት በልዩ ጉዳት፣ መሸ በከንቱ ስራ በፈቱ እና የደንቆሮዎች ቴአትርን ፅፎ፣ መርቶና አዘጋጅቶ አቅርቧል፡፡ ባለቅኔው የሚያዘጋጃቸው ቴአትሮች ሁሉ ማለት ይቻላል በመዝሙር የታጀቡ ናቸው፡፡
ዮፍታሔ በርካታ ዜማዎችን የደረሰ ሲሆን ከነዚህ መካከል የወላድ ኢትዮጵያ ዜማ፣ ጉሳማዬ፣ መድኔ መድኔ፣ አንተ ባላጎዛ፣ የጌታው አቶ ከምሲ ዜማ፣ ሶረቲዮና የኛማ ሙሽራ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ የኛማ ሙሽራ የሚለው ዜማ ልዑል አልጋ ወራሽ እና ልዕልት ወለተ እስራኤል ሠርጋቸውን ባደረጉበት ወቅት የተዘጋጀ ሲሆን ይህን ዜማ ዛሬም ድረስ በሰርግ ዘፈኖች ውስጥ እንሰማዋለን፡፡የሀገራችን የመጀመሪያው ብሔራዊ መዝሙር ግጥምና ዜማ የተሰራውም በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ነበር፡፡
የበርካታ ስራዎች ባለቤት የሆነው ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ህይወቱ ያለፈው በድንገት ነው፡፡ ዮሐንስ አድማሱ በመፅሐፉ እንደገለፀው የዮፍታሔ አሟሟት በግልፅ አይታወቅም፡፡ ‹‹ዮፍታሔ ከሞተበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ‹በከሰል ጢስ ነው የሞተ› የሚባለው ተረት ይመስለኛል፡፡ የሞተበትን እውነተኛና ዓይነተኛ ምክንያት ለመሸሸግ ሲባል በረቂቅ ስልት የተፈጠረ ተረት ይመስላል››፡፡

የባለቅኔው ሞት መንስኤው ባይታወቅም ቀኑ ግን ሐምሌ 1 ቀን 1939 ዓ.ም ነበር፡፡ እድሜው ደግሞ 52፡፡ በኪነጥበብና በመንግስት አስተዳደር (የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ም/ፕሬዚዳንት ነበሩ) እንዲሁም በመምህርነት (የሚኒሊክ ት/ቤት አስተማሪ ነበሩ) ሀገራቸውን ያገለገሉት ዮፍታሔ ንጉሴ ሞት ከሚያንገበግባቸው ሰዎች መካከል አንዱ ዮሐንስ አድማሱ አንዱ ነው፡፡ ለዚያም ነው ተወርዋሪ ኮከብ በሚለው ግጥሙ እንዲህ ስለ ዮፍታሔ የተቀኘው፡፡
ብሩህ ነፀብራቁ
ውበትና ድምፁ አንድነት ተሰምተው አንድነት ቢበርቁ
የሚያውቅለት ጠፍቶ
ሚስጥሩን አካቶ
ተወርዋሪ ኮከብ በራሱ ነበልባል በራሱ ነዲድ ተቃጥሎ የጠፋ
ተወርዋሪ ኮከብ በምናውቀው ሰማይ ነበረ በይፋ፡፡
(እስኪ ተጠየቁ፡ 1990)
የዮፍታሔ ንጉሴ ቀን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
ሰሞኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ የቴአትር ፌስቲቫል አዘጋጅቷል፡፡ በዮፍታሔ ንጉሴ ስም የተሰየመው ቴአትር ትምህርት ቤት ከጥቅምት 28 ቀን እስከ ህዳር 6 ቀን 2007 ዓ.ም ለሚያካሂደው የቴአትር ፌስቲቫል እያንዷንዱን ቀን በተለያዩ ለቴአትር እድገት አስተዋፅኦ ባደረጉ የጥበብ ሰዎች ስም መሰየሙን ይፋ ያደረገ ሲሆን በ9 ቀናት ውስጥ 9 ቴአትሮች ለእይታ በቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህም መሰረት የፊታችን ጥቅምት 29 ቀን 2007 ዓ.ም የመጀመሪያው ቀን በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ስም የተሰየመ ሲሆን በዕለቱ ዮፍታሔ ለሀገራችን ቴአትር ያደረጉት አስተዋፅኦ ይዘከራል ተብሏል፡፡ በተከታታይ ባሉት ቀናት ደግሞ ተስፋዬ ሳህሉ፣ ፀጋዬ ገ/መድህን፣ ተ/ፐሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ፣ መንግስቱ ለማ፣ አባተ መኩሪያ፣ ረ/ ፐሮፌሰር ሃይማኖት አለሙና ፍስሃ በላይ ይማም ይታሰባሉ፡፡

ዩኒቨርሲቲው የቴአትር ት/ቤቱን በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ስም መሰየሙና በዮሐንስ አድማሱ የተጻፈውን የዮፍታሔን ግለ ታሪክ መጽሐፍ ማሳተሙ ለተማሪዎቹም ሆነ ለሌላው ማህበረሰብ የሀገራችን ቴአትር ፋና ወጊ መሆናቸውን ማስተማሪያነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የዮፍታሔ አፅም የወደቀበትና ቦታ በመለየት ክብሩን ጠብቆ እንዲቀመጥና ለታሪክ እንዲሻገር የማድረግ ሀላፊነቱንም አብሮ ሊወጣ ይገባል፡፡ በፎቶግራፍና በስም ብቻ የሚታወቁ የታሪክና የኪነ ጥበብ ጀግኖቻችንን መቃብር በአግባቡ መጠበቅና ማክበር ነገ አዲስ ታሪክ እንዲሰሩ ለምንጠብቃቸው አፍላ ወጣቶች የታሪክ ስንቅ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት በ2003 ዓ.ም በዮፍታሔ ንጉሤ ስም እንዲጠራ መወሰኑ ታላቁን ሰው ለመዘከርና ለማሰብ ትልቅ ሚና ቢኖረውም የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችም ሆኑ ሌላው ማህበረሰብ ስለጉዳዩ መረጃ የላቸውም፡፡ ትምህርት ቤቱ በዮፍታሄ ስም መሰየሙን ለማስተዋወቅ የተሰራ ስራ የለም፡፡ በዚህ ወቅት የዮፍታሔ ቲአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋዬ እሸቱ ከቁምነገር መጽሔት በጉዳዩ ዙሪያ ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሽ ሲሰጡ ትምህርት ቤቱ በዮፍታሔ ስም በአሁኑ ወቅት እንደማይጠራና ምክንያቱንም እንደማያውቁ ነግረውናል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእስክንድር ቦጎስያን የስነጥበብ ኮሌጅ ዲን የሆኑት አቶ ነብዩ ባዬ በአንጻሩ ትምህርት ቤቱ አሁንም በዮፍታሄ ስም እንደሚጠራ ገልጸው ነገር ግን ስሙ የተሰጠው ለማስታወሻነት በመሆኑ በዮፍታሔ ስም የሚጠራው በገደብ መሆኑን ነግረውናል፡፡ ‹ደብዳቤዎች ለተለያዩ አካላት ሲጻፉ ስማቸው ይጠቀሳል› ብለዋል አቶ ነብዩ፡፡ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤቱ ሰሞኑን ለሚያከብረው የቴአትር ፌስቲቫል ተብሎ ባዘጋጃቸው ፖስተሮችና ሎጎው ላይ የዮፍታሔን ስም አለመጠቀሙ ቸልተኝነት ይመስለናል፡፡ እየዘነጉ እንደገና ለማስታወስ መሞከር ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡

ምናልባትም ዩኒቨርሲቲው ለዮፍታሔ በመደበው ዕለት ዮፍታሔ እንደማንኛውም ታሪክ ሰርቶ እንዳለፈ ኢትዮጵያዊ አፅሙ በክብር እንዲያርፍ እና ሀውልቱ እንዲቆም ቤተክርስቲያኗን መጠየቅ ይገባዋል፡፡ ከአንድ ስንዝር መሬት በላይ ወስደው ላልተቀበሩ ሰዎች ሳይቀር አክሱምና ላሊበላን የሚወዳደር የሚመስል መቃብር ቤትና ሐውልት ለመገንቢያነት ቦታ ከልክላ የማታውቀው ቤተክህነት ለዮፍታሔ አፅም ማረፊያ ቦታ ታጣለች ተብሎ አይጠረጠርም፡፡ አለበለዚያ ግን ዮፍታሔ እንዳለው
‹‹ሀገሬ ተባብራ ካረገጠች እርካብ
ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ››
ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላለ
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ› ይሆናል፡፡ አሁን ያለበትን ሁኔታ ዮፍታሔ ንጉሤ ለአፍታ ቀና ብሎ ቢመለከት
‹‹አይኔን ሰው አማረው
የሰው ያለህ የሰው›› ማለቱ አይቀርም፡፡ ከዚህ ስሜት እንድንወጣ ታድያ አስፈላጊው ነገር መደረግ አለበት እንላለን፡፡
ሌሎች የጥበብ ሰዎች መቃብርስ?

ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ለጉብኝት ወደ አዲስ አበባ የመጡት የጃፖኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ጋር በተያያዘ ስለ አበበ ቢቂላ ሐውልትና የመታሰቢያ ሙዚየም ግንባታ በቁም ነገር መፅሔት በኩል ብዙ ብለናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት የሮምና የቶኪዮ ማራቶኑ ጀግና አበበ ቢቂላን ቤተሰቦች ለመጎብኘት ቀጠሮ ሲይዙ አበበ በስሙ የተመሰረተ ደረጃውን የጠበቀ ሙዚየም ባለመኖሩ ቤተሰቦቹን በአንድ ሆቴል አነስተኛ ክፍል ውስጥ በተጨናነቀ ሁኔታ እንዳነጋገሯቸው ፅፈናል፡፡ ሐውልቱም በቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን በሙታን መንደር እንደዋዛ ቆሞ የሚታይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ አደባባይ ይውጣ ብለን ፅፈናል፡፡ ምንም እንኳ ምላሹ ከመንግስትም ይሁን ከሌሎች አካላት (ከጃፓን ኤምባሲ በስተቀር) ዝምታ ቢሆንም፡፡

ከዚሁ ከአበበ ቢቂላ የመቃብር ቦታ ዙሪያውን ይገኙ የነበሩ የታዋቂ ኢትዮጵያውያንና የጥበብ ሰዎች መቃብሮች ከቦታው ለልማት መፈለግ ጋር በተያያዘ ፈራርሰውና ሐውልታቸውም ተሰባብሮ መመልከት ሀላፊነት ለሚሰማው ሰው ሁሉ ያማል፡፡
የዛሬ ሁለት ዓመት መላ የጥበብ ስራቸውንና ባለ ግርማ ሞገስ መኖሪያ ቤታቸውን ለመንግስት ያወረሱት እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈርቅ ተክሌ መቃብር ቦታም ሃውልት ሳይሰራለት ተረስቶ ይገኛል፡፡ ‹ነብይ ባገሩ አይከበርም› እንዲሉ ፈረንጆቹ በክብር ጨረቃ ላይ ስማቸውን ያኖሩላቸውን ታላቅ ሰዓሊ እኛ ግን ሐውልት እንኳ ልናቆምላቸው አልቻልንም፡፡ የሰጠናቸው ቦታ ከማውራት የዘለለ አልሆነም፡፡ ቢያንስ ቤታቸውን የወረሰው የኢትዮጵያ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ይኖርበት ነበር፡፡

በቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን መካነ መቃብር ውስጥ ድምፀ መረዋዋ ብዙነሽ በቀለንም ታገኟታላችሁ፡፡ ከአበበ ፊት ለፊት የሚገኘው የብዙዬ ሃውልት ፈራርሷል፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ በፍርስራሹ መካከል ስሟን ላልተመለከተ ሰው የሷ መሆኑን ለማወቅ ይቸገራል፡፡ በአደባባይ ላይ በታላቅ ክብር ልንመለከተው የሚገባው የብዙነሽ በቀለ ሃውልት በመካነ መቃብሩ መካከል እንኳ በሚያሳዝን ሁኔታ ተጎሳቁሏል፡፡ የወደቀውና የፈራረሰው ሲሚንቶ ላይ ግን ይህ ጽሁፍ ይነበባል፡-‹‹ብዙዬ››
በሜክሲኮው ኦሎምፒክ ላይ በማራቶንና በ10 ሺህ ሜትር የተወዳደረው አትሌት ማሞ ወልዴም አስከሬኑ ያረፈው በዮሴፍ ቤተክርስቲን ግቢ ውስጥ ሲሆን የሱም ሃውልት ‹‹የሰው ያለህ›› እያለ ነው፡፡ የጀግናው አትሌት መቃብር ላይ ያለው ሃውልት መሬት ላይ ከወደቀ አመታት አልፈዋል፡፡ ከአበበ መቃብር ጀርባ መገኘቱን የሰማ ሰው ምናልባት በግምት ማሞ ወልዴ መሆኑን ካልጠረጠረ በቀር የሜክሲኮውን ጀግና መቃብር ይህ ነው ብሎ ማግኘት ይቸግራል፡፡ ማሞ ወልዴ ከዚያ መሬት ስር ማረፉን የሚጠቁም አንዳች ልዩ ምልክት እንኳ የለም፡፡

ሰለሞን ተሰማ በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ታሪክ ፈር ቀዳጅ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ያለመታከት ለሃገሩ የሚዲያ እድገት ሰርቷል፡፡ ለዚህ ታላቅ ሰው ሃገሩ የሰጠችው ቦታ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ሰለሞን በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው የስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ እንደሆነና ከበርካታ የጥላሁን ገሠሠ ዘፈን ግጥሞች ጀርባ እንዳለ የምናውቅ ስንቶቻችን ነን?
ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ የተገኘ ሰው ደግሞ ይሄን በአይኑ አይቶ ያረጋግጣል፡፡ የታላቁ ጋዜጠኛ መቃብር ላይ የተቀመጠው ሃውልት ፈራርሷል፡፡ እነዚህ ሁሉ ታላላቅ ሰዎች ድንገት ከመቃብራቸው ተነስተው ሁኔታውን ቢመለከቱ እንዴት ይታዘቡን?

በመጨረሻም

ትውልድ ይፈራረቃል፡፡ ትላንት በዛሬ ይተካል፡፡ ይሁንና ዛሬ በትላንት ውስጥ አለ፤ ወይም ትላንትን በዛሬ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ ህይወት እንደ ዱላ ቅብብሎሽ ነው፡፡ ትላንትን ካላከበርን፣ ላለፈው ትውልድ ቦታ ካልሰጠን፣ መጪው ትውልድም እኛን እንዳልተፈጠርን ሁሉ ይዘነጋናል፡፡ ማንን አርአያ ማድረግ እንዳለበት አያውቅም፤ ተነሳሽነት በውስጡ አይኖርም፡፡ ስለሀገሩ ሳይሆን ስለራሱ ብቻ የሚጨነቅ ትውልድ እየፈጠርን እንሄዳለን፡፡ ራዕዩ ከመብላትና ከመጠጣት፣ ቤት ከመስራትና መኪና ከመግዛት ያላለፈ ይሆናል፡፡
አበበ ቢቂላን ሳናከብር ሌላ አበበ ቢቂላ ልናገኝ አንችልም፤ ጥላሁን ገሠሠን ዘንግተን ሌላ ጥላሁንን መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ ፈረንጆቹ ከዕድገታቸውና ከስልጣኔያቸው ጀርባ ያለፈው ትውልድ እንዳለ ይገነዘባሉ፡፡ ላለፈው ትውልድ ክብር መስጠታቸው ለአሁኑ ትውልድ ትልቅ መነሳሳትን እንደሚፈጥር ያውቃሉ፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>