Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Health: ‹‹በእንቅልፍ ማጣት የዕለት ተዕለት ሕይወቴ ደስታ ርቆታል›› ጥያቄና የሕክምናው ምላሾች

$
0
0

ተከታታይ የሆነ የእንቅልፍ ማጣት ችግር አለብኝ፡፡ በዚህ ምክንያት የዕለት ተዕለት ህይወቴ የተመሰቃቀለና ደስታ የራቀው ሆኖብኛል፡፡ ከዚህም በላይ ከሰዎች ጋር የሚኖረኝ ግንኙነት በድብርት የተሞላ ነው፡፡ በሥራ አካባቢም በጣም ውጤታማ መሆን አልቻልኩም፡፡ ለመሆኑ እንቅልፍ ማጣት ከምን ይመነጫል? ህክምናውስ ምን ይመስላል? በጥቅሉ የእንቅልፍ ማጣት ችግሬን እንዴት ላቃልል እችላለሁ?
አቤኔዘር የሻው ነኝ

ከአዘጋጁ፡-
ውድ ጠያቂያችን እንቅልፍ ማጣት የብዙ ሰዎች ችግር ነው፡፡ ዶ/ር ሆነሊያት ኤፍሬም ቱፈሮ በድረገፃቸው ካሰፈሩት መረጃና በችግሩ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ የህክምና ባለሙያዎች በድረገፅ ያሰፈሯቸውን መረጃዎች ተንተርሰን የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተንሃል፡፡
ዶ/ር ሆነሊያት እንደሚሉት በቂ እንቅልፍ ካላገኘን የመነጫነጭ፣ ለሥራ ተነሳሽነት ማጣት፣ ድካም የመሳሰሉት ይከሰታሉ፡፡ ከእነዚህ ቀላል ከሚባሉ የዕለት ተዕለት ባህሪ ለውጦች በተጨማሪ የእንቅልፍ እጦት ከፍተኛ የጤና ችግሮችን ያከስትላል፡፡
1. የእንቅልፍ እጦት ለሚከተሉት የጤና ችግሮች መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡ ለልብ ህመም፣ ለደም ግፊት፣ ለስትሮክ፣ ለስኳር ህመም፡፡
sleep disorder2. የመደበት ስሜትን ያስከትላል
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ለረጅም ጊዜ በእንቅልፍ እጦት የሚሰቃዩ ሰዎች የመደበት ስሜት ያጠቃቸዋል፡፡ ይጫጫናቸዋል፣ ያፋሽካሉ፣ አይናቸው ይቀላል በአጠቃላይ በድብርት የተሞሉ ናቸው፡፡
3. የሰውነት ክብደት መጨመር
የእንቅልፍ እጦት የረሃብ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ሆርሞኖችን በሰውነታችን እንዲመነጩ ስለሚያደርግና ከፍተኛ የምግብ ፍላጎት እንዲኖረን ስለሚያደርግ የሰውነት ክብደታችን እንዲጨምር ያደርጋል፡፡
4.ቆዳችን ያለ ዕድሜ እንዲሸበሸብ ምክንያት ይሆናል
የእንቅልፍ ማጣትን ተከትሎ የሚታየው የአይን ማበጥና መቅላት እንዳለ ሆኖ ከዚህ ባለፈ በዓይን አካባቢ ጥቁር የሆኑ ቀጭን መስመሮችና የቆዳ መሸብሸብ የእንቅልፍ እጦት ከሚያስከትላቸውና በቆዳ ላይ ከሚታዩ ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
5. ውጤታማነትን ይቀንሳል
በቂ እንቅልፍ የማያገኝ ሰው ማንኛውንም ስራ ለመተግበር አቅም ስለማይኖረውና የሥራ ፍላጎቱ ስለሚቀንስ በሥራ ወቅት የሚፈጥራቸው ስህተቶች ጉልህ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ውጤታማነት በእጅጉ ይቀንሳል፡፡
6. ለአደጋ ያጋልጣል
እንደ አንዳንድ የጥናት ውጤቶች መረጃ የእንቅልፍ እጦት ለመንገድ ትራፊክ አደጋዎች፣ በስራ አካባቢ የሚደርሱ የማሽን አደጋዎችና በቸልተኝነት ለሚከሰቱ የእሳት አደጋዎች ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል፡፡
እንቅልፍ የማጣት ስሜት እንዴት ይከሰታል?
በርካታ የህክምና ባለሙያዎች ባካሄዷቸው ጥናቶች እንቅልፍ የማጣት ስሜቶች በጊዜያዊና በተከታታይ የሚከሰቱ በሚል በሁለት ይከፍሏቸዋል፡፡
ጊዜያዊ የእንቅልፍ እጦት መንስኤዎች
– አነቃቂ (አደንዛዥ) እፆችን መጠቀም
– በእንቅልፍ ሰዓት እንደ ሻይ ቡና ጫት የመሳሰሉ አነቃቂ ነገሮችን መውሰድ
– ሃሳብና ጭንቀት በህይወታችን ውስጥ አንድ አልሳካ ያለ ጉዳይ ሲገጥመንና ጉዳዩ ከባድ ሐሳብ ሲያስከትል ለተደጋጋሚ ውጥረትና ጭንቀት ሊዳርግ ይችላል፡፡
– የመኝታ ስፍራ አለመመቸት
– አስፈሪ ፊልሞችን በምሽት መመልከት
– ሰላማዊና ፀጥታ የሰፈነበት ቦታ ካለመተኛትና ከመሳሰሉት ገጠመኞች ጊዜያዊ የእንቅልፍ እጦት ሊያስከትል ይችላል፡፡
በተከታታይ የሚከሰት የእንቅልፍ እጦት መንስኤዎች
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ለተከታታይ ቀናት የእንቅልፍ ማጣት ችግሮች መንስኤዎቻቸው ውስብስብ ናቸው፡፡ እነዚህም እንየግለሰቡ ባህሪ የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዋናነት ግን ብስጭት ይጠቀሳል፡፡ በህይወት ሂደት የሚገጥሙ መሰናክሎች አንዳንድ ጊዜ ረፍት ሊነሱና ጤናማ እንቅልፍ ሊያሳጡ ይችላሉ፡፡ ፍቅር ሲይዝ ይህ ሁኔታም ሊያጋጥም እንደሚችል አንዳንድ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በፍቅር የተያዘ ወይም የተያዘች ሴት ለተከታታይ ቀናት እንቅልፍ እስከማጣት የደረሰ የስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡

ውድ ጠያቂያችን
ለአጭር ጊዜ ወይም ለረዥም (ለተከታታይ ቀናት) የሚያጡት እንቅልፍ የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች ቀደም ሲል ተመልክተናል፡፡ መንስኤዎቹንም አይተናል፡፡ በማስከተል ደግ የመፍትሄ ሃሳቦችን እንጠቁምህ፡፡

መፍትሄዎች

1. መኝታ ቦታን ምቹና ፅዱ ማድረግ
የመኝታ ክፍሎቻችን ፅዱና ማራኪ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል፡፡ ፍራሾችና ትራሶችም በተቻለ አቅም ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንሶላዎቻችን መልካም መአዛ (ጠረን) እንዲኖራቸው ብንሞክርም አይከፋም፡፡
2. ተገቢውን ጊዜ መስጠት
አንድ ሰው በቀን ውስጥ ስምንት ሰዓታትን በእንቅልፍ ቢያሳልፍ ለጤናማ የእለት ተዕለት ህይወቱ ይመከራል፡፡ በመሆኑም ለእንቅልፍ ሰዓት ተገቢውን ጊዜ መስጠት ያሻል፡፡
3. ከአደንዛዥና አነቃቂ ዕፆች መላቀቅ
አንዳንድ ሰዎች በራሳቸው ችግር ለእንቅልፍ እጦት ይዳረጋሉ፡፡ ለምሳ በምሽት አነቃቂና አደንዛዥ ዕፆችን ከመጠቀም በመቆጠብ ጤናማ እንቅልፍ መተኛት እየቻሉ ልምድ (ሱስ) ሆኖባቸው ሲጠቀሙ ይስተዋላል፡፡
4. ሃሳብና ጭንቀትን ማቃለል፡-
ከአቅም በላይ ለሆኑ ጉዳዮች ብዙ አለመጨነቅ፡፡ ነገሮች እንዲሳኩ ተገቢውን ጥረት ከማድረግ ውጪ ከአቅም በላይ በሀሳብና ጭንቀት ራስን ከመጉዳት ይታቀቡ፡፡ ምክንያቱም ነገሮች ሁል ጊዜ በፈለግነው መልኩ ብቻ ሊሄዱ አይችሉምና፡፡

የእንቅልፍ መድሃኒት

ለተከታታይ ቀናት በእንቅልፍ እጦት የሚሰቃዩ ሰዎች የእንቅልፍ እንክብል (ክኒን) በመውሰድ እንቅልፍ ለመተኛት ሲሞክሩ ይስተዋላል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን መንገድ የህክምና ባለሙያዎች አያበረታቱም፡፡ ምክንያቱም በመድሃኒቱ በመታገዝ የሚተኛው እንቅልፍ በተፈጥሮ የምንተኛውን ያህል አይሆንም፡፡ ከዚህም በላይ መድሃኒቱ የልብ ድካም ላለባቸው ሰዎች አይመከርም፡፡ ለማንኛውም ሰው የሰውነትን ሆርሞኖች ወይም ሴሎች የማዳከም ባህሪም አለው፡፡ ስለሆነም በተቻለ መጠን በተፈጥሮ ሰውነታችን የሚፈልገውን እረፍትና እንቅልፍ እንዲያገኝ ማድረግ ይገባል፡፡
ለረዥም ጊዜ በእንቅልፍ እጦት የሚሰቃይ ሰው ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ሐኪም በማማከር ተገቢውን የህክምና እርዳታ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ እንጂ በራሱ የእንቅልፍ መድሃኒት ከመድሃኒት መደብሮች ገዝቶ ከመጠቀም እንዲታቀብ የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

ውድ ጠያቂያችን የዕለት ተዕለት ሕይወትህ በእንቅልፍ እጦት ከመመሰቃቀልና ደስታን ከማጣት የምትላቀቅባቸውን ጠቃሚ ሃሳቦች አካፍለናል፡፡ ከእንቅልፍ እጦት ጋር በተያያዘ በርካታ ቤተሰቦች ሲቸገሩ እናያለን፡፡ ከቤተሰብ አባላት መካከል አንድ ወይም ሁለት ሰዎች በእንቅልፍ እጦት ሲቸገሩ የሌሎችን የቤተሰብ አባላት ሰላማዊ እንቅልፍ ሲያውኩ ማየት የተለመደ ነው፡፡ በተለይም እናቶች ህፃናት ልጆቻቸው የእንቅልፍ እጦት ሲገጥማቸው አባብለው ለማስተኛት ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ በመሆኑም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለእናቶች ጠቃሚ ሃሳቦችን ለማካፈል ወደድን፡፡
በኖተርዳም ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ፕሮፌሰር የሆኑት ጀምስ ማክኪና ለህፃናት ሰላማዊና ጤናማ የእንቅልፍ አካባቢን ለመፍጠር የሚረዱ ሃሳቦችን እንደሚከተለው ያካፍላሉ፡፡
ለእናቶች
– ህጻናት በተለይም ጨቅላ ህፃናትን ከመተኛታቸው በፊት ለብ ባለ ውሃ በማጠብ የሌሊት ልብስ አልብሰውና ጡት በሚገባ አጥብተው ያስተኙ፡፡
– የህፃኑ መተኛ ስፍራ በቂ ሙቀት የሚስብ ይሁን
– የመኝታ አካባቢው ከጭስ ነፃ ይሁን
– ጨቅላው በጀርባው ተንጋሎ የሚተኛ በመሆኑ መኝታው በሚገባ የተደላደለ (የማይጎረብጥ) መሆን አለበት
– ጭንቅላታቸውን አይሸፍኑ (ከባድ ብርድ ልብስ አይጫኑ)
– ደማቅ ብርሃን ሰጪ አምፖሎች በመኝታ አካባቢው እንዲኖር አያድርጉ
– በመኝታ አካባቢው እንደ ድመትና ውሻ ያሉ የቤት እንስሳት እንዳይቀርቡ ያድርጉ፡፡

አልጋን በጋራ ስለመጠቀም

አንዳንድ ወላጆች በተለይም እንደኛ አገር ታዳጊ በሆኑ ሀገሮች የሚኖሩ ወላጆች አልጋዎቻቸውን በጋራ የሚጠቀሙበት ሁኔታ በስፋት ይታያል፡፡ በተቻለ መጠን በእናትና አባት (ወላጆች) መኝታ አቅራቢያ በቅርብ ርቀት የህፃናት መተኛ አልጋ ለብቻው ሊዘጋጅ ይመከራል፡፡ ካልተቻለና አስገዳጅ ከሆነ ህፃኑ ከወላጆች ጋር መተኛቱ አይቀርም፡፡ በዚህ ወቅት ታዲያ ወላጆች የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች እንዲያደርጉ ይመከራሉ፡፡
– ህፃኑ የመኝታ ቦታ በቂ መሆኑን ያረጋግጡ፤ በጫፍ በኩል ከሆነ እንዳይንሸራተት ተገቢውን ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡
– የሚለብሰው ብርድ ልብስ ከአዋቂ የተለየና ቀለል ያለ እንዲሆን ያድርጉ፡፡
– ጡት የሚጠባ ከሆነ ጡጦውን እየጠባ (በአፍ) እንደያዘ እንቅልፍ እንዲወስደው አያድርጉ፡፡ ከመተኛቱ በፊት የጡጦውን ጫፍ ከአፉ ይንቀሉ፡፡
– አልጋውን የሚጋሩት ከሆነ (እናትና አባት) ለህጻኑ ምቾትና ደህንነት ሁለቱም በጋራ ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል፤
– ህፃኑ የአንድ ዓመትና ከዚያ በታች ዕድሜ ላይ ከሆነ በኋላ ከሌሎች ልጆች ጋር አያስተኙት፤
– እናቶች ረዥም ፀጉር ካላቸው በህፃኑ አካል (ፊት) ላይ ሊያርፍ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የህፃኑን ሰላማዊ እንቅልፍ የሚያውክ በመሆኑ እናቶች ከልጃቸው ጋር ሲተኙ ሻሽ እንዲያስሩ ይመከራሉ፤
– ህፃኑ እንዳይታፈን ተገቢውን ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ ምክንያቱም ከአንድ ዓመት በታች ያሉ ህፃናት በመኝታ ላይ እያሉ ድንገተኛ ለሆነ ሞት የሚጋለጡበት አጋጣሚ ሊከሰት ይችላል፡፡ በእንግሊዝ አገር በተካሄደ አንድ ጥናት አልጋን በመጋራት የሚጠቀሙ ወላጆች (ከወላጆቻቸው ጋር በአንድ አልጋ ላይ የሚተኙ ህፃናት) ለድንገተኛና ላልተጠበቀ የመታፈን ህልፈተ ህይወት ይገጥማቸዋል፡፡ በዚህም እንደ ጥናቱ ከሆነ በአንድ ዓመት ውስጥ 300 ጨቅላ ህፃናት በመኝታ ላይ እያሉ በመታፈን ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

በተሌም ከአተነፋፈስና ከልብ ጋር የተያያዘ የጤና ችግር ያለባቸው ጨቅላ ህፃናት ይህ ችግራቸው ጎልቶ ከመውጣቱ በፊት በዚህ ሁኔታ ታፍነው የሚሞቱበት ዕድል ሰፊ መሆኑን ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ ወላች እንደ አልኮል ያሉ አስካሪ መጠጦችን የሚያዘወትሩ ከሆነ በስካር መንፈስ ሆነው ወደ አልጋ ለመኝታ ስለሚሄዱ በዚህ ወቅት ለጨቅላው ተገቢውን ጥንቃቄ ላያደርጉለት ይችላሉ፡፡ በተመሳሳይ አጫሽ ከሆኑም የሲጋራው ጢስ ለጨቅላው የምቾት እንቅልፍ ፀር ይሆናል፡፡
የአዋቂዎች አልጋ ለህፃናት ሰላማዊ እንቅልፍ ምቾት የመንሳታቸውን ጉዳይ በሚመለከት በእንግሊዝ የተካሄደው አንድ ሌላ ጥናት እንዳመለከተው ከ1,500 ቤተሰቦች 88 በመቶ የሚሆኑት ለልጆቻቸው ሰላማዊ እንቅልፍ እጦት ዋነኛ ምክንያት የሆነው ህፃናትን ከአዋቂዎች ጋር በማስተኛታቸው የሚያጋጥም ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በእንግሊዝ የሚኖሩ 50 በመቶ የሚሆኑት እናቶች ለህፃናት ልጆቻቸው የተለየ አልጋ ለማዘጋጀት ያልቻሉ በመሆናቸው ችግሩ ተባብሶ እንደሚታይም ይኸው ጥናት አረጋግጧል፡፡ ብዙዎቹ እናቶች ልጆቻቸው ስድስት ወር ከሞላው በኋላ ከእነርሱ ጋር (ከአዋቂዎች ጋር) አንድ ላይ እንዲተኛ ያደርጋሉ ያለው ጥናቱ ይህ ሁኔታ ታዲያ ለህፃናቱ ድንገተኛ የመኝታ ላይ ሞት (በመታፈን) መንስኤ መሆኑን አመላክቷል፡፡

ለህፃናት ጤናማ እንቅልፍ እጦት ዋነኛ መንስኤ የሆነው ምቹና ሰላማዊ እንዲሁም ለደህንነታቸው አመቺ የሆነ የመኝታ አካባቢ ያለመኖር ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ወላጆች በከፍተኛ ጥንቃቄና ትኩረት ችግሩን ማስወገድ እንዲችሉ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በሰፊው ተካሂደዋል፡፡ በእንግሊዝ ሀገር የተካሄዱት እነዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ወላጆች ለልጆቻቸው በተለይም ለጨቅላ ህፃናት ልጆቻቸው ምቹ የመንታ አካባቢ እንዲፈጥሩላቸው በማድረግ ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ጤናማ አስተዳደግ ለልጆች የተሰኘ ፕሮጀክት በመሰል ጉዳዮች ላይ በድረገፅ መረጃ ለወላጆች የምክር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

በአገራችን የሚገኙ ወላድ (እናቶች) ሌሊት ልጆቻቸው (ህፃናት) ከሰላማዊ እንቅልፋቸው ሲነቁ የእነርሱንም የሌላውንም ቤተሰብ አባላት እንቅልፍ ሲነሱ ይስተዋላል፡፡ ይህ ችግር ከየት እንደሚመነጭ ቆም ብሎ ማሰብና መፍትሄ ማበጀት ከወላጆች ይጠበቃል፡፡ የየኛ ፕሬስ የህይወት ስንክሳር አምድም ለዚህ የሚረዱ ጠቃሚ ሃሳቦችን ከጠያቂያችን አቤነዘር የሻው ጉዳይ ጋር በማያያዝ ያቀረበው ችግሩ በስፋት የሚስተዋልባቸው ቤተሰቦች (ወላጆች) ቁጥር ቀላል አለመሆኑን በመገንዘብ ጭምር ነው፡፡
ሰላም፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>