Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Sport: አንድሬስ ኢንዬሽታ –የዘመኑ የእግር ኳስ ቴክኒሽያን

$
0
0

ወደ ባርሴሎናው ካምፕኑ ያመራ ዕድለኛ የሆነ ሰው ሁሉ አንድ ነገር ያስተውላል፡፡ ‹‹Mesque un lcub›› የሚሉትን ቃላት፡፡ ‹‹ከክለብም በላይ!›› ይህ መፈክር የካታላኑን ክለብ ፍልስፍና የሁሉም አቅጣጫዎች በአንድ ላይ ሰብስቦ የሚይዝ ነው፡፡ አሁን በክለቡ ያለው የከዋክብት ስብስብ ይህን የባርሴሎናን ስሜት የሚወክል ነው፡፡ ፍልስፍናውን በኩራት ከሚወክሉት ተጨዋቾች መካከል በመጀመሪያዎቹ ረድፍ የሚቀመጠው ደግሞ አንድ ሰው ነው፡፡ አንድሬስ ኢንዬሽታ፡፡
inesta
እርሱን ስትመለከቱት ወደ ጭንቅላታችሁ የሚመጣው ምስል ላለፉት 10 ዓመታት እግርኳስን ውብ ያደረገ ተጨዋች ላይሆን ይችላል፡፡ የቁመቱ ማጠር እና በኋለኛው ክፍለ ዘመን ከአንድ አትሌት የሚጠበቁት ፍጥነት እና ኃይል የሌለው መሆኑ በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ጎልቶ ከመውጣት አላገዱትም፡፡ በዚህ ያጣውን ነገር ባለው የላቀ የቴክኒክ ተሰጥኦ ያካክሰዋል፡፡ ላለፉት ዓመታት ከጎኑ ካልጠፋው ዣቪ ሄርናንዴዝ ጋር በመሆን ተጋጣሚዎቻቸውን አስገብረዋል፡፡ ኢኒዬሽታ ባለው የፈጠራ እይታ እና የኳስ ማቀበል ችሎታ ኑ ካምፕን አድምቋል፡፡ የ30 ዓመቱ ተጨዋች በዘመናዊው እግርኳስ ባላቀ የመሀል ሜዳ አማካይነት ስኬታማ ለመሆን የሚያስፈልገው ምን እንደሆነ ላለፉት 10 ዓመታት በብቃት አሳይቷል፡፡ ጨዋታን በመቆጣጠር ታላቁ የባርሴሎና ቡድን የዓለም ኃያል እንዲሆን አስችሎታል፡፡

እግርኳስ ውብ ጨዋታ ነው፡፡ ኢኒዬሽታ ደግሞ የእግርኳስ ውበት ምልክት ነው፡፡ የቦታ አያያዙ ከማንም ያነሰ አይደለም፡፡ ጨዋታን የማንበብ ብቃቱ በተአምራዊ የእግሮቹ ጥበብ ሲታገዝ ለማየት ያጓጓል፡፡ በእርግጥ አብዛኛው የእግርኳስ ደጋፊ የኢኒዬሽታን ብቃት መታዘብ የቻለው ከ2009 ወዲህ ቢሆንም የአማካይ ክፍሉ አርቲስት ግን ከ2002 ጀምሮ የኑካምፕ ደጋፊዎችን ልብ ሀሴት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በወቅቱ የ18 ዓመት አማካይ የባርሳን የዋናውን ቡድን ማልያ ለመጀመሪያ ጊዜ የለበሱት ልዊስ ቫን ሃል ናቸው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ በላ ማሲያ ያደረገው ኢኒዬሽታን ለብሉ ግራንስ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው በቻምፒዮንስ ሊጉ ቡድን ክለብ ብሩዥን ሲገጥም ነበር፡፡ ከባርሴሎና ቢ ቡድን ጋር ሲጫወት የነበረው ወጣቱ ኢኒዬሽታን በመጀመሪያ የውድድር ዘመኑ ተፅዕኖው ከፍ ያለ ነበር፡፡ ሆኖም የካታላኑን ቡድን የሚከታተሉ ሁሉ ልጁ እምቅ ችሎታ እንዳለው ታዝበዋል፡፡

በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ኢኒዬሽታ በባርሴሎና ወሳኝ ሚና እያደረገ መጥቷል፡፡ በ2004/05 በፍራንክ ራይካርድ ስር በላሊጋው በ37 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ተጫወተ፡፡ ምንም እንኳን አብዛኛዎቹን ጨዋታዎች ከተጠባባቂ ወንበር እየተነሳ ቢሳተፍም በወቅቱ ላበረከተው አስተዋፅኦ ኩራት ተሰምቶታል፡፡ በዚያ የውድድር ዘመን ባርሴሎና ከ1999 ወዲህ የመጀመሪያ የሊግ ዋንጫን አግኝቷል፡፡ በቀጣዩ የውድድር ዘመን በ2005/06 ዣቪ ያጋጠመው ጉዳት ኢኒዬሽታ ብዙ ጨዋታዎችን እንዲያደርግ አስቻለው፡፡ በሊግ የውድድር ዘመንም ባርሴሎና የላሊጋ ሻምፒዮንነቱን በድጋሚ አስከበረ፡፡ ሆኖም ደጋፊዎቹ ዣቪ እና ኢኒዬሽታ አንድ ላይ መጫወት እንደማይችሉ ማሰብ ጀመሩ፡፡ ሆኖም በ2006 የቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ሁለቱ ተጨዋቾች ተጠባባቂ ሆኑ፡፡ ራይካርድ አርሰናል በሜዳው የመሀል ክፍል ያለውን አካላዊ ጥንካሬ ለመግታት የኤድሚልሰን፣ ዴኮ እና ማርክ ቫን በሜልን ጥምረት ተጠቀመ፡፡

ሆኖም ኢኒዬሽታ የተጎዳውን ኤድሚልሰን በእረፍት ሰዓት ቀይሮ ገባ፡፡ ሳሙኤል ኤቶ ያስቆጠራት የአቻነት ጎል መነሻም የኢኒዬሽታ ችግሮች ነበሩ፡፡ ባርሴሎና ጨዋታውን 2-1 አሸነፈ፡፡ ውጤቱ ቡድኑን የአውሮፓ እግርኳስ ቁንጮ አደረገው፡፡ ከዚያ በኋላ ክለቡ የእግርኳስ ፍልስፍናን መሰረት የጣለው በዚያ ቡድን መነሻነት ነው፡፡ ራይካርድ የራሱ ስኬት ተጎጂ ሆነ፡፡ በ2008 ባርሴሎና አንድም ዋንጫ አለማሸነፉን ተከትሎ ራይካርድ ከአሰልጣኝነቱ ተሰናበተ፡፡ ለፔፕ ጋርዲዮላም በር ከፈተለት፡፡ አዲሱ የቲካታካ ዘመንም ተጀመረ፡፡

ሞዴሉ ጋርዲዮላ ከመምጣቱም በፊት የባርሴሎና ፍልስፍና የልብ ምት ነበር፡፡ የኳስ ቁጥጥር እና አጭር ቅብብል ከታዳጊዎቹ ጀምሮ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ የአጨዋወት መንገዶች ናቸው፡፡ ፔፕ ከመጣ በኋላ የካታላኑ ክለብ በዓለም እግርኳስ ተከታታዮች ልብ ውስጥ ገባ፡፡ ባርሴሎና እና ኢኒዬሽታም የታላቅነት ማማ ላይ ወጡ፡፡ የ2008/09 ከምንጊዜውም ምርጥ ቡድኖች የመጀመሪያውን ረድፍ ላይ የሚቀመጥ ቡድን ሆነ፡፡ የጋርዲዮላ የመጀመሪያው የውድድር ዘመን አይረሴ ነበር፡፡ ገና የውድድር ዘመኑ ሳይጀመር የኮከብ ሮናልዶንም መልቀቅ ቡድኑን እንዳልነበር ያደርገዋል የሚል ከፍተኛ ግምት ነበር፡፡ በምት ግን ሊዮኔል ሜሲ የዓለም ታላቅ ተጨዋች ሆኖ ብቅ አለ፡፡ ትንሹ አርጀንቲናዊ ከባለ ተሰጥኦ ከዋክብት አንዱ የነበረ ቢሆንም የተደረገለት የቦታ ለውጥ ከፍ ያለ ነፃነት አስገኝቶለት ብቃቱ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋገረ፡፡ ባርሴሎናም በዚያ የውድድር ዘመን የላ ሊጋውን ያለ ችግር አሸነፈ፡፡ ሜሲ በሊጉ 23 ጎሎችን አስቆጠረ፡፡ በኮፓ ዴል ሬይ ስድስት ተጨማሪ ጎሎችን አስቆጠረ፡፡ የካታላኑ ክለብ የሀገር ውስጥ ሁለት ዋንጫዎችን አገኙ፡፡

ለባርሴሎና ስኬት የትንሹ ጥበበኛ አስተዋፅኦ ከፍ ያለ መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ ያለ እርሱ ባርሴሎና እዚህ ደረጃ ለመድረስ ይቸገር ነበር፡፡ ሆኖም የኢኒዬሽታ ዋጋም ያነ አይደለም፡፡ አማካዩ ጨዋታዎችን በመቆጣጠር ብሉ ግራንሰን ለክብር መርቷል፡፡ ኢኒዬሽታ በ2008/09 ለሁለት ወራት በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቆ ነበር፡፡ ሆኖም ወደ ሜዳ ከተመለሰ በኋላ በኮፓ ዴል ሬይ እና በላሊጋው ስኬት ትልቅ ድርሻ ነበረው፤፤ የእርሱ ከፍተኛው አስተዋፅኦ የተገኘው ግን በቻምፒዮንስ ሊጉ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ከመጀመሪያ የውድድር ዘመኑ ሁለት ዋንጫ ማሸነፉ ለጋርዲዮላ ስኬት ይህን የተጨዋቾች ስብስብ ወደ ሌላ ዓለም ወሰደው፡፡ ነገር ግን የቻምፒዮንስ ሊጉ ግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ በስታምፎርድ ብሪጅ ሲደረግ ካታላናዊያኑ ከውድድሩ ለመውጣት ተቃርበው ነበር፡፡ ቼልሲ እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ በድምበር ውጤት ለፍፃሜ የሚያደርገውን ደረጃ አግኝቶ ነበር፡፡
በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ግን ነገሮች ተገለባበጡ፡፡ ኢኒዬሽታ ለታላቅነት ተንደረደረ፡፡ አማካዩ የምርጥ ብቃት ባለቤት ቢሆንም በጎል አግቢነት አይታወቅም፡፡ ተጨዋቹ ይበልጥ የሚታወቀው ለጎን የተመቻቹ ኳሶችን በማቀበል ነው፡፡ በስታምፎርድ ብሪጅ ግን ይህ አልሆነም፡፡ ከፍፁም ቅጣት ምቱ በዚህ ላይ በግራ እግሩ አክርሮ የመታት ኳስ የፔተር ቼክ መረብ ላይ አረፈች፡፡ ስፔናዊው ከድጋፍ ሰጪነት ወደ ኮከብነት በአንድ ምሽት ተሸጋገረ፡፡ ጎሏ በቻምፒዮንስ ሊጉ አይረሴ ከሆኑት ጎሎች መካከል አንዷ ሆነች፡፡ ባርሳም ለቻምፒዮንስ ሊጉ ፍፃሜ ደረሰ፡፡ አንድሬስም በካታላዊያን ልብ ውስጥ ላይፋቅ ተቀመጠ፡፡
ከሜሲ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሉ ጫፍ ላይ ተቀበለ፡፡ ማድረግ ያሰበው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ወደ ግብ መምታት፡፡ እንደ እርሱ አይነት ሙከራ አድርገው የሚሳካላቸው ጥቂት ተጨዋቾች ብቻ ናቸው፡፡ ሙከራው ተሳካለት፡፡ ስታምፎርድ ብሪጅ በፀጥታ ተሞላ፡፡ ስታምፎርድ ብሪጅ በፀጥታ ተሞላ፡፡ የስታዲየሙ አንድ ክፍል ግን ከፍተኛ ጩኸት ይሰማበታል፡፡ የባርሳ ደጋፊዎች የሚይዙትን የሚጨብጡትን አጡ፡፡ ካታላናዊያንም ወደ ሮሙ ፍፃሜ አመሩ፡፡ በፍፃሜው ግጥሚያ ኢኒዬሽታ ወደ ተለመደ ሚናው ተመለሰ፡፡ ማንቸስተር ዩናይትድን 2-0 ባሸፉበት ጨዋታ ሳሙኤል ኤቶ ላስቆጠራት የመጀመሪያ ጎል ምርጥ ኳስ አቀብሏል፡፡ ምርጥ ብቃት ካሳየበት የውድድር ዘመን በኋላ በመላው ዓለም እውቅናን ማግኘት ጀመረ፡፡ ደጋፊዎች እና ሌሎች ተጨዋቾች አንድሬስ የምርጥነት ምልክት መሆኑን በተደጋጋሚ ተናገሩ፡፡

የስፔኑ ክለብ የቻምፒዮንስ ሊግን ዋንጫ በማንሳት በአንድ የውድድር ዘመን ሶስት ትልልቅ ክብሮችን ሲያሸንፍ ኢኒዬሽታ ወሳኝ ተጨዋች ነበር፡፡ በዚያ የውድድር ዘመን የላ ሊጋው ምር የሀገር ውስጥ ተጨዋች ተብሎ ተመረጠ፡፡ የላ ሊጋው ምርጥ ሌይሜከርነትንም ማዕረግ ተጎናፀፈ፡፡ ባርሴሎና በጋርዲዮላ ስር ኃያልነቱን ቀጠለ፡፡ ሀለት የሊግ ዋንጫዎች፣ የኮፓ ዴል ሬይ ክብር፣ ሌላ የቻምፒዮንስ ሊግ ማዕረግ እና ሁለት የዓለም ሻምፒዮንነትን ተቀዳጀ፡፡ ኢኒዬሽታም የዚህ የእግርኳስ ኃያልነት ዘመን አቀጣጣዮች አንዱ ሆኖ ቀጠለ፡፡ ከዓለም ምርጥ አማካዮች አንዱ መሆኑንም አስመሰከረ፡፡ ምንም እንኳን ከግብ ፊት ያሉ ሪከርዶችን ሁሉ የሰባበረው ሜሲ በግሉ በርካታ ሽማቶች ቢሰበስብም ለባርሴሎና ስኬት ኢኒዬሽታ የነበረውን አስተዋፅኦ ማንም አይጠራጠርም፡፡ ያለ ምርጡ አማካይ አጥቂው ሜሲ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በመጠኑም ቢሆን ሊቸግር ይችል ነበር፡፡ አርጀንቲናዊው ኮከብም ቢሆን የስፔኑን ውለታ አይረሳም፡፡ እንዲያውም ሜሲ ያለ ኢኒዬሽታ እና ጓደኞቹ ድጋፍ ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ይቸገር እንደነበር አምኗል፡፡ ምንም እንኳን የኢኒዬሽታ የባርሴሎና ኮከብ ተጨዋችነት ለክርክር የሚቀርብ ቢሆንም የክለቡን በዋንጫ የተሞላ ዓመታት መሪ ከሆኑት ተጨዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡

በሀገር ደረጃም ቢሆን ስፔን ከ2008 እስከ 2012 ድረስ ያስመዘገባቸው ስኬት በኢንተርናሽል ደረጃ የሚስተካከለው የለም፡፡ ከአልባሴቴ የተገኘው ኢኒዬሽታ ደግሞ ለቡድኑ ስኬት ቁልፍ ከነበሩ ተጨዋቾች አንዱ ነው፡፡ የኢኒዬሽታ የብሔራዊ ቡድን ስኬት የተጀመረው ግን ከዩሮ 2008 ድል በፊት ነው፡፡ የላ ሮያ ወጣት ቡድኖችን በ2001 እና 2002 ለድል መርቷል፡፡ ወደዋናው ቡድን እስኪጠራ ድረስም ከ21 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች በአምበልነት መርቷል፡፡ በዋናው ቡድን ምርጥነቱን ያሳየው ግን በዩሮ 2008 ነው፡፡ በኦስትሪያ እና ስዊዘርላንድ በተዘጋጀው የአውሮፓ ዋንጫ በተከታታይ ጨዋታዎች ድንቅ ብቃቱን ማሳየት ችሏል፡፡ በመድረኩ ያሳየው ብቃት በውድድሩ ምርጥ ቡድን ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ስፔን ከ1964 ወዲህ ትልቅ ዋንጫን እንድታገኝ ቡድኑን በሚገባ ረድቷል፡፡ 2008 ደግሞ የስፔን ዓለም አቀፍ የበላይነት መጀመሪያ ነው፡፡

2010 ሌላው የኢኒዬሽታ እና ስፔን የስኬት ዓመት ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ የዓለም ዋንጫ ቡድኑ ለሻምፒዮንነት ተገምቶ ነበር፡፡ ሆኖም ለ6 ቁጥር ለባሹ ዓመቱ በሜዳ ላይም ሆነ ውጪ የተቸገረበት ዓመት ነበር፡፡ በውድድር ዘመኑ ያጋጠመው ጉዳት ግን በባርሴሎና የተጫወተባቸውን ጨዋታዎች ቁጥር ከመቀነሱም በላይ በዓለም እግርኳስ ትልቁ ውድድር ላይም ላይሳተፍበት የሚችል ዕድል ሰፋ፡፡ ጉቱ ከቪሴንቴ ዴል ቦስኬ ባሉ 23 ተጨዋቾች ስኳድ ውጪ ሊያደርገው ተቃርቦ ነበር፡፡ ከጉዳቱ በተጨማሪ ከሜዳ ውጪ ልብን የሚሰብር ነገር ገጥሞታል፡፡ የአማካይ ክፍሉ ድንቅ ተጨዋች በ2009/10 የውድድር ዘመን ሊጀመር ሲል የልጅነት ጓደኛውን ዳኒኤል ሀርኬን በሞት ተነጠቀ፡፡ በኦገስት 2009 የኤስፓኞል አምበል የነበረው ዳኒኤል ባጋጠመው የልብ ህመም ህይወቱ አለፈ፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ አሳዛኝ የሚያደርገው ደግሞ ተጨዋቹ ህይወቱ ያለፈው ኤስፓኞል በጣልያን የቅድመ ውድድር ዝግጅት በሚያደርግበት ወቅት ነበር፡፡ ዳኒኤል በወቅቱ 26 ዓመቱ ነበር፡፡

ኢኒዬሽታን ሀዘን ጎዳው፡፡ የባርሴሎናውን ኮከብ በቅርብ የሚያውቁት ሁሉ የጓደኛው ሞት ምን ያህል እንደጎዳው ታዝበዋል፡፡ ሆኖም የውድድር ዘመኑ መጨረሻ ላይ ዕድል ከተጫዋቹ ጋር ነበረች፡፡ በፍፃሜው ግጥሚያ ሆላንድ ላይ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ኢኒዬሽታ ማሊያውን አወለቀ፡፡ በውስጥ በለበሰው ቲሸርት የሀርኬ ምስል ታትሞ ነበር፡፡ መላው ዓለም ጨዋታውን የተከታተለ ሁሉ ይህን ምስል አይረሱትም፡፡ የዓለም መገናኛ ብዙሃንም ምስሉን ተቀባበሉት፡፡ አንድሬስም የልጅነት ጓደኛውን በሚገባ አስታወሰ፡፡ የሟቹ ጓደኛው ፎቶ ምን ጊዜም ከስፔን ታላቅ ስኬት ጋር መገናኛት ችሏል፡፡

ስፔን በዓለም አቀፍ እግርኳስ የላይኛው ጫፍ ላይ እንደምትገኝ የ2012ቱን የአውሮፓ ዋንጫ በማሳየት አነሳች፡፡ በድጋሚ ኢኒዬሽታ ምርጥ ብቃቱን በማሳየት የውድድሩ ምርጥ ቡድን ውስጥ ከመካተት አልፎ የቶርናመንቱ ምርጥ ተጨዋችነትን ማዕረግ አገኘ፡፡ ኳስን ተቆጣጥሮ ማቆየት እና ለጎን የተመቻቹ ኳሶችን የማቀበል ችሎታው ከማንም ልቆ መታየት ቻለ፡፡ ምንም እንኳን በብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ስፔን ሳይጠበቅ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ተሸንፋ ከምድቧ ሳታልፍ ብትቀርም ይህ ልዩ ቡድን የራሱን ገድል በታሪክ ድርሳናት ላይ ማስፈር የቻለ ነው፡፡ ከአልነሴቴ የተገኘው ልጅ ደግሞ የስኬቱ ምልክት ነው፡፡ በመጪዎቹ ዓመታት ከ2008 እስከ 2012 ያሉትን ዓመታት የሰፔን እግርኳስ ወርቃማ ዘመናት በማለት ደጋፊዎች ማክበራቸው አይቀርም፡፡ ይህ ወርቃማ ዘመን ሲነሳ ደግሞ የአኒዬሽታ ስም በድምቀት መዘከሩ አይቀሬ ነው፡፡ ባርሳን በ12 ዓመቱ የተቀላቀለው ልጅም ወደ ታላቅነት ተለውጧል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>