በአሶሳ እና በሽሬ እንደስላሴ ከተማ የሚኖሩ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃባችሁን አውልቁ በሚል ከትምህርት ገበታቸው እየተፈናቀሉ እንደሚገኙ ተገለፀ::
አቡ ዳውድ ኡስማን
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በአሶሳ ከተማ በሚገኙ የ1ኛ ደረጃ ት/ቤት የሚማሩ ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው መማር እንዳይችሉ እየተደረጉ መሆናቸውን ምንጮች አስታወቁ፡፡
በአሶሳ ከተማ በሚገኙ ት/ቤቶች ውስጥ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት እንደማይችሉ የት/ቤቱ አስተዳደሮች እየከለከሏቸው መሆኑ ታውቋል፡፡በቤኒሻንጉል ጉምዝ በአሶሳ ከተማ በሚገኝ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት 35 የሚሆኑ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃባችሁን ካላወለቃችሁ መማር አትችሉም በመባላቸው ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀላቸውን ምንጮች አስታውቀዋል፡:
የትምህርት ቤቱን ርዕሰ መምህርን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር በአሶሳ ከተማ በስፋት በህዝብ ዘንድ የሚታወቀው ሰለፊያ ተብሎ የሚጠራው መስጂድ ኮሚቴዎች ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ርዕሰ መምህሩ “እናንተ አሸባሪዎች እስካሁን አላቹ እንዴ” በማለት የተሳለቀባቸው ሲሆን ሴት ተማሪዎቹ ሂጃባቸውን እስካላወለቁ ድረስ በትምህርት ገበታቸው ላይ እንደማይቀጥሉ ምላሽ እንደሰጣቸው ታውቋል፡፡
በተመሳሳይም በትግራይ ክልል በሽሬ እንደስላላሴ ከተማ በሚገኙ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው መማር እየተከለከሉ መሆናቸውን ምንጮች ዘግበዋል፡፡
በበሽሬ እንደስላሴ ከተማ የሚኖሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃባችሁን አውልቃችሁ ተማሩ በመባላቸው ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው በቤት ውስጥ ተቀምጠው እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
የትምህርት ቤት አስተዳደሮች የተማሪዎችን ወላጆች በመሰብሰብ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገሩ ሲሆን ወላጆችን እና ተማሪዎችን ሲያስፈራሩ እንደነበር ተዘግቧል፡፡
በመላው ሃገሪቱ የሙስሊሞች ዋነኛ የእምነታቸው መገለጫ የሆነውን ሂጃብ እንዲያወልቁ ለማድረግ በመንግስት በኩል ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ የፌደራል ጉዳዬች ሚኒስተር ዶ/ር ሽፈራው በኢስላም ላይ ባላቸው የግል ጥላቻ በመነሳት ከመሰሎቻቸው ጋር በመቀናጀት ሙስሊም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ለማፈናቀል በክፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን በመላው ሃገሪቱም በሴኩላሪዝም ሽፋን ሙስሊሞች ትምህርታቸውን አልያም ሃይማኖታቸውን እንዲመርጡ በማስገደድ ሙስሊሙን ከትምህርት ገበታ ለማራቅ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ሂጃብ የሙስሊም ሴት ህልውናዋ እንጂ ለድርድር የሚቀርብ የፖለቲካ አጀንዳ አይደለም።