Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Sport: የቱሬ እንቆቅልሽ: እውን የሲቲ አማካይ ክፍል ችግር አይቮሪኮስታዊው ነው?

$
0
0

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የያያ ቱሬ ጎሎች ለማንቸስተር ሲቲ ድል ወሳኝ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ሲቲ በእንግሊዝ እግርኳስ ከአናት እንዲቀመጡ የእርሱ አስተዋፅኦ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ችግሩ በማጥቃት እንቅስቃሴው ላይ የሚያሳርፈው በጎ ተፅዕኖ እየጎላ በሄደ ቁጥር የመከላከል ድክመቱ መጋለጡ ነው፡፡ በመሆኑም ያያ ቱሬ በሲቲ በሚኖረው ቆይታ ላይ ጥያቄዎች መነሳት ጀምረዋል፡፡
yaya toure
በእርግጥ በ28 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ ባርሴሎናን ለቅቆ ማንቸስተር ሲቲን ሲቀላቀል ቱሬ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ይበቃል ብሎ የጠረጠረ አልነበረም፡፡ ሮቢንሆ በኢቲሃድ ያልተሳካ ጊዜን ካሳለፈ በኋላ ሲቲ ብቃታቸውን አሟጠው የጨረሱ ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋይ ተጨዋቾች ማረፊያ እንዳይሆን ተሰግቶ ነበር፡፡ ቱሬ ግን ለእንግሊዝ እግርኳስ የተሰራ ሰው ነው፡፡
ምንም እንኳን በወቅቱ በጋርዲዮላ ባርሴሎና ውስጥ በቋሚነት የመጫወት ዕድሉ ያልነበረው ቢሆንም ለፕሪሚየር ሊጉ እግርኳስ ፍፁም ተስማሚ የሆነ ተጨዋች ነበር፡፡ ቅልጥፍናው እና ጥንካሬው በሊጉ ለመጫወት ብቁ አድርገውታል፡፡ የእንግሊዝ እግርኳስ የተጋጋለ ባህሪይ ያንን መቋቋም የሚችሉ ተጨዋቾችን መያዝ ግድ ይላል፡፡ በተለይ በአማካሪ ክፍል ያንን ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡

ግዝፈት እና ቅልጥፍና በአማካይ ክፍል ያለው አስፈላጊነት

ቱሬ የአርሴናል ጥንካሬ መሰረት ከነበሩ እንደ ፓትሪክ ቪዬራ፣ ጂልቤርቶ ሲልቫ እና ኢማኑኤል ፐቲ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ሞውሪንሆ ከ2004/2007 በቼልሲ በነበሩበት ወቅት በቡድናቸው ከያዟቸው ተጨዋቾች ጋር ይቀራረባል፡፡ ፕሪሚየር ሊጉን ካደመቁ ምሉዕ አማካዮች ሁሉ ቀዳሚው እንደሆነ ከሚነገርለት ማይክል ኤሲዬን (ቪዬራ እና ሮይ ኪን ለክብሩ ሊፎካከሩ ይችላሉ) ጋር ማወዳደርም ይቻላል፡፡

እግርኳስ ከአስር ዓመት በፊት ከነበረው ብዙም አልተለወጠም፡፡ በእርግጥ ቬንገር ግዙፍ እና ጉልበተኛ አማካዮችን ትተው ‹‹ደቃቃ›› አማካዮችን መጠቀም መርጠዋል፡፡ (ይህም በሊጉ ስኬታቸው ላይ ጉዳት አድርሷል)፡፡ ባርሴሎና እና ስፔን ጨዋታዎችን ግዙፍ ባልሆነ ቴክኒሺያኖች በበላይነት መቆጣጠር ሲጀምሩ የፈረንሳዊው አሰልጣኝ ውሳኔ ትክክል መሰለ፡፡ እውነታው ግን ግልፅ ነበር፡፡ ስኬታቸው የተመሰረተው በሆልዲንግ አማካዩ ጥንካሬ ላይ ነው፡፡ ያንን ሚና የሚወጣው ኤድሚልሰን፣ ያያቱሬ፣ ማርኮስ ሴና አልያም የዓለማችን ምር ሆልዲንግ አማካይ ሰርጂዮ ዙስኬትስ ሊሆን ይችላል፡፡ ስኬታማ ለመሆን ጨዋታዎችን በበላይነት የሚቆጣጠር የተከላካይ አማካይ ማስፈለጉ ግን አያጠራጥርም፡፡ የተከላካይ መስመሩን ያግዛል፡፡ በማጥቃ እንቅስቃሴ ላይ የሚሳተፉ ተጨዋቾች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ መደላደሉን ያመቻቻል፡፡

ይህ እውነታ በአብዛኛው ሰው ዘንድ ከታወቀ ከ10 ዓመት በላይ ይሆነዋል፡፡ ዲዲዬ ዴቮ እና ክሎድ ማኬሌሌ የዚህ ሚና መገለጫዎች ነበሩ፡፡ እንደ እነ ኤሲዬን፣ ቪዬራ፣ እና ዳ ቪድሰን የመሳሰሉ ‹‹ምሉዕ›› ተጨዋቾች ሚናውን ይበልጥ አሻሻሉት፡፡ በቅርቡ ሽዌንስታይገር እና አርቱሮ ቪዳል በሚናው ደምቀው ታይተዋል፡፡ ሌሎች እንደ አንድሬያ ፒርሎ፣ ቬሮን፣ ማይክል ካሪክ እና ዣቢ አሎንሶን የመሳሰሉ ተጨዋቾች በበኩላቸው ባፈገፈገ ሚና ልቀው ታይተዋል፡፡ ይህ የሆነው ከጎናቸው የሚሰለፈው የተጋጣሚ ቡድንን እንቅስቃሴ በመግታት ላይ የሚያተኩረው የተከላካይ አማካይ (destroyer) ለመፍጠር የሚያስፈልጋቸውን ጊዜ እና ቦታ እንዳያገኙ ለማስቻል ያለመታከት ስለሚለፉ ነው፡፡

በትልቅ ደረጃ ላይ በሚከናወኑ ጨዋታዎች በአማካይ ክፍል ግዙፍ እና የማይዳከሙ ተጨዋቾችን መያዝ የግድ እየሆነ መጥቷል፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ወሳኝ የሆነውን ያህል በአውሮፓም አስፈላጊ ነው፡፡ ያያ ቱሬ የበላይነቱ እና ታታሪነቱ ጎልቶ በሚወጣበት ሊግ ስኬታማ መሆን ችሏል፡፡ አይቮሪኮስታዊው የሲቲ ‹‹ቁልፍ ሰው›› በመሆኑ ከተጣለበት ኃላፊነት እጅጉን ተጠቅሟል፡፡ ቡድኑን እንዲቆጣጠር ተፈቅዶለታል፡፡

ሁሉም የቡድኑ እንቅስቃሴ የሚያልፈው በእርሱ በኩል ነበር፡፡ በአጭሩ መሪ ነበር፡፡ በባርሳ የቡድኑ አንድ አካል ብቻ ነበር፡፡ በሲቲ ግን እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የተሻለ ተጨዋች ሆነ፡፡ ተፅዕኖውም እየጎላ ሄደ፡፡ በባርሳ ሳለ ከሶስቱ አማካዮች አንዱ ነበር፡፡ በሲቲ ግን ወደፊት እየሄደ በተጋጣሚ ቡድን ላይ አደጋ እንዲጥል ፈቃድ ተሰጠው፡፡ ሚናውን በአግባቡ መወጣት እንደሚችልም አስመሰከረ፡፡ ጨዋታዎች ከባድ ሲሆኑ አልያም የማሸነፊያውን ጎል ማስቆጠር አስቸጋሪ ሲሆን እርሱን እንደ አጥቂ መጠቀምም እየተለመደ መጣ፡፡ የማንቺኒ የመጫወቻ ካርድ ቱሬን ወደፊት ተጠግቶ እንዲጫወት ማድረግ ነበር፡፡ ውጤቱም ያማረ ነበር፡፡ የውሳኔውን ፍሬያማነት የተመለከቱት ማኑኤል ፔሌግሪኒም ወደፊት እየሄደ የማጥቃቱን ሂደት እንዲያግዝ የበለጠ ነፃነት ሰጡተ፡፡ ቱሬ ያለ ስጋት ወደፊት እንዲሄድ እና የተከላካይ መስመሩን ከአደጋ ለመከላከል በማሰብ ቺሊያዊው አሰልጣኝ ፈርናንዲንሆን ወደ ቡድኑ ቀላቀሉ፡፡ ፔሌግሪኒ በሲቲ በቆዩበት የመጀመሪያው የውድድር ዘመን ቱሬ 20 ጎሎችን በስሙ አስመዘገበ፡፡ ለሲቲ የፕሪሚየር ሊግ ስኬት ቁልፉ ሚና ከተጫወቱት ተጨዋቾችም ግንባር ቀደም ሆነ፡፡
ሆኖም በአሁኑ ወቅት የቱሬ የሲቲ ቆይታ ወደ ማብቂያው ተቃርቦ ይሆን? በቡድኑ ውስጥ እንቅፋት እየሆነ መጥቷል ለማለት የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት ይኖር ይሆን? ቱሬን በአማካይ ክፍሉ የያዘው ሲቲ በአውሮፓ ውጤታማ መሆን ይችላል?

የአማካይ ክፍል እንቅፋት?

ቱሬ በአማካይ ክፍል የሚፈጠረው ችግር በጉልህ መታየት የጀመረው ባለፈው የውድድር ዘመን ነው፡፡ ከዚያ በፊት ሲ በአውሮፓ መድረክ በአማካይ ክፍል የበላይነት ሲወሰድበት እንደ ምክንያት የሚጠቀሱት የቡድኑ ትስስር ማጣት ሮቤርቶ ማንቺኒ የሚመርጡት ታክቲክ እና የመሳሰሉት ነገሮች ነበሩ፡፡ የተጠቀሱት ምክንያቶች እውነት እና ፍትሃዊ ናቸው፡፡ አንድ ቡድን በአውሮር መድረክ ስኬታማ ለመሆን 100 ፐርሰንት ቁርጠኝነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ህብረቱ የማያወላዳ መሆን አለበት፡፡ በተለይ ኳስ በተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾች እግር ስር ስትሆን የተጨዋቾች ትጎት ወሳኝ ነው፡፡ በጥረ ሁኔታ የሚከላከሉ ቡድኖች ቻምፒዮንስ ሊግን የሚያሸንፉት በአጋጣሚ አይደለም፡፡ ዋንጫዎችን የሚያስገኘው መከላከል ነው፡፡ ሲቲን በአውሮፓ መድረክ ስናየው የምንመለከተው ቱሬ በመከላከሉ ያለበትን ድክመት ነው፡፡

ባለፈው የውድድር ዘመን በቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ሲቲ በሜዳው በባየርን ሙኒክ 3-2 ሲሸነፍ የሲቲ የአማካይ ክፍል ግራ ተጋብቶ አምሽቷል፡፡ የጀርመኑ ቡድን ተጨዋቾች የሚያደርጓቸውን ፈጣን የኳስ ቅብብሎች መቆጣጠር ተስኖት ታይቷል፡፡ የሲቲ አማካይ ክፍል ደካማ እና ተጋላጭ ነበር፡፡ ቱሬ ተጫዋቾችን ተጠግቶ መጫወት አልቻለም፡፡ ቀርፋፋ መስሎም ታይቷል፡፡ በድካም የዛለ ሰው ይመስል ነበር፡፡ ‹‹በዓለም እግርኳስ እጅግ የተሟላ ተጨዋች›› ተደርጎ የሚቆጠረውን አማካይ አይመስልም ነበር፡፡ ምናልባት ጨዋታው የተደረገው ከአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ክለብ ጋር መሆኑ ችግሩን አጉልቶት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ችግሩ በሌሎች ጨዋታዎች ላይም ተስተውሏል፡፡

ይህ ችግር በሊጉም መታየት ጀምሯል፡፡ ሲቲ ከሜዳው ውጪ ከስዋንሲ ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ ቱሬ ወደ ኋላ ተመልሶ የመከላከል ፍላጎት አጥቶ ታይቷል፡፡ ሲቲ ከሜዳው ውጪ ከቶተንሃም ጋር ያደረገውን ጨዋታ የተመለከተው ጋሪ ኔቭል ለፈርናንዲንሆ የሚሆን የአድናቆት ቃል ለማግኘት ብዙ ጥሯል፡፡ ብቻውን የአማካይ ክፍሉን የተከላከለበት መንገድ ለማመን የሚያስቸግር ነበር፡፡ ቱሬ ሲቲን በመከላከሉ ረገድ ሊያግዝ አለመቻሉ ትችቶች ጎልተው እንዲሰሙ አድርጓል፡፡
20 ጎሎች የተጫዋችን ድክመት ሊሸፍኑ ይችላሉ፡፡ ወደፊት እየሄደ እንዲያጠቃ የበለጠ ፈቃድ እንደተሰጠው ግልፅ ነው፡፡ ሆኖም ሲቲ በፈጣሪ ተጫዋቾች እና በታላላቅ አጥቂዎች የታደለ ነው፡፡ በአውሮፓ መድረክ ውጤታማ ለመሆን ቁልፉ ጨዋታዎችን በተሳካ መንገድ መቆጣጠር መቻል ነው፡፡ ሲቲ በአውሮፓ መድረክ ባደረጋቸው የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ተራ ቡድን መስሎ ታይቷል፡፡ ለመልሶ ማጥቃት በቀላሉ ይጋለጥ ነበረ፡፡ ተጋጣሚዎች በርካታ አጋጣሚዎችን እንዲፈጥሩም ይፈቅድ ነበር፡፡ በእርግጥ ያስተናገደው ሁለት ጎሎችን ብቻ ነው፡፡ ያም ቢሆን በሚያሳቅቅ መል ክፍት ነበር፡፡ ቡድ ፈርናንዶን በማጣቱ እጅጉን ተጎድቷል፡፡ በዚያ ላይ ቱሬ በመሀል ሜዳ ያለበትን ችግር አጋልጧል፡፡ በዚያ ላይ ቴሬ በመሀል ሜዳ ያለበትን ችግር አጋልጧል፡፡ ፈርናንዶ የተገዛው ፈርናንዲንሆን እንዲያግዝ ነው፡፡ እርሱ ባልነበረባቸው ጨዋታዎች አማካይ ክፍሉ ደክሞ ታይቷል፡፡ ከአስቶን ቪላ ጋር በተደረገው ጨዋታ ላይ የእርሱ ወደ ሜዳ መግባት ጨዋታውን ለውጦታል፡፡ አማካይ ክፍሉ እንዲረጋጋ አድርጓል፡፡ ሲቲም መልሶ ጨዋታውን መቆጣጠር ችሏል፡፡ ፈርናንዲንሆን ከወጣ በኋላ የሲቲ የአማካይ ክፍል በቱሬ እና ፍራንክ ላምፓርድ ተዋቀረ፡፡ በዚያን ወቅት ቪላ ጥቃት በሰነዘረባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ አስፈሪ ነበር፡፡

የአማካይ ክፍሉ ከስንት ተጨዋቾች ይዋቀር

ፈርናንዲንሆ ፈርናንዶ በአንድነት ሲሰለፉ ሲቲ ጠንካራ እና የበለጠ ዲሲፕሊን ያለው ቡድን ይሆናል፡፡ ያም ቢሆን በአውሮፓ ውጤታማ ለመሆን የአማካይ ክፍልን በሶስት ተጨዋቾች መገንባት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ምክንያት ፔሌግሪኒ ሊወቀሱ ይችላሉ፡፡ የደቡብ አሜሪካውያንን 4-2-2-2 ፎርሜሽን መጠቀማቸው የሲቲን አማካይ ክፍል ተጋላጭ ያደርገዋል፡፡ ቴሬን በተደራቢ አጥቂነት ቢያሰልፉት እንኳን ሲስቁም ወደ 4-2-3-1 አልያም 4-3-3 የመቀየር ዕድሉ የጠበበ ነው፡፡

ቱሬ እንደ ሶስተኛ ሰው ድጋፍ መስጠት አልቻለም፡፡ ሚሱት ኦዚል፣ ሁዋን ማታ እና ዌስሊ ሽናይደርን እንደመሳሰሉ ተጨዋቾች ቡድኑን በመከላከሉ ረገድ አያግዝም፡፡ ሆኖም ጨዋታውን ለመቆጣጠር እና በበላይነት ለመምራት በጋራ ጥረት ማድረግ ወሳኝ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ሎካሞድሪች፣ ማሪዮ ጎትዘ፣ አንሄል ዲ ማሪያ፣ ኦስካር እና ፋብሪጋዝን የመሳሰሉ ዘመናዊ 10 ቁጥር ተጨዋቾች ግን ለቡድናቸው የበለጠ የመከላከል ሽፋን ይሰጣሉ፡፡ ይህም ቡድኑ በመከላከሉ ጥብቅ እና አስተማማኝ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ የቼልሲን የአማካይ ክፍል አማራጮች ተመልከቱ፡፡ ኔማኒያ ማቲች፣ ራሚሬዝ፣ ኦስካር እና ፋብሪጋዝን ታገኛላችሁ፡፡ የምትመለከቱት አስደናቂ የማጥቃት ኃይል ብቻ አይደለም፡፡ መከላከል ላይ ጠንካራ ናቸው፡፡

የሲቲ መፍትሄ ምን ይሆን? ቱሬ በሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጪ ችግር ፈጣሪ ሆኗል፡፡ ወኪሉ ተጨዋቹ ደስተኛ አለመሆኑን መናገሩ በቡድኑ ውስጥ የነበረውን ህብረት አናግቷል፡፡ አይቮሪኮስታዊው ለበርካታ ዓመታት የሲቲ ቁልፍ ተጨዋች እንደነበር አይካድም፡፡ ሲጎርፉለት የከረሙ ውዳሴዎች በባህሪው ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ መጠርጠር መልካም ነው፡፡ ትኩረት ማጣት እና ለራስ በሚሰጥ የተጋነነ ግምት ምክንያት የሚፈጠር እብሪት ሊከሰት እንደሚችል መረዳት አዋቂነት ነው፡፡ ቱሬ ማረጋገጥ ያለበት ምንም ነገር እንደሌለ ይሰማው ጀምሯል፡፡ አሳሳቢው ነገር ይህ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ከመጀመሪያ አሰላለፍ ውጪ አይሆንም፡፡

የትኛውም ተጨዋች ከክለብ በላይ ሊሆን አይችልም፡፡ አንድ ተጨዋች የብቃቱን 100 በመቶ አውጥቶ ቡድኑን እያገለገለ እንዳልሆነ እና የቡድኑን ሚዛን ለማናጋት እየተንደረደረ መሆኑ ከታወቀ ቡድኑ ፊቱን ወደ ሌላ አማራጭ ማዞር ይጠበቅበታል፡፡ ታዲያ ሲቲ ሊያማትር የሚገባው ወዴት የሆነ? ጀምስ ሚልነር ትክክለኛ ምትኩ ይመስላል፡፡ ሚልነር ለሲቲ ከሶስት ተጨዋቾች የተዋቀረ የአማካይ ክፍል ሊያስገኝ ይችላል፡፡ ለቦታው የሚያስፈልገውን የታክቲክ ዲሲፕሊን እና ታታሪነት ያሟላል፡፡ ለዚህ እንደ ማሳያ የሚያገለግለው አንሄል ዲ ማሪያ ባለፈው የውድድር ዘመን በመሀል ሜዳ የተፈጠረው ተፅዕኖ ነው፡፡

ሲቲ ሚሊነርን የአማካይ ክፍሉ ቁልፍ ተጨዋች ቢያደርገው ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ከሚቀጥለው የውድድር ዘመን ጀምሮ ከቱሬ ይልቅ ለእርሱ ቅድሚያ ቢሰጥ እርምጃው ብልህነት ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ክሮስ ባርክሌይ ጋር የተያያዙት ጭምጭምታዎች ትርጉም ይሰጣሉ፡፡ ታዳጊው እጅግ ‹‹ምሉዕ›› ከሆነ ተስፈኛ እንግሊዛውያን እግርኳስ ተጨዋቾች ቀዳሚው ነው፡፡ከጉዳት ነፃ መሆን ከቻለ የዓለም ምርጡ ተጨዋቾች የመሆን ዕድል አለው፡፡

ሲቲን ወደ እንግሊዝ እግርኳስ አናት በመምራት ሂደት የቱሬ ሚና ወሳኝ ነበር፡፡ ከአውሮፓ ትላልቅ ተጨዋቾች አንዱ ሊሆን ችሏል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የቀድሞው ብቃቱ አብሮት የለም፡፡ የወንድሙ ሞት እና በክረምቱ ያከናወነው የዓለም ዋንጫ ትኩረቱን እና ጉልበቱን አሳጥቶታል፡፡ የማሸነፍ ረሃቡ ተቀዛቅዞም ይሆናል፡፡ ምክንያቱ ምንም ቢሆን ሲቲ ያለ ቱሬ ለመጓዝ መዘጋጀት አለበት፡፡ በአውሮፓ መድረክ ስኬታማ ለመሆን የነደፈውን ውጥን ወደፊት ማራመድ የሚችለው ያንን ሲያደርግ ብቻ ነው፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>