አቶ ዮናስ ካሳሁን የተባለ ግለሰብ የወ/ሮ አኪኮ ስዩምን ኢ-ሜይል አድራሻ የይለፍ ቃል (ፓስወርድ) ያለ ግለሰቧ ፈቃድ ባልታወቀ መንገድ በመጠቀም ግለሰቧ ከተለያዩ ሰዎችና ድርጅቶች ጋር የምታደርገውን የመረጃ ልውውጥ ወደራሱ አድራሻ በመላክ፣ በማጥፋትና ለ3ኛ ወገን አሳልፎ በመስጠት ወንጀል ጥፋተኛ ተባለ፡፡ ግለሰቡ በአሁኑ ሰዓት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኝ ሲሆን የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ፍ/ቤቱ ለሰኞ ጠዋት ቀጠሮ ይዟል፡፡
የኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆነችው የግል ተበዳይ ወ/ሮ አኪኮ ስዩምን የኤሌክትሮኒክ አድራሻ ባልታወቀ መንገድ አልፎ የግል የመረጃ ልውውጦቿን ወደራሱ አድራሻ መላኩና ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠቱ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መረጋገጡም ታውቋል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የፎረንሲክ ምርመራ ዳይሬክቶሬት ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከኤሌክትሮኒክስ አድራሻ (ኢ.ሜል) መረጃ የመስረቅና የማጥፋት ወንጀል ዙሪያ ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርግለት በጠየቀው መሰረት፤ ተጠርጣሪው ወንጀሉን ለመፈፀም በህገ-ወጥ መንገድ የተበዳይዋን የወ/ሮ አኪኮ ስዩምን የኤሌክትሮኒክ አድራሻና የይለፍ ቃል (ፓስወርድ) ባልታወቀ መንገድ በመጠቀም ግለሰቧ ከተለያዩ ሰዎች እና ድርጅቶች ጋር የምታደርገውን የመረጃ ልውውጥ ወደ ራሱ ከመላኩም በተጨማሪ ኢ/ር ግርማ ገላው ለተባለ ሶስተኛ ወገን መላኩን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ያረጋገጠ ሲሆን ግለሰቧ በተለያዩ ወቅቶች ለተለያዩ የንግድ ስራዎች ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር መልእክት የተላላከችበትን ቀናት በአገራችንና በአውሮፓውያን ዘመን ቀመር በግልፅ አስቀምጦ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የፎረንሲክ ምርመራ ዳይሬክቶሬት ልኳል፡
ከኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ሦስት ጠበቆች አንዱ የሆኑትን አቶ ወገኔ ካሳሁንን አነጋግረን በሰጡን ምላሽ፤ ተከሳሽና ተበዳይ ቀደም ሲል የፍቅር ግንኙነት እንደነበራቸውና ግንኙነታቸው መቋረጡን፣ ከዚያ በኋላ የተበዳይዋን የኢሜል ሳጥን በመስበር በርካታ መረጃዎችን እንደሰረቀ በመታወቁ መረጃዎቹን እንዲመልስላት ራሷም በአማላጅም ጠይቃው እንደነበር ጠበቃው ተናግረዋል፡፡
“ተጠርጣሪው መረጃዎቹን እንድመልስልሽ 40 ሚሊዮን ብር ክፈይኝ፤ ያለበለዚያ መረጃውን አልመልስም” ማለቱን የጠቆሙት ጠበቃው፤ ከዚያም ወመረጃዎችን በመያዝ ክስ መመስረቱን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
“ምስክሮች እንድናቀርብ ፍ/ቤቱ ጠየቀን፤ በምስክርነትም ራሷ ተበዳይና የሰረቃቸውን የኢ-ሜይል መረጃዎች እንዲመልስላት አማላጅነት የላከቻቸው ሰዎች ቀርበው የሚያውቁትን አስረዱ” ያሉት ጠበቃው፣ ከዚህ ሁሉ ሂደት በኋላ ተጠርጣሪው በበቂ ሁኔታ መከላከል ባለመቻሉና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲም ሆነ ምስክሮች በበቂ ሁኔታ ጥፋተኝነቱን በማረጋገጣቸው ባለፈው ረቡዕ ፍ/ቤቱ ጥፋተኛ ብሎታል ብለዋል፡፡
ፍ/ቤቱ የቅጣት ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ተጠርጣሪው ማረሚያ ቤት እንዲቆይ ያዘዘ ሲሆን የቅጣት ውሳኔውን ለመስጠት ለሰኞ ጠዋት 3፡30 ሰዓት ቀጠሮ ይዟል፡፡
“በአገራችን የግለሰቦችን የመረጃ ሳጥን በህገ-ወጥ መንገድ በመስበር ጥፋተኛ የተባለ ሰው ስሰማ የመጀመሪያዬ ነው” ያሉት የኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ጠበቃ፤ እነዚህ ወንጀሎች በአገራችን አዲስ ናቸው፤ በ1949 የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ላይ አልተካተቱም፤ በአዲሱ ላይ ግን ተካተው ይሄው እየሰሩ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ በኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ በውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ በአስጐብኚ ድርጅትና ማሽነሪዎችን በማከራየት እንዲሁም በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማራ ኩባንያ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
Source : Addis Admas