- ቅ/ሲኖዶሱኻያ ኹለት የስብሰባ አጀንዳዎችን በማጽደቅ መወያየት ጀምሯል
- በሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያው ሥልጣናቸውን የማጠናከር ውጥን አላቸው
- የማኅበረ ቅዱሳን ደንብ አጀንዳ እንዳይኾን መቃወማቸው ውድቅ ተደርጓል
- ሊቃነ ጳጳሳቱን ባዘለፉባቸው ሕገ ወጥ ስብሰባዎች ይቅርታ ጠይቀዋል
- የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በራሱ የሚመራው ሊቀ ጳጳስ ይመደብለታል
- በደቡብና ምዕራብ ኢትዮጵያ የቤተ ክርስቲያን ጸጥታ ጉዳይና የተሐድሶ መናፍቃን የሚፈጥሯቸው ችግሮች በአጀንዳነት ተይዘዋል
- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው ከፍተኛ ሥልጣን ባለቤትና ከማንኛውም መዋቅር ኹሉ የበላይ አካል የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለምልአተ ጉባኤው መደበኛ ስብሰባ ያሰሙትን የመክፈቻ ንግግር ‹‹ለቤተ ክርስቲያን የማይመጥን ነው›› በሚል በጥብቅ ተቃወመው፡፡ ተቃውሞው የተገለጸው፣ ምልአተ ጉባኤው የስብሰባው ቁጥር አንድ አጀንዳ ባደረገውየፓትርያርኩ የመክፈቻ ንግግር ላይ በተወያየበት ወቅት ነው፡፡በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፭ ቁጥር ፻፷፬ ድንጋጌ መሠረት ከጥቅምት ፲፪ ቀን ጀምሮ የሚካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲከፈት፣ ፓትርያርኩ በብዙኃን መገናኛ ፊት በንባብ ያሰሙት ንግግር፣ ከወቅታዊነቱና አግባብነቱ አኳያ ቅዱስ ሲኖዶሱ አስቀድሞ ሊመክርበት ይገባ ነበር በሚል የምልአተ ጉባኤው ተሳታፊዎች በአንድ ድምፅ አቋም እንደያዙበት ተመልክቷል፡፡
የምልአተ ጉባኤውን ስብሰባ በርእሰ መንበርነት የሚመሩት ፓትርያርኩ በመክፈቻ ንግግራቸው÷ በምእመናን ፍልሰት፤ በቤተ ክርስቲያን ስም ሀብትና ንብረት ይሰበስባሉ ባሏቸው ማኅበራት፤ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን በማያሰፍን እንዲኹም በቴክኖሎጂ ባልተቃኘ የሰው ኃይል፣ የገንዘብና የንብረት አስተዳደር ችግር ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ግልጽና አደገኛ ፈተናዎች እንደተጋረጡባት ገልጸዋል፡፡
ፓትርያርኩ ከጠቀሷቸው ዐበይት ችግሮች መካከል ለማኅበራት ጉዳይ የተለየ ትኩረት የሰጠ በሚመስል ንግግራቸው÷ ማኅበራቱ፣ የሚሰጣቸውን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኝነቱና ቅንነቱ የሌላቸው ኾነው እንደተገኙና በአስተዳደር ሥራ በቀጥታ ጣልቃ እንደሚገቡ በመጥቀስ ‹‹የሰላም ጠንቆች›› ብለዋቸዋል፤ ቤተ ክርስቲያን በአክራሪነት የምትፈረጀው ማኅበራቱ በመንግሥትና በቤተ ክርስቲያን የማይታወቅ ሀብት ስለሚሰበስቡ እንደኾነም አመልክተዋል፡፡
በክርስትናችን ትውፊት የማኅበራት ሚና ‹‹ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ጸበል እየቀመሱ መኖር›› ብቻ እንደኾነ የተናገሩት አባ ማትያስ፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማኅበራትንና የምእመናን ፍልሰትን የተመለከተ ሕጋዊና ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ ‹‹ቤተ ክርስቲያንን የመታደግ ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የምእመናን ፍልሰትን ይኹን የሀብትና ንብረት አስተዳደርን የንግግራቸው ማጀቢያ ያደረጉት ያኽል እንደ ማኅበራቱ ጉዳይ ብዙም ያላተቱት ፓትርያርኩ፣ በነጠላ ቁጥር ወደሚጠቅሱትና ስሙን በግልጽ ወዳልጠሩት ‹አንድ ማኅበር› በመሸጋገር፣ ‹‹በሕግ ማስተካከል አለብን›› ለሚለው አቋማቸው አጽንዖት ለማስገኘት ሲጥሩ ተስተውለዋል፤ ሕዝበ ክርስቲያኑም ‹‹ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያን ሕግ እንዲመራና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኾኖ እንዲያገልግልእ የተደረገ ነው፤›› ያሉትን ጥረታቸውን እንዲያግዛቸው ጥሪአቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የምእመናን ፍልሰት፣ የሰው ኃይልና የንብረት አስተዳደር ይኹን የብዙኃን መንፈሳውያን ማኅበራት ጉዳይ አሳሳቢነቱ የቱንም ያኽል ቢኾን፣ በፓትርያርኩ ንግግር ውስጥ የተጠቀሱበት መንገድ በቅዱስ ሲኖዶሱ የተመከረበትና የምልአተ ጉባኤው አቋም ያረፈበት ሊኾን እንደሚገባው የገለጹ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ‹‹ቋንቋው የቤተ ክርስቲያን አይደለም፤ አይመጥናትምም›› በሚል በጽኑ እንደተቹት ተሰምቷል፡፡
የአባ ማትያስ የመክፈቻ ንግግር ከይዘቱም አኳያ ሲፈተሽ፣ ‹‹ግልጽና አደገኛ ፈተናዎች›› በተባሉት ችግሮች ላይ ቤተ ክርስቲያን የያዘችውን አቋምና የወሰደችውን ርምጃ የማያመላክትና ወቅታዊነት የጎደለው ነው በሚል ተነቅፏል፡፡ ይኸውም በንግግራቸው ለተጠቀሱት ችግሮች መፈታት ምልአተ ጉባኤው ቀደም ሲል ጥናታዊ ውሳኔ ያሳለፈባቸው፣ የይኹንታ አቅጣጫና መመሪያ የሰጠባቸው በመኾኑና መፍትሔውም እነርሱኑ መዋቅሩን ጠብቆ ለማስፈጸም ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ጉዳይ ተደርጎ በመወሰዱ ነው ተብሏል፡፡
ለብዙኃን መገናኛ መገለጽ ያለባቸው የፓትርያርኩ ንግግሮች፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውና የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ በበቂ ከመከረ በኋላ በመጨረሻ በሚደርስባቸው ስምምነቶች ላይ ተመሥርቶ የሚያወጣቸው መግለጫዎች ብቻ እንዲኾኑም በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ሙሉ የጋራ አቋም እንደተያዘበት ታውቋል፡፡ በመኾኑም ከአኹኑ የቅ/ሲኖዶስ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ በኋላ ርእሰ መንበሩ ፓትርያርክ አባ ማትያስ የሚያደርጉት የመክፈቻ ንግግር፣ በቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት አስቀድሞ የተመከረበትና በምልአተ ጉባኤው አባላት የ‹‹እንኳን ደኅና መጣችኁ›› አቀባበል ላይ ብቻ ያተኮረ እንዲኾን መወሰኑን የስብሰባው ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በፓትርያርኩና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ መካከል ጠንካራ የቃላት ልውውጥ እንደነበረና ፓትርያርኩ ‹‹ወትሮም ጠላቴ›› በሚል ሊያሸማቅቋቸው የሞከሩ ብፁዓን አባቶች እንዳሉም ተሰምቷል፡፡ ይኹንና የሢመት ቅድምና ያላቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ ኹሉም የምልአተ ጉባኤው አባላት ፓትርያርኩ በአመራራቸው፣ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና የቅዱስ ሲኖዱሱን ውሳኔ በመፃረር የቤተ ክርስቲያንን ክብር እያስደፈሩና ልዕልናዋን እያዋረዱ እንዳለ በመጥቀስ በተባበረ ድምፅ በመገሠጻቸው ይቅርታ ለመጠየቅ እንደተገደዱ ተዘግቧል፡፡
ፓትርያርኩ ተግሣጹን ተቀብለው ምልአተ ጉባኤውን ይቅርታ ከጠየቁባቸው መተላለፎቻቸው ውስጥ፣ በመስከረም ወር መጨረሻ ከመዋቅር ውጭ በልዩ ጽ/ቤታቸው በኩል በጠሯቸውና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ ተደምረው በአማሳኞች የተዘለፉባቸው ስብሰባዎችና ቅዱስ ሲኖዶሱ ያልመከረበት የመክፈቻ ንግግራቸው እንደሚገኝበት ተጠቅሷል፡፡ ፓትርያርኩ ያሻቸውን እየፈጸሙ ይቅርታ መጠየቅን እንደ ስልት መያዛቸውን የሚጠቅሱ ወገኖች በበኩላቸው፣ ከይቅርታው ጋራ የፓትርያርኩ አመራርና አካሔድ ለአማሳኞች የጥፋት ምክርና ለውጭ ተጽዕኖ ከተጋለጠበት ኹኔታ ተጠብቆ የቅዱስ ሲኖዶሱን ልዕልናና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ለማስከበር የሚያስችል የማስተካከያ ርምጃ እንዲወሰድበትና ቋሚ አሠራር (የጠንካራ እንደራሴ ጉዳይ እንደ አብነት ተጠቅሷል) እንዲበጅለትይጠይቃሉ፡፡
የቤተ ክርስቲያን ‹‹ግልጽና አደገኛ ፈተናዎች›› በሚል በፓትርያርኩ የመክፈቻ ንግግር ለተጠቀሱት የምእመናን ፍልሰትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሔው÷ ለመዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር ለውጥ የቀረቡትንና የብዙኃኑን ካህናትና ምእመናን ተቀባይነት ያረጋገጡ ጥናቶች በትግበራ ስልት ወደ ፍጻሜ ምዕራፍ በማሸጋገርና የቅዱስ ሲኖዶሱን አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች በማስከበር ልዕልናውን ለማረጋገጥ የሚበቃ የመሪነት ብቃትና ቁርጠኝነት ገንዘብ አድርጎ መገኘት እንደኾነ ተገልጧል፡፡
ስለ ማኅበራት ጉዳይ በተመለከተም ቅዱስ ሲኖዶስ በግንቦት ፳፻፬ ዓ.ም. መመሪያው፣ የተከሠቱትና ወደፊትም ሊከሠቱ የሚችሉት ችግሮች በቀላሉ የሚታዩ እንዳልኾነ ገልጾ መንሥኤው በሕግና በሥርዐት የሚመሩበት ደንብ ስላልተሰጣቸው መኾኑንገልጧል፡፡ መፍትሔውም ማኅበራቱን ፓትርያርክ አባ ማትያስ እንዳሉት‹‹በጸበል ቀማሽነት›› መወሰን ሳይኾን ለቤተ ክርስቲያን እየሰጡ ያሉትን ታላቅ አገልግሎትና ብዛታቸውን መቆጣጠርን የተገነዘበ፣ ‹‹ራሱን የቻለና የሚያሠራ ሕግ›› ማዘጋጀት እንደኾነም አስቀምጧል፡፡ ለዚኽም ብፁዓን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ባለሞያዎች ያሉበት ደንብ አዘጋጅ ኮሚቴ ሠይሞ ነበር፡፡
ፓትርያርኩ ‹‹ኹላችኁ የምታውቁት አንድ ማኅበር፤ ማኅበሩ›› በሚል ስሙን በግልጽ ስለማይጠቅሱት ማኅበረ ቅዱሳንም ቢኾን ቅዱስ ሲኖዶሱ በዚያው መመሪያው፣ ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀ ደንብ ተሰጥቶት ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጠ የቆየና አኹንም እየሰጠ ያለ መኾኑን አረጋግጧል፡፡ የተሰጠው መተዳደርያ ደንብና የአሠራር መዋቅሩ÷ የማኅበሩን ዕድገት የሚመጥን፣ ለቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊና የላቀ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለማበርከት የሚያስችለው ተደርጎ መሻሻል እንደሚያስፈልገው በመወሰንም የ፲፱፻፺፬ ዓ.ም. መተዳደርያ ደንቡን መርምሮ የሚያሻሽል ከብፁዓን አባቶች፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ከሕግ ዐዋቂዎች የተውጣጣ ኮሚቴ ሠይሟል፡፡ ደንቡ ተሻሽሎ እስከሚጸድቅም ማኅበሩ ተጠሪነቱ ለብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ኾኖ አመራር በመቀበል እየሠራ እንዲቆይም መመሪያ ሰጥቷል፡፡
አምስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ሦስት የሕግ ባለሞያዎችንና ሦስት የማኅበረ ቅዱሳን አመራሮችን በአጠቃላይ ዐሥራ አንድ አባላትን የያዘው የመተዳደርያ ደንብ አጥኚ ኮሚቴም በሐምሌ ወር ፳፻፬ ዓ.ም. የጀመረውንና በተለያዩ ምክንያቶች ሲስተጓጎል የቆየውን የማሻሻያ ጥናት በ37 አንቀጾችና በ34 ገጾች አካትቶ በሚያዝያ ወር ፳፻፮ ዓ.ም. ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አቅርቧል፡፡
ይኹንና ከማኅበሩ የታወጀ ኦርቶዶክሳዊ ዓላማ ጋራ ርእዮታዊና ሃይማኖታዊ ተፃባኢነት (ተፃራሪነት) ያላቸው የውስጥ አማሳኞችና የውጭ ኃይሎች ለፓትርያርኩ ያቀበሏቸው የሚመስለውና ፓትርያርኩ አንዳችም ሳይጨመርና ሳይቀነስ በማሻሻያው ይካተት በሚል ሕጋዊነትም ምክንያታዊነትም የጎደለው የተልእኮ አስፈጻሚነት መመሪያ ሳቢያ የማሻሻያ ረቂቁ ዘግይቶም ቢኾን ጸጽቆ በሥራ ላይ መዋል ከሚገባው ካለፈው ዓመት ግንቦት የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ አድሮ በእጅጉ ተጓትቶ ይገኛል፡፡
ከማኅበሩ የአገልግሎት ፈቃድ ዕድሳት፣ ከአመራሮችና አስፈጻሚዎች ምርጫ፣ ከአባላት አያያዝ፣ ከሪፖርት አቀራረብ፣ ከገንዘብና ንብረት ቁጥጥር ጋራ የተገናኙ 24 ነጥቦችን የያዘው መመሪያው፣ የማኅበሩን የአገልግሎት ነፃነትና የአገልግሎት አቅሞች በሒደት የሚያዳክምና በመጨረሻም የሚያጠፋ እንደኾነ በመተዳደርያ ደንብ አጥኚ ኮሚቴው አብላጫ አባላት ስለታመነበት በማሻሻያው እንዳለ ይካተት ብሎ ለመቀበል አዳጋች እንደኾነ በወቅቱ ለፓትርያርኩ ተገልጦላቸዋል፡፡ ኮሚቴው በነጥቦቹ ላይ በወቅቱ ለፓትርያርኩ በሰጠው በሕግ ሞያ የተደገፈ ማብራሪያ፣ በመመሪያው ከተጠቀሱት ነጥቦች የተወሰኑት ቀድሞም በማሻሻያ ረቂቁ ያሉ መኾናቸውን የተቀሩት ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ደንቡ ዝግጅት ከሰጠው ውሳኔ ጋራ የሚቃረን መኾኑን በግልጽ አስረድተዋቸዋል፡፡
- ባለፈው ዓመት ግንቦት፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ የማሻሻያ ረቂቁን በአጀንዳነት ይዞ በተወያየበት ወቅት ይህንኑ የአጥኚ ኮሚቴውን ሐሳብ የተቀበሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ የፓትርያርኩን የእልከኝነትና ግትርነት አካሔድ ተቃውመዋል፤ ‹‹24ቱን ነጥቦች ሳይጨምር ሳይቀነስ ካላስገባችኁ ውይይቱ አይቀጥልም፤ ስብሰባውንም አልመራም›› ያሉት ፓትርያርኩም ለብዙኃኑ ውሳኔ ባለመገዛታቸው የስብሰባው ሒደት እግዳት ውስጥ ገብቶ በዚያው ተቋጭቷል፡፡ ምልአተ ጉባኤው በመነጋገርያ አጀንዳዎች ላይ በተወያየበት በትላንቱ የቀትር በፊት ውሎውም ፓትርያርኩ ካለፈው ዓመት ግንቦት ለዘንድሮው ጥቅምት ያደረው የማኅበሩ የመተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ በአጀንዳነት እንዳይያዝ በብዙ ታግለው እንደነበር ተገልጧል፡፡ይኹንና ፓትርያርኩ በስብሰባው መጀመሪያ ላይ ቋሚ ሲኖዶሱ ለምልአተ ጉባኤው ካቀረበው የመነሻ አጀንዳ ዝርዝር ውስጥ ረቂቁ እንዳይያዝ በማድረግ ቢሳካላቸውም ምልአተ ጉባኤው የሠየመው ሰባት አባላት ያሉበትና በጉዳዩ ላይ ጽኑ አቋም የያዘው አጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ እንዳያካትተው ለመከላከል ግን ሳይቻላቸው ቀርቷል፡፡ በመኾኑም የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ከምልአተ ጉባኤው 22 ያኽል የመነጋገርያ አጀንዳዎች ውስጥ በተራ ቁጥር 14 ሊካተት ችሏል፡፡ ይህም ፓትርያርኩ በ፴፫ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ በቅስቀሳ መልክ ያነሷቸው ጥያቄዎች በአማሳኞች ጩኸትና በውጭ ኃይሎች ግፊት ሳይኾን በቅዱስ ሲኖዶሱ ታይቶ እንዲወሰን የያዘውን አቋም ትክክለኛነትና አሸናፊነት ያሳየ ኾኗል፡፡
በመክፈቻ ንግግራቸው ማኅበሩን በሕግ ለማስተካከል የዛቱት አባ ማትያስ፣ በእጅጉ የተጓተተው የማኅበረ ቅዱሳን ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ በአጀንዳ ተይዞ እንዳይጸድቅ መከላከላቸው፣ ፍላጎታቸው ላይ ላዩን እንደሚወተውቱት ማኅበሩን በሕግና በሥርዐት መምራት አለመኾኑን እንደሚያሳይእየተገለጸ ይገኛል፡፡ ለዚኽም ለአኹኑ ምልአተ ጉባኤ የመጨረሻ መልኩን ይዞ እንዲቀርብ በተወሰነው የ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. ሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቅ ከተሰጠው የእርምትና ማስተካከያ አቅጣጫ ውጭ ሥልጣናቸውን የሚያጠናክሩባቸው አግባቦች እንዲካተቱ መደረጋቸው ተጠቁሟል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ ተጨማሪ እርማትና ማስተካከያ እንዲያደርጉ ከሠየማቸው ብፁዓን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ባለሞያዎችመካከል ልዩ ጸሐፊያቸውን ያስገቡት ፓትርያርኩ÷ በተለይም በሊቃነ ጳጳሳት ምደባና ዝውውር እንዲኹም በማኅበራት ጉዳይ ላይ የወሳኝነት ሥልጣን እንዲኖራቸው እንዲኹም ከቅዱስ ሲኖዶሱ ውጭና በላይ ራሳቸውን ተጠሪ አድርገውባቸዋል የተባሉ ሌሎች የማሻሻያ አግባቦች ምልአተ ጉባኤውን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያነጋግሩ ይጠበቃል፤ ምናልባትም የማሻሻያ ረቂቁን ከመጽደቅ ሳያዘገየው እንደማይቀርም ተሰግቷል፡፡
የመንበረ ፓትርያርኩ መቀመጫ የኾነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት የኾነበት ልማድ፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ እያንዳንዱ ሀገረ ስብከትበቅዱስ ሲኖዶስ በተሾመ ሊቀ ጳጳስ ወይም ጳጳስ ወይም ኤጲስ ቆጶስ እንዲመራ ከሰፈረው ድንጋጌ አኳያ ተፈትሾ ራሱን የቻለ ሊቀ ጳጳስ ሊመድብለት እንደሚችልተጠቁሟል፡፡ ይህም በአኹኑ ወቅት ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ ልዩ ጽ/ቤት በተዘረጋው የአማሳኞች የምዝበራ ሰንሰለት ካህናትና ምእመናን በተለይም የመዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር ለውጡን የደገፉ ወገኖች፣ ‹‹ከዛሬ ነገ እንባረራለን›› በሚል ስጋት አቤት የሚሉበት አጥተው በብቀላ ዝውውር የሚንገላቱበትን አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት እንደሚገታው ተገልጧል፡፡
- ከምልአተ ጉባኤው ሌሎች አጀንዳዎች መካከል÷ ምእመናን በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን በእጅጉ ስለተፈተኑባቸው፤ የቤተ ክርስቲያን መሥሪያና የመቃብር ቦታ እስከመከልከልና እስከማጣት ስለደረሱባቸው፣ አብያተ ክርስቲያን ስለተቃጠሉባቸው በክልላዊ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት ካህናትና ምእመናን ለኅልፈት ስለበቁባቸው የሐዲያና ስልጤ፣ የምዕራብ ወለጋና ቄለም ወለጋ እንዲኹም የጋምቤላ አህጉረ ስብከትይመክራል፡፡ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት አስተዳደር በብፁዕ ሊቀ ጳጳሱና በማኅበሩ መካከል ስላለው አለመግባባት፤ በሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት የሕፃናት መርጃ ኾነው የተቋቋሙ ማእከላት ነባር ይዞታዎች መጠበቅ እንዲኹም በቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ከፍተኛ የግንባታ ፕሮጀክቶች ዙሪያ በመምከር ውሳኔ እንደሚያሳልፍም ይጠበቃል፡፡
- source: haratewahido
↧
ፓትርያርኩ: የቤተ ክርስቲያን ራስ ቅዱስ ሲኖዶስ ባልመከረበትና ‹‹ለቤተ ክርስቲያን የማይመጥን ነው›› በተባለው የመክፈቻ ንግግራቸው ተገሠጹ፤ ውሳኔም ተላለፈባቸው!
↧