አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ በአሁኑ ሰዓት ከመቼም ጊዜ በላይ በጠንካራ አቋም ላይ ይገኛል። በፓርቲው ውስጥ ጎልቶ እየታየ የመጣው የለውጥና የማንሰራራት ፍላጎት ተገንዝበው የፓርቲው ፕሬዚደንት የነበሩት ኢንጂነር ግዛቸው ሺፈራው በራሳቸው ፍቃድ መልቀቃቸው የፓርቲው የዴሞክራሲ ባህል የላቀ ደረጃ ላይ መድረሱን በትክክል የታየበት፤ ፓርቲው በተሻለ ቁመና ላይ እንዲጓዝ በር የከፈተ ትልቅ እርምጃ በመሆኑ ሊደነቅ የሚገባ ጉዳይ ነው። በመሆኑም ብሄራዊ ምክር ቤቱ ጥቅምት 2/2007 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የኢንጂነር ግዛቸውን የመልቀቂያ ጥያቄ አዳምጦ ካፀደቀ በኋላ የፓርቲው መተዳዳሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሰረት አስመራጭ ኮሚቴ አቋቁሞ ፓርቲውን በቀጣይነት የሚመራ ሰው በዕለቱ ከቀረቡት ሶስት እጩዎች መካከል አቶ በላይ ፍቃዱን በከፍተኛ ድምፅ የፓርቲው ፕሬዝዳንት አድርጎ መርጠዋል።
አንዳንድ ወገኖች በዚህ ፍፁም ደንባዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሂደት ያለፈና የፀደቀ ጉዳይ የደንብ ጥሰት የተፈፀመ በማስመሰል ጫጫታ ለመፍጠር የተንቀሳቀሱበት ሁኔታ ቢኖርም፤ በዚህ ዴሞክራሲያዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር ላይ ምንም ዓይነት የደንብ ጥሰት ያልተፈፀመ መሆኑ አፅንኦት ሰጥተን ለመግለፅ እንፈልጋለን። አንድነት ውስጣዊ የዴሞክራሲ ባህል ያለው፤ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት የሚችልና በዚህ ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ልምድ ያለው ፓርቲ ነው።
በአሁኑ ሰዓት አዲሱ ፕሬዚዳንት በአዲስ መንፈስ ካቢኔያቸውን አቋቁመው በፍጥነት ወደ ስራ የገቡበት ሁኔታ ነው ያለው። ፓርቲው የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ውስጡን የማጥራትና የማስተካከል ስራ እየተሰራ ከመሆኑም ባሻገር የሁሉም ኢትዮጵያውያን ቤት እንዲሆንና ብቃት ያላቸው አመራሮች ወደፊት እንዲመጡ በማድረግ አንድነት በሰላማዊ ትግሉ ታግሎ በማታገል የስርዓት ለውጥ ማምጣት የሚችል ህዝባዊ መሰረት ያለው ፓርቲ እንዲሆንና ጠንካራ ቁመና እንዲኖረው ርብርብ እየተደረገ ይገኛል። ህዝቡ ይህን ተገንዝቦ እንደ ከዚህ ቀደሙ ከጎናችን እንዲቆም፤ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ በምናደርገው ትግልም ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
ኢትዮጵያ በነፃነቷና በአንድነቷ ለዘላለም ትኑር!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ
ጥቅምት 12/2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ