እኛ 1ኛ/ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት/መኢአድ/
2ኛ/ የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/መኢዴፓ/
3ኛ/ የመላው ዐማራ ህዝብ ድርጅት/መዐህድ/
4ኛ/ ሰማያዊ ፓርቲ/ሰማያዊ/
5ኛ/ የሶዶ ጎርደና ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት/ ሶጎህዲድ/
6ኛ/ የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ/ኢብአፓ/
7ኛ/ የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት/ኦህዲኅ/
8ኛ/ የከምባታ ህዝቦች ኮንግረስ /ከህኮ/
9ኛ/ የጌዲኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት/ጌህዴድ/
የአገራችንን ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታ በማጤን፣ እስካሁን የተደረጉ የትብብር ጥረቶች ለምን አልተሳኩም የሚለውን ጥያቄ ለመመለስና የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ባደረግነው ግምገማና ዳሰሳ ባገኘነው ውጤትና ጭብጥ መሰረት ላይ በደረስነው የጋራ ስምምነት በትናንትናው ቀን በጋራ የምንሰራበትን የስምምነት ሰነድ ተፈራርመናል፡፡ መነሻችን በገዢው ፓርቲ/መንግሥት የሚፈጸሙ ኢ-ህገመንግሥታዊ እና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ተግባራት በአገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን እውን ለማድረግ ከማያስችሉበት ደረጃ በመድረሱ በአገራችን የተፈጠረውን ምስቅልቅል ለመሸከምም ሆነ ለቀውሱ ተመጣጣኝ መፍትሄ መስጠት ከገዢው ፓርቲም ሆነ ከአንድ ተናጠል ፓርቲ አቅም በላይ ነው በሚለው የጋራ ግንዛቤኣችን ላይ በመመሥረት አንድ ጠንካራ የተባበረ ህዝባዊ የፖለቲካ ኃይል መፍጠር ከመቼውም ጊዜ በላቀ አስፈላጊ ብቻ ሣይሆን ለአገራችን ህልውና ወሳኝ መሆኑ ነው፡፡ የትብብሩ አስፈላጊነትና ወቅታዊነት በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ማለትም ፡-
ነጻ፣ፍትሃዊ፣አሳታፊና ተኣማኒ ምርጫን፣
የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት፣
የዜጎችን ሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ በሚመለከት
በሁላችንም በተደረሱ የጋራ ግንዛቤዎች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በነዚህ የጋራ ግንዛቤዎች ላይ ተመስርተን ለቀጣይ የጋራ ጉዞኣችን ሁለት ዋና ዓላማዎች በማበጀት ለነዚህ ዋና የጋራ ዓላማዎችም የማስፈጸሚያ ተግባራትን ለይተን ለተፈጻሚነታቸው በአጭር ጊዜ በመጪው ምርጫ 2007 ዙሪያ በጋራ የምንቆምበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ በረጅሙ በመካከላችን ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ ስለሚቀጥልበትና በአገራችን ለማየት ለምንሻው ለውጥ መሰረት ለመጣል እጅ ለእጅ ተያይዘን ለመሥራት የሚያስችለን ጠንካራ የጋራ የፖለቲካ ኃይል ስለምንፈጥርበትና አገራችን ከገባችበት አዘቅት ለማውጣት ሁሉንም ባለድርሻ የሚያሳትፍ የብሄራዊ መግባቢያና ዕርቅ መድረክ ለማመቻቸት ከጋራ ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ ውጥን ‹‹ኅብረት ኃይል ነው›› ከሚለው ንድፈ ኃሳብ ደረጃ አልፎ ተግባራዊ እንዳይሆን ባለፉ ጊዜያት የተስተዋሉብንን ድክመቶችና ውስንነቶች ፣ያጋጠሙ ችግሮችንና በቀጣይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ደንቃራዎችን በአንድ በኩል ፣ ጥቂት ቢሆኑም ካለፉ ጥረቶች የተገኙ ውጤቶችንና ገንቢ ልምዶችን፣ ያሉትን አመቺ ሁኔታዎችና ለቀጣይ የጋራ ትግላችን የሚጠቅሙ መልካም አጋጣሚዎችን በሌላ በኩል የተመለከትንበትና በዚህ ላይ ቆመን የቀጣይ አቅጣጫችንን ያሰመርንበት ነው፡፡ የዚህ ስምምነት ዘላቂ ግብ ማንም ተጎጂ የማይሆንበትና ሁላችንም ተጠቃሚ የምንሆንበትን አቅጣጫ የተከተለ እንደመሆኑ ገዢው ፓርቲ/መንግስት እኔ ከሥልጣን ከለቀቅሁ በቀጣይ በሚመጣው ለውጥ አገር ትበታተናለች በማለት ህዝብን ከሚያስፈራራበት፣ ካድሬዎቹን ፣መከላከያ ሠራዊቱንና የፀጥታና ደህንነት ኃይሉን ተቃዋሚዎች ካሸነፉ አንድም ለወህኒ ካነሰም ‹‹ለልመናና የጎዳና ተዳዳሪነት›› ትዳረጋላችሁ… በሚል ሽብር ከሚነዛበት ፕሮፖጋንዳና አካሄድ እንዲመለስና እንዲታረም ዕድል የሚሠጥ ነው፡፡
ለእኛ ከምንም እና ከማንም በላይ ቀዳሚው አገርና ህዝብ እንደመሆኑ የጋራ ግባችን ዜጎች ከዘላቂ ሠላምና ልማት ያለአድልኦ ተጠቃሚ የሚሆኑባት ፣ የህግ የበላይነት ሰፍኖ ዜጎች በእኩልነትና በነጻነት ተከባብረው የሚኖሩባት ፣ሉዓላዊነቷ የተከበረ ዲሞክራሲዊት ኢትዮጵያን መገንባት ነው፡፡ በእኛ እምነት እነዚህ ሁኔታዎች በተሟሉበት እውነታ ውስጥ በሁለት ጽንፎች የተወጠረው የአገራችን የአሸናፊ-ተሸናፊ የጠቅላይ ሥልጣን ፖለቲካ ልምድ ይቀየራል፤ በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በህዝቦች መካከል ያለውን አብሮነት ለመበጣጠስ የተዘራውን አጥፊ ዘር ማድረቅ፣ የተሰራጨውን መርዝ ማርከስ ይቻላል፡፡
በትናንትናው ቀን ይህን ትብብር የመሰረትን ፓርቲዎች ለጋራ ዓላማችን እውን መሆን ያለፈው አካሄዳችን የትም እንዳላደረሰንና እንደማያደርሰን ከውድቀታችን ልምድ ቀስመን በአዲስ አስተሳሰብና የአመራርና አሰራር ሥርዓት ለማይቀረው ሥር ነቀል ሁለንተናዊ ለውጥ በግልጽነት በተጠያቂነት መርህ በጽናት ለመታገልና ለማታገል የደረስንበትን ስምምነት ስናበስር ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን አገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነት በመገንዘብ ነው፡፡ ስለሆነም ከዓላማችን ለሚያደርሱን ተግባራት ተፈጻሚነት በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ የምትገኙ ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎና አስተዋጽኦ ያለው ድርሻ ከፍተኛ ስለሆነ ከጎናችን በመቆምና በንቃት በመሳተፍ የዜግነት ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ፣ እንዲሁም በሂደቱ ከጅምሩ እስከ መጨረሻው ተሳትፋችሁ በተለያየ ምክንያት በትናንትናው ቀን የስምምነቱን ሰነድ ያልፈረማችሁም ሆነ የአገርና ህዝብን ጉዳይ ከፓርቲ ጥቅምና ዓላማ አብልጣችሁ የምትመለከቱና ለዚህም በጋራ ለመሥራት ዝግጅቱና ቁርጠኝነቱ ያላችሁ ሌሎች ሠላማዊ የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከጋራ ትግሉ እንድትቀላቀሉ
ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
በጠራ ኃሳብ ላይ የተመሰረተ በራሱ አቅጣጫ የሚጓዝ የተባበረ ህዝባዊ ትግል ያሸንፋል //
ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ