አሻራ፦ ጤና ይስጥልኝ አርቲስና አክቲቪስት ታማኝ በየነ፤ በቅድሚያ ስለ ጊዜህ በአንባቢያን ስም ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ። አቶ አንዳርጋቸውን ለምን ያህል ጊዜ ታውቃቸዋለህ ? እንዴትስ ትገልጻቸዋለህ?
ታማኝ፦ አንዳርጋቸውን የማውቀው ከምርጫ 97 ጀምሮ ነው።በምርጫ 97 ቅንጅትን ተቀላቅሎ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ማለት ነው። ያኔ መቼም ሁላችንም ልባችን የምርጫው እንቅስቃሴ ላይ ስለ ነበር በየእለቱ እየደወልን ሁኔታውን እንከታተል ነበር። እኔም ራሴ ሃገሬ ገብቼ እንደልቤ በነጻነት ለመኖር የምችልበት ጊዜ አሁን ነው ከሚል እምነት የመግባት እቅድ ነበረኝ። አንዳርጋቸውን የማውቀው እንግዲህ በዛ ግዜ በነበረን የስልክ ግንኙነት ነው። እስኪታሰር ድረስ ማለት ነው። በነገራችን ላይ ከመታሰሩ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ያናገረኝ እኔን ነበር። ከኔ ጋር አውርተን ስልክ እንደዘጋ ነው የታሰረው።
ከንግግራችን የማስታውሰው እኔ እዚህ ሆኜ በስልክ ብቻ ከምከታተል ልምጣ እያልኩት ነበር። እሱ ደግሞ በዚህ ደረጃ መምጣት የለብህም እዛው ብትሆን ነው የምትጠቅመን እያለኝ ተነጋግረን እንደጨረስን ታሰረ። ከዚያም ተፈቶ ወደ እንግሊዝ አገር ተመለሰ። በኋላም በቅንጅት ኢንተርናሽናል ተመርጦ ሲሰራ በስልክም በአካልም እንገናኝ ነበር። ከአንዳርጋቸው ጋር የነበረን ትውውቅ ይህን ይመስል ነበር፡፡
እንዴት ትገልጸዋለህ? ላልከኝ፦በጣም አስቸጋሪ በሆነበት ጊዜና መንገድ ህልሙን ሊያሳካ የደከመ ሰው ነው!። በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት የውጭውን ዓለም ዘመናዊ ህይወት የለመዱ ከአውሮፓና ከአሜሪካ እየሄዱ የኢህአፓን ትግል ተቀላቅለው በርሃ የቀሩ ወጣቶች እንደነበሩ አንብቢያለሁ። በንባብ የምታውቀውን ታሪክ በአካል የምታውቀው ሰው ሲያደርግ ስታይ ደግሞ በጣም ከባድ ነው። በአውሮፓና አሜሪካ ህይወት ፤ ምግብ፤ አልባሳት፤መኝታ፤ መዝናኛ፤
ብቻ እያንዳንዷን ነገር በምርጫና በፍላጎት የምታደርግበትን ህይወት ለምደህ በርሃ ገብተህ፤ ድንጋይ ለመንተራስ፤ አሸዋ ለመልበስ፤ ላለመታጠብና ያልታጠበ ለመልበስ መወሰን እጅግ በጣም ከባድ ነው። አስበው ከእንግሊዝ አገር ከንግስቲቷ ከተማ ሄዶ አሸዋ ላይ መተኛት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ!።
ባጠቃላይ አንዳርጋቸው ከልጅነቱ ጀምሮ ከራሱ ህይወት አልፎ ቤተሰቡ የከፈለውን መስዋዕትነት ሳይ የሚሰማኝ ስሜት ሃዘን ሳይሆን ይህን ሥርዓት በተለያየ መልኩ እንታገላለን ለምንል ወገኖች ትልቅ ምሳሌና አርአያ የሆነ ሰው መሆኑን ነው።
አሻራ፦ የወያኔ መንግስት አንድን ግለሰብ ለመያዝ ይህን ያህል ተጨንቆና ተጠቦ፤ ቀደም ሲል የግድያ ሙከራ ማድረጉ አሁን ደግሞ ከፍተኛ ወጪ አፍስሶ፤ ሁለተኛ አገር(የመን) የተሳተፈችበት ድንበር ዘለል አፈና መፈጸሙ ምን የፖለቲካ ፋይዳ አገኝበታለሁ ብሎ ይመስልሃል?
ታማኝ፦ በመጀመሪያ የአንዳርጋቸውን የዓላማ ጽናት (ኮሚትመንት) አብሯቸው በሰራ ጊዜ አይተውታል። ያውቁታል። ከወጣትነት ዕድሜው ጀምሮ በኢ.ህ.አ.ፓ በኋላም ከነሱ ጋር ሲሰራ ለራሴ የሚል ሰው እንዳልሆነ፤ ስልጣን ይዞ ለመንደላቀቅ፤ ቤት ለመስራት፤ መኪና … የመሳሰሉት ቁሳዊ ፍላጎት የሌለው ሰው እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቁታል። የአንዳርጋቸው የዘወትር ቁጭት ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ብዙ ያልተሟሉ ጉዳዮች ስላሏት እነሱን ለማሟላት መሆኑንም ያውቃሉ። ከቅርብ ጊዜው ብናይ እንኳ በምርጫ 97 ቅንጅትን ተቀላቅሎ በአጭር ግዜ ውስጥ ምን ያህል ህዝብን የማሰባሰብና የማደራጀት ስራ እንደሰራ እናስታውሳለን።
ባለፈው አስመራ ድረስ ቅጥር ነፈሰ ገዳይ ልከው ሊያስገድሉት መሞከራቸውን ኢሳት በዘገበበት ጊዜ እንዴት ሊሆን ይችላል?ይሄ የኢሳት ወሬ ነው ያሉኝ ሰዎች ነበሩ። እነሱ(ወያኔዎች) ግን በየት በኩል ጉዳት ሊመጣ እንደሚችል በደንብ ገብቷቸዋል።በኔ ግንዛ አንዳርጋቸው የማስተባበሩን ስራ ጥሩ አድርጎ እንደሚሰራ ስላወቁ ይመስለኛል ይህን ያህል ክትትል አድርገው ሊይዙት የቻሉት።
አሻራ፦ እንዳልከው አቶ አንዳርጋቸውን መያዝ ማለት የተቃዋሚውን አከርካሪ እንደመስበር ሳይቆጥሩት የቀሩ አይመስልም።ይሁንና አቶ አንዳርጋቸውን የመን ላይ ይዘው መውሰዳቸው ለግዜው ጮቤ ቢያስረግጣቸውም፤ ውጤቱ ግን “ አሳ ጎርጓሪ….” ሆኖባቸዋል የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡ አንተስ በዚህ ሃሳብ ትስማማለህ?
ታማኝ፦ በጣም እንጂ የምስማማው።እኔ እንግዲህ ህወሃት አገሪቷን ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንስቶ በተቃዋሚነት አብሬ ኖርያለሁ። በውጭው ዓለምም አውሮፓ ፤ አውስትራሊያ ፤ አሜሪካ …ያለውን የተቃዋሚውን ወገን እንቅስቃሴ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አውቃለሁ እላለሁ። እናም ከቅንጅት በኋላ “የምን ፖለቲካ?…ፖለቲካ በቃኝ!” እያለ የሸሸው ሰው ሁሉ በፈቃደኝነት “ምን እናድርግ?” ብሎ የመጣበት ወቅት ነው አሁን።
የአንዳርጋቸውን ነገር የተለየ የሚያደርገው ደግሞ፦ አንዳርጋቸው በየመድረኩ የሚታይ ሰው አይደለም። ከሱ በበለጠ እኔ በብዙ መድረክ እታያለሁ።
እሱ ግን የሚሰራ እንጂ የሚታይ ሰው አልነበረም፡፡ ይሁንና ህውሃት ይህን ያህል ሊያጠፋው የፈለገው አንዳርጋቸው ምን አይነት ሰው ቢሆን ነው? የሚለውን ነገር እንድት ጠይቅና እንድታገናዝብ ያደርግሃል። ለዚህም ይመስለኛል በውጭም በሃገር ቤትም የሚገኘው ህዝብ በሚያስደንቅ መልክ የተንቀሳቀሰው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር ጋር ስንወያይ “በታሪክ ውስጥ አንዳንድ ሰዎች ለለውጥ ምክንያት ይሆናሉ” ነበር ያለኝ። እኔም አንዳርጋቸው የለውጥ ምክንያት እንደሆነ ነው የሚሰማኝ። በርግጥ በዚህ መልክ መሆኑና እየደረሰበት ያለውን ስቃይ ስታስብ ቢያምህም በህዝብ ውስጥ የፈጠረው የመተሳሰብና የአብሮነት ስሜት ግን ቀላል አይደለም። ፊት ለፊት የማይተያዩና መነጋገር የማይፈልጉ ተቃዋሚዎች ያወጡትን ተመሳሳይ ቁጭት፤ እልህና ንዴት የተንጸባረቀበትን መግለጫ ስታየው ህወሃቶች እራሳቸው ምነው በቀረብን ሳይሉ የሚቀሩ አይመስለኝም። አንዳርጋቸውን መያዛቸው በርግጥም “አሳ ጎርጓሪ..” ሆኖባቸዋል በሚለው ሃሳብ እስማማለሁ።
አሻራ፦ አሁን ደግሞ በቅርቡ ለእይታ ወዳቀረብከው “ተላላኪው ማነው?” ወደሚለው የምስል ዘገባ ልመልስህ፦ ይህን ስራ ለማቅረብ ምክንያት የሆነህ ወይም መነሻ ሃሳቡን ያጫረብህ ጉዳይ ምንድነው?
ታማኝ፦ እእ …! ሁሌም በአይምሮዬ የሚመላለሱ ጥያቄዎች አሉ፦ የህወሃት መሪዎች ከሟቹ ጠ/ሚንስትራቸው ጀምሮ “እነዚህ የሻቢያ ተላላኪዎች” የሚሉት ነገር አለ። እናም ሁሌ እነኝህ ሰዎች እውነት ሰው አያውቅብንም ብለው ያስባሉ? እያልኩ እራሴን እጠይቃለሁ። አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር “እነኚህ የሻቢያ ….” ሲሉ እየቀለዱ ነው? እላለሁ።
አሁን ደግሞ አንዳርጋቸውን ከያዙ በኋላ ይህንኑ አባባላቸውን ደጋግመው ሲጠቀሙበት …. አልበዛም? የሚል ስሜትና የነሱ መሬት የለቀቀ ውሸት ነው ለሥራው ያነሳሳኝ።
አሻራ፦ አቶ አንዳርጋቸውን ለሁለተኛ ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮ ያቀረቧቸው “ተላላኪው ማነው?” የሚለው የታማኝ የምስል-ዘገባ በኢሳት እንደሚቀርብ ከማስታወቂያው በማወቃቸው ሳይቀደሙ ለመቅደም አስበው ነው ሲሉ ብዙዎች አስተያየት ሰንዝረዋል። በተለይ ያቀረቡት የፊልም ዘገባ የሚጀምረው “የሻቢያ ተላላኪዎች” በሚሉ ቃላት መሆኑ የአስተያየቱን ትክክለኝነት ያጎላዋል ይላሉ…በዚህ መልክ ታይቶሃል?
ታማኝ፦ እንዳልከው የተሰነዘሩ አስተያየቶችን ሰምቻለሁ። ምንድነው ከባዱ ነገር መሰለህ ? የኔ ስራ ከመውጣቱ በፊት ለመቅደም ሲሉ አዘጋጁት ብል የኔ ከፍታ ሊጨምር ነው፤ መንጠራራት ሊሆንብኝ ነው። ከኔጋ እየተከራከሩ ነው ማለት በጣም በጣም ይከብዳል። ከተለያዩ ሰዎች የተሰነዘሩ አስተያየቶችን ስትመለከት፤ የቪዲዮው ያለ ጥንቃቄ ተከታትፎ (በአግባቡ ኤዲት ሳይደረግ) በችኮላ መቅረብ፤ የተጠቀሙበት ቃልና ከኔ ሥራ ጋር በአንድ ቀን መልቀቃቸው እነኚህን ነገሮች እንድታስብ ያደርግሃል። ጥድፊያቸው ደግሞ ከአንዳርጋቸው ቃል ጀርባ ያለውን የጣር ድምጽ እንድንሰማ እስከማድረግ ያደረሳቸው ነው። ይህን ይህን ደማምረህ ስታይ አንተ ከምትለው ጋር ይቀራረባል ። እኔ ግን ለኔ መልስ ሰጡ ብዬ ማለት ይከብደኛል።
አሻራ፦ እንደ መንግስት አስበሃቸው ይሆን ለኔ መልስ እየሰጡኝ ነው ማለት ይከብደኛል ያልከው?
ታማኝ፦ በጭራሽ!! እንደ መንግስት ቢያስቡና እኔም እንደ መንግስት ባስባቸውማ በወደድኩ ነበር። ዋናው ችግር እንደ መንግስት አለማሰባቸው ፤ እንደ መንግስት አለመስራታቸው አይደል እንዴ?እንዴት አድርጌ ነው እንደ መንግስት የማስባቸው? እኔ ይህን የምለው ሕዝብን ከማክበር ነው። በግለሰብ ደረጃ የሰጠሁት አስተያየት ወይም ያቀረብኩት ስራ ሊታይ የሚገባው በዛው ደረጃ መሆኑን ስለማምንበትና ከዛ በራቀ እንዳይታይብኝ ነው።
አሻራ፦ በቅርቡ በጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና አወያይነት አንተ፤ አቶ ኤርሚያስ ለገሰና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ወንድማገኝ ጋሹ በኢሳት ቀርባችሁ ባደረጋችሁት ውይይት ብዙዎችን ያስገረመ ነገር አስደምጠሃል። ያስደመጥከው ነገር፦ ጥቂት የወያኔ ባለስልጣናት በተገኙበት ውይይት ላይ አቶ በረከትና አቶ አዲሱ የተናገሩትን ነው። ይህ ውይይት በኢሳት መደመጡ ተቃዋሚው ወያኔ ጉያ ውስጥ ለመግባቱ አመላካች ሆኗል የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ትግሉ የደረሰበትን ደረጃም ያሳያል የሚሉም አሉ፡፡ እንደ ጥያቄ ማንሳት የምሻው ይህን አይነት ጥብቅ ሚስጥር ኢሳት እጅ ሊገባ መቻሉ የተቃዋሚው የመረጃ ክፍል ጥንካሬ ወይስ ወያኔ ውስጡ ከመቦርቦሩ ጋር በተገናኘ እየሆነ ያለ …?
ታማኝ፦ ህዝቡ እኮ ታፍኖ የመጨረሻ ግፍ እየተቀበለ ነው ያለው። ደርግ ክፉ ነገሮችን ሁሉ ጨርሶ አድርጓቸው ሄዷል፤ ከደርግ በላይ ማንም ምንም አይነት ግፍ ሊፈጽም አይችልም የሚል እምነት ነበርን፡፡ እነዚህ ግን እኮ ሁሌም የሚሰሩት ግፍና ክፋት እያስደነቀን ነው።
ክፋታቸውን ቢያሳይ አንድ ምሳሌ ልንገርህ፦ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ፍርድ ቤት ቀርበው በነበረበት ጊዜ፤ በርሃብ ምክንያት መናገር እንኳ አቅቷቸው፤ ለዳኛው ምግብ በልተን አናውቅም ብለው ሲናገሩ፤ ዳኛው ደንግጦ ምግብ አምጡላቸው ብሎ ፍርድ ቤት ውስጥ እኮ ምግብ ተበላ! እነኚህ ሰዎች እኮ ያሰሩትን ሰው በርሃብ የሚቀጡ ናቸው ! እረ ስንቱን…… ዘርዝሬ እችለዋለሁ?
የህዝብን ስሜት በጥቂቱም ሊያሳይ ከቻለ አንድ ነገር ልንገርህ፦ በቅርቡ ለኢሳት አራተኛ አመት ወደ ጀርመን ሄጄ ነበር፡፡ በዝግጅቱ ላይ አንድ ሰው እጁን አውጥቶ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ሄጄ ነበር፡፡ በክፍለ ሃገር ቤተሰቤ በሚገኝበት አካባቢ ለሚኖሩ አንድ አዛውንት ለቡና መግዣ ብዬ 50 ዩሮ ሰጠኋቸው። ተቀብለው ካመሰገኑኝ በኋላ፤ ሰማህ ወይ ልጄ ከዚህች 50 ብር ላይ ዘርዝርና 10 ብሩን ለዛ ለታማኝ በእጁ ስጥልኝ፤ ለኢሳት ገቢ እንዲያረግልኝ ብለው ሰጥተውኛል።” ነበር ያለው፡፡ ተመልከት በዚህ አይነት የኑሮ ደረጃ ያሉ ኢትዮጵያዊ እንኳ ከተሰጣቸው 50 ዩሮ 10 ለኢሳት ይሰጥልኝ አሉ።ይሄ እኮ ሌላ ምንም ማለት አይደለም። ህዝቡ ምን ያህል ነጻነት እንደናፈቀ የሚያሳይ ነው። የሰውን ፍላጎት ነው የምነግርህ፡፡
በመረጃ በኩልም ህዝቡ ለትግሉ የሚጠቅም መረጃ ለመላክ በሚገርም መልኩ ፍቃዱና ፍላጎቱ አለው። ባገኘው ቀዳዳ ሁሉ ሳይፈራና መስዋዕትነት ከፍሎም ቢሆን መረጃዎችን ለመላክ ይፈልጋል።
ኢሳት አሁን አብዛኛውን መረጃ የሚያገኘው ከህዝብ ነው። እኔ በግለሰብ ደረጃ ነው መረጃዎቹ የሚደርሱኝ፡፡ አንድ ጠንካራ ድርጅት ተፈጥሮ በዚህ ረገድ ስራ ቢሰራ ደግሞ ምን ያህል እንደሚተባበር መገመት ከባድ አይሆንም።
አሻራ፦ ወደ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ልመልስህ፦ አቶ አንዳርጋቸው ላይ አፈናው በተፈጸመበት ሰሞን በለንደን በተደረገ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተህ በነበረበት ወቅት አቶ አንዳርጋቸው የአንበሳ ምስል በልዩ ሽልማት መልክ ሲሰጡህ ከሚያሳይ ክሊፕ ጋርአዳብለህ “ አንዳርጋቸው አንበሳውን መልሰህ ተቀበለኝ፤ ለኔ አይገባኝም!” የሚል መልዕክት አስተላልፈሃል። ይህን ያዩ ሰዎች ለአንድ ሃገር አንድ አንበሳ ብቻ ነው የሚያስፈልጋት እስካልተባለ ድረስ ታማኝም አንዳርጋቸውም ለሃገራችን አንበሶች ናቸውና ታማኝ ለምን ያንን አደረገ? ሲሉ ይጠይቃሉ። በርግጥ ለአቶ አንዳርጋቸው ያለህን ክብር ለመግለጽ የተጠቀምክበትን አገላለጽ ብዙዎች ወደውታል ። እስቲ ይህን ልትል ያስቻለህን …. ግለጽልን፡፡
ታማኝ፦ ያንን ያልኩት በስሜታዊነት ወይም በግብታዊነት አይደለም። ከልቤ የተሰማኝንና የሚሰማኝን ነው የተናገርኩት። አንዳርጋቸው አንበሳውን ለኔ ሲሸልም ስለኔ የተናገረው ራሱ በጊዜውም ከብዶኛል። እኔ ቀደም ሲል እንደ ገለጽኩልህ ራሴን የማየው እንደ አንድ ለህዝብ ነጻነትና ለሃገሩ ሰላም ፤ ….የሚናፍቅ ዜጋ ነው። አንዳርጋቸው በዚህ እድሜው ለህዝቡና ለሃገሩ ሲል የወሰደው እርምጃ በጣም ያስደንቀኛል። ሊከፍል የተዘጋጀው መስዋእትነት ሳያንስ እንደገና አፈናው ሲፈጸምበት ልንላቸው ይገባል፡፡
እነሱ (ገዢው ፓርቲ) በፍርሃት ዓለም ውስጥ ስለሆኑ ሁሉንም ነገር ለመቆጣጠር ነው ሩጫቸው፡፡ ወደፊት መቼም ቻይና የማትሰራው ነገር የለምና አገር ስትገባ ኤርፖርት ላይ ለመንግስት ክፉ -ልብ ያለውን ስካን የሚያደርግ መሳሪያ ሁሉ ሊያሰሩ ይችላሉ ….(ሳቅ)። ምርጫውንም ቢሆን ከዚህ በተለየ አይደለም የማየው። ፍርሃት ውስጥ ያለ አካል እውር ድንብሩን ብዙ ነገር ሊያደርግ ይችላል።
አሻራ፦ አንዳንድ ሰዎች ታማኝ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝን የራራላቸው ይመስላል። አቶ መለስን የተነፈሷትን ቃል ተከትሎ ወዲህ ወዲያ ያደርጋቸው እንዳልነበር ለአቶ ሃይለማሪያም ምነው ዝም አለ ይላሉ?
ታማኝ፦ ሳቅ…………! ይህን የሚሉ ሰዎች እውነት ከልባቸው እኔ በአቶ ኃይለማሪያም ላይ ግዜ እንዳጠፋ ፈልገው ነው? አይመስለኝም፡፡ አቶ መለስ እኮ የራሳቸው ተረት ፤የራሳቸው ስድብ ፤የራሳቸው፤ ውሸት የራሳቸው ምናምን…የነበራችው ሰው ነበሩ። አቶ ኃይለማሪያም ደግሞ ሳይዛቸው አልሆን ብሎ እንጂ የአቶ መለስን ልብስ ሊለብሱ የሚፈልጉ ነው የሚመስለኝ።
የአገር መሪዎች ከስራ ውጭ መጽሄት ማገለባበጥ፤ የአለም ዜና መከታተል …. እንዲህ እንዲህ አይነት ነገር እደሚያደርጉ ነው የማስበው፡፡ አቶ ኃይለማሪያም ግን ሌሊት ሁሉ ቁጭ ብለው የአቶ መለስን ቪዲዮ የሚያዩ ነው የሚመስለኝ፡፡ “ እስኪ የ 94ቱን አምጪልኝ የ93ቱን ጨርሻለሁ እያሉ…” እና በእኝህ ሰው ላይ ነው ግዜ እንዳጠፋ የሚፈለገው? ለሳቸው የሚሆን ግዜ እንኳ የለኝም፡፡ በቁምነገር ልወስዳቸው አለመፈለጌ እንጂ አቶ ኃይለማሪያም እንዴት ያለ ኮሜዲ ሊሰራባቸው የሚችሉ መሰሉህ?
አንተ ኮ! ስትኮርጅ የሰውን ሃሳብ፤ ወይም ሻል ያለ ነገር ትኮርጃለህ ። ማዛጋት ትኮርጃለህ?…..(ሳቅ) እሳቸው እኮ የአቶ መለስን ማዛጋት ሁሉ እየኮረጁ ነው! (ሳቅ)……! እኔ እንደ መዝናኛና ኮሜዲ ሾው ነው የማያቸው። ከዚህ ባለፈ አላያቸውም። አይ የግድ ይሰራባቸው ከተባለም ለቁምነገር ሳይሆን ለትርፍ ግዜ መዝናኛ ሊሰራባቸው ይችላል፡፡ከዚያ ውጭ ግን በሳቸው ላይ ግዜ ማጥፋት ያለብኝም ያለብንም አይመስለኝም።
ደግሞ ምን መሰለህ..? እኔ ጠ/ሚ/ር ስትለኝ የሚመጣብኝ ምስል እንደ አክሊሉ ሃብተወልድ አይነት ሰው ነው፡፡ ….እና በዚህ ስም ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሲጠራበት ……(ፋታ) ልክ አይሆንም፡፡
አሻራ፦ የወያኔን ከፍተኛ ባለስልጣናት በስልክም ቢሆን ለማግኘት ሞክረህ አታውቅም? ሞክረህ ከሆነ ውጤቱ ምን ነበር?
ታማኝ፦ እምምም.. አዎ! አንድ ሶስት ግዜ ሞክርያለሁ፡፡ አንዴ የቤንሻንጉል መፈናቀል ጊዜ …ሌላው ደግሞ አርሲ ውስጥ ሙስሊሞች የተገደሉ ጊዜ ይመስለኛል…አንዱን ዘነጋሁት። ብቻ ለ3 ጊዜ ያህል አቶ በረከት ጋ ደውዬ ነበር።መጀመሪያ የደወልኩ ጊዜ አነሳ፤ ጤና ይስጥልኝ ከአሜሪካ ነው የምደውለው አልኩት። “ማን ልበል? ” አለኝ። አይ እኔ የመንግስትዎ ተቃዋሚ ነኝ፤ ነገር ግን አሁን እየሆነ ባለው ጉዳይ መረጃ ይሰጡኝ እንደሁ ብዬ ነው የደወልኩት አልኩት።
እሱም “ማንነትክን ካልገለጽክልኝ ምንም መረጃ መስጠትም ሆነ ማውራት አልችልም” አለኝ።
መልሼም፦ማንነቴን ከነገርኩዎት አያናግሩኝም አልኩት። “ግዴለህም አናግርሃለሁ!” አለኝ።
ታማኝ በየነ ብዬ ሳልጨርስ ስልኩ ላዬ ላይ ተዘጋ፡፡በሌላም ጊዜ የሆነው እንዲሁ ነው፡፡ ታማኝ በየነ ነኝ ስለው ስልኬን ይዘጋዋል።
አሻራ፦ ለማነጋገር ፈቃደኛ ቢሆን ኖሮ በምን አይነት ስሜት ነበር የምታናግረው? ምንስ ነበር የምታናግረው?
ታማኝ፦ ለነገሩ በተለይ በመጀመሪያ የደወልኩለት ጊዜ አልተዘጋጀሁም ነበር፡፡ አሁን ስልኩን ሲያነሳ እንዴት ብዬ ነው የማናግረው? ንዴትም ቁጣም ፤ እልህም ይኖራል እና እንዴት እንደማናግረው አላውቅም ነበር፡፡ ሰዎችም አብረውኝ ነበሩ። ለማንኛውም የምለውን ሳልል እሱም ስልኩን ዘጋው። ሁለተኛ ስደውል ግን አስቤበት ነበር፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው ስልኩ ይነሳና ራሴን ሳስተዋውቅ ይዘጋል።
አሻራ፦ ምን ትለው ነበር ?
ታማኝ፦ሁሌ ራሴን የምጠይቀውን ነገር ነበር ልጠይቀው የፈለኩት። እንደው መጨረሻችሁ ምንድነው? እውነት እናንተ ሰዎች የምታደርጉትን ነገር ሁሉ የምታደርጉት የምር!! ለሃገርና ለህዝብ ጥሩ እየሰራን ነው ብላችሁ አምናችሁበት ነው? ልጆቻችሁን ትወዳላችሁ? ልጆቻችሁ ከሌሎች ልጆች ጋር በፍቅር እዲኖሩ አስባችሁ ታውቃላችሁ? ብዬ ጠይቄ ከራሳቸው አንደበት ብሰማው ፈልጌ ነበር አልሆነም ዘጋብኝ፡፡
አሻራ፦ ወደ ወቅቱ ጉዳይ ልመልስህ፦ የአቶ አንዳርጋቸው መያዝ ኢትዮጵያዊውን ሁሉ አስቆጥቷል፡፡ በወያኔ መንግስት ላይ ያለው ተቃውሞና ለለውጥ ያለው ተነሳሽነት ከመቼው ጊዜ በተለየ ጠንክሯል። ይህን ተነሳሽነት ወደ ውጤት ለመለወጥ ምን መደረግ አለበት ትላለህ?
ታማኝ፡- አንድ ነገር አለ! በአሁኑ ሰአት በሃገራችን እየሆነ ያለው ነገር በጣም የሚያስፈራ ነው፡፡ እኛ የምንቃወማቸው ስለምንጠላቸው አይደለም፡፡ የምንቃወማቸው እያደረጉ ያሉት ነገር በጣም የሚያስፈራ፤ ሃገራችን እንደ ሃገር ህልውና እንዳይኖራት፤ ህዝባችንም አብሮ መኖር እንዳይችል የሚያደርጉ ሥራዎችን እየሰሩ በመሆኑ ነው። በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተደጋጋሚ የዘር ቅራኔዎችን እያየን ነው። እገሌ ከዚህ ክልል እገሌ ከዚህ ክልል ውጣ እየተባለ ህዝብና ህዝብ እየተቂያቂያመ እንዲሄድ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በጣም ያስፈራል፡፡
የህክምና ባለሙያ ባልሆንም አንድ ዶክተር ወደ ካንሰር ሊለወጥ የሚችል በጣም ከባድ የጤና ችግር ያለበትን በሽተኛ ፡ በአግባቡ መርምሮ ዘለቄታዊ መፍትሄ ይፈልግለታል እንጂ ህመም አስታጋሽ (ፔይን ኪለር) የሚሰጠው አይመስለኝም፡፡ የሃገራችን ወቅታዊ ጉዳይም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። ዛሬ አንድ ዘላቂ መፍትሄ ነገር ካላደረግን ችግሩ ሊድን ወደማይችል ካንሰርነት መለወጡ አይቀርም።
ኢትዮጵያን ሃገሬ የምንላት ሁሉ አትሌቶቻችን ባንዲራዋን ለብሰው ትራክ ላይ ሲያሟሙቁ፤ ማን በ10 ሺህ ተሰለፈ ? ማን ለወርቅ ተስፋ አለው? …. እያልን እንጨነቃለን ። በውጤቱም እንደሰታለን። አሁን ደግሞ አትሌቶቿ ወርቅ ሲያስገኙላት የምንቦርቅላት ሃገር እንደ ሃገር መቀጠሏ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። ይህ ደግሞ በኛና በኛ ትከሻ ላይ ብቻ ያረፈ ችግር ነው። ስለሆነም ከዚህ በፊት በተቃዋሚነት ሲንቀሳቀስ የቆየውም ሆነ ያልተንቀሳቀሰው ዜጋ፤ ብቻ ሁሉም ሁሉም ባመነበትና ታግሎ ያታግለኛል ባለው በአንዱ መስመር ገብቶ መታገል አለበት እላለሁ፡፡ ዛሬ አንዱ ተመልካች አንዱ ሯጭ የሚሆንበት ጊዜ አይደለም። ማንም ለምንም ጥሪ የሚያደርግበት ጊዜም አይደለም። ዛሬ አንድ ነገር ካላደረግን ለልጆቻችን የምናስተላልፈው “ነገ” የለም፡፡በዚህ ደረጃ ነው መታየት ያለበት የሚመስለኝ።
አሻራ፦ በተነሳንበት እንቋጭና አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለህዝብ ነጻነት በጽናት ሲታገሉ ጠላት እጅ ወድቀዋል ፤ ህዝብስ ለሳቸውም ሆነ ለሃገር ነጻነት በመታገል ረገድ ምን ይጠበቅበታል ትላለህ?
ታማኝ፡- አንዳርጋቸው በወያኔ እጅ እስከወደቀበት ጊዜ ድረስ የራሱንና የቤተሰቡን ህይወት ሰውቶ፤ በርሃ ገብቶ የቻለውን ሁሉ አድርጓል። የአንዳርጋቸው የትግል ጉዞ እዛ ጋ አብቅቷል። ዓለም ላይ ያሉ ሰውን የማስቃያ ቴክኒኮችን ሁሉ በእጁ ያስገባው የወያኔ መንግስት ደህንነት ባለፉት ሁለት ወራት አንዳርጋቸው ላይ ምን ሲፈጽምበት እንደቆየ ለመገመት የካፒቴን ተሾመ ተንኮሉን ቃለ ምልልስ ማድመጡ በቂ ይመስለኛል፡፡ አንዳርጋቸው ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል። እየከፈለም ነው።
የወያኔ መንግስትን ባህሪ መለስ ብለን ብናይ ሕዝብ የሚያከ ብራቸውን ሰዎች አዋርዶና አቅልሎ ለማሳየት የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ እንረዳለን፡፡
በአቶ አንዳርጋቸው መታፈን የተቆጣውን ህዝብ ተስፋ ለማስቆረጥ በተለመደው መልክ አቶ አንዳርጋቸውን አስገድደው በማናገር ሌላ የፊልም ቅንብር ለመስራት ተፍ! ተፍ! እያሉ እንደሆነ መረጃ ደርሶናል። ዋናው ቁምነገር ግን ህዝባችን ለዚህ መሰሉ የወያኔ ተደጋጋሚና አሰልቺ ህዝብን የማሳሳት፤ ጉምቱ የህዝብ ወኪሎችን የማዋረድ ሴራ አዲስ ስላልሆነ ምንም ይበሉ ምንም ይስሩ ፕሮፓጋንዳው ውጤት እንደማይኖረው አልጠራጠርም፡፡
ዋናው ቁም ነገር የነሱን ፕሮፓጋንዳ ማክሸፍ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት ስንታገልለት የቆየነው ዘረኛውን መንግስት ከሕዝብ ጭንቃ ላይ የማውረድ ዓላማ በውጤት እንዲቋጭ ሁላችንም አንድ ሆነን መነሳት ነው!!!።
አሻራ፡ ስለ ጊዜህ በድጋሚ እናመስግናለን! ታማኝ፡ እኔም ስለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ::
በአውስትራሊያ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለማስታወስ ከታተመችው አሻራ መጽሄት የተወሰደ::