(ፍኖተ ነፃነት) በምዕራብ ሁመራ ማይካራ መቻች በተከሰተ የብሔር ግጭት የሰዎች ህይወት ጠፋ፤ መንግስት ግጭቱን ለማስቆም የወሰደው እርምጃ አለመኖሩ በአካባቢው ተከታታይ ግጭቶች ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩን የአካባቢው ምንጮች ለፍኖተ ነፃነት አስታወቁ፡፡
ሱዳን ጠረፍ ላይ ቅዳሜ ግንቦት24 ቀን 2005 ዓ.ም በብሄር ምክንያት የተቀሰቀሰው ይኸው ግጭት በሁለት ቀናት ውስጥ የ12 ሰዎችን ህይወት መቅጠፉንፉን የፍኖተ ነጻነት ምንጮች ጨምረው ገለፀዋል፡፡ በኢትዮጵያና ሱዳን ጠረፍ አካባቢ በምትገኘው መቻች በረሃ በቀን ራያ የተሰማሩ ሰዎች በብሄር እየተቧደኑ መገዳደል ከጀመሩ ሶስት አመታት ማስቆጠራቸውን ያስታወሱት ምንጮቻችን መንግስት ችግሩን መፍታት ምንም አይነት ሚና ለመጫወት አለመፍቀዱ የሟቾቹንና የተጎጂዎቹን ቁጥር እንዲያሻቅብ አድርጓል፡፡
ሰራተኞቹ በወሎ፣በጎጃም፣በጎንደርና በራያ ተወላጅነት ተቧድነው በካራ፣በዱላና በእሳት በፈጠሩት ግጭት የሰው ህይወት ተቀጥፏል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አካባቢውን ጠሚያውቁ አስተያየት ሰጪዎች “መንግስት በኢትዮጵያ የብሄር ጥያቄ ተመልሷል በማለት የብሄር ብሄረሰቦችን በዓል በሚያከብርበት ወቅት በጎሳ ፖለቲካ እንዲህ አይነት ዘግኛኝ ድርጊቶች እየተፈጠሩ የሰው ህይወት መብላታቸው ጥያቄዎቹ በተገቢው መንገድ ላለመመለሳቸው ማሳያ ይሆናል” ብለዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በዚሁ በሁመራ በረከት ወረዳ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ለመዝረፍ የሚሞክሩ ሽምቅ ተዋጊዎች በተለያዩ ጊዜያት ድንገተኛ ወረራ በማድረግ የአካባቢውን ነዋሪዎች ሲያስጨንቁ እንደነበር የጠቀሱት ምንጮቻችን በቅርቡ ታጣቂዎቹ አካባቢውን ከሚጠብቁ ሚልሺያዎች ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ በሁለቱም ወገን ህይወት መጥፋቱን አጋልጠዋል፡፡ በተደጋሚ የማያባራ የተኩስ ልውውጥ መስማት በአካባቢው የተለመደ እንደሆነም የፍኖተ ነፃነት ምንጮች ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በሁመራ ስለተከሰተው የግጭት ለማጣራት የአካባቢውን ባለስልጣናትና የፖሊስ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡