(ዘ-ሐበሻ) በሆላንድ አምስተርዳም በተደረገው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ቤተልሄም ሞገስ ድል ቀናት።
በዚሁ ተመሳሳይ ዓመት በዱባይ ማራቶን ድል ቀንቷት የነበረችው አትሌት ቤተልሄም ሞገስ የአምስተርዳሙን ማራቶን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 2:28:35 ሲሆን ኬንያዊቷን አትሌት ኦልጋ ኪማዮን አስከትላ ገብታለች ያሉት የዘ-ሐበሻ የአምስተርዳም ዘጋቢዎች ቤተልሄም ኦልጋን በ40 ሰከንዶች ቀድማ የገባች ሲሆን ያስመዘግበችው ውጤትም በአመርቂነቱ ተመዝግቧል ብለዋል።
ወጣቷ አትሌት ቤተልሄም 2:28:35 ከሮጠች በኋላ አንዳችም የድካም ስሜት ያልታየባት ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ ወደፊት ኦሎምፒክን ጨምሮ በዓለም ዋንጫና በሌሎች መድኮች ለሚጠብቃት የማራቶን ውድድሮች ትልቅ ተስፋን ጥሏል።
ቤተልሄም እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሜይ 3 ቀን 1991 ነው የተወለደችው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ34ኛው የቤንጂንግ ኢንተርናሽናል ማራቶን ላይ የተካፈለው ኢትዮጵያዊው አትሌት ግርማይ ብርሃኑ ገብሩ በአሸናፊነት አጠናቀቀ።
ከ55 ሃገራት በላይ የመጡ አትሌቶችና 30 ሺህ የሚጠጉ ራጮች በተካፈሉበት በዚሁ የማራቶን ውድድር ግርማይ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ42 ሰከንድ ነው።