(ከአዘጋጁ፡ ወ/ሮ አልጋነሽ በርሔ መገደላቸው የተሰማው ዴሴምበር 2 ቀን 2006 ዓ.ም ነው። የወ/ሮዋ ሞት 8 ዓመት ሊሞላው የቀሩት ጥቂት ጊዜያት ነው፤ እስካሁንም አሟሟቷ አነጋጋሪ ከመሆኑ አንጻር ሌሎም እንዲማሩበት፣ ልክ እንደመታሰቢያም በማሰብ ኢሳያስ ከበደ ታሪኩን አቀነባብሮ አቅርቦታል።)
‹‹…አሜሪካን በአስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ላይ ነው በኮሎምቦስ የተገኘችው፡፡ በወቅቱ የሚኖሩት ቀይ ህንዶች ቢሆኑም ዛሬ ግን ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ሰዎች ኃይል አድርገዋታል፡፡
‹‹መጀመሪያ ኮሎምቦስ ያገኘው ኩባንና በዛሬዋ አሜሪካን ዙሪያ ያሉትን ደሴቶች ነበር፡፡ ከአራት ዓመት በኋላ ግን ቩስፑሲ የተባለ ጣልያናዊ በ1496 ዋናዋን አሜሪካንን አገኘ፡፡ ወደ አውሮፓም ተመልሶ አዲስ ዓለም አገኘሁ ሲል ተናገረ፡፡ የእሱን እግር ተከትለው እንግሊዞች ወደ ቦታው ደርሰው እስከ 1776 ዓ.ም ድረስ አሜሪካንን ቅኝ ገዟት፡፡
‹‹የዛሬዋ ኃያል ሀገር ከሁለት ክፍለ ዘመን ባለፈ በእንግሊዝ ተገዝታለች፡፡ በ1776 ዓ.ም ነፃ ስትወጣ ጆርጅ ዋሽንግተን የተባለ ሰው የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት ሆነ፡፡ ዛሬ የሀገሪቱ ዜጎች ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ዜጎች ናቸው፡፡ በአያቱና በቅድመ አያቱ አውሮፓዊና አፍሪካዊ ያልሆነ የለም፡፡ ሆኖም ሁሉም አሜሪካውያን ናቸው፡፡ በአንድ መንፈስ ለሀገራቸው ዕድገት በመጣራቸው አሁን ካሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ እንዲሁም ትላንት ከገዛቻቸው ሀገር፣ ከእንግሊዝም በላይ ለመሆን በቅተዋል፡፡
(ከሰላዮች ትንቅንቅ የተወሰደ)
አሜሪካ ለብዙዎች የምትናፈቅ ሀገር ናት፡፡ ‹‹የማያውቁት አገር አይናፍቅም›› የሚለው የሀገራችን ተረት ለሀገረ አሜሪካን አይሰራም፡፡ ምክንያቱም የማያውቁት ሁሉ ይናፍቋታል፡፡ በተለይ በታዳጊ ሀገር ለሚገኙ ሰዎች የምድር ገነት መስላ ነው የምትታየው፡፡ እና ሁሉም አመቺ ባለው መንገድ አሜሪካን ሄዶ መኖርን ይመርጣል፡፡ በየዓመቱ እድሉን ለመሞከር ዲቪ የሚሞላው ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ወደ አሜሪካን ለመሄድ ከሚመኙት ጥቂቶቹ ተሳክቶላቸዋል፣ ያሰቡት ሞልቶላቸዋል፡፡ እንዳለሟት የምድር ገነት ሆና ያልጠበቀቻቸውም አሉ፡፡ ከሀገር፣ ከወገን ርቆ መኖሩ እንደ መርግ ቢከብድም የግል ጥረታቸው የስደትን ኑሮ ውጣ ውረድ ተጋፍጠው ራሳቸውን የቻሉ፣ ከራሳቸውም አልፈው እዚህ ሀገር ቤት ላሉ ወገኖቻቸው መትረፍ የቻሉም አሉ፡፡ የተሻለ እውቀት የገበዩም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡
በተቃራኒው የስደት ህይወት ያልተመቻቸው፣ ያሰቡት ቀርቶ ያላለሙት የገጠማቸውም አሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣች ሁለት መቶ ሰላሳ አንድ ዓመታትን ያስቆጠረችው የዓለማችን ሃያሏ ሀገር አሜሪካን ዛሬም የብዙዎች ምኞት የሆነችና የምድር ገነት መስላ የምትታይ ሀገር ናት፡፡
አሜሪካን ሀገር የስደትን ኑሮ ተጋፍጠው የህይወትን ፈተና በአሸናፊነት ለመወጣት ከቻሉ ጠንካራ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዷ አልጋነሽ በርሄ መሸሻ ነበረች፡፡ አምስት የእሷን ድጋፍ የሚሹ ልጆችን ይዛ በሰው ሀገር ሰው ለመሆን የበቃች፣ ከራሷም አልፎ የስደት ህይወት ለጨለመባቸው የሀገሯ ልጆች መከታና አለኝታ ለመሆንም የቻለች ነበረች፡፡ በአሜሪካን ዴንቨር ኮሎራዶ ነዋሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ በሙሉ አልጋነሽን ያውቃታል፡፡ በግፍ እስከተገደለችበት ቀን ድረስም የብዙዎች አለኝታ ነበረች፡፡ በሰው ሀገር፣ በስደት ህይወት የራሷን ድርጅት ለመክፈትም በቅታለች፡፡ የአምስት ልጆችን የነገ ህይወት የተሻለ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች፡፡
በግፍ መገደሏ ልጆቿን ብቻ ሳይሆን የሚያውቋትን በሙሉ ያሳዝን ነበር፡፡ ደግነቷ ሁሉንም አስለቅሷል፡፡ በግፍ መገደሏም የሁሉን አንጀት አላውሷል፡፡ ‹‹አልጋነሽ የብዙዎች እናት ነበረች›› ይላሉ በቅርብ የሚያውቋት በሙሉ፡፡ ኑሮዋን ለማሸነፍ፣ የእሷን እርዳታ ለሚሹትም ለመትረፍ ደፋ ቀና ስትል ነበር ይገድለኛል ብላ በማታስበው ግን በምትረዳው ሰው እጅ በ36 ዓመቷ በሞት የተቀጨችው፡፡
ከአባቷ ከአቶ በርሄ መሸሻና ከእናቷ ከወ/ሮ ዘርትሁን ገሰሰ በትግራይ አክሱም ከተማ ግንቦት 21 ቀን 1962 ዓ.ም ነበር አልጋነሽ የተወለደችው፡፡ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ከተከታተለች በኋላ በትውልድ ከተማዋ በአክሱምና በመቀሌ ፍርድ ቤት በፀሐፊነት አገልግላለች፡፡ በዕድገት ወደ አዲስ አበባ የመጣችው በ1980 ዓ.ም ነበር፡፡
እዚህ አዲስ አበባ ተዘዋውራ በምትሰራበት ወቅት ከሰዎች ጋር በነበራት መልካም ቅርርብ ዛሬ ድረስ የሚያስታውሷት በርካቶች ናቸው፡፡ ደግ ነበረች፡፡ ያላትን በሙሉ እስኪያልቅ ድረስ ለተቸገረ ሰው የምትሰጥም ነበረች፡፡ አንዴ ከቢሮዋ ስትወጣ ከፍርድ ቤት በራፍ የተሰባሰቡ ሰዎች ታያለች፡፡ እነዛ ሰዎችንም ችሎት ክርክር ላይ አይታቸው ነበር፡፡ ሁኔታቸውን ስትመለከት አሳዝነዋታል፡፡ እያዘኑ መሄድ የእሷ ባህርይ አልነበረምና ለመርዳት ራቅ ካለ ስፍራ የመጡትን ሰዎች ቀርባ ታነጋግራቸዋለች፡፡ ወደ ቤታቸው ለመመለስ ለትራንስፖርት የሚከፍሉት ገንዘብ አልነበራቸውም፡፡ ይህንን ችግራቸውን ነገሯት፡፡ የሰው ችግር ሰምቶ ለማለፍ የሚችል የደነደነ አንጀት አልነበራትምና ከቦርሳዋ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ በሙሉ ትሰጣቸዋለች፡፡ ፊታቸው ላይ ያየችው ፈገግታ ለእሷ ከምንም በላይ ዋጋ ነበረው፡፡ ደግ ሰው የሌሎችን ደስታ ከማየት የበለጠ የሚያረካው ነገር የለም፡፡ እና በደስታቸው ተደስታ፣ በፈገግታቸው ረክታ ስታበቃ ከሰው አንድ በር ተበድራ ነበር ያን ዕለት ወደ ቤቷ የገባችው፡፡
ነሐሴ 1993 ዓ.ም 16 ዓመት የቆችበትን ስራ ለቃ ወደ አሜሪካን ተጓዘች፡፡ የሚወዷት፣ በደግነቷ የሚያደንቋት፣ በመልካም ሰውነቷ የሚያከብሯት፣ የስራ ባልደረቦቿ፣ ጓደኞቿ፣ ዳኞች፣ ጠበቆችና ዐቃቤ ህጎች እንዲሁም ወዳጅ ዘመዶቿ በሰው ሀገር መልካሙ ሁሉ ይገጥማት ዘንድ መልካም ተመኝተውላት ወደ አሜሪካን ተጓዘች፡፡
በስደት ህይወት ያጋጠማትን ፈተና በቆራጥነት ተወጣችው፡፡ ኑሮን አሸንፋ በድል ተወጣች፡፡ አምስት ልጆቿን የማሳደግ ኃላፊነቱን ለመወጣት ጠንክራ ሰርታ ራሷን ለመቻል በቃች፡፡ ቤተሰቦቿንም ወደ አሜሪካን ወሰደች፡፡ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዘመዶቿንም ትረዳለች፡፡
በስደት ዴንቨር የደረሱ ወገኖቿ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከሆነ የእርዳታ እጇ አይታጠፍም፡፡ በሰው ሀገር ያገኘቻቸውን ወገኖቿን በግል ድርጅቷም ሆነ በመስሪያ ቤቷ የምታስተናግድ፣ በዴንቨር ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የሚያውቋት፣ የሚያደንቋት ደግ ሰው ነበረች፡፡
አንድ ቀን በዴንቨር ጎዳና ላይ አንድ ሰው ታያለች፡፡ ቀርባ ስታናግረውም ግራ የገባው የሀገሯ ሰው እንደሆነ ትገምታለች፡፡ እናም አልፋው ለመሄድ አልፈለገችም፡፡ መልኩ የሚመስላትን፣ የሀገሯ፣ የወንዟ ልጅ እንደሆነ የገመተችውን ሰው ግራ እንደገባው እያየችው እንዴት ትለፍ? ለተቸገሩ የሚያዝነው አንጀቷ ተገለባበጠባት፡፡ የሀገሯ ልጅ በሰው ሀገር የሚሆነውን አጥቶ ሲጨነቅ ስታየው ሀዘኑ ውስጧን ረበሻት፡፡ እናም ጠጋ ብላ አነጋገረች- አቶ ሸሞንዴ ገ/ሥላሴን፡፡
ሸሞንዴ ዴንቨር ከገባ አጭር ቀኑ ነረብ፡፡ በእዚያ ሀገር የሚያውቀው ሰው አልነበረም፡፡ ከሚያያቸውና ጎዳናው ላይ ከሞሉት ነጮች መካከል ቀልቡ ለፈቀደው ችግሩን እንዳይናገር የቋንቋ ችግርም ነበረበት፡፡ እንዲህ ግራ ሲገባው ነበር አልጋነሽ የደረሰችለት፡፡ ደማቸውና የቆዳ ቀለማቸው አንድ፣ የሚግባቡበትም ቋንቋ ተመሳሳይ፣ የአንድ ወንዝ ልጆች፣ እናም ሸሞንዴ ደስ አለው፡፡ የቸገረውን መርዳት፣ የተከፋውንና ያዘነውን ማፅናናት፣ የጎደለበትን መሙላት ባህርይዋ የሆነው አልጋነሽ አቶ ሸሞንዴን ከወደቀበት የዴንቨር ጎዳና ላይ አነሳችው፡፡ ጨለማ መስሎ የታየው የስደት ህይወት ላይ ብርሃን ፈነጠቀችለት፡፡ የእርዳታ እጇንም ዘረጋችለት፡፡ ውሎ ሲያድር ለሌሎች ባይተርፍም ለራሱ ግን የማያንስ ሰው እንዲሆን አደረገችው፡፡
እያደር መቀራረቡ ቀጠለ፡፡ ቢቀራረቡም መርዳቷን አላቋረጠችም ነበር፡፡ ለእሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ከመርዳት የሚታጠፍ እጅ አልበራትም፡፡ ለሰዎች መልካም የምትመኝ፣ ጥሩ የምታስብ፣ ሀይማኖቷን የምታከብር፣ የአምስት ልጆች ብቻ ሳይሆን የሌሎችም እናት ነበረች፡፡
(እ.ኤ.አ) ዲሴምበር 2/2006) ምሽት ላይ፡፡ ዴንቨር ጀምበር ጠልቃለች፡፡ የከተማይቱ እንቅስቃሴ ግን እንደዛው ነበር፡፡ ኑሮን ለማሸነፍ የሚጣደፈው ወደ ምሽት ስራው ይከንፋል፡፡ ሲደክም የሚውለው ደግሞ ጎኑን ለማሳረፍ ወደ ቤቱ ለመሄድ ይጣደፋል፡፡
አልጋነሽ የግል ድርጅቷን ዘጋች፡፡ የናፈቋትን አምስት ልጆቿን ለማየት፣ ጎኗንም ለማሳረፍ ወደ ቤቷ መድረስ ብቻ ነበር የምትፈልገው፡፡ ቀኗን በሰላም እንደዋለች ሁሉ ምሽቱም ሆነ ሌሊቱ የሰላም እንደሚሆንላት ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አልነበራትም፡፡ ለሰው ደግ ነበረችና ማን በክፉ ያስበኛል ብላ ትጠራጠር? ለሰው የምታዝን ነበረችና የትኛው ሰው ይጨክንብኛል ብላ ትገምት? የሁሉ እናት ማን ጨካኝ እጁን ይዘረጋብኛል ብላ ትጠራጠር?
የግል ድርጅቷ በር መዘጋቱን አረጋገጠች፡፡ ከራሷና ከቤተሰቧ አልፎ ሌሎችንም እንድትረዳ ያስቻላትን ድርጅቷን ትወደዋለች፡፡ ድርጅቱን ለማስፋፋትና የተሻለ ለመስራት፣ ውጥኗን ወደ ተግባር ለመለወጥ የመጨረሻ የመሰናዶዋ ወቅት ነበር ያ ጊዜ፡፡ የዴንቨር ከተማ ባለስልጣናት ፈቅደውላታል፡፡ የሰሞኑን ሀሳቧ ይህ ነበር፡፡ እቅዷን ወደ ተግባር ለመለወጥ ነበር ምኞቷ፡፡
የመኪናዋን በር ከፍታ ገባች፡፡ የመኪናውን ሞተር እንዳስነሳች አንድ ሰው ወደ እሷ ተጠጋ፡፡ ቀና ብላም አየችው፡፡ የምታውቀው ሰው ነበር፡፡ አቶ ሸሞንዴን ገ/ሥላሴ፡፡ በድንገት መምጣቱ ቢያስገርማትም ስለት ያለው ቢላ እስኪያወጣባት ድረስ ግን የመጣው ለክፉ ነው ብላ አልተጠራጠረችም፡፡
የሞባይል ካርድ፣ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችንና የኢትዮጵያ ዕቃዎችን ከምትሸጥበት የግል ሱቅ በራፍ ላይ በራሷ መኪና ውስጥ፣ እየረዳች ሰው ባደረገችው ሰው በቢላ አንገቷን ያረዳት ሸሞንዴ ደሟ ከውስጧ ተንጠፍጥፎ ነፍሷ ከስጋዋ እስክትለይ ድረስ አጠገቧ ነበር፡፡ የዴንቨር ፖሊስ የሟቿን አስክሬን በዕለተ ቅዳሜ ምሽት በህንፃ ቁጥር 1400 በIVY ስትሪት እንዳገኘው በምርመራ ውጤቱ ላይ አስፍሮታል፡፡
የወ/ሮ አልጋነሽ ሞት እንደተሰማ የማያውቋትን ሁሉ ነበር ያሳዘነው፡፡ የገዳይዋ በፖሊስ ያለመያዝ ደግሞ ሀዘኑን እጅግ በጣም ነበር ያባባሰው፡፡ ይሁን እንጂ የዴንቨር ፖሊስ ይህንን ወንጀል የፈፀመውን ሰው ደርሰንበታል፣ አቶ ሸሞንዴ ገ/ሥላሴ ይባላል፡፡ ይህ ሰው አንደኛ ተጠርጣሪ ሆኖ በፖሊስ እየተፈገለ ነው፡፡ ግለሰቡ አራት በር ያለውና የ1995 ዓ.ም ስሪት የሆነ ፓንቲያክ ግራንድ (pantiac Grand) የሰሌዳ ቁጥር 493 N.P.B የሆነ መኪና ያሽከረክር እንደነበር ገልፆ ያየው ሰው ለዴንቨር ፖሊስ እንዲጠቁም መግለጫ ያወጣል፡፡
በዴንቨር ያሉ ኢትዮጵያውን በመልካም ተግባሯ፤ በደግነቷ የሚያደንቋት፣ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቿ፣ በሰው ሀገር የምታሳድጋቸው ልጆቿና የምትረዳቸው ዘመዶቿ የተገኙበት ቀብሯ ተፈፀመ፡፡ ከቀብር መልስ የሁሉም መነጋገሪያ የነፍሰ ገዳዩ ጉዳይ ነበር፡፡ ለምን እንደገደላትም አልታወቀም፡፡ በተቻላት ትረዳው ነበር እንጂ በመሀከላቸው ለግድያ የሚያበቃ ምክንያት አልነበረም፡፡ የ12 ዓመቱ የወ/ሮ አልጋነሽ በርሄ ልጅ ሳሙኤል ካሳዬ ‹‹እናቴ በጣም ግሩም ነበረች፡፡ በጣም ጥሩ ነበረች፡፡ ይህንን ሁላችሁም ታውቁት ነበር›› ሲል ነበር ስለ እናቱ መልካም ሰውነት የተናገረው፡፡
ለቀሪ ወገኖቿ ዘላለም የማይረሳ የሀዘን ጠባሳ ጥላ ያለፈችው አልጋነሽ ከተገደለች ቀናት ተቆጠሩ፡፡ የዴንቨር ፖሊስ በአንደኛ ደረጃ በነፈስ ግድያ የጠረጠረውን ግለሰብ ለመያዝ ክትትሉን ቀጥሏል፡፡ ይህ በነፍስ ግድያ የተጠረጠረው ግለሰብ ሎስ አንጀለስ ከተማ ውስጥ መታየቱ ለፖሊስ ጥቆማ ይደርሰዋል፡፡ ሰውዬውን እንዳዩ ለፖሊስ የጠቆሙት ደግሞ ሀይማኖታዊ አገልግሎት የሚሰጡ አንድ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ ፖሊስ ከግለሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ተጠርጠሪውን ለመያዝ የተጠናከረ ክትትል ማድረጉን ቀጠለ፡፡ ወ/ሮ አልጋነሽ ከተገለደች ከአስር ቀናት በኋላ ግለሰቡ ከሎስ አንጀለስ ወደ ሜክሲኮ ለመሻገር ሲሞክር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ለመዋል በቃ፡፡
የተጀመረውን የፍርድ ሂደት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነበር የሚከታተለው፡፡ ጃንዋሪ 14/2007 ደግሞ በሀመረ ኖህ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን የ40 ቀን የመታሰቢያና የፀሎት ስነ ስርዓት ተደርጎ ነበር፡፡
በነፍስ ግድያ ተጠርጥሮ የተያዘው አቶ ሸሞንዴ ገ/ሥላሴ ያደረገችለት እርዳታ በሰው ለመገደል የሚያበቃት ሳይሆን ሰው ሆኖ ራሱን እንዲችል በማብቃቷ ልትመሰገን እንደሚገባት ነው በደንብ የሚያውቋት ሰዎች የሚናገሩት፡፡ ‹‹ሰው ማለት ሰው በጠፋ ጊዜ ሰው የሚያደርግ ነው›› የሚል ብሂል በዚህ ዘመን አይሰራም ይላሉ የነፍስ ገዳዩን ጭካኔ የሚገልፁ ሰዎች፡፡ መልካም ማድረግ ለሞት የሚያበቃ ነው ወይ? የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ ለምን በቢላ አርዶ እንደገደላትም በግልፅ የሚታወቅ ምክንያት የለም፡፡ የዴንቨር ፖሊስም በዚህ ዙሪያ የገለፀው ነገር የለም፡፡የነፍስ ግድያው ወንጀል ለፍርድ ቤት ቀርቦ ጉዳዩን ሁሉም እየተከታተለው ነበር፡፡ ግን ጉዳዩ ከወራት በፊት በእንጥልጥል ቀረ፡፡ በዴንቨር ፍርድ ቤት የተከፈተው ፋይል ውሳኔ ሳይሰጥበት ተዘጋ፡፡ በነፍስ ግድያ የተከሰሰው ሸሞንዴ ገ/ሥላሴ በእስር ቤት እያለ በኤሌክትሪክ የራሱን ህይወት ማጥፋቱ ነበር ለፋይሉ መዘጋት ምክንያት የሆነው፡፡ አንዳንዶች ተከሳሽ የራሱን ህይወት ያጠፋው በፈፀመው የጭካኔ ግድያ ተፅእኖ ነው ብለው ይገምታሉ፡፡ ግምቱ እውነት ቢሆን እንኳን ወ/ሮ አልጋነሽ የእሷን እገዛ የሚሹ ያለ አባት የምታሳድጋቸውን አምስት ልጆቿን በሰው ሀገር በትና በጭካኔ ተገድላ ይህችን ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡