ከሊሊ ሞገስ
መዋብን ማን ይጠላል? ማንም! መዋብን እና ቁንጅናስ የሴቶች ብቻ ፍላጎት ያደረገው ማነው? ማንም! ወንዶችም እንደ ሴቶች አምሮና ተውቦ መታየትን ይሻሉ፡፡
ርዕሳችንን እንደግመዋለን፡፡
የቁንጅናሽ ግዙፍ ኃይል ያለው በውስጥሽ ነው፡፡ የውበት ስሜት፣ የቁንጅና ድባብ እንዲሰማው ለውስጥሽ ፍቀጂለት፡፡
‹‹የወጣት ሴቶች ሁሉ የጋራ ፍላጎት ቆንጆ ሆኖ መታየት ነው›› ሉናል ስታሲ አልድራጅ የ‹‹Real women-all you need to look and feel your best›› ዘገባ አቅራቢ፤ በሀሳባቸው እንስማማለን፡፡ በአፍላ የዕድሜ ዘመኗ በርካታ ሰዓታትን መስታወት ፊት የማታጠፋ ሴት የትኛዋ ናት? ቢሆንስ መዋብን መፈለግ ምን ስህተት አለበት? የሚታይ ውበት… በሌሎች ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ውበት… ተፈላጊ የሚያደርግ ውበት የበርካታ ሴቶች የጋራ ፍላጎት ነው፡፡
የሆነው ሆነና ውበት አካላዊ ማማር ብቻ ነው? ፈፅሞ! እንዲሁም የሴቶች የቁንጅና ግዙፍ ኃይል ያለው በውስጣቸው ነው፡፡ ይህን አውቀው የሚገነዘቡት ምን ያህሎች ናቸው? ውብ እና ታዋቂ ሴቶች ስለ ቁንጅና በተናገሩት አባባል ወደ ዝርዝር ማብራሪያችን እንግባ፡፡
ታዋቂ እና ውብ ሴቶች ስለ ቁንጅና ምን አሉ?
‹‹ቁንጅናን በአንፀባራቂ ብርሃን እመስለዋለሁ፡፡ እውነተኛ የሆነው ውበት ያላቸው ሰዎች አይኖቻቸው ብርሃንን ይፈነጥቃሉ፡፡ ቆዳቸውም አንፀባራቂ ነው›› (ካሜሮን ዲያዝ)
‹‹ቁንጅና የቆዳ ማማር ነው፡፡ አስፈላጊውና ዋናው ነገር ግን የሰውነት፣ የአዕምሮና የመንፈስ መመጣጠን ነው፡፡ የሆነ ሰው በአንድ ወቅት ያለኝን አባባል መቼም አልዘነጋውም፡፡ ‹‹ሃያ ዓመት እስኪሞላሽ ስትወለጂ ጀምሮ አብሮ የነበረው ውበት ይንጸባረቅብሻል (ይታይብሻል)፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ተንከባክበሽ ያቆየሽው ውበት›› የምወደው አባባል ነው፡፡ ውበታችን በትክክልም ማንነታችንን ይመሰክራል›› (ጄኒፈር ሉፔዝ )
‹‹…የሰውነት፣ የአዕምሮና የመንፈስ መመጣጠን›› የሚለውን የጄኔፈር ሎፔዝ ገለፃ እንዴት ተመለከታችሁት? ትክክል! ውጫዊ ውበት ያለ ውስጣዊ ውበት ምን ሊረባ? ብስለትን፣ በራስ መተማመንን፣ ስለ ሌሎች በጎ ማሰብን፣ ስለ ራስ ጤናማ ስሜት መሰማትንና ተዛማጅ ነጥቦችን በቁንጅና መስፈርቶች መሀል ይመድቧቸዋል፡- የስነ ውበት ባለሞያዎች፡፡ ለነገሩ የቁንጅና ተወዳዳሪዎች ሁነኛ መስፈርት የአዕምሮ ብስለታቸው አይደል? ስለዚህ አባባላችን ያስኬዳል ማለት ነው፡፡ እንደዚህ ከሆነ ደግሞ እያንዳንዱ ነጥብ እያነሳን እናብራራ፡፡
ከዚያ በፊት ግን በዕድሜ የደረጁ የዕድሜ ባለፀጋ (ሲበዛ ቆንጆ እና መስህብ ያላቸው እንደሆኑ ብዙዎች መስክረውላቸዋል) ውብ የሆኑበትን ምስጢር እንዴት እንደገለፁት እንመልከት፡፡ እንዲህ ነበር ያሉት የዕድሜ ባለፀጋዎች፡፡
– ለአንደበቴ እውነትን
– ለድምፄ መልካም ቃልን
– ለጆሮዬ ቅን ንግግርን
– ለእጆቼ እርዳታ አድራጊነትን
– ለልቤ ፍቅርን
አስተማርኩ፡፡ እኔ ማራኪና ውብ ያልተባልኩ ማን ሊባል ኖሯል? ውስጥን ዘልቆ የሚገባ አገላለፅ፡፡ ከእድሜ ባለፀጋው ተሞክሮ የምንማረው ቁም ነገር እንዳለ እንገነዘባለን፡፡ ወደ ነጥባችን እንመለስ፡፡
የምታደርጉትን ነገር ሳይሆን ማንነታችሁን አፍቅሩ
Love your WHO, not your do
እውነታው ይኸውላችሁ፡፡ ሁሉን ነገር ሁል ጊዜ በትክክለኛው መንገድ ላላደርግ እችላለሁ፡፡ ራሳችንም ላናደርገው እንችላለን፡፡ ያ ግን በማንነታችን ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የለበትም፡፡ ሰው ነንና ስህተት ልንፈፅም እንችላለን፡፡ ቁም ነገሩ ፈጥኖ ከስህተት መመለስ ነው፡፡ ለማንነታችን የምንሰጠው ግምት ከፍተኛ ከሆነ ከስህታችን ለመመለስ አንዘገይም፡፡ ስለ ራሳችን መልካም ስሜት እየሰማን ስንሄድ የባህርይ ለውጥን፣ ዕድገትንና መሻሻልን እናሳያለን፡፡ ይህ ከውስጣዊ ውበት ይመደባል፡፡
በእውነተኛ ጓደኝነት እመኑ
ሰዎች ‹‹ምን አይነት ውብ ልጅ መሰለቻችሁ? ባህሪዋም እንደ ቁንጅናዋ ነው›› የሚል በጎ አመለካከት ባንቺ ላይ እንዲያድርባቸው በእውነተኛ ጓደኝነት እመኚ፡፡ እዚህ ላይ የእውነተኛ ጓደኝነት መስፈርት ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ታነሺ ይሆናል፡፡ እኚውልሽ፡-
እውነተኛ ጓደኛ
– አንቺነትሽን በአንቺነትሽ የሚቀበልና በአንቺ የሚያምን ነው
– በችግርሽ ጊዜ ቀድሞ የሚደርስ ነው
– ስህተትሽን ይቅር ይላል
– ሁሌም ከአንቺ ጋር መሆንን ይፈልጋል
– እውነቱን ይነግርሻል
– ይገነዘብሻል፣ ይረዳሻል
– ውድቀትሽን አይመኝም
አንቺስ ከእነዚህ መስፈርቶች መሀል ምን ያህሉን ታሟያለሽ? ካላሟላሽ አሁኑኑ ለማሟላት አስፈላጊውን እርምጃ ውሰጂ፡፡ በዚህ የእውነተኛ ጓደኝነት ጎዳና ላይ ለመጓዝ ውስጥሽን አሳምነሽ የውስጣዊ ውበት ባለቤትነትሽን እንዳትጠራጠሪ፡፡
የመዋቢያ እቃዎች ምርጫሽ ላንቺ የሚስማሙ ይሁኑ
ሰው ላይ ያየሽው ጌጥና ልብስ ደስ ስላለሽ ብቻ አንቺም ማድረግ አለብሽ? የለብሽም! ምክንያቱም ለሌላው የተስማማው ለአንቺ ላይስማማ ይችላልና፡፡ ለእኔ የሚስማሙት መዋቢያዎች የትኞቹ ናቸው? ብለሽ ራስሽን ጠይቂ፡፡ በምርጫ በኩል እናትሽ ወይም ቀሪ ቤተሰብሽ አስተያየት ሊሰጡሽ ይችላሉ፡፡ ‹‹ሰዎች ራሳቸውን ትተው ሌሎችን መሆን ሲፈልጉ ትልቅ ስህተት ይፈፅማሉ፡፡ ራሳቸውንም አያገኙትም፣ ሌሎችንም መሆን አይችሉም›› የሚሉን የማህበራዊ ህይወት ባለሙያው አለን ፓርከር ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በላይ ውበታችንም ሆነ በውስጣዊ ማንነታችን ላይ ትልቅ ተፅዕኖን ይፈጥራል፡፡
ሁሌም የመልካም ጠረን ባለቤት ሁኚ
ጠረን በፍቅርም ላይ ሆነ ቁንጅናን አጉልቶ ለማውጣት ወይም ለማጥፋት የራሱ አስተዋፅኦ አለው፡፡ በውጫዊ ውበቷ እጅግ የምትማርክ እንስት የመጥፎ ጠረን ባለቤት ከሆነች ወንዶች ዘወር ብለው እንደማይመለከቷት ለአንቺ መንገር አያስፈልገን ይሆናል፡፡ ውበትሽን እንዳታደበዝዢ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ነውና አታናንቂው፡፡
ውበትሽን አጉልተው የሚያወጡ በርካታ ሻምፖዎች፣ ሽቶዎችና ዶድራንቶች አሉና እነሱን በመጠቀም የበለጠ የምትማርኪ ሁኚ፡፡
ለአብነት እነዚህን ዘርዝረንልሻል
– REVLON
– ESTEE LAUDER
– LOREAL
– MATRIX
– PANTENE
– AVEENO
ቀደም ብለን ለመጥቀስ እንደሞከርነው የቆዳ ማማርና ውጫዊ ውበት ብቻውን የቁንጅናሽ መሰረት መሆን አይችልምና እወቂ፡፡ የፊልም ተዋናይና አቀንቃኝ ጄኒፈር ሎፔዝ እንዳለችው ሰውነትሽን፣ አዕምሮሽንና መንፈስሽን በማመጣጠን ቁንጅናሽን አጉልተሽ ለመውጣት ሞክሪ፡፡ የተመጣጠነ ምግብ፣ የአካል እንቅስቃሴና በቂ እረፍትም በውበትሽ ላይ ያላቸውን ጉልህ አስተዋፅኦ መዘንጋት የለብሽም፡፡
እናሳ? ጊዜው አልረፈደምና ቁንጅናሽን አጉልተሽ በማውጣት የሁሉም ሰው የዓይን ማረፊያ ለመሆን አንድ ብለሽ እርምጃሽን ብትጀምሪስ? መልካም ጉዞ!!
ይህን ጽሁፍ ስትወስዱ ከዘ-ሐበሻ ማግኘታችሁን ግለጹ።