Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ጫልቱን የገደላት ወያኔ ኢህአዴግ ሆኖ ተገኘ

$
0
0

ገለታው ዘለቀ

የስደተኛው ማስታወሻ ከተሰኘው መጽሃፍ ውስጥ ኣንዲት ምእራፍ መዝዤ በዛ ላይ የሰላ ግምገማ ለማድረግ ነው የዛሬው ኣነሳሴ ። መጽሃፉን የጻፈው ተስፋየ ገብረኣብ ሲሆን በዚህ መጽሃፍ ውስጥ የተለያየ ጭብጥ ያላቸውን ጉዳዮች በየምእራፉ ያነሳ ሲሆን “ጫልቱ እንደ ሄለን” የሚለው የብዙዎችን ትኩረት እንደሳበ ሁሉ የእኔንም ስቦ ነበርና በዚህ ክፍል ላይ ያነጣጠረ ትችት ኣቀርባለሁ።መጽሃፉ ከተለቀቀ ዘግየት ቢልም የጫልቱ እንደሄለን ጉዳይ ግን መወያያነቱ ረዘም ላለ ጊዜ ቆይቶ ስላየሁ ነው ዛሬ የተነሳሁት።
yesidetegnaw
ደራሲው ይህን ክፍል ሲጀምር በፍቃዱ ሞረዳ በተባለ ገጣሚ የተደረሰ ግጥምን በማንበብ ነው። የዚህ ግጥም ይዘት ወይም ጭብጥ ከዘረኝነት ጋር የተያያዘ ነው። በዚህ ግጥም ብእሩን ያሟሽና ኣንዲት ጫልቱ የተባለች ቆፍቱ ተወልዳ ያደገች ውብ፣ የኣስራ ኣራት ኣመት ልጅ ጋር ያስተዋውቀናል ። ይህቺ ህጻን ቆፍቱ ውስጥ የታወቀች ፈረስ ጋላቢ እንደነበረች ይናገራል። ከወንዶች ጋር ሁሉ ተወዳድራ ፈረስ ግልቢያ እንዳሸነፈች በዚያም ምክንያት ፈረስ እንደተሸለመች፣በዚህም ስሟ እስከ ዋጂቱ፣ እስከ ወልመራ፣እስከ ሴራ፣ እስከ ደዋራ፣ እስከ በቾ፣ እስከ ጭቋላ፣ እስከ ድሬ፣ እስከ ጊምቢቹ ድረስ ተሰምቶ እንደነበር ያስረዳናል። ይህ የሆነው ከኣስራ ኣራት ኣመቷ በፊት በመሆኑ በርግጥ ይህቺ ህጻን ከቆፍቱ ትላልቅ የታወቁ ፈረስ ጋላቢዎች ጋር ተወዳድራ ኣሸነፈች? የሚለው የተኣማኒነትን ጥያቄ ያስነሳል። ወይ እንደሷ ከሆኑ ታዳጊ ህጻናት ጋር ተወዳድራ ከሆነ ደራሲው ኣንድ ይበለን እንጂ የኣስራ ሁለት የኣስራ ሶስት ወይም ከዚያ በታች ህጻን ሆና ከኣካባቢው ወንዶች ጋር ተወዳድራ ኣሸነፈች ቢለን ከመነሻው ተዓማኒነት የሚባለውን ጉዳይ እንድናነሳ ያደርገናል። ይሁን…. እንግዲህ….. ብለን ይህንን ጉዳይ ተወት ኣድርገነው ማንበባችንን ስንቀጥል ጫልቱ ብቻዋን በኣስራ ኣራት ኣመቱዋ ፈረስ ጋልባ ዘመድ ለመጠየቅ ጉዞ ስትጀምር ያሳየናል። ይህቺ ኣንድ ፍሬ ልጅ ብቻዋን ፈረስ ጋልባ ዘመድ እንድትጠይቅ ቤተሰብ መፍቀዱ ሌላው ኣንድ ኣንባቢ የሚጠይቀው ጉዳይ ሆኖ ለማናቸውም መንገድ ላይ ሊጠልፏት የከበቧትን ጎረምሶች በጣጥሳ እንዳመለጠች ይተርክልናል። ጋላቢ ስለነበረች ከዚያ ሁሉ ጎረምሳ ሽምጥ ጋልባ ኣመለጠች ይለናል። ምን ኣይነት ፈረስ ቢሆን? ምን ኣይነት ህጻን ጋላቢ ናት ያሰኘናል። ይሁን ብለን እንቀጥላለን….. ደራሲው ብዙ ሳይቆይ ጫልቱ በኣስራ ኣምስት ኣመቷ ከድሬ ለመጣ ታዋቂ የአድአ ቤተሰብ መዳሯን ያረዳናል። የሚገርመው ደራሲው ይህን መርዶ ለተደራሲያኑ ሲያቀርብ ኣለመከፋቱ ነው። በኣስራ ኣምስት ኣመት ትዳር መጀመርና መደፈር በጣም ኣሰቃቂ ጉዳይ ነበር። ደራሲው ለዚህች ህጻን ኣዛኝ ቢሆን ኖሮ ያለእድሜዋ በመዳሯ ብዙ ሊል ይገባው ነበር። ይህቺ ህጻን ያገባችው በኣስራ ሰባት ኣመቱዋ ኣይደለም። በኣስራ ኣምስት ኣመቷ ነው የተደፈረችው። ይህቺ እህታችን ምን ኣልባትም ገና የሴቶቹን ወግም ኣላየችም ይሆናል። በገጠር የሚወለዱ ሴቶች ቶሎ የሴቶችን ወግ የሚያዩ ኣይደሉም። ኣካሉዋና ስሜቱዋ(emotion) ለወሲብና ለትዳር ሳይበቃ መዳሩዋ ቀጣይ የህይወት ዘመኑዋን ሁሉ ሊያበላሸው ስለመቻሉ ጥያቄ የለውም።የስነ ልቡና ሰዎች እንደሚሉት ሴቶች ለኣቅመ ህያዋን ሳይደርሱ ወሲብ ሲፈጽሙ ህይወታቸውን ሁሉ የሚከተላቸው የስሜት ችግር ኣለ። ደራሲው ለዚህች ወጣት ስስ ስሜት እንዳለው እንደራራላት በዚህ ኣካባቢ ሳያሳየን መቅረቱ ለጫልቱ ያለውን ፍቅር ከወዲሁ እንድንመዝን ያደርገናል።

ጫልቱ ብዙም ሳትቆይ ጠፍታ ወደ ቤቷ ተመለሰች። ምነው ትዳር ይሻላል ቢሏት ሰካራም ነው ይደበድበኛል ኣለች። በርግጥ ከዚህ ሌላ በቃል ለመግለጽ የፈራችው ምክንያት እንዳለ ሁሉ ተሰምቶኛል። ችግሩዋን ማስረዳት ስለማትችል ይህንን ምክንያት በመስጠት እንቢኝ ማለት ፈልጋ ይሆናል። ለማናቸውም ይህን ክፍል ሳነብ ኣንጀቴን ያላወሰው ጉዳይ ያለእድሜዋ ምናልባትም የሴቶችን ወግ እንኳን በቅጡ ሳታይ ዘላ ሳትጠግብ የቤተሰብ ሃላፊነት ቀንበር ትከሻዋ ላይ መጫኑ ነው።

ጸሃፊው ወደ ኣዲስ ኣበባ ሊሸኛት ሲል የባህሪ ለውጥ ማምጣቱዋን ቁጡ መሆኑዋን ጥቂት ጠቆም ኣድርጎን እሱን ስላብከነከነው የሄለንና የጫልቱ ስያሜ ጉዳይ ያሮጠናል። ኣንባቢዎች እንከተልና ንባባችንን ስንቀጥል ከብዙ የቤተሰብ ምክር በሁዋላ ወደ ሸገር ሄዳ እንድትማር ተወሰነ ይለናል። ቤተሰብ ወደ ሸገር እንድትሄድ መወሰኑ ስለሸገር መልካምነት የሰማው ጉዳይ ቢኖር ነው ብለን እንድናስብ ያደርገናል። የጫልቱ ዘመዶች የሚወዱዋትን ቆንጆ ልጃቸውን ወደ ክፉ ቦታ ሂጂ ኣይሉም ብለን እናስባለን። ቆፍቱ ከኣዲስ ኣበባ ብዙ የማይርቅ በመሆኑ እነዚህ የጫልቱ ቤተሰቦች ተመላልሰው ኣይተውም ሊሆን ይችላል። ከሁሉም በላይ ኣዲስ ኣበባ ያለችው የጫልቱ ኣክስት ምስክርነትም ጥሩ ነበር ማለት ነው። የሆነ ሆኖ ጫልቱ ወደ ሸገር እንድትሄድና በዚያ እንድትማር ስምምነት በመያዙ ጫልቱ ሸገር ገባች። ሸገር ስትገባ ያረፈችው በኣክስቷ ቤት ነው። ኣክስቷ ኣዲስ ኣበባ ውስጥ ከኣንድ መሬ ኣማራ ጋር ጋብቻ መስርታ በጥሩ ሁኔታ ትኖራለች። ጫልቱን ኣዲስ ኣበባ ጥሩ ኣርጋ ስተቀበላት ነው የምናየው። የኣክስቷ ባል ሲቆጣት እንኳን ኣናይም። ጫልቱ ኣዲስ ኣበባ ውላ ስታድር ተወደደች።ጎረቤቶች ሁሉ እንዴት ይገልጿት እንደነበር ደራሲው ሲገልጽ። እንዲህ ኣድርጎ በኣክስቷ በኩል ያቀብለናል።
“ሄለን የኔ ቆንጆ፦ ጎረቤቶቻችን ሁሉ ወደውሻል። ግልፅና ልበ ሙሉ ናት ብለው ነገሩኝ። ቁመናሽና መልክሽን የማያደንቅ የለም።”

ይህ የሚያሳየው ቆፍቱ ላይ ወጪ ወራጁ ይላት እንደነበረው ኣዲስ ኣበባም ተቀብላ ጫልቱን እያደነቀች እንደሆነ ነው። የምትኖርበት ኣካባቢ ኣእምሮ ብሩህ ቆንጆ እያለ ውስጥና ውጪዋን ኣድንቋል። በርግጥ ደራሲው ይህን ከነገረን በሁዋላ ኣክስቷ ስሟን መቀየር እንዳለባት፣ ትምህርት ለመማር ኣማርኛ መማር እንዳለባት ገለጸችላት ይለናል። በርግጥ ትምህርት ለመማር ኣማርኛ መማር ያለባት እዚህ ኣዲስ ኣበባ ስለመጣች ብቻ ኣይደለም። ቆፍቱ ሆና ትምህርት ለመማር ብታስብ ኖሮ በዚያን ጊዜ ቁቤ ኣልነበረምና ያው ኣማርኛ መማር ነበረባት። ይህ ጉዳይ ያሳዝነኛል። ሁሉም የሃገራችን ቡድኖች ሁሉ በቋንቋቸው መማር ቢችሉ ኖሮ ጥሩ ነበር። ባይልንጉዋል ሆኖ ማደግ ቀድሞ ቢቻል ኖሮ ጥሩ ነበር።

ለማናቸውም ጫልቱ ኣማርኛ ገና መልመድ መጀመሩዋ ሲሆን በዚህ ጊዜ ኣዲስ ኣበባ ውስጥ ሊስቁብሽ ይችላሉና ቶሎ ቶሎ ኣጥኚ መባሉዋን ይነግረናል። በርግጥ እዚህ ጋር ልገልጸው የምፈልገው ኣለ። ደራሲው በዋናነት ለዚህች ውብ ወጣት የህይወት መጥፋት ተጠያቂ ለማድረግ የሚሞክረው የቋንቋን የስምንና የንቅሳትን ጉዳይ በማመናፈስ ስለሆነ ኣንድ ነገር ማለት እፈልጋለሁ። እርግጥ ነው ኣዲስ ኣበባ በሄለን ቅላጼ (Accent) መሳቁዋ ኣይካድም። እዚህ ጋር ግን መነገር ያለበት ኣዲስ ኣበባ በቅላጼ የምትስቀው ጫልቱ ኦሮሞ ስለሆነች ኣይደለም። ኣዲስ ኣበባ ከኣዲስ ኣበባ ውጭ ተወልደው በመጡ ኣማሮች፣ ትግሬዎች፣ ዶርዜዎች፣ ጉራጌዎች ወዘተ እንደሳቀች ነው የምትኖረው። ይሄ ጉዳይ ደግሞ በጣም ክፉ (serious) ተደርጎ ኣይታይም ነበር። ከጫልቱ ኣማርኛ ይልቅ ኣዲስ ኣበባ በመንዞች ኣማርኛ ተንፈራፍረው ይስቃሉ። ለምን የራሴን ልምድ ኣልነግራችሁም። ኣዲስ ኣበባ በነበርኩበት ሰዓት ወላጅ እናቴ ከገጠር ኣንዲት የዘመዳችንን ልጅ ወደ ኣዲስ ኣበባ ይዛ መጣች። ይህቺ የዘመዳችን ልጅ ወደ ኣዲስ ኣበባ የመጣችው መሃን የሆነችውን ኣክስታችንን እንድታግዝ፣ በዚያውም ትምህርት እንድትማር ነው። ይህቺ ልጅ ተወልዳ ያደገችበት ቀበሌ ከስልጣኔ በብዙ ርቀት ወደ ኋላ የቀረ ነው። መኪና እንኳን ኣይታ ስለማወቋ እርግጠኛ ኣይደለሁም። ለማናቸውም ኣዲስ ኣበባ መጣችና ትምህርት ቤት እንዳስገባት ታዘዝኩ። ወደ ትምህርት ቤት ልወስዳት ስል ያሳሰበኝ ነገር የስሟ ጉዳይ ነበር። ስሟ በልጌ ነው። በዚህ ስም ልጆች ይስቁባትና ስሜቱዋ ይጎዳል ብየ ረድዔት ኣልኳት። በዚያ ስም ተመዘገበችና ትምህርት ቀጠለች። ኣልፎ ኣልፎ በንግግሩዋና በገርጋራ የገጠር እንቅስቃሴዎቹዋ ህጻናት ይስቁባት እንደነበር ተረድቼኣለሁ። በኣማርኛዋ የትምህርት ቤት ህጻናት ከሚስቁት ይልቅ እኛ ቤት ውስጥ የምንስቀው ኣይረሳኝም። ኣንድ ቀን እንደዚህ ሆነ። ምሳ ልንበላ በዝግጅት ላይ ሳለን ረድዔት ለማስታጠብ ትዘጋጃለች። በወጉ መሰረት ኣባወራ መጀመሪያ ይታጠባልና ማስታጠቢያውን ይዛ ወደ ኣክስቴ ባል ቀረበች። የኣክስቴ ባል ኣሁን ያስታውሱታል ብየ ኣስባለሁ። በዚያን ጊዜ እሳቸው ሬዲዮ ይጎረጉሩ ነበርና ረድዔት መቆሙዋን ኣላዩም። ትንሽ ጠበቀችና
“ኣብባ እጣትሁ ላይ ውሃ ላርግልሁ” ኣለቻቸው። የኣክስቴ ባል ዘወር ኣሉና
“ምን?”
“ጣትኩን ውሃ ኣስነኩት”

የኣክስቴ ባል ፈገግ ኣሉና ሌባ ጣታቸውን ብቻ ወደ ማስታጠቢያው ዘረጉ። ሁላችንም በሳቅ ኣለቅን። በረድዔት ቤት “ጣትኩን ውሃ ኣስነኩት” ማለት እጅሁን ታጠቡ ማለት ነው። እንዲህ ባሉ ዘየዎች ኣዲስ ኣበባ ትስቃለች። ይሁን እንጂ የምትስቀው መራራ ጥላቻን በሆዷ ይዛ ሳይሆን በቀልድ ነው።
በርግጥ እንደጫልቱ ከተለያየ ገጠር የሚመጡ ሁሉ ኣዲስ ኣበባ ሲገቡ ሊሰማቸው የሚችለውን ጫልቱም ሊሰማት እንደሚችል ስሜቱዋን ልንረዳላት ይገባል። የሆነ ሆኖ በኣጠቃላይ በጎረቤቶቹዋ ዘንድ ባለ ብሩህ ኣይምሮና ልበሙሉ ቆንጆ የተባለች ስለሆነች የተጋነን ችግር ኣልገጠማትም። እንዴውም መልካም ስም ወጥቶላታል። መልካም ልጅ ተብላለች። ከማሪቱ ጋር ያላት ግንኙነት በጣም ጥሩ ነበር። ብዙ ጊዜ በኣንድ ሰው ቤት ያለውን ንትርክ ሁሉ ጫልቱ ኣላየችም።
ጥሩ በሚባል ቤተሰብና ጎረቤት መሃል ቆየችና ኣማርኛዋ ሲሻሻልላት የማታ ትምህርት ገባች። የማታ ትምህርት በገባችበት ሰዓት ምንም መጥፎ ነገር ኣይገጥማትም። ነፍስ ካወቁ የማታ ተማሪዎች ጋር ምን ኣልባትም በጣም ጥሩ ግንኙነት ነበራት። ኋላ ላይ ለጫልቱ ቤተሰቦች ጫልቱን ወይም ሄለንን ወደ ቀን ማዛወሩ መልካም መስሎ ታያቸውና ወደ ቀን ስትዛወር ደራሲው በሚገርም መንገድ እንዲህ ሲል ልባችንን ያንጠለጥለዋል።
“የጫልቱ መራር ፈተና የጀመረው በዚህ ጊዜ ነበር።”…….

ምን ይሆን የሚገጥማት? ኣስተማሪ ምን ሊላት ነው? ምን ትሆን ይሆን? ………. ብለን ልባችን ይሰቀላል:: ደራሲው መጨረሻ ላይ ለደረሰበት ድምዳሜ ትልቅ ኣስተዋጾ ያደረገው ኣሁን በዚህ በትምህርት ቤት የምታሳልፈው የህይወት ልምዱዋ ነው ማለት ነው። ደራሲው ለጫልቱ ህይወት መመሰቃቀል ተጠያቂ የሚያደርገው ስርአታዊ ሽብር (systemic Violence) ነው ብሎ ያምናል። በራሱ ቋንቋ እንዲህ ይገልጸዋል።

“የሆነችውን አፍርሶ፣ ያልሆነችውን እንድትሆን ያደረጋት ማነው? ይህ ስርአታዊ ሽብር (systemic Violence) ስለመሆኑ ጫልቱ ግንዛቤው አልነበራትም።”

የሚገርመው ግን ለዚህ ስርዓታዊ ሽብር (systemic violence)ና ለጫልቱ ስሜት መጎዳት ዋና ተጠያቂ የሚያደርገው ህጻናትን ነው። ከፍ ሲል እንዳልኩት ጫልቱ ኣዲስ ኣበባ ስትመጣ ብዙም የሚያስከፋ ነገ ኣልገጠማትም። ነፍስ ካወቁ የማታ ተማሪዎች ጋር ስትማር የከፋ ችግር የመረረ ነገር የለም። ትልቁ ችግር የመጣባት ወደ ቀን ስትዛወር የሰባተኛ ክፍል ተማሪ የሆኑት በትምህርታቸው ኣርባ ኣንደኛ የወጡ ሰነፎች እንደነ ሳምሶን ኣይነት ህጻናት ማብሸቃቸው ነው። የሚገርመው በትምህርት ቤቱዋ ውስጥ መምህራኖቹዋም ለጫልቱ ያደሉ ነበር። ይወዱዋት ነበር። ችግሩ የነበረው እነዚያ የኣስራ ሶስትና የኣስራ ኣራት ዓመት ህጻናት ጋር ነው። እነዚህ ህጻናት በጫልቱ ንቅሳትና ቋንቋ መሳቃቸው ጫልቱን ሊጎዳ የሚችል መሆኑ ኣያጠያይቅም። ነገር ግን ጫልቱ በነዚህ ህጻናት መጎዳቷ ስርዓታዊ ሽብር(Systemic Violence) ለሚል መደምደሚያ ኣያደርስም። ጫልቱ እኮ ወደ ማታ ተመልሳ በዚያ ትምህርቱዋን መቀጠል ትችል ነበር። ለምን ከነዚያ ህጻናት ጋር እያበሸቁዋት ትኖራለች።

እነዚህ ህጻናት ጫልቱን በማብሸቃቸው ከስርዓት ጋር ምንም የተያያዘ ነገር የለውም። ቤተሰብ ኣላስተማራቸው፣ ኣስተማሪ ኣላስተማራቸው ይህንን መሳቅ ከየት ኣመጡት። እነዚህ ህጻናት ከኣዲስ ኣበባው ዘየ ለየት ያለ ኣማርኛ ሲሰሙ መቀለዳቸው ኣይቀርም። ጫልቱ ኦሮሞ ስለሆነች ኣይደለም።
ደራሲው ኣንዲህ ይላል። ኣንድ ጋጠ ወጥ ተማሪ የሚለውን ይመስለኛል የሚገልጸው።

“ ቆንጆ ነሽ የሆንሽ ኒቂሴ ገላ ሆንሽ እንጂ”
በርግጥ ኣንድ የኣስራ ሶስት ኣመት ሕጻን “ቆንጆ ነሽ” ይላል? ኣይመስለኝም። ንቂሴ ገላ…. ሊል ይችላል። በርግጠኝነት ግን ጫልቱ ኦሮሞነቱዋን ሳትገልጽ ስሟንም ደብቃ “ሄለን ነኝ” ያለች ሲሆን ኣንድ የኣስራ ሶስትና ኣስራ ኣራት ኣመት ህጻን
“የጋላ ነገር ይህን የመሰለ ውበት ቸክችከው ቸክችከው ኣበላሹት” ኣይልም።

እንዴ?…. ህጻናት እኮ ናቸው:: ህጻናት የጠሉትን ንቅሳት ኣልፈው ሌላ ውበት በጫልቱ ፊት ላይ ማየት ኣይችሉም። ከሁሉ በላይ ደግሞ “የጋላ ነገር….” ኣይሉም።ይህንን ያለው ራሱ ተስፋየ ነው። ደራሲው ራሱ የፈለገውን መልእክት ለማስተላለፍ እነዚህን ህጻናት ለምን ወንጀል እንደሚያናግራቸው ኣልገባኝም። በደርግ ጊዜ እንኳን የኣስራ ሶስትና የኣስራ ኣራት ኣመት የኣዲስ ኣበባ ህጻን ይቅርና እኔ ራሴ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኘም ስለ ብሄር ብዙ ኣላውቅም። ትላልቅ የሆኑ ሰዎችም ብዙ ኣያውቁም ነበር። ሌላው ቀርቶ መንግስቱ ሃይለማርያም ኦሮሞ ይሁን ኣማራ ወይ ወላይታ ኣይታወቅም ነበር። ሁዋላ ላይ ዚምባብዌ ሳለ ኧረ ኣገሩ ሁሉ ዘሩን እየተጠየቀ ነው እርስዎ ከየት ነዎት? ተብሎ ነው ኦሮሞና ኣማራ መሆኑን ለ VOA ተናግሮ የታወቀው። ይህንን ስናይ በፍጹም ከእውነታው የራቀ ነገር እነዚህን ህጻናት ደራሲው እንዲናገሩ ያደርጋቸዋል። በዚህ ኣዝኛለሁ። ከሁሉ የሚያሳዝነው ጎረቤቱን፣ ኣስተማሪውን ሁሉ ለጫልቱ ጥሩ ኣድርጎ፣ የማታ ተማሪዎችን እንከን ሳያወጣ፣ የሰባተኛ የቀን ተማሪዎችን ለጫልቱ መሰበር ዋና ተጠያቂ ማድረጉ ብሎም የስርዓቱን ሽብር የፈጠሩት ዋና ተጠያቂ እነዚህ ህጻናት እንደሆኑ ኣይነት ድምዳሜ ማሳየቱ በጣም ገርሞኛል።

ከፍ ሲል እንዳልኩት ደራሲው የሚያሳየን እነዚህ ህጻናት ጫልቱ ኦሮሞ መሆኑዋን ያወቁት በንቅሳቷ ነው። ይሄ ደግሞ በጣም ይገርማል።በመጀመሪያ ደረጃ ንቅሳት የሚነቀሱት ከፍ ሲሉ ነው። ጫልቱ በስንት ኣመቷ ደረቷን ሁሉ ሳይቀር እንደተነቀሰች ኣላውቅም። ይሁን…. ኣልፎ ኣልፎ በኣስራ ኣንድ በኣስራ ሁለት ኣመት ጊዜ የሚነቀሱ ይኖሩ ይሆናልና ይህን እንለፈው። በመሰረቱ የኣስራ ሶስትና ኣስራ ኣራት ኣመት የኣዲስ ኣበባ ህጻን በዚያን ጊዜ ንቅሳት የኦሮሞ መገለጫ መሆኑን ኣያውቅም። ኣይደለምም። ንቅሳት ያለው እንዴውም በብዛት የሚታየው በኢትዮጵያ ኣይሁዶች፣ በዎሎዎች፣ በትግሬዎች፣ በመንዞች ኣካባቢ ነው። እነዚያ ህጻናት ንቅሳትን በማየት ሄለን ኦሮሞ ናት ሊሉ ኣይችሉም። ደራሲው ሊደርስበት ለፈለገው መደምደሚያ የወሰዳቸው መንደርደሪያዎች(premisis) ተዓማኒነት የጎደላቸው ከመሆናቸውም በላይ ህጻናት መራሽ ስርዓታዊ ሽብር የተፈጠረ ኣስመስሎ ማቅረቡ ይህን ክፍል ባዶ እንዳያስቀርበት እሰጋለሁ።ደራሲው ኣጥብቆ የሚታገለው ጫልቱ ስሟን መቀየሩዋ ከማንነት መምታታት(identity confusion) ጋር እንዲያያዝለት ነው። በመሰረቱ በቋንቋ ሳይንስም ቢሆን በስምና በተሰያሚ መካከል ምንም ዓይነት ተፈጥሮኣዊ ግንኙነት የለም።

እኔ ራሴ ስሜ ከኦሮሞ የተወሰደ እንደሆነ ብዙ ሰው ይነግረኛል። በዚህ ደስተኛ ነኝ። ወላጅ እናቴ ኦሮሞ ኣገር ደራ የተባለው ቦታ ኣድጋ ስለነበር ስለ ኦሮሞዎች ጥሩነት ኣውርታ ….ኣውርታ ….ኣውርታ……..ኣትጠግብም ነበርና በልጅነት ጊዜየ እኔም ኦሮሞ በሆንኩ ብየ ኣስቤ ኣውቅ እንደነበር ትዝ ይለኛል።
የስም ጉዳይን ይዘን ወደ ኣዲስ ኣበባ ስንመጣ ብዙ ኣስቂኝ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል። እርግጠኛ ነኝ እነዚያ የጫልቱ የክፍል ጓደኞች ከኣማራ ኣካባቢ የሄደች ኣንድ ንቅሳት ያላት ወጣት ክፍሉ ውስጥ ብትኖር ስሟ ደግሞ ቁንጥሬ ጭንቅል ቢሆን በስሟም በንግግር ዘየዋም መሳቃቸው ኣይቀርም። ኣንድ ኣምታታው ውርጋጥ የሚባል ወንድ ተማሪ ቢኖርም ክፍሉ በሳቅ ማለቁ ኣይቀርም። በዚህ በስም ኣካባቢ ብዙ ነገር ኣይቻለሁ። እዚህ ስማቸውን ብጠቅስ ጓደኞቼ ይቆጡኛል ብየ እንጂ የማውቃቸው ሰዎች ኣዲስ ኣበባ ሲገቡ ዘመንኛ ስም ለውጠው ኣይቻለሁ። ይሄ ደግሞ መራራ ከሆነ ስሜት ጋር የተያያዘ ሳይሆን ሸገርን ለመምሰል ነው።እነዚያ ህጻናት ሃጎስ በሚለውም ስም መሳቃቸው ኣይቀርም። ሸምሱ በሚባል የጉራጌ ልጅም መሳቃቸው ኣይቀርም።ይህ ነገር መልካም ኣይደለም። ሕጻናቱ የሚስቁት ከብሄር ከደም ሃረግ ጋር ኣያይዘው ሳይሆን ኣዲስ ኣበባ ሰለጠንኩ ስትል ዘመንኛ ያለቻቸውን ስሞች ዘርዝራለች። ከጥንት ጀምሮ በገጠሩና በከተሜው መካከል ሰፊ ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ክፍተቶች ተፈጥረው እየሰፋ በመምጣቱ ኣዲስ ኣበባ ለየት ማለቱዋን በስም ኣወጣጥ፣ በኣነጋገር ዘየ ለማሳየት ፈልጋ ነው። ይሄ ደግሞ እጅግ መራራ ነገር ኣይደለም። የገጠሩን ወንድሙዋና እህቱዋን ኣትጠላም።

ጸሃፊው የኣተቴን ነገር ኣንስቶ ጫልቱ በዚህም እንዳዘነች ይገልጻል። ያለችው እኮ ኣዲስ ኣበባ ነው።ርቃ ሄዳለች እኮ። የተለየ ባህል የተፈጠረበት፣ ኣዲስ ኣገር ነው ያለችው።ጫልቱ ለመልቲ ካልቸራሊዝም ክፍት መሆን ኣለባት እኮ። ቆፍቱ ያለው ኣተቴ እዚህ ባለመጠራቱ ልታዝን ኣይገባትም። እዚያው ኦሮሚያ ክልል ያሉ ብዙ የኦሮሞ ልጆች ኣይቀበሉትም። ወለጋ ያሉ ፕሮቴስታንት ኦሮሞዎች በየሱስ ስም እያሉ ነው የሚረግሙት። እዚያው ኦሮሞዎች መካከል ስትሄድም ልትጎዳ ነው ማለት ነው። ርቃ ስድትሄድ በተውጣጣ ማህበረሰብ ውስጥ ስትኖር በቀበሌዋ የነበረውን ባህል ሁሉ ታገኘዋለች ማለት ኣይደለም። ይህቺ ልጅ ይህን የኣተቴ ባህሉዋን እዚያው ቆፍቱ እያለች እንዳትንከባከበው የሚያደርግ ኣካል ቢፈጠርና ኣዘነች ቢባል ስሜት ይሰጣል። ይህንን መገንዘብ ያስፈልጋል። በተረፈ ግን ኣተቴ ያለው ኦሮሞ ጋር ብቻ ኣይደለም። ወሎና መንዝ ብንሄድ ብዙ ኣለ። ኣዲስ ኣበባ መጥታ ተይ ልጆቹን ስለ ኣተቴ ኣታስተምሪ መባሉዋ የመጨረሻ ስሜት ሰባሪ ነገር ተደርጎ መቅረቡ ትክክል ኣይደለም።

በመሰረቱ ማህበራዊ ለውጥ ኣይጠላም። ጫልቱ ጂንስ መልበሷ፣ ቦርሳ መያዟ፣ ከተሜ መምሰሏ ምንም ችግር የለውም። ዋናው ነገር ለለውጥ ስትዘጋጅ ኣንዳድ ጠቃሚ የሆኑ ባህሎቹዋን እንዳትጥል መምከር ነው። ስልጣኔ ሲመጣ ማህበራዊ ለውጥም ይመጣል። በዚህ ጊዜ ኣዳዲስ ባህሎችን ለመማር መዘጋጀት ማለት ነው እድገት ማለት።ይሄ ደግሞ ከማንነት መምታታት ጋር የተገናኘ ኣይደለም። ማንነት በነገራችን ላይ የሚቀየር፣ የሚያድግ ነገር ነው። ትናንትና ሙስሊም የነበር ዛሬ ክርስቲያን ቢሆን ማንነቱን ቀየረ ማለት ነው። ባህላዊ ማንነትም እየተቀየረ ሊሄድ ይችላል። ዜግነትም ይቀየራል። በመሆኑም እግራችን ሲርቅ ያለንበት ኣካባቢ ባህል ሲውጠን ስሜታችን ሁሉ ስብርብር ይላል ማለት ኣይደለም።

ወደ ጫልቱ የሰባተኛ ክፍል ብሽሽቅ ጉዳይ እንመለስና መምህር ጽጌ ያን ዱርየ ሳምሶንን ኣንዴ ሲዠልጡት ኣልቅሶ ቆይ ሰኔ ሰላሳ እንገናኛለን ነው ያለው። ጫልቱ ማድረግ የነበረባት ይህንን ነው። የሚሰድቧትና የሚያበሽቋት ህጻናት በኣስተማሪዎች የተላኩ ኣይደሉም። ስለዚህ ማድረግ የነበረባት ለመምህር ጽጌ መናገርና ጸጥ ማሰኘት ነው።

ደራሲው ጫልቱን ከሚገባው በላይ ስሜቷን ለመስበር ይሞክራል።ኣንባቢን ከንፈሩን ለማስመጠጥ ይሞክራል። ይሁን እንጂ የሄለንን ህይወት የወሰደበት መንገድ እሱ እንዳሰበው ኣንባቢ እንዲሰማው የሚያደርግ ኣይደለም። ራሱ ደራሲው እነዚያ የኣንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ስሜቱዋን ሁሉ ዖሮሞ ከመሆኑዋ ጋር ኣያይዞ እንዲሰብሩዋት ያደርግና በተሰበረ ስሜት ወደ ቆፍቱ ለእረፍት ይልካታል። በዚያ ደግሞ ስሟን በመቀየሯ መሳቂያ ያደርጋታል። ቆፍቱ ስትሄድ ኣክስቷ ኣማርኛ ብቻ ተናገሪ ኦሮምኛ ኣልችልም በይ ኣለቻት ይለናል። እንደዚህ ይባላል? ለማናቸውም እረፍት ጨርሳ ወደ ኣዲስ መጣች።ወዲያው ደግሞ በትምህርቷ ብዙ ሳትገፋ ከዘጠነኛ ክፍል ኣካባቢ ኣቋርጣ ትዳር መሰረተች ይለናል።

የሚገርመው ሄለን ያገባችው ኣውራጃ ኣስተዳዳሪ ነው። ስርዓቱ ምን ያህል ተቀብሏታል ማለትነው? ኣዲስ ኣበባ ውስጥ ያለ ኣውራጃ ኣስተዳዳሪ ጫልቱን ከነንቅሳቷ በፍቅር ወድቆ፣ ብዙ ቆንጆ ባለበት ኣዲስ ኣበባ ጫልቱ ኣሸናፊ ሆና ኣውራጃ ኣስተዳዳሪ ማግባቷ የሚያሳየው ከነዚያ ከህጻናት ከነሳምሶን ውጭ ከፍተኛ ከበሬታና ተቀባይነት ኣላት ማለት ነው። ባሏም ደስ ብሏት ኣብራው እየኖረች ነበር። ኣገር ዘመድ ኣውራጃ ኣስተዳዳሪ ኣገባች ብሎ ሳይኮራ ኣልቀረም። በዚያን ጊዜ ኣውራጃ ኣስተዳዳሪ መወሸም እንኳን ለሴቶች እንደ ትምክህት እንደነበር ኣይዘነጋም።
ከዚህ ተነስተን የሄለን ህይወት ሰመረላት ኣለፈላት ወደሚባል የህይወት መስመር ውስጥ እንደገባች መረዳት ያስችላል። ይህቺ ልጅ ገረድ ኣይደለም የሆነችው። ኣውራጃ ኣስተዳዳሪ ነው ያገባችውና።
ደራሲው ሄለን ኣውራጃ ኣስተዳዳሪ ኣግብታ እያለ በመሃል ኢህዓዴግ ኣዲስ ኣበባን እንደተቆጣጠረ ይነግረናል። ከዚህ በሁዋላ ኣውራጃ ኣስተዳዳሪው ባሏ ወደ ወህኒ ሲወርድ ምን ኣልባትም ሃብትና ንብረቱንም ኣጣ። የዚህን ጊዜ ሄለን ወይም ጫልቱ ትልቅ ችግር ላይ ወደቀች። ለባለቤቷ ስንቅ እንኳን ማቀበል ተሳናት። ትዳሯ ፈረሰ። ጎጆዋ ዘመመ። ከሁሉ የሚያሳዝነው ደራሲው በራሱ ኣንደበት
“ለባሏ ስንቅ ማቀበያ ቀርቶ ለራሷም የምትመገበው አልነበራትም።” ይላል።

ይልቅ ይሄ ኣንጀቴን በላው። የኣንድ ኣውራጃ ኣስተዳዳሪ ሚስት ያላትን ሁሉ በኣጭር ጊዜ ውስጥ ኣጥታ የምትበላው ሁሉ ስታጣ የለውጡን ኣስከፊነት ያሳያል። የምትበላው ብቻ ሳይሆን ማደሪያም በመቸገሩዋ ኣንድ ካፌ ውስጥ እየሰራች መተዳደር ጀመረች። ትንሽ ቤት ተከራይታ መኖር ጀመረች። ቤታቸውም ተወረሰ ማለት ነው። ይህ ኑሮ ለኣንድ ኣውራጃ ኣስተዳዳሪ ሚስት ከባድ ነበር። ስሜትን ይጎዳል።

ደራሲው ቀድሞ ለወሰነውና ሊያስተላልፍ ላሰበው ጭብጥ ሲል ሄለንን እንደፈለገው ሲያናግራት እናያለን። ወደ መጨረሻ ወጉን ሲቀጥልልን ይህቺ የኣውራጃ ኣስተዳዳሪ ሚስት ደርግ ወድቆ ኢህዓዴግ በገባ ሰሞን ቴለቪዥን ትከታተል ነበር ይለናል። ከዚያ ኣንድ ቀን “ጭቆና” የሚለውን ቃል በቴሌቪዥን ስትሰማ ጊዜ ለመረዳት ጥረት አድርጋ ነበር ይላል ደራሲው። ይሄ ኣይመስልም። ይህቺ ልጅ በስርዓት ደረጃ ጭቆናን በህይወቷ ኣላየንም።ማነው የጨቆናት። የት ቦታ ጭቆናን ኣየች። እንዴውም ኢህዓዴግ ራሱ የጨቋኝ ሚስት ብሎ ኣለማሰሩም ኣንድ ነገር ነው። የኣንደኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ ያውም እነሳምሶን ኣበሸቋት ማለት ወደዚህ ከፍ ያለ ማህበራዊ ጉዳይ ኣያመጣንም። ከሁሉ በላይ ማህበራዊ ለውጥ እንዲህ ቀላል ነገር ኣይደለም። በኣንዴ በቴለቪዥን ስታይ ኣሃ! ብላ ጭቆናን ተገነዘበች ለማለት ኣይቻልም።በቀጥታም ባይሆንም የኣውራጃ ኣስተዳዳሪ ባል ኣግብታ ያለፈውን ስርዓት የቀመሰች ሴት በትምህርት ቤት ብሽሽቅ “ጭቆና!” ትላለች ለማለት እኛ እራሳችን ልጅ መሆን ሊኖርብን ነው።

ደራሲው እነዚህን የማይመስሉ ነገሮች ሁሉ ኣንስቶ ጫልቱ የማንነት መምታታት ውስጥ እንደገባች ሊያሳየን ይሞክራል። በመሰረቱ የብሄርን ማንነት ከስም ጋር ኣያይዞ የማንነት መምታታት ውስጥ ለመግባትና ለመጨነቅ እውቀት ይጠይቃል። ስለብሄር ፖለቲካ መማር በዚያ መጠመቅ የመንፈስን መረበሽ ሊያመጣ ይችላል። ይህቺ ለግላጋ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ በስም ለውጧ ምክንያት ተጨንቃ፣ ኣሁን እኔ ሄለን ነኝ……. ጫልቱ ነኝ……..ጫልቱን ፈልጌ ኣጣሁት ከውስጤ…….. ብላ በመጨነቅ ሰውነቷ ከስቶ ለሞት ደረሰች ማለት በሬው ወለደ ከሚለው ጠብደል ፈጠራ ኣይተናነስም:: ታዲያ ጫልቱን ምን ገደላት? ካልን ወያኔ ኢሃዲግ ኣዲስ ኣበባ ሲገባ ትዳሯን ኣፍርሶ ሜዳ ላይ ጥሏት ስለነበረ፣ የሚበላ ስላጣች፣ ተስፋ ስለመነመነባት፣ በብስጭት ኩርምት ብላ ነው የሞተችው። ማን ገደላት ካልን ወያኔ ኢህዓዴግ ኣበሳጭቶ ተስፋ ኣሳጥቶ ለበሽታ ሰጥቶ ነው የገደላት ለማለት ጠንካራ መረጃ ኣለን። ይህቺ ልጅ የሁዋላ ታሪኳ ማለትም ያለእድሜዋ ማግባቱዋ፣ ሁዋላም ኣዲስ ኣበባ ስትመጣ ለባህል ግጭት (culture shock) መጋለጧ በተለያየ ደረጃ የጎዱዋት የህይወት ልምዶች ቢሆኑም ከዚያ በሁዋላ ኣግብታ ኣካባቢውን ለምዳ ትኖራለች ተብሎ ነው የሚታሰበው።
የዚህ ጽሁፍ ደራሲ በቅርቡ በኣንድ ስብሰባ ላይ ሲናገር ለጫልቱ ሃውልት ይገባታል ሲል ሰምቻለሁ። በዚያ ኣልከራከርም።ለሃውልት የሚያበቃ ነገር ካለ ችግር የለውም። በሚሰራው ሃውልት ላይ ግን የሚጻፈው የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች ብሽሽቅ ሳይሆን ወያኔ ኢሃዴግ ትዳሯን ኣፍርሶ ሜዳ ላይ ስለጣላት ለሞት የተዳረገችው ጫልቱ ተብሎ መሆን ኣለበት።

ማጠቃላያ
“ጫልቱ እንደ ሄለን” ጭብጡ በጣም የቀለለብኝ የኣንድን ሰው ህይወት ኣንስቶ ማህበረሰብን ወክሎ ለማሳየት ስለሞከረ ኣይደለም። ደርሶ ማጠቃቃለል (hasty generalization) የሚባለው እዚህ ጋር ኣይሰራም። የኣንድ ሰውን ይወት እየተረኩ የማህበረሰብን ህይወት ቁልጭ ኣድርጎ ማሳየት ይቻላል። ዋናው ግን የተሳሉት ገጸ ባህርያት ያንን ልናሳይ የምንፈልገውን ማህበረሰብ ህይወት የሚወክል ባህርይ ስንፈጥርላቸው ይመስለኛል። ጫልቱ እንደ ሄለን በሚለው ውስጥ የኦሮሞ ወገኖቼን ብሶት ማሳየት ኣይቻልም። ከሁሉ በላይ ደራሲው የሲስተም ሽብር ያለውን ጉዳይ ለማሳየት ህጻናት ዋናውን ድርሻ መያዛቸው ልቦለዱ እንዲወርድብኝ ኣድርጓል።
ይህንን ካልኩኝ በሁዋላ ግን የኦሮሞ ህዝብ ብሶትና እንግልት ባለፉት ስርዓቶች ሁሉ ያሳለፈው ጉዳት ከስም ለውጥ ከኣተቴ ልምድ ያለፈ ነው። የኦሮሞን ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ክፍፍል፣ የፖለቲካ ውክልና ጥያቄዎች እንዲህ ባሉ በስያሜ በምናምን ማውረድ ተገቢ ኣይደለም።ኢትዮጵያን ከኦሮሞ ውጭ ማየት ኣይቻልም። ይህ ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ታሪክ ያለው ከሌሎቹ ወንድሞቹ ጋር ለሃገሩ መስዋዕት ሲሆን የኖረ ልበ ሰፊ ህዝብ ነው። ይሁን እንጂ በመጡት ስርዓቶች ሁሉ ተጠቅቱዋል። በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊው መስክ ተጎድቱዋል። ይህ ማለት ግን ሌላው ወገኑ ኣልተጎዳም ማለት ኣይደለም። ሁሉም ቡድኖች በተለያየ ቅርጽና ይዘት ተጎድተዋል። የኦሮሞው ህዝብ ኣሁን ያለው ፍላጎት ብሄርን ነጥሎም ይሁን በጅምላ የሚደረግ ጭፍጨፋ ይቁም እኩልነት በሃገራችን ይስፈን ነው። ይህ ጥያቄው ደግሞ ተገቢና እውነተኛ ነው። በቋንቋው በኩል ኦሮምኛ ኣንዱ ዋና መግባቢያ ቋንቋ መሆን ኣለበት። ከዚያ ውጭ ግን ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ሲኖር ኣንዳንድ የኦሮሞ ተወላጆች የኣማራ ስም ወይ የትግሬ ስም ወይ የወላይታ ስም ኣውጥተዋል ብሎ የሚከፋ ኣይደለም። ኣማራ ሆነው የኦሮሞ ስም ያላቸው ብዙ ኣሉ። የደቡብ ተወላጅ ሆነው የኦሮሞ ስማ ያላቸው ሰዎችና ቦታዎች ብዙ ናቸው። በመሆኑም የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ ከፍ ኣርጎ ማየትና ከፍትሕ ከዴሞክራሲ ኣንጻር መመለስ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው። በኢትዮጵያ የሚኖሩ ብሄሮች ሁሉ ኣንዱ የኣንዱን ብሶት በመረዳትና እውቅና በመስጠት ተከባብረው ሲኖሩ ጥያቄዎቻቸው ይፈታሉ። ከዚህ ውጭ ግን ባህል ለመካፈል፣ ባህልን ሰጥቶ ለመቀበል፣ ለዘመናዊነት ክፍት መሆን በጣም ኣስፈላጊ ነው።

እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ

geletawzeleke@gmail.com


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>