ከአሸናፊ ደምሴ
በ63 ዓመት እድሜው ላይ ይገኛል። ከ44 ዓመታት በላይ በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ አገልግሏል። በርካታ ሙዚቃዊ ቴአትሮችን ሰርቷል። ከሚታወስባቸው ሥራዎቹ መካከል “የት ሄደሽ ነበር?”፣ “እሁድ የቁብ ጠላ” እና በቅርቡ “ትዝታ” የተሰኘው ሙዚቃዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው። ይህ አርቲስት “ስነ-ስቅለት፣ እሳት ሲነድ፣ ነቃሽ፣ ጤና ያጣ ፍቅር፣ ሶስተኛው አይን፣ ሰዓት እላፊን” ጨምሮ ከ39 በላይ ቴአትሮችን ተጫውቷል፤ 12 የቲቪ ድራማዎችንና 16 ሙዚቃዎችን ሠርቷል። በፊልሙም ቢሆን አልቦዘነም። ሔርሜላ፣ አዶናይ፣ መክሊትና ወፍራሙ ዱርዬ “በተሰኙት ፊልሞች ላይ ተሳትፏል። ጡረታ የወጣ ቢሆንም ብዙ የመስራት አቅም ያለው አርቲስት ፋንቱ ማንዶዬ፤ በዚህ ሳምንት የመዝናኛ አምድ እንግዳችን ሆኖ ዘና የሚያደርጉ ወጎችን ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ተጨዋውተዋል፤ መልካም ንባብ።
ሰንደቅ፦ ጥያቄዬን ስለእድሜ በማውራት ብንጀምር ደስ ይለኛል። ለአንተ የ63 ዓመት እድሜ ባለፀጋ መሆንህ ምን የተለየ ትርጉም አለው?
ፋንቱ፦ ዕድሜ ለኔ ትምህርት ቤቴ ነው። ብዙ ተምሬበታለሁ። ስህተቶቼን አርሜያለሁ፤ ቆንጆ ስራዎቼን ደግሞ ተከትያለሁ። ከስህተቶቼ መካከል መጠጥ መጠጣት፣ ሲጃራ ማጨስ ፣ ጫት መብላት የሚጠቀሱ ናቸው። እነሱን አርሜ አሁን በትክክለኛው መስመር ላይ ነኝ።
ሰንደቅ፦ አሁን ላይ ሆነህ ስታስበው ባላደርገው ኖሮ ብለህ የሚቆጭህ ነገር አለ?
ፋንቱ፦ እውነቱን ለመናገር አሁን ላይ ባላደርገው ኖሮ ጥሩ ነው ብዬ የምቆጭበት ምንም ነገር የለም። ያደረኩትን ሁሉ እንኳን አደረኩት፤ ምክንያቱም ባላደረገው ኖሮ አልማርበትም ነበር። ወይም የምማርበት ነገር አላገኝም ነበር ማለት ነው። ስለዚህ ባለፈው ዘመኔ ራሴ ባደረኳቸው ነገሮች መጥፎና ጥሩነታቸውን በተግባር ለይቼባቸዋለሁ፤ ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ ብልጥ ከኔ ይማር እኔ ግን ከራሴ ተምሬያለሁ የምለው።
ሰንደቅ፦ በተቃራኒው ባደርገው ኖሮ ብለህ የምትመኘው ነገር ግን፤ ያላደረከው ምንድነው?
ፋንቱ፦ እኔ ያላደረኩት ነገር የለም። ብዙ ነገሮችን ባደርጋቸው ብዬ እንደ አቅሜ ተመኝቼ አድርጌያለሁ። በመሆኑም ይህ ቀርቶብኛል ብዬ የሚቆጨኝም ነገር የለም። ሁሉም ነገር ለኔ ጥሩ ነው።
ሰንደቅ፦ የተወለድከው በ1944 ዓ.ም ሲሆን ከማዘጋጃ ቤት በ2002 ዓ.ም ከስራ በጡረታ ስትገለል ደግሞ 44 ዓመታትን በስራ አሳልፈሃል፤ እንዴት ነው 44 ገጠመልህሳ?
ፋንቱ፦ እውነት ነው፤ በ1958 ዓ.ም ነው ከፈጥኖ ደራሽ ጋር ስራዬን የጀመርኩት። ከዛም ማዘጋጃ ገብቼ ለ44 ዓመት ካገለገልኩ በኋላ በ2002 ዓ.ም ሐምሌ ወር ላይ ነው በጡረታ የተሰናበትኩት። 44 ዓመት በስራ መቆየት ያውም በምትወደው ኪነት ውስጥ በጣም መታደል ነው።
ሰንደቅ፦ የ44 ዓመታት ያንተ የኪነት ህይወት ምን ይመስላል?
ፋንቱ፦ በመጀመሪያ የኪነት ህይወታችን በዘመናችን ጥሩ ነበር። በእኛ ዘመን ተወዛዋዥ ብቻ ነኝ፤ ዘፋኝ ብቻ ነኝ፤ ተዋናይ ብቻ ነኝ ብሎ ነገር አይሰራም። ሁላችንም በሁሉም መስክ እንድንሳተፍ ይደረግ ነበር። እወዛወዝ ነበር፤ በቴአትር ውስጥ በትወና እሳተፍ ነበር። ሰልፍ ሲኖር ደግሞ ከባንዱ ጋር ዘንግ ወሪዋሪም ሆኜ እሰራ ነበር። በአጠቃላይ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ያሉ ስራዎችን ሁሉ የኔ ስራ ይሄ ብቻ ነው ሳንል ነበር የምንሰራው። አስተማሪዎቻችን ደግሞ በባህል በኩል ለማ ገ/ህይወት፤ በዘመናዊው ተፈራ አቡነወልድ ነበሩ። ጥሩ አስተማሪዎች ነበሩን። አሁን እኔ ለምሳሌ ከፈጥሮ ደራሽ ስመጣ ዘንግ ወርዋሪ ነበርኩ። እሱን ብቻ ብሰራ ኖሮ 44 ዓመት ሙሉ ዘንግ ወርውሬ አልችለውም ነበር። ነገር ግን ዘንግ ውርወራን እየሰራሁ ድምጻዊነት፤ ከዚያም ሙዚቃዊ ድራማ ላይ በተዋናይነት ቀጥሎም በሙሉ ተዋናይነት ነው የሰራሁት።
ሰንደቅ፦ ስለልጅነትህ ሳነብ ለእግር ኳስ የነበረህ ፍቅር ልዩ መሆኑን ተረድቻለሁ። በኋላ ደግሞ አርቲስት ሆነሃል፤ እስቲ ወደኪነጥበቡ መንገድ እንዴት እንደመጣህ አጫውተኝ?
ፋንቱ፦ እንግዲህ በልጅነቴ ኮልፌ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብቼ ስለነበር እግር ኳስና ቮልቮል መታወቂያችን ሆኖ ነበር። በኃላፊነት ያሳድገን የነበረው ማዘጋጃ ቤት ነው። እዛ እያለን መጋቢያችን “ቱቶ” ይባላል፤ ታዲያ ኳስ ስንጫወት ምሳ ሰዓት ደረሰ፣ አልደረሰ ማንም ትዝ አይለውም። መጋቢያችን መጥቶ በዱላ እያባረረ ወደ ምግብ አዳራሹ ያስገባናል፤ እኛም ያው ነካ-ነካ አድርገን በልተን ወደጨዋታችን ነው የምንመለሰው። እኔ ኳስ በጣም ነበር የምወደው፤ በ11 ቁጥር ተሰላፊ ነኝ። ከዚያ በኋላ ግን ወደማዘጋጃ ቤት ስመጣ ሁሉንም ነገር ተውኩና ወደመጠጡ ገባሁ። ብዙ እጠጣ ነበር።
ሰንደቅ፦ ወደመጠጡ እንድትገባ የገፋፋህ ምንድነው?
ፋንቱ፦ እውነቱን ለመናገር ቤተሰቦቻችን ይመስሉኛል። ልጅ እያለን ጠላ ግዙ፣ ጠጅ ግዙ እየተባለን እንላክ ነበር። ያም ሆኖ “ልጅ አይጠጣም፤ ዞር በል” እየተባልክ ታድጋለህ። ይህም በመሆኑ መቼ አድጌ በጠጣሁ የሚያሰኝ እልህ ውስጥ ትገባለህ። ትልቅ የመሆን ጉጉቴ ነው ለመጠጥ ሱስ የዳረገኝ ብዬ አስባለሁ። ታዲያ ኮልፌ ካገባሁ በኋላ እዛው ጴጥሮስ ወጳውሎስ አካባቢ ሰንበቴ ቤት ጠላዋን መቀማመስ ጀመርኩ። በዚህም ምክንያት ስራ ጀምሬ ደሞዝ ሳገኝ ያን ጊዜ ቂም የያዝኩትን ነገር ለመበቀል ሮጬ ጠጅ ቤት ላይ ነው ያረፍኩት(ሳቅ)። ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ የጃንሆይ የ20 ብር ደሞዝተኛ ነበርኩ። በደሞዜ ለ20 አመታትም ሳላቋርጥ ጠጥቻለሁ። የዛሬ 24 ዓመት መጠጥ ባላቆም ኖሮ አሁን ድረስ በሕይወት አልቆይም ነበር።
ሰንደቅ፦ የመጀመሪያው ደሞዝህ 20 ብር ከነበረ በጡረታ ከመሰናበትህ በፊት የመጨረሻው ደሞዝህ ስንት ነበር?
ፋንቱ፦ ያኔ በጃንሆይ ጊዜ ምግባችንና ማደሪያችን ተችለን ነበር 20 ብር የሚከፈለን። 44 ዓመታት አገልግዬ ጡረታ ስወጣ ደሞዜ 1ሺ472 ብር ነበር። የሚገርምህ ነገር ዛሬ አንተ ስትጠይቀኝ መንግስት ለጡረተኛውም ባደረገው ማስተካከያ መሰረት የማገኘው ደሞዝ 1ሺ460 ብር ሆኖልኛል (ሳቅ) ስለዚህ ጡረታ እንደወጣው አይሰማኝም ሙሉ ደሞዜን እያገኘሁ ነው።
ሰንደቅ፦ ከማዘጋጃ በጡረታ ተሰናብተሃል። እኔ ደግሞ ያገኘውህ እዚሁ ማዘጋጃ ቤት ነው። እንዴት ነው የግቢው ፍቅር?
ፋንቱ፦ ይህ ግቢ በኔ ህይወት ውስጥ ትልቁ ትምህርት ቤቴ ነው። ልጆች ያፈራሁበትና ያደኩበት ቤት ነው። ከምንም ቦታ እዚህ ስመጣ ነው ደስታ የሚሰማኝ። አንደኛ እዚህ መጥቼ ሙዚቃ ነው የምሰማው፤ አሁንም ደግሞ መስራት ስላላቆምኩ አንዳንድ ጥናቶች ሲኖሩብኝ ፀጥታ ስላለ እዚህ ነው የማጠናው። ጓደኞቼን የማገኘውም እዚሁ ነው። ሕይወቴን በአብዛኛው ያሳለፍኩበት ግቢ በመሆኑ መስሪያ ቤቴን በጣም እወደዋለሁ።
ሰንደቅ፦ ከዘውግ ወርዋሪነት በቀዳሚነት ወደተወንክባቸው ቴአትሮች እንለፍና ያለህን ትውስታ አካፍለኝ፤ አብዛኞቹ ሙዚቃዊ ድራማዎች ናቸው?
ፋንቱ፦ እንግዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ቴአትር የሰራሁት ለስልጠና ተብሎ ወደብሔራዊ ቴአትር በተላኩበት ወቅት ነበር። “ስነ -ስቅለት” የተሰኘ ቴአትር እየተሰራ ነበር። ያኔ ያየሁት ነገር አሁን ድረስ ከአምሮዬ አይወጣም፤ ሙዚቃና ቴአትር በዚያ ደረጃ ተዋህደው አሁንም ቢሆን አይቼ አላውቅም። ከዚያ በኋላ ለኔ ሙዚቃዊ ተውኔት “እሳት ሲነድ” ነው። ይህን ቴአትር የመጀመሪያው ሙዚቃውን የፃፈው ተፈራ አቡነወልድ ነው። ያዘጋጀው ደግሞ አባተ መኩሪያ ነው። የቴአትሩ ድርሰት ደግሞ አያልነህ ሙላቱ ነው። እንዳልከው ስራዎቼ በአብዛኛው ሙዚቃዊ ድራማ ይዘት ያላቸው ናቸው። ስጀምር “የት ሄደሽ ነበር?” አለ፤ በ1963/64 የተፈራ አቡነወልድ ድርሰት ነው። ከዚያ በኋላ “እንጮኛዬ ናት” የሚለው ድራማ ተከተለ። ከዚያ ደግሞ “ጤና ያጣ ፍቅር” የተሰኘ ድራማ ሰራሁ። ቀጥሎ የአዲስ አበባ ኮረዳና “ምን ጠጅ አለና?” የሚሉ ስራዎችን ሰራሁ አብዛኞቹ የተፈራ አቡነወልድና የንጉስ ረታ ስራዎች ናቸው።
ሰንደቅ፦ “የትሄደሽ ነበር” የተሰኘው ስራ ሲነሳ አንተ አትረሳም፤ እስቲ ስለዚያ ሙዚቃዊ ድራማ ንገረኝ እንዴት ተመረጥክ እንዴት ሰራኸው?
ፋንቱ፦ በመጀመሪያ ስራው ሲሰራ እኔና ስንዱ ደረሰ (አሁን ጣሊያን ሀገር ነው ያለችው) አብረን ነው የሰራነው። ከዚያ በኋላ በ1970 ዓ.ም እኔና ፀሐይነሽ በቀለ የሰራነው ነው በድጋሚ የተቀረፀው። ይህ ስራ የተፈራ አቡነወልድ ነው፤ እሳቸው ናቸው የመረጡኝ። የድራማ አቅም ስለነበረኝ ያኔ ፀጉሬን ሸበቶ ለማስመሰል ቾክ ተቀብቼ ነው የሰራሁት። አሁን ግን ትክክለኛው ቾክ (ሸበት) መጥቷል። (ሳቅ) የሚገርመው ስራውን በሰራንባቸው መድረኮች ሁሉ ጥሩ አቀባበል አግኝተናል። ነገር ግን እኛ ስራውን መድረክ ላይ ብቻ ሳይሆን ሰርግ ላይም እንሰራው ነበር። አንዳንዱ ምንም አይመስለውም። አንድ ቀን ግን ወደፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ አንድ አፈ ንጉስ ልጃቸውን ሲድሩ ሄደን ስንሰራው አቶ ለማ ገብረሕይወት ናቸው ያተረፉን። ሰውዬው “እንዴት በኔ ሰርግ ላይ ሻይ ቡና ይበቃል ይባላል?” ብለው አምጡት ብለው ሊገርፉኝ ነበር። ከዚያ በኋላ ደግሞ እቴጌ ሆቴል ላይ በተዘጋጀ ሰርግ ስንሰራ አንድ አባት ናቸው፤ ስሰራ በጣም ደስ ብሏቸው ሲያዩኝ ቆዩና መጨረሻ ላይ ጠሩኝና “እንዴት ሰርተህ ሰርተህ ታጨማልቀዋለህ፤ ወዲያው እሺ ማለት አልነበረብህም” ማለታቸው ትዝ ይለኛል(ሳቅ)
ሰንደቅ፦ ድምፅህ አሁን ድረስ ጥሩ ነው፤ ከወጣቶች ጋር በአጃቢነት (በፊቸሪንግ) ስለመስራት ምን ታስባለህ?
ፋንቱ፦ በቅርቡ “ትዝታ” የሚል ዘፈን ከአንድ ልጅ ጋር ሰርቻለሁ። ትዝታ ሰርቼ ባላውቅም በመካከላችን ያለው የድምፅ ልዩነት በራሱ አንድ ውበት ሆኗል። ህብረ-ዝማሬ ግን ብዙ ጊዜ እሰራለሁ። የህብረ-ዝማሬ ሙዚቃን ነርሲስ ናልቫንዲያን ጥሩ አድርገው አስተምረውኛል። ወደፊትም ስራው ካለ በደንብ መስራት የምችል ይመስለኛል።
ሰንደቅ፦ በፊልም ደረጃም እየተሳተፍክ ነው። በአዶናይ፣ መክሊት፣ ሔርሜላና ወፍራሙ ዱርዬ የተሰኙ ፊልሞችን ሰርተሃል። ፊልም ትመርጣለህ? ወይስ ክፍያህ ውድ ሆኖ ነው ብዙ ያልሰራኸው?
ፋንቱ፦ ክፍያዬ ውድ ስለሆነም፤ ፊልም ስለምመርጥም አይደለም። ነገር ግን እኔን የሚፈልጉ ሰዎች ሲመጡ ነው የምሰራው። አንዳንዶቹ ይመጡና ፍራንክ የለንም ይሉሃል። በመጀመሪያ አንድ ሰው ፍራንክ ከሌለው ፊልምን ያህል ስራ ለምን ይጀምራል? ያንን ነገር አልደግፈውም። እኔም ፍራንክ ስለሌለኝ እንጂ ስንት የምሰራው ስራ ነበር (ሳቅ)። ፊልም በተለይ ገንዘብ ሳይኖርህ የምትሰራው ስራ አይደለም። ብዙ ስራዎችን ብሰራም ለምን እንደሆነ አይገባኝም አብዛኞቹ የተነጋገሩትን እንኳን አይከፍሉም። በዚህም ምክንያት ብዙ ፊልሞችን ሳልሰራ ቀርቻለሁ። አሁን በቅርቡ ግን አንድ አዲስ ፊልም ሰርቻለሁ፤ ይወጣል።
ሰንደቅ፦ በትወና ብዙ ሰርተሃል ላንተ ፈታኝ የነበረው የቱ ነው?
ፋንቱ፦ ከቴአትር ወደፊልም ለሚሄድ ባለሙያ ፊልም ትንሽ ቴክኒኩ ከበድ ይላል። ግን ጥሩ አዘጋጅ ካገኘህ ደግሞ በቀላሉ ትሰራዋለህ። ከቴአትር ግን አሁን በቅርብ እንሰራው የነበረው “ሰዓት እላፊ” ቴአትር በጣም ነው የከበደኝ። ለምንድነው? ገፀባህሪው ዕድሜው 60 ዓመት ሆኖ “አክት” የሚያደርገው ደግሞ እንደ 25 ዓመት ወጣት ነበር፤ ይህ በጣም ፈትኖኛል። ነገር ግን ከአዘጋጁ ጋር በመነጋገር ጥሩ አድርገን ሰርተነዋል።
ሰንደቅ፦ ምን ያዝናናሃል?
ፋንቱ፦ እዚህ ቴአትር ቤት ስመጣና ጓደኞቼን ሳገኝ በጣም ዘና እላለሁ። በተረፈ ፊልሞችን አያለሁ። አብዛኛውን የፈረንጅ ፊልሞችን አልፎ አልፎ ደግሞ አገራችንን ስራዎች በማየት እዝናናለሁ። ከዚያ በተረፈ ከረንቡላ እጫወታለሁ።
ሰንደቅ፦ ጋሽ ፋንቱ ከሆሊውድ ተዋናይ ሞርጋን ፍሪ ማን ጋር ይመሳሰላል የሚሉህ ሰዎች አሉ አንተ ምን ትላለህ?
ፋንቱ፦ የሞርጋን ፍሪማን ብዙ ፊልሞችን አይቻለሁ። ድምፁ በጣም ደስ የሚለኝ ተዋናይ ነው። ከኔ ጋር እንደምንመሳሰልም አውቃለሁ (ሳቅ)። የሚገርምህ ነገር ባሳለፍነው ሳምንት ባዛር ሲከፈት ተገኝቼ ነበር። እዛ አንድ ኬኒያዊ በግድ ሞጋን ፍሬማን ነህ ብሎ ፎቶ አብሮኝ ተነሳ፤ እኔ ግን ፋንቱ ማንዶዬ ነኝ አልኩት። እስራኤል ሀገርም በሄድኩ ጊዜ ጣሊያኖች ያረፍኩበት ሆቴል አግኝተውኝ አብረውኝ ፎቶ ካልተነሳን አሉኝ “ሞርጋን ፍሬማን አይደለሁም ብልም አልሰሙኝም። ብዙዎች ከሞርጋን ጋር ያመሳስሉኛል።