‹ እስረኞች መብት አላቸው፡፡ አንዳንድ እስረኞች ግን ከሌሎቹ የተለየ መብት አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ ምንም መብት የላቸውም››
ዛሬ ወደቃሊቲ አቅንተን ነበር፡፡ የእነ አቶ በቀለ ገርባ፣ የአዛውንቱ ሲሳይ ብርሌ፣ የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ምክር፣ ትንታኔና ተስፋ አንዳች ጥንካሬ ይሰጣል፡፡ የእነዚህ ታሳዎች ጥንካሬ ቃሊቲ እስር ቤት መሆኑን ሁሉ ያስረሳል፡፡
መጀመሪያ እነ በቀለ ገርባን ጠይቀን ነው ወደ ጋዜጠኛው ያቀናነው፡፡ ውብሸትን ለመጠየቅ ስናቀና የገቢዎችና ጉምሩክ ምክትል የነበረው ገብረወሃድ እስረኞች ከሚጠየቁበት ውጭ አንድ ጥግ ላይ ከቤተሰቦቹ ጋር ሰብሰብ ብሎ አየነው፡፡ እስረኞች ወደሚጠየቁበት ስናመራ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዳይሬክተር የነበረው መላኩ ፋንታና ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ለመጠየቂያነት የተከለለው ቦታ ላይ ጎን ለጎን ቆመው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እያወሩ ደረስን፡፡
ከውብሸት ጋር ለተወሰኑ ደቂቃዎች ካወራን በኋላ ይበቃል ተባለ፡፡ ገና ወደ ውብሸት ስንመጣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የነበሩት መላኩ ፋንታ አሁንም ከቤተሰቦቻቸው ጋር እያወሩ ነው፡፡ ገብረ ወሃድም እንደዛው፡፡ እንግዲህ በእስረኞች መካከል የሚፈቀደው የሰዓት ገደብም ይለያያል ማለት ነው፡፡ ለ‹‹አሸባሪ›› ጋዜጠኛ 10ና 20 ደቂቃ፣ ለ‹‹ኪራይ ሰብሳቢ›› ባለስልጣን ደግሞ የፈለገውን ያህል ጊዜ ይሰጣል፡፡
ያቆሰለኝ ግን ይህ አይደለም፡፡ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ከእናትና አባቷ ውጭ በማንም አትጠየቅም፡፡ እህቷ እስከዳርና እጮኛዋ ጋዜጠኛ ስለሽ ሀጎስ ርዕዮትን መጠየቅ ይቅርና ወደ ግቢው እንዳይገቡ ተከልክለዋል፡፡ ውብሸትን ጠይቀን ስንወጣ ለመረዳት እንደቻልኩት እስረኞች ከሚጠየቁበት ውጭ አንድ ጥግ ይዞ ከቤተሰቦቹ ጋር ሰብሰብ ብሎ (ወንበርና ጠባብ ጠረጴዛ ነገር ቀርቦላቸዋል) በዓል እያከበረ የነበረውን ገብረወሃድ ብቻ አልነበረም፡፡ በእጮኛዋና በእህቷ እንዳትጠየቅ ከተደረገችው ርዕዮት ዓለሙ ጋር ታስራ የምትገኘው የገብረ ወሃድ ባለቤት ኮሎኔል ኃይማኖት ከባለቤቷና ከቤተሰቦቿ ጋር ሆና በዓል እንድታከብር ተፈቅዶላታል፡፡
የእኔ ጥያቄ ለምን እነ ገብረወሃድ ተፈቀደላቸው አይደለም፡፡ ነገር ግን ርዕዮት በእጮኛዋና በእህቷ እንዳትጠየቅ በተደረገችበት ወቅት እነ ገብረወሃድና ከርዕዮት ጋር ታስራ የምትገኘው ባለቤቱ ያለ ምንም የሰዓት ገደብ እንዲያውም እስረኞች ከሚጠየቁበት ክልል ውጭ በዓል እንዲያከብሩ መደረጉ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ‹‹እስረኞች መብት አላቸው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ እስረኞች ከሌሎቹ የተለየ መብት አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ ምንም መብት የላቸውም›› የሚል ያልተጻፈ ህግ እንዳለ ያሳያል፡፡ ህግ በእንሰሳዊ ስልት ለሌቦች አድልታ ስለ እውነት ለቆመችው፣ በብዕሯ ለህዝብ ለማሳወቅ ለጣረችው ወጣት ፊቷን ስታዞር አበቃላት፡፡ ይህ ርዕዮት ላይ ሆኗል፡፡ በቃሊቲ፣ በኢትዮጵያ ፍትህ እንዲህ አብቅቶላታል፡፡