Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

“ሀገርን እግዚአብሄር ካልጠበቀ ሰራዊቱ በከንቱ ይደክማል”

$
0
0

ሥርጉተ ሥላሴ 27.09.2014 / ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ/

ይህ ቃል አካል የሌለው ዬህዝብ አገለጋይ የሆነው ቃለ ወንጌል ነው። እንዴት ናችሁ የእኔዎቹ? እንኳን ለአዲሱ ዘመን እንዲሁም ለተዋህዶ አማንያን እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ – አደረሰን። ጠፍቼ ከረምኩ ባለመቻል። ንፍቅ አላችሁኝ።

ብዙ ሰው በጣም የሚጨነቅበት – የሚጠበብት መሰረታዊ ጉዳይ የሠራዊት መኖርና አለመኖር። የመሳሪያ – መጠንና ጥራት እንዲሁም የሎጅስቲክ ብቃት ታክሎ ስሌት ውስጥ ይገባል። ስለሆነም የነፃነት ትግሉ ውጤታማነትም ሆነ የድርጅቶች የብቃት ተልዕኮ በዚህው ይመትሩታል። ለእኔ ደግሞ ይህ ምንም ነው። ስለምን?

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ)

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)

መሣሪያ ከአለመንፈስ ደጋፊነት ባዶ ነው። ሎጅስቲክም ቢሆን የፈቀደ መንፈስ ከሌለው ባዶ ነው። ባዶ + ባዶ  ውጤቱ ባዶ ነው። ሰው ብቻውን ሆነ መሳሪያ ብቻውን፤ በተጨማሪም ሎጅክስቲክስ ብቻውን ባዶ ነው። የመጀመሪያው ነገር ፈቃደ እግዚአብሄር ወሳኝ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ውስጡ ዬነፃነት ራህብ የፈጀው የምልዕት ህዝብ የለማ መንፈስ አስፈላጊ ነው። አብሶ ለነፃነት ትግል ፍሪያማነት ነፃነቱን የፈለገ፣ የለውጥ አስፈላጊነት ከውስጡ ያመነ፣ ለለውጡ ሂደት መንፈሱን በገፍ ለመቀለብ የተሰናዳ፣ ለውጡን ለማዬት የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመቀበል የቆረጠ – የወሰነ፤ ግን ያልነፈሰበት መንፈስ ያስፈልጋል።

“የለማ መንፈስ” ይህ ማለት የጠላትን ፍሬ ነገር፣ ፍላጎተ – ግብ፣ መርምሮ ህዝብ ከነፃነት ትግሉ ጎን እንዲሰለፍ መንፈሱን ሊያነሳሱ፤ ሊያዳብሩ፤ ሊያንቀሳቅሱ የሚችሉ የህሊና ሥራዎች በስፋትና በተከታታይነት የመከወን አስፈላጊነትን ያጠይቃል። ሁሉ ሰው የሚያስበው ሁሉን ያወቀ ሆኖ እንደተገኘ አድርጎ ይገምታል። ይህ ስህተት ይመስለኛል። ለምሳሌ “ድርጅት ማለት” በፅንሰ ሃሳብ ደረጀ ሆነ በተግባር ሂደት፤ በፈተናዎቹ ዙሪያ፤ በተግባር ስንቅና ትጥቁ ዙሪያ፤ በመብትና በግዴታዎቹ አካባቢ ምን ያህሉ በቂ ግንዛቤ ወይንም ዕውቀት አለው? በጥናት ቢሰራ መረጃዊ ዳታው ከገመትነው በታች ቁልቁል ይወርዳል። ይህ ለናሙና ያነሳሁት ጉዳይ ነው እንጂ መንፈስን በጥንቁቅ አጥቂነት፤ ደጀንነት ወይንም አብሪነት ለማሰለፍ መጠነ ሰፊ ያልሰራንባቸው ጉዳዮች አሉን እንጂ ከብረቱ ቆጠራ ይልቅ ለድሉ ቅርብ የሆነው ጠላትን በለማ ህሊናና መንፈስ መርታት መስዋዕትነቱም ሆነ ጊዜው በጣም ቅርብ ያደርገዋል። እርግጥ ኃይል በጎጥ ያለተደራጀ ወጥ ኢትዮጵያዊ ሠራዊት ደጀን አያስፈልግም ማለቴ ግን አይደለም። የሆነ ሆኖ ላነሳሁት ነጥብ መነሻወችን ትንሽ ልበል።

ይቻላል። አዎን ይቻላል። ትልቁ መሳሪያ የህዝብን መንፈስን ልማት ለማስበል … “ራዲዮ” ፕሮግራም ሰፊውን ድርሻ ሊወጣ ይችላል። ሚሊዮወን የመሳሪያ ጋጋታ፤ የትጥቅና ስንቅ ሆነ ዬሎጅስቲክስ ድርጅት የሚሠራውን ፋይዳ ያህል የመከወን አቅሙ ራዲዮን አለው። እኔ እንደማስበው ዘለግ ባለ ብልጫ ራዲዮ ፕሮግራሞች ሊሠሩት ይችላሉ። ራዲዮ ፕሮግራሞችን በሁለት አቅጣጫ ከፍለን ማዬት እንችላለን።

  1. የኮምኒቲ ራዲዮ ፕሮግራሞች /በደጀንነት/ ለነፃነት ትግሉ የቀረቡና ጠላታቸውን ጠንቅቀው ያወቁትን ማለቴ ነው። እነዚህን ራዲዮ ፕሮግራሞች ውጪ ያለውን የነፃነት ደጋፊ፣ ማህል ሠፋሪ፤ ዝመተኛ ወገን፤ አልፍ ሲልም በጎጥ አስተዳደር ደጋፊነት የተሰለፈውንም አክሎ በአንድ ማዕድ ዙሪያ ሊያመጡ የሚችሉ መሰመሮችን እንዲከተሉ ማድረግ ይቻላሉ። ነገር ግን አብዛኞቹ በዚህ ዙሪያ ከሚሠሩት ይልቅ ለተደጋገመ መረጃ የሚሰጡት የአዬር ጊዜ ሰፊ ነው። ብዙዎቹ በጣም የተደጋጋመ ጉዳዮችን በተወራራሽነት ነው የሚነሱት። አንድ ሰው ቃለ ምልልስ ከተደረገለት ያው ደግሞ በሌላው ይደገማል ይሰለሳል። ይህ ለእኔ ጊዜን የሚበላ ዕዳ ይመሰለኛል። በዚህ ዙሪያ ሌላ ማንሳት የምሻው ጉዳይ ሁሉ ሰው የተስተካከለ ግንዘቤ እንዳለው – እንዳወቀ አደርጎ ይገምታል። እእ! በጣም በብዙ እርቀት ላይ እንደምንገኝ ሃቁን ብንቀበል መልካም ነው። መንፈሳችን አለመደራጀቱ የሚረጋገጠው ለተመሳሳይ ጉዳይ ምን ያህል አቅምን እያሾለኩ – አቅምን የሚሰልቡ አቅለ ቢስ ጉዳዮችን እንደምንከበክብ ሁላችንም እናውቀዋለን። ስለዚህ ሁላችንም ገና ነን። ስለዚህ መንፈሳችን በመስኖ መልማት አለበት …. ቢቻል ቢቻል የኮሚኒቲ ራዲዮ ፕሮግራሞችን በአህጉር ደረጃ እንኳን አቅጣጫቸውን ማዕከላዊ ለማድረግ ቢሞከር አንድ መንገድ ነው። ካልተቻለ ግን የኮሚኒቲ ራዲዮ ፕሮግራሞች “በመንፈስ ልማት” ላይ ሰፊውን የአዬር ጊዜ ቢሰጡ መልካም ይስለኛል። በተደራጀ ሁኔታ የመንፈስ ፈሎች ተከታታይ በሆኖ እንደ አልሚ ምግቦች መስጠት፤ በታቀደና በተሰናዳ ሁኔታ የማስተማር፣ የማሰናደት ተግባር መከወን ያለበት ይመስለኛል። ጊዜም ሆነ አቅም መባከኑ ካልቀረ ዒላማው ወደ ጎሎ ማነጣጠር አለበት። ይህ መስክ የተዘለለ ነው ማለት እችላለሁ።
  2. ሀገር ቤት የሚደርሱ የራዲዮ ፕሮግራሞች /በአጥቂነት/ እኔ እንደማዬው ሀገር ቤት በሚደርሱ ራዲዮ ፕሮግራሞች ላይ የጥራት – የብቃት የዝግጅት አቅም ሙሉ ነው። አብሶ የድምጽ ጉዳይ ለራዲዮ ፕሮግራም ወሳኙ ክፍል ነው። በዚህ በኩል ብዙም ችግር አላዬሁም። የመረጃው ዕውነትነትም እንዲሁ። እንደ ሥርጉተ መንፈስ የነፃነት ትግል ራዲዮ ፕሮግራሞች ከቤት መከራና ችግር የሚነሱ ተከታታይ መስኖችን በመንፈስ ሥር በመቀዬስ መስኩን ማልማት በሚመለከት ሰፊ ጊዜ ሊሰጠው ይገባል ባይ ነኝ። ለእኔ እራህብ ላይ ለሆነ ወገን መዝናኛ ፕሮግራም ወይንም ትረካ ምኑ ነው? የወያኔ ዜና የተንተራሰ መረጃ ከሆነ ሃቁን ሳይሸፋፍን የገለጠና የደፈረ የመሆንም አለበት ባይ ነኝ። የወያኔን የሚዲያ ቅጥፈት በሚገባ ማገለጥ በእጅጉ ያስፈልጋል።

ከዚህም ሌላ ዜናዎች ይሰማሉ ዜናዎችን መነሻ ያደረጉ የጠላትን የጎን አጥንት እንኩት ዬሚያደርጉ የህሊና ሥራዎች ግን እንብዛም ነው። ለምሳሌ አቶ ኤርምያስ ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በሰጡት መልስ ላይ “ማስፈራራት የሥርአቱ ባህሪ ስለሆነ እኔም ከዚህ ልወጣ አልችልም ነበር በማለት የእምነት ቃላቸውን ሰጥተውናል” ወሸኔ ነው። ይህ አገላለጽ የወያኔን ሆድ ዕቃ ቁልጭ አድርጎ ያሳዬ፤ ተረት ተረት ያልሆነ ተጨባጭ አምክንዮ ነው። በዚህ ዙሪያ ማገናዘቢያ ስለተገኘ ለዓለም ዓቀፍ የሰባዕዊ መብት አስከባሪ ድርጅቶች በሚጻፉ ደብዳቤዎች ላይ መረጃውን በትክክል ማቀበል። ሀገር ውስጥ ለሚቀጠቀጠው ወገንም አጫጭር ጹሑፎችን በማዘጋጀት በዚህ ዙሪያ ተከታታይ፤ ጠንካራና ጫሪ አቀጣጣይ ስሜቶችን አባብሎ ወደ ግንባሩ ማምጣት ይቻላል። ሰራዊት እምለው እኔ ይሄን ነው። ፈንጅም በሉት አዬር መቃወሚያም ሆነ ተዋጊ ጀትም እምለው ይሄን ነው። ለዛውም ቋፍ ላይ ላለ ምልዕትማ ከሚሊዮን ሠራዊት ወይንም የብረት ኳኳቴ በላይ በአጭር ጊዜ ምልዕትን መንፈሱን አሸፍቶ ለድሉ ማብቃት ይቻላል። አንጋጦ ሰማይ ከማዬት መሬት ላይ ያለውን ዕድል በቅጡ አደራጅቶ የመምራት አቅምን ይጠይቃል። ብዕርና ብራና እንዲሁም ሸበላ ድምጽ ብዙ ያተርፋሉ። በጎጥ የተጠቀሙ /የተሰፉ/  ዲሪቶዎችን ሁሉ አመድ የማደረግ አቅማቸውም አንቱ ነው። ከሁሉ በላይ ሰፊው ህዝብ በፋፋ መንፈስ የሚያገኘው ድል የራሱ ነው። የማንም – የምንም ጥገኛ አይሆንም። ተስፋው መዳፉ ላይ አሱን ብቻ ይጠበቃል።

እኔ እላለሁ – ከጠላት የሚመጡ ማናቸውም መረጃዎች ሁሉ ከዜናቸው ቀጥሎ መረጃውን ተንተርሶ የጠላትን አቅም የሚቀጠቅጥ፤ አከርካሪውን እንኩትኩት አድርጎ የሚሳባብር በጉልበታም ድምጽ አጫጭር ጹሑፎች የአዬር ላይ የትምህርት ዜግነት ት/ ቤቶች ናቸውና የዘመኑ ቅኝት በዚህ ላይ ቢያተኩር መልካም ነው።

ጹሑፎቹ ግልጽ፣ አጭር፤ በቀላል አማርኛ የተቀነባበሩ፤ ራህብን ጠረጴዛ ላይ ቁጭ አድርገው የሚያወያዩ መሆን ይኖርባቸዋል። ደቂቃው ቢበዛ አምስት ቢያንስ 3 ደቂቃ መሆን አለበት። ለነገሩ በራዲዮ ፕሮግራም እኮ ከአምስት ደቂቃ በላይ ህጉም አይፈቀድም። አጃቢ ሙዚቃው በሚመለከት ውስጥን የሚያቆላምጥ ግን የሚያስቆርጥ መሆን ይገበዋል ባይም ነኝ።  ብሄራዊነት ወንጀል በሆነበት ሁኔታ ላይ ህዝብን ሆ! ብሎ እንዲነሳ ለማደረግ ከሻንበል፤ ከሻለቃ፤ ከብርጌድ፤ ወይ ከክፍለጦር በላይ አዛዥም ኮከብም ሳይኖር አቶ ራዲዮ መከውን ይችላል። ዜግነታችን ተጠቅጥቋል – ለነገም እንዲጠፋ ተዶልቶበታል፤ ማንነታችን ተረግጧል – ለነገም ስደት ታውጆበታል፤ ክብራችን ተፍቋል ለነገም መቃብር ተቆፍሮለታል። ከዚህ በላይ ሊመጣ የሚችል ነገር የለም – በፍጹም።

መሳሪያ ለሚቆጥሩ፤ የሠራዊትን አቅም ለሚያገኑ ወይንም ለሚያንኳስሱ ወገኖች እኔ የምላቸው መሣሪያ ዬሰው ልጅ ያለው በእጁ ነው። እሱም አንጎሉ ነው። አንጎሉን በሚገባ መምራት ከተቻለ ድሉ በእጅ ነው። የወያኔ ሽንፈቱም አይቀሬ ነው። አለኝ ለሚለው ሠራዊት እሱ ከሚነዛው የጎጥ ፕሮፖጋንዳ ይልቅ ተጨባጩን እንዲተረጉም መንፈሱን ማልማት ከተቻለ አረሙ ወያኔ ባደራጀው  ዬእኔ ባለው ሠራዊት ይቀባራል። ነገር ግን ይህ ከግብታዊነት ሆነ ከበቀል የጸዳን የመምራት አቅምን ሆነ ብቃትን ይጠይቃል። አብዝቶ ማሰብን – ማብሰልንም።

ከዚህ ላይ እንደ ህልም – እንደ ታምር የማዬው አንድ ሀቅ አለ። “የድምጻችን ይሰማ” የአመራር – የክህሎት ተመክሮ – የእውቀት መብለጥ – ብቃት ለእኔ የዘመኑ ፊኖሚናል ነው። እንደ ማንኛውም እንቅስቃሴ በውስጣቸው ፈታኝ ሁኔታወች ገጥሟቸዋል። የወጣት ጆዋር ጉዳይ ብቻም ሳይሆን እሱን ተከትለው የተመዘዙ ህፃፆች። ለንቅናቄው እጅግ ፈታኝ ነበር። መሪዎቻቸው ደጋፊዎቻቸው ተሰቃይተዋል፤ ታስረዋል፤ ተገድለዋል። ግን ተዘናጉ? ተረቱ? ወይንስ ፈረሱ? በፍጹም። በአዲስ መንፈስና ሃይል፤ በብቁ ስልትና በስልጡን አመራር ደምቀው አሉ። የለማ የመንፈስ ሀብታት ባለቤቶች ስለሆኑም በአኃታዊነት ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ትጉሃን ናቸው። አቅም አይባክንም ወይንም ሲሾልክ አይታይም። የሚገርመው ነገ ሰላማዊ ሰልፍ ከኖራቸው እንዲቀር ሰልፉ ሌሊት ቢወሰን በተቆረጠው ሰዓት አንድም ሰው በሰልፉ ቦታ ዝር አይልም። በምን ታምር ይህን እንደሚከውኑት ጥበቡ ልቅናው ዘሊቅ ነው። መሪና ተመሪ በትክክል በእትብት የተገናኙበት ከድንቅ በላይ አመክንዮ ነው – ለእኔ። ለእኔ ይህ ንቅናቄ ተስፋዬን የሚያለምልም ንጹህ አዬሬ ነው። ልንማርበት የሚገባ የተግባር ተቋም። ዘመኑ መማሰን ያለበት ተመክሮውን እንደ አንድ የልምድ ማዕከል ማደረግን ነው።

እኔ በግሌ እምመኘው እንዲህ ዓይነቱ፣ ፍጹም የላቀ አዎንታው የአዛዥና የታዛዥ የፍላጎት አዎንታዊ ጋብቻን ነው። ወይንም የመሪና የተመሪ አዎንታዊ የራዕይ ጋብቻን ነው። ይህን ለማምጣት ደግሜ – ደጋሜ እምገልጸው ነገር እራሰን አሸንፎ ለማደር መቁረጥና መወሰንን ነው። ስልቶቻችን – ሂደቶቻችን በመመርምር ወቅቱን ያዳመጠ፣ ከዘመኑ ጋር ሊሄዱ የሚችሉ ፈጠራዎችን አክሎ አዲስ መስመርን መከተል የነፃነት ትግሉ ያለበት ይመስለኛል።

የሠራዊት ሆነ የመሳሪያ ብቃት መለኪያው ለእኔ መንፈስን የማልማትና ለማብቀል ዝግጁ የማደረግ በእንግሊዘኛው /ፈርታይል/ መሆኑን ነው። ይቅርታ ፎንቱን ቀይሬ በእንግሊዘኛ አልፋቤት ለመፃፍ ለጊዜው አልችልም። /ፈርታይል/ መደረስ … ሴት ልጅ ልትጸንስ የምትችልበት ጊዜ አላት። የነፃነት ትግሉም ጊዜና ወቅት እንዲሁም ፈቃደ እግዚአብሄርና ቀን ያስፈልጋቸዋል። ቅድመ ሁኔታውን ማሟላት ደግሞ የሁላችንም ግዴታ ነው። ወቃሽም ሆነ ተወቃሽ ሊኖር አይገባም። የጎደለውን መሞላት የሁላችንም ነው። እንደ እኔ ፊት ለፊት ወጥተው ከጠላት ጋር በማናቸውም ዘርፍ ለመታገል የቆረጡ ሁሉ ሊደገፉ፤ ሊበረታቱ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ተከፍሎት የሚሰራ የለም። አብዛኛው ነፃ አገልግሎት ነው የሚሠጠው። ካላ ቋሚ የፖለቲካ ሠራተኛ ወይንም ፋንክሽነሪ የነፃነት ትግል ጉዙ ረጅም መሆኑንም መቀበል ያለብን ይመስለኛል።  ይህም ቢሟላ እንኳን በጎጥ የተደራጀን መንፈስ አሸንፎ ህዝባዊነትን ለማምጣት የሰከነ ትዕግስት – በማስተዋል የተቀመመ ተግባር ይጠይቃል።

በተረፈ የኔዎቹ አብርሽ በዘሃበሻ የተከበሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በኢሳት ምርጥ ሰውነታቸው ድምጽ ስላገኘ ደስ ብሎኛል። ጀግና አልጋነሽ ገብሩ ደግሞ ልጆች ት/ቤት ከመጀመራቸው በፊት መፈታቷ ሰላም ሰጥቶኛል። በተረፈ ሳይታክቱ ሌትና ቀን የአራዊትን ግፊያና ግልማጫ ችለው የሚሰቃዩትን የእስረኛ ቤተሰቦች፤ የትዳር አጋሮች፤ ልጆች፤ ደጋፊዎች፤ ጠያቂዎች ሁሉ ላደረጋችሁት መልካም ነገር ሁሉ ምስጋናዬን ሆነ አክብሮቴን ሸልሜ የልቤን የሚያደርስልኝን ዘሃበሻ ዝቅ ብዬ አመስግኜ ልሰናበት። መሸቢያ – ሰንበት።

 

ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>