የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ገና መጀመራቸው ነው፡፡ የውድድር ዘመኑ ገና አልተሟሟቀም፡፡ ባሎን ዶሩን ማን ያሸንፈው ይሆን የሚለው ጥያቄ ግን በብዙዎች አዕምሮ እየተመላለሰ ነው፡፡ ምክንያቱ ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ይህንን ክብር ከተጎናፀፉት መካከል የተወሰኑት በብዙሃኑ የስፖርት አፍቃሪያን እይታ የተቀዳጁት ድል የማይገባቸው ነበሩ፡፡ በእርግጥ መቼም ቢሆን የሃሳብ ልዩነት መኖሩ አይቀርም፡፡ የስፖርት ጋዜጠኝነት መኖር ምክንያቱ ያ ነው፡፡ እንደ ባሎን ዶር ላለ ትልቅ ሽልማት እጅግ አስፈላጊ የሆኑት መመዘኛዎች ለመዳሰስም አይዳዳውም፡፡ ገና በጊዜ አላስፈላጊ መረጃ መስጠትም አይሻም፡፡ የተለየ ምልከታ ለመፍጠር ፈጥሯል፡፡ ይህም እይታ የሚገባቸው ሌሎች እያሉ ሽልማቱን ስለወሰዱ ‹‹ጥቂቶች›› ለዘብተኛ አስተያት እንዲኖር ይረዳል፡፡
በቅርቡ የዝላታን ኢብራሂሞቪች ቃለ ምልልስ በኢኤስፒኤን ላይ ቀርቦ ነበር፡፡ ግዙፉ አጥቂ ለቀረቡለት በርካታ ጥያቄዎች ያለ መታከት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ከጥያቄዎቹ መካከል አንዱ ከባሎን ዶር ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ በእርግጥ ለስዊድናዊው ይህን መሰል ጥያቄ ሲቀርብለት የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ባደረጋቸው አብዛኞቹ ቃለ መጠይቆች ላይም ቀልደኛ እና ግድየለሽ ሆኖ ቀርቧል፡፡ በምላሾቹ ውስጥ የሚታየው ወጥነት ያስገርማል፡፡ በሜዳ ውስጥ የሚያሳየው የማይዋዥቅ አቋምም ያስደንቃል፡፡ ስለ ባሎን ዶላር የሚሰማውን የገለፀው ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው ቃለ ምልልሶች ላይ በተናገረበት መንፈስ ነው፡፡
‹‹እንደሚመስለኝ አሸናፊ ለመሆን ምርጥ ተጨዋች መሆን ብቻ በቂ አይደለም፡፡ በርካታ የእግርኳስ ፖለቲካ በዙሪያው ይሽከረከራል፡፡ ጥሩ እና መጥፎ ተጨዋች (በባህሪይ) የሚባል ነገር አለ፡፡ ለእኔ እጅግ አስፈላጊው ነገር እኔ እና በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች ስለ እኔ የሚያነቡት ነገር ነው፡፡ ዳኞቹ (የባሎን ዶር) የሚያስቡት ነገር ግድ አይሰጣቸውም››
ምንም እንኳን ንግግሩ ከሰፊው ቃለ ምልልስ የተወሰደ ቁንፅል ሃሳብ ቢሆንም ጠንካራ ምልከታዎች የታጨቁበት ነው፡፡ ዝላታን የሚሰማውን ከመናገር ወደኋላ የሚል አይነት ሰው አይደለም፡፡ ያ ደግሞ መልካም ነው፡፡ በሰጠው አስተያየት ውስጥ ምላሽ የሚያስፈልጋቸው የተወሰኑ ነጥቦች አሉ፡፡ በተለይ የሽልማቱን ዋጋ የተጠራጠረበት ክፍል ሊታለፍ አይገባውም፡፡ በእርግጥ ሁሉም አትሌቶች የተለያዩ ናቸው፡፡ ለራሳቸው የሚሰጡትን ግምት ከፍ የሚያደርግላቸው የተለያዩ ሽልማቶችም አሉ፡፡ የእነዚህ ነገሮች ምንጭ ቤተሰብ፣ ገንዘብ፣ ሚዲያ አልያም እንደ ባሎን ዶር አይነት ሽልማቶች ይሆናሉ፡፡ እዚህ ጋር ምላሽ የሚያሻው ወሳኝ ጥያቄ አለ፡፡ ሽልማቱ አትሌቱን የተሻለ ያደርገዋል? ምናልባት እንዲህ ያሉት ነገሮች አትሌቱ ብቃቱን እንዲያሻሽል በተወሰነ መልኩ ይረዱት ይሆናል፡፡ ለስኬት የሚረዳውን ተነሳሽነት ያጎናፅፉታል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ያለፈ ሚና ይኖራቸዋል? በእርግጥ የሚዲያው ትኩረት ይጨምራል፡፡ ዝናቸውም በመላው ዓለም ይናኛል፡፡ በዚያ ዓመት የተሻለ አትሌት እንደነበሩ ለማሳየት ብዙ ይደክሙም ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ለታይታ የሚደረግ ነው፡፡ ሽልማቱ የሚያስገኘው ጥቅም እና ተነሳሽነት ከአሰልጣን የሚገኘውን አይተካም፡፡ አንጋፋ ተጨዋች ለታዳጊ ባለተሰጥኦ ተጨዋች ከሚያደርጉት ድጋፍ ጋር አይስተካከልም፡፡ ሌላው ቀርቶ ንፁህ ቁርጠንነት እና ታታሪነት ከሚያጎናፅፉት ብቃት ጋር እንኳን አይነፃፀርም፡፡
በሁለቱም የሣንቲም ገፅታዎች አንድ ነገር መመልከት ይቻላል፡፡ ሽልማቱ በስነ ልቦና ረገድ ጠንካራ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ለረዥም ዕድሜ የሚኖረው የትኛው ነው? ከጨዋታ ሲገለሉ በልባቸው ተቀርፆ የሚኖረውስ? ሙገሳዎቹ እና በመፅሔቶች የፊት ገፅ ላይ የሚወጡ ርዕሶች ወይስ በመልበሻ ቤት የነበረው መተማመን እና ፍቅር?
የሲኤንኤኑ ፔድሮ ፒንቶ ‹‹ቻምፒዮንስ ሊግን አሸንፈህ አታውቅም፡፡ ይህንን ውድድር ለማሸነፍ ምን ያህል ትፈልጋለህ?›› ሲል ዝላታንን ጠይቆት ነበር፡፡ ስዊዲናዊውም ‹‹በጣም እፈልጋለሁ፡፡ ባይሳካልኝ ግን ምንም ማለት አይደለም፡፡ እርሱን ባላሸንፍም የተጫዋችነት ዘመኔ ድንቅ እንደነበር አይካድም›› ሲል ምላሽ ሰጠ፡፡ በምላሹ የተገረመው ፒንቶ ‹‹ቶርናመንቱን ሳታሸንፍ የተጫዋችነት ዘመንህ ቢጠናቀቅ አትፀፀትም?›› በማለት ድጋሚ ጥያቄ ሰነዘረ፡፡ ‹‹በጭራሽ›› ሲል ዝላታን በቁርጠኝነት መለሰ፡፡
ኢብራሂሞቪች ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነገር ግልፅ ነው፡፡ በተሞክሮው ደስተኛ ነው፡፡ እግርኳስን በትልቅ ደረጃ በታላቅ ብቃት መጫወት በመቻሉ ይኮራል፡፡ ሽልማቶች የሚሰጡበት መንፈስ እምብዛም አይማርከውም፡፡ ‹‹ምርጡ ተጨዋች ማን ነው?›› ለሚለው ጥያቄ ብቻ መልስ ለመስጠት የሚፈፀም እንዳልሆነ ያምናል፡፡ ያ ባይሆንማ ኖሮ 23 ዋንጫዎችን ያሸነፈ፣ በአምስት የአውሮፓ ሀገራት በሚገኙ ዘጠኝ ክለቦች የተጫወተ እና በአሁኑ ወቅት በዓለማችን እጅግ ፈጣሪ እንደሆኑ ከሚነገርላቸው ተጨዋቾች አንዱ የሆነው አጥቂ ወደ ጎን ባልተገፋ ነበር፡፡
ዝላታን በእርሱ እና በሌሎቹ ‹‹የዓለም ምርጥ›› ተጨዋቾች መካከል ስላስቀመተው ልዩነት ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ በእግርኳሱ ዓለም ትልቅ ግምት በሚሰጣቸው ቶርናመንቶች በቂ ተሳትፎ አለማድረጉ አይካድም፡፡ ስለዚህ ከምርጦቹ ተርታ ሊሰለፍ አይችልም? ነገሩ እንደዚህ ነው ‹‹ምርጡ ተጨዋች ማነው?›› ለሚለው ጥያቄ ብቻ ሲል መናገር የፈለገው ነገር መኖሩ ግልፅ ነው፡፡ ‹‹እንደሚመስለኝ በርካታ የእግርኳስ ፖለቲካ በዙሪያው ይሽከረከራል›› የሚለውን ሐረግ ሲያክል ግን ሃሳቡ ይበልጥ ግልፅ ይሆናል፡፡ ዝላታን ባሎን ዶርን ስለማሸነፍ የማይጨነቀው በበርካታ ውዝግቦች የታጀበ በመሆኑ ነው፡፡ ይህም በሽልማቱ ዋጋ ላይ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ አብዛኞቹ ደጋፊዎች በአሁኑ ወቅት እግርኳስ ቢዝነስ መሆኑን ይረዳሉ፡፡ በዙሪያው ፖለቲካ እንደሚሽከረከርም ያውቃሉ፡፡ ክብር ባለበት ሁሉ ስልጣን አለ፡፡ በአብዛኞቹ ደጋፊዎች እይታ ባሎን ዶር እነዚህን ሁሉ ነገሮች አካትቷል፡፡ የዝላታን ኢብራሂሞቪችም እምነት ተመሳሳይ ነው፡፡ ያለፈው ዓመት ውጤት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ የድምፅ መስጫ ጊዜው በመራዘሙ ሲያመነቱ የነበሩ መራጮች ድምፃቸውን ቀድሞ ምርጫቸው ሊያደርጉት ካሰቡት ተጨዋች በተቃራኒ እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፡፡
ኖቬምበር 2013፣ የአውሮፓ አገራት ለ2014ቱ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚያደርጉት ማጣሪያ የመጨረሻ ምዕራፍ የሚከናወንበት ነበር፡፡ ስዊድን እና ፖርቹጋል የተጫወቱት በዚህን ወቅት ነው፡፡ ሁለቱም ቡድኖች የያዙት እዘህ ግባ የማይባል ስብስብ ቢሆንም በውስጣቸው አንድ ድንቅ መሪ ነበራቸው፡፡ በዚህን ወቅት ለባሎን ዶር ድምፅ እየተሰጠ አልነበረም፡፡ ነገር ግን የጨዋታው ውጤት በሂደቱ ላይ የራሱን ጥላ አጥልቷል፡፡
በዚያኑ ሰሞን ትንሽ ቀደም ብሎ የፊፋው ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር ስለ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ‹‹አወዛጋቢ›› አስተያት እንዳልወደደው አሳውቋል፡፡ ሚዲያውም ጉዳዩን አጋጋለው፡፡ ሁለቱ ግለሰቦች በእግርኳሱ ዓለም ትልቅ ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችሉ ናቸው፡፡ በመሆኑም ንትርካቸው ትኩረት ይስባል፡፡ ፖርቹጋል በደርሶ መልስ ስዊዲንን ካሸነፈች በኋላ የድምፅ መስጠት ሂደቱ ዳግመኛ መጀመር ግን ሁኔታውን ይበልጥ አነጋጋሪ ያደርገዋል፡፡
ጨዋታው የክርስቲያኖ የአምበልነት ብቃት የሚያረጋግጥ ነበር፡፡ ቡድኑ በአስደናቂ ሁኔታ ስዊዲኒን አሸንፎ ወደ ብራዚል ማምራቱን ያረጋገጠው በእርሱ ያላሰለሰ ጥረት ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሊዮኔል ሜሲን በ4 በመቶ ድምፅ በመብለጥ አሸናፊ ሆነ፡፡
ድርጊቱ ሴራ ሆነም አልሆነም ማሳያዎቹ ተገጣጥመዋል፡፡ የመራጮች ድምፅ ከጨዋታው ቀደም ብሎ ወደ እርሱ እንዲያመሩ ተደርገው ሊሆንም ይችላል፡፡ ይህንን ማንም አያውቅም፡፡ በጉዳት ምክንያት የሜሲ አቋም ረዘም ላለ ጊዜ በመውረዱ የሮናልዶ ዕድል ሰፍቶም ይሆናል፡፡
ሮናልዶ ጫና እና ኃላፊነትን መቋቋም የሚችል አይነት ተጨዋች ነው፡፡ በምንም ምክንያት አቋም ሸርተት ቢል ሚዲያው ይቅር እንደማይለው ግልፅ ነው፡፡ በዚያን ዓመት በተደረጉ የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ላይ ግን ተፅዕኖ ፈጣሪ አልነበረም፡፡ ሪያል ማድሪድ በሜዳው በቦሩሲያ ዶርትሙንድ 4-1 ሲሸነፍ ፖርቹጋላዊው ሜዳ ውስጥ ነበር፡፡ በመልሱ ጨዋታም ቢሆን የኃያል ሚዛናቸውን ማስጠበቅ አልቻለም፡፡ ጋላክቲኮዎች መሪ ባስፈለጋቸው ጊዜ ሚናውን ለመወጣት ዝግጁ አልነበረም፡፡ ብሔራዊ ቡድኑንም ቢሆን በጥሩ ሁኔታ መርቷል ሊባል አይችልም፡፡ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በተደረገው ትንቅንቅ ራሽያ እና እስራኤል የፖርቹጋል በርቱ ተፎካካሪዎች ነበሩ፡፡ ወደ ቶርናመንቱ ማምራቷን ለማረጋገጥ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ መጠበቅ ነበረባት፡፡ ከላይ የተጠቀሱት የመከራከሪያ ሃሳቦች አላማ ግልፅ ነው፡፡ እነዚህን መሰል ‹‹ግጥምጥሞሾች›› የሽልማቱን ዋጋ የስነሳሉ፡፡
እንደ ፑሽካሽ እና የእግርኳስ ፀሐፊዎች ማህበር የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች አይነት ሽልማቶች አብዛኛውን ጊዜ አመኔታን ያተርፋሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ መራጮቹ የተለዩ መሆናቸው ነው፡፡ የባሎን ዶርን አሸናፊ ለመለየት ድምፅ የሚሰጡት የብሔራዊ ቡድን አምበሎች እና አሰልጣኞች እንደዚሁም የተመረጡ የታወቁ ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ እዘህ ላይ ጎልቶ የሚታየው ችግር ካላቸው ቀርበት ተነሳ የብሔራዊ ቡድን አምበሎች ለቡድን ጓደኞቻቸው ድምፅ የመስጠት ዝንባሌ ማሳየታቸው ነው፡፡ እንደ ፑሽካሽ ላሉ ሽልማቶች ግን መራጮቹ የእግርኳስ ተመልካቾች ናቸው፡፡ በእግርኳስ ፀሀፊዎች ማህበር የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች የሚመረጠው ደግሞ በመቶዎች በሚቆጠሩ እንግሊዛውያን ጋዜጠኞች ነው፡፡
አንዳንዶች የፑሽካስ ሽልማት እንደ አማተር ሊቆጠር ይገባል ብለው የረካረካሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ አሸናፊው ከህዝብ በሚሰበሰብ ድምፅ የሚታወቅ መሆኑ ነው፡፡ መከራከሪያቸው ስፖርቱን ደግፈው የቆሙት ደጋፊዎች መሆናቸውን ይዘነጋል፡፡ የእግርኳስ ፀሐፊዎች ማህበር በበኩሉ በስሩ በርካታ የታወቁ ጋዜጠኞችን ይዟል፡፡ የጋዜጠኞቹ ሥራ መረጃ መስጠት ብቻ አይደለም፡፡ ከዕድሉ የፀዳ ምልከታ እንዲኖራቸው በቁርጠኝነት መረጃዎችን በብልሃት ይመረምራሉ፡፡ ቢያንስ ይህኛውን መንገድ ማጣጣል የሚቻል አይመስልም፡፡ የእግርኳስ ፀሐፊዎች ማህበር አካሄድ ከሁሉም የተሻለ ይመስላል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ለዓለም እግርኳስ ይህ መሰል አካሄድ ተቀባይነት የሚያገኝ አይመስልም፡፡ ሌላው ቀርቶ በፕሪሚየር ሊጉ እንኳን አልተተገበረም፡፡
በየትኞቹም ሽልማቶች ውስጥ አሻጥር አለ፡፡ የባሎን ዶር አሸናፊ የሚረመጥበት ሂደት ላይ ማሻሻያ ለማድረግ በርካታ ሃሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ አብዛኞቹ አወዛጋቢ ክስተቶች መነሻ ፊፋ መሆኑ ግን ነገሩን ያወሳስበዋል፡፡
ብዙም ሳንርቅ በቅርቡ በተከናወነው የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ‹‹የቶርናመንቱ ምርጥ ተጨዋችነት›› ክብርን ሳይገባው ሜሲ መቀዳጀቱ አነጋጋሪ ነበር፡፡ ክብሩ የሚገባው ለሌሎች እንደነበር ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ለፊፋ ወርቃማ ልጅ የተበረከተ የማስተዛዘኛ ሽልማት መሆኑም አይጠፋቸውም፡፡
የክርስቲያኖ ሮናልዶ ጉዳይም እንደ ምሳሌ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ሪያል ማድሪድ ከከተማ ተቀናቃኙ አትሌቲኮ ማድሪድ ሲጫወት አጥቂው የፈፀመውን የእግርኳሱ ዓለም አይዘነጋውም፡፡ ፖርቹጋላዊው በአትሌቲኮው ተከላካይ ዲያጎ ጎዲን ላይ ቡጢ ሲሰነዝር በካሜራ እይታ ውስጥ ገብቷለ፡፡ ነገር ግን ምንም አይነት ቅጣት አልተጣለበትም፡፡ ሚዲያውም ቢሆን ጉዳዬ አላለውም፡፡
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ዶርን ካሸነፈ በኋላ ተፎካካሪው ፍራንክ ሪቤሪ ሽልማቱ የሚገባው ለእኔ ነበር ሲል ተደምጧል፡፡ ‹‹ከባየርን ሙኒክ ጋር ማሸነፍ የምችላቸውን ነገሮች በሙሉ አሸንፌያለሁ፡፡ በአንፃሩ ሮናልዶ ምንም አላሸነፈም፡፡ ባለማሸነፌ አላዝንም፡፡ ነገሩ ግን ያሳምማል፡፡ ባሎን ዶርን ማሸነፍ የነበረብኝ እኔ እንደሆንኩ ግልፅ ነው፡፡ ሮናልዶ እንደሚያሸንፍ ግን ግልፅ ነበር፡፡ የመምረጫ ጊዜው በሁለት ሳምንት እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ ከዚህ ቀደም ይህን መሰል ነገር ተፈፅሞ አያውቅም፡፡ ምክንያቱ እግርኳሳዊ እንዳልነበር ግልፅ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነበር››
ሪቤሪ ፍፁም ትክክል ነው፡፡ ምክንያቱም ከፖርቹጋላዊው አጥቂ የበለጠ ዋንጫዎችን እና ግለሰባዊ ሽልማቶችን አሸንፏል፡፡ በ2010 ስፔን በደቡብ አፍሪካ ባለድል መሆኗን ተከትሎ ስፔናዊ ተጨዋች ሽልማቱን እንዲወስድ የእግርኳስ ዓለም ፍላጎት ነበር? ለዚህ ተወቃሽ የሚሆነው ማን ነው? ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሃት-ትሪክ ሰርቶ ቡድኑ አሸናፊ እንዲሆን ካስቻለ በኋላ ለተከተለው ውጤት መራጮችን መውቀስ ይቻላል? ወይስ የድምፅ መስጫው ቀን እንዲራዘም ያደረገው ፊፋ ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት እንላለን?
በመጨረሻ የሚነሳ አንድ ጥያቄ አለ፡፡ ሽልማቱ ያን ያህል ጠቃሚ ነው? የሚል፡፡ ውዝግቦቹን ወደ ጎን ብንገፋቸው ያን ያህል የጎላ ዋጋ እንደሌለው እንረዳለን፡፡ የትኛውም ተጨዋች የባሎን ዶላር አሸናፊ ቢሆን የተጫዋቹን አቋም አይጨምርም፡፡ አልያም አይቀንስም፡፡ የተቀሩት የቡድን ጓደኞቹ የተሻለ ተጨዋቾች እንዲሆኑ አያደርግም፡፡ ተጨዋቹ በልምምድ ሜዳ ተነሳሽነት እንዲኖረው ሊያደርግ ይችላል፡፡ ግን ቆይታው ምን ያህል ነው? የተሻለ አቋም እንዲያሳይ ብርታት ይሰጠዋል? ሰውነቱ እረፍት ሲሻ አዕምሮው ማነቃቃት ይችላል? ደጋፊዎች የዓለም ምርጡ ተጨዋች ማን እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ ፊፋ በበኩሉ የራሱን ወርቃማ ልጆች ማሰቡን ገፍቶበታል፡፡