ደርግ የዘመን ጀንበሩ ልትጠልቅበት በዳዳችበት የመጨረሻ ዓመታት በጦር አውድማ ላይ እየገጠመው የነበረውን መፈረካከስ ጠግኖ ከውድቀት ለመዳን በሚውተረተርበት ማብቂያ ዘመኑ ላይ ነው፡፡ 1982፡፡ ሰራዊቱ በሰሜኑ ግንባር የለቀቃቸው ቦታቸው ነፃ መሬት፣ ተብለው እንኳን ጦሩ ደግሞ ሊሰፍርባቸው ቀርቶ ደርግ የሚለው ስም የማይጠራባቸው ቀጠናዎች ከሆኑ ሰነባብተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ትቅደም ወደ ኢትዮጵያ ትለምልም… ከአብዮታዊት ወደ ህብረተሰባዊነት መፈክሮች እየተሻገረ 16 ዓመታትን የዘለቀው ወታደራዊ አገዛዝ ጎረቤት ሀገራት የፈሩትንና በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን የጦር ሀይል ተሸክሞ ከስሩ እንደተቆረጠ ዛፍ መገርሰስ ጀምሯል፡፡ በዚህ ቀውጢ ወቅት ጎዶሎውን የመስመር መኮንኖች ቦታ ለመሙላት እና በጦር አውድማ ላይ የሳሳውን ወታደራዊ ዕዝ ለማጠንከር በግርድፉ ሊያሰለጥናቸው ወደ ጦር ካምፖች የሰበሰባቸው ሰልጣኝ መኮንኖች በየማሰልጠኛ ሊሰፍሩ ከትመዋል፡፡ የጦላይና ሁርሶ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ምልምሎች ያጠረቃቀሟቸውን ሁሉ በተለያዩ አውደ ውጊያ ትምህርቶችና ሙያዎች አሰልጥነው ለማስመረቅ ‹‹ሱሪ በአንገት›› አይነት ሩጫ ይዘዋል፡፡ 1982 ለሁርሶ ያልተለመደ እንግዳ ይዛ የመጣች ዓመት ናት፡፡ ወጣቶች የበዙበት የመካከለኛ አመራርና የመስመር መኮንኖች ስልጠና እንደከዚህ ቀደሙ አፈር የሚያስበላና፣ እናቴ ድረሺልኝ የሚያስብል ውጥረት አልነበረበትም፡፡ ያ ወታደራዊ ትዕዛዝና ስርዓት ከሞትም በላይ አስፈሪና ቁርጥ የሚሆንበት፣ አድርግና አታድርግ የሚሉ ሁለት ቃሎችን መፈፀም ብቻ እንጂ ለምንና እንዴት ብሎ መጠየቅ ቅጣት ውስጥ የሚከትበት ወታደራዊ ትምህርት ተረስቶ ስልጠና ለብ ለብ የሆነበት ጊዜ ነበር፡፡ ለአስቸኳይ የሰው ኃይል ጠኔ ማስታገሻ የሚውል ወታደር የሚፈልግበት ጊዜ ነበራ፤
በጥቂት ወራት ውስጥ እንደምንም እንደምንም ተብሎ በተካሄደ ስልጠና በምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ ከተመረቁት ብዛት ያላቸው የበታች መኮንኖች ውስጥ አንደኛው ነው ተሰማ ፋንቱ፡፡
ተሰማ ከኖረበት የተራ ወታደር ህይወት ወጥቶ በስልጣን ሽግግር ወደ መኮንንነት ከተጠጋ በኋላ ያሉትን ጊዜያት በቅጡ አላጣጣማቸውም፡፡ ሩጫ፣ ሽብርና የመፈረካከስ ወሬ የበዛበት ጊዜ ነበርና በየአውደ ግንባሩ የሚሰማው የመሸነፍና የመበታተን ወሬ ጦሩን እየፈታው መጥቷል፡፡ መደበኛው ስራ ከመሰራቱ በፊት ነገሩ ተጠናቋል፡፡ የነተሰማ ብርጌድ በመበታተኑ ነፍሱን ለማዳን መራወጥ ጀመረ፡፡ 1983 ከገባ ወዲህ የነበረው የደርግ ህይወት የመጨረሻ ማጣፊያው ያጠረበት ነበር፡፡
ለምክትል መቶ አለቃ ተሰማ ይህ ጊዜ የተስፋ መቁረጥና መውደቂያ ቢስ የመሆን ስሜት የጠናበት ነበር፡፡ ወሬው ሀሰት እንዳልሆነ፣ የስርዓቱም ዕድሜ ማጠናቀቂያም እውን መሆኑ መረጋገጥ ጀመረ፡፡ ግንቦት ወር ደርግ የሚለው ስያሜ ያበቃለት ጊዜ ሆነ፡፡ ከውጊያ የተረፈው ሰራዊት ተበታተነ፡፡ ልብሱን እየቀየረ መሳሪያውን እየወረወረ ህይወቱን ለማትረፍ ሩጫ ጀመረ፡፡ ም/መ/አ ተሰማማም ጭምር፡፡
ሐምሌ 1983 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የ28 ዓመቷ ወሰን የለሽ ደበበ ላምበረት አካባቢ በተከራየችው አንድ ክፍል ቤት ውስጥ ጠላ እየሸጠች በምታገኘው ገቢ ትተዳደራለች፡፡ ከቡታጅራ ከመጣች 8 ዓመት ሆኗታል፡፡ ሰው ቤት አስቀጥርሻለሁ ብላ ባመጣቻት የእናቷ ጎረቤት ልጅ አማካኝነት አዲስ አበባን ካየች በኋላ እዚሁ ቀርታለች፡፡ ከሰው ቤት ሰው ቤት ስትል ኖራ በመጨረሻ ላይ በ150 ብር በተከራየቻት አንዲት የጭቃ ቤት ውስጥ ጠላና አረቄ በመሸጥ ራሷን ማስተዳደር ጀመረች፡፡ እነሆ ላለፉት ሶስት ዓመታት እዚህችው ቤት ናት፡፡ ብዙ የአካባቢው ወንዶች ሴትነቷንና ብቻዋን መሆኗን እያዩ ለትዳርም ለጉንተላም በሰበብ አስባቡ ቢቀርቧትም ልጅቷ ኮስተር ያለ ባህሪ የነበራት ናትና ቶሎ ፊት አልሰጠቻቸውም፡፡ ለእርሷ ህይወትና ትዳር ማለት ራስን ችሎ መኖር ብቻ ነው፡፡ ይህ ብቸኝነቷ ረጅም ርቀት ሊጓዝ እንደጀመረው ሊቀጥል ግን አልተቻለውም፡፡ ከተሰማ ጋር ከተዋወቁ ወዲህ አቋሟ ተለውጦ ብቸኝነቷን መጥላት ጀምራለች፡፡
ጦሩ ከተበተነ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች የቀን ስራ እየሰራ ነው የቆየው፡፡ የቤት ኪራይ ጥቂት ቀለል ሊል ይችላል ብሎ ባሰበበት የቀድሞው ወረዳ 28 ክልል ውስጥ መኖር የጀመረው ያኔ ከማሰልጠኛ ተቋም ተመርቆ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ደርግ ከወደቀ በኋላም ቢሆን ቀድሞ ከነበረበት ቤት ለቀቀ እንጂ አካባቢውንም አልራቀውም፡፡ እዚያው ሰፈር ውስጥ በወር 200 ብር የሚከፍልባትን አንዲት ዛኒጋባ ቤት ተከራይቶ መኖር ጀምሯል፡፡
ተሰማና ወሰን የለሽ የተዋወቁት አንድ ቀን ከጓደኛው ጋር ጠላ ለመጠጣት ወደርሷ ቤት ጎራ ካሉበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ የተሰማ ጓደኛ ቀልደኛ ቢጤ ነበርና አዲሱን እንግዳ እያሳያት ዛሬ ባል ይዤልሽ መጣሁ አላት፡፡ ከ12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 1፡30 ሰዓት ድረስ ቆየ፡፡ በዚህ ወቅት ወሰኔ እና ተሰማ በዓይናቸው የተግባቡ መስለዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላ ግንኙነታቸው እየጠነከረ ሳያስቡት ወደ ፍቅር ያደላ ስሜታቸውን እያደመጡ ቆዩ፡፡ መቀራረባቸው መዋደዳቸውን ሲስበው አብረው ለመኖር እስከመወሰን አደረሳቸው፡፡ የሁለቱ ብቸኞች ጉዞ በፍቅር አጋጣሚ አጣማጆቻቸውን አስገኝቶላቸውና በየፊናቸው ከመኖር በጋራ አንድ ቤት ውስጥ ለመጠቃለል አሰቡ፡፡
1984 ዓ.ም
የለውጡ አየር አዲስ አበባን እየቀየራት ነው፡፡ የተጨነቀው የነዋሪዎቿ ስሜት መረጋጋት ጀምሯል፡፡ ሁሉም ኑሮን ለማሸነፍ በየፊናው ይቃትር ይዟል፡፡ የ36 ዓመቱ ተሰማ በበኩሉ የውትድርና ህይወቱን ረስቶ የቀን ሰራተኝነቱን ተያይዞታል፡፡ ቃታ በፈለቀቁ እጆቹ አካፋ ጨብጦ፣ ክላሽ በተሸከመ ትከሻው ሲሚንቶ አዝሎ የህይወት መስመር በወለደችው ቦታ ላይ ይውተረተራል፡፡ ሁለቱም በየፊናቸው በሚሰሩት ስራ የሚያገኟትን ገቢ እያብቃቁ የአብሮነት ህይወታቸውን መግፋት ጀምረዋል፡፡
ይዋደዳሉ፡፡ ኑሮ ያገናኛቸው ቀን የጎደለባቸው ሰዎች ናቸውና የጋራችን ነው የሚሉትን እሴት ይዘው በመተሳሰብ መኖር ጀምረዋል፡፡ ተሰማ በወቅቱ የተጋነነ የመጠጥ ሱስ የሌለበት፣ ሚስቱን አክባሪ ትዳሩን ወዳጅ ነበር- ጓደኞቹ እንደሚመሰክሩለት፡፡ ወሰን የለሽ በበኩሏ ከብዙዎች የዕለታዊ ስሜት ግፊት አስጥላ ያቆየችውን የሴትነቷን ክብር በትዳር በመጠቃለል መግለፅ የቻለች ናት፡፡ በዚህም የሚያወቋት ሁሉ ያደንቋታል፡፡ እንደ አረቄ ኮማሪነቷ እንደ ጠላ ሻጭነቷ ሱሳቸውን ሳይሆን እሷን ብለው የሚግተለተሉ ወንዶች በበዙበት ወቅት ራሷን ሳታራክስ የቆየች ጠንካራ ሴት ናት ይሏታል፡፡ ዛሬ ፍቅር ልቧ ገብቶ የተዘጋውን በሯን ከፍታለች፡፡ የመጀመሪያዋ የሆነውን ወንድ አግብታ መኖር ጀምራለች፡፡ ደስተኛ ህይወት በመምራት ላይ ናት፡፡
የሁለቱ ኑሮ እየሰመረ-ገቢያቸውም ከፍ እያለ መጣ፡፡ ተሰማ ቀልጣፋና በስራቸው ጠንካራ ሰው ስለነበረም በሚሰራበት ቦታ በየጊዜው እድገት እያገኘ መጣ፡፡ ከረዳት ግንበኝነት ወደ ዋና ግንበኝነት ደረጃ ሲሸጋገር ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ አሁን ጠቀም ያለ ገንዘብ ማግኘት ሲጀምር የሚስቱ ጠላ መሸጥ ስራ እንዲቆም ፈለገ፡፡
ወሰኔ በበኩሏ ይህን ሀሳቡን አልተቀበለችውም፡፡ እሱ ከዛሬነገ ሊባረርበት ወይም ሊቀነስበት በሚችልበት ስራ ላይ ያለ ሰው ሆኖ ለረጅም ዘመን ደንበኛ ያፈራችበትንና አስተማማኝ ገበያ ያገኘችበትን ስራዋን ሊያስተዋት መፈለጉ ብዙም ደስታ አልሰጣትም፡፡ በዚያ ሳቢያ መጋጨት ጀመሩ፡፡ ጫናውን መቋቋም ባለመቻሏም የመጨረሻ ያለችውን አማራጭ ከመጠቀም ውጪ እድል አልነበራትም፡፡ ስራውን መተው አለባት ያለበለዚ ትዳራቸው ሊፈርስ ነው፡፡
ተሰማ በሆነ ባልሆነው ይነተርካት ጀምሯል፡፡ ቤት ጠላ ለመጠጣት የሚመጡት የወሰኔ ደንበኞች ሁሉ እሷን ለማማገጥ የሚመጡ እየመሰለው ከሷ ጋር ጭቅጭቅ ጀመረ፡፡ ‹‹ውሽማ ይዘሻል›› እስከማለት ደረሰ፡፡ በተለይ እረፍት በሆነበት ቀን ቤት ይቀመጥና ገቢ ወጪውን እየገላመጠ የቤቱን ገበያ ያርቀው ጀመር፡፡ የሷ የረጅም ዘመን ደንበኞችና ጓደኞች የሆኑት ወንዶች እንደሚናገሩት ተሰማ የነርሱን መምጣት የማይፈልግ ሰው ሆነ፡፡ በዚህ የተነሳ ቀስ በቀስ ሁሉም እየተንጠባጠቡ ቀሩ፡፡ ያኔም ወሰኔ ተይ የተባለችውን መተዳደሪያዋን መተው ግድ ሆነባት፡፡ ተሰማ ወደ ኮተቤ ብረታ ብረት ፋብሪካ ጀርባ የተከራየው አንድ ክፍል ቤት ውስጥ ይዟት ሄደ፡፡ የላምበረት ኑሮ አበቃ፡፡
1984 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ወሰኔ ፀነሰች፡፡ በዚህ ወቅት ተሰማ በኮተቤ መብራት ኃይል ሰፊ ጊቢ ውስጥ እየተገነባ የነበረውን መኖሪያ ቤት እየሰራ ነበር፡፡ የሚከፈለው ገንዘብም ሞቅ ያለ ነበር፡፡ በተለይ መስሪያ ቤቱ ለቤቱ ቅርብ ስለነበረ ገባ ወጣ ለማለት አስችሎታል፡፡
በዚህ ወቅት ሚስቱን እተቆጣጠረ ወደ የትም እንዳትሄድ እየከለከለ በሌላ በኩል ራሱ ከአንዲት የቀን ሰራተኛ ከሆነች ረዳቱ ጋር መቅበጥ ጀመረ፡፡ ልጅቷ ወጣት በመሆኗና ወዲህም አለቃዋ ስለሆነ ከሱ ጋር ለምታደርገው ነገር ብዙም ፀፀት አላደረባትም፡፡ የስራ ባልደረቦቹ እስኪያውቁ ደረስ የነዚህ ሰዎች ግንኙነት ቅጥ አጣ፡፡ ተሰማ ሁል ጊዜ በምሳ ሰዓት የቡና ሱሱን ለማስታገስና ምሳውን በልቶ ለመመለስ ወደ ቤቱ ይሄዳል፡፡ በዚያን ሰሞን ግን ምሳውን በአካባቢው ባሉ ምግብ መሸጫዎች መብላት ቡናም መጠጣት ጀመረ፡፡ አፍና አፍንጫ የሆኑት መኖሪያ ቤቱና መስሪያ ቤቱ የተራራቁ ያህል የሰው አይን ሳይፈራ ከልጅቷ ጋር ያለውን ግንኙነት ለሰው ይፋ አደረገው፡፡ ይህ ወሬ ታዲያ ቀስ ብሎም ቢሆን ለወሰኔ መድረሱ አልቀረም፡፡
በባልና ሚስቱ መካከል ከፍ ያለ ብጥብጥ ተፈጠረ፡፡ ነፍሰ ጡሯ ወሰኔ በላይዋ ላይ ባሏ እያደረገባት ባለው አፀያፊ ድርጊት ተበሳጨች፡፡ ጎረቤት ተሰበሰበ፡፡ ከርሱ ጋር መኖር እንደማትፈልግ ገለፀች፡፡ እሱ ደግሞ በበኩሉ ከማንም ሴት ጋር ግንኙነት የሌለው መሆኑን ቢገልፅም ከልጅቱ ጋር ታዩ የተባሉባቸው ቦታዎችና በተለይ ከስራ ውጪ በሆኑ ቀናት ገብተውባቸው ነበር የተባሉትን መኝታ ቤት ያላቸው ሆቴሎች ጭምር ነበር ወሰኔ ታውቅ የነበረው፡፡ በመጨረሻ ላይ ግን ይቅርታ መጠየቁ አልቀረም፡፡ ከዚህች ረዳቱ ጋር አንሶላ እስከመጋፈፍ ያደረሰውን ፍቅር ተጋርቷል፡፡
በሽማግሌዎች አግባቢነትና ልመና ወሰን የለሽ ተረታች፡፡ ስራዋን የተወችበትን፣ ይዘልቃል ብላ የያዘችውን ትዳር ላለመናድ ጥቃቷን ውጣ ይቅርታዋን ለባሏ ለመስጠት ወሰነች፡፡ እሱም ጥቂት ቀናት ተለማምጦና አክብሮ አብሯት ይኖር ጀመር፡፡ 3 ወራት አለፉ፡፡
ወሰኔ 9ኛ ወሯ ውስጥ ገብታለች፡፡ ሚያዚያ ወር ላይ የወለደቻት የመጀመሪያ ልጇ በባለትዳሮቹ መካከል ሶስተኛ ሰው የጨመረች የፍቅርና ትዳር ማሰሪያ ቀለበት ሆነች፡፡ በወቅቱ ተሰማ ህይወቱ ከተመሰቃቀለበትና ጓደኞቹ ካለፉበት የጦር አውድማ ወጥቶ ህይወቱ መቀጠሉን ለማብሰር የልጅቷን ስም ‹‹ትርፌ›› አላት፡፡ ትርፌ ተሰማ፡፡ የተሰማን የህይወት ውጣ ውረድ ድምር ውጤት የያዘች ህፃን ሆነች፡፡ በቤቱ ላይ ደስታ ሆነ፡፡ ትዳራቸው ፍሬ አፈራ፡፡ ጎረቤት ጓደኛ የደስታቸው ተካፋይነቱን አረጋገጠላቸው፡፡ አሁን ህይወት ለነጠላ ነፍስ ሳይሆን ለልጅ ሆኗል፡፡ ሩጫው ጥረቱ ልፋቱ፡፡ ልጄን ላሳድግ ብዬ ነው በሚል ቃል ሊታጠር ግድ ሆኗል፡፡ ሃላፊነት በወላጆች ትከሻ ላይ አረፈ፡፡
ከ3 ወራት በኋላ
1985 መጨረሻ
ተሰማ ያ ባህሪው ድንገት ተነሳ፡፡ ወሰኔ ከአራስ ቤት ከወጣች በኋላ ያሉት ጊዜያት ቤቱ ውስጥ ንዝንዝ የሰፈነባቸው ሆኑ፡፡ ለጥቂት ጊዜ ጋብ ብሎ የነበረው የባህልና ሚስቱ ስምምነት ማጣት ዳግሞ አገረሸ፡፡ እሷ ቤት ሆና እሱ ውጪ እየዋለ መምጣቱ እንደልቡ እንዲሆን አደረገው፡፡ ከዚህ ቀደም ይታማበት የነበረውን ከሌላ ሴት ጋር ወዲህ ወዲያ የማለት ባህሪ እንደገና ተመልሶ እንደገባበት ወሬዎች መሰማት ጀመሩ፡፡ ሚስቱ በወለደች ማግስት ወደ ቀድሞው የባህሪ ችግር መግባቱን ያልወደዱለት ብዙዎች መክረውታል፡፡ ከምንም በላይ በፍቅር ያገባት ሚስቱና ከአብራኩ ያፈራትን ልጁን ሲል ትዳሩን እንዲያከብር ወትውተውታል፡፡ አልተቀበላቸውም እንጂ፡፡
ተሰማ ማንም ባላወቀው ወሰን የለሽም ባልገመተችው መንገድ ልቡ ውጪ ውጪ ማለት ጀመረ፡፡ አምሽቶ ይመጣል፣ ቤት ሲገባም ይጨቃጨቃል፡፡ በመጠጥ ኃይል የናወዘ አንደበቱ ጥሩ ነገር መናገር ቸግሮታል፡፡ የ3 ወር አራስ ልጇን በማሳደግና የሱን ፀባይ መንከባከብ የቸገራት ሚስቱ በድርጊቱ መማረር ጀምራለች፡፡ ትሸሽበት የሌላት፣ ትተወው የተቸገረች ናትና አማራጭ አጥታለች፡፡
የተሰማ ፀባይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እተበላሸ፣ ውጪ ማደርም ጀመረ፡፡ ቤት ገብቶ በለመደው ሁኔታ ቡና ተፈልቶ ካልጠበቀው ፀብ ይጀምራል፡፡ ይህንን የምታውቀው ወሰኔ የመምጫ ሰዓቱ ነው ካለችበት 2 ሰዓት ጀምራ ቡና አቀራርባ ትጠብቀዋለች፡፡ የፈለገውን ሰዓት ያህል ቆይቶ ይመጠና መጠጥ ባናወዘው አንደበቱ ስድብ ይጀምራል፡፡ አራሷ ሚስት የቀጠረቻት የ18 ዓመት ከገጠር የመጣች ልጅ በዘወትር ጭቅጭቃቸውና በሚያነሱት ፀብም ታማርራለች፡፡ ተመላላሽ ሰራተኛ በመሆኗ ግን የማታውን ትዕይንት ለመታዘብ ጊዜ አልነበራትም፡፡ በአጋጣሚ በወሰኔ ጥያቄ አንዱን ቀን እዚያ ቤት ብታድር ያየችው ነገር ለራሷም እንድትፈራ አድርጓታል፡፡
በዚያ ዕለት ማምሻውን ጀምሮ ወሰኔ ንዴት ንዴት ሲላት ቆይቷል፡፡ ተሰማ ለምሳ አልመጣም፡፡ ሌሊቱንም ቤት አላደረም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ያው ከአንድ ሴት ጋር ጊዜውን ማሳለፉ መሆኑ ለወሰኔ ግልፅ ነበር፡፡
የሚሰራበት ቦታ ድረስ ሄዳ ዘበኛውን ስትጠይቀው በ11፡30 ከሰራተኞች ጋር ሲወጣ ያየው መሆኑን ገልፆላታል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ያየው ሰው የለም፡፡ በዚያ የተነሳ ሌሊቱን ስትበሳጭ አድራለች፡፡ በምሳ ሰዓት አለመምጣቱም ተጨማሪ ንዴት ፈጥሮባት ወደ ስራ ቦታው ሄዳ ነበር፡፡ አስጠርታው ሲመጣ ግን ‹‹ለምን ትፈልጊኛለሽ?፣ የምሰራበት ድረስ ለምን ትመጪያለሽ?›› ብሎ በሰው ፊት ስለጮኸባት ቤቷ ተመልሳ መግባቱን እየተጠባበቀች ነበር፡፡ ከወትሮው ሰዓቱ ቀደም ብሎ 1፡30 ላይ ቤት ገባ፡፡ ቡና አልቀረበም፡፡ ዝም ብሎ ተቀመጠ፡፡ ራት ይበላ እንደሁ ጠየቀችው፡፡ ‹‹ማን ያዘጋጀውን ነው የምበላው?›› አላት፡፡ ይህን ሁሉ ምልልስ ሰራተኛዋ እየታዘበች ነው፡፡ ወሰኔ ‹‹ውሽማህ ያዘጋጀችውን ላመጣልህ ትፈልጋለህ?›› አለችው፡፡ ይሄኔ በንዴት ተነሳ፡፡ ተራ ሴት መሆኗን በመናገር መሳደብ ጀመረ፡፡ ቤት ውስጥ ያገኘውን ነገር በሙሉ በእግሩና በእጁ ማተረማመስ ጀመረ፡፡ ከዚያም ድንገት ወሰኔን በጥፊ መታት፡፡ ተያያዙ፡፡ ራሷን ለመከላከል ሞከረች፡፡ አልቻለችውም፡፡ መሬት ላይ ጥሏት በእግሩ ጭምር በመርገጥ ደበደባት፡፡ ደም ከአፏ ሲወጣና መሬት ላይ ሆና ስታቃስት ሰራተኛዋ መጮህ ጀመረች፡፡ ጎረቤት ተሰበሰበ፡፡ በዚህ ወቅት ተሰማ ቤቱን ጥሎ ሄደ፡፡
ወሰኔ በደሏን ውጣ ዝም ከማለት ያለፈ አማራጭ አልነበራትም፡፡ መሄጃና መሸሻ ሌላት፣ የወለደቻትን ህፃን ለማሳደግ ማንኛውንም የጥቃት አማራጭ በፀጋ ከመቀበል ውጪ ሌላ እምጃ ለመውሰድ የማትሞክር ሴት ሆናለች፡፡ በዚያ ድህነት ቀንበሩን በጫነበት ቤት ውስጥ ሰላምና ፍቅር ጓዛቸውን ጠቅልለው ጠፍተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የነበሩት ጊዜያት ሁሉ ድብደባና እንግልት የበዛባቸው ነበሩ፡፡ ተሰማ ቤት መጥቷል ማለት ጥፊና እርግጫ ቀርቷል ማለት አይደለም፡፡ ይህ የዘወትር ጩኸትና ግልግል የሰለቻቸው ጎረቤቶች አቤቱታ ማሰማት ጀመሩ፡፡ የተሰማ አከራይ የሆኑት አሮጊትም ሰላማቸውን ለማግኘት የሚሹ መሆኑንና ተሰማም ቤቱን ለቆ እንዲወጣላቸው እንደሚፈልጉ ተናገሩ፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ሰውየው ጥቂት ቀዝቀዝ ያለው፡፡ ይህን ቤት ለቆ ሌላ ቤት ሊያውም በእርሱ ባህሪ እንደማያገኝ አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ አከራይዋ የሰጡት ጠበቅ ያለ ማስጠንቀቂያ አደብ አስይዞታል፡፡ በመሆኑም ለጥቂት ጊዜ ቤቱ ሰላም አገኘ፡፡ ውጪው የማይሰማው የቤት ውስጥ ጦርነት መኖሩ ሳይቀር፡፡
ተሰማ እንደጠላቱ ልጅ እያያት የመጣችው ወሰኔ ህይወት ጨልማባታለች፡፡ ሁልጊዜ ትደበደብበት የነበረበት ምክንያት ግን ስትናግረውም ይገርማት ነበር፡፡ አንዲት ጎረቤቷ የሷ ጥንካሬና ታማኝነት አሳምራ ታውቀዋለች፡፡ ነገር ግን ‹‹ሸርሙጣ ነሽ›› እያለ የሚደበድባት ባሏ የራሱን ባህሪ በሚስቱ ላይ ማላከኩ ይገርማል፡፡ ከተሰማ ውጪ ሰው ቀና ብላ የማታይ፣ ትዳሯንና ቤቷን አክባሪ የሆነችው ሴት ወጣትነቷ በኑሮ ጉስቁልና ተሸፍኖ ያለዕድሜዋ ትልቅ ሴት መስላለች፡፡
1986 ጥቅምት
አሁንም በዚያው ቤት እየኖሩ ነው፡፡ ልጅቷ 6 ወር ሞልቷታል፡፡ ክርስትና አልተደገሰላትም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ተሰማ ገንዘብ የለኝም ማለቱ ነው፡፡ ቤቱ ውስጥ ተበልቶ እንዲታደር ያህል ብቻ በወር ጥቂት ገንዘብ ይወረውራል፡፡ የሚጠጣበት ገንዘብ እያጣ የሚሰራበትን ዕቃ እስከመሸጥ የሚደርስበት ጊዜ ነበር፡፡ ከዚህም የባሰ ችግር ግን መጣ፡፡ አብረው መተኛት ከተዉ ከ8 ወር በላይ የሆናቸው ባልና ሚስትን የሚለያይ ችግር፡፡ ወሰኔ ለጤናዋ ስትል አብራው መተኛት አልፈለገችም፡፡ እሱም ስለሚፀየፋትና ‹‹ድሮ ሸርሙጣ ነበርሽ›› ስለሚላት አብሯት መተኛት አይሻም፡፡ እሷ ፍራሽ አንጥፋ መሬት ላይ፣ እሱ ደግሞ አልጋው ላይ ይተኛሉ፡፡ አንድ ቀን ግን እንደተለመደው አምሽቶ መጣ፡፡ ብቻውን አልነበረም፡፡
በመጠጥ ብዛት ጥንብዝ ብሎ የሰከረው ሰውዬ በሩን ከከፈተችለት ሚስቱ ጋር የተፋጠጠው በደግ አልነበረም፡፡ ከኋላው አንዲት ሴት አለች፡፡ ያለጥርጥር ሴትየዋ ሴት አዳሪ ናት፡፡ እየተንገዳገደ እጇን ጎትቶ ይዟት ገባ፡፡ ልጅቷ ሰክራለች፡፡ እንደገባች የጠየቀችው ሴትየዋ/ወሰንየለሽ ምኑ መሆኗን ነበር፡፡ ‹‹ሰራተኛዬ ናት›› አላት፡፡ ወሰኔ ይህን ትሰማለች፡፡ እሷን ማመን ባትችልም የሆነው ግን ሆኗል፡፡ ልጅቷ አትኩራ ስታያት ዝምታዋ መቀጠል አልቻለም፡፡ ሚስቱ መሆኗንና ልጅ እንዳላቸውም ተናገረች፡፡ ተሰማ ግን ሴተኛ አዳሪዋ ተመልሳ ልትወጣ ስትል ጎትቶ አስገባትና በሩን ዘጋው፡፡ ጎረቤት ያሉት ሴት ይህን ሁሉ ያዳምጡ ነበር፡፡ ከምሽቱ 4 ሰዓት ሆኗል፡፡ ወሰኔ ወደየትም መሄድ አትችልም፡፡ ልጅቷም እንዲሁ፡፡ ህፃኗ ልጅ ታለቅሳለች፡፡ ወሰኔም ጥቃቷን ውጣ ታለቅሳለች፡፡ ተሰማ እየተሳደበ ልጅቷን ወደ አልጋው ይዟት ሄደ፡፡ ወሰኔ አይኗ እያየ ባሏ ከሰከረች በሴት ጋር ተኛ፡፡ አይኗ እያየ በወለደችበት አልጋዋ ባሏ ከሌላ ሴት ጋር ወሲብ ፈፀመ፡፡ ሌሊቱን አነጋችው፡፡
12 ሰዓት ላይ ሴተኛ አዳሪዋ ተነሳች፡፡ ማታ በመጠጥ ኃይል የሆነውን አታውቅ ስለነበር መሬት ልጇን አቅፋ የተኛችውን ወሰኔን ስታይ ደነገጠች፡፡ ይቅርታ ጠይቃት ወጣች፡፡ ወሰኔ መፈጠሯ የጠላችበት ዕለት ይህ ነበር፡፡ ተሰማ ተኝቶ እያለ ቤቱን ጥላ ወጣች ወደ ቤተክርስቲያን፡፡
ረፋዱ ላይ ተመልሳ የሆነውን ሁሉ ለጎረቤቶች ስትናገር ሁሉም ተበሳጩ፡፡ በተለይ ወጣቶቹ በቀጥታ ወደ ህግ አካላት ሄዳ መክሰስ እንዳለባት ነገሯት፡፡ ወሰኔ ተሰማን በመክሰስ የምታተርፈው ነገር አለመኖሩን ብቸኛ መተዳደሪያዋ የሱ እጅ በመሆኑ ይህቺን ህፃን ልጅ የምታሳድግበት አቅም እንደማይኖራት ተረድታለች፡፡ ወይም የመጨረሻ አማራጯ ልመና መውጣት ነው፡፡ በሰው ቤት ተቀጥራ ለመስራት ብታስብም ከነልጇ ሊሆን የማይችል ተግባር ሆኖባታል፡፡ ልጅቷን ለአሳዳጊዎች ለመስጠት ደግሞ የርሱ መኖርና ወላጅ ልቧ አለመጨከን ውሳኔውን አክሽፎባታል፡፡ ባታውቀውም ቅሉ የሆነ ቦታ ቤቱን ጥላ መውጣት እንዳለባት ወስናለች፡፡ መቼና የት የሚለው ግን ለርሷም ጥያቄ ነበር፡፡ ጎረቤቶቿ ችግሯ ሳይገባቸው ‹‹አውቃ እየተበደለች ነው፣ መወሰን አቅቷት ፈልጋ እየተዋረደች ነው›› ብለው ስሞታዋንና አቤቱታዋን ከቁም ነገር አልጥፍ ብለዋታል፡፡ ይህ ድርጊት ካለፈ ሳምንት ሞላው፡፡
ጥቅምት 27 ቀን 1986
አዲስ አበባ
በማለዳ የመድኃኒዓለም በዓልን ለማክበር ቤተክርስቲያን ሄዳ ነበር የመጣችው፡፡ ለተሰማ የደመወዝ ቀን ስለሆነ እንደተለመደው ጠጥቶና ሰክሮ ወይ ይመጣል አሊያም ያድራል፡፡ ይህ በየወሩ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ወሰኔ ልጇን አቅፋ ቤት ተቀምጣ ዋለች፡፡ ውሳኔዋ ምሽቱን የሚሰጣትን ገንዘብ ተቀብላ በማግስቱ አክስቷ ወዳሉበት ቡታጅራ መሄድና የሚሆነውን ማየት ነው፡፡ ገንዘብ ባላትና ስራ በምትሰራበት ጊዜ ባትጠይቃቸውም ስጋ ናቸውና ጥለው አይጥሏትም፡፡ በዚህ ሀሳቧ ዙሪያ አከራይዋ የሆኑትን ሴትዮ አማክራቸው ተስማምተዋል፡፡ ምናልባትም እሱ ሲተኛ ኪሱ ውስጥ የተረፈ ገንዘብ ካለ እንድትወስድ ጭምር ነበር የመከሯት፡፡
እንደተለመደው ምሽቱ ሲመጣ ወሰኔም ተቀምጣ የሱን መምጣት መጠባበቅ ጀመረች፡፡ በነበረቻት 2 ብር ቡና ገዝታ ቆላች፡፡ ከምሽቱ 2 ሰዓት ሲሆን ቡናውን ጥዳ ጠበቀችው፡፡ 3 ሰዓት 4 ሰዓት አልመጣም፡፡ በእንቅልፍ ብዛት ተዳከመች፡፡ ያፈላችውን ቡና ራሷ ጠጣችውና አነሳስታ አልጋው ላይ ጋደም አለች፡፡ ከምሽቱ 5 ሰዓት ሲሆን መጣ፡፡ በሩ ተንኳኳ ተነስታ ከፈተች፡፡
እንደገባ የጠየቀው ‹‹ቡና›› ነበር፡፡ እሷም የሰጠችው መልስ አንድ ብቻ ነው፡፡ ‹‹አሁን የቡና ሰዓት አይደለም›› ቱግ አለ፡፡ በመጠጥ ናላው ዞሯል፡፡ ድንገት ሳታስበው በቡጢ አፍንጫዋን መታት፡፡ ልጅ ይዛ ነበርና አብራ ወደቀች፡፡ በወደቀችበት ረገጣት፡፡ ልጅቷ እሪ ትላለች፡፡ ወሰኔ የሞት ሞቷን ተነስታ ለማምለጥ ጥረት ማድረግ ጀመረች፡፡ በሰይጣናዊ ኃይል ፀጉሯን ጎትቶ ከግድግዳ ጋር እያጋጨና ድንጋይና ብረት ባደደረው እጁ ፊቷን በቦክስ እየመታ ደም በደም አደረጋት፡፡ ተዳከመች፡፡ መሬት እንደወደቀች ደረቷን ደጋግሞ በወታደር ጫማው ረገጣት፡፡ ሆዷን ጭምር፡፡ መጮህ አቅቷት አይኗ በጣእር ፈጠጠ፡፡ ህፃኗ ‹‹እሪ!…›› ትላለች፡፡ ጎረቤቶች በሩ ላይ ቆመው ‹‹ተዉ!›› እያሉ ይለምኑታል፡፡ እሱ ደግሞ ይሳደባል፡፡ በመሀል ላይ የወሰኔ ድምፅ መጥፋቱን ሲሰሙ ሰላም ተፈጥሮ ይሆናል ብለው አሊያም እሷ ስላልፈለገች ይሆናል ድምጿን ያጠፋችው ብለው አስበው ወደየቤታቸው ሄዱ፡፡ አከራይዋ ብቻ የዛሬን ሌሊት አዳር ማወቅ ይሻሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ወሰኔ በዕቅዷ መሰረት ስትሄድ እሳቸውም ተሰማን ማባረር ነው የሚፈልጉት፡፡
ተሰማ መሬት ላይ ተዘርራ በስቃይ ሆዷን ይዛ የምትገላበጠውን ሚስቱን ቁልቁል አያት፡፡ የሆነ አንዳች ሰይጣናዊ መንፈስ በላዩ ላይ ሰፈረበት፡፡ ‹‹ግደል ግደል አለኝ›› ይላል፡፡ አንገቷ ላይ በእግሩ ቆመባት ቀድማ የተዳከመችው ሴት ይህንን ከባድና ግፈኛ የሆነ ስቃይ መቋቋም አልቻለችም፡፡ አይኗ በአየር እጦት ሲፈጥ ያያታል፡፡ በእጁ እግሩን ብትይዘውም ለማስለቀቅ የሚሆን ኃይል ግን አልነበራትም፡፡ ጥቂት ቆይታ እንቅስቃሴዋ ሁሉ ቆመ፡፡ እግሩን አነሳ ዘወር ብሎ ሳያያት አልጋው ላይ ወጥቶ ተኛ፡፡
ሲነጋ ነቃ፡፡ ማታ ላይ ያደረገውን ነገር ማወቅ አልቻለም፡፡ ሌሊቱን ስታለቅስ የነበረችውን ልጁ እንዴት አድርጎ አልጋው ላይ እንዳስተኛትም አያስታውስም፡፡ እናትየዋን በተናችበት ቦታ አያት፡፡ ዓይኗ ፈጦ ጣራ ላይ ተሰክቷል፡፡ እጆቿ ግራና ቀኝ ተሰባጥረዋል፡፡ የለበሰችው ቀሚስ በከፊል ተቀዶ እርቃኗን ያሳያል፡፡ ሞታለች፡፡ ደነገጠ፡፡ ከአልጋው ተፈናጥሮ ተነሳና በሩን ከፈተው፡፡ ሊጮህም አሰበ፡፡ ተመልሶ ቤት ገባና ነካካት፡፡ ቀዝቅዛለች፡፡ ተመልሶ በሩን ከፈተና ወደ አከራዩት ሴትዮ ቤት ሄደ፡፡ በሩን ሊያንኳኳ ብሎ ከጀመረ በኋላ ተወውና በቀጥታ ቁልቁለቱን በሩጫ መውረድ ጀመረ፡፡ የወረዳ 28 ፖሊስ ጣቢያ መውጫው ላይ አለ፡፡ ወደ ግቢው ሲገባ በር ላይ የነበረው ዘብ አስቆመው፡፡
‹‹ሰው ገድያለሁ ሚስቴን ገድያታለሁ…›› ባልተረጋጋና በተጣደፈ አኳኋን የሚናገረው ተሰማ የሆነ መፍትሄ እንዲመጣለት የፈለገ ይመስላል፡፡ ፖሊስ በፍጥነት እንዲመጣለት የፈለገ ይመስላል፡፡ ፖሊሱ በፍጥነት ጣቢያ ውስጥ ያደረውን ተረኛ መርማሪ ጠራው፡፡ ተሰማ ገባ፡፡ ፖሊሶቹ የተነገራቸውን ነገር ለማጣራት በወረዳዋ መኪና ተረኛ መኮንንኑን ይዘው ወደ ተሰማ ቤት ሄዱ፡፡ ነገሩ እውነት ነው፡፡ የመኪናና የሰዎች ኮቴ ድምፅ የሰሙት ጎረቤቶች ከቤት የወጡት ተሰማ ጮክ ብሎ ማልቀስ በመጀመሩ ነበር፡፡ ከንጋቱ 12፡30 ላይ ፀጥ ብሎ የነበረው መንደር በለቅሶና በጩኸት ተናጋ፡፡
ፖሊሶቹ አስፈላጊውን ምርመራ ካደረጉ በኋላ ነበር የሟችን አስከሬን ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የወሰዱት፡፡ ተሰማን ደግሞ ወደ ጣቢያ፡፡ ያቺ ያልታደለች የ6 ወር ህፃን ለጊዜው ጎረቤቶች ጋር ቆየች፡፡ ተሰማ በሰጠው የእምነት ቃል ሙሉ ለሙሉ ጥፋተኛ መሆኑን ለፍርድ ቤትም ለፖሊስም አረጋግጧል፡፡ በመጠጥ ኃይል ተገፋፍቶ የፈፀመው መሆኑን ጭምር፡፡ በወቅቱ የድብደባ ድምፅ ሰምተው የመጡ ጎረቤቶችም ከዚህ በፊት በወሰንየለሽ ላይ ይፈፀምባት የነበረውን ግፍ በሙሉ ለፖሊስ ተናገሩ፤ ምሽቱን ያደረሰባትን ድብደባ ጨምሮ፡፡ የአስክሬን መርማሪ ባለሙያዎቹ ሟቿ ባደረሰባት ድብደባ የደረት አጥንቶቿ በመሰባበራቸውና ጉሮሮዋ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ ሳቢያ ለህልፈት መዳረጓን በሪፖርታቸው ገልፀዋል፡፡
3 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ አብራው የኖረችውን ሚስቱን የገደላት ባል ወደወህኒ ቤት ገባ፡፡ ህፃኗ ለህፃናት ማሳደጊያ ተሰጠች፡፡ እናት ተቀበረች፡፡ በወቅቱ ቤተሰቦቿን የሚያውቅ ባለመኖሩ ጎረቤቶች ነበሩ የአካባቢውን ሰው አሰባስበው ኮተቤ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የቀበሯት፡፡
ያልታደለው ትዳር በዚህ ሁኔታ ተፈታ፡፡ በመጨረሻ የውሳኔው ቀን ላይ ህይወቷን ያጣችው ወጣት ነገሩ ‹‹በሬ ካራጁ›› ሆኖባት ህይወቷ በባል ጠላት እጅ ማለፉ ግድ ሆኗል፡፡ ከነዚህ ወላጆች የወጣችው ፍሬ ዛሬ ምናልባት የ15 ዓመት ልጅ ሆናለች፡፡ ይህን ታሪክ ስለማወቋ ግን ማንም እርግጠኛ አይደለም፡፡ ‹‹ግደል ግደል አለኝ›› ያለው ባል የመጠጥ ፈረስ ያዘዘውን አደረገ፡፡ በጎጆዋ የሚኖሩት ሶስት ነፍሶችም ወደማይገናኙበት አቅጣጫ ተበታተኑ፡፡ አሳዛኙ ፍፃሜም ይህ ሆነ፡፡