Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ማስታወሻ ለኢሣይያስ፣ ለኤልያስ፣ ለብርሃኑና መሰል ኢትዮጵያውያን ወገኖች በሙሉ!!!!

$
0
0

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ (ከአዲስ አበባ)

ኧኸ …. ዴዴዴዴዴዴዴ …. ነይ ነይ ያገሬ ልጅ፣ ነይ ነይ የወንዜ ልጅ … (2)

መለሎ ቁመናሽ ሸምበቆ አንገትሽ (2)
ከቶ ወዴት ገባ ያ ሰውነትሽ (2)

አይ አንቺ ገራገር አይ አንቺ ሞኝ አድባር (2)
በቁመናሽ ፈቱት ያሰርሽውን አምባር (2)

እምዬ ቀሚስሽን በጠባቡ አሰፊው (2)
ዛሬ በሙሉ አካል የለሽም በሰፊው (2)

እንግዲህ እናቴ ቁራጭ ልበሽልኝ (2)
ወጪም አላበዛ እንዲህ ካነስሽልኝ (2)

ጠበቃሽ ማን ይሆን? ዋስሽስ ማን ይሆን? እማኝሽ ማን ይሆን? ጠበቃሽ ማን ይሆን?
የነበረሽ ሁሉ እንዳልነበር ሲሆን፡፡ (2)

ኧኸ… ኤዴዴዴ… ዴዴዴዴ ….ዴዴዴ… ያገሬ ልጅዬ፣ የወንዜ ልጅዬ … ነይ ነይ ያሬ ልጅ … ነይ ነይ የወንዜ ልጅ

እትብቴ ከወዲያ መቃብሬ ወዲህ (2)
በተወለድኩበት አልኖርኩም ከእንግዲህ (2)
ምንድነው ውዳሴ ከእንግዲህ ለጠላ (2)
የደረቡት ሁሉ ከሆነ ነጠላ (2)

ጠበቃሽ ማን ይሆን … (አዝማች)

ከሌሎች ያነሰነ ምንስ ብንሆን ድሃ (2)
እንዴት እናጣለን ከቤታችን ውሃ (2)
አንዲቷ ጎረቤት ያለውን ስትቀዳው (2)
እኛ ብዙ ሆነን ተጠማን ከጓዳው (2)

የቤቱን ስባሪ ሸክም የሚያግዝ (2)
ማን አይዞህ ይለዋል ቢያዝን ቢተክዝ (2)
ሲጠፋ እማያየው እልፍኝ አዳራሽ (2)
አይጨነቅም ወይ ለነገው ወራሽ (2)

ጠበቃሽ ማን ይሆን? ዋስሽስ ማን ይሆን? እማኝሽ ማን ይሆን? ጠበቃሽ ማን ይሆን …
የነበረሽ ሁሉ እንዳልነበር ሲሆን፡፡ (2)

ድምፃዊ ቻላቸው ከበደ ካቀነቀናቸው ግሩም ሀገራዊ ዜማዎች ውስጥ የአንደኛው ግጥም (ነፍሱን ይማር)



በኢትዮጵያዊነታችሁ የምታምኑም ሆናችሁ የማታምኑ ከፍ ሲል በርዕሴ የጠቀስኳችሁ ውድ ኢትየጵያውያን ወገኖቼ፣ እንደምን አላችሁልኝ? የአዲሱን ዓመት ዋዜማና መባቻ እንዴት አያችሁት? መጪውን ዘመንስ ለእናንተም ሆነ ለእናት ሀገራችሁ ምን እንደሚሆን ትጠብቃላችሁ? ለማንኛውም አንድ ወንድማችሁ በግል ተነሣሽነትና በነፃ ፍላጎቱ ይህችን ማስታወሻ ልኮላችኋልና የእርኩሳን መናፍስት ጠባይ ከሆኑት ትዕቢትና ዕብሪት ታቅባችሁ እንድትመለከቷት አደራ ይላችኋል፡፡ መልካም አዲስ ዓመት፡፡ አዲሱ ዓመት ሁላችንም ልብ ገዝተን ወደዬኅሊናችን የምንመለስበት እንዲሆን የወቅቱ ምኞትና ጸሎቴ ነው፡፡
Eliask4513697854126548
ግልጽ ለመሆን ያህል በርዕሴ የተጠቀሱት ኢትዮጵያውያን ኢሣይያስ አፈወርቂ፣ ኤሊያስ ክፍሌና ብርሃኑ ነጋ መሆናቸውን መጠቆም እወዳለሁ፡፡ እነዚህ ወገኖች በየራሳቸው ከአንድ ግለሰብነት የማይዘሉ ተራና ብናኝ ሰብኣዊ ፍጡራን መሆናቸውን አምናለሁ፡፡ ነገር ግን እንደዬፖለቲካ አቋማቸው የተለያዬ ውክልና ያላቸው በመሆናቸውና በአንድ ወይ በሌላ መንገድ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆናቸው ስለሚታወቅ ግምታቸው ከፍ ሲል ከገለጽኩት የአንድ ግለሰብነት ይዞታ ይበልጣል፡፡ ይህም ማለት ብዙ ኢሣይያሶች፣ ብዙ ኤሊያሶችና ብዙ ብርሃኑዎች መኖራቸው የአደባባይ መሥጢር ነው ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ አነሳሴ ከወቅቱ የፖለቲካ ሙቀት ጋር የሚቀጣጭ ነው፡፡ አንዴ ሞቅ ደመቅ አንዴ ደግሞ ፈዘዝ ቀዝቀዝ እያለ ሲሻው ደንገላሣ ሳያሻው ሶምሶማ የሚጋልበው የወቅቱ ፖለቲካችን በአብዛኛው ከነዚህ ሦስት ግለሰቦች ዙሪያ አይወጣም – በሒሣባዊ የ“set and subset” ቀመር አኳያ ብንመለከተውም በሺህ ጎራ ተሰልፎ የሚደናቆረው የፖለቲካ ተቃዋሚ ነኝ ባይ ግሪሣ ሁሉ በነዚህ ሦስት ሰዎች ሊወከል ይችላል፡፡ የምናገረው ለኔ እንደመሰለኝ እቅጭ እቅጯን ነው፡፡


ሎራን ካቢላ በአሥራ አንድ ወራት የአመፅ ትግል ሞቡቱን ገልብጦ ሥልጣን ያዘና “ዴሞክራሲያዊት ሪፑብሊክ ኮንጎ”ን መሠረተ – በሥልጣን ብዙ ጊዜ ባይቆይም፡፡ ኢሣይያስ አፈወርቂ የመራው ጦር በመለስ ዜናዊ ትብብርና ሁለንተናዊ ድጋፍ ኢትዮጵያን እንደደሮ ገነጣጥሎ በጥቂት ስኬታማ ዓመታት ውስጥ ለማንም የማትሆን ባለቤት አልባ ሀገር አስገኘ፡፡ የመለስ ዜናዊ የመንፈስ ወንድም የሩዋንዳው ፖል ካጋሜም በጥቂት ወራት ውጊያ መንግሥት ጥሎ በሩዋንዳ “ዴሞክራሲ”ን ገነባ፡፡ ለሤራ ፖለቲካ ማራመጃነት በኃያላኑ መንግሥታት ተጠፍጥፈው እንደተሠሩ የሚነገርላቸውና እንደአለቆቻቸው ሁሉ እነሱም በአምልኮታዊ የሰው ነፍስ ግብር (ጭዳ – death cult) የሚያምኑት ክፉዎቹ የኢስላሚክ እስቴት ወያኔዎችም በጥቂት ወራትና ዓመታት ዝግጅትና ፍልሚያ ምዕራባውያንን የሚያርበደብድ ዘመቻቸውን በማጧጧፍ ዓለምን ጉድ እያሰኙ ነው፤ የኡክሬን አማጽያንም በጣት በሚቆጠሩ ወራትና ሣምንታት ውስጥ ባደረጉት ዘመቻ ከመገንጠል ጀምሮ የራስን መንግሥት እስከመመሥረት ደርሰዋል፤ መነሻውም መድረሻውም የሰውን ዘር በእምነቱ አሳብቦ ከምድር ማጥፋት የሆነው የናይጄሪያው ቦኮሃራም በጥቂት ወራት ትግል ዓለምን “እያስጨነቀ” ናይጄሪያንም እያመሳት ነው፤ … በነዚህ ሁለት ቀናት እንኳን የየመኖቹ ኅዳጣን ሁቲዎች በጥቂት ሣምንታት ውስጥ – ለ‹አንዳርጋቸው ጽጌና ለብዙዎች ኢትዮጵያውያን ዕንባና ጸሎት ምሥጋና ይድረስና› – የሀገሪቱን ቆሾቆምበሬ መንግሥት ዋና ከተማዋ ሰንዓ ድረስ ገብተው ስሊውን በማነቅ ለድርድር እንዲቀመጥ አስገድደውታል፡፡ ስንክሣሩ ቀጣይና እስከዓለም ፍጻሜም የማያባራ ነው፡፡ የዓለም የነማን መፈንጪያ ሆችና …..


በኢትዮጵያ ውስጥ ከወያኔና ከሻዕቢያ በኋላ የተሣካ ዐመፅ ማካሄድና የመንግሥት ሥልጣን መያዝ ያልተቻለው ለምንድን ነው? ከተቋቋሙ ዐርባና ሃምሣ ዓመት የሞላቸው ንቅናቄዎችና የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴዎች ለምንድን ነው – ዘወትር እንደሚባለው ሁሉ – አንዲትም ትንሽዬ መንደር ሊይዙና በ“ጉጉት የሚጠብቃቸውን” ሕዝብ በደስታ ማስፈንደቅ ያልቻሉት? “አታምር ወይ አታፍር” ይባላል፡፡ ንቅናቄዎች ተብዬዎቹ እንዳልሆነላቸው ሲረዱ – መሆንና አለመሆንን መረዳት የሚያስችላቸው አእምሮ ካላቸው ማለቴ ነው – የማያዋጣ የለበጣ መንገድ እየተከተሉ በሕዝብ ላይ ከሚያላግጡ – የወያኔንም ጅራፍ ከሚያባብሱበት – የፖለቲካ ትግሉንም እንደሃይማኖቱና ንግዱ ሁሉ የመተዳደሪያ ቀፈት መሙሊያ ከሚያደርጉት ለምን በጊዜው ጥግ አይዙምና በሕዝብና በሀገር ስቃይ ከመቀለድ አይቆጠቡም? ለምሳሌ ከድርጅት ኦነግ፣ መኤሶን፣ ኢሕአፓ፣ … ከግለሰብ መረራ፣ በየነ፣ ግዛቸው፣ ነገደ፣ ኢያሱ፣ … ሌሎችም የዓዞ ዕንባ አንቢዎች ሁሉ ለምን ከሕዝቡ ጫንቃ ወርደው ራሳቸውን አይችሉም? ወጣቱስ ለምን ተኛ? ለነገሩ ቦታውን ማን ሰጠውና፡፡ አለቃ ገ/ሃና ያቺን ቤታቸው ውስጥ ያሰለቻቸውን ጎመን ጠልተው ጓደኛቸው ቤት ቢሄዱ ያቺው ጎመን ቀረበችላቸውና “በየት ዞረሽ መጣሽ?” አሏት አሉ፡፡ ንቅናቄዎችና እንቅስቃሴዎች እንዲሁም -ዲዶችና ታዋቂ ግለሰቦች ሁሉ ሕዝቡ “ነቄ” ብሏልና በሩ ሳይዘጋ ራሳችሁን እንድትመረምሩ ሃሳብ አቀርባለሁ፡፡


isayas afewerkiኢሣይያስ አፈወርቂ – በቃህ፡፡ ታሪክ ሥራና ሙት፤ የልጅነት ዕድሜህን መስዋዕት ያደረግህበትን የዚያን ዘመን ሁሉ የትግል ውጠየት አየኸው፤ ለአንተ ምን ተረፈህ? መብላት መጠጣትና መስከር? ርሀብን ሊያስታግስ ከማይችል ባዶና አንተው የፈጠርከው ብሔራዊ ስሜት በስተቀር ለኤርትራና ዜጎቿስ ምን አተረፍክላቸው? እውነቱን ብቻ እንነጋገር ካልን በትግልህ ከተጠቀሙት ይልቅ የተጎዱት ይበልጣሉ፡፡ የእልህ ፖለቲካ ከምን ተነስቶ ምን ላይ እንደሚደርስም በራስህ ተሞክሮ ተረዳኸው፡፡ እንዴት እንደምትኖር ከውስጥ ዐዋቂዎች እንሰማለን፡፡ እንዲያ የተቅበዘበዘና አደብ ያጣ ሕይወት የምትመራው ወደህና ፈቅደህ ባይሆንም በሕዝብ ዕንባና ልቅሶ ምክንያት መሆኑን እኔ ትንሹ ወንድምህ ላስታውስህ እወዳለሁ፡፡ ተለያይተው የማይለያዩ የአንዲት እናት ልጆችን በማለያየት ሁለቱንም የቁም ስቅል ስታሳይ ላለፉት 23 ዓመታት ዘለቅህ፡፡ ወደድክም ጠላህም አሁን ሰዓቱ መሽቷል – “ምን እሆናለሁ? ማንስ ምናባቱ ያደርገኛል?” በሚል የቀድሞ ትዕቢትና ዕብሪት የምትመራ ከሆነ የጊዜንና የታሪክን ፍርድ በትግስት ጠብቅ ከማት ውጪ የምልህ የለኝም – አየህ፣ ጠብ-መንጃና ወኔ የሚሠሩበትና የማይሠሩበት ጊዜ መኖሩን አንተም ታውቃለህ ብዬ እገምታለሁ፡፡ የሆነው ሁሉ ሆኖ በዚህ የምሽት ወቅት ግን የአፍሪካ ሲንጋፖር ልትታይ አልቻለችም፡፡ ሕዝብህንም ከስደትና በስደት ከሚገኝ መዋጮ አላዳንከውም፤ ተያይዘን እየጠፋን እንደምንገኝ አታውቅም አልልም፡፡

በአንተ፣ በመለስና በመንግሥቱ የሦስትዮሽ ውጋት ምክንያት ኢትዮጵያ ያጣችው የተማረ የሰው ኃይልና አምራች ገበሬ ለግምት ያስቸግራል፡፡ በዚያም ላይ የዓመታት ጦርነቱን ለማካሄድ የወጣው በመቶ ቢሊዮን ዶላሮች የሚገመተው ገንዘብ ሀገራችንን በአሁኑ ወቅት ከነቻይናና ማሌዥያ ባልተናነሰ በከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ባስቀመጣት ነበር፡፡ ወጪውም ለጦርነት ማካሄጃ በሁለቱም ወገን የተከሰከሰውን ሀብትና ንብረት ብቻ ሣይሆን በጦርነቱ የወደመውን መንግሥታዊና ሕዝባዊ ታህታይ መዋቅርና የዜጎችን በቀላሉ የማይተካ ውሱን አንጡራ ንብረት ሁሉ የሚያካትት ነው፡፡ ድሆች ጦርነትን ሊሠሩ ቢችሉም የመኖር ኅልውናን ግን ሊያረጋግጡ እንደማይችሉ ከነስዬ ዲስኩርና የዲስኩር ባዶነት ተገንዝበናል፡፡ ያ ሁሉ ውድመት የተከናወነው መሠረት በሌለው ጥላቻና ቂም በቀል ተነሳስታችሁ በተለይ አንተና ወንድምህ መለስ ዜናዊ ባካሄዳችሁት እልህ አስጨራሽ አፍራሽ የብረት ትግል ነው፤ እርግጥ ነው አንተና መሰሎችህ ባታምኑበትም ትንቢቱንና የትንቢቱን የአፈጻጸም ቅደም ተከተል ከመነሻው እስከመድረሻው ሳናውቀው ቀርተን አይደለም፤ እናም ታዲያ የጥፋቱ ማሽን ዘዋሪ አንተና ወንድምህ መሆናችሁ ባይካድም መንስኤው ግን ኃጢኣታችንና ክፉ ተግባራችን እንደሆነ ልጠቁምህ እፈልጋለሁ፡፡ ታውቃለህ – “እግዜር ሲቆጣ ሽመል አይቆርጥም፤ ያደርጋል እንጂ ነገር እንዳይጥም” የሚል ብሂል እንዳለን፡፡ አሁንም የምታውቀው ይመስለኛል “ፈጣሪ አንድን ሕዝብ ሊቀጣ ሲፈልግ ጨካኝ ንጉሥን ይሾማል” የሚል ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ተቀምጦ እንደሚገኝ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ያንተና የፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ጀምበር እያዘቀዘቀች፣ ገሚስ አካሏም እየገባች መሆንዋን በድፍረት መናገር የተቻለበት ምክንያትም የኢትዮጵያ ታሪካዊ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ተቀስፈው የተያዙበትን ምችና ዋግ ጠንቅቀን ስለምናውቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የነካ ሁሉ በአሁኑ ወቅት ብጉንጅ በብጉብጅ ሆኖ እያቃሰተ እንደሚገኝ አንተም ከያዘህ ብጉንጅ በመነሳት የምታውቅ ይመስለኛልና በዚያ በኩል ብዙ አልናገርም፡፡

ይልቁንስ ወደልቦናህ ብትመለስ የመልካም ታሪክ ተሻሚ ከመሆን የሚያግድህ ነገር የለም፡፡ በምከተለው ሃይማኖት፣ በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ በመባል የሚታወቀው የክርስቶስ አገልጋይ በፊተኛው ሕይወቱ ልክ እንዳንተው ወንበዴና ፀረ-ክርስቶስ ነበር – ፀረ- ኢትዮጵያዊትህን በውል ሳውቅ ፀረ-ክርስቶስነትህን ከግምት ውጪ አላውቅምና ምስስሉን በዚህ ማሻሻያ አስተካክልልኝ፡፡ ንስሃና ጸጸት ግን አዲስ ስብዕና ያላብሳሉና ከአንጀቱ በማልቀስ ሳዖል ተመለሰ፤ በሩ ሳይዘጋበትም ወደ ጠባቡ አዳራሽ ገብቶ አንገቱን ለሠይፍ እስከመስጠት በሚደርስ ጽናት ክርስቶስን አገለገለ፡፡ ሁሉም ባይሆን ብዙ ነገር ይቻላል፤ አዲስ ስብዕናም መላበስ ይቻላል፤ ባንታደል እንጂ ችኮነትና ካፈርኩ አይመልሰኝ ባይነት የሰውኛ ባሕርይ መገለጫ አይደለም፤ እንደዚያ ከሆን የአእምሮ ባለቤቶች አይደለንም ማለት ነው፡፡ ትልቁ ነገር ራስን መመርመር ነው፡፡ በ11ኛው ሠዓትም ቢሆን የኢትዮጵያ አምላክ የልብ መሰበርን ይቀበላል፡፡ የአንተ ልብ ቢሰበርና አንተን እንደሰው ትታይ ዘንድ የመልካም ሰውነት ባሕርይ ቢያሰጥህ አንተን በጭፍን የሚከተሉና ግደሉ ስትላቸው የሚገድሉ፣ እሠሩ ስትላቸው የሚያስሩ፣ አሰቃዩ ስትላቸው የሚያሰቃዩ አገልጋዮችህ ሁሉ ንጹሓን ዜጎችን ወደምድራዊ ሲዖል ከመክተት ይታቀቡ ነበር፡፡ ለነሱም የጽድቅ መንገድን በከፈትክላቸውና ለምትጨነቅ ነፍሳቸው ዕረፍትን በሰጠሃት ነበር፡፡ በተረፈ ሃሳብ አይግባህ – ኢትዮጵያን ከማንም የዓለም ሀገር ባልተናነሰ ሁሌ የሚያስታውሳት ፈጣሪዋ ነፃነቷን በቅርብ ያቀዳጃታል፡፡ ከቻልህ ምክሬን ስማ፤ ካልቻልክ እንድትቸገርብኝ አልፈልግም፤ ባለህበት ሰላሙን ይስጥህ፡፡


ኤሊያስ ክፍሌ፤ በጣም ከምወዳቸው ጋዜጠኞች አንዱ ነህ፡፡ ልፋትህንና ድካምህን ሰዎች ሲያጣጥሉ ስመለከት እናደዳለሁ፡፡ ዛሬ ለምሳሌ ድረ-ገጽህን ሳነብ ከነብርሃኑ ጂ-7 በተያያዘ ባለህ አቋም የተነሣ ብዙዎች አስተያየቶች ሊያውም በራስህ ሚዲያ ሲያብጠለጥሉህ ሳይ ከፍቶኛል፡፡ ተፃራሪህን ማስናገድህን ግን በጣም ወደድኩልህ፡፡ እንዲህ መለመድ አለበት፡፡ ስለራስ ከሚነገሩ ደግ ደጉን ብቻ እየመረጡ መስማትማ ማን ይጠላል? ይህ በከንቱ የመነቃቀፍና ጫፍ እየያዙ መናቆር እንዲቀር በበኩሌ እየጸለይኩበት መሆኔ በታሳቢነት ተይዞልኝ በጻፍካቸው አንዳንድ ነጥቦች ላይ ግን እኔም የተሰማኝን ቅሬታ መጠቆም ፈለግሁ፡፡ ትፈቅድልኛለህ አይደል?

ብዙዎቹ የምትላቸው ነገሮች በጥንቃቄ ሊታዩና ጆሮ ሊነፈጋቸው የማይገባ መሆናቸውን በበኩሌ አምናለሁ፤ ጭፍን አማኝ መሆንም አልፈልግም – ይጎዳልና፡፡ ግን ግን ለምሳሌ ግንቦት ሰባት ያለው የተዋጊ ኃይል ከአሥር አይበልጥም ስትል ምን ማለት እንደሆነ ደጋግሜ አስተንትኜው ፈጽሞ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ አንተም በቅጡ ያሰብክበት አልመሰለኝም፡፡ የምትለውን ሁሉ ለማመን የማላመነታ ቅንና የዋህ አንባቢ ነኝ ልበልና ራሴን ላሳምን፡፡ ግንቦት ሰባት ታዲያ ለማስመሰልም ቢሆን ከአሥር የሚበልጡ ወታደሮች አይኖሩትም ብለህ ትገምታለህ? እንደሰማሁት ወደ ሰባት ይሁን ዘጠኝ ዙር ያህል ተዋጊ ወታደሮቹን እንዳስመረቀ ተዘግቧል፡፡ በአንድ ዙር ሁለት ወታደሮችን አሠልጥኖ ቢያስመርቅ እንኳን ቢያንስ አሥራ አራት ወይም አሥራ ስምንት ወታደሮች አይኖሩትምን? ታዲያ በዚህ ረገድ ኤሊያስ ምን ትለኛለህ? ይህ ግነት መንስኤው ምን ሊሆን ይችላል? ይህን ያህል ዝቅ ብለህ – መረጃው እውነትም እንኳን ቢሆን – የወዳጅን ምሥጢር ለጠላቶች መስጠት ተገቢስ ነው ወይ? የጦር ኃይል መጠንና የሥልጠና ሁኔታ፣ የመሣሪያ ዓይነትና ብዛት፣ የስንቅና ትጥቅ ምንጭና አቅርቦት፣ ወዘተ. የአንድ ድርጅት ምሥጢሮች መሆናቸው ይታወቃል – አንተ ደግሞ ምድብህ በተቃውሞው ጎራ መሆኑን ስለማውቅ – እንደእስካሁኑ ከሆነ ማለቴ ነው – ቢያንስ ከወታደራዊ ምሥጢሮች ወጣ ያሉ ተቃውሞችህን በንቅንቄው ላይ ብታሰማ የወግ ነው፡፡ ለምሳሌ የኤርትራ መንግሥት ሊታመን የማይችል በመሆኑ ሌላ አማራጭ መፈለግ ይሻላችኋል ዓይነት ሃሳብ ብትሰነዝር በበኩሌ አይከፋኝም ብቻ ሣይሆን ደጋፊህም ልሆን እችል ነበር፡፡ ያ የጂ -7 ተዋጊዎች ከአሥር አይበልጡም የሚለውና መሰል ውኃ የማያነሱ ቃላተ-ቅዋሜዎች ግን ምን ዓላማ ሊያራምዱልህ እንደሚችሉ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ እንዲያ በማለትህ በአንተና በንቅናቄው መካከል ያለውን ግንኙነት በጣሙን እንድጠራጠር አድርጎኛል፡፡ ምሳሌ ነው ይህን ያልኩህ፡፡ በተረፈ “ሽልም ከሆነ ይገፋል፤ ቂጣም ከሆነ ይጠፋል” እንዲሉ ነውና የምትወራከቡበትን ማዕከላዊ የቅራኔ ነጥብ እውነትነት ለማረጋገጥ ትንሽ ጊዜ ሳያስፈልገን የሚቀር አይመስለኝም፡፡ እስከዚያው ግን ለትዝብት በማይዳርግ ሁኔታ ብንተቻች ቢኖረን ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ሁሉም ጥንቅር ብሎ ለሚቀረው ነገር በከንቱ መጠላለፉ ለማንም አይጠቅምም፡፡

እስኪ ዐይናችንን እንጨፍንና ከመቶ ዓመት በፊት ወደነበረው ጊዜ በምናብ እንሂድ፡፡ እስኪ አሁንም ዐይናችንን እንጨፍንና ከአንድ መቶ ዓመት በኋላ ያለውን ጊዜ በምናባችን ለማየት እንሞክር፡፡፡ ይህ ሁሉ መራኮት ከነዚህ ሁለት መቶ ዓመታት ውስጥ በየትኞቹ አሠርት ዓመታት ውስጥ ነው ተዘርቶ፣በቅሎ፣ አሽቶና ተመርቶ ወደታሪክ ጎተራ የሚከተተው ብለን ደግሞ እናስብ፡፡ አያችሁ – ነቢዩ ሶሎሞን በመጽሐፈ መክብብ “ሁሉም ከንቱና የከንቱ ከንቱ ነው” ማለቱ ለዚህ ነው፡፡ ይህ ሁሉ መጠላላታችን፣ ይህ ሁሉ ጠብና ግጭታችን፣ ይህ ሁሉ መገዳደላችን፣ ይህ ሁሉ ለገንዘብና ለሥልጣን መጓጓታችንና መስገብገባችን፣ ይህ ሁሉ ትርምስ … እንግዲህ ለዚህች ብቅ ብላ ለምትጠፋ እንደጤዛም ለምትመሰል አጥበርባሪ ሕይወት ነው ማለት ነው፡፡ እውነትን እያስታወስኩ እንጂ ሃይማኖትን እየሰበክሁ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡ ሴትዮዋ ምን ነበር ያለችው ? “እንዲህ ልጠግብ በሬየን አረድኩ”፡፡ ኋላ የምንቆጭባቸው ነገር ግን ደስ እያለን የምንገባባቸው ጉዳዮች ብዙ ናቸው፤ ዲያብሎሳዊ ምርቃና ደግሞ ክፉና የክፉ ክፉ ነው፡፡ ሦስተኛውን ዐይናችንን እንዲከፍትልን አምላክን እንጠይቅ፡፡ (በነገራችን ላይ የቪኦኤው ሄኖክ ሰማእግዜር ፈንቴን ምን ነካውና እንዲያ በቁሙ የተበለሻሸው? ምን ጎደለብኝ በሎ ነው ቆሻሻ ቱቦ ውስጥ ወድቆ እየተግማማ ቪኦኤንም ሊያበክተው የፈለገው? ለገንዘብ ነው ለዓላማ ወይንስ ለእውነት ጥብቅና የቆመው? ወዳጅ ካለው ይምከረው፡፡)


Dr. Berhanu Nega and Dr. Beyan Assoba on ESAT TVዶክተር ብርሃኑ ነጋ፡፡ ሀገር ቤት ውስጥ ስላለሁ ለናንተ ንቅናቄ ሕዝቡ ያለውን ደግና በርህራሄ የተሞላ አመለካከት ለመገንዘብ ችያለሁ – ስሜታዊ ቅኝት እንጂ ሣይንሳዊ ጥናት ግን አላደረግሁም፡፡ ዕድል እንዲገጥማችሁ ፈጣሪን የሚለምነው ብዙ ነው፡፡ በተለይ አንዳርጋቸው ጽጌ ታሪክ በቅርቡ ሊያወጣው በሚችለው አሁን ግን ሥውር በሆነ ምሥጢር የተነሣ ለወያኔው የምሥራቅ አፍሪካ ካሊፌቶች ተላልፎ ከተሰጠ ወዲህ የሕዝቡ ስሜት ክፉኛ ተለውጧል፤ በግልጽ አይናገረው እጅ ውስጥ ውስጡን እየተብሰከሰከ ነው – የሚፈልገው ማስተንፈሻ ቀዳዳ ነው፡፡ ሕዝብ ስል በሆዳምነትና በዘረኝነት አረንቋ ገብቶ የሚዳክረውን በሰው ቅርፅ የሚንቀሳቀስ አጋሰስና አድርባይ ሣይሆን ጭቁኑንና የኢትዮጵያን ትንሣኤ አንጋጦ በጉጉት የሚጠባበቀውን ማለቴ ነው፡፡ ሕዝብ ሕዝብ ሲባል ሁሉም እየተነሣ ይህን መከረኛ ቃል ስለሚናገር ሕዝብ ሲባል ምንና ከማን አንጻር እንደሆነ መለየት አስፈላጊ ነው፡፡ ዘምቦለል አርቲስቱም፣ መዥገር ፖለቲከኛውም፣ ሐሳዩ መሲህ ‹የሃይማኖት አባቱ›ም፣ … ብቻ ሁሉም እየተነሣ “ሕዝብ፣ ሕዝቡ፣ ሕዝቤ፣ ሕዝባችን፣ ለሕዝባችን፣ በሕዝባችን፣ ከሕዝባችን…” ሲል ሁልጊዜ ይገርመኛል፡፡ ዓለም ለይቶላት የውሸት መናኸሪያ መሆንዋን ከምረዳባቸው አመላካች ነጥቦች ውስጥ አንዱ ይሄው ነው፡፡
ወያኔን መጣል የተፈቀደለት አካል ይህን ዕኩይ የአፍሪካ ካሊፌት በቀላሉና ካለብዙ ወጪ እንደሞጄሌ ከነሰንኮፉ መንግሎ እንደሚጥለው በበኩሌ ቁልጭ ብሎ ይታየኛል፡፡ … ሌሊን የዛሩን መንግሥት ለመጣል በሚታገልበት ወቅት መካሪዎች “አንተ ምን ቅብጥ አድርጎህ ነው ይህን ግምብ መንግሥት ለመጣል ካለአቅምህ የምትፍጨረጨረው?” አሉት አሉ፡፡ እሱም አላቸው – “የምትሉት ነገር እውነት ነው፣ የዛሩ መንግሥት ትልቅ ግምብ ነው፤ ነገር ግን ግምቡ የበሰበሰ በመሆኑ በቀላል ግፊ ይወድቃል፡፡” ሌኒን እውነቱን ነበር፡፡

የወያኔ ግምብም ሰው አጥቶ እንጂ ከበሰበሰ ቆይቷል፡፡ ደፋሪ አጣ፤ ጀግና አጣ፡፡ በኅብረት የሚበላ እንጂ በኅብረት አታግሎ ለድል የሚያበቃ የነፃነት አርበኛ አጣ(ን)፡፡ ይህን እውነት የሚናገሩ ዜጎችን ቀንድ ቀንዳቸውን ማለት የተለመደ ቢሆንም የበሰበሰ ዝናብ ስለማይፈራ እኔ የሚሰማኝን እናገራለሁ፤ አሃ፣ መፍራት ደግ ነው ጎበዝ! ሥነ ልቦናችንን ሁሉም ከየአቅጣጫው አደቀቁትና ልምጥምጥ ሆነን ቀረን አይደል?

ለኢትዮጵያ ነፃነት በጦር እታገላለሁ ብሎ ማንም ኢትዮጵያዊ መነሣት ይችላል ብዬ በበኩሌ ካመን ቆይቻለሁ፡፡ ምክንያቱም ወያኔ ካለጦር በምንም መንገድ አራት ኪሎን እንደማይለቅ ግልጽ ነውና፡፡ ውሻን ከአጥንት፣ ጅብን ከአህያ በድን ማላቀቅ የሚቻለው በኃይልና በጉልበት እንጂ በጩኸት የማይሞከር ነው፡፡ በግሌ የማላምንበት ግን ከአሁን ወዲያ የዚህ ወይም የዚያ ጎሣ ጦር የሚባል ነገር ዳግም ሊጠቀስ የማይገባው መሆኑን ነው፡፡ እሱ ነውር ነው፡፡ በዘጠና ነገድ መሀል የአንድን ነገድ ወይም ዘውግ መብት ለማስከበር ዘጠና ጦር ሠራዊት ማቋቋም ማለት እንደወያኔ ሀገርን በኳስ አበደች ለማተራመስ ማቆብቆብ ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አሁን የምናያቸው ዴምሃትን የመሳሰሉ የትጥቅ ኃይሎች ለሕዝብ የሚያስቡና ሕዝብን ማዕከላቸው የሚያደርጉ ከሆነ ብዙ ሳይረፍድባቸው ስማቸውንና የፖለቲካ አመለካከታቸውን ወደ ኅብረ ብሔራዊነት ይቀይሩ፡፡ ስም ብቻም አይደለም – ሕዝብ በሚወዳት ሰንደቅ ዓላማ ላይ የለጠፉትን ሀውልት በአፋጣኝ ያንሱ፡፡ እንዲህ የምለው “የአክሱም ሀውልት ለደቡቡ ምኑ ነው?” ያለው የዚያ ጋጠወጥ ልጅ ንግግር ትዝ ብሎኝ አይደለም፤ የጎሣ ወይም የቡድን ፖለቲካ አንዱ ችግር ባንዴራንና ሕገ መንግሥትን በመሳሰሉ ታላላቅ ጉዳዮች ላይ ኃይል የሚሰማቸው ጥቂቶች በዝግ ስብሰባቸው እየወሰኑ ሕዝብ ላይ መጫናቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንገሽግሾናል፤ ቋቅ እስኪለን ባለፉት በስባሳ ማኅበራዊ ሥርዓቶቻችን አለውድ በግዳችን እንድንጋታቸው ተደርገናል፡፡ ማንም ግን አልተጠቀመም፤ ስንረጋገም ይሄውና እነሱም እኛም መቅኖ አጥተን በምናብም ይሁን በአካል ከመንከራተት አልወጣንም፡፡ ድንጋይ ራሷ ሰምሃል መለስ አምስት ቢሊዮን ዶላር በስሟ መቀመጡን እንደመታደል ከቆጠርነው ስህተት ነው፡፡ ዶክተር አርከበ ዕቁባይ በተንጣለለ ግቢ በብዙ ሀብት እየተዝመነመነ መኖሩን ከጤና ከቆጠርነው ተሳስተናል – ለዚህም ነው ሁላችንም በሽተኞችና ሰላም የሌለን ተንከራታቾች ነን የምለው፡፡ አሁንም ልድገመው – በኢትዮጵያ ምድር ገዢዎችም ተገዢዎችም አልታደልንም፡፡

እነብርሃኑ የነፃነታችን ምክንያቶች መሆናችሁ እውነት ከሆነ በበኩሌ እንዲህ ብታደርጉ ደስ ይለኛል፡፡ እንዴት ብሎ መጠየቅ ከጨዋ ሰው ይጠበቃል፡፡ በግል ካልጠየቃችሁኝ ደግሞ እዚህ አልናገርም፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ ኧረ ቆይማ አንድ ነገር ትዝ አለኝ – በሀገራዊ ወኔው በጣም የምወደውና የማከብረው እንትናዬ አንድም ቀን በቀጥታም ይሁን በተዛዋሪ ስለፈጣሪ (ስለእግዚአብሔር አላልኩም) ትንፍሽ ብሎ የማያውቀው ለምን ይሆን? ለነገሩ ማመን አለማመን የግል ጣጣ እንጂ እኔን ምን አገባኝ?…)

ለመሰነባበቻ፤
“የታሪክ አጤሬራ”

አጤሬራ ማለት የዘመኑ ትምህርት ቤታዊ ልክፍት ነው – ተማሮች በእጃቸውም በወረቀትም ለፈተና መልስ ይሆናሉ ብለው የሚገምቷቸውን ነጥቦች ባጭር ባጭሩ ጽፈው ወደፈተና አዳራሽ የሚያስገቡት የባዶ ጭንቅላት ማሳያ ጽሑፍ አጤሬራ ይባላል፡፡ ቀጣዩን አጤሬራ አንብበህ የማትናደድ ከሆንክ መናደድ ብሎ ነገር አልፈጠረብህም፡፡ ስለዚህ ያለህበት ሁኔታ እንደሚገባህ ወስነሃል ማለት ነው፡፡

ሀ. ተፈሪ መኮንን፤ ጅብ፣ ዓሣማ፣ ምሥጥ፣ መሠሪ፣ ተንኮለኛ፣ አስመሳይ፣ ራስ ወዳድ፣ የሁለት ጌቶች ተገዢ፣ ‹አነር›፣ ስግብግብ፣ሥልታዊ፣ …
ለ. መንግሥቱ ኃ/ማርያም፤ አህያ(ከደደብነት አንጻር ብቻ!)፣ ቆቅ፣ ግልብ፣ ደንቆሮ፣ ግትር፣ እልኸኛ፣ ሥልጣን ወዳድ፣ ሰይጣን፣ ጭራቅ፣ ዕብሪተኛ፣ ኢ-ሥልታዊ፣ ግልፍተኛ፣ አርቆ የማያይ፣ የአንድ ጀምበር ሰው፣ …
ሐ. መለስ ዜናዊ፤ (ከ“ሀ” እና ከ“ለ” ብዙ የሚጋራቸው ባሕርያተ ሰውና ባሕርጣተ አጋንንት አሉት)፣ ውሻ፣ ፍየል፣ እባብ፣ እስስት፣ ከሃዲ፣ ዘረኛ፣ አግቦኛ፣ አሽሙረኛ፣ ሥራየ ቤታዊ፣ ሊቀ ሣጥናኤል፣ ግብዝ፣ …
መ. ምዕራባውያን፤ ፍየሎች፣ ሰይጣን አምላኪዎች፣ ባፎሜታውያን፣ ሸፍጠኞች፣ አስመሳዮች፣ ገሃነማውያን፣ መሠሪዎች፣ ሆዳሞች፣ አስመሳዮች፣ የታሪክ ቀበኞች፣ ዘረኞች፣ ፀረ-ሕዝቦች፣…

የኤርትራን ካርታ ለአፍታ አስብ፡፡ ከሱዳን ተነስቶ የሣህል በረሃንና ቀይ ባሕርን ይዞ ሺዎች ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ የት እንደገጠመ ልብ በል፡፡ የኮንጎን ካርታ ደግሞ ለአፍታ አስብ፡፡ እንዴት በመሰለ ቀጭን መስመር ኮንጎን ወደባሕር እንዳቆራኛት አስተውል፡፡ የሰዎችን ተንኮልና ቀናነትም በዚህ ተረዳ፡፡ አንዲትን ሀገር ሆን ብሎ የራሷን ግዛት በመቀስ እንደዶሮ በልቶና ቆርጦ ቆራርጦ የባሕር መውጫ ለማሳጣት የተሤረውን ሤራና ያን ሰይጣናዊ ሤራ እውን ለማድረግ የተሄደውን ርቀት ልብ በል፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ ዜጎች ለዓመታት ደጅ ጠንተውና ከፍተኛ እጅ መንሻ ጉቦ ከፍለው 72 ሜትር ካሬ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ እየተሰጣቸው ባለበት ሁኔታ፣ የውጪ ኤምባሲዎቻችን በየሽንቁላው በአነስተኛ ክፍሎች ተወትፈው በሚገኙበት ሁኔታ፣ … የአሜሪካንን፣ የፈረንሣይንና የእንግሊዝን ኤምባሲዎች የግቢ ስፋት ልብ በል፡፡ እያንዳንዳቸው እነዚህ ሀገሮች የያዙት ቦታ ጂቡቲ፣ ጂቡቲን ያካክላል – ፈረስ ያስጋልባል የሚለው ሥነ ቃልም አይገልጸውም፡፡ ምክንያቱም ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣላ፡፡ ደግሞም ምክንያቱም “ሞኝ የለቱን ብልህ ያመቱን” ይባላላ፡፡ እናሳ መሪዎች ነበሩን? አሁንስ አሉን? የአሁኖቹን ግዴለም ተዋቸው፡፡ ዱሮስ ነበሩን? ከነበሩንስ ከአንድ ወር በላይ ሊራመድ የሚችል ርዕይ(ቪዥን) ነበራቸውን? እንዲያ ገምድለው ገምድለው ለየኤምባሲው ያን ያህል ኹዳድ የሰጧቸው ምን ነክቷቸው ይሆን? ከመግረም አልፎ በሞኝነት ያስቀኛል፡፡

ለ1600 ዓመታት ጳጳስ ከግብጽ እናስመጣ ነበር አሉ፡፡ ሙስሊሞቹ ግብፆች ቢቸግራቸው ቁመተ ዠርጋዳውን ሙስሊም ሰላይ የጳጳስ ልብስ እያለበሱ በስመ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ወደኛ ይልኩልን ነበር አሉ – በሣይቸግር ጤፍ ብድር የገባንበትን ዕዳ በወርቅና በእምነት ሊያስከፍሉን፡፡ በማከያው ከኛ ሰው የጠፋ ይመስል ምሥጢሩ እስካሁን ባልታወቀ ሁኔታ ኢትዮጵያ በግብጽ ተፅዕኖ ምክንያት የዓለም ሬሞርኬ (ተጎታች) ሆና ቀረች፡፡ ለምን ቢሉ – እሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣልና፡፡ ሀፍረትን አናውቅም እንጂ ይህም ነገር እጅግ በሀፍረት ሸማቅቀን በተገባ ነበር፡፡ የክርስቲያን ደሴት የሆነችው ኢትዮጵያ ከሕዝቧ 90 በመቶው ሙስሊም ከሆነና መንገሥታዊ ሃይማኖቷ እስልምና ከሆነ የጥቅም ተጋሪ ሀገር – ለሸፍጥ ሥራ ቀጭን ሰበብ በሚያስፈልጋት ግብጽ ጳጳስ “ኢምፖርት” እናደርግ ነበር፡፡ ዕንቆቅልሽ፡፡ ተናደድ!

ያገርህን የዘመኑን ደናቁርት ባለሥልጣናት ተመልከት፡፡ ከዋሽንግተን ቀርቶ ከመንግሥተ ሰማይ ሳይቀር ስልክ ደዋይ ጋዜጠኛ “ወንጀለኛ”ን ካለበት ሊያስር የሚችል ሊያውም ነቃ ባለው የቦሌ ወረዳ የተመደበ የፖሊስ ኮሚሽነር የምታገኘው በሀገርህ ብቻ ነው፡፡ ሀፍረት ሞታ ተቀብራለች፡፡ ያሣፍራል፡፡ እንደሀገር ብቻ አይደለም ይህ ሁኔታ ሊያሣፍር የሚገባ – እንደሰው ፍጡርነትም በሀፍረት ሰውነትን ሊያሳንስ የሚገባው መራር እውነት ነው፡፡ ሰው ጠፍቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስን የመሰለ በወሣንሳ የሚነሣ ባዶ ቀፎ ሀገርህን በፕሬዝደንትነት “እንዲመራልህ” ተሹሞልህ በዚህ ቶርቶራ ሰውዬ “ወርቃማ አመራር” ዓለምህን ቀጭተሃል – ዕድገትህም ሰማይ ደርሶ ስደትህንና ጠኔህን አስፋፍተህ ቀጥለሃል፡፡ ሰው ጠፍቶ በስመ የፖለቲካ ታማኝነት ራሱንና አካባቢውን እንኳን አስተካክሎ ሊገልጽ የማይችል የምሁር ማይም ደሳለኝ የሚባል ጠቅላይ ሚኒስትር ተጎልቶልሃል፡፡ በየዓለም ሀገራቱ ኤምባሲዎቻችንን ለብቻ ተቆጣጥረው የሚገኙት ወያኔ ወንድም እህቶቻችን ከፊደል መቁጠር እምብዝም ያለፉ አይደሉም – ማይም አጋሰስ ደግሞ ከ24 ሰዓት ውስጥ ወደ 30 የሚጠጋውን ስለሆዱ ሲጨነቅ ይውል ያድራል እንጂ ለሀገር ሥራ አንዲት ሴከንድም አያውልም፡፡ ሦስተኛና አራተኛ ክፍል “ግራጁየት”(ምሩቅ) ጄኔራልና ከርኔል የሆኑባት ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ምርጫ በሌለበት ሁኔታ በምርጫ ስም እጅግ ብዙ ገንዘብ በይስሙላው ምርጫ ሰበብ የሚከሰከስባት ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ናት – በዚህስ ኤርትራ ተሻለች – ወዲ አፈወርቂ እውነቱን ነው በትያትር ለምን ገንዘብ ይባክናል? ከቀበሌ እስከ ታላቁ ቤተ መንግሥት ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎች በአንድ ዘውግ የሚዘወሩና በአብዛኛው የአንድ መከረኛ ዘውግ አባላት የሆኑ ከነዚሁም ብዙዎቹ ፍጹም ዘረኛና ትምህርት ዕርማቸው የሆኑ ማይማን ሆዳሞች ናቸው – ይህም በግልጽ የሚታየው በሀገርህ ውስጥ ነው፡፡ በአንድ ዘውግ ላይ በፈረንጅኛው አጠራር ጄኖሣይድ የሚባለው ዕልቂት ታውጆ ያ ዘር በየሚገኝበት ሥፍራ ሁሉ እንደዐይጥ እንዲጨፈጨፍ፣ ዘሩም እንዲመክን፣ ከሀብትና ከመንግሥታዊ ሥልጣንም እስከወዲያኛው እንዲወገድ የሚደረገው በኢትዮጵያ ሊያውም በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሰው ልጆች ሥልጣኔ ላይ ነው፡፡ በአንድ የታሪክ አንጓ ላይ በሰሜናዊ ምዕራብ ኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ነዋሪ የነበሩ ሕዝቦችን በመሪር አገዛዝ ያንቀጠቅጥ የነበረውን የቀድሞ ንጉሠ ነገሥት ዓርማ በማንሣት እነዚህ አሁን ሥልጣን ያሉ በላኤሰቦች በ“የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ” አረመኔያዊ አገዛዛቸው ተሻሽሎ የተቀመረን ስቃይ ሕዝብ ላይ ቀጥለው የሚገኙት በዚሁ ዘመን ነው፡፡ እሊህ የእፉኚት ልጆች የባንዳ አባቶቻቸውን ቂም በቀል አንግበው ከየአካባቢው የሚገኘውን ለምና ምርጥ ቦታ የኛ ክልል ነው ወደሚሉት ነዋሪን እያፈናቀሉና አልነሳም ብሎ የሚያንገራግርንም አለርህራሄ እየጨፈጨፉ የሚገኙት በዚህ ዘመን ነው፡፡ በኦጋዴን፣ በሶማሌ፣ በጋምቤላ፣ በሸዋ፣ በጎጃም፣ በሐረር… ሰዎቻቸውን እያዘመቱ መሬት የሚቀሙና ለጥሪ እንኳን በማይበቃ ርካሽ ዋጋ ለባዕዳን የሚሸጡ፣ ባለይዞታዎችን በመትረየስ እየረፈረፉ አስከሬኖችንም ከጭፍጨፋ ለጥቂት በተረፉ ምሥኪን ወገኖቻችን ከየወደቁበት እያሰበሰቡ “ደርድር፤ እዚያ ጋ በብዛት አለ አይደል እንዴ” የሚሉ ጉዶች የተፈጠሩብን በዚህ ዘመን ነው፡፡ የአሜሪካን ወታደሮች በአልቃኢዳዎች ሬሣ ላይ ሽንታቸውን ቢሸኑ የሥልጣኔያቸው ጉዳይ ውሃ እንደበላው ተቆጥሮ በሀገር ልጅነትና በሌሎች ነገሮች ስለሚለያዩ ነው ሊባል ይችል ይሆናል – ሰብኣዊነትንም ለጊዜው ዘንግተንላቸው፡፡ የኞች ግን ምን እንደነካቸውና ልባቸው ለምን እንደዚያ እንደደነደነ፣ በሬሣ ላይ ሣይቀር ለምን እንደዚያ የሰውነት ባሕርያቻው ወደ ጭራቅነት እንደተለወጠ ቀን ሲመጣ መጠናት ያለበት አስደንጋጭ ጉዳይ እንጂ አሁን በቀላሉ ልንመልሰው የሚቻለን አይደለም፡፡ አጤሬራየን እዚህ ካልቋጨሁት- ስዶጎዱግ ውዬ ስዶፎዱግ ማደሬ ነው፡፡ ለማንኛውም መልካም አዲስ ዓመትና መልካል የመስቀል በዓል በዓል፡፡ መስከረም 13 ቀን 2007፡፡ ይቺን 13ትን እንኳን አልወዳትም ነበር …


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>