ወንድሙ መኰነን
የለንደኖቹ ልማታዊ “ ካኅናት ” ወያኔያዊ ዘጋቢ ፊልምአቀናበሩብን !
ኢንግላንድ መስከረም ፯ ቀን ፪፲፻፯ ዓ.ም
መግቢያ
እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ። መባል ስላለበት ነው። ያለፈውማ ዓመትአንደኛውን ጥቁር ዓመት ተብሏል። ሲያንሰው ነው። ወያኔ ከመቼው በበለጠ ጥቃቷን በኢትዮጵያ ልጆች ላይ በሁሉም አቅጣጫ ያጧጧፈችበት ዓመት ነበር። ነጻውን መገናኛ ብዙሀን ከጨዋታ ውጪ አድርጋለች። ብዙ ጋዜጠኞች በማሠሯ ወህኔ ቤቱ ጠቧል መሰለኝ፣ አሁን አሁን የያዘችው ዜዴ፣ በቁጥጥሯ ሥር ከሌሉ፣የፋሺን ጋዜጠኞችም ሳይቀሩ ማዘዣ ሳይደርሳቸው፣ በሬዲዮዋና በጋዜጦቿ “ከስሼአቸዋለሁ!” በማለት ፣ ነጭ ሽብር እየነዛችባቸው በርግገው ከአገር እንዲጠፉ ማሳደዷን በሰፊው ተያይዛቸዋለች።
በዓመቱ መጨረሻ ወር ብቻ 21 ጋዜጠኞች ተደናብረው አገር ጥለው እግሬ አውጪኝ ብለዋል።ሲሸሹም እያየች አታስቆማቸውም። ብቻ ሲወጡላት፣ “እስየው ተሰደዱልኝ!” ብላ “ደቁሴ ንሬ፣ ተባራብሬ!”ዋን ትደልቃልች! ወንድማችን እስክንድር ነጋ፣ እህታችን ርዕዮት ዓለሙና ሌሎች ጋዜጠኞች ብዕር ስላነሱባት ተሸብራ “ሽብርተኞች” ብላ ወህኒ አጉራቸዋለች። አንዷለም አራጌ፣ በአንደበቱ፣ “ወያኔ የሰው ልጅ መብት ረጋጭ ነው” ብሎ ጮክ ብሎ በመናገሩ ተሸብራ፣ 14 ዓመት ፈርዳበት ቃሊቲ ወርዶ ፍዳውን እያየ ነው። ነፍጥ አንስቶ አንድ ሁለቱን ቢደፋማ ኑሮ፣ “እንደራደር” እያለች አፏን ታሞጠሙጥ ነበር። አሁን በቅርብ ቀን ወያኔ እያዳፋች የወሰደቻቸው እነ ኃብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ ዳኒኤል ሺበሺ፣ አብርሀ ደስታ በቃላት ካለሆነ በጥየት የት ቦታ ነክተዋት! ዕውነትም ዓመቱ የጨለማ ዓመት ነበር። የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል ግን፣ ወንድማችንን፣ አንዳርጋቸው ጽጌን፣ አለማቀፍ የአየር ትራንስፖርት የመንገደኞችን ደኅንነት በጣሰ ሁኔታ መጥለፏ ነው። ይኸ ወንጀል ብዙዎቻችንን ቆሽታችንን አድብኖታል። ለንደን ደብርጽዮን ቅድስት ማርያምን ከሕዝቡ ቀምተው ለወያኔ ሊያስረክቡ ለሁለት ዓመታት ጎልተው የሚሞግቱን ልማታዊ ካኅናቶቿ ግን በደስታ እያሸበሸቡ ነው። እንዲያም ዘጋቢ ፊልም ሠሩብን!
ካኅን ማነው ?
አንድ ጭብጥ እንያዝ። በመጀመሪያ “ካኅን ሊባል የሚቻለው ማነው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጥ። ክኅነት የተቀበለ ሁሉ ካህን አይደለም። ክኅነት ደረጃ ደረጃ አለው። ከንፍቀ ሲያቆን ይጀምራል። ከዚያም ዲይቆን ይባላል። ቀጥሎም ለሊቀ ዲአቆንነት የደረሳል። ሊቀ ዲያቆኑ ን|ጽሕናውን እንደጠበቀ፣ ሲዳር (ትድር ሲይዝ) ይቀስሳል። ከዚያ በኋል ካህን ይባላል። በመሀሉ ዘማሪዎችና መሪጌታዎች አሉ። እንደሱ ካልሆነማ እኔም ካህን ልባል ነዋ! የንፍቀ ድቁና ክኅነት እኮ ተቀብዬአለሁ። ያውም ከአቡነ ቄርሎስ እጅ! አንድ የቤተ እግዚአብሔር አጋልጋይ ለካኅንነት ማዕረግ የሚበቃው፣ ቄስ ሲሆን ብቻ ነው። ዲያቆን ካህን አይደለም! ገና ይቀረዋል። የመነኰሰ ሁሉም ካኅን አይደለም። መነኵሴ በሁለት ይከፈላል። አንዱ ገና ከሕጻንነቱ/ልጅነቱ ጀምሮ እራሱን ለእግዚአብሔር የለየ ድንግል ( ይሰሙኛል አባ ተባዩ – መንደር ሲያውደ ለድል ሕይወት አጣጥሞ ከብሒራዊ ውትድርና ለማምለጥ ገዳም የተሸሸገ ወሮ – በላ ሳይሆን ከሕጻንነቱ የተለየ ድንግል !!)ባሕታዊ ነው። ይኸ ሰው ከመጀመሪያውም ለአገልግሎት የተጠራ በመሆኑ ገዳማዊ መነኵሴ ይባላል። በድቁና እያገለገለ ይኖርና፣ እድሜው ለአቅመ አዳም ሲደርስ፣ ንጽሕናው፣ ተመስክሮለት በቅስና ያገለግላል። ያ ገዳማዊ መንኵሴ ነው። ሌላው ደግሞ የዚህች ዓለም አሸሻ ገዳሜን ሲጨርስ፣ የተወሰነ የአካሉ ክፍል አልሠራ ሲለው በቃኝ ብሎ የሚመነኵስ ነው። የሶስት ዓመቱን አመክሮ ከጨረሰ በኋላ፣ ቆብ ደፍቶ ዓለም በቃኝ ያለ ነው። ያ ሰው፣ በምንም ዓይነት ሊቀስሥ አይችልም። የቀረችውን ጊዜውን አምላክን እየለምኑ ይኖርና ዓለሟን መገላገል ነው። “አባ ግርማ” ካኅን ናቸው? ካህን ጥራ ቢባል እራሱ ግሩም መጣ ተብሏል። ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ! ካኅን ጠብቅ የተባለውን መንጋ አይበትንም! ካህን ሥልጣን አይፈልግም። ካህን ገንዘብ አይወደም!
የለንደኖቹ ልማታዊ “ ካኅናት ” ዘጋቢ ፊልም።
አንዳርጋቸው መጠለፉን ተከትሎ፣ ወያኔ፣ ዶኩመንተሪ አይሉት ዜና፣ እንደልማዷ አንድ ዝግጅት አዘጋጅታ፣ በቴሌቪዥን ለዓለም ሕዝብ አሰራጭታዋለች። የቤተክርስቲያናችንም ጉዶች ከወያኔ ጋር በመተባበርና የወያኔን ቴሊቪዢን እንደዋና መረጃ ምንጫቸው አድርገው፣ ዘጋቢ (ዶክዩመንታሪ) ፊልም፣ ይታይላቸው እንጂ! እነሆ እየኮመኮማችሁ ተዝናኑበት!
በውስጡ የታጨቀው የወያኔ ቱልቱላ ነው። ባጭሩ ፍሬ ከርሲኪ ነው። እሱን ለተመልካቹ ተተን፣ አቅናባሪውና ተዋንያኖቹ እነመማን እንደሆነ በአጭሩ ቀርብ ብለን፣ በመረጃ ተንተርሰን እያንዳንዳቸውን እንመርምር። “ጉድና ጅራት ከበሰተኋላ ነው” የሚሉት አበው ሲተርቱ?
የስም ላጲሱ የወያኔ ፊልም ቀራጭ
እንዳለ ወንዳፍራሽ ይባላል። ሲበዛ ባሌጌ ነው። አዋራጅ ነው። የወያኔ አገልጋይ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ፣ ጥቁር መነጽርና ኩፊያ ከራሱ ወርደው አያውቁም። በፈረንጆቹ አቆጣጠር እስከሁለት ሺ ዓ.ም. ድረስ እኔን፣ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢን በጣም ይቀርበኝ ነበር። እኔም ሰው መስሎኝ፣ አቀርበው ነበር። ጽሑፎቼንና ግጥሞቼን በአማርኛ እየተየበ፣ በራሱ አነሳሽነት እያባዛ ይበትን ነበር። በፈረንጆቹ አቆጣጠር፣ ያንን ሰው ከአገር ወዳድነት በአሻገር ለወያኔ ያገለግላል ብዬ አንድም ቀን ጠርጥሬው አላውቅም። በሬ ከአራጁ ጋር ይውላል ማለት እኔ ነኝ። የትም እንሂድ ቢለኝ፣ እሄድለት ነበር። እንገናኝ ብለኝ ምንም ሳላወላውል አገኘው ነበር። አንድ ቀን አንድ የወያኔ አራጊ ፈጣሪ ግለ ሰብ ከሚያስተዳድረው ድርጀት ሲወጣ ፊት ለፊት ተገጣጠምን። ምን እዚህ ትሠራለህ? ወያኔ መሆኑን አታውቅም አልኩት። ለጉዳይ እንደሄደ ብቻ ነግሮኝ ተለያየን። እዚያ መሥራት እንደጀመረ በተዘዋዋሪ መንገድ ደረስኩበት። ከዚያ በኋላ እሱም ሸሸኝ፣ አኔም አልፈለግኩትም። የድርጅቱ አስተዳዳሪ፣ወያኔው ባለሟል፣ “አዎንታ” የተባለ፣ ኢትዮጵያውያንን ለመጥለፍ የተዘጋጀ ድርጅት ሊቀ መንበር ነው። የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ብሎ ሐምር-ስሚዝ መሥርቶ እንደ እንዳለ ያሉትን ጠላፊዎች ቀጥሮ፣ አዲስ ስደተኞች ኢትዮጵያውያንን እየመለመሉ፣ በአምስት እያደራጁ፣ ማወየን ነበር ተግባራቸው። እነ እንዳለም፣ ኮባኒያ ፈጥረው ኮንሱልተንት ተብለው ይሠሩለት ነበር። የገንዘብ መሰብሰቢያ ኮባኒያውን ስም ለማየት በአደባባይ ከሚገኘው የመረጃ ምንጭ፣ ከ http://companycheck.co.uk/director/906368336 ማግኘት ይቻላል። በበለጠ ወደ ውስጥ ገብቶ ለማየት፣ መመዝግብ ያስፈልጋል እንጂ፣ ጉዱንና ጉድጓዱን፣ በሚቀጥለው ተቋሚhttps://www.duedil.com/company/03183927/refugee-advice-and-support-centre ወይም በዚህኛው ጠቋሚ https://www.duedil.com/director/906368336/endale-wondafrash ማየት ይቻላ። እንዳለን፣ ወያኔ ሌላ ሥራ ላይ አሠማራችው። ስደተኛውን መልሶ የወያኔ እጅ የማስገባት የኮንሰልታንሲውን ሥር ቶት ፊልም አቀናባሪአቸው ሆነ። Endexeye [i] በሚል የተበላሸ ስም፣ ብዙ ስም አጥፊ ፊልም አቀናብሮ በዩ-ትዩብ በትኗል። ሞገደኛው መነኵሴ ነኝ ባይ፣ ቤቴክርስቲያናችንን ለወያኔ ሊያስረክቡ ሲነሱ፣ እንዳለ ፊልም አንሺአቸው ብቻ ሳይሆን የወያኔ ተቃዋሚ የሆነውን ሁሉ እየተከታተለ፣ ስማችንን ማጥፋት፣ ማሸማቀቅና ማዋረድን ዋናው ተግብሩ አድርጓል። የኔንማ ተውት። ባንኪንግሀም ይኒቨርሲቲ ድረስ፣ ግብረሰዶማውያንን አስተባብሮ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያስወጣብኝ [ii] [iii] የሞከረው ጉድ፣ ነው።
አንዳርጋቸው ከተያዘ ጀምሮ እንዳለ የማይለው የለም። ቫይበር በተባለው የመገናኛ ዘዴ በሚበትነው የዕውነተኛ ሽብር ጽሑፉ፣ ከዚህ በፊት በሳውዲ አረቢያ የተጨፈጨፉትን ወንድሞችና እህቶች ምክንያት ተናደን ሆ ብለን አንድ ላይ ስንወጣ፣ እንደዓይጥ ጓዳው ውስጥ ተውሽቆ “እሰየው! እንኳን ጨፈጨፏቸው! የሳውዲ አረቢያ መንግሥት ያንን ለማድረግ መብት አለው” ባለን አንደበቱ፣ አሁንም የአንዳርጋቸው ጽጌን መወሰድ ነገር በየቀኑ ይጽፋል። እያንዳንዳችን እንደምንወሰድ እየዛተብን ይገኛል።
አሰፋ ምንተስኖት [iv] የተባሉ ጸሕፊ፣ ስለዚህ ጉዳይ በመረጃ በተደገፈ ጽሑፍ፣ ሰለዝህ ጉደኛ ሰው፣ ጽፈዋል። ታዲያ እንዳለ፣ Atse Tewodrose II በሚል የውሸት ስም 12 ጊዜ ተንገብግቦ አስተያየት ኢካዲኤፍ ድረ ገጽ ላይ ዘባርቋል። የሚገርመው ነገር፣ ስለእያንዳንዳችን እንደፈለገ ተንስቶ ሲመርግብን፣ አንድ አሰፋ ምንተስኖት በጻፉት ጽሑፍ፣ ያን ሁሉ እየተንገበገበ መጻፉ ነው። ለዚህ ሰውዬ አንድ መርዶ አለኝ። ወንድሙ መኰንን፣ እንኳን ለእንደዚአህ ያል ፍርፋሪ ለቃሚ የወያኔ ቡችሎች፣ ለአሳዳሪ ጌቶቻችሁም ስሜን ደብቄ እንደማላቅ ነው! ግሩምን መሰልኩ እንዴ አባቴና እናቴ ያወጡልኝ ስም ወደ ግሩማ የምቀይረው? “አይ አለማወቅሽ አገርሽ መራቁ!” አለ ሰውዬው! ጌቶቹንም ብግን የሚያደርጋቸው ይኸው ነው። እነሱ ስማቸውን ይደብቁ እንጂ እኔ ምን ነውር ሠርቼ፣ እኔ ምን ተዳዬ!
አንዲት እህት ስለዚህ ጉደኛ ፍጡር ብግን ብላ ስትናገር “ትንሽ እንጀራ ወጥ ይጨርሳል፣ ትንሽ ሰው ሰው ያሳንሳል” ብላዋለች። እንግዲህ ወያኔ ከመደበችብን በቤተክርስቲያናችን ውስት የፕሮፓጋንዳው ክፍል አራጌ ፈጣሪ ይኸው ሒሊና ቢዝ ሰው ነው።
“ ካኅን ” እንበለው “ አርበኛ ”
ግራ የገባው ነገር እኮ ነው። ሰውዬው አርበኛም አልነበረም ካህንም አይደልም። ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ! መንገሻ መልኬ አርበኛ ነው “ካህን”? በየትኛው ሒሳብ? እንኳን ካህን ሊባልና ለድቁና መብቃቱንም ማረጋገጫ እስካሁን አልተገኘለትም። ስለዚህ ሰው ብዙ ብዙ አሳፋሪ ምግብሮችን እንሰማለን። ወያኔ የሚጠቀምበትን ዕቃ ካገኘ፣ ሥነ-ምግባር ጉዳዩ አይደልም። አንድ ነገር ብቻ ለምሳሌ ልጥቀስላችሁ። ሰውዬው እንደመጣ ሲነግረን የነበረው ጸረ-ወያኔነቱን ነው። ከአንዲት ሰላማዊ ሰልፍ ቀርቶ አያውቅም ነበር። እኔማ ሞኙ፣ የዋህ የተገፋ የአገሬ ልጅ መስሎኝ፣ እንደወንድሜ ስፍስፍ ነበር የምልለት። ወያኔን ማስወገድ የሚቻለው በነፍጥ ብቻ መሆኑን አጥብቆ ተከራካሪ ነበር። አሁን አሁን እንዲዚህ ዙሮ የወያኔ መንከሻ ጥርስ ሊሆንብን! ጠረጠርኩት! ስለአርበኝነት ካነሳን አይቀር፣ መንገሻ መልኬ የአርበኞች ግንባር አባል ነበር። የአርበኞች ስብሰባ ላይ፣ ቀስቃሽ፣ አራጌ ፈጣሪ፣ እልፍኝ፣ አስከልካይ ነበር። ማመን ያዳግታል አይደል? ካሜራና ሞኝ የያዘው አይለቅ! ይኸውና!
ይኸ ነው ካህን? ድንቄም የቅድስት ማርያም “ካኅን!” ትንሽ ዕውቀት አደገኛ እንዲሉ! እንዳለ ወንዳፍራሽ መንገሻን የወያኔ ክኅነት ካባ አጥልቆለት “መጥ” አስብሎታል። ጉድ እኮ ነው! ተሰጥዖ እንኳን መመለስ የማይችል፣ ካህን ተባለ? ይኽቺ ናት የወያኔ ካኅን! “ጉድና ጅራት ከወደኋላ” ነው የሚባለው! ለይምሰል አመንኵሰው በየገዳማቱ የሰገሰጉት ነፍሰ ገዳይ ሁሉ ዛሬ ለቆሞስነትና ጵጵስና በቅቶ የለ? መንገሻ ከመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት በስተቀር ከነዚአይ በምን ያንሰዋል! ቁመቱን እንዲሁ ሰጥቶታል። “ረዥም ባይፈራ አጭር ባይኮራ ነው” የሚባለው? እንዲያው በሞቴ፣ ከላይ ያያችሁትን ፊልምና ከዚህያቀርብኩላችሁን ፎቶግራም ስታዩ አንድ ነገር አልከነከናችሁም? አንዳንድ ሰዎች በየቀኑ እስሥት ይመስል አቋማቸውን ለምን ይሆን የሚለዋውጡት? ሕሊና-በስ በመሆናቸው!
“ መሪ ጌታ ” ካኅን ነው ?
የአንተ ያለህ! “የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ ልኳንዳ ቤት ተገኘ!” ይሉሀል ይኸ ነው። መንገሻስ ስለሀይማኖት የሚያውቀው ነገር ስለሌለ፣ እሺ ይንከሰን፣ መሪ ጌታ ተባዩ ኼኖክ፣ “ሊቀ-ሊቃውንቱ” ምነዋ የመጽሐፍ ቅዱስን ሀ-ሁ ጠፋው??? ወያኔ አዞረበት እንዴ! እኮን ጉድ ነው! መሪ ጌታ ኸኖክና የወያኔ መንከሻ ጥርስ እየተቀባበሉ “መዲኃኔዓለምበአደራ ያስረከበኝንመንጋ በትኜ አልተባበራችሁም” ብለውከኛ ጋር በርብዱ፣ በውርጩ፣ በጽሐዩ፣በዝናቡ የሚንከራተቱትን ካኅን፣ መልአከ ብርሀን ቀሲስ ብርሀኑን ብሥራትን ሥጋቸውንእንደጅብ እየተፈራረቁ ቦጨቁ።መሪ ጌታ ሄኖክ አንድ ቀን በግዕዝ አንድ መዝሙር ተቀኝቶ መጥቶ ሲያሸብሽብ ሳየው፣ የሽብሸባውን ትርጉም እየተነተነ ሲያስረዳ፣ ሞቅ ብሎኝ ሄጄ አመሰግንኩት። የራሴን ቋንቋ በደንብሳልውቅ ባዕድ ቋንቋ (ያውም ሁለት) ስማር ያጠፋኹት ጊዜ ሳስበው ቆጨኝ። ስምንት የግዕዝ መማሪያ መጽሕፍት አስምጥቼ እራሴን ማስተማር የጀመርኩት በመንፈሳዊ ቅናት ተነሳስቼ ነበር። ትልቁ ዳቦ ሊጠ ሆነላችሁ! ለካንስ ሰውዬው ቃላቱን ከመሸምደድ ውጪ የክርስቶስ ትምሕርት በውስጡ አልተዘራም። ጋን መስሎኝ ነበር፣ ለካስ እሱም ምንቸት ኑራል?
እንግዲህ እኔ፣ መሪ ጌታ ኼኖክን መጽሐፍ ቅዱስን ላስተምረው!“ካህን እረኛ አይደለም፣ እረኛው እየሱስ ክርስቶስ ነው” ላለው መልሴ አጭር ነው። ጌታ “እኔ መልካም እረኛ ነኝ” ያለው ለደቀመዛሙርቱ፣ ነበር። ይኽቺን ዓለም ቶቶ ወደ መንበሩ ሲመለስ ግን እረኝነቱን ለካኅናቱ (ለቀሳውስቱ፣ ለኢጲስቆጶሳቱ እና ለጳጳሳቱ) አስረክቦአቸው ነው የአረገው! እናንተ ነዳፊ የእፉኝት ልጆች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ካላችሁ አውጡ። እኔ ትንሹ፣ ልሟገታችሁ፣ እናንተ “የተለሰናችሁ ግድግዶች”ጌታ እየሱስ ክርስቶስ ደቀ-መዝሙሩን ጴጥሮስን በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፩ ከቁጥር ፲፭ እስከ ፲፯ “ግልገሎቼን አሰማራ … ጠቦቶቼን ጠብቅ … በጎቼን አሰማራ” ሲል ካኅናት ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የእረኝነትን ኃላፊነት እንደተቀብሉና እኛ ግልገሎቹ፣ ጠቦቶቹ እና በጎቹ እንደሆን ቁልጭ አድርጎ አስተምሯል። አይ መሪ ጌታ! ሳትበስል ኑሯል “መሪ” የተባልከው?
የአዋቂ አጥፊው ካህን
ሦስተኛው የወያኔ ዘገባ (ዶኩዩሜንታሪ) ቅንብር ተዋናይ፣ ከሁልቱም በትምሕርትና በመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት የላቀ ነው። ቄስ አባተ ይባላል። ልብ በሉ፣ ቄስ ስል በትምሕርተ ትቅስ አላስቀመጥኩም። ለነገሩ ቄስ መሆኑን ያውቅኩት፣ ነገሮችን የወያኔ ጀሌዎች ቡክት ካደረጉት በኋላ ነው። ቢሆንም ዕውቀቱን በተመለከተ ቅስና ይገባዋል። ያገባም፣ የወለደም ነው። እንዴሌሎቹ ሲልከሰከስም አይታይም። ግን የአዋቂ አጥፊ ነው። ምን-ናካው! እነዚያ ሁልቱ፣ ስለእረኛ ሲናገሩ አዘበራርቀው ሲያወሩ፣ እሱ በትክክል ተናግሯል። ዳሩ ግን “እረኛ” የሚለው አባባል ለመላከ ብርሀን ቀሲስ ብርሀኑ ብሥራት ሽንጡን ገትሮ ተከራከረ። ታዲያ ለማን ነው የሚገባው? የቤተክርስቲያኗን በር ምዕምኑ ላይ ጥርቅም ላደረጉት ለመንጋውን በታኝ የቀበሮ ባኅታዊ ግሩምና ለራሱ አስቧት ይሆን? ሲያምረው ይቅርበት። እረኛው የክርስቶስ መንጋ ጠባቂ ነው። “የናንተ ጥቅም ባፍንጫዬ ይውጣ ብለው” የሰበሰቡን አባት ዕውነተኛ የጌታ በጎች ጠባቂ ካልተባሉ፣ በታኞቹማ የበግ ልምድ የለበሱ ተኵላዎች ናችው! አይ አባተ! “አባተ ግድግዳው ምን ሁኖ ሰከረ?” የሚል ቀልድ በልመንህ አይታችኋል? እሱም ምንቸት ሆነ። ጋኖቹ የት ገቡ?
ውይ ረስቼው! ዲያቆን አባተ፣ ቅስናውን ከማን ንበር የተቀበልው? ቀጥሎ ያለውን ደብዳቤ ምስጢሩን ይናገራል።
አባተ ለካንስ ቅስናውን ያገኘው ከአባታችን ከአቡነ ኤሊያስ ኑሯል! አባታችን የወያኔ ሲኖዶስ ሊቀ ጳጳስ ሳይሆኑ የሕጋዊው ስድተኛ ሲኖዶስ ሊቀ ጳጳስ ናቸው እኮ። ወይ ጉድ! ግሩማና አባተ ሕጋዊው ሲኖዶስ አዲስ አበባ ያለው ነው እያሉ ወዶ ገባነታቸው በመጮኽ ሲያረጋግጡ፣ዲያቆን አባተ፣ ቅሰናውን ከየት እንዳገኘው ረስተው ነውን?
ሞገደኛውና ከሀዲው መነኵሴስ ካህን ናቸው ?
እሳቸውም ያው ምንቸት ናቸው! ፖሊቲከኞች አሉን። ቅንጅት አሉን። ደርግ አሉን። ግንቦት ሰባቶች አሉን። እንሱስ ፱ ቦታ የሚረግጡ፣ ምን ሊባሉ? ካኅናት! ድንቄም!። ስደተኛውን ለሶልዲ የሸጡትን የቀበሮ ባሕታዊውን ካህናት ከተብሉ ነገሩ፣ ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ ነው የሚባለው። ሞገደኛው ያደረሱብንን እንግልት፣ ትሪካችንን የተከታተለ ሁሉ ያውቃል። ወሎጆቻቸው የፊት ጉዳቸውን ትተው በትክክል “ግሩም” ብለውአቸው ነበር። ሰውዬው ምኑ ዋዛ! እናት አባታቸው የወጡላቸውን ስም ተግባራቸው ስለሚያጋልጥባቸው አሽቀንጥረው ጣሉት። ትንሽ ዘውር አድርገው “አባ ግርማ” ነኝ አሉን። አልፈው ተርፈውም “ወያኔ ፈለጠኝ፣ ቆረጠኝ፤ አሳደደኝ፣ አሳበደኝ” ብለው በስደተኛነት ተመዝገበው ተቀላቀሉን። ይግርማሉ እንጂ፣ ግርማውንስ አልተላበሱትም። ሰላማዊ ሰልፍ ከኛ ጋር ወጥተው “ወያኔ ይውደም!” ሲሉ ዕውነት የተበደሉ እንጂ የቀበሮ ባኅታዊነታቸው አልታየንም ነበር። ቀስ በቀስ ስደተኛው ክርስቲያን በጃቸው ካስገቡ በኋላ፣ የቤተክርስቲያኗን ቁልፍ ተረከቡ። እወንተኛው ቀንደኛው ስይጣንነታቸዋ መጣባቸዋ! “እድሜ ልክ ካልሾማችሁኝ ብለው ቤተክርስቲያናችንን በቀብድ ያዟት! እምቢ ስንላቸው ለወያኔ አሳልፈው ሸጡን። መዋሸቱን፣ መሸፍጡን፣ ማደናገሩን እና ማወናበዱን የመርካቶም ነፍሰ በላ አይስተካከላቸውም። አራዳ!
የኛው ራስፑቲንና አሽቃባጮቻቸው
ወያኔ ድሮውንም ሌባ ትወዳለች! ከጠባቂ ዘበኛ ጀምሮ እስከ ክብር አስጠባቂዎች ቀጥራ አቁማላቸዋለች። እንደ ራስፑንም አሽቃባጭ ወጣቶች ተኮልኵለዋል። እኛ በውጭ በውርጭ ስንገላታ፣ እነሱ ከውስጥ በሙቀት ይቀልጣሉ። “በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት” ይሉሀል ይኸ ነው! የወያኔ አሽከሮች የአባ ደንገጡሮች ከሆኑ በዙ ወራት አስቆጥረዋል። ወያኔ አዲስ አበባ ላይ በኢቲቪ የወሸከተውን ድራማ፣ ወያኔ ያቆመላቸው እንዳለ ሆዬም እዚህ የራሱን ተመሳሳይ ቅንበር አዘጋጀ። የወያኔን ኢቲቭ ተከትለው፣ “የለንደን ደብረ-ጽዮንን ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን ካኅናት ነን ብለው አይናቸውን በጨው አጥበው የውሸት ጋጋታቸውን በፊልም አቅናብረው አግተውናል። በሕገ-ወጥ መንገድ ቤተክርስትያኗን ያያዙት የወያኔ አጋዦቻቸው ሰተት ብለው ከሥላሴና ከገብርኤል ተጠራርተው መክርቸማቸው ሲገርመን፣ የወያኔን ቴሌቪዥን ዋቢ በማድረግ፣ዘጋቢ ፊልም ሠርተው ሁላችንንም በጅምላው የገንቦት ሰባት አባላት አድርገውን አርፈውታል። የግንቦት ሰባት አባል መሆን እንሱን የሌሊት ቅዥት ሁኖ ያባንናቸው እንደሆን እንጂ፣ ለኛስ ምናችንም አይደለም። እርግጥ የግንቦት ሰባት ስም ሲነሳ እንሱን እሬት-እሬት ሊላቸው ይችላል።ወንድማችን አንዳርጋቸው ጽጌ በሕገ-ውጥ መንገዱ መጠለፉን ለመሸዋወድ ወያኔ ያቀነባበረችውን ተንቀሳቅሽ ፊልም እንደመረጃ ተጠቅመው ስም ማጥፋት የተሳካላቸው መስሎአቸው፣ በዙ-ብዙ ብዙ ነገር ወሽክተዋል። እንዲመሩን የመረጥናቸውን ሰዎች በሙሉ በጅምላው “የግንቦት ሰባት አባላት” ብለዋቸዋል።
አባ ተባዩ፣አንዴ ከዚህ፣ አንዴ ከዚያ ናቸው። በቅንጅት ጊዜ ከቅንጅትም ቅንጅት ነበሩ። አብረው እላይ እታች ብለዋል። ለቶኒ ብሌር ሰላማዊውን ሰልፈኛ፣ ደብዳቤ ካስገቡት መሀል ነበር። አንዳርጋቸው ጽጌ ሽርካቸው ነበር። ዶር ብርሀኑ ጀግናቸው ነበር። ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ለንደንን ስትጎበኝ አባተና እሳቸው፣ ለምነው የመታሰቢያ ፎቶ ተነስተዋል። ከሁለት ዓመት በፊት የወልድባ ገዳም ወያኔ ስትመዘበር፣ አባተና ግሩም አደባባይ ወጥተው ላንቃቸው እስኪነቃ፣ ወያኔን አውግዘዋል[v]። ያንን ሁሉ ያመቻቸላቸው፣ ዛሬ ፖሊቲከኞች፣ ግንቦት ሰባቶች እያሉ የሚያብጠለጥሉት ሕብረትሰብ ነው። ምነው ያኔ ግንቦት ሰባትነታቸው አልታያቸውም? ምነው ያኔ የደርግ መኰንኖች መሆናችን አልታያቸውም? ምነው ያኔ የቅንጀት አባላት መሆናችን አልታያቸውም? ለመሆኑ እንደዚያ ወያኔን ያኔ ሲያወግዙ፣ ካህን ነበሩ ወይስ ፖሊቲከኛ። አሁንስ በትከሻው ላይ ቢሸከማቸው የሚወድ ሕዝብን እንደዚያ ሲያሳዝኑ፣ ከፖሊቲካ ተገልለው ካኅን ሆኑ? በመጀመሪያ ያልተካነ ካህን የለም። ከህነቱን መቀባላቸውንም መረጃ የለንም። አለበለዚያ እንዴት ለንደን መጥተው ቅዳሴን ተማሩ? ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ!
ከኛ ሲለዩ ወዴቱ ሄዱ? ወደ ገዳም? የለም! ትላንት ያወግዙት ወደ ነበረው፣ ወደ ወያኔ ጎራ ነው የነጎዱት። ያ ካህን ያስብላቸዋል? ምናልባት “ልማታዊ ካኅን!” ፖሊቲካውን ትተው እኛን ፖሊቲከኞች ቢሉን ባማረማቸው! ከላይ ፎቶአቸውን የምታዮአቸው ወጣት ሴቶችና ወንዶችአሽቃባጮቻቸው “አባ ወያኔ አይደሉም” ሲሉን ከረሙ።ገድላቸውን ሲዘምሩላቸው ሰንበቱ። እራሳቸውንም “የአባቶች እርስት ጠባቂዎች” ብለው አክሌሲያ ነን አሉ። አባ ተባዩ፣ ሕዝባችን የተዋረደበትን ግንቦት ፳ን ሊያከብሩ ወያኔ እምባሲ ዓይናቸውን በጨው ታጥበው ተገኙ።ልብሱን ለበሱት! መስቀሉን ያዙት። አሁን የሚሠሩት ፖሊቲካ አይስብላቸውም ብሎ የሚከራከረን ካለ፣ እሺ ግን ካኅን አይደሉም ነው የምንለው።የሚከተለው ፎቶግራፍ አፍ አውጥቶ ይናገራል [vi]።
የካኅንነቱን መሥፈርት ካየን፣ በተግባር፣ “አባ ግርማ” እንኳን ካህንነት፣ ሽታውም ሽው አላለባቸውም። እግዚአቤሔር ከእንዲህ ዓይነቱ ራስፑቲን ይሰውራችሁ።
የወያኔያዊ ዘጋቢ ፊልም ዓላማ
ዓላማው ግልጽ ነው። አንዳርጋቸው በሕገ-ወጥ መንገድ በወያኔ ተጠልፏል። እነ እንዳለ ወንዳፍራሽ፣ “እያንዳንድሽ እንደዚህ እየተለቀምሽ ትወሰጂያለሽ” እያሉ ይዝቱብናል። ግንቦት ሰባትን ጌቶቻቸው አውግዘዋልና፣ ግንብቶ ሰባት ስንባል፣ የምንሸማቀቅላቸው መስሎአቸው ነው የሚፈራገጡት።
ከመሀከላችን ሻለቃ ማሞ የተባሉ፣ የቤተክርስቲያኗ ምሰሶ የሆኑ ምዕምን አሉ። ሻለቃ ማሞ ወያኔን ሲያደሙ የነበሩ የጦር ሜዳ መኰንን ናቸው። የወጣላቸው ደራሲም ናቸው። “የወገን ጦር ትዝታህዬ” የሚል መጽሐፍ ያበረክቱልን ጸሕፊ ናቸው። እንግዲህ የወያኔ ልማታዊ ካኅናት፣ በሕግ በኩል ሂደው ማሸነፍ ስለማይችሉ፣ ሕገ ወጥ መንገድ መረጡ። ከሕግ ይልቅ፣ አሉባልታ ሕብረተ-ሰቡ መሀል በመዝራት ሻለቃ ማሞን ከግንቦት ሰባት ጋር በማገናኘት አሻማቀው አስበርግገው ከቤተክርስቲያኗ ግቢ የሚያስጠፏቸው መስሎአቸው ነው ይኸን ሁሉ ርቀት የሄዱት። ከንቱ ልፋት!
አንድ አበበ ወንድማገኝ የሚባል ወንድም ቤተሰቡን ለመጠየቅ ኢትዮጵያ ይኸዳል። ምንም ዓይነትፖሊቲካ ውስጥ ገብቶ የሚያውቅ፣ ሰው አይደለም። ስለዚህ ሰው፣ የሰማሁት ወያኔና የ”አባ” ደንገጡሮች ዘጋቢ ፊልሞቻቸው ሲያሰራጩ ነበር። ሻለቃ ማሞን ለማሸማቀቅ፣ የወያኔ ቴሌቪዥን፣ ፈንጂ እንዲያፈነዳ እንዳሰለጠኑት ተናገረ ብለው አቀረቡ። የኛዎቹ የወያኔ ቡችሎች፣ ያንን ይዘው የራሳቸውን ዘጋቢ ፊልም ሠሩበት። ሻለቃ ማሞ፣እንኳን አበበ ወንድማገኝንሊያሰላጡኑትና ከሱ ጋር ተቀምጠው ቁም-ነገርም አውርተው አያውቁም። የወያኔ ነገር ሁሉ በውሸት ላይ የተገነባ ነው። ለመሆኑ እንዲያው አንድ ጥያቄ ለወያኔዎች ላቅርብ። ግንቦት ሰባት አስታጥቆ፣ አስልጥኖ እናንተን የሚያሸብር መላክ ከቻለ፣ የናንተ መሪዎች ወደተሰባሰቡበት ወደ አራት ኪሎ ነው እንጂ ምን አድረገኝ ብሎ ነው ቦምብ አፈንጂ ኃይል ቦሌ መድኃኔዓለም የሚልከው? ስትዋሹም ትንሽ ትንሽ ማስመሰል የአባት ነው! እዲያ ምኖቹ ዓይን አውጣዎች አጋጠሙንጃል!ጋን አስመሳይ ምንቸት ድሮም እንዲሁ ነው።
እንግዲህ የዘጋቢ ፊልሙ ዓላማ፣ በሕግ ሊነጥቁን ያላቻሉትን፣ ግንቦት 7 ናቸው ሲሉን፣ በርግገን የምንተው መስሎአቸው ነው። ትርኪ-ምርኪ ዝባ-ዝንኪ የገበያ ጌሾ! በነገራችን ላይ በክርክራችን ወሳኝ ቦታ ላይ ደርሰናል። ቻሪቲ ኮሚሺን እነዚህ ቀማኞች ትረስቲም እንዳልሆኑ፣ ለሚጥይቃቸውም ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ፣ እኛ ወደፍርድ ቤት ብንሄድ የሚፈቅድ መሆኑና፤ ኮሚሺኑ የራሱን ምርመራ የሚያካሄድ መሆኑን ውሳኔ ላይ ደርሷል። ደብዳቢውንም የሚከተለው ድረ-ገጽ ላይ ማንባብ ይቻላል። http://londondebretsion.org/wp-content/uploads/2014/09/Charity-commission-response-28Aug14.pdf ይቁርጥ ቀን ደርሷልና በዓለም ዙሪያ የተበተናችሁ ወገኖች ከጎናችን ቁሙ እያልን ጥሪ እናስተላልፋለን።
ድል የእግዚአብሔር ነው!
[i] https://www.youtube.com/watch?v=otlM6x8mzWk
[ii] http://ecadforum.com/Amharic/archives/9750/
[iii] http://www.tigraionline.com/articles/wondemu-mekonen-cadre.html
[iv] http://ecadforum.com/Amharic/archives/12972/
[v] http://www.youtube.com/watch?v=e5dhKLk0Nzc&feature=share
[vi] http://www.ethioembassy.org.uk/news_archive/Ginbot-20_celebrated_in_London.pdf